“አይዲ ዲሪካሞ” የአፋሮች ውበት መገለጫ

“ውበት እንደተመልካቹ ነው” በሚለው ሀሳብ ብዙዎች ይስማማሉ:: ለአንዱ ቆንጆና ውብ የሆነው ለሌላው ትርጉም ላይኖረው ይችላል። ውበት ከሰው ሰው ብቻም ሳይሆን ከማኅበረሰብ ማኅበረሰብ ከአካባቢ አካባቢ የተለያየ ነው። የአንዱ አካባቢ ለውበት የሚሰጠው ትርጓሜ ለሌላው አካባቢ ላይዋጥለት ይችላል::

አፍንጫ ስንደዶ፣ ጥርሰ በረዶ፣ አይኑ ጎላ ያለ፣ ስስ ከንፈር፣ ዞማ ጸጉር ብሎ ውበትን መግለጽ እንደማይቻል ዘመናዊ የሥነ-ውበት ባለሙያዎች ይገለጻሉ:: ምክንያቱም የአንዱን አካባቢ ከሌላው አካባቢ ውበት ለመለየት በአንድ መስፈርት ውስጥ ማስቀመጥ ፈጽሞ አይቻልምና:: ለዚህም ነው ውበት እንደ ተመልካቹነው የሚባለው::

ከመብላትና ከመጠጣት ባሻገር የሰው ልጅ እርካታን ከሚጎናጸፍባቸው መንገዶች አንዱ ውበት ነው:: በየትኛውም ባሕል ውስጥ የሚኖሩ ሕዝቦች ውበትን በተቀበሉት ልክ ይስማሙበታል በተስማሙት ልክ ደግሞ ይደነቁበታል:: በመረጡትና በተሰማሙበት ልክም ቆንጆ ሆነው መታየትን ይፈልጋሉ:: አምረውና ተውበው ለመታየት ደግሞ ማኅበረሰቡ ያመነበትን ወይም የተቀበለውን የመዋቢያ አይነቶች ይጠቀማሉ::

የዓለማችን የሥነ-ውበት ጠበብቶች ስለውበት ብዙ ብለዋል። በየዕለቱ ቀላል የማይባል ሰው ብዙ ገንዘብ ለውበት መጠበቂያ ያወጣል። ዓለማችን በየወቅቱ ቆነጃጅትን እያወዳደረች ትሸልማለች…ሌላም ሌላም:: ለመሆኑ ውበት ምንድን ነው? ውበት በምን መስፈርት ይለካል? በምን ቋንቋ ይገለጻል? ውበት ከሥነ-ምግባር ምን ዝምድና፤ ከሃብት ጋርስ ምን ግንኙነት አለው? ሥነ-ውበት (Aesthetics) የውበትን ጽንሰ ሃሳብ ምንነት፣ እሴቶች፣ አተያዮች እንዲሁም የመገምገሚያ መስፈርቶችን የሚያጠና ዐቢይ የፍልስፍና ዘርፍ ነው።

የሥነ-ውበት ፈላስፎች ውበት የሚለው ጽንሰ ሃሳብ በአጠቃላይ የሰው ልጅን፣ ኪነ-ሕንጻን፣ ስዕልን፣ ሙዚቃን፣ ቅርጻ-ቅርጽን፣ ቲያትርን፣ ሥነጽሁፍን፣ ፊልምንና የመሳሰሉትን የሰው ልጆች የጥበብ ሥራዎች፤ እንዲሁም የተፈጥሮን መስህቦች አካቶ የሚያጠና ዘርፍ መሆኑን ይናገራሉ::

ውበት ማለት የአንድ ነገር የሚስብ፤ የሚያረካ ወይም የሚያስደስት ገጽታ ወይም ሁኔታ ማለት ነው። ውበት ውጫዊ ቅርጽን፣ ቀለምን፣ መጠንን፣ መልክን ወይም ደምግባትን የሚያመለከት አልያም ውስጣዊ ማንነትንና ሥነ-ምግባርን የሚመለከት ጉዳይ ሊሆን ይችላል:: ነገር ግን አስቸጋሪው ጥያቄ ማንን የሚስብ፣ ማንን የሚያስደስት ወይም የሚያረካ የሚለው ነው – የውበቱን ባለቤት? ማኅበረሰቡን? ማንን? የዓለማችን ሊቃውንት እነዚህን መሰረታዊ የሥነ-ውበት ጥቄዎች ለመመለስ በሁለት ታላላቅ ጎራ ተሰልፈው ለበርካታ ዘመናት ተሟግተዋል፤ መጻህፍትን ጽፈዋል፤ የሰው ልጆችን የአስተሳሰብ አድማስም አስፍተዋል:: በመጀመሪያ የምናገኘው የሁሉን አቀፎች ወይም የፍጹማውያኑን ርዕዮተ ዓለም ሲሆን ይህም ውበት መለካት ያለበት ነገሮቹ በራሳቸው ባላቸው ማንነት እንጂ ከእነርሱ ውጪ በሚገኝ ማንኛውም ነገር ላይ ማለትም በማኅበረሰቡ ወግ፣ አመለካከት ወይም እምነት ላይ ተመስርቶ መሆን የለበትም የሚል አቋምን የሚያራምድ ነው::

በአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ባኅልና ቱሪዝም ቢሮ በታተመ «ባሕል ወቱሪዝም» የተሰኘ መጽሔት ላይ «ሴቶችና የውበት ማድመቂያቸው ድሮና ዘንድሮ» በሚል ርዕስ ከተጻፈ ጽሑፍ ስለቁንጅና እንዲህ ይላል….

«ለቁንጅና በዓለም ላይ ያልተደረገና ያልተሞከረ ጥረት የለም። የፈረንሳይ ንግስት ኢውጀኒ ገላዋን በታጠበች ቁጥር ለሰውነቷ ቆዳ ማሳመሪያና ማለስለሻ አንዳንድ ቅርጫት እንጆሪ ያስፈልጋት ነበር። ቤድፎርድ የተባለች የሆላንድ ወይዘሮ ደግሞ ገላዋን ስትታጠብ አንድ ደርዘን ጠርሙስ ወተት አዘጋጅታ ከውሃ ጋር በመቀየጥ ለሰውነቷ የተለየ ውበት ለመስጠት ትጥር እንደነበር ይነገርላታል።»

ሁሉም የሰው ልጅ ለውበቱ የሚጨነቅ ቢሆንም ሴቶች የበለጠ ለውበታቸው ስሱ ናቸው። በአንጻሩ ደግሞ ወንዶች በሴቷ ፊት የሚታይ ጀግንነታቸው ብቻውን ውበታቸው እንደሆነ ሲቆጠር እናያለን። በተለይ እንደ ኢትዮጵያ ባሉ በጦር ጀግንነት ፊትአውራሪዎች በበዙባት ሀገር። ሥነጽሑፋዊ ሥራዎቻችንም የወንዶችን ሳይሆን የሴቶችን ውበት ነው በብዛት አድምቀውና አድነቀው የሚጽፉት። ቆንጆ መባልና ውብ ሆኖ መታየት ለራስ ያለን ግምት ከፍ ለማድረግ ይረዳል። በራስ መተማመን ይጨምራል። በሌሎች ዐይን ውስጥ ውብ ሆኖ መታየት ደስ ይላል። ለዚህ ታዲያ የውበት መጠበቂያና መዋቢያዎችን መጠቀም በየትኛውም ማኅበረሰብ ዘንድ የተለመደና ማኅበረሰቡ የሚቀበለው እውነታ ነው።

ይህን ያህል ስለውበት ለመንደርደሪያነት ከጠቀስን ወደሀገራችን ጫፍ እንዝለቅና ስለ አፋር ወንዶች የጸጉር አሠራር በጥቂቱ እናስቃኛችሁ::

የአፋር ወንዶች ከሴቶቹ ይልቅ ለውበታቸው ይጨነቃሉ:: መጨነቅም ብቻ ሳይሆን ብዙ ጊዜያቸውን ለፀጉራቸው ውበት ያጠፋሉ::

የአፋር ኮበሌዎች በብዛት የሚጠቀሙበት የጸጉር አሠራር መካከል ቀዳሚው “ አይዲ ዲሪካሞ” ይሰኛል በአማርኛ “ኮልኮሎ” ይባላል:: የአፋር ኮበሌዎች (ጎረምሶች) በኮልኮሌ ለመዋብ ጸጉሩን ንጹህ አድርጎ ማሳደግ የግድ ነው:: በየጊዜው ንጽኅናውን መጠበቅና ቅባት መቀባትም ይጠበቃል:: ጠጉሩ በሚፈለገው መጠን እንዲያድግ ማድረግ ያለባቸውን ሁሉ አድርገው በቂነው ብለው ሲያስቡ ወደ መጸቅለሉ ይገባሉ:: ለመጠቅለያነት የሚጠቀሙት ደግሞ የሰሊጥ እንጨት ያዘጋጃሉ::

አንድን የአፋር ወጣት ጸጉር ለመሥራት ሌሎች ሁለት ሰዎች ያስፈልጉታል:: በሰሊጥ እንጨት ወይም በእስኪርቢቶ ቀፎ ለሁለት ይጠቀልሉለታል:: ከመጠቅለሉ በፊት ሞራና ቅቤ ወይም ቅባት ይቀባል:: ሞራው ነጭ እንደሆነ የሚያቆየው ሲሆን ቶሎ እንዳይበታተንም ያደርገዋል:: ቅባቱ ከሌለ ቶሎ ይበላሻል ነጭ እንደሆነ አንድ ሳምንት ይቆያል:: መጨረሻ ላይም ሞራው ቀልጦ ይፈሳል።

ዲረካሞ በወጣቶች ዘንድ እጅግ የሚወደድ ሲሆን ጥሩ የውበት መገለጫም ነው:: ወጣትነት ካለፈ ይህን አይነት መዋቢያ ስለማይጠቀም ጸጉሩን ይቆረጣል:: ከ30 ዓመት በላይ የሆነው ወንድ በኮልኮሎ ሊዋብ ማኅበረሰቡ አይፈቅድለትም:: በኮልኮሎ ስለሚያምር የአፋር ኮረዶች በጣም ይወዱታል::

ኢትዮጵያውያን ወጣቶች አሁን ላይ ለፋሽን ልዩ ቦታ የሚሰጡ ናቸው። ባጠቃላይ ኢትዮጵያውያን በየራሳቸው ባሕል መዘነጥ፣ ውበትን መጠበቅ፣ መልበስን የሚወድ ማኅበረሰብ መሆኑን መረዳት እንችላለን።

ቀደም ባሉት ግዜያት ኢትዮጵያውያን በባኅላቸውና ባላቸው የራሳቸው የፋሽን ስልት ተውቦ ለመታየት ይጥሩ ነበር። የአፋር ወንዶችን እንደ ምሳሌ ማንሳት ይቻላል። አሁን ላይ ደግሞ በተለየ መንገድ በማኅበራዊ ድረ ገፅና በተለያዩ የመገናኛ ብዙሃን ይህን ልምድ በማስፋት የፋሽን ኢንዱስትሪው እንዲያድግ እየሠሩ እንደሚገኙ ይታወቃል።

ኢትዮጵያውያን ለዓለም ልናስተዋውቀው የምንችለው ቋንቋ፣ ውበት አጠባበቅ፣ አለባበስ፣ አመጋገብና ሌሎች በርካታ ነገር እንዳለን ማሳየት ስንችል ነው። ይህን በፋሽን ኢንዱስትሪው አማካኝነት ለማስተዋወቅ ደግሞ ባለሙያዎቻቸን ተግተው ሊሠሩ ይገባል።

አዲስ ዘመን ሰኞ ሰኔ 9 ቀን 2017 ዓ.ም

Recommended For You