በአገራችን የአልባሳት ፋሽን አልፎ አልፎ በመድረክ ለዕይታና ለግዢ ይቀርባል፡፡በተለይ በብዛት ሃይማኖታዊና ባህላዊ በዓላት ሊከበሩ ጥቂት ቀናት ሲቀራቸው የፋሽን አልበሳት ዐውደ ርዕዮች ይጐመራሉ ፡፡ በገበያ ቦታዎችም በልዩ ልዩ ዲዛይን የሚሠሩ ባህላዊ አልባሳት ሽያጭ ይደራል፡፡እንደ አዲስ አበባ በመሳሰሉ ከተሞች የፋሽን አልባሳት ዐውደ ርዕይና ባህላዊ አልባሳት ገበያ የሚደራው በበዓላት አቅራቢያ ነው፡፡ ኤግዚቢሽን ማዕከል እንኳ ገበያው ለጎብኚዎች በብዛት ክፍት የሚሆነው በዓላት በሚቃረቡበት ሳምንት ነው፡፡ በያዝነው ዓመት መስቀል አደባባይ በሚገኘው የኦሮሞ የባህል ማዕከል የባህላዊ አልበሳት ፋሽን ዐውደ ርዕይ የኢሬቻ በዓል ዋዜማን ተንተርሶ ለጎብኚዎች ክፍት መሆኑና መታየቱ ይታወሳል።
ይህ የባህላዊ አልባሳት ፋሽን ዐውደ ርዕይ ከተካሄደ ከወር በኋላ ደግሞ ከጥቅምት 25 እስከ ጥቅምት 28 ቀን 2015 ዓ.ም የአፍሪካ የጨርቃ ጨርቅና የአልባሳት ፋሽን ዐውደ ርዕይ በአዲስ አበባ ስካይ ላይት ሆቴል ተካሂዶ ነበር።በዚህ 8ኛው የአፍሪካ ሶርሲንግና የፋሽን ሳምንት ዓለም አቀፍ ዐውደ ርዕይም ከ30 በላይ አገራት የተሳተፉበት ነበር፡፡ የአፍሪካ መዲና በሆነችው አዲስ አበባ በተካሄደው በዚህ የፋሽን አልባሳትና ጨርቃ ጨርቅ ዐውደ ርዕይ ብዙ የአፍሪካ አገሮች ባህላዊ አልባሳቶቻቸውን እና ፋሽናቸውን ከማሳየት በተጨማሪም የኢትዮጵያን አልባሳት በማየትም ተደምመዋል።ዲፕሎማቶች ጭምር ይህን የአልባሳትና የጨርቃ ጨርቅ ዐውደ ርዕይ እንደጎበኙ መታዘብ ተችሏል፡፡
ይህ የፋሽን ዐውደ ርዕይ መከፈቱ ዓለም አቀፍ ተቋማት በኢትዮጵያ በዘርፉ ለመስራት ያለውን ሰፊ ዕድል እንዲገነዘቡ የሚያደርግ እና ለአገር ውስጥ አምራቾችም ሰፊ የገበያ ዕድል የሚፈጥር መሆኑን የኢንድስትሪ ሚኒስቴር ሚኒስትር አቶ መላኩ አለበል በመክፈቻው ስነ ሥርዓት ላይ ተናግረው ነበር ።
ዐውደ ርዕዩ ለአልባሳት እና ጨርቃ ጨርቅ ኢንዱስትሪዎች ትልቅ የምሥራች መሆኑን የተናገሩት አቶ መላኩ አለበል፤ በኮቪድ እና በሀገር ውስጥ የሰላም እጦት ምክንያት ከእነዚህ የኢንዱስትሪ ፓርኮች ማግኘት የሚገባውን ጥቅም ማግኘት ሳይቻል መቆየቱን ጠቁመዋል። የፋሽን አልባሳት ዐውደ ርዕይ የኢንዱስትሪ ፓርኮች ተገቢውን ጥቅም እንዲያገኙና ኢትዮጵያን ለማስተዋወቅ እንደሚያግዝም ነበር ሚኒስትሩ የተናገሩት። የቱሪዝም ሚኒስቴር ሚኒስትር ወይዘሮ ናሲሴ ጫሊ በበኩላቸው በወቅቱ ዐውደ ርዕዩ ሲከፈት እንደተናገሩት፣ በእንግዳ ተቀባይነቷ የምትታወቀው ኢትዮጵያ ይህንን ዓይነት የፋሽን ዐውደ ርዕይ በማዘጋጀቷ በቱሪዝም ዘርፍ ያላትን እምቅ አቅም ለመጠቀም ያስችላታል ።
ይህን መሰል ዓለም አቀፍ የፋሽንና የአልባሳት ዐውደ ርዕይ ከኮቪድ በኋላ ሲዘጋጅ በአገራችን የመጀመሪያው ነው ፡፡ቀደም ባሉት ዓመታት የኮረና ወረርሽኝን ተከትሎ በመጡት ተግዳሮቶች በንግዱ ዙሪያ ተፅዕኖ ፈጥረው እንደነበር ይታወሳል፡፡በንግድ ሰንሰለቶችና አቅርቦቶች ላይ ካደረሱት ችግር መካከልም በተለይም በአልባሳት እና ጨርቃ ጨርቅ እንዲሁም በቆዳው ዘርፍ ተፅዕኖ ማሳደሩ የሚታወስ ነው።
ለአራት ቀናት የቆየው የአልባሳት ፋሽን ዐውደ ርዕዩ ከ30 አገራት የተውጣጡ 200 ዓለም አቀፍ የጨርቃ ጨርቅና አልባሳት አምራቾችና ላኪዎች ምርቶቻቸውን አሳይተውበታል፡፡ በተጨማሪም ከ50 አገራት የመጡ ከ6ሺ በላይ ዲዛይነሮች እና ገዢዎች ተሳትፈውበት ነበር። በውጭ አገር መገናኛ ብዙሃንም ሠፊ ሽፋን የተሰጠው የፋሽን ዐውደ ርዕይ ነው።
በዚህ ከብዙ አገራት የመጡ አምራቾች እና ዲዛይነሮች በተሳተፉበት የአልባሳትና የጨርቃ ጨርቅ የፋሽን ዐውደ ርዕይ የኢትዮጵያን ባህላዊ አልባሳቶች ለውጭ ጎብኚዎች ለማሳየት ምቹ አጋጣሚ ነበር ማለት ይቻላል፡፡ ይህም በኢትዮጵያ ለረጅም ጊዜ የቆዩ ከጥጥ የሚዘጋጁ ጋቢዎች፣ ነጠላዎች፣ ኩታ እና ቀሚሶች በፋሽን መልክ ለጎብኚዎች መታየታቸው አገራችንን ከአልባሳት ፋሽኑ አልፎ የማይዳሰሱ ቅርሶቿ ድምቀት እና የቱሪዝም አቅሟን ለማሳደግ የሚያስችል ነው።
የአልባሳትና የጨርቃ ጨርቅ የፋሽን ዐውደ ርዕዩ አፍሪካ ከዓለም አቀፍ የአልባሳት ኢንዱስትሪ ተዋናዮች ጋር ልምድን እንድትጋራ የገበያ ዕድልም እንድታመቻች ከማድረጉ በተጨማሪ የረጅም ጊዜ ግንኙነትንም እንድትፈጥር የሚያመቻች እና በዘርፉም ላይ ውሳኔ ሰጪ አባል ለመሆን የሚያስችል ነው፡፡የአፍሪካ ፋሽንና ኢንዱስትሪዎች ከኢንቨስተሮች ከጅምላ ሻጮችና ቸርቻሪዎች ጋር እንዲገናኙም ያስቻለ መሆኑ በወቅቱ ተጠቁሟል፡፡ በዐውደ ርዕዩ የአፍሪካ የአልባሳት ዲዛይነሮች በመላው ዓለም የፋሽን ገበያ ውስጥ ያለቀለት ፋሽን ከፈጠሩ ባለሙያዎች ጋር እንዲገናኙም አስችሏል። ከአፍሪካ አቻዎቻቸውም ጋር አጋርነት በማመቻቸት ‹‹አፍሪካ ውስጥ የተሠራ ፋሽን›› እንዲፈጥሩ የሚያመቻች ነው፡፡ ይህም የአፍሪካ የጨርቃ ጨርቅና የአልባሳት ፋሽን ዐውደ ርዕይ አፍሪካ የባህል አልባሳትና የፋሽን ገበያ እንዲጎመራና እንዲደራ ያስችላል ተብሎ ተስፋ እንዲጣልበት አድርጓል፡፡
አውደ ርዕዩ ዘመናዊ የቤት ውስጥ ንድፎችን አልያም ኢንትሪየር ዲዛይን ለእይታ የቀረበበት መሆኑም ሌላ እድል ፈጥሯል፡፡ ይህም አፍሪካውያን ዲዛይነሮች በዓለም አቀፍ ደረጃ በሚዘጋጁ ተመሳሳይ ትዕይንቶች ላይ እንዲሳተፉ መንገድ የጠረገ ነው፡፡
አፍሪካ እምቅ የጨርቃጨርቅ ምርት አቅም ቢኖራትም አሁንም አብዛኛው አፍሪካዊ አልባሳትን ከበለጸጉ አገራት በከፍተኛ ውጪ ምንዛሪ እያስገቡ ነው፡፡ ይሄንን ለመቀየር እና አፍሪካዊ ሸማኔዎችን ለማበረታታት የፋሽን ሾውና መሰል አውደ ርዕዮች የገበያ ትስስር፣ የቴክኖሎጂ እና የእውቀት ልምዶችን እንዲፈጠሩ በማድረግ ረገድ ትልቅ አስተዋፅኦ ማበርከት ይችላሉ። የአፍሪካ ልማት ባንክ ሪፖርት እንደሚያመለክተው የጨርቃጨርቅ ኢንዱስትሪ በአፍሪካ ለዜጎች የስራ እድሎችን በመፍጠር ከግብርና ቀጥሎ ሁለተኛው ነው።
ኃይለማርያም ወንድሙ
አዲስ ዘመን ታህሳስ 3/2015