ኢትዮጵያ ከብዙ ሀገራት መፈጠራቸው እና መኖራቸው ከነአካቴው ሳይታወቅ በፊት ያልተጻፈ ሕገ መንግሥት፣የሙዚቃ ኖታ ፣ ቅራት( የመጀመሪያው የኢትዮጵያ ፖሊስ)ወዘተ ነበሯት። የስልጣኔ መንገዶች ለዓለም ሕዝብ በተሞክሮነትም አበርክታለች። የተለያዩ ማኅበራዊ፣ ፖለቲካዊ፣ ኢኮኖሚያዊ ፣ ሃይማኖታዊ ወዘተ ተሞክሮዎችን ከተለያዩ ሀገራት ማምጣቷም እሙን ነው። ለአብነት ያህል በበጅሮንድ ተክለሐዋሪያት ተክለማሪያም አማካኝነት የተጻፈው የ1923ቱ የመጀመሪያው የኢትዮጵያ ዘመናዊ ሕገ መንግሥት የተወሰደው ከጃፓን ነበር።
አሁን እየተከተልነው ያለነውም የመንግሥት አወቃቀር (forms of government) ማለትም ( structure of the state) አንዱ ፌዴራሊዝም አካል ምንጩ ሌሎች ሀገራት ናቸው። ኦዲቲንግ ሲስተም፣ ሁሉን አካታች ዘመናዊ ትምህርት ወዘተ እያልን የምንጠቀምባቸው አሠራሮችም የኢትዮጵያ ሳይሆኑ ሌሎች ሀገራት ሲጠቀሙባቸው የቆዩባቸው አሠራሮች ናቸው። እናም ኢትዮጵያ ከሌሎች መልካም ነገሮችን ወስዳለች ተጠቅማለችም። እነኝህን ለአብነት አነሳሁ እንጂ ኢትዮጵያ ሀገረ መንግሥቷን በጸና መሠረት ላይ ለማስቀመጥ እጅግ በርካታ የዓለም ተሞክሮዎችን ከጥንት ጀምሮ እስከዛሬ ድረስ እየወሰደች ትገኛለች።
ኢትዮጵያ የጸና አገረ መንግሥት ለመመሥረት አጋዥ የሆኑ የተለያዩ ተሞክሮዎችን ከተለያዩ አጋራት መውሰዷን የታሪክ ድርሳናት ያመለክታሉ። ይሁንና እስከዛሬ ኢትዮጵያ ከሌሎች ሀገራት መውሰድ ያልቻለችው አንድ ጥሩ ልምድ አለ። ይህም መጥፎ አጋጣሚን ለመልካም የመጠቀም በጎ ልምድ ነው። ለአብነት ዛሬ በዚህ ጽሑፍ የምንዳስሰው በቅርብ ያሳለፍነውን ጦርነት ለመልካም አጋጣሚ መጠቀም ያለመቻላችንን ሁነት ነው።
በርካታ ሀገራት የመከራ ጊዜያቸውን አይተውና መርምረው ወደ መልካም አጋጣሚ ለመቀየር ይሞክራሉ። አድርገውም ያሳዩ ጥቂት አይደሉም። ጦርነት አውዳሚ የተሳሳተ ትርክትን ለተከታይ ትውልድ የሚያወርስ እንደሆነ ማንም ይረዳዋል። ይህንን ማወቅ ብቻ ግን እንደማያሻግር ይታመናል። ምክንያቱም በወቅቱ የነበሩት መጥፎ አጋጣሚዎች መታረም አለባቸው። ወደ ጥሩ አጋጣሚ መቀየርም ይገባቸዋል። ነገር ግን እንደ ሀገር እስከአሁን ድረስ የነበረው ጦርነትን ስላሸነፍን ብቻ በጦርነቱ በተገኘው ድል እየፎከሩ እና እየሸለለ መኖር ነው።
አጉል በጀግነንት መኮፈስ ደግሞ ምን ላይ እንደሚያደርሰን ከቀደመው ታሪካችን መማር እንችላለን። ከቅርቡ እንኳን ብንጀምር ኃይለ ሥላሴን ጣሊያን ሳይጥላቸው ደርግ ነው ያስወገዳቸው፤ ደርግን ደግሞ ሌሎች ሀገራት ሳይፈትኑት ኢሕአዴግ አሸንፎት ዓመታትን ገዛ። አሁን ደግሞ ኢሕአዴግ ወድቆ ብልጽግና ቦታውን ተረከበ። ይህም ሆኖ ሰላም የሚባል ነገር ሳይታይ ዓመታት ተቆጥረዋል።
ጦርነቱ መልካም አጋጣሚዎችን ሳይሆን መከራን ብቻ ይዞ ተጉዟል። ታዲያ በዚህ መልኩ እስከመጨረሻ እንቀጥል ወይ የሚለው ሊያሳስበን ይገባል። ለዚህም ሌሎች ሀገራት የጦርነት መጥፎ ገጽታን እንዴት ወደ መልካም ቀየሩት የሚለውን ማየትና ለእኛ መጠቀም ያስፈልገናል። ለምሳሌ፡- አሜሪካን ብናነሳ ለዚህ የበቃችው ዝም ብላ አይደለም። ጸረ ቅኝ ገዥ ትግል አድርጋ ከፈተናው በኋላ የተጋረጠባትን የእርስ በእርስ ጦርነት በማስቆም ነው። ዕልቂት እና ኪሳራዋን አውቃም ወደፊት ያለው ይብሳል በሚል ኪሳራዋን ሊተካ በሚችል መልኩ መንቀሳቀስ ላይ አተኮረች። መልካም አጋጣሚዎችን ብቻ አሰፋችና ተገበረች። በዚህም አሁን ኃያል ነሽ እንድንላት አደረገች።
ዛሬ ላይ በዓለማችን በኢኮኖሚያዊ እድገቷ በግንባር ቀደምትነት የምትጠቀሰው ቻይናንም ብናነሳ ብዙ የመከራ ጊዜያቶቿን መጥቀስ እንችላለን። አንዱ በ1920 መጀመሪያ የዙ ሥርወ መንግሥት ከጣሉ በኋላ የነበረው የከፋ የእርስ በእርስ ጦርነት ነው። ይህም በኬምቲ እና ኮሚኒስት ፓርቲ መካከል የሆነው ነው።
በዚህ ጦርነት ውስጥ እንደኛ ሀገር ሁሉ የውጭ ኃይሎች እጅ እጅጉን አደገኛ ነበር። ነገር ግን ያሳለፉትን የእርስ በእርስ ጦርነት ጉዳት በደንብ ለክተውታልና ዳግመኛ እንዳይደግሱት ተስማሙበት። ይህ ሁኔታ መምህራቸው መሆን እንዳለበት አመኑበት። ስለዚህም መልካም አጋጣሚ አድርገውት የዛሬዋን ቻይና ገነቡ።
ጀርመንም እንዲሁ ይህ ታሪክ ያላት ናት። በአንደኛው እና በሁለተኛው የዓለም ጦርነት የደረሰባት ሰቆቃ በቃላት ለመግለጽ የሚያስችግር ነው። ነገር ግን ከገቡበት ችግር ለመውጣት የገቡበትን ችግር እንደ መልካም አጋጣሚ አይተውታል። የሆነውን ነገር ዳግመኛ ሊያዩትም አልፈለጉም። ለዚህ ደግሞ ምን መልካም ነገሮች ነበሩን በሚል ተነስተው ስህተታቸውን አርመው የዛሬዪቱን ጀርመን አሳይተዋል። የወደፊቷ ጀርመን ምን ትሆናለች የሚለውን ጭምር እየሠሩበት ነው። እናም እነዚህ አገራት ጦርነት ወደፊት መራመድን ብቻ ሳይሆን ያለን ጭምር እንደሚቀማ አውቀዋል፤ ከዚያም አልፈው እውቀታቸውን በመልካም አጋጣሚ ተርጉመውታል። እኛስ ከተባለ መልሱን ሁላችንም እናውቀዋለን።
እኛ ግን ከመጥፎው አጋጣሚ ወደ ጥሩ አጋጣሚ መቀየር ከተሳነን ሰነባብተናል። ብቃት እያላት፣ ከሌሎችም በርካታ ልምዶችን መውሰድ የምትችልና እስካሁንም የወሰደች ሃገር ሆና ሳለ ለምን እንዲህ ዓይነቱን ምርጥና ሀገርን የሚያሻግር ተሞክሮ መውሰድ እንደተሳናት ግራ ያጋባል። በዚህ ረገድ ላለው ችግር አንደኛው ምክንያት ግን ስግብግብነትና የማያበራው የስልጣን ሽሚያ እንደሆነ ይታመናል።
ያም ሆኖ አንዳንድ በጎ ጅምሮች አሉ። ለአብነት የውጪ ኃይሎች እኛን ለመብላት ባሰፈሰፉበት ወቅት ሀገርን የሚያስከብር ተግባር ተከናውኗል። ይህም የእርስ በእርስ ጦርነቱን እንዲያበቃ ያደረገው ስምምነት እንዲፈጠር አስችሏል። ራስን ማስማማት ከተቻለ ጠላት በምንም መልኩ መግባት እንደማይችልም አመላክቷል። ከዚያ ባሻገርም የውጪ ኃይሎች እኛን ወደማዘዙ ሊያቀርባቸው የሚችለው ድህነታችን ሲሆን፤ እርሱንም ከምድረ ገጽ ለማጥፋት በርካታ ተግባራት እየተከናወኑ ናቸው። ለዚህም በብዙ ለውጥ ውስጥ ያለው የስንዴ ምርት ጉዳይ ጥሩ ማሳያ ነው። አሁን እንደበፊቱ ልስጣችሁ ሳይሆን እንስጣችሁ ልንል የምንችልበት ሁኔታ ላይ ደርሰናል።
ሌላው ራስን በምግብ ለመቻል የጀመርነው የሌማት ፕሮጀክት ሲሆን፤ ገበሬው ተርፎት ፤ ነጋዴው ሞቆት፤ ቤተሰቡ ከጓሮው ቆርጦት ሁሉም ደስታና ፌሽታ የሚያደርግበት ጊዜ ላይ ያቆመናል። በዚህ ላይ በጦርነቱ ያየነውን መከራ መልካም አጋጣሚን ለመፍጠር እንደመነሻ ከተጠቀምንበት፣ መንግስትም የጀመረውን መልካም ጅማሮ አጠናክሮ ካስቀጠለ፣ ሕዝቡም መጥፎውን ሳይሆን መልካሙን እየመረጠ ወደፊት መጓዝ ከቻለ ሰላም የሰፈነባትና የዕድገትና ብልጽግና ተስፋ የሚታይባት የተሻለች ኢትዮጵያን የምንመለከትበት ጊዜ ሩቅ አይሆንም።
ክብረ ነገሥት
አዲስ ዘመን ታህሳስ 3/2015