1ኛ ዙር ብሔራዊ የቦክስ ሻምፒዮና ከታኅሣሥ 20 እስከ 23/2015 ዓ.ም በአዲስ አበባ ትንሿ ስታድየም ይካሄዳል። ሻምፒዮናውን የኢትዮጵያ ቦክስ ስፖርት ፌዴሬሽን ከሚያካሂዳቸው ዓመታዊ ውድድሮች አንዱ መሆኑ የተገለጸ ሲሆን በአራት የተለያዩ ዙሮች ለማካሄድ እንደታቀደ ተጠቁሟል። ይህም በዓለማቀፍ ደረጃ በሚካሄዱ ውድድሮች ኢትዮጵያን የሚወክሉ ስፖርተኞችን ለመምረጥ እንደሚረዳ የኢትዮጵያ ቦክስ ስፖርት ፌዴሬሽን ከትናንት በስቲያ በሰጠው መግለጫ አሳውቋል።
ፌዴሬሽኑ በመግለጫው ላይ ውድድሮችን ለማዘጋጀት የበጀት እጥረት እንዳለበት የጠቆመ ሲሆን፣ ይህን ችግሩን ለመቅረፍና አገር አቀፍ ሻምፒዮናውን ለማዘጋጀት ከሲሳይ አድማሴ ፕሮሞሽን ጋር በትብብር እንደሚሠራ አሳውቋል። በዚህም የፌዴሬሽኑ ምክትል ፕሬዚዳንት አቶ አብዱልሰመድ መሐመድ እና ሲሳይ አድማሴ ፕሮሞሽን ውድድሩን ደማቅ ለማድረግና በጋራ ለመሥራት የመግባቢያ ስምምነት ተፈራርመዋል።
ፌዴሬሽኑ ውድድሩን ለማዘጋጀት በዋናነት ዓላማ አድርጎ የተነሳው በዘንድሮ ዓመት በዓለም አቀፍ ደረጃ ሦስት ትላልቅ ውድድሮች ላይ ኢትዮጵያን የሚወክሉ ቦክሰኞችን ለመምረጥ መሆኑን በመግለጫው ወቅት አስረድቷል። በዓለም አቀፍ ደረጃ ከሚካሄዱት የቦክስ ውድድሮች አንደኛው ግንቦት ላይ በሕንድ የሚካሄደው የሴቶች የዓለም የቦክስ ሻምፒዮና ሲሆን፣ ሁለተኛው ሰኔ ላይ በኤሽያ ካዛኪስታን የሚደረግ ሌላ የዓለም ሻምፒዮና መሆኑ ተገልጿል። ሦስተኛውና ዋናው ውድድር ደግሞ በመጪው ሐምሌ በጋና መዲና አክራ የሚካሄደው የመላ አፍሪካ ጨዋታዎች ሲሆን በብሔራዊ ሻምፒዮናው በነዚህ ታላላቅ ውድድሮች ኢትዮጵያን የሚወክሉ የቡጢ ተፋላሚዎች ይመረጣሉ ተብሎ ይጠበቃል።
ብሔራዊ ሻምፒዮናው ሐሙስ ታኅሣሥ 20/2015 በ8፡00 በትንሿ ስታድየም በድምቀት ተጀምሮ መዝጊያውን እሁድ ታኅሣሥ 23 እንደሚያደርግ ተገልጿል። በውድድሩ የመክፈቻ ሥነሥርዓት ላይ ማርሽ ባንድን ጨምሮ ሌሎች የመዝናኛ መርሐግብሮች እንደሚኖሩም ታውቋል። ይህ ሻምፒዮና እንደ መጀመሪያ ዙር በአዲስ አበባ ከተደረገ በኋላ ሁለተኛና ሦስተኛው ዙር ውድድር በጎንደር እና አርባ ምንጭ ከተሞች ተካሂዶ ፍጻሜውን ተመልሶ በአዲስ አበባ እንደሚያደርግ ተገልጿል።
ብሔራዊ ሻምፒዮናው በሁለቱም ፆታ የሚካሄድ ሲሆን፤ በውድድሩ ላይ ስምንት የቦክስ ክለቦች ተሳታፊ እንደሚሆኑ ታውቋል። በዚህ ሻምፒዮና ከሚሳተፉ ክለቦች መካከል አዲስ አበባ ፖሊስ፣ፌደራል ፖሊስ፣ፌደራል ማረሚያ ቤት፣ድሬዳዋ ከተማ፣ ወላይታ ሶዶ ዩኒቨርሲቲ፣ ወጣቶች ስፖርት አካዳሚ፣ደሴና ጎንደር ከተሞች እንደሚገኙበት ተገልጿል።
የፌዴሬሽኑ ምክትል ፕሬዚዳንት አቶ አብዱልሰመድ እንደተናገሩት፣ የተለያዩ የቦክስ ውድድሮች ዓመቱን ሙሉ የሚካሄዱ ቢሆንም ተመልካች የላቸውም። ይህን የውድድሮች ተመልካች ማጣት ለመቅረፍና ለሕዝብ ተደራሽ በማድረግ በኩል የመገናኛ ብዙኃን ሚና ከፍተኛ ነው። በመሆኑም “በስፖርቱ ውጤት ሲመጣ እንደ ሃገር ሁለችንም የምንመሰገንበት ስለሆነ እንደየኃላፊነታችን እንወጣ” ሲሉ ጥሪያቸውን አቅርበዋል።
የቦክስ ስፖርት በቀደሙት ጊዜያት በኢትዮጵያ ከአትሌቲክስ ቀጥሎ በዓለም አቀፍ መድረኮች በተሳትፎ በተለይም በኦሊምፒክ ሁለተኛ ደረጃ የሚቀመጥ የነበረ ሲሆን ተወዳጅና ኢትዮጵያን ማስጠራት የቻለ እንደነበር ይታወሳል። የቦክስ ስፖርት አሁንም በበርካቶች ዘንድ ተወዳጅ ሲሆን በዓለም አቀፍ ደረጃ ኢትዮጵያን ያስጠሩና ባንዲራዋን ያውለበለቡ ጀግኖችን እንደማፍራቱ ማደግ አልቻለም። ከቅርብ ዓመታት ወዲህም እንቅስቃሴው ተዳክሞ እንደሚገኝ በመግለጫው ተገልጿል።
የኢትዮጵያ ቦክስ ስፖርት ፌዴሬሽን የጽሕፈት ቤት ኃላፊ አቶ ስንታየው ተስፋዬ ለስፖርቱ መዳከም ትልቁ የበጀት እጥረት መሆኑን ገልጸው ለዚህም መንግሥትና የሚመለከታቸው ባለድርሻ አካላት የበኩላቸውን አስተዋጽዖ ሊያበረክቱ እንደሚገባ አሳስበዋል። “የቦክስ ስፖርት ብዙ ወጪ የማይጠይቅና ከእግር ኳስ ጋር ሲነጻጸር የአንድ የእግር ኳስ ተጫዋች የወር ደሞዝ የአንድ የቦክስ ክለብ የዓመት ወጪ ሊሆን ይችላል” በማለትም የጽሕፈት ቤት ኃላፊው ስፖርቱን ለማሳደግ ከወጪ አንጻር ብዙ ከባድ አለመሆኑን አስረድተዋል።
በተጨማሪም የቦክስ ስፖርት የታዳጊ ፕሮጀክት እጥረት እንደሌለበት የጠቀሱት የጽሕፈት ቤት ኃላፊው፣ በአስራ አንዱም ክልልና ከተማ አስተዳደሮች የታዳጊ ፕሮጀክቶች እንዳሉ ተናግረዋል። ነገር ግን የታዳጊ ፕሮጀክቶችን አቅም ወደፊት አምጥቶ በመጠቀም ረገድ ችግሮች መኖራቸውን አክለዋል። ስለዚህ የቦክስ ስፖርት መሠረት ላይ ችግር የለበትም። ችግሩ ዓለም አቀፍ ውድድር ማድረግና የጨዋታ ልምድ ማግኘት ላይ መሆኑን ነው ሲሉ ተናግረዋል።
በኢትዮጵያ ከ1950ዎቹ ጀምሮ የቦክስ ስፖርት እንደ አንድ የስልጠና ዓይነት በጦር ኃይል ውስጥ ለወታደሮች ሲሰጥ እንደነበር መረጃዎች ያመለክታሉ። በተለይ በሐረር ጦር አካዳሚ ያሰለጥኑ የነበሩ እንግሊዞች የቦክስ ስፖርትን እንደ ዋነኛ የስልጠና ዓይነት ይሰጡ ነበር። በሠራዊቱ ውስጥ ከተቋቋሙ ክለቦች መካከልም የክቡር ዘበኛ፣ መኩሪያ፣ ምድር ጦር፣ ፖሊስ፣ ፈጥኖ ደራሽ የሚባሉ ክለቦች ይጠቀሳሉ። ስፖርቱን ለማስፋፋት የኢትዮጵያ ቦክስ ፌዴሬሽን በ1954 ዓ.ም ተመሥርቷል።
ዓለማየሁ ግዛው
አዲስ ዘመን ሰኞ ታኅሣሥ 3 / 2015