ኢትዮጵያ የጥበብ ባህር ብቻ ሳትሆን የአያሌ ዘመን ተሻጋሪ የጥበብ ፈርጦችም መገኛ ናት። በተለያዩ ዘመናት በበርካታ የጥበብ ዘርፎች አለምን ያስደነቁ ታላላቅ የጥበብ ቀንዲሎች ከኢትዮጵያ ማህጸን ወጥተዋል። ከነዚህ ጥበበኞች ደግሞ አንዳንዶቹ በአለም እጅግ የተከበሩና የተፈሩ ከመሆናቸው ባሻገር ስማቸውን ቀለል አድርጎ እንኳን ለመጥራት አይቻልም። ለዚህ አንዱና ዋነኛው ቀለምን በብሩሻቸው ጠቅሰው ሸራ ላይ ብዙ ተአምራትን ለአለም አኑረው ያለፉትና በስእል ጥበባቸው ገናና ስም ያተረፉት እጅግ የተከበሩ የአለም ሎሬት ሜትር አርቲስት አፈወርቅ ተክሌ በጉልህ ይጠቀሳሉ። እኛም በዛሬው የዝነኞች ገጽ አምዳችን ስለእኚህ በአለም ገናና ስም ያተረፉ የጥበብ ሰው በተለያዩ ጊዜዎች የተጻፉ መዛግብትንና ድረ ገፆችን አገላብጠን የሚከተለውን ጽሁፍ በማዘጋጀት ለንባብ አቅርበናል።
እጅግ የተከበሩ የዓለም ሎሬት ሜትር አርቲስት አፈወርቅ ተክሌ በሰሜን ሸዋ በምትገኘው አንኮበር ጥቅምት 13 ቀን 1925 ዓ.ም ነው የተወለዱት። አባታቸው አቶ ተክሌ ማሞ እናታቸው ደግሞ ወይዘሮ ፈለቀች የማታወርቅ ይባላሉ።
ገና በጨቅላ ዕድሜያቸው ፋሺስት ጣልያን ኢትዮጵያን በግፍ ሲወራት ተመልክተው በቁጭት ነው ያደጉት። የልጅነት ትዝታቸውም ይሄው የግፍ ወረራ እና ጦርነት የሚያስከትለው የሰው፣ የንብረት እና የባህል ጥፋት ነበር። የጠላት የግፍ ወረራ እና እልቂት ያስከተለውን የሰው፣ የንብረት እና የባህል ጥፋት ገና በህጻንነት ዕድሜያቸው የተመለከቱት ሜትር አርቲስት አፈወርቅ ከነጻነት በኋላ ሃገራቸውን እንደገና እንዴት መገንባት እንደሚቻል ሲያወጡ እና ሲያወርዱ ከቆዩ በኋላ ዋናው እና ቀዳሚው ጉዳይ እውቀት መሸመት መሆኑን የተረዱት ገና በልጅነት እድሜያቸው እንደነበረ በብዙ መዛግብት ተጽፎ ይገኛል። ለዚህም ለሀገር ግንባታ አስፈላጊውን እውቀት መሸመት የፈለጉት በማዕድን ምሕንድስና ዘርፍ ነበር። ወላጆቻቸውና ዘመድ አዝማዶች ግን የኪነ ጥበብ ተሰጧቸውን በቤታቸውና በከተማው ዙሪያ በሚስሏቸው ስዕሎች ተገንዝበውት ነበር።
የመጀመሪያና መካከለኛ ትምህርታቸውን የት እና መቼ እንዳጠናቀቁ የተጻፈ መረጃ ባይገኝም፤ ገና በአሥራ አምስት ዓመታቸው በ1940 ዓ/ም ለከፍተኛ ትምህርት ተመርጠው የምሕንድስና ትምህርት ለመከታተል ወደ እንግሊዝ አገር መላካቸው ተዘግቧል ፡፡
ለትምህርት የተመረጡት ተማሪዎች ንጉሠ ነገሥት ቀዳማዊ ኃይለ ሥላሴን ሲሰናበቱ የተሰጣቸውን ምክር ሁሌም እንደሚያስታውሱት ሜትር አርቲስት አፈወርቅ ተክሌ ሲናገሩ ‹‹ንጉሠ ነገሥቱ ተግታችሁ አጥኑና ተማሩ፣ ጠንክራችሁ ለመስራትና ሀገራችሁ ኢትዮጵያን የምትገነቡበትን ዕውቀት ይዛችሁ ተመለሱ። ‹‹ ከናንተ የሚፈለገው አዕምሯችሁን ዝግጁ አድርጋችሁ ኢትዮጵያን ለመገንባት የሚያስችል እውቀትንና ጥበብን ሸምታችሁ እንድትመለሱ ነው እንጂ አውሮፓ ውስጥ ስላሉት ረዣዥም ፎቅ ቤቶች ወይም ስለመንገዶቻቸው ስፋት በአድናቆት እንድትነግሩን አይደለም›› ብለዋቸው እንደነበር ሁሌም ያስታውሱ ነበር፡፡
እጅግ የተከበሩ የዓለም ሎሬት ሜትር አርቲስት አፈወርቅ ተክሌ በእንግሊዝ አገር በትምህርት ላይ ሳሉ የአዳሪ ትምህርት ቤትን ኑሮ በማስታወስ የባእድ ሃገር እንግዳ በዓላት እና የአየር ሁኔታው መለዋወጥ እንዳስቸገራቸው በተለያዩ ጊዜዎች ተናግረዋል።
በትምህርት አቀባበላቸውም በሒሣብ፣በኬሚስትሪ እና በታሪክ ትምህርቶች ጥሩ ውጤት በማምጣት ከመምህሮቻቸው ተደጋጋሚ አድናቆት ቢያገኙም የተፈጥሮ መክሊታቸው ኪነ ጥበብ እንደሆነ መምህሮቻቸው ለመገንዘብ ብዙ ጊዜም አልወሰደባቸውም።
በመምህራቸው አበረታችነት በዚህ ስጦታቸው ላይ የበለጠ ለማተኮር ወስነው በለንደን ማእከላዊ የኪነ ጥበብ ትምሕርት ቤት የገቡት አፈወርቅ ከዚህ ትምህርት ቤት ትምህርታቸውን በጥሩ ውጤት በማጠናቀቅ ለከፍተኛ ጥናት በስመ ጥሩው የለንደን ዩኒቨርሲቲ የስሌድ ኪነ ጥበብ ማዕከል የመጀመሪያው አፍሪካዊ ተማሪ ሆነዋል ፡፡
በዚህ ትምህርት ቤት ቆይታቸውም በቀለም ቅብ፣ በቅርጻ ቅርጽ እና በኪነ ህንጻ ጥናቶች ላይ በመስራት ተመርቀዋል። ትምህርታቸውን አጠናቀው ወደ ኢትዮጵያ እንደተመለሱ በተለያዩ ግዛቶች በመዘዋወር በአንዳንድ ቦታም እስከ ሦስት ወራት በመቀመጥ የኢትዮጵያን ታሪክ እና የብሔር ብሔረሰቦቿን ባህልና ወግ ሲያጠኑ ቆይተዋል።
በ1946 ዓ.ም ገና የ22 ዓመት ወጣት እያሉ የተለያዩ የስነ ጥበብ ሥራቸውን የሚያሳይ የመጀመሪያውን ኤግዚቢሽን በአዲስ አበባ ማዘጋጃ ቤት አቅርበዋል። ከትርዒቱ ባገኙት ገቢ በድጋሚ ወደ አውሮፓ በመሄድ ለሁለት ዓመት በጣሊያን፣ በፈረንሳይ፣ በስፔን፣ በፖርቱጋል፣ በእንግሊዝና ግሪክ ጥልቅ የኪነ ጥበብ ጥናት አከናውነዋል።
በጦርነትና በሌሎች ምክንያቶች ተዘርፈው በነዚህ ሃገራት የሚገኙትን የኢትዮጵያ ጥንታዊ የሃይማኖትና የታሪክ የብራና መጻሕፍትን በጥልቅ አጥንተውና የመስታወት ላይ ስዕል ( የሞዛይክ አሠራር ጥበብን ) ቀስመው ወደ አገራቸው ተመልሰዋል።
እጅግ የተከበሩ የዓለም ሎሬት ሜትር አርቲስት አፈወርቅ ተክሌ ወደ ሃገራቸው እንደተመለሱ ንጉሠ ነገሥቱ አዲስ አበባ በሚገኘው የመናገሻ ቅዱስ ጊዮርጊስ ቤተ ክርስቲያን ግድግዳ፣ ጣሪያና መስኮቶችን በሃይማኖታዊ ምስሎች በቀለምና በመስታወት ስዕሎች እንዲያስውቡት ባዘዟቸው መሰረት የዳግም ምጽአት ፍርድ፣ የድንግል ማርያም ንግስና ፣ ኪዳነ ምሕረት፣ እና የቀዳማዊ ኃይለ ሥላሴን የዘውድ ስርዓት የሚያሳዩ ሥራዎችን ሰርተዋል። በሐረር ከተማ የሚገኘውን የልዑል ራስ መኮንን ሀውልት የቀረጹትም እሳቸው ናቸው። ከዚህም በኋላ የአርቲስቱ የስዕል እና ሌላ የኪን ሥራዎቻቸው ወዲያው በ’ቴምብሮች’፣ በሀገር ውስጥም ሆነ በውጭ ሀገር የኪነ ጥበብ ትርዒት ላይ እጅግ በጣም እየታወቁና እየገነኑ መጡ።
እጅግ የተከበሩ የዓለም ሎሬት ሜትር አርቲስት አፈወርቅ ተክሌ እንደ ኢትዮጵያዊ ምሁርና የጥበብ ሰው በጥንታዊት ኢትዮጵያ ታሪክ፣ ነጻነት፣ ባሕልና ሥልጣኔ እንዲሁም በግዕዝ ቋንቋ፣ በኦርቶዶክስ ተዋህዶ ሃይማኖታዊ አስተምህሮቶች፣ ትውፊትን ጠንቅቀው የሚያውቁ የታሪክ ሰውና ቅርስ ጠባቂ ሰው እንደነበሩ በቅርብ የሚያውቋቸው ሁሉ ይመሰክሩላቸዋል።
ሜትር አርቲስት አፈወርቅ ተክሌ በሀገራቸውና በአውሮፓ ለረጅም ዓመታት የሥነ ጥበብ ሙያን የተማሩ ከመሆናቸው ባሻገር በሀገራቸውና በዓለም አቀፍ ደረጃም በተለያዩት ጊዜያት በርካታ የስዕል አውደ ርዕዮችን በማቅረብ ትልቅ አድናቆትንና ክብርን ለመጎናጸፍ ችለዋል። በዚህ ልዩ ተሰጥኦአቸውና ችሎታቸው የተነሳም በተለያዩ የዓለማችን ክፍሎች ከሚገኙ ታላላቅ የጥብብ ሰዎች ጋር ለመገናኘትና ስራዎቻቸውንም ለሌሎች ለማሳወቅ ችለዋል። በስነ ጥበብ ስራዎቻቸውም ለዓለማችን ሰላምን፣ ለሰው ልጆች አንድነትና እኩልነትን በመስበካቸውም በዓለማችን ከሚገኙ ታላላቅ መሪዎችና ፖለቲከኞች፣ ታዋቂ ሰዎችና የሃይማኖት አባቶች ጋር ለመገናኘት የቻሉ ዓለማቀፋዊ ዝናን እና ክብርን ያተረፉ የሥነ ጥበብ ሰው ሆነዋል።
በዚህም ከቀዳማዊ ኃይለ ሥላሴ የስነ ጥበብ ከፍተኛ ሽልማት ጀምሮ በሀገር ውስጥና በዓለም አቀፍ ደረጃ ከ90 በላይ የሚሆኑ ሜዳሊዎች፣ ሽልማቶችንና ዲኮራሲያኖችን እንዲሁም የክብር ዜግነት ያገኙ ሰው ሲሆኑ፤ ለአብነትም በሐምሌ ወር 1997 ዓ.ም በአየርላንድ ዋና ከተማ በዱብሊን በተደረገው በ30ኛው የኪነ ጥበብ የባሕልና የሳይንሶች ዓለማአቀፋዊ በዓል ላይ (The International Biographical Center of Cambridge) በስነ ሙያ ጥበብ የመጨረሻ ሽልማት የሆነውን (Davinci Diamond) የደቬንቺ አልማዝ የተባለውን ሽልማት ሰጥቷቸዋል። ይህንን ሽልማት በማግኘትም ብቸኛው አፍሪካዊ የሥነ ጥበብ ሰው ለመሆን በቅተዋል። በዚሁ በዓል ላይም “The United Cultural Convention of the United States of America” ለእኚሁ ታላቅ ሰው አለም አቀፍ የሰላም ሽልማት (International Peace Prize) ልዩ ሽልማትና፣ የክብር የሰላም አምባሳደርነትን ሰጥቷቸዋል። ይህም ሽልማትና የክብር ዲፕሎማ በዘር፣ በሃይማኖት፣ በፖለቲካ፣ በባሕል በተከፋፈለች ዓለማችን ለዓለም ሰላምንና ፍትህን፣ ለሰው ልጆች እኩልነትንና አንድነትን ለማስፈን ለሚጥሩ ሰዎች የሚሰጥ ዓለምአቀፋዊ ሽልማት እንደሆነ የድርጅቱ ኃላፊዎች በሽልማቱ ወቅት ገልጸው ነበር። ሜትር አርቲስት አፈወርቅ ተክሌም በሀገር ውስጥም ሆነ በውጭ ካገኟቸው በርካታ ሽልማቶች መካከል እነዚህ ለሁለቱ ዓለም አቀፍ ሽልማቶች ልዩ ክብርና አድናቆት እንደላቸው ገልጸው ነበር። እጅግ የተከበሩ የዓለም ሎሬት ሜትር አርቲስት አፈወርቅ ተክሌ የነገሥታት መናገሻና መዲና በነበረችው አንኮበር ተወልደው እንዴት ለእዚህ ዓይነት ዓለምአቀፋዊ እውቅና እና ዝና ሊደርሱ እንደቻሉ በተጠየቁበት በአንድ ወቅት ‹‹አገራችን በብዙ ነገሮች ቀደምት በመሆኗ እንደምትታውቅና እንደምትደነቅ ሁሉ እኔም በዚህ የሙያ መስክ የአገሬን ስም እንዳስጠራ የኢትዮጵያ አምላክ ፈቃድ የሆነ ይመስለኛል።›› በማለት ከፍተኛ ትህትና እና የሀገር ፍቅር ስሜት የተሞላበት መልስ ሰጥተዋል።
የእኚህ ታላቅ የጥበብ ሰው አጭር የሕይወት ታሪክ ከልጅነት ጀምሮ ጓደኛቸው በሆኑት በፕሮፌሰር ሪቻርድ ፓንክረስት በአማርኛና በእንግሊዘኛ ‹‹አፈወርቅ ተክሌ አጭር ሕይወት ታሪክና ምርጥ ስዕሎቹ›› በሚል ርዕስ ባቀረቡት መጽሐፍ መግቢያ ላይ አስተያየታቸውን ያሰፈሩት በደርግ ዘመነ መንግሥት የባሕልና የስፖርት ጉዳይ ሚ/ር የነበሩት ሻለቃ ግርማ ‹‹የሜትር አርቲስት አፈወርቅ ተክሌ ምርጥ የሥዕል ሥራዎች በሺህ ዓመታት አንዴ ብቅ እንደሚሉ የፈጠራ ሰዎች ውድና ብርቅ የሥነ ጥበብ ውጤቶች ናቸው። አብዛኛዎቹ ሥዕሎቻቸው ጠንካራ የሀገር ፍቅር ስሜትና የተፈጥሮ ውበትን ሕያው በሆኑት ታዋቂ ሥራዎቻቸው አንጸባርቀዋል፤ በጥንታዊነቷና በታሪካዊነቷ በርካታ የምርምርና የጥናት ሰዎችን ለምትስበው እናት ኢትዮጵያ የሜትር አርቲስት አፈወርቅ ተክሌ ምርጥ የሥነ ጥበበብ ሥራዎች ተጨማሪ ጌጥና ኩራት ናቸው።›› ሲሉ አስተያየታቸውን ሰጥተው ነበር።
አፍሪካውያን ከቅኝ ግዛት ቀንበር ስር ለመውጣት በሚያደርጉት የሞት ሽረት ትግል የጥቁር ሕዝቦች ነጻነትና አይበገሬነት ልዩ መገለጫ በሆነችው ኢትዮጵያ የአፍሪካ አንድነት ድርጅት ሲቋቋም የአፍሪካውያንን ታላቅ ስልጣኔ፣ አኩሪ ባሕል፣ ታሪክና ነጻነት በበሩሻቸው ቀለም በድርጅቱ መሰብሰቢያ አዳራሽ እውን ያደረጉት እኚሁ ታላቅ የጥበብ ሰው ነበሩ። በድርቅ፣ በጦርነትና በረሃብ የተጎሳቆለችውን እናት ሀገራቸውን ኢትዮጵያን በብሩሻቸው የገለጹበት ‹‹ዋይ ዋይ የት ትሄዳለህ›› የሚለው የጥበብ ስራቸውም በሀገራችን በወቅቱ በደረሰው አስከፊ ድርቅና ረሃብ የደረሰባቸውን የልብ ስብራትና ጥልቅ ሐዘን የገለጹበት ስራቸው ነው።
ከታዋቂ ሥራዎቻቸው መካከል በከፊል
• በአዲስ አበባ በቀድሞው የአፍሪቃ አንድነት ድርጅት አዳራሽ መግቢያ የሚታየው በመቶ ሃምሳ ካሬ ሜትር ላይ የተሳለው ትልቅ የመስታወት ስዕል
• አዲስ አበባ በመናገሻ ቅዱስ ጊዮርጊስ ቤተ ክርስቲያን የውስጥ ስዕሎች፣ ሞዛይኮች
• አዲስ አበባ በቅዱስ ጳውሎስ ሆስፒታል የሚገኘውን የመጀመሪያውን የ’ዳግም ምጽዓት ፍርድ ስዕል
• በሐረር የልዑል ራስ መኮንን ሐውልት
• በአዲግራት የ’ዳግም ምጽዓት ፍርድ ስዕል
• በለንደን ‘ታወር ኦፍ ለንደን’ የቅዱስ ጊዮርጊስ ጸሎት ቤት ከብር እና ከእንጨት የተሠራ የመንበር መስቀል
• በሩሲያ፣ አሜሪካ እና በሴኔጋል ኤግዚቢሽን ላይ የቀረበው ‘የመስቀል አበባ’ ስዕል
• “እናት ኢትዮጵያ’
• የአቡነ ተክለ ሃይማኖት ምስል እና
• ‘ደመራ’ ተጠቃሾች ናቸው ፡፡
እጅግ የተከበሩ የዓለም ሎሬት ሜትር አርቲስት አፈወርቅ ተክሌ ማክሰኞ ሚያዝያ 2 ቀን 2004 ዓ/ም በተወለዱ በ79 ዓመታቸው ከዚህ አለም በሞት ተለይተው ከፍተኛ የመንግስት ባለስልጣናት ፣ወዳጅ ዘመዶቻቸውና አድናቂዎቻቸው በተገኙበት አዲስ አበባ በሚገኘው መንበረ ጸባኦት ቅድስት ስላሴ ካቴድራል ቀብራቸው ተፈጽሟል ፡፡
ቦጋለ አበበ
አዲስ ዘመን ታኅሣሥ 2 /2015