ቲዊተር ኃያልነትንና ሀብትን ያገኘው ከሶስት ማህበ ረሰቦች ማለትም ከፖለቲከኞች፣ ከታዋቂ ሰዎችና ከጋዜጠኞች ነው ይለናል በዚያ ሰሞን ለንባብ የበቃው የTIME መጽሔት። እነዚህም ተጽዕኖ ፈጣሪ የሕብረተሰብ ክፍሎች ቲዊተርን የመረጡት ሀሳባቸውን ወይም አቋማቸውን በቀጥታ ያለከልካይ ለ238 ሚሊየን መሰሎቻቸው ስለሚያጋሩ ነው። በቀን 500 ሚሊየን ቲዊቶች ዓለምን ያካልላሉ። በተለይ ጋዜጠኞች ተክለ ስዕብናቸውን ለመገንባትና ለዜና የሚሆኑ መነሻ ሀሳቦችን ስለሚያገኙ ቲዊተርን ይመርጡታል። የተቀረው ተጠቃሚ ደግሞ በሌላ መንገድ የማያገኛቸውን ታዋቂ ሰዎችንና ባለስልጣናትን በቀላሉ አግኝቶ ሀሳቡን ለማጋራት ይጠቀምበታል ።
የአሜሪካውን ፕሬዚዳንት ጆ ባይደን፤ የውጭ ጉዳይ ሚኒስትሩን አንቶኒ ብሊንከንን እና ሌሎች ሚኒስትሮችን፤ የሪፐብሊካኖችን ሊቀ መንበር ሮና ማክዳኔልን፤ የዴሞክራቶችን ሊቀ መንበር ጄሚ ሀሪሰን፤ በአጋማሽ ዘመን ምርጫው ዴሞክራቶች ኮንግረሱን ስለተነጠቁ አፈ ጉባኤው የሪፐብሊካኑ ኬቨን ማካርቲ ይሁን አንዲ ቢግስ፤ የቀድሞዋን የዴሞክራቶች አፈ ጉባኤ ናንሲ ፔሎሲን የተካቸውን ሀኪም ጄፍሪስ፤ የኮንግረስና የሴኔት አባላትን፤ ያለምንም ደጅ ጥናት በቀላሉ በቀጥታ የምታገኛቸው በቲዊተር ብቻ ነው።
የአገርን ስም የሚያጠለሹትን እንደ CNN ጋዜጠኛ ኒማ ኤልባገር ያሉ የዋሽንግተን ፖስትና የዘ ኒውዮርክ ታይምስ ጋዜጠኞችን በቀላሉ በቀጥታ ማግኘት የሚቻለው በቲዊተር ነው። የመንግስታቱ ድርጅት ዋና ጸሐፊን አንቶኒዎ ጉተሬዝንና ተቋማቸውን፤ የአውሮፓ ሕብረት ኮሚሽን ፕሬዚዳንት ኡርሱላ ቮን ዴር ሌዬን፤ የሉላዊነት መገለጫ የሆኑትን እነ የዓለም ባንክ፣ ዓለማቀፍ የገንዘብ ተቋምና የዓለም የንግድ ድርጅት መሪዎችንና ተቋሞቻቸውን፤ መርጦ አልቃሽ የሆኑትን እነ አመንስቲ ኢንተርናሽናልንና ሒውማን ራይትስ ዎችን ከእነ አመራሮቻቸው ያለ ቢሮክራሲና ያለብዙ ውጣውረድ በቀላሉ የሚገኙት በቲዊተር ነው።
በጥቂት ሆሄያት በአንድ ጊዜ ፖለቲከኞችን፣ ተጽዕኖ ፈጣሪ የሆኑ ታዋቂ ሰዎችንና ጋዜጠኞችን መድረስ የሚቻለው በቲዊተር ነው። የዓለም ፖለቲካ፣ ኢኮኖሚና ማህበራዊ ጉዳይ የሚመራው በቲዊተር ነው። መደበኛ ሚዲያው ከዚያ ይከተላል ። የአገራት መሪዎችና የዓለማቀፍ ተቋማት ዳናውን ይከተላሉ።
ታዲያ ፖለቲካው፣ ኢኮኖሚውና ሚዲያው እንዲህ በሚዘወርበት የቲዊተር ዓለም ኢትዮጵያውያን የፖለቲካ መሪዎች፣ ተጽዕኖ ፈጣሪ ታዋቂ ሰዎችና ጋዜጠኞች የት አሉ ። በጣት ከሚቆጠሩ ኢትዮጵያዊ ፖለቲከኞች፣ ተጽዕኖ ፈጣሪዎችና ጋዜጠኞች በስተቀር አብዛኛዎቹ የሉም። ያሉትም ቢሆኑ ከተወሰኑት በስተቀር መደበኛ ተሰላፊዎች አይደሉም። በአንጻሩ በፌስ ቡክ፣ በዩቲውብ፣ በቴሌግራም፣ በቲክቶክና በሌሎች ማህበራዊ ሚዲያዎች ከሊቅ እስከ ደቂቅ እኔን ጨምሮ ሲራኮት እንታዘባለን።
ይሄን አስመልክቶ የሚወጡ መረጃዎች መሬት ላይ ያለውን ሀቅ ያረጋግጣሉ። ከ64 ሚሊየን በላይ የተንቀሳቃሽ ስልክ ተጠቃሚ ባለበት አገር፤ ወደ 7 ሚሊየን የሚጠጉ የፌስቡክ፣ 6.5 ሚሊየን የሜሴንጀር፣ 826,500 የሊንክዲን፣ 666,900 የኢንስታግራም ተጠቃሚዎች ሲኖሩ የቲዊተር ተጠቃሚዎች ግን ከ35ሺህ አይበልጡም። እነዚህም ገባ ወጣ የሚሉ ናቸው። ንቁ ተሳታፊዎች ደግሞ ከዚህ በእጅጉ ያነሱ እንደሚሆኑ አያጠያይቅም።
የሊንክዲን ተጠቃሚዎች ፊደል የቆጠሩ ቢያንስ የመጀመሪያ ዲግሪና ከዚያ በላይ ያላቸው ናቸው ተብሎ ይገመታል። እነዚህ እንኳ የቲዊተር አካውንት ቢከፍቱ ባለ ቲዊተር አካውንቶችን ቁጥር ከ20 እጥፍ በላይ ያሳድገዋል። 120 ሚሊየን ሕዝብ ይዘን፣ እውነትንና ፍትሕን ታቅፈን የአናሳዎች ሀሰተኛ መረጃና ገጽታ ማጠልሸት ሲረታን እንዴት አይቆጨን አያንገበግበንም። በቲዊተር የግጥሚያ ሜዳ ጠላቶቻችን ቀድመው ትጥቃቸውን አሳምረው ቢገኙም እኛ በሰዓቱ ባለመገኘታችን “ዳኛው”በፎርፌ መረታታችንን አርድተውናል።
ሰው ለአገሩ ለአንድያ ህይወቱ ሳይሰስት መስዋዕት እየሆነ እንዴት የቲዊተር አካውንት ከፍተን ለአገር ዘብ መቆም ይሳነናል። የቱንም ያህል ልዩነት ቢኖረን ለአገራችን እውነት መቆም እንዴት ያቅተናል። እነ ማርቲን ፕላውት፣ አሌክስ ድዋልና ጭፍራዎቻቸው የተነሱት፤ ሌት ተቀን ሀሰተኛ መረጃ የሚያንበለብሉት ኢትዮጵያና እና ኢትዮጵያዊነት ቀና እንዳይሉ የመቅበር የምዕራባውያን ታላቅ ሴራ አካል ስለሆኑ እንጂ የዐቢይን አስተዳደር በማዳከም የሚቆሙ ከመሠለን ተሳስተናል። የታሪካዊ ጠላታችን ግብጽ በአገራችን በህቡዕ ያወጀችው የግራጫ ጦርነት አካል መሆኑንም ለአፍታ ልንዘነጋ አይገባም።
የገዥው ፓርቲም ሆነ የተፎካካሪ ፓርቲዎች አባላትና ደጋፊዎች፤ በስፖርቱም ሆነ በኪነ ጥበቡ አንቱታን ያተረፉ ኢትዮጵያውያን፤ የመንግስትና የግል ሚዲያ ጋዜጠኞች፤ ከ100 በላይ በሆኑ የመንግስትና የግል ዩኒቨርሲቲዎች የሚያስተምሩና የሚመራመሩ በብዙ ሺህዎች የሚቆጠሩ ምሁራን፤ በዓለማቀፍ ተቋማት የሚሰሩ የበቁና የነቁ ኢትዮጵያውያን፤ በአገር በቀል ሲቪል ማህበረሰብ ድርጅቶች የሚሰሩ ወገኖቻችን፤ በየሙያ ማህበራቱ ያሉ ዜጎቻችን፤ ወዘተረፈ የት ሄደው ነው እውነትንና ፍትሕን ይዘን በቲዊተር በተደጋጋሚ ፎርፌ እየሰጠን የምንረታው።
በብዙ ነገሮች ላንደሰት፣ በገዢው ፓርቲ ልንከፋ ወይም የፖለቲካ ልዩነት ሊኖረን ይችላል። በአገራችን ግን ልዩነት የለንም። በሀሰተኛ መረጃ ሊያፈርሷት ፣ ገጽታዋን ሲያጠለሿት እያየን እንዳላየን፣ እየሰማን እንዳልሰማን መሆን እንዴት አስቻለን። ደማቸውን አፍስሰው፣ አጥንታቸውን ከስክሰው ያቆዩንን አገር፤ ዛሬም እህት ወንድሞቻችን በየጋራ ሸንተረሩ እየተዋደቁላት፤ እንደ ዜጋ ዝቅተኛውን ኃላፊነት መወጣት እንዴት ይሳነናል።
በሞቀ ቤታችን ወይም ቢሯችን ተቀምጠን ስለ አገራችን እውነትና ፍትሕ በቲዊተር እማኝ መሆን እንዴት ይሳነናል። እውነትንና ፍትሕን ታቅፈን እስከ መቼ አስተባባይና ተከላካይ እንሆናለን። አጠቃቀሙን ለመማር ቀላል፣ ብዙ ሰዓት የማይወስድ፣ ኤልሳቤታዊ እንግሊዘኛ የማይጠይቅ፣ ካልሆነም like እና share ለማድረግ እንዴት እንሰንፋለን። በተለይ ተጽዕኖ ፈጣሪ ታዋቂ ሰዎች እና ባለስልጣናት ባለሙያ ቀጥረው ሀሳባቸውንና አቋማቸውን በንቃት ማጋራት እየቻሉ ለምን በኢቴቪና በፋና እስኪጠየቁ ይጠብቃሉ።
አገራችን ገና ከፊቷ ብዙ ፈተና ይጠብቃታልና ያለ ልዩነት ሰራዊት ልንሆናት ይገባል። በፖለቲካችን፣ በኢኮኖሚያችንና በማህበራዊ ጉዳያችን ብዙኅን ሆነን ሳለ ዝምታን በመምረጣችንና ባለመሳተፋችን አናሳዎች መልካውን ተቆጣጥረው የእነሱ ድምጽ ብቻ ነው ጮሆ እየተሰማ ያለው። ዝምታችንንና ዳር ቆሞ ተመልካችነትንና ኬረዳሽነታችን ሰብረን ከዛሬ ጀምሮ ወደፊት በመምጣት አገርም ሆነ ትውልድ መታደግ ካልቻልን ነገ እንዳንቆጭ በብርቱ እሰጋለሁ። ትውልድ እንዳይወቅሰን እፈራለሁ።
እንደ ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ ካቢኔያቸው በቲዊተር ንቁ ተሳታፊ ቢሆን፤ በተዋረድ ያሉ አመራሮች ይሄን ቢከተሉ፤ የክልሎች ርዕሳነ መስተዳደሮችና የየቢሮ ኃላፊዎቻቸው ይሄን አርዓያ ቢከተሉ፤ የየዩኒቨርሲቲዎች ፕሬዚዳንቶች ግንባር ቀደም ተሳታፊ ቢሆኑ መምህራን ቢከተሉ፤ ከታዋቂና ተጽዕኖ ፈጣሪ ሰዎች ጀግናው አትሌት ሻለቃ ኃይሌ እነ ቀነኒሳን አስከትሎ ቲዊተር ላይ ምሳሌ ቢሆን፤ አርቲስት ቴዎድሮስ ካሳሁንና ሌሎች አርቲስቶች ከእነ አድናቂዎቻቸው፤ ገጣሚው፣ ተዋናዩ፣ ጸሐፊ ተውኔቱና አዘጋጁ ጌትነት እንየውና ደቀ መዛሙርቱ፣ አድናቂዎች፣ አርቲስት ሙሉ ዓለምና ተከታይና አድናቂዎቿ፣ ወዘተረፈ በቲዊተር ከአገራቸውና ከሕዝባቸው ጎን ቢቆሙ ሚሊዮኖችን ዳር እስከ ዳር ማነቃነቅ ይቻላል።
በነገራችን ላይ የማህበራዊ ሚዲያን መስፋፋት ተከትሎ ተጽዕኖ ፈጣሪና ታዋቂ ሰዎች ስለ አገርና ስለ ሕዝብ እውነት ድምጽ መሆን በመላው ዓለም እየጎለበተ ያለ ሒደት ነው። መተኪያና ልዋጭ ስለሌላትና ስለ ታላቁ የኢትዮጵያ ሕዝብ ዳር ቆሞ መመልከት ሊበቃ ይገባል። ዝምታን የመረጠው ብዙኅን the silent majority ውድ አገሩን በጯሂ ጥቂቶች the crying minority ዕብሪትና ማንአህሎኝነት አገሩ ስትታመስ እጁን አጣጥፎ በመቀመጥ በታሪክም በትውልድም ተጠያቂ ላለመሆን የዜግነት ኃላፊነቱን ሊወጣ ይገባል።
አገራችን ሰላም ልትሆን ነው፤ የተሻለ ቀን ሊመጣነው ብለን ተስፋ ባደረግንበት፤ ብዙኅኖች ዝምታን ስለመረጡ ጥቂት ጽንፈኛ ብሔርተኞች ሰሞኑን ከየጎሬያቸው እየወጡ ሕዝባችንንና አገራችን እረፍት እየነሱት ነው። ብሔርና ሀይማኖት ለይተው አንዱን በሌላው ላይ እየቀሰቀሱ ነው። እንደለመዱት እሳቱ ላይ ቤንዚን እያርከፈከፉ ነው። አበው ሳይቃጠል በቅጠል እንዳሉት መንግስት አደብ ሊያስገዛቸውና ሊያስጠነቅቃቸው ይገባል።
ወደ ተነሳሁበት ነጥብ ስመለስ፤ ባለፉት አራት ዓመታትም ሆነ ዛሬም በተከታታይ ማንነትን ኢላማ አድርገው የተፈጸሙ ጥቃቶች፤ በማንነት ላይ የተዋቀረው አስተዳደር፤ በሀሰተኛ መረጃ የተለወሰው የሴራና የደባ ፖለቲካ፤ መንግስት ጥቃቶችን ሙሉ በሙሉ ቀድሞ መከላከል፣ ተከስተው ሲገኙም ቶሎ ደርሶ ማስቆም አለመቻሉና ሌሎች ደራሽ ምክንያቶች ተደማምረው ልሒቃኑን ሆደ ባሻና አኩራፊ እንዳደረጉት አይካድም።
ሆኖም በእናትና በአገር ስለማይጨከን ቁጥሩ ቀላል ያልሆነ ልሒቅ ኩርፊያም አገር ስትኖር ነውና በሚል በዚህ ክፉ ቀን ከጎኗ በመቆም አለኝታነቱን ያረጋገጠ ሲሆን አብዛኛው ግን ዛሬም በአንድነት መቆም ተስኖታል። ዛሬም ፖለቲካዊ ነጥብ ለማስቆጠር የሚተጋ፤ ቀን እንደጎደለባት አይቶ ይሄን ጊዜ ነው እጇን መጠምዘዝ ብሎ የተነሳ እና አገራዊ ጥሪ ሲቀርብለት እግሩን እየጎተተ ያለው ልሒቅ ብዙ ቢሆንም፤ በአንጻሩ ደግሞ በዲያስፖራም ሆነ በአገር ቤት በዚህ ክፉ ቀን ከአገራቸው ጎን በቆሙና ባልተለዩ ልሒቃን ወገኖች ቲዊተር ላይ ግብግቡ የቀጠለ ቢሆንም በአባዮችና መልቲዎች ብልጫ ተወስዶብናል። በእውነቱ ይህ ያለልዩነት ሊያስቆጨንና በእልህ ሊያነሳሳን ይገባል። ስለቲዊተር ከተነሳ ላይ ዕድልም አደጋም ይዞ ስለመጣው በይነ መረብ ትንሽ ከማለቴ በፊት ስለቲዊተር አጠቃቀም አንዳንድ ነጥቦችን ላነሳሳ ።
ሰዎች በተፈጥሯቸው ሰው ያምናሉ። ስለሆነም የቲዊተር አካውንታችሁን ፕሮፋይል እውነተኛ እንድታደርጉ፤ ማንም ሳይቀድማችሁ ዜናውን ማብሰር፤ በተከታታይ ቲዊት ማድረግ ተመራጭ ቢሆንም በእያንዳንዱ ቲዊት ቢያንስ የግማሽ ሰዓት እንዲኖር፤ ጥያቄ በመጠየቅ ተከታዮቻችሁ ንቁ ተሳታፊ እንዲሆኑ ማድረግ፤ በመደበኛ ህይወትም ሆነ በቲዊተር በተቀረው ማህበራዊ ሚዲያም የመገናኛ ድልድይና አገናኝ ሆኖ መገኘት፤ የቋሚ ተከታዮችን ቲዊት እንደገና ቲዊት በማድረግና በማመስገን ማበረታታት ያስፈልጋል።
ቲዊት የሚያደርገውን መልዕክት በጥንቃቄ መቅረጽ፤ ቲዊት ሲጋራ ወይም ሪቲዊት ሲደረግ የራስ አስተያየት ቢታከልበት ወይም ሪቲዊት ከሚደረገው ሀሳብ ጥቅስ ተመርጦ ከራስጌ ቢሆን፤ ቲዊት ሲደረግ ከ140 ፊደሎች ባይበልጥ ቲዊቱን የሚያጋሩ ሰዎች ሀሳባቸውን ለማከል ዕድል እንዲያገኙ፤ ቲዊትን እንዲያጋሩ ወይም ሪቲዊት እንዲያደርጉ መጠየቅ፤ ምንጭን ማሳወቅ፤ ተከታዮች በተለያዩ አገራት ስለሚገኙ እዚህ ቀን ቢሆን እዚያ ሌሊት ሊሆን ስለሚችልና ቲዊቱ በፍጥነት ሊያልፋቸው ስለሚችል ደግሞ ቲዊት ማድረግ እና ግንኙነትን ማስፋት ሌሎችን መከተል ይመከራል። ስለቲዊተር አንዳንድ ነጥቦችን ካነሳሁ አይቀር እገረ መንገዴን በይነ መረብ ወይም ኢንተርኔት የሚዲያውን መልክዓ እንዴት እንደተጫነውና እንደደረማመሰው ላነሳሳ።
በይነ መረብ የክፍለ ዘመኑን ጋዜጠኝነትም ሆነ የመረጃ ዝውውርን በሁለት መንገድ ተፅዕኖውን አሳርፎበታል። የመጀመሪያው የዜና አጠነቃቀር ባህል እንደገና ከመበየን አልፎ ሒደቱን አመሰቃቅሎታል። በአናቱ የዜጋ ጋዜጠኝነትን citizen journalism ጨምሯል። የእጅ ስልክ፣ ላፕ ቶፕና የዴስክ ቶፕ ባለቤት ሁሉ “ጋዜጠኛ ” ሆነ ማለት ነው። ሁለተኛው የበይነመረብ፣ የተግባቦትና የመረጃ ማዕዶች platforms ማለትም ፌስቡክ፣ ዩቲውብ፣ ቲዊተር፣ ቴሌግራምና ሌሎች ማህበራዊ ሚዲያዎች መረጃን ዴሞክራሲያዊና ተደራሽ በማድረግ የመረጃ የኃይል ሚዛን ከመንግሥትና ከግል የሚዲያ ኩባንያዎች ወደ ሲቪል ማህበራት፣ ጦማሪያን፣ የዜጋ ጋዜጠኞችና ሕዝብ እንዲያዘነብል አድርጎታል።
በይነ መረብ መረጃም ሆነ ሀሳብ የሚዘዋወሩበትን አግባብ ፍጹም ቀይሯል። በቅድመ በይነ መረብ ዘመን መረጃ የሚዘዋወረው የሚተላለፈው በጋዜጣ፣ በመጽሔት፣ በሬዲዮ፣ በቴሌቪዥን፣ በፖስታ፣ በመልዕክተኛ፣ በስብሰባ፣ በማህበራዊ አጋጣሚዎች (በቡና፣ በማህበር፣ በእቁብ፣ በዳጉ፣ ወዘተረፈ)ነበር። በድህረ በይነ መረብ ግን መረጃም ሆነ ሀሳብ በፌስ ቡክ፣ በዩቲውብ፣ በቲዊተር፣ በቴሌግራም፣ በኢሜይል፣ ወዘተረፈ በስፋት መዘዋወርና መሰራጨት ጀመረ። በዚህም የመረጃ ተጠቃሚው በይዘትም ሆነ በተደራሽነት የተሻለና ቀላል አማራጭ እንዲኖረው አስችሏል።
ዛሬ ዜናም ሆነ ሌላ መረጃ ለማግኘት የአዲስ ዘመንን እትም፤ የኢትዮጵያ ሬዲዮና ቴሌቪዥንን ዜና እወጃና ዝግጅት፤ የኢትዮጵያ ፖስታ አገልግሎትን መልዕክትና ቴሌግራም አይጠብቅም። በእጅ ስልኩ ሁሉንም ማግኘት ይችላል። ከማህበራዊ ሚዲያዎች ዜናውንም መረጃውንም በቀላሉ መቀራረም ይችላል። ሀሳቡን ለመግለጽም ወደ መደበኛ ሚዲያው መሔድ ሳይጠበቅበት ባለበት ቦታ ባሻው ጊዜ በእጅ ስልኩ አማካኝነት ያጋራል። በይነ መረብ መረጃን ተደራሽና ዴሞክራሲያዊ አድርጓል አየተባለ የሚወደሰውም ለዚህ ነው።
ሆኖም ይህ ተአምረኛ ለውጥ የጥቅሙን ያህል ይዞት የመጣው ጣጣም የትየለሌ ነው። በቅደመ በይነ መረብ ዘመን በመደበኛ ሚዲያው መረጃዎች ከመሰራጨታቸው በፊት በዘጋቢውና በአርታኢው ተጣርተውና ታርመው ያልፉበት የነበረው አሰራር በማህበራዊ ሚዲያው በመቅረቱ ሆን ተብሎ ለሚዛባ መረጃ disinformation፣ ለተሳሳተ መረጃ misinformation እና ለሀሰተኛ ወሬ fake news በር በመክፈቱ የመረጃ መልክዓውን አባጣ ጎርባጣ አድርጎታል።
ለሴራ ኀልዮት conspiracy theory፣ ለውዥንብር የተመቸ በመሆኑ የዴሞክራሲያዊ ሥርዓት ተቋማትን ክፉኛ እንዲጎዱ፤ የዜጎች ግንኙነት እንዲሻክር፤ ዘረኝነትና ጎሰኝነት እንደ ሰደድ እሳት በቀላሉ እንዲዛመት፤ ጥላቻ ልዩነትና ግጭት እንደ እንጉዳይ እንዲስፋፋ፤ ሕፃናትና ወጣቶች ለወሲብ ፊልም እንዲጋለጡ ከማድረጉ ባሻገር ለወሲባዊ ጥቃት በር ከፍቷል። የማህበራዊ ሚዲያ ሱስ ዜጎችን ለጭንቀትና ለድብርት፤ ቤተሰባዊ ግንኙነትን ለዝንፈት፤ ወዘተረፈ በመዳረግ አገራትን ለተለያዩ ህልቁ መሳፍርት ቀውሶች እየዳረገ እያወዛገበ ይገኛል።
ራሱን ” የጋዜጠኝነት ድምጽ “ብሎ እንደሚጠራው እንደ ኮሎምቢያ ጆርናሊዝም ሪቪው CJR መፅሔት የቅርብ ጊዜ ጥናት ከሆነ ከአሜሪካውያን 60 በመቶው ዜና የሚያገኙት ከፌስቡክ ወይም ከቲዊተር ነው። ከ200 ዓመታት በላይ የዳበረ፣ የጎለበተ፣ የደረጀ ዴሞክራሲና ልምድ ያለው መደበኛ ሚዲያ ባለበት አገር ከ10 ሰው ስድስቱ ዜና የሚያገኙት ከማህበራዊ ሚዲያ ከሆነ፤ የዳበረ ነፃና ገለልተኛ የሆነ መደበኛ ሚዲያ በሌላት አገራችንማ ቁጥሩ ወደ 80፣ 90 በመቶ ከፍ ሳይል ይቀራል። ለዚህ ነው ማህበራዊ ሚዲያው ከመደበኛው ባልተናነሰ በሰው ኃይልና በቴክኖሎጂ ሊጠናከር የሚገባው። ሚዲያዎቻችን ዘመኑን የሚዋጁ መሆን አለባቸው የሚባለው።
ፈጣሪ የአገራችንንና የሕዝባችንን መከራ በቃ ይበለን!!! አሜን።
በቁምላቸው አበበ ይማም (ሞሼ ዳያን)fenote1971@gmail.com
አዲስ ዘመን ታህሳስ 6/2015