በምናባችን የልደት ፕሮግራም ለመሳተፍ በጉጉት እየጠበቁ ያሉ ልጆችን እንመልከት። በጊቢው ውስጥ ያሉት ልጆች ሁሉ ሰዓቱ እርቋቸው እየተቁነጠነጡ ነው። ልደትን ማክበር ልዩ ስሜት ይፈጥርላቸዋል። የራስ ልደት ሲሆን ደግሞ የበለጠ።
ልጆች ልደታቸውን በጉጉት እንዲጠብቁ ከሚያደርጋቸው ነገሮች መካከል አንዱ ስጦታ ነው። የሚሰጣቸው ስጦታን ታሳቢ አድርገውም ይጠብቃሉ።
የልደቱ ሰዓት ተጀመረ። እናት ፕሮግራሙን በጸሎት አስጀመሩ። ልደቱ ስለሚከበርለት ልጅ አምላካቸውን እያመሰገኑም ጸለዩ፤ በመቀጠልም መዝሙር ተዘመረ። በማስከተል ልደቱን ሊያከብሩ የተሰበሰቡ ልጆች ስለ ጓደኛቻቸው የሚሰጡትን አስተያየት መስጠት ጀመሩ። ሁሉም አስተያየታቸውን ሰጡ። ከአስተያየቶቹ መካከል የልጁ ታናሽ እህት አስተያየት ትኩረትን የሚስብ ነበር፤ “ወንድሜ በጣም እወድሃለሁ፤ አንተ ለእኔ ስጦታዬ ነህ፤ እና መልካም ልደት።” ብላ ንግግሯን ዘጋች። ባለልደቱ በእህቱ አስተያየት ልቡ ተነካ።
ባለልደቱ ታዳጊ እንደወትሮው “ማን ምን ስጦታ ይሰጠኛል?” ብሎ እየጠበቀ ነው። እንደተለመደው አባቱ፣ እናቱ፣ ወንድሞቹ፣ እህቱ፣ አጎቶቹ ወዘተ ይህን ለልደተህ እያሉ የሚያበረክቱትን እየጠበቀ ነበር። ከታናሽ እህቱ የመጣው አስተያየት ስለ ስጦታ የሚያስበውን አስተሳሰብ እንዲጠይቅ ያደረገው ሆነ። እርሱ ምን ያህል ዋጋ እንዳለው፤ እርሱ ስጦታ ሆኖ በመሰጠቱ ውስጥ ስላለው ትልቅ ነገር እንዲያስብ አደረገው።
ኬክ ተቆርሶ የልደት ፕሮግራሙ እየተደረገ እያለ ዘወትር በስራ የሚባክነው አባት ከቤት ደረሰ። አባትም ለልጁ የገዛለትን እቃ ይዞ ቀረበ። ልጁም አባቱን “አባዬ ተቀይሜሃለሁ እኔ ከስጦታው በላይ የምፈልገው አንተን ነው፤ አንተ ለእኔ ቦታ ካለህ ቢያንስ በልደቴ ቀን ቀልብህን ሰብስበህ መገኘት አለብህ። እኔ ለአንተ ዋጋ እንዳለኝ የምለካው በምትገዛለኝ ቁሳቁስ ውድነት አይደለም፤ አንተ ለእኔ በምትሰጠው ጊዜ እንጂ” ሲል ተናገረ። አባት ከልጁ ባገኘው ባልጠበቀው መልስ ደነገጠ። ልጁ ነገሮችን በጥራት ማሰብ የሚችልበት እድሜ ላይ እንደሆነም ተረዳ።
የልደት ፕሮግራሙ አልቆ ሁሉም ወደቤቱ ሲመለስ ልደቱ የተከበረለት ታዳጊ ግን በአይኑ ላይ እምባ ሞላ፤ እህቱ አንተ ለእኔ ስጦታዬ ነህ ያለችው ቃል በውስጡ ጎልቶ አሁንም ይሰማዋል።
ሰዎች መፈለግን፤ መወደድን፤ በሰዎች ውስጥ ቦታ ያለን መሆኑን እንድንረዳ እንፈልጋለን። በእለቱ ታዳጊው ክፍል ከሞሉት ስጦታዎች መካከል ጎልቶ በውስጡ ያለው የታናሽ እህቱ ንግግር ሆነ።
ዛሬ በስጦታ ገብያው ሰፊ የሆነ የቁሳቁስ ልውውጥ ይደረጋል፤ አንዱ ገዢ ሌላው ሻጭ ሆነው ተሰልፈዋል። ቁሳቁስ ከአንዱ ወደሌላው ይቀያየራል። ቁሳቁስን ተከትሎ የሚመጣው ቅጽበታዊ ተስፋም እንዲሆ ቦግ እልም እያለ ይቀጥላል። የሰው ልጅ ግን ቦታን የሚሰጠውን ሰው በልዩ ሁኔታ እየናፈቀ ይገኛል፤ ስጦታን በመሰጠት ውስጥ ፈልጎ።
በዚህ መጣጥፍ ውስጥ በሕይወታችን ውስጥ ልዩ ቦታ ስላላቸው ሰዎች እያሰብን እንዘልቃለን። የምናነሳው ቁልፍ ነጥቦችም ስጦታን፤ መሰጠትን እና መስጠትን የሚያነሱ ሆነው ይገኛሉ።
ስጦታ መስጠትም ሆነ መቀበል ከፍቅር ይመነጫል። ሰው ሊሰጠው የሚችለው የመጨረሻ ነገር ህይወቱን ነው። ከህይወት መለስ ጊዜ፣ ገንዘብ፣ ወዘተ ስጦታ ሆኖ ይቀርባል። ሰጪውም ሆነ ተቀባዩ ለራሱ ግለሰብ ነው። ለራሱ ፍቅርን መስጠት በመጀመር ውስጥ በመሰጠት ውስጥ ያለው መስጠት ትርጉም አለውና ስለ ፍቅር እናንሳ።
ለመሰጠት መነሻ የሆነው የፍቅር ህይወት
ከፍቅር ውጭ የሆነች ዓለም ምን እንደምትመስል ለማሰብ እንሞክር። እናት ለልጇ የምትሆነው ከውስጥ የሆነ ፍቅር የሌለባት ዓለም። መስጠትን እንጂ መቀበልን ስሌቱ የማያደርገው እውነተኛ ጾታዊ ፍቅር የሌለባት ዓለም። ሕዝብን ለማገልገል ብሎ በፖለቲካ መድረክ ላይ የሚገኝ የህዝብ ወዳጅ ሰው የሌለባት ሀገር። የእድሜ ልክ ጉርብትና ሆኖ የሚቀርብ ወዳጅነት የሌለባት ማህበራዊ ህይወት። መቀበልን ሳያስቡ መስጠት ስሌትን ያላደረጉ ሰዎችን የማታውቅ ፕላኔት።
ፍቅር የምድር ትልቁ ሃይል ነው። ራስን ከመውደድ ተነስቶ በመሰጠት ውስጥ ወደ ሌሎች መድረስ የሚቻልበት።
በተሳሳተ መንገድ ትርጉም ከሚሰጣቸው ነገሮች መካከል አንዱ ራስን መውደድ ይገኝበታል። ራስን በመውደድ ውስጥ የሚኮነን ሰው ራስ ወዳድ ይባላል። ራስ ወዳድነትን በማነወር ስንገልጽ በሰፊው ይስተዋላል። ለራስ የተጋነነ ቦታ መስጠት ላይ ስላለው ችግር ስምምነት ላይ ለመድረስ አንቸገር ይሆናል። ራስን መውደድ ግን በሚዛኑ ቦታው ሊፈለግለት ይገባልና አስቀደምነው።
“ባልንጀራን እንደራስ መውደድ” አምላካዊ ትእዛዝ ውስጥ በውስጠተዋቂነት ራስን መውደድ የእያንዳንዱ ሰው ተፈጥሯዊ መገለጫ መሆኑን አምኖ የተቀበለ ነው። በሕይወት ውስጥ ትርጉም ያለው አስተዋጾ ለማድረግ ራስን መውደድ ግድ ነውና። ለሌሎች ለመስጠት ስንነሳ ለራሳችን መስጠትን ማስቀደም ይኖርብናል።
ራስህን ትወዳለህ? ራስሽን ትወጃለሽ? እንግዲያውስ ውስጣችንን እናዳምጥ። በውስጣችን የሚፈጠረውን የትኛውንም ተፈጥሯዊ ስሜት እንግራ። መቀበልን ስሌት ሳናደርግ የመስጠት ህይወታችንን እንመርምር። በፍቅር ስሜት ላይ ስሌትን ጨምረን ፍቅር አልባ ህይወትን ከመኖር ራሳችንን እንጠብቅ። ፍቅር ተፈጥሮ፤ ተኮትኩቶ፤ ፍሬ እንዲያፈራ ሲደረግ የተፈጠረበትን ዓላማ የሚያሳካ ይሆናልና። ለራስ ብቻ ከመኖር ወደ ሌሎች መዘርጋትን ያስከትላልና።
ራስን ተቀብሎ በመሰጠት ውስጥ መኖር ተግባራዊ ህይወትን መኖርን ይጠይቃል። ለራሱ ቦታ የሚሰጥ ሰው ተግባራዊ ኑሮ በመኖር ውስጥ ለሌሎች መድረስ የሚችል ነው። አባት በልጁ የልደት ፕሮግራም ላይ አለመገኘቱ ለታዳጊው የፈጠረው ስሜት የምናብ ታሪካችን ይነግረናል። በመስጠት ውስጥ መሰጠትን የሚፈልገው ታዳጊ ተግባራዊነትን የፍቅር መገለጫ አድርጎ ለአባቱ ነገረ።
ተግባራዊነት የመሰጠት እውነተኛ ማሳያ
አንድ የቆየ አባባል አለ እንዲህ የሚል “ፍላጎቱ ካለህ ትችላለህ” የሚል። በፍቅር ተነሳስተው ለውጤት የሚሰሩ ሌላ ሰው መጥቶ እስኪቀሰቅሳቸው ድረስ የሚጠብቁ አይደሉም። እራሳቸውን ከምቾት ቀጠና ገፍተው ከፍቅር ወደ ሆነ ተግባር ስራ የሚያስገቡ ናቸው። ይህንንም መደበኛ ስራቸው ያደርጋሉ። በእዚህም ምክንያት ነው የ20ኛው ክፍለዘመን ምርጥ አነሳሽ መሪዎች መካከል ፕሬዝዳንት ሩዝቬልት የሚጠቀሱት። እኒህ ፕሬዝዳንት እንዲህ አሉ “እንድሰራው የማምንበትነት ነገር ከመስራት ውጪ በእኔ ውስጥ ትልቅ ቦታ የምስጠው አስደማሚ ነገር የለም። እንድሰራ ያመንኩበትን ነገር ለመስራት የተግባር እርምጃን የምወስድ ነኝ።”
እድሎች ወዳለህበት በር ድረስ መጥተው ላያንኳኩ ይችላሉ። አንተ ወደ እድሎችህ ልትሄድና ልታንኳኩ ይገባል። ያለህን ሃብት፣ ችሎታ እና ልዩ-ልዩ ሃብቶችን ቁጠር፤ ይህን ማድረግህ ያለህን እምቅ-አቅም ሊያሳይህ ይችላል። ከእዚያን በየእለቱ ያሉትን እድሎችን መመልከት ጀምር። የሆነ ነገር እንደሚያስፈልግህ የሚሰማህ ምን ላይ ነው? አንተ ያለህን ችሎታ/ክህሎት የሚያስፈልገው ሰውስ ማን ነው? የትኞቹ ያልተደረሱ የህብረተሰብ ክፍሎች አንተ ያለህን ነገር ባለማግኘታቸው በተግባር እየሞቱ ነው? እድሎች ሁሉም ቦታ አሉ፤ ከፍቅር የሆነ ተግባራዊነት ከእያንዳንዱ ሰው ይጠበቃል።
በመሰጠት ህይወት ውስጥ መስጠትን በተግባራዊነት ለማሳየት አንዳንዴ የመጋፈጥ ጫፍ ላይ እንድንገኝ ሊያደርገን ይችላል።
መጋፈጥ የመሰጠት ጫፍ፣
እናት ስለ ልጆቿ ስትል የማትጋፋጠው ምንድን ነው? መሪው ምን እንደሚፈልግ ከተረዳና ወደ ተግባር ለመቀየር ግፊት ካደረግ አንድ ሊያልፈው የተገባ መሰናክል አለ። ይህም መሰናክል ስጋቶችን ለመጋፈጥ መፍቀድ ነው። ተነሳሽ ሰዎች ሁልጊዜ ስጋቶችን የሚጋፈጡ ናቸው። ስጋቶችን የሚጋፈጡበት ምክንያቱ ተነሳሽ የሆኑለት ነገር ባይከናወን የሚያጎድለውን ነገር ስለሚያውቁ ነው። ፕሬዝዳንት ጆን ኤፍ ኬኒዲ እንዲህ አሉ “የተግባር ስራን በመስራት ፕሮግራም ውስጥ ስጋትም ሆነ ዋጋ መክፈል አለ፤ ነገርግን ከእዚህ የበዛው ዋጋ መክፈል ያለውን ስራ ለመስራት ባለመነሳት ውስጥ ነው።”
ተጋፋጭነት መሰጠታችን የእውነት እንዲሆን ያደርጋል። በመሰጠት ውስጥ የመስጠት ህይወትን ለመለማመድ ተጋፋጭነትን ባህሪያችን ማድረግ ያስፈልጋል። በምንኖርበት ምድር ውስጥ ምንም ነገር አልጋበአልጋ አይመጡም፤ መጋፈጥን የሚጠይቁ አያሌ ጉዳዮች አሉና።
ብዙ ጊዜ መጋፈጥን በመሸሽ ለሰዎች መስጠት የምንችለው አያሌ ነገር እያለ አልችልም ባይነትን መለያችን እናደርጋለን።
የአልችልም ጠላት መሆን
በተጨባጭ እንደምናየው እችላለሁ ብሎ መነሳት ለብዙ ሰው ይቸግረዋል፤ ምክንያቱም እችላለሁ በማለት ብቻ የሚሆን ነገር ስለሌለ። የአልችልም ጠላት ለመሆን ራስ ላይ መስራት ይገባል፤ ከራስ በላይ መመንዘር የሚቻለው በመቻል መንፈስ ውስጥ በመሆን ስለሆነ።
ሁላችንም አዲስ አመት በመጣ ቁጥር በአመቱ ውስጥ ምን ማሳካት እንዳሰብን የመዘርዘር ልማድ ይኖረን ይሆናል። ማሳካት የፈለግነውን ማሳካትን ስናስብ አስቸጋሪ የሚሆኑብንን ነጥቦችም እንዲሁ ልንለያቸው እንሞክራለን። ለለውጥ መነሳትን ስንመርጥ አትችልም የሚለን በአካባቢያችን የሚሰማ ድምጽ እግራችን ላይ የታሰረ ገመድ ሆኖ ልናገኘው እንችላለን።
አትችልም፤ አትችይም የሚለው ድምጽ በበረከተበት ከባቢ ውስጥ እየኖርን በእችላለሁ መንፈስ ለለውጥ የሚነሱት ማግኘት አንችልም፤ መሰጠትም ሆነ መስጠት የለውጥ መንፈስ ውጤት ነውና።
አለመቻልህን በውስጥህ ከምታመላለስ መቻልህን ለራስህ ንገረው። የጊዜ ቀለበት ውብ ሆኖ የሚታየው በመቻል መንፈስ፤ ለመቻል ተግባራዊ እርምጃን በመራመድ ነውና። በዙሪያህ ያለው ሳርቅጠሉ ስለመቻል የሚናገረው ድምጽ ጎርናነቱ በዝቶ ጆሮህን እስክትይዝ የሚያደርስ ቢሆንም አሁንም መቻልን አስብ። በመቻል መንፈስ ውስጥ ስለ መሰጠት መጋፈጥ ትችላለህ።
የምንኖርበት የድህነት ጥግ ይታወቃል። አልጠራ ያለው የፖለቲካ መንገዳችን የፈጠረው ውጥንቅጡ እንዳለ ነው። የትምህርት ጥራቱ አሽቆልቁሎ ባለዲግሪውና ዲግሪው የሌለው መካከል በእውቀት ላይ ልዩነት የሌለው ሆኖም ይታያል። ሁሉም ነገር አለመቻላችንን እየነገረን ባለንበት ዘመን ውስጥ ስለ መቻል ማንሳት እብደትም ሊመስል ይችላል። በመሰጠት ህይወት የለውጥ መንገዱ ውስጥ ግን የመቻል መንፈስ ግን የሚይዘው ቦታ በቀላሉ የሚታይ አይደለም። የመቻል መንፈስ ለሁላችን እንዲሆንልን በመስጠት ውስጥ የምንሰጠው ትርጉም ውስጥ ቦታ ይኑረው። በአንድ ወር ውስጥ ይህን ማድረግ እችላለሁ፤ በአመት ውስጥ፤ በሦስት አመት ውስጥ ብሎ ግብን ለማስቀመጥ የመቻል መንፈስ እጅጉኑ ያስፈልገናል።
በመቻል መንፈስ ውስጥ ተጋፋጭነት ይኖራል፤ ተጋፋጭነት ከምክንያት በላይ የሆነ መሰጠት በውስጣችን ይነግሳል፤ መሰጠታችን መስጠትን ከሕይወታችን እንዲገኝ ያደርጋል። የመስጠት ህይወት አንዳችን ለሌላችን ስጦታ እንደሆንን በማሰብ ውስጥ።
የሌሎቹ ጩኸት
ለረጅም ጊዜያት በወለጋ እንዲሁም በተለያዩ ቦታዎች የሚሆነው ነገር እንደ ሀገር ሁላችንንም አንገት ያስደፋ ነው። ከሞት ጋር የሰው ልጅ እንደ ቀላል እንዲገናኝ ያደረገ ስብራት። ያልተደመጡ ድምጾች በሞት ሜዳ ውስጥ። አንዳችን ለሌላችን ያለን መሰጠትን ደረጃው ጥያቄ ውስጥ እንዲገባ ያደረገ።
በጭንቅ ላለችው ነፍስ የሚያደምጥ ቢገኝ ምንኛ እፎይታን ታገኝ ነበር። በሞት ጥላ ውስጥ ለሚያልፉ የሚታደግ አካል ኮቴ ትርጉሙ ምን ያህል ይሆን። ጆን ማእክስዌል የተባለው ጸሐፊ አንድ ጥያቄ ይጠይቃሉ እንዲህ በማለት፤ “ከአሜሪካ ተጽእኖ ፈጣሪ ሰዎች መካከል ዝርዝር ብትባል የማንን ስም ትጠቅሳለህ? ፕሬዝዳንቶቹን ትጠቅስ ይሆን? ወይንስ ማይክል ጆርዳንን? ወይንስ ቢል ጌትስን? እኔ ግን በዝርዝርህ ውስጥ ኦፕራ ዊንሬን እንድትጨምር እጠይቅሃለሁ።” ይላሉ። ስለ ኦፕራ ሲጽፉም “ኦፕራ በ1985 እ.አ.አ ኦፕራን በተግባር የማትታወቅ ተራ ዜጋ ነበረች። በቺካጎ አካባቢ ስርጭት ባለው የጠዋት ሾውን በመምራት ለአንድ አመት ወደ መድረክ ስትወጣ ትኩረት መሳብ ጀመረች። የእርሷ ስኬት ጀርባ ያለው ጉዳይ የመናገር አቅሟ ጥሩ መሆኑ እንደሆነ በብዙ ሊታሰብ ይችላል፤ በእርግጥ ትክክል ነው። በልጅነት ወቅት ማለትም የሁለት አመት ልጅ እያለች በቤተክርስቲያን መድረክ ላይ ንግግር አድርጋ ምእመናኑ ጥሩ ተናጋሪ ነሽ ብለዋት እንደነበር ታስታውሳለች። ነገርግን ከመናገር በላይም የማዳመጥ አቅሟም ትልቅ ነው። ከዘውትር ልምዷ መካከል ዋናው ለመማር ያላት ፍላጎት ነው። የጸሃፊያንን ጥበብ በንባብ ውስጥ እንደሚገኝ በማዳመጥ ውስጥ በሰዎች ውስጥ ያለውን ጥበብ ለማግኘት ትወዳለች። ሰዎች እንዴት እንደሚያስቡና እንደሚሰማቸው ለማወቅ ልብወለድ መጻህፍትን፣ የግለታሪኮችን ወዘተ ለማወቅ ትጥራለች። የአድማጭነት አቅሟ የስራዎን መስመር አሳድጎታል። በተግባርም በቴሌቪዥን መስኮት የምታቀርበውን ፕሮግራም ተወዳጅነት ጨምሮታል። ጉዳዮቹን ለአየር ለማብቃት በተከታታይነት ነገሮችን መመልከት እና ማድመጥ ትወዳለች። ወደ ፕሮግራሙ የምታቀርባቸውን ባለሙያዎች፣ ጸሃፊዎች፣ አርቲስቶች በትኩረትና ከውስጥ በሆነ መስማት ታደምጣቸዋለች። ኦፕራ ባላት የአድማጭነት አቅም ተጽእኖ ፈጣሪ ሰዎች ተርታ እንድትሰለፍ ሆናለች። እርሷ የአለማችን ከፍተኛው የመዝናኛ ዘርፍ ተከፋይ ባለሙያዎች ተርታ ትመደባለች፤ ግማሽ ቢሊዮን ዶላር የሚገመትም ሃብት አላት። በአሜሪካ ብቻ የሳምንቱ ሰላሳ ሦስት ሚሊዮን ህዝብ የእርሷን የቴለቪዥን ፕሮግራም ይከታተላል።” በማለት የኦፕራን የማድመጥ አቅም ይናገራሉ።
ኦፕራ ያደመጠቻቸው በሞት ዋዜማ ላይ ያሉትን አይደለም። በድረሱልን ጩኸት ውስጥ ያሉ አይደሉም። ነገርግን በመደበኛ ህይወታቸው ውስጥ ሆነው መደመጥን የሚፈልጉ። መደመጥን ከዚህ ከፍ አድርገን በአደጋ ባለ ሰው ህይወት ውስጥ ሆነን ስንመለከት የሚገባን ትልቅ ነው። አቅማችንን አይተን ፈጽሞውኑ ወደ ኋላ እንድንል የማያደርጉ ድምጾች።
ዛሬ ስለ መስጠት ስናነሳ ያልተሰሙ ድምጾችን ለመስማት የምንሄድበትን እርቀት ልናስብ ግድ ይላል። በተጋፋጭነት መንፈስ ሁላችንም ስለ አንድ ሰው ሞት አብረን የምንቆምበት ጊዜ። ሰው ስጦታ መሆኑን ተረድተን አንዳችን ለሌላችን ስጦታ ሆነን የምንኖርበት ህይወት።
ቀኖች መጥተው ይሄዳሉ። ህይወትም ይቀጥላል። አንዳችን በሌላችን ህይወት ውስጥ የሚኖረን ቦታ ግን ለህይወት ትርጉም ያለው ሆኖ ይታያል። በእንባ ውስጥ ለሚገኝ እምባን ማበስ በሌላው ሰው እንዲሆን እሻለሁ።
በአገልጋይ ዮናታን አክሊሉ
አዲስ ዘመን ታኅሣሥ 1 /2015