«አሰብ፤ቀይ ባሕርና ወደባችን በዚያን ጊዜ» በሚል ርእስ በደራሲ ዮሐንስ ተፈራ የተዘጋጀ አዲስ መጽሐፍ መጋቢት 28 ቀን 2011 ዓ ም በኢቫንጀሊካል ድኅረ ምረቃ ኮሌጅ የስብሰባ አዳራሸ ጥሪ የተደረገላቸው እንግዶች፤የሥነ ጽሑፍ ባለሙያዎችና የታሪክ ምሁራን በተገ ኙበት መመረቁ ይታወሳል፡፡ መጽሐፉ 26 ምዕራፎችና 375 ገጾች ያሉት ሲሆን ዋጋው 150 ብር፤ በዶላር ደግሞ 20 ነው፡፡
የመጽሐፉ አጠቃላይ ጭብጥ አሰብ ወደዛሬይቱ ኤርትራ ከመጠቃለሉ በፊት የኢት ዮጵያ በነበረበት ጊዜ የኢትዮጵያ መንግሥትና ሕዝብ ለወደቡና ለከተማው እድገት ስላደረጉት አስተዋጽኦና አዘጋጁ በወቅቱ የአሰብ ማኅበራዊና ኢኮኖሚያዊ ግንባታ ውስጥ ስለነበረው ተሳትፎና የወጣትነት ዘመኑን ከሚወድደውና ከሚያከብረው የአፋርና የኤርትራ ማኅበረሰብ ጋር እንዴት እንደኖረ፤ የወደቡ ሥራ አስኪያጆች ጥረት እንዴት እንደነበር ማለፊያ በሆነ አተራረክ ያስቃኘናል፡፡
በተጨማሪም የወደቡና የነዳጅ ማጣሪያው ፤ሌሎችም የኢኮኖሚ ተቋማት እየተስፋፉ እንዴት አድርገው የመኻል አገሩን ሕዝብ ትኩረት እየሳቡ እንደሔዱ ያወሳናል፡፡ አሰብ ወደብ ሠራተኞች ከሥራ ኃላፊዎች ጋር የነበራቸው ፍቅርና የጠበቀ ግንኙነት እንደማይረሳው ይተርክልናል፡፡
አቶ ዮሐንስ ከአፋር ሕዝብ ጋር በፈጠረው መልካም ግንኙነት የተነሣ የአፋር ባላባቶችና ሽማግሌዎች ከዓፄ ምኒልክ ፤ በንግሥት ዘውዲቱ፤ ከልጅ ኢያሱና በቀዳማዊ ኃይለ ሥላሴ የነበረውን ሥርዓት ከዘመነ ደርግ ጋር እያነጻጸሩ የነገሩት ታሪክ ለመጽሐፉ በግብዓትነት እንደጠቀመው ይገልጽልናል፡፡ ከ27 ዓመት የስደት ዘመኑ በኋላ በአሰብ ከተማ አብረውት ስለነበሩትና በሕይወት ስላሉት ጓደኞቹ፤ ከዐፀደ ሥጋ ስለተለዩትም ወገኖቹ ያለው ትዝታ ከፍተኛ ነው፡፡
አቶ ዮሐንስ የአሰብ ወደብ ሠራተኛ ከነበረበት ከመስከረም ወር 1969 ዓ.ም ጀምሮ በሻዕቢያና በሕወሐት ጦር እስከተፈናቀለበት ግንቦት 1983 ድረስ በዐይኑ ስለአየው፤ በጀሮ ውም ስለሰማውና ልዩ ልዩ የታሪክ መጻሕፍትንና ሰነዶችን አንብቦ ከተረዳው ጭብጥ በመነሣት አሰብ እንደአስፈላጊ ከተማና ወደብ ከመታወቋ በፊት ጥቂት የኢትዮጵያውያን የአንካላ ጎሳ አፋሮች የሚኖሩባት የበረሀ መንደር እንደነበረች፤ ከ1889 ወዲህ ደግሞ ሀሰን ኢብራሂም የተባለ ያካባቢው ገዥ ከኢጣሊያው ቄስ ጁሴፔ ሳፔቶ ጋር ባደረገው ስምምነት ሩባቲኖ ለተባለ የኢጣሊያ መርከብ ኩባንያ በ8100 ማሪያ ትሬዛ ገንዘብ አሰብን እንዴት እንደሸጣት፤ ከዚህ ጊዜ ጀምሮ አሰብ ለባብኤል መንደብና ለዐረቢያ ካላት ወሰንተኛነት
የተነሣ ጠቃሚ ወደብ እየሆነች ስለመምጣቷ ያስረዳ ናል፡፡ በደርግ ዘመን የሕወሐት ዕቃ ከውጭ መጥቶ በምሥጢር በአሰብ ወደብ እየተራገፈ ይሰራጭ እንደነበርም መጽሀፉ ጥቁምታ ይሰ ጣል፡፡
ዶክተር ያዕቆብ ወልደ ማርያምም ቀደም ሲል አሰብ የማነች»? በሚል ጽሑፍ ያስነበቡን ሲሆን ደራሲው ግን ሌሎች ምን ጮችን በዋቢነት ሲጠቅስ ከጉዳዩ ጋር ቀጥታ ግንኙነት ያለውን ይህን መጽሐፍ በምንጭነት ለምን እንዳልተ ጠቀመበት ግልጽ አይደ ለም፡፡ መሬቱን ገለባ ያድርግላቸውና የቀድሞው ጠቅላይ ሚኒስትር አቶ መለስ ዜናዊ የአሰብ ወደብ ለኢትዮጵያ እንደማይጠቅም በማውሳት «ግመሎቻቸውን (የኤርትራ ሰዎች ለማለት ነው) ውሃ ያጠጡበት አንፈልገውም» ብለው ፌዘኛ ንግግር በተናገሩ ጊዜ በርካታ ብዕረኞች አሰብን አስመልክቶ ጠንካራ የተቃውሞ ጽሑፎችን በየጋዜጣውና በየመጽሔቱ ያወጡ ነበር፡፡ ምክንያቱም የአሰብ ወደብ ከግመል መጠጫነት በላይ በዓለም አቀፍ ወደብነቱ ለኢትዮጵያና ለመላው ዓለም የኢኮኖሚ ስላለው ነው፡፡ የዚህ ጽሑፍ አቅራቢም «ትንቅንቅ» በተሰኘ የሥነ ግጥም መድበሉ (1993 ገጽ 265) አሰብ በኢትዮጵያ መንግሥት የፖለቲካ ውሳኔና ፊርማ በሔደች ጊዜ ቅሬታውን
«አይኖርም ነበረ አስችሎት አሉላ፤
ያሳደጋት አሰብ ከእጁ ተነጥላ፡፡
በጉልበት ተነጥቃ ያሳደጋት ልጁ፤
አይኖርም ነበረ አሉላ በደጁ፡፡
ከደጋማው ሀገር ማኽዳና ጉሎ፤የወደብ ግርግር ባለበት ቃተሎ፤
አይፈርምም ነበር አሰብ ትሒድ ብሎ» መግለጹ ይታወሳል፡፡
በዘመኑም ስለአሰብም ሆነ ስለኤርትራ መጻፍ፤ መናገር ትምክህተኛ፤ የለየለት ጦረኛ፤ ነፍጠኛ ጽልመተኛ፤ ያለፈውን ሥርዓት ናፋቂ፤ ደርግ -ኢሠፓ በሚል በኢህአዴግ ካድሬዎች የስድብ ውርጅብኝ ይወርድበት ነበር፡፡ አቶ ዮሐንስ ግን ስለአሰብ የጻፈው የኢትዮጵያና የኤርትራ ሕዝብ ተለያይቶ መቅረትን አይፈልግምና በአቶ ኢሳይያስ አፈወርቂና በዶክተር ዐቢይ አህመድ መልካም ፈቃድ ፍቅር ተርፎ በፈሰሰበት ሰዓት ላይ በመሆኑ ይመሰገንበታል እንጂ አይወቀስበትም፡፡ አቶ ዮሐንስ በትጋቱ በአዘጋጀው መጽሐፍ የሚያሳየን ስለ አፋር ሕዝብ ማኅበራዊና ኢኮኖሚያዊ ሕይወቱ፤ ስለ ተከበረው የባህል ዕሴቱ ስለ ኢትዮጵያዊነቱና ደግነቱ፤ ስለቋንቋው ፤ስለጋብቻው፤ ስለ ግመሉ፤ ስለመረጃ ልውውጡ፤— በአሰብ ከተማ በኢትዮጵያ መንግሥት ተሠርተው ስለነበሩት ዘመናውያን የወደብ፣ ሕንጻዎች፣ ሆስፒታሎች፣ ትምህርት ቤቶች ፣መኖሪያቤቶች አፓርትማዎች፣በአማንያን ሀብትና
ንብረት ስለተገነቡት አብያተ ክርስቲያናት፤ ቤተ መስጊዶች፣ስለ ልዩ ልዩ የመንግሥት መሥሪያ ቤቶች፣በከተማዋ ውስጥ ይኖሩ ስለነበሩትና በቁጥር 40 ሺህ ያህል ዜጎች፤ በከተማዋ ውስጥ ይኖሩ ስለነበሩ ታላላቅ ሰዎችና የመንግሥት የሥራ ኃላፊዎች፣ ስለነዋሪዎቹ፣ ስለግዙፉ ነዳጅ ማጣሪያ፤ ትዝታ እንጂ ወደቡ የኢትዮጵያ ነውና ይገባናል የሚል አይደለም፡፡
በመሠረቱማ የዛሬን አያድርገውና እንደነ ዓጼ ዐምደ ጽዮን፤ዓጼ ዘርአ ያዕቆብ፤ እንደነ ዓጼ ወናግ ሰገድ፤እንደነ ዓፄ ሠርፀ ድንግል ፤እንደነ ዓጼ አድያም ሰገድ ኢያሱ ፤ እንደነ ዓጼ ቴዎድሮስ ዓጼ ዮሐንስ እና የመሳሰሉ ነገሥታት ከቀይ ባሕር ጠረፍ እስከ ጠረፍ እየዘመቱና ከውጭ ወራሪዎች ማለት ከቱርክና ከመሐዲስቶች፤ ከግብጾች ጋር እየተዋጉ የሀገ ሪቱን አንድነትና የባሕር በር አስጠብቀውና እንደነ አዶሊስ፤ ዘይላ፤ ምጽዋ፤ አሰብ፤ ጂቡቲ፤ በርበራና ኪስማዩ፤ ቦሳሶ፣ ሞቃዲሾ የመሳሰሉ ወደቦቻቸውን አስከብረው ለትውልዱ ቢያስተላልፉም እንደ እንግሊዝ፤ ፈረንሳይና ኢጣሊያ የመሳሰሉ ተኩላዎች በኢትዮጵያውያን ላይ በፈጠሩት የልዩነት መንፈስ ያሁኑ የተፈጥሮ ወደቦቻችንን እንድናጣና ኢትዮጵያን ጨምሮ በኢኮኖሚ የደከሙ ትናንሽ መንግሥታት እንዲፈ ጠሩ ተጽእኖ ፈጥረውብናል፡፡
እናም ቀደም ሲል በመንግሥትነት የማይ ታወቁትና የኢትዮጵያ አካል የነበሩት ሶማሊያ፤ ጂቡቲና ኤርትራ በባእዳን ግፊት፤ አጠገባቸው በሚገኝ በውሃ ሀብት ተማምነውና በወደቦቹ በበለጠ መጠቀም ያለብን እኛ ነን ብለው ከኢትዮጵያውያን እኅት ወንድሞቻቸው በመለየት የራሳቸውን መንገድ መርጠዋል፡፡ ግን ኢትዮጵያ በመንግሥት አወቃቀሯና በኢኮኖሚ አደረጃጀቷ ልዕለ ኃያል ብትሆን ኖሮ እንኳን የገዛ ልጆቿ ኤርትራ፤ ጂቡቲና ሶማሊያ ይቅሩና ጎረቤቶቿ ሱዳን፤ኬንያና ዑጋንዳ አብረንሽ ተዋሕደንሽ እንኑር፤ አብረን እንብላ፤ አብረን እንደግ ይሏት ነበር፡፡
እናም ሰው ከኖረበት፤ ካደገበት፤ እትብቱ ከተቀበረበትና ከሚወድደው ሀገር በድንገት ውጣ ተብሎ ሲፈናቀል የሚሰማው ስሜት ዘለዓለማዊ እንጂ በቶሎ ሊረሳ የሚችል ወቅታዊ ጉዳይ አይሆንም፡፡ ዛሬም ቢሆን በመኻል ኢትዮጵያ የሚገኙ የአንዳንድ ክልል ፖለቲከኞችና አክቲቪ ስት ተብየዎች የእኛ ክልል በነዳጅ፤ በወርቅ በአልማዝና በተፈጥሮ ሀብት ክምችት የበለጸገ ነውና ከኢትዮጵያ እንገነ ጠላለን ፤ ለዚህም በሕገ መንግሥቱ አንቀጽ 39 የተቀመጠው ይደግፈናል እያሉ የሚያሟርቱትና ሕዝቡን የሚያሰቃዩት ለዚህ ነው፡፡ ትርፉ ግን ከዚህ በፊት በኤርትራ እንደታየው ሞት፤ ስደት መከራ ፤ እልቂት ነው፡፡
ድምጻዊው የክብር ዶክተር ጥላሁን ገሠሠ
«ዑዑታ አያስከፋም ሲለዩ ተዋድዶ፤
ከዚህ የበለጠ ከየት ይምጣ መርዶ»
ብሎ እንዳቀነቀነው በብዙ ጥረት ይህንን መጽሐፍ ያዘጋጀልን አቶ ዮሐንስ ከአሰብ ተፈናቅሎና በየመን በኩል ወደሰው አገር ተሰድዶ ለ27 ዓመታት ያህል ቢኖርም የልጅነት ጊዜውን ያሳለፈባት አሰብ በፍጹም ልትረሳው ስለአልቻለች የትዝታውን ቅባት ያፈሰሰበትን አሰብን እነሆ በዓይነ ልቡና ተመልከቷት ይለናል ፡፡
በደራሲ ዮሐንስ ብዕር በተለይ ከቀዳማዊ ኃይለሥላሴና ከደርግ ዘመነ መንግሥት ወዲህ አሰብ በአምስት ወረዳዎች ተከፋፍላና ራስ ገዝ ሆና ከመንደርነት ወደዘመናዊ ከተማነት፣ እንዴት እንደተለወጠችና እንዳደገች፣ የወደቡና የሠራተኛው ታሪክ፣ የሥራ ኃላፊዎችና የሕዝቡ ትጋት፣ ስለንግድ መርከቦች ማለት ስለ ባልደር ዚያ፣ስለ ግርማዊነታቸው የጦር መርከብ፣ ስለምጽዋ ኮከብ መርከብ፣ ስለንጋት ፣ስለ ንግሥተ ሳባ ፣ ስለላሊበላ፣ስለጣና ሐይቅ፣ ስለአብዮትና ስለ ነጻነት የኢትዮጵያ መርከቦች፣ በከተማዋ ይኖሩ ስለነበሩ ታላላቅ ሰዎች፣ ንጉሠ ነገሥቱ ቀዳማዊ ኃይለ ሥላሴና ሊቀ መንበር መንግሥቱ ኃይለ ማርያም የአሰብ ከተማን በየዘመናቸው ሲጎበኙ የነበረው ፌስታ ምን ይመስል እንደነበር በፎቶግራፍ ጭምር በተጠናከረ ማስረጃና አይረሴነት በአለው አተራረኩ ያስቃኘናል፡፡
በአጠቃላይ መጽሐፉ በታሪክ ሰነድነት ጭምር የሚፈለግና በምንጭነትም የሚጠቀስ ስለሆነ ቀሪውን ይዘት ከመጽፉ ለማየት ይቻላል፡፡ ነገር ግን አቶ ዮሐንስ መጽሐፉን በ26 ምዕራፎች ቢከፍለውም በማውጫው ላይ ይህ ምዕራፍ ስለዚህ ነገር ያስረዳል እያለ ማሳየት ሲገባው ማውጫ ብሎ በ7 ገጾች በየምዕራፉ ሥር ንዑሳን ርእሶችን እየደረደረ መሄዱ ማውጫውን አሰልቺ አድርጎታል፡፡ ለወደፊቱ በዳግም ህትመት በዚህ ላይ ትኩረት ቢያደርግበት የመጽሐፉ ሕይወት ማለፊያ እንደሚሆን እገምታለሁ፡፡
አዲስ ዘመን ሚያዝያ 6/2011
በታደለ ገድሌ ጸጋየ (ዶ/ ር)