ስለለውጥና ስኬት የሚያጠኑ ዓለም አቀፍ ባለሙያዎች ሀገራዊ ለውጥ በግለሰባዊ ለውጥ ውስጥ እንዳለ ይናገራሉ፡፡ ይሄን እውነት ተመርኩዞ ዓለም አቀፉ የኢኮኖሚስት ማህበር ደግሞ ‹የሀገርን ለውጥ ከግለሰብ ለውጥ ጋር፣ የትውልድን ለውጥ ደግሞ ከሀገር ለውጥ ጋር ያቆራኘዋል፡፡ ከእኛ በቀር ሁሉም የዓለም ሕዝብ ይሄን እውነት ያውቃል፡፡ ወደ እኛ ሀገር ስንመጣ የለውጥ መሰረት ምን እንደሆነ ገና የገባን አይመስለኝም። ምክንያቱም ከትናንት እስከዛሬ የተራመድንባቸው ጎዳናዎች የለውጥን ሕግ የሳቱ መሆናቸው ነው፡፡
ዛሬም ድረስ እያደረግንው ያለው ነገር ከለውጥ ሕግ ጋር የሚቃረን ነው፡፡ ራሳችንን ሳንቀይር ሀገር ለመቀየር የቆምን ብዙዎች ነን፡፡ በአንድ ሃሳብ ሳንስማማ ሀገር ለመቀየር የፖለቲካ ፓርቲ አቋቁመን የምረጡኝ ቅስቀሳ የምናደርግ ብዙ ነን፡፡ ተነጋግረን ሳንግባባ ደጋፊና ተከታይ አቋቁመን የነገዋ የኢትዮጵያ ተስፋ ስንል ለራሳችን የማይገባ ስም ሰጥተን የምንቀሳቀስ ሞልተናል፡፡
ለዚህ ነው የለውጥ ሕግ አልገባንም ስል የተነሳሁት፡፡ ለውጥ ራስን ከመቀየር፣ አስተሳሰብን ከማዝመን የሚነሳ ነው፡፡ እድገት ሥልጣኔ ከእኔ ወደ ሌላው፣ ከሌላው ወደ ሌላው ከዛም ማህበረሰብ ላይ የሚያርፍ ነው፡፡ ያን የማህበረሰብ ለውጥ ነው የሀገር ለውጥ ብለን የምናወራው፡፡
ራስን መቀየር ስንል አስተሳሰብን፣ ልማድን፣ የኑሮ ዘይቤን መቀየር ማለት ነው፡፡ ራስን መቀየር ማለት ተነጋግሮ ለመግባባት፣ ተግባብቶ በአንድ ለመቆም ራስን ማዘጋጀት ማለት ነው፡፡ ራስን መቀየር ማለት ከራስ በፊት ለሀገርና ሕዝብ የሚያስብ ሰውነትን መፍጠር ማለት ነው፡፡ እኛ ደግሞ እኚህኝ ሁሉ ያሟላን አይደለንም፡፡ እኚህ ሁሉ በሌሉበት ነው ሀገር ለመፍጠር የምንፍጨረጨረው፡፡
በትናንት አስተሳሰብ ዛሬን እየኖርን፣ ተነጋግሮ መግባባት እየተቻለ ተለያይቶ በመቆም ሀገር አንለውጥም፡፡ ወንድም ወንድሙን ተኩሶ እየገደለ፣ በፖለቲካ ደባ አንገት ለአንገት ተናንቀን ቆመን የምናመጣው ለውጥ የለም፡፡ የሀገር ለውጥ የእኔና የእናተ ለውጥ ነው፡፡ ፖለቲካችንን ካልቀየርነው፣ ፖለቲከኞቻችን ካልተቀየሩ፣ እኔና እናተ ካልተለወጥን በነበርንበት እየረገጥን እንኖራለን እንጂ ለውጥ አናመጣም፡፡
እኛ ሳንሰራና ሳንለፋ የራሳችንን ለውጥ ከሀገራችን ለውጥ የምንጠብቅ ነን፡፡ ሀገራችንን ለመለወጥ ሳንሞክር ድሀ ሀገር ላይ በመፈጠራችን የምናዝን ነን፡፡ እውነቱ ግን ሀገራችንን ድሀ ያደረግናት ራሳችን ነን የሚለው ነው፡፡ ግለሰብ ሳይሰለጥን ሀገር አትሰለጥንም፡፡ ዜጋ ሳይለወጥ ሀገር አትለወጥም፡፡ መጀመሪያ እኛ እንለወጥ፡፡
መጀመሪያ አስተሳሰባችንን እንግራ፡፡ በእውቀት፣ በአንድነት መንፈስ መተባበርን ልማድ እናድርግ፡፡ ከዚህ እውነት ቀጥሎ ነው የሀገር ለውጥ የሚመጣው። ራሳችንን በጥላቻ፣ በመለያየት እያኖርን ብልጽግና መጠበቅ ሞኝነት ነው፡፡ ራሳችንን ከአንድነት፣ ከወንድማማችነት አርቀን ስልጡን ሀገርና ሕዝብ መጠበቅ የማይታሰብ ነው፡፡
ከትናንት ዛሬ የተራመድንባቸው ጎዳናዎች አንድ አይነት ናቸው፡፡ የተቀየረ ምንም ነገር የለንም፡፡ ይሄ ማለት ራሳችንን አልቀየርንም ማለት ነው፡፡ ይሄ ማለት ትናንታችንን አረሳንም ማለት ነው፡፡ ለዛ ነው መለወጥ ያልቻልንው፡፡ ግለሰባዊ ለውጥ የምንም ነገር መሰረት ነው፡፡ ሰው ራሱን ካለወጠ ሀገሩን መቀየር አይችልም።ሀገር የግለሰቦች አስተሳሰብ ናት፡፡
ሀገር በግለሰቦች ሃሳብና ድርጊት የተሰፋች ክንብንብ ናት፡፡ አስተሳሰብና ድርጊታችንን እስካላስ ተካከልን ድረስ አዲስ ነገር ማየት አንችልም። ሕይወት የብዙ መልኮች ስብጥር ናት፡፡ ብዙ እውነትን፣ ብዙ ተፈጥሮን ለብሰን ነው ወደ ምድር የመጣንው።ሁሉም እውነት፣ ሁሉም ተፈጥሮ የሰውን ልጅ መሰረት ያደረጉ መሆናቸው ነው፡፡ በምድር ላይ አንደኝነትን የሚሹ በርካታ ነፍሶች ተፈጥሮዋል፡፡ ሁላችንም ለብኩርና የምንጋፋ ነን፡፡ ሁላችንም አንደኛ ለመሆን የምንኖር ነን፡፡ በሌላ መንገድ የሁሉም የሰው ልጅ ፍላጎት አንደኛ መሆን ነው እያልኩ ነው፡፡
ለማሸነፍ የማንፈነቅለው ድንጋይ የለም፡፡ ለመብለጥ የማናደርገው የለም፡፡ የማሸነፍን ጥቅምና ዋጋ ያወቅነውን ያክል እንዴት ማሸነፍ እንዳለብን የምናውቅ ግን ጥቂቶች ነን፡፡ ለዚህም ነው ህልመኞች ሆነን የምንኖረው፡፡ ለዚህም ነው ከሙላታችን ጎለን የቆምነው፡፡ ማሸነፍ የማሰብ ውጤት ነው፡፡ አንደኝነት ከሩጫ ባለፈ የእውቀትና የአስተውሎት ጎዳና ነው። ባጠቃላይ መልካም ነገር የመልካም ልብና የመልካም አእምሮ ፍጻሜ ነው፡፡
እግሮቻችንን ሩጫ ሳናሰለጥን ለሩጫ የሚሆን ጥሩ ጫማ ብንገዛ ዋጋ የለውም፡፡ እጆቻችንን ስራ ሳናስለምዳቸው ብዙ እቅድ ብናወጣ ጥቅም የለውም። ልቦቻችንን እውነት ሳናስተምራቸው በእውነት መንገድ ላይ መቆማችን በራሱ ትርፍ የለውም፡፡ እንታደስ… በሃሳባችን በግብራችን እንለወጥ፡፡
አብዛኞቻችን ራሳችንን ሳናድስ ጥሩ ነገር ለመቀበል እጆቻችንን የዘረጋን ነን፡፡ ብዙዎቻችን እንዴት ማሸነፍ እንዳለብን ሳንረዳ ለውድድር ወደ ሜዳ የምንገባ ነን፡፡ ግን አሸንፈን አናውቅም… ግን አንደኛ ሆነን አናውቅም። ራሳችንን ማደስ ይኖርብናል፡፡ ራስን ማደስ ራስን መፍጠር ነው፡፡ ራስን ማደስ ራስን መስራት ነው፡፡ ራስን ማደስ የራስን እድል በራስ መወሰን ነው፡፡
ከትናንት ተላቆ ዛሬን መኖር ነው፡፡ ነገን ዛሬ ላይ መስራትም ነው፡፡ ራስን ማደስ እየሄድንበት ያለንውን ጎዳና ቆም ብሎ ማየት ነው፡፡ ከራስ ጋር መነጋገር፣ ከራስ ጋር መስማማት ነው፡፡ በሁለት እግራችን መቆም ባቃተን በዚህ አስቸጋሪ ዘመን ላይ ራስን አድሶ ዳግም እንደመኖር መልካም ነገር አለ ብዬ አላስብም፡፡ አሁን ላይ አብዛኞቹ ችግሮቻችን እኛው የፈጠርናቸው ናቸው። ችግሮቻችንን በገዛ እጃችን ስንፈጥር ለፈጠርናቸው ችግሮች የሚሆን መፍትሄ ግን የለንም፡፡
የሰው ልጅ አእምሮውን በሚገባ ከተጠቀመ ችግሮቹን በቁጥጥር ስር ማድረግ አያቅተውም። ይሄ ተፈጥሮአዊ እውነት ነው፡፡ እኛም ፍቅርን ከለበስን፣ አንድነትን ካበዛን ምንም ነገር ለማድረግ አቅሙ ይኖረናል፡፡ ብዙዎቻችን ተነጋግሮ በመግባባት ችግሮቻችንን በቁጥጥር ስር ከማድረግ ይልቅ ለእሰጣ ገባ እጅ የሰጠን ነን፡፡ ምክንያቱም ራሳችንን አለወጥንምና ነው፡፡
በትንሽ አእምሯችን ትልቅ ችግር ፈጥረን ለራሳችንም ሆነ ለሌላው መከራ ሆነን እናውቃለን። አሁን ላይ ሀገራችን ኢትዮጵያ አበሳዋን እያየች ያለችው ራሳቸውን ባለወጡ ዜጎቿ ነው፡፡ ይህ ማለት ለሀገራችን ጉስቁልና ተጠያቂዎች እኛ ነን ማለት ነው። አብዛኞቿ ችግሮቿ በእኛው የተፈጠሩ ሀገር በቀል ችግሮች ናቸው፡፡
ለችግሮቻችን የጋራ መፍትሄ ከመፈለግ ይልቅ አያገባኝምና አይመለከተኝም በሚል አጉል አስተሳሰብ በችግሮቻችን ላይ ሌላ ችግር የምንደርብ ነን፡፡ አሁን ላለነውም ሆነ ነገ ልንፈጥራት ለምንመኛት ሀገር እኛ የታደሰ አዲስ ማንነት ያስፈልገናል፡፡ አሁን ላለችውም ሆነ ነገ ለምትፈጠረው ኢትዮጵያ የታደሰ ሀገርና ሕዝብ ያስፈልጋታል፡፡
መታደስ ችግር ሆኖ አያውቅም፡፡ መታደስ ራስን ጠቃሚና አስፈላጊ አድርጎ በላቀ እሳቤ መፍጠር ነው። ራሳችንን በመለወጥ ለችግሮቻችን መፍትሄ የሚሰጥ አቅም ማዳበር ይኖርብናል፡፡ እጅ የሚሰጠን እንጂ እጅ የምንሰጠው ችግር መኖር የለበትም፡፡ በላቀ አስተሳሰብ ሁሉን መግዛት፣ ሁሉን መቆጣጠር የእኛ ድርሻ ነው፡፡ ሀገር ታማኝና ለለውጥ የበረታ ዜጋ ከሌላት ዋጋ የላትም፡፡ ሀገር ለእርቅ ልቡን፣ ለድርድር በሩን የከፈተ መንግሥትና ሕዝብ ከሌላት ተስፋ የላትም፡፡
በአንድ ሀገር ላይ ሁሉም እድሎች፣ ሁሉም ስኬቶች በግለሰብ ለውጥ የተፈጠሩ ናቸው፡፡ ሀገራችንን ለተሻለ ነገር የምናበቃት እኛ ነን፡፡ ሕይወት የምትሰምረው ዝም ብሎ በመኖር ሳይሆን እንዴት መኖር እንዳለብን ስንረዳ ነው፡፡ በዚህ መረዳት ውስጥ ነው አሸናፊነት የሚኖረው፡፡ በዚህ መረዳት ውስጥ ነው አንደኝነት የሚፈጠረው፡፡ በዚህ መረዳት ውስጥ ነው ሙሴን ሆነን ሀገራችንን የምናሻግረው፡፡
እንደ ዜጋ በሕይወት ሩጫ ውስጥ አሸናፊ ሆኖ ለመገኘት ባለ ራዕይ መሆን ያስፈልጋል፡፡ እንደ ሀገር የተሻለ ኢኮኖሚና ለመገንባት ደግሞ ከትናንት የተሻለ ዘመኑን የዋጀ አስተሳሰብ ግድ ይለናል፡፡ አሸናፊ ለመሆን ከፍላጎት በላይ ጽናት ያስፈልጋል፡፡ ነገሮችን በተለየ መልኩ ማየት ግድ ይላል፡፡ ብዙዎቻችን አንደኝነትን የምንፈልግ ነን አንደኛ ለመሆን ግን ስንሮጥ አንታይም። ብዙዎቻችን ሀገራችንን ለመለወጥ የምንፈልግ ነን ግን በሀገር ጉዳይ ላይ ስንግባባና አንድ ስንሆን አንታይም፡፡
ለምንም ነገር ራስን ማደስ ያስፈልጋል። በምንፈልገው በማንኛውም ነገር ላይ ለውጥ ለማምጣት ለውጥ በሚያመጣ ሃሳብ ራሳችንን መክበብ ያስፈልጋል። የማያግባቡንን በእርቅ እየፈታን በሚያግባቡን ነገሮች ላይ አንድ ብንሆን ዛሬ ሀገራችን ከኢኮኖሚ ባለፈ በሌሎች ነገሮች ላይም የበላይነቷን ባሳየች ነበር እላለሁ፡፡ ግን እኛ ስላልተለወጥን ሀገራችን አልተለወጠችም፡፡ ግን ተነጋግረን ስላልተግባባን ተነጋግሮ የሚግባባ ትውልድ አላገኘንም፡፡ ለዚህም ስር ነቀል ለውጥ ያስፈልገናል፡፡
ራሱን ለውጦ ሀገሩን ለመለወጥ የተጋ አእምሮ ግድ ይለናል፡፡ ካንቀላፋንበት እንቃ… ፡፡ ዓለም ርቆን እየሄደ ነው፡፡ ራሳችንን እያደስን ወደ ፊት መሄድን እንማር፡፡ ራስን ማደስ ለአዲስ ሕይወት አዲስ ምዕራፍ ነው፡፡ ራስን ማደስ ለምንም ነገር ሌላ እርምጃ ነው። እንደትናንት መኖር ይብቃን፡፡ እርቅና ይቅርባይነት በሌለው ሕይወት ውስጥ መኖር ይብቃን፡፡ ራስን ማደስ ራስን ከትናንት መለየት ነው፡፡ ከስህተትና ከውድቀታችን እየተማርን ለአዲስና ለሌላ ድል መዘጋጀት ነው፡፡ ባልታደሰ እና ባልተለወጠ ጭንቅላት ውስጥ ለውጥ የለም፡፡ ለውጣችን ያለው በመታደሳችን ውስጥ ነው፡፡
የዓለም ሥልጣኔ የአንድነት ሥልጣኔ ነው። የዓለም ሥልጣኔ ራስን የመለወጥ ሥልጣኔ ነው፡፡ እኛ ዛሬም ድረስ አምና ውስጥ ነን፡፡ እንደ ሀገርም እንደ ሕዝብም ከትናንትነት ውስጥ አልወጣንም። ለአንደኝነት ባላበቃን ትናንት ውስጥ ምን እናደርጋለን? አሸናፊነት የልምድና የተሞክሮ ውጤት ነው፡፡ አንደኝነት የፍቅርና የመቻቻል ነጸብራቅ ነው። እንደ ሀገርም ሆነ እንደ ግለሰብ ፍቅርን ማወቅ ብዙ ትርፍን ያመጣልናል፡፡
ፍቅር አጥተን በጥላቻ እየኖርን የምናመጣው የጋራ ድል የለም፡፡ እንደ ትናንት አትኑሩ… ራሳችሁን አድሱ ያልኳችሁ ለዚህ ነው፡፡ ዛሬ ላይ ብዙ ነገር ሞክረን ባይሳካልን ሊገርመን አይገባም ምክንያቱም ፍቅርና ይቅርታን አናውቅምና ነው፡፡ ዛሬ ላይ ብዙ ነገር ተመኝተን ባይሆንልን አይግረመን ምክንያቱም ተነጋግረን ተግባብተን አናውቅምና ነው፡፡ ለውጥና ስኬት ከፍቅር ጀምረው በአንድነት የሚጠቃለሉ ናቸው፡፡ ፍቅርን በማያውቅ ልብ ውስጥ አሸናፊነት የለም፡፡ አንድነት በሌለው ሀገርና ሕዝብ ውስጥ ልዕልና የማይታሰብ ነው፡፡ ስለዚህም እንታደስ፡፡ እንለወጥ፡፡
ዓለም ላይ ደስታ ከራቃቸው ሕዝቦች ውስጥ ቀዳሚዎቹ ነን፡፡ ይሄን እውነት ለማረጋገጥ ሚዲያ መከታተሉ በቂ ነው፡፡ ዋናው ጥያቄ ግን ይሄን ሁሉ እሴት፣ ይሄን ሁሉ የተፈጥሮ ሀብት፣ ይሄን ሁሉ የተማረ ወጣት፣ ይሄን ሁሉ ታሪክና ሥልጣኔ፣ ይሄን ሁሉ ባህልና ወግ ይዘን እንዴት ከዓለም ደስታ የራቃቸው ሕዝቦች ቀዳሚዎቹን ሆነን የሚለው ነው፡፡ ይሄ ጥያቄ አንድ መልስ ነው ያለው እርሱም ፍቅር ማጣት ነው። ደስታ በጎ አስተሳሰብ ነው፡፡ በጎ አስተሳሰብ ደግሞ ከፍቅር የሚመነጭ ነው፡፡
ሰው ፍቅር ከሌለው ደስታ የለውም፡፡ ሕዝብ አንድነት ከሌለው እድገት የለውም፡፡ ጉዳችንን አያችሁት? እናድግ ዘንድ፣ ከፍ እንል ዘንድ ፍቅር እና አንድነት ያስፈልገናል፡፡ ዓለም ላይ ከኢኮኖሚ ባለፈ የደስተኝነትን ክብር ያገኙ ሀገራት ፍቅርና አንድነትን ያስቀደሙ ናቸው፡፡ ከትናንት እስከዛሬ በማሸነፍ ዓለም ውስጥ የሚኖሩ እነሱ በፍቅር ሃይል ራሳቸውን ያደሱ ናቸው፡፡ ፍቅር የመጨረሻው ድህነታችን ነው።
ራስን መለወጥ ሀገር ለመለወጥ ቁልፍ ነገር ነው። በሕይወታችን ብዙ ነገሮች ልክ የሚሆኑት ለሌሎች ባለን ፍቅር ልክ ነው፡፡ ልባችን ውስጥ ፍቅር ከሌለ መቼም አናሸንፍም፡፡ መቼም ከፍ አንልም፡፡ ልባችን ውስጥ የለውጥ ሃይል ከሌለ ከትናንት የተሻለ ነገ አይኖረንም፡፡ የምንፈልጋቸው መልካም ነገሮች ሁሉ ሌሎችን በወደድንና ባፈቀርን ሰሞን የምናገኛቸው ናቸው፡፡
የምንፈልገው ጥሩ ነገር ሁሉ የእኛ የሚሆነው ልባችን ውስጥ ባለው ፍቅር ልክ እንደሆነስ ስንቶቻችሁ ገብቷችኋል? መልካምም ይሁን መጥፎ የምትፈልጉት ነገር ሁሉ በፍቅርና በጥላቻችሁ የሚሳብ ነው። እስከዛሬ ያላሸነፍነው በጥላቻ ልባችን ለማሸነፍ ስለሮጥን ነው፡፡ እስከዛሬ አንደኛ ያልወጣንው ይቅርታ በሌለው ልብ ስለተወዳደርን ነው፡፡ እስከዛሬ ነግደን ያላተረፍንው፣ ተምረን ስራ ያልያዝነው፣ ኖረን ለቁም ነገር ያልበቃንው የፍቅርን ሃይል ስላልተረዳን ነው፡፡
ሀገር ፍቅር ትሻለች፡፡ ሀገር ይቅር የሚል ልብ ያስፈልጋታል፡፡ ለዚህም ነው ራሳችንን እናድስ ስል የተነሳሁት፡፡ መታደስ ከቻልን በእያንዳንዳችን ቅጽበት ውስጥ ብዙ አሸናፊነት፣ ብዙ አንደኝነት አለ፡፡ መለወጥ ከቻልን ለሀገር የሚሆን ብዙ ነገር ይኖረናል። ከትናንት በመማር፣ ከስህተት በመመለስ መታደስ እንችላለን፡፡ ተነጋግሮ በመስማማት፣ ተወያይቶ ለችግሮቻችን መፍትሄ በማምጣት መለወጥ ይቻላል። በዚህም ሀገርን መለወጥ ይቻላል!።
አዲስ ዘመን ታህሳስ 3/2015