አዲስ አበባ፡- የጠቅላይ ሚኒስትር ዶክተር አብይ አህመድ በሰሜን ሸዋ ዞን ሞረትና ጅሩ ወረዳ ያደረጉት ጉብኝት በወረዳው ህዝብ ካሳደረው ደስታ ባለፈ በመላው የዞኑ ህዝብ ዘንድ ተስፋና መነቃቃትን የፈጠረ መሆኑን የዞኑ አስተዳዳሪ ተናገሩ፡፡
ጠቅላይ ሚኒስትሩ ዞኑን የገለጹበት ሂደትም ከፋ ያለ፤ በቀጣይም ከፍ ለማድረግ የሚያስችሉ የቤት ሥራዎችን ሰጥተው የሄዱበት እንደሆነም ገልጸዋል፡፡
ጠቅላይ ሚኒስትር ዶክተር አብይ አህመድ ከምክትል ጠቅላይ ሚኒስትር ደመቀ መኮንን፣ ከኦሮሚያ ክልል ፕሬዚዳንት አቶ ለማ መገርሳ እና ከሌሎች የፌዴራልና የክልሉ ከፍተኛ ኃላፊዎች ጋር በሰሜን ሸዋ ዞን ሞረትና ጅሩ ወረዳ በኩታ ገጠም የተዘራ የስንዴ ሰብልን ጎብኝተዋል፡፡ ከጉብኝቱ በኋላም ከወረዳው ነዋሪዎች ጋር ተወያይተዋል፡፡
በውይይታቸውም የወረዳው ብሎም የዞኑ የልማትና መልካም አስተዳደር ጉዳዮች የተነሱ ሲሆን፤ ጠቅላይ ሚኒስትሩም ለነዋሪዎች መልስ ሰጥተዋል፡፡ በዚህ መልኩ የተካሄደው የጠቅላይ ሚኒስትሩ ጉብኝትም ለወረዳው ብቻ ሳይሆን ለመላው የዞኑ ህዝብ ተስፋና መነሳሳትን የፈጠረ ስለመሆኑ የዞኑ አስተዳደር ተናግረዋል፡፡
የዞኑ ዋና አስተዳዳሪ አቶ ተፈራ ወንድማገኘሁ ለዝግጅት ክፍላችን በስልክ እንደተናገሩት፤ የዞኑ ህዝብ ለጠቅላይ ሚኒስትሩ ከፍተኛ ክብርና ፍቅር አለው፡፡ ያደረገላቸው አቀባበል ድምቀትም ይሄንኑ የሚናገር ነበር፡፡ በቴሌቪዥን መስኮት ሲመለከታቸው የነበሩ መሪውን በዚህ መልኩ በአካል አግኝተው የልማት ሥራውን ሲጎበኙለትና የሚጎድለውንም ሲጠይቁት የደስታ ሲቃ እየተናነቀው ነበር ሲገልጽላቸው የነበረው፡፡ ጠቅላይ ሚኒስትሩም የህብረተሰቡን ጥያቄ ተቀብለው ተገቢውን ምላሽ ሰጥተዋል፡፡
ጠቅላይ ሚኒስትር ዶክተር አብይ በዚህ መልኩ ከህዝቡ ጋር ተገኝተው ልማቱን መጎብኘታቸውም ሆነ አብረው ቁጭ ብለው በህዝቡ ችግሮች ዙሪያ መምከርና ለጥያቄዎችም ምላሽ መስጠታቸው በአርሶአደሩ፣ በወጣቱ፣ በአመራሩ፣ በጥቅሉ በመላው የዞኑ ህዝብ ታላቅ ደስታና መነሳሳትን ፈጥሯል፡፡
እንደ አቶ ተፈራ ገለጻ፤ የጠቅላይ ሚኒስትሩ ጉብኝት፣ በወረዳው ቴክኖሎጂን በአግባቡ ለመጠቀምና ምርታማነትን ለማሳደግ እንዲቻል የተሰራውን የኩታ ገጠም ስንዴ ልማት በመመልከት አርሶአደሩን በማበረታታት ነው የጀመረው፡፡ አገር በቀል እውቀትን ተጠቅሞ ጥቁር አፈርን በማጠንፈፍና በክላስተር በመዝራት በሞረትና ጅሩ ወረዳ ውጤት ያመጣ እንደመሆኑም፤ ጉብኝቱ ይሄን እውቀትና ልምድ ወደሌሎች ለማስፋት ዕድል የሚፈጥር ነው፡፡በዚህ መልኩ የጀመረው ጉብኝትም በወረዳዋ ያሉ የመልካም አስተዳደርና የልማት ችግሮች ላይ ወደ መምከር ተሸጋግሯል፡፡
«ህብረተሰቡ የስቃ እንባ እየተናነቃቸው ጥያቄዎቻቸውን አንስተዋል» ያሉት አቶ ተፈራ፤ ቀደም ሲልም ለቀድሞው ጠቅላይ ሚኒስትር ያነሷቸውን ነገር ግን መልስ ያላገኙ የመንገድ፣ የውሃ፣ የሆስፒታልና ሌሎች የልማት ጥያቄዎችን ማቅረባቸውን ገልጸዋል፡፡ ቀድሞ ከተጠየቁና ምላሽ ካላገኙት አንዱ የደብረ ብርሃን- ደነባ- ለሚ መገንጠያ- እነዋሪ ጅሁር መንገድ ቀዳሚ ተጠቃሽ መሆኑን በመጠቆምም፤ እነዋሪ ላይ ሆስፒታል ያስፈልገናል፣ ከፍተኛ ኢኮኖሚያዊ ፋይዳ ያለው ከጅሁር ደቡብ ወሎ የሚያገናኘው መንገድ፣ የንጹህ መጠጥ ውሃ ጥያቄዎችም መነሳታቸውን ተናግረዋል፡፡
በመንገድ ችግር የእናቶች ሞት ስለመከሰቱ፣ በጠቅላይ ሚኒስትሩ የተጎበኘው ሰብል ሳይቀር ገበያ ለማድረስ የመንገድ ችግር መኖሩንና ሌሎች ማሳያዎችን በማንሳትም ነዋሪዎቹ ጥያቄዎቻቸውን ማቅረባቸውን አብራርተዋል፡፡
«ጠቅላይ ሚኒስትሩም የህዝቡን ጥያቄ በጥሞና አዳምጠዋል፤ ከፍ ባለ ስሜትም ተመልክተዋል፤» ያሉት አቶ ተፈራ፤ የተነሱ ጥያቄዎችን ቀድሞ እንደተደረገው ሙሉ ለሙሉ ይሰራሉ ብለው ከመሄድ ይልቅ ወደ ጽህፈት ቤታቸው ሲመለሱ ከሚመ ለከታቸው አስፈጻሚ አካላት ጋር ተወያይተው ጥያቄውን ለመመለስ እንደሚሰሩም መግለጻቸውን ጠቁመዋል፡፡
ለዚህ ደግሞ የፌዴራሉም ሆነ የክልሉ መንግሥት የቤት ሥራውን ወስዶ መስራት እንዳለበት ማስረዳታቸውንና፤ በአካባቢው ላይ ተጽዕኖ ፈጣሪ ብቻ ሳይሆን የአገር ባለውለታ የነበሩትን የጀነራል አበበ አረጋይን የጀግንነት ታሪክ በማውሳትም፤ በአካባቢው የሚሰሩ የልማት ሥራዎችም በዛ ልክ ከፍታ እንዲኖራቸው ታሳቢ የሚደረግ ስለመሆኑ አጽንዖት ሰጥተው መናገራቸውን ገልጸዋል፡፡
የጠቅላይ ሚኒስትሩ ንግግር በራሱ አቅም የሚሆን ነው፤ በዚህ ላይ በዞኑ በመገኘት የህዝቡን የልማት እንቅስቃሴና የመልካም አስተዳደር ችግር መመለከት መቻላቸው በከተማው ነዋሪ፣ በአርሶአደሩ፣ በወጣቱና በአመራሩ ጭምር ከፍተኛ ስሜትን የፈጠረ ነው ሲሉም ተናግረዋል፡፡
የአካባቢው ህብረተሰብ ብራንድ ያገኘ የጅሩ ሰንጋን በስጦታ ያቀረቡላቸው ሲሆን፤ የሸዋ ነገስታት ሲለብሱ የነበረውን በርኖስም ለእርሳቸውና ሌሎች ከፍተኛ ኃላፊዎች አበርክተውላቸዋል።
አዲስ ዘመን ህዳር 24/2011
በወንድወሰን ሽመልስ