የተወለዱት በደቡብ ጎንደር ነው። አባታቸው ሊቀ ካህናት መኮንን ታዬ በኃይለሳሴ ዘመነ መንግሥት በጎንደር ጠቅላይ ግዛት በከፍተኛ ኃላፊነት ደረጃ ይሰሩ ነበር። እስከ 12ኛ ክፍል ያለውን ትምህርታቸውን በደቡብ ጎንደር መካነ እየሱስ ሁለተኛ ደረጃ ትምህርት ቤት ነው የተከታተሉት።
በ1980 ዓ.ም የ12ኛ ክፍል ትምህርታቸውን ሲያጠናቅቁ በሀገሪቱ ጦርነት ስለነበርና አማራጭ ስላልነበራቸው ትምህርቱን ገታ አደርገው ፊታቸውን ወደ ንግድ አዞሩ። ገና በ19 ዓመታቸው የንግዱን ዓለም መቀላቀል ሲያስቡ ለመነሻ የሚሆን ገንዘብ የሚሰጣቸው አላጡም። ከቅርብ ቤተሰባቸው 500 ብር አገኙ፤ ንግዱንም አሀዱ ብለው ጀመሩት።
እኚህ የዛሬው የስኬት አምድ እንግዳችን አቶ መሠረት መኮንን ይባላሉ። ባገኙት ገንዘብ ጥራጥሬ ወደ ሱዳን እየወሰዱ መሸጡን ተያያዙት። ከሱዳን ደግሞ ጨው በማምጣት ጎንደርና ባህርዳር አካባቢ መሸጥ ጀመሩ። በዚህ ንግድ ዓመታትን ቆዩ፤ ጥሪትም አጠራቀሙ።
ጦርነቱም ረገበ። እርሳቸውም በወርሃ ነሃሴ 1983 ዓ.ም አዲስ አበባ ላይ ከተሙ። ከዚያም ወደ ቶጎ ጫሌ፣ ኬኒያ፣ ሞያሌ፣ ጅቡቲ በመመላለስ የተለያዩ ሸቀጣ ሸቀጦችንና ዕቃዎችን መነገዱን ቀጠሉ። አቅማቸው ይበልጥ እየደረጀ ሲመጣ በ1992 ዓ.ም ኃላፊነቱ የተወሰነ የግል ማህበር የሚል ኩባንያ መሰረቱ።
በዚህ የንግድ ዓለም ውስጥ ነገሮች አልጋ ባልጋ እንዳልነበሩም ይናገራሉ። ብዙ ፈተናዎችን አልፈዋል። በርሃ ለበረሃ ተንከራተዋል፤በዚህም ሙቀቱ ፈትኗቸዋል። በማያውቁት አካባቢ ሲሄዱ ቋንቋ ፈትኗቸዋል። አልፎ አልፎም የንግድ መንገራገጮች ገጥሟቸዋል።
ቀደም ሲል በንግድ ዓለም ከተዋወቁዋቸው ሰዎች ጋር መመካከርና አዳዲስ ሐሳቦችንም ማፍለቅ ጀመሩ። 1992 ዓ.ም የኢትዮጵያን ባለሃብቶች ምርታቸውንና አገልግሎታቸውን እንዲያስተዋውቁ የሚያስችል ትልቅ አለም አቀፍ ኤግዚቢሽን በሳውዲ አረቢያ አዘጋጁ። ሜድሮክ ኢትዮጵያ፣ ኢስት አፍሪካ ሆልዲንግ፣ አምቦ ውሃ፣ አያት መኖሪያ ቤቶች፣ የኢትዮጵያ ማዕድንና ኮርፖሬሽንና ሌሎችም በኤግዚብሽኑ ተሳታፊ እንደነበሩ አቶ መሰረት ይገልጻሉ። እነዚህ ድርጅቶችም በዚያ ኢግዚቢሽን ብዙ ተጠቅመዋል ብለው እንደሚያስቡ የሚናገሩት አቶ መሰረት፣ እሳቸውም በዚያ ሥራቸው በሳውድ አረቢያ ልዩ ተሸላሚ ለመሆን በቅተዋል።
አቶ መሰረት በመቀጠልም ከሌሎች ባለሃብቶች ጋር በመቀናጀት ጥራጥሬ፣ ቅባት እህሎች፣ የሥጋ ውጤቶችና ቅመማ ቅመም ለውጭ ገበያ ማቅረብ ጀመሩ። ከአስመጪነትና ላኪነት በተጨማሪም በተለያዩ የኢንቨስትመንት መስኮች መሰማራቱን ተያያዙት።
በማኑፋክቸሪንግ ኢንዱስትሪ፣ በሆቴል እና ቱሪዝም ዘርፍ፣ በሪል ስቴት ፕሮጀክት፣ በመኪና ኪራይ፣ በህንፃ ሽያጭና ኪራይ፣ በአስመጭነትና ላኪነት የተሰማሩ አገር በቀል ድርጅት ባለቤት ለመሆን በቅተዋል።
በአዲስ አበባ በ300 ሚሊዮን ብር ያስገነቡት ቤዝ ኢትዮጵያ ኢንተርናሽናል ሆቴል በአሁኑ ወቅት አግልግሎት እየሰጠ ይገኛል። በኦሮሚያ ክልል ሰበታ ከተማ በ130 ሚሊዮን ብር ካፒታል የታይልስ ፋብሪካ ያቋቋሙ ሲሆን 230 ዜጎች የሥራ ዕድል ማግኘት ችለዋል። 15 የትራንስፖርት ተሽከርካሪዎች፣ በአዲስ አበባ በኩባንያው ስም የተመዘገቡ ሦስት ግዙፍ ህንፃዎች ባለቤትም ሆነዋል።
በ500 ብር የጀመሩት ንግድ አጠቃላይ የፕሮጀክት ካፒታል በአሁኑ ወቅት 10ነጥብ5 ቢሊዮን ብር መድረሱን የሚናገሩት አቶ መሰረት፣ ሁሉም ፕሮጀክቶቻቸው በስራ ላይ መሆናቸውንም ነው የሚገልጹት። በእነዚህ የንግድ እና የኢንቨስትመንት ተቋሞቻቸው ለበርካታ ኢትዮጵያውያን የሥራ ዕድል መፍጠር ችለዋል።
አቶ መሠረት አገራቸውን እና ዜጎቿን በእጅጉ እንደሚወዱ ይገልጻሉ። ይህንንም መንግሥት ለሚጠይቃቸው የልማትና የድጋፍ ጥያቄዎች ሁሉ ቀድመው ምላሽ በመስጠት እያረጋገጡ መሆናቸውን ነው የሚናገሩት። በዚህ በኩል ላከናወኗቸው ተግባሮች በርካታ የምስክር ወረቀቶች ከአዲስ አበባ ከተማ አስተዳዳር ከንቲባ፣ ከአዲስ አበባ ፖሊስ ኮሚሽንና ከሌሎች የመንግስት የሥራ ኃላፊዎች እንደተበረከቱላቸውም ይጠቅሳሉ።
ባለሀብቱ አሁንም ሌላ ትልቅ ራእይ ሰንቀው መስራት ጀምረዋል። ለአዲስ አበባ ከተማ አቅሜ የፈቀደውን ይዤ መጥቻለሁ ሲሉ ይገልጻሉ። በአሁኑ ወቅት በሰፊው የገቡበት የሪል ስቴት ልማት ለዜጎች ከፍተኛ የሥራ ዕድል የሚፈጥር ከመሆኑም በላይ ትልቅ የውጭ ምንዛሬ ገቢን የሚያስገኝ ነው። ዳያስፖራዎችንና ትውልደ ኢትዮጵውያንን ከባንክ ጋር በማስተሳሰር የቤት ባለቤት ለማድረግ አቅደዋል።
ለዚህም ሥራ በአቃቂ ቃሊቲ ክፍለ ከተማ በ8ነጥብ5 ቢሊዮን ብር ለሚገነባው ዘመናዊ መንደር በአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ውሳኔ መሰረት በሊዝ መሬትና ካርታ ተረክበው ሥራ ጀምረዋል። ግንባታው 10 ባለ 12 ወለል ህንጻዎች፣ 90 ባለ ሁለት ወለል ቪላዎችና ዘመናዊ ቤቶች፣ ሲኒማ እና ሞል ያካተተ ነው። ይህ ግንባታ ለ2ሺ300 ዜጎች የሥራ ዕድል ይፈጥራል።
ጠቅላይ ሚኒስትር ዶክተር ዓብይ አህመድ በተደጋጋሚ ስለሀገሪቱ ዕድገት፣ ቱሪዝምና ምጣኔ ሃብት ዕድገት ይመክራሉ፤ በተግባርም ያሳያሉ ሲሉ የሚጠቅሱት ባለሀብቱ፣ እንጦጦ ፓርክንና ሌሎች ፕሮጀክቶችን ማስገንባታቸውን ጎርጎራና የመሳሰሉትን ደግሞ እያሰሩ መሆናቸውን ይጠቅሳሉ።
ባለሃብቶች ከዚህ በበለጠ መሥራት አለብን ሲሉም ነው ያስገነዘቡት። ጠቅላይ ሚኒስትሩ በግብርና፣ በቱሪዝም፣ ቴክኖሎጂና ሌሎች መስኮች እያደረጉት ያለው ጥረት በጣም የሚደነቅ ነው። የእርሳቸውን ራዕይና ተልዕኮ ከጎናቸው ሆነን ማሳካት አለብን ሲሉ ገልጸው፣ይህ ሲሆን ኢትዮጵያን ወደ ብልጽግና ማማ መውሰድ በጣም ቀላል ይሆናል ይላሉ።
እኛ እንደ አንድ ድርጅት የኢትዮጵያን ቱሪዝም ለማሳደግ በስፋት እየሰራን ነው ይላሉ- አቶ መሰረት። አሜሪካ፣ ካናዳ፣ ሳውድ አረቢያ፣ አውስትራሊያ፣ ዱባይ እና ሌሎች ሀገራትም የቢዝነስ አጋር እየፈጠርን ነው ሲሉ ይገልጻሉ።
በአዲስ አበባ ብቻ ሳይሆን በክልል ከተሞችም ከፍተኛ የቤት እጥረት መኖሩን በመጥቀስም፣ ልማቱን ወደ ክልልም ይዘን ለመግባት ወስነን ከከተማና መሰረተ ልማት ሚኒስትርና ከክልሎች ጋር ተነጋግረናል ይላሉ። በዚህም በቀጣይ በአማራ፣ ኦሮሚያ፣ ሶማሌ፣ ደቡብ፣ ድሬዳዋ ተጋጣጣሚ ቤቶችን ለመገንባት ዝግጅት እየተደረገ ነው። ለሥራቸው መቀናትም ከቱርክ ኩባንያዎች ጋር ተነጋግረዋል። ባለሀብቶች ጠቅላይ ሚኒስትሩን በትንሹም ቢሆን ማገዝ ይጠበቅብናል ሲሉም መልዕክት አስተላልፈዋል።
‹‹ኢትዮጵያ ውስጥ ለመስራት የሚያስችሉ ምቹ ሁኔታዎች አሉ፤ እኛ ግን መሥራት አልቻልንም›› የሚሉት አቶ መሰረት፣ ኢትዮጵያ ተስማሚ የአየር ንብረት፣ የማዕድን፣ የተፈጥሮና የእንስሳት ሃብት እንዳላት ጠቅሰው፣ በቱሪዝም፣ በኢንዱስትሪ፣ በኮንስትራክሽን፣ በሪል እስቴትና ሌላውም ዘርፍ ለመስራት የሚያስችል በጣም ብዙ ዕድል እንዳለ ተናግረዋል።
የፖለቲካው ውጥንቅጥ፣ የሥራ ባህል አለመጠናከር፣ የውጭ ምንዛሬ እጥረት፣ የተረጋጋ ገበያ አለመኖር ግን ፈተናዎች መሆናቸውን ነው የገለጹት። ይህ ሁሉ ተግዳሮት ብዙ መሥራት እየቻልን እንዳንሰራ እያረገን ነው ይላሉ። እነዚህን ችግሮች ለማቃለል ችግር አለ ብሎ ከማውራት ይልቅ መፍትሄ አይጠፋውም ብሎ መንቀሳቀስ ይበጃል ባይ ናቸው።
እኔ አንድ የሚሰማኝ ነገር አለ ይላሉ አቶ መሰረት፤ ሃብት የሚፈጠረው ለግልና ለሀገር ብቻ አይደለም ሲሉም ይገልጻሉ፤ በርካታ የሀገሪቱ ዜጎች ሥራ አልባ ናቸው። በዚህ ወቅት እንደ ባለሃብት የሥራ ዕድል መፍጠር አለብኝ። እኔ ያለኝን ሃብት ተጠቅሜ የሥራ ዕድል መፍጠር ግዴታዬ ነው። ሥራ የፈጠርኩለት ዜጋ ልጆቹን፣ እናቱን፣ አባቱን ወገኑን ሲረዳ ማየት ከምበላውና ከምጠጣው በላይ ያስደስተኛል ብሎ ማሰብ እንዳለበት ነው ያስገነዘቡት። ካለው ሃብት በላይ ትልቅ ተስፋ እና ደስታ መስጠት ነው። የእኔ ትልቁ ሱስ ሥራ መሥራት እና ለአቅመ ደካሞች መስጠት ነው። ያለን ማካፈል ሁሌም ያስደስታል። ምንም የማይሰሩት እናቶችና አባቶች ተስፋቸው እኛ ነን። ይህችን ሀገር ያቆዩ ሰዎች ሲጎሳቆሉ ማየት ያማል ይላሉ።
እኔ በቅርቡ የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ባቀረብልኝ ጥሪ መሰረት፤ ለአቅመ ደካሞችና ለድሃ ድሃ የከተማዋ ነዋሪዎች የሚያገለግሉ ቤቶችን ሰርቻለሁ ሲሉ ይጠቅሳሉ። በአቃቂ ቃሊቲ ከፍለ ከተማ ባለሃብቶች ኮሚቴ ሆነን 180 ቤቶች ገንብተናል። ለድሃ ድሃ አራት የዳቦ ፋብሪካዎች በ87 ሚሊዮን ብር አቋቁመናል። በአጠቃላይ 210 ሚሊዮን ብር አሰባስበን ወጪ አድርገናል።
ከሸገር ዳቦ ፋብሪካ ጋር በመዋዋል በቀን 30ሺ ዜጎች ዳቦ እንዲያገኙ ማድረግ ችለናል። የሸገር ዳቦ ሱቆችን በአቃቂ ቃሊቲ ክፍለ ከተማ በሚገኙ 13ቱም ወረዳዎች ገንብተናል። አሁንም በ90 ቀን ሰው ተኮር ፕሮጀክት ባለሃብቶችን በማስተባበር የተለያዩ ፕሮጀክቶችን እየሠራን ነው።
ድርጅታቸው ደግሞ የቱሉ ዲሚቱ ዓደባባይን በ10 ሚሊዮን ብር እጅግ ዘመናዊ በሆነ ዲዛይን እየገነባ መሆኑን ይገልጻሉ። እኔና ቤተሰቤ አሁን ያለንበትን ህይወት እግዚአብሄር ሰጥቶናል፤ ቤተሰቤ ሲደሰት ሌላው መብራት ላይ ቆሞ ሲለምን ውስጤን ይነካኛል ይላሉ።
እሳቸው ሰው ለምን ይለምናል? ሲሉ ይጠይቃሉ። ሥራ ቢኖረው፤ አቅመ ደካማ ባይሆን ወይንም ወላጅ አልባ ባይሆን አይለምንም። እነዚህን መርዳት ከደስታ በላይ ነው። እኔ ለአንድ ድሃ ስሰጥ መጀመሪያ ጥሪውን የሚያቀርበው፣ የሚያመሰግነውና ደውል የሚደውለው ለፈጣሪው ነው። ይህ ደግሞ በእምነት ዓይን ትልቅ መልዕክት አለው። መስጠት በረከት ነው፣ በራሱ ዕድል ነው፤ ፀጋ ነው። ሃብት ሰብስበን መጨረሻ ጥለነው እንሄዳለን። ለሀገር፣ ለወገን፣ ለዜጋ ሰጥቶ መሄድ መልካም ነው ሲሉ ያስገነዝባሉ።
አቶ መሠረት በብዙ ስራዎች ውስጥ ናቸው፤ እንዲያም ሆኖ አሁንም ቢሆን፣ ገና ምን ተሰርቶ ሲሉ ይጠይቃሉ። ኢትዮጵያ በሁሉም ዘርፍ ያልተነካ ሃብት እንዳላት ነው የሚናገሩት።
ከዘመናዊ አፓርታማዎች በተጨማሪ ከ5 እስከ 10 ዓመታት በሚሆን ጊዜ ውስጥ ከመንግስት ጋር በመሆን አንድ ሚሊዮን አነስተኛ እና ወጪ ቆጣቢ ቤቶችን ለመገንባት ዝግጅት እያደረጉ ነው። ለዚህ የሚያስፈልጉትን ሁሉንም ግብዓቶች ኢትዮጵያ ውስጥ ማምረት እንደሚቻል ይናገራሉ። ለዚህም ይረዳ ዘንድ ቴክኖሎጂ የማስገባት ሥራ መጀመራቸውን ይገልጻሉ።
ባለሀብቱ በአገልግሎት ዘርፍ ብዙ ሥራዎችን ያሰቡ ቢሆንም፤ በአሥር የቱሪስት መዳረሻዎች ላይ መዝናኛና የባህል ማዕከላትን መገንባት ቀዳሚው ሥራቸው ነው። ቤዝ ኢትዮጵያ ኢንተርናሽናል በአሥር የቱሪስት መዳረሻዎች አካባቢዎች እያንዳንዳቸው ከ20 ሚሊዮን ብር በላይ የሚያወጡ የቱሪስት መዝናኛና የባህል ማዕከላት የመገንባት ውጥን አለው። በተለይም ኤርታሌ፣ ሶፍ ኡመር፣ ጢስ ዓባይ፣ አክሱም፣ ላሊበላ፣ ዳሎል አፋር፣ አርባ ምንጭ፣ ኮንሶ፣ የቱሪስት መዳራሻዎች በዚህ ፕሮጀክት ታቅፈዋል።
ኢትዮጵያ በቱሪዝም ዘርፍ ከኬኒያ፣ ታንዛኒያ፣ ዑጋንዳ በብዙ እጥፍ የሚበልጥ አቅም አላት፤ የምታገኘው ገቢ ግን እነዚህ ሀገራት ከሚያገኙት አኳያ ሲታይ አምስት በመቶ አይሞላም የሚሉት አቶ መሠረት፤ በርካታ የቱሪስት መዳረሻዎች ሠላማቸው የተጠበቀ ባለመሆኑና ባለሃብቱም በዚህ ላይ ባለመስራቱም ሀገራችን ከዘርፉ አልተጠቀመችም የሚል ቁጭት አላቸው። በቀጣይ በእነዚህ የመዳረሻ ቦታዎች የመዝናኛና የባህል ማዕከላትን የሚገነቡት ይህን ታሳቢ በማድረግ ነው።
በተለያዩ አካባቢዎች የሚገነቡት እነዚህ ማዕከላት ከጥቂት ኤሌክትሮኒክስ ዕቃዎች በስተቀር ሙሉ በሙሉ አካባቢው ላይ ባሉ ባህላዊ ቁሳቁስ የሚሠሩ ናቸው። እያንዳንዳቸው ከ50 በላይ የመኝታ ክፍሎች፣ ዘመናዊና ባህላዊ ሬስቶራንቶች፣ የየክልሉን ባህል የሚያሳዩ ሙዚቃ የሚቀርቡባቸው፣ ጎብኚዎች ባህላዊ ምግብና መጠጦች የሚያገኙባቸው አዳራሾች፣ አነስተኛ ሙዚየሞች፣ የመኪና ማቆሚያ ቦታዎችና ሌሎችም ዘመናዊ አገልግሎት የሚሰጡ ናቸው። ለእነዚህ ስራም የገንዘብ አቅርቦት ከባንክ መገኘቱን አቶ መሰረት ጠቅሰው፣ የፀጥታው ችግር መፍትሄ ካገኘ ግንባታውን በቀጥታ እንደሚጀምሩም ነው የተናገሩት።
አቶ መሰረት መልዕክትም አስተላልፈዋል። ሁልጊዜም የምናገረው ኢትዮጵያ ትልቅና ሃብታም ሀገር ናት። በሁሉም ዘርፍ ተዝቆ የማያለቅ ሃብት አላት፤ ግን አልተጠቀመችበትም ይላሉ። እንድትጠቀም የምናዳርገው ደግሞ በዚህች ሀገር ጥላቻን በማስወገድ፣ በመተባበር፣ በቅንነትና በመተሳሰብ እና በመተባበር ነው ሲሉ ያስገነዝባሉ።
ፍቅር፣ አንድነትና ሠላም ካለን ኢትዮጵያ ታላቅ ሀገር ናት፤ ኢትዮጵያ ከሌሎች ሀገሮች በበለጠ ትልቅና የተለየች ናት፤ ችግሩ የእኛ የዜጎቿ እንጂ ኢትዮጵያ እንከን የለባትም ያሉት አቶ መሰረት፣ ሀገሪቱ በአጭር ጊዜ ትልቅ ለውጥ ማምጣት እንደምትችልም ነው ያስታወቁት። ማንም ባለሃብት፣ ዜጋ ሆነ ባለስልጣን ሀገሩን መስረቅ እንደሌለበት አስገንዝበው፣ ይህን የሚደርግ ከራሱ እንደሰረቀ ማሰብ አለበት ብለዋል።
ጠቅላይ ሚኒስትሩ በቅርቡ በፓርላማ ስለሙስና የተናገሩት በጣም ትክክል መሆኑንም በመጥቀስ፣ እኔ የሚታየኝ ይህችን ሀገር አምስት ቡድኖች እያጠቋት እንደሆነ ነው ሲሉ ይጠቁማሉ። ማፊያ ባለስልጣናት፣ ማፊያ አክቲቪስቶች፣ ማፊያ ባለሃብቶች፣ ማፊያ ፖለቲከኞች እና በሃይማኖት ካባ ተደብቀው የሚንቀሳቀሱ ማፊያ ሃይማኖተኞች ሀገሪቱን በከፍተኛ ደረጃ እያጠቁ እና ህዝብን ለችግር እየዳረጉ ነው ሲሉ አመልክተዋል።
እሳቸው እንዳሉት፤ ባለሃብት ነኝ የሚል ሰው፤ ሀገሩን፣ መንግስትን፣ ህዝብን፣ ሃይማኖቱን የሚያከብርና ከሀገሩ የማይሰርቅ መሆን አለበት። ታሪክን ለማሸጋገር መጀመሪያ ለራስ ንጹህ መሆን ያስፈልጋል። ጥሩ ዜጋ ለመፍጠር መጀመሪያ ንጹህ መሆን ይገባል።
‹‹ራዕይችን ሰፊ መሆን አለበት፤ ሀገራችን ለሁላችንም ሁሉንም መሆን ትችላለች፤ ሀገራችን የተፈጠርንባት፣ ያደግንባትና የምንኖርባት ስለሆነ ልንጠብቃት ይገባል›› ሲሉ አስገንዝበው፣ ፍቅር፣ ሠላም፣ አንድነትና ለውጥ እንደሚያስፈልግ አስታውቀዋል።
ክፍለዮሐንስ አንበርብር
አዲስ ዘመን ታኅሣሥ 1 /2015