ነዋሪነቱ በኦሮሚያ ክልል ምዕራብ አርሲ ዶዶላ ወረዳ ነው። የፈጠራ ሥራን የጀመረው ገና ልጅ ሳለ በትንንሽ ነገሮች ሲሆን፤ ሁልጊዜ ደግሞ ከቅርቡ ችግር ይነሳና መፍትሄ ለመስጠት ይሞክራልⵆ ተማሪ አብዱልቃድር ሁሴን። በንድፈ ሀሳብ የተማረውን ወደ ተግባር መቀየርም የሁልጊዜ ልምምዱና ሥራው ነው። በእርሱ እሳቤ መማር ንድፈሀሳብን ብቻ ሳይሆን ተግባርንም ነው። ስለዚህም ትምህርት ቤቱ ተግባር ተኮር ትምህርት ባይሰጣቸውም ራሱ ችግሮችን ለይቶ የመፍትሄ ሀሳቦችን ለማመንጨት ይሞክራል። ለማህበረሰቡ ለማድረስም የተቻለውን ያደርጋል።
አብዱልቃድር ቤተሰቦቹ አቅመ ደካማ በመሆናቸው ብዙ ችግሮች ሲገጥማቸው ዘወትር ይመለከታል። በዚህም ፈጠራ ለሰው ሁሉ ያለውን ጠቀሜታ ቀርቦ ያውቀዋል። እናም የፈጠራ ሥራውን ለሌላ ሰው ሳይሆን ለራሱ ሲል ደከመኝ ሰለቸኝ ሳይል ይሰራል። በእርግጥ ብዙ እንደሚያለፋው ይረዳል። ትምህርቱንም ከአምስት ጊዜ በላይ እንዲያቋርጥና ከእኩዮቹ ጋር እንዳይማር አድርጎታል። በዚያ ላይ የቤተሰቡንም ችግር ለማቅለልም ሆነ የእራሱን ፈጠራ ውጤት ወደ ተግባር ለመቀየር መሥራት ግዴታው ነው። ስለዚህም በቀን ሰራተኝነት ዓመታትን አሳልፏል። አሁን ገና የአስረኛ ክፍል ተማሪ የሆነበት ምክንያትም ይህ ነው። በዚህ ግን ተበሳጭቶ አያውቅም። ምክንያቱም ከችግር መውጫው የፈጠራ ውጤቱ እውን ሲሆን እንደሆነ ጠንቅቆ ያውቃል።
‹‹ፈጠራ መሰረቱ እውቀት ቢሆንም ገንዘብ ከሌለ ዋጋ የለውም›› ይላል ከገጠመው ውጣውረድ ተነስቶ። እርሱ ፈጠራዎቹን ይሰራል እንጂ ተግባራዊ የሚደረጉበትን ነገር ማድረግ አይችልም። ከዚያ የሚብሰው ደግሞ አንዳንዴ ለፈጠራው የሚሆኑትን ቁሳቁስ መግዢያ ሲያጣ ነው። እናም የቀን ሥራው እንኳን መፍትሄ ሳይሆነው ሲቀር እጅጉን ያዝናል። ሆኖም ከእርሱና ከቤተሰቦቹ ውጪ የተረፈውን በመጠቀም ያንን ቀን ማለፍ ችሏል።
አብዱልቃድር ለትምህርቱ ከፍተኛ ፍቅር አለው። ከፈጣራው ጋር ጎን ለጎን ስለሚሰራበት ደግሞ እጅግ ደስተኛ ያደርገዋል። ወደ 25 የሚደርሱ የፈጠራ ሥራዎችን መሥራት የቻለውም በዚህ መልኩ ስለተጓዘ እንደሆነ ያምናል። ትምህርቱን መጨረስ በሚችልበት ሁኔታ ላይ ሳለ ዛሬ የ10ኛ ክፍል ተማሪ ቢሆንም ተስፋ ቆርጦ አያውቅም። ይልቁንም ያልተማረ ፈጣሪ የትም አይደርስም ብሎ ያስባልና ይቀጥላል።
አብዱልቃድር በዚህ መልኩ በመጓዙ በ2014 ዓ.ም በተካሄደው የፈጠራ ሥራ ውድድር ላይ ‹‹ፉራ›› የሚባል የመኖ ማቀነባበሪያ ሠርቶ ለሽልማት በቅቷል። ‹ፉራ›› የሚለው ቃል የተጠቀመበት ምክንያት ልዩ ትርጉም ስላለው ነው። ቃሉ የኦሮምኛ ሲሆን፤ ትርጓሜውም ‹‹ችግር ፈቺ›› የሚለውን ይይዛል። ስለዚህ የእርሱ ፍላጎት የማህበረሰቡን ችግር በቻለው ሁሉ መፍታት ነውና የንግድ ስያሜ አድርጎ እንዲንቀሳቀስበት ሆኗል።
አብዱልቃድር የፈጠራ ሥራውንና ሽልማቱን በከንቱ አላባከነውም። ውጣ ውረድ ቢኖረውም ለውጤት አብቅቶታል። ከውጪ ያሉ ሰዎች በሚዲያ አማካኝነት ሰምተው ድጋፍ (ስፖንሰር) ሆነውት ለገበያ ለማቅረብ ችሏል። በዚህም ዛሬ ላይ ብዙዎች እየገዙትና እየተጠቀሙበት ነው። በዘንድሮው ዓመት ደግሞ በተሻለ የፈጠራ ሥራ መጥቷል። ይህም ውጤታማ እንደሚሆንለት ያምናል። ምክንያቱም ሰው ከጣረ የፈለገበት ላይ እንደሚደርስ ይረዳል። ስለዚህም እንደቀደመው የፈጠራ ሥራው ስያሜውን ‹‹ፉራ›› ብሎ ልዩ ሦስት ሰዎችን መያዝ የምትችልና በሞባይል ስልክ የምንቆጣጠራት መኪና ይዞ መጥቷል። መኪናዋ ብዙ የተራቀቀባት በመሆኑ ብትጠፋ እንኳን ደውሎ ማግኘት ይቻላል። ምክንያቱም መቆጣጠሪያ ስልክ አላት። የት ላይ እንዳረፈችም ይነግረዋል።
ሌላኛዋ የፈጠራ ሥራ ተወዳዳሪ ነቢሃት ነስሩ ስትሆን የ12ተኛ ክፍል ተማሪ ነች። ከወልቂጤ ዩኒቨርሲቲ ስቴም ማዕከል የመጣች ሲሆን፤ የፈጠራ ውጤቷ ደግሞ በየቀኑ የብዙዎችን ሕይወት እየቀጠፈ እና ብዙዎችን ለአካል ጉዳተኝነት እየዳረገ ያለውን የመኪና አደጋ መከላከልን መሰረት ያደረገ ማሽን ነው። መኪናው ከአሽከርካሪው ቁጥጥር ውጪ በሚሆንበት ወቅት ይህን ሊቆጣጠር የሚችል የሚገጠም ማሽን ሲሆን፤ ቁልቁለት ላይ አደጋ ከመፈጠሩ በፊት በሴንሰር አማካኝነት ራሱ ታኮ በማበጀት ከአደጋ ሊከላከል የሚችል ነው።
ሌላው ማሽን ደግሞ ጠጥተው የሚያሽከረክሩ አሽከርካሪዎችን የአልኮል ሽታ የሚለይ ሲሆን፤ የመሪው ሲስተም ላይ በመግጠም ከመጠን ሲያልፍ የመኪናውን ሞተር በመቆለፍ ለትራፊክ ፖሊሶች በጂፒኤስ መልዕክት እንዲደርሳቸው የሚያደርግ ነው። ይህንንም ለመሥራት ያነሳሳት በአገራችን ያለው የትራፊክ አደጋ ጉዳይ ነው። ስለዚህም ግንዛቤ ከማስጨበጡ ጎን ለጎን እኔም የበኩሌን ላድርግ በሚል የፈጠራ ሥራዋን ለውድድር አቅርባዋለች። ይህ ደግሞ ብዙዎችን ያስደመመና ለሽልማት ያበቃት ሆኖላታል።
ነቢሃት፤ የፈጠራ ሥራዎችን ወደ ምርትነት ወይም ወደ ችግር ፈቺነት ለመቀየር ፈተና እንደሆነ ታነሳለች። ለመስራትም ቢሆን አጋዥ ከሌለ አስቸጋሪ እንደሆነ ታስረዳለች። እነርሱ ወልቂጤ ዩኒቨርሲቲ ከጎናችሁ አለሁ ስላላቸው ዛሬ የተሻለ የፈጠራ ሥራ ይዘው ቀርበዋል። ነገ ግን ምን እንደሚሆን አታውቅምና እዚህ ላይ መንግስትና የሚመለከታቸው አካላት ልዩ ትኩረት ቢሰጡት መልካም ነው ትላለች። ዛሬ የተሸለመችበትም ሆነ በቀጣይ ልትሰራቸው ያቀደቻቸው የፈጠራ ሥራዎች ለኢትዮጵያ ብቻ ሳይሆን ለዓለም የሚጠቅም ነገር አላቸውና ቸል ባይባሉም ስትል መልእክቷን ታስተላልፋለች።
የፈጠራ ሥራዎች ተጠቃሚ የሚሆኑት ወደ ተግባር ተቀይረው ማህበረሰቡ ጋር ሲደርሱ ብቻ ነው። አለበለዚያ እውቀት ብቻ ሆነው ከፈጣሪው ጋር ይቀበራሉ የሚለው ደግሞ እንደ ነቢሃት ሁሉ በወልቂጤ ዩኒቨርሲቲ ሲቲም ሴንተር አጋዥነት የፈጠራ ሥራውን ለውድድር ያቀረበው ተማሪ ይድነቃቸው ተክሉ ነው።
ተማሪ ይድነቃቸው ከዚህ በፊት የነበረውን ውድድር ተሳትፏል። ተሸልሞበታልም። ነገር ግን ሥራውን እውን ለማድረግ የሚያስችለው ምህዳር ስላላገኘ ፈጠራው ከእጁ ወጥቶ ማህበረሰቡ ጋር አልደረሰም። አሁንም ዩኒቨርሲቲው በአመቻቸለት እድል ዳግመኛ ለውድድር የሚሆነውን የፈጠራ ሥራ ለመስራት ችሏል፣ እንደውም አንዳንድ ነገሮችን የሸፈነው አምና በሽልማት የተሰጠውን ገንዘብ በመጠቀም ነው። ስለዚህም ‹‹ፈጠራ መስራት ስም እንጂ ውጤት ሊሆን አልቻለም›› ይላል።
ይድነቃቸው የ12ኛ ክፍል ተማሪ ቢሆንም ወደ ፈጠራ ልቡ የተሳበው ገና ልጅ ሳለ ነው። እናም ወደተግባር ባይቀየሩም እስካሁን በነበረው ጉዞ ከ21 በላይ የፈጠራ ሥራዎችን መስራት ችሏል። ሁሉም ተመርተው ወደህብረተሰቡ ቢወርዱ ኖሮ ጥቅማቸው የትዬለሌ እንደሚሆን አሁን ይዞት የመጣው ፈጠራ ያመላክታል። ፈጠራው እንደአገር ከውጪ የሚመጣውን በመቀነስ ትልቅ ጥቅም ይሰጣል ። እንደ አገር ከተወሰደ ደግሞ በተለይም በክልል ከተሞች አካባቢ ለሚከሰተው የድንገተኛ እሳት አደጋ ፍቱን መፍትሄ የሚሰጥ ነው።
እንደሚታወቀው የአዲስ አበባ እሳትና አደጋ ስጋት ሥራ አመራር ኮሚሽን ድንገተኛ የእሳት አደጋዎች ሲያጋጥሙ ክልሎች ድረስ እየሄደ ይሰራል። በዚህም ብዙ አደጋዎች ካጋጠሙ በኋላ መፍትሄ ሲሆን እንመለከታለን። ይህ ደግሞ ችግሩን ፈጥኖ ከመታደግ አኳያ ዘገምተኛ ያደርገዋል። በዚህም ብዙ ሀብት ንብረት፣ የሰው ሕይወት መጥፋት ይደርሳል። የአካል ጉዳተኝነትንም ያበራክታል። ስለሆነም ይህንን የተመለከተው ተማሪ ይድነቃቸው መፍትሄ ይሆናል ሲል የፈጠራ ሥራውን አቅርቧል።
የፈጠራ ሥራው የሚሰጠው ጠቀሜታ የእሳት አደጋ በሚነሳበት ወቅት ራሱ አስተካክሎ (አጀስትመንት ሰርቶ) እሳቱን ያስቆማል። ይህንን ሲያደርግም በሁለት አይነት መልኩ ሲሆን፤ የመጀመሪያው በኤሌክትሪክ ሲሆን ኤሌክትሪኩን በማቋረጥ እሳቱ ወደሌላ ክፍል እንዳይዛመት ማድረግና ግለሰቡ ከተኛ ደግሞ እንዳይታፈንና እንዳይሞትም በሮችን ከፍቶ ጭሱን በማስወጣት ያተርፋል፡፡
ሁለተኛው በወተር ፓንፕ አማካኝነት የተነሳውን እሳት ማጥፋት ሲሆን፤ በተለያዩ ቋንቋዎች እንድንጠቀመው የሚያስችለን ስርዓት ያስቀመጠበት ነው። የራሱ ማሳያ (ስክሪን ዲስፕሌ) ተገጥሞለት የሚሰራና መነሻ ቋንቋውም እንግሊዝኛ ነው። በተጨማሪም እንግሊዝኛ ቋንቋን ተጠቅሞ መጻፍ የሚችሉ ቋንቋዎችን ሁሉ ያስተናግዳል። ማለትም እንደ ኦሮምኛ ቋንቋ አይነቶችን። አማርኛ ቋንቋንም ቢሆን በእንግሊዝኛ ፊደላት ተጽፎ እንዲስተናገድ ያደርጋል። የእርሱ ፈጠራ ከውጪው የሚለየው ከመጮህ ያለፈ ሥራ መስራቱ ነው። ይህም በማስቆምና በማጥፋት ላይ ተንተርሶ ሰውን ይታደጋል።
ይድነቃቸው እንደሚለው፤ በ2014 ዓ.ም ብቻ በኢትዮጵያ የዘጠኝ ወር ሪፖርት 377 አደጋዎች ተመዝግበዋል። ከእነዚህ ውስጥ ደግሞ 251 የሚሆኑት የእሳት አደጋ ናቸው። በዚህ ውስጥም የ104 ሰዎች ህይወት ተቀጥፏል፤ በ54 ሰዎች ላይ ደግሞ ከባድና ቀላል ጉዳት ደርሷል። 47 የሚሆኑት ደግሞ የእሳት አደጋ ሰራተኞች ሲሆኑ፤ ይህ ሁሉ አደጋ መፍትሄ ካልተቸረው ቀጣይነቱ አጠያያቂ አይደለም። ሊብስም ይችላል። እናም የፈጠራ ሥራው ወደ ምርት ተቀይሮ ለገበያ ቢቀርብ መልካም አጋጣሚዎችን ይሰጣል።
ትምህርት ሚኒስቴር ለሰባተኛ ጊዜ ባዘጋጀው ዓለም አቀፍ የሳይንስ ቀን ላይ የትምህርት ሚኒስቴር የአጠቃላይ ትምህርት ዘርፍ ሚኒስትር ዴኤታ ዶክተር ፋንታ ማንደፍሮ እንዳሉት፤ የፈጠራ ሥራ ውድድር የንድፈ ሃሳብ ዕውቀትን ወደ ችግር ፈቺነት የምንቀይርበት አጋጣሚ ነው። ተማሪዎች በክፍል ውስጥ የቀሰሙትን የንድፈ ሃሳብ ዕውቀት ወደ ችግር ፈቺነት እንዴት እንደሚቀይሩት የሚማሩበትም ነው። ምክንያቱም ሌሎች ፈጥረው የሚያሳዩበት አጋጣሚ ስለሆነ። በተጨማሪም ተማሪዎችንና መምህራንን በማገናኘት ልምድ እንዲለዋወጡ ያደርጋል።
‹‹ሳይንስ አውቀነው የምንቀመጥ ሳይሆን ወደ ተግባር በመቀየር የእለት ተእለት ኑሯችንን የምናቀልበት ነው። ስለዚህም ተማሪዎች በዚህ ላይ የተቻላቸውን ሁሉ ማድረግ እንዲችሉ ማገዝ ያስፈልጋል። ሚኒስቴር መስሪያ ቤቱ ደግሞ ይህንን እያደረገ ነው። ወደፊትም ያደርገዋል፡፡›› ያሉት ዶክተር ፋንታ፤ የአገር እና የማሕበረሰብ ችግሮችን ለመቅረፍ በፈጠራ ሥራዎቻቸው ላይ ጠንክረው መሥራት የሚችሉ ተማሪዎችን ማበርታታት ያስፈልጋል። ለተወዳዳሪነት ብቁ የሆኑ ተማሪዎች እና መምህራንን ማበራከትም ግድ ነው። ስለዚህም የትምህርቱን መስክ ይህንን እንዲያሰፋ የተለያዩ ሥራዎች እየተከናወኑ እንደሆነም ያነሳሉ ዶክተር ፋንታ።
እንደነዚህ አይነት የፈጠራ ውድድሮች የተማሪዎችን አቅም ከማጉላቱ ባሻገር የማህበረሰቡን ችግር ማቃለል ያስችላሉ። ከዚያ ሻል ያለ አገርን ከፍ የሚያደርግ ተግባርም ለመከወን እድል ይሰጣል ያሉት ደግሞ በትምህርት ሚኒስቴር የምርምር እና የማሕበረሰብ ጉድኝት መሪ ሥራ አስፈጻሚው ዶክተር ሰለሞን ቢኖር ናቸው። እርሳቸው እንደሚሉት፤ ተማሪዎች በአጠቃላይ ይሁን በከፍተኛ ትምህርት ተቋማት ላይ ክፍል ውስጥ ከሚማሩት የንድፈ ሃሳብ ትምህርት ባለፈ የሚሠጡ ትምህርቶች ተጨባጭ እና ተግባር ተኮር እንዲሆኑላቸው ይፈልጋል። ለዚህ ደግሞ እንደነዚህ አይነት ሁነቶች ጠቃሚ ናቸው። በተጨማሪም እውቀታቸውን ሊያጎለብቱባቸው የሚችሉባቸው ተቋማት ሊኖራቸው ይገባል። በመሆኑም እንደ አገር ብዙ ተግባራት ተከውነዋል።
አንዱ በሳይንስ እና ቴክኖሎጂ ጥሩ ተሰጥኦ እንዲኖራቸው እና የፈጠራ ውጤታቸውን እንዲያጎለብቱ የሚያደርጋቸው ተቋም ሲሆን፤ ይህም የሳይንስ፣ ቴክኖሎጂ፣ ምህንድስና እና ሂሳብ ማዕከላት ናቸው። ማለትም አሁን ላይ 38 የስቴም ማዕከላት ያሉ ሲሆን ፤በቀጣይም በሁሉም ዩኒቨርሲቲዎች እንዲስፋፉ እና አገልግሎታቸውም በአካባቢያቸው ለሚገኙ የመጀመሪያ እና የሁለተኛ ደረጃ ትምህርት ቤቶች የፈጠራ ችሎታቸውን እንዲያዳብሩ ለማድረግ ታስቧል። ይህ የሚሆንበት ምክንያት ደግሞ እንደአገር በትምህርቱ ዘርፍ የፈጠራ ሥራዎች እንዲበዙ በማስፈለጉ ነው። ተማሪዎች አቅማቸውን እንዲያወጡም ያስፈልጋል።
የሚኒስቴሩ አመራሮች እንዳሉት የፈጠራ ውድድሮችና የፈጠራ ሥራዎች አስፈላጊነትና ጠቀሜታ በተለያየ መልኩ ያለ ቢሆንም በእገዛ ተደግፎ ወደ ተግባር ካልተገባበት ግን ምንም ነው። እናም ተወዳዳሪዎቹ እንዳሉት ሥራቸው መና እንዳይቀር በሥራው ልክ ወደ ተግባር መገባቱ ላይ ሁሉም የበኩሉን ያበርክት በማለት ለዛሬ አበቃን።
ጽጌረዳ ጫንያለው
አዲስ ዘመን ሰኞ ታኅሣሥ 3 / 2015