ማሰላሰያ፤
በኢትዮጵያ ውስጥ ምን ያህል ሕጋዊ የማረሚያ ቤቶች እንዳሉና የታራሚዎች ቁጥርም ምን ያህል እንደሆነ የሚመለከተው መንግሥታዊ ተቋም በቂ መረጃ እንዳለው ተስፋ እናደርጋለን። ቀደም ሲል በነበረው ሥርዓት በሹክሹክታና አንዳንዴም ጮክ በሚሉ የሚዲያ ድምጾች ሲታሙ የነበሩትና “በባለ ጊዜዎች” ይተዳደሩ የነበሩት ድብቅ የማሰቃያ እስር ቤቶች ዛሬም ድረስ ይኑሩ አይኑሩ ለጊዜው የአደባባይ ምስክርነት ለመስጠት መረጃውም ሆነ ማስረጃው ስለሌለን ርዕሰ ጉዳዩን ጫን ብለን ለመዳፈር አንሞክርም። “ነበርን” ያስታወስነው ሆድ ሆዳችንን እንደ ሻህላ እየበላ ፋታ የነሳን ወቅታዊ ችግር ተጋርጦን እንጂ የላይኛውን ጉዳይ የጠቀስነው ዋና ትኩረታችን ስለሆነ አይደለም።
ከቅርብ ጊዜያት ወዲህ የምንሰማቸውና የምና ደምጣቸው አንዳንድ የንጹሐን ዜጎች የእገታ ትራዤዲዎች ከአሁን ቀደም በስፋት ያልተለመዱ ክስተቶች ከመሆን አልፈው የዕለት አፍ ማሟሻ ወደ መሆን መሸጋገራቸው እንቅልፍና እረፍት እየነሱን መሆናቸውን መሸሸጉ ግን አግባብም ጥበብም አይመስለንም። በጠራራ ፀሐይ ግለሰቦች እየታፈኑ በመቶ ሺህዎች እና በሚሊዮኖች ብር ቤዛ (Ransom) መጠየቁ የዕለት ተዕለት መርዶ ከሆነብን ውሎ አድሯል።
ይህን መሰሉ አዲስ መጥ የሽብር ድርጊት የግለሰባዊ ፍርሃት ውጤት ብቻም ሳይሆን ሀገራዊ እፍረት ወደ መሆን ደረጃ እየተሸጋገረ መሆኑን ጫን ብለን የምንገልጸው ዋነኛው የስጋት ምክንያትና ለፈውስም ይረዳ ስለመሰለን ነው። በሰላም ሀገር ምን ያስፈራችኋል? ምንስ ያስደነግጣችኋል? ተብለን እንደማንገሰጽና እንደማንወቀስ ተስፋ እናደርጋለን። ብንወቀስም ሆነ ማስተባበያ ቢሰጠን እውነቱ ስለማይደበቅ ሕግ ማስከበሩ ላይ ማተኮሩ ይበልጥ ያዋጣ ይመስለናል።
ደግሞም እኮ አለባብሰን ብናርስ በአረም መመለሳችን ስለማይቀር ገና በጠዋቱ ለመፍትሔ መጮኹ እኛን ዜጎችን ለጥንቃቄ፤ መሪዎቻችን ጨክነው ፍርሃታችንን እንዲገፉልን ጠቋሚ ሊሆን ስለሚችልም ሹመኞቻችንን እንደማያስቆጣ ተስፋ እናደርጋለን። ስለሆነም ነው ጉዳዩን ሳናድበሰብስ ለመንግሥታችንና ለሕግ አስከባሪ ክፍሎች በግልጽ ቋንቋ “አቤት! አቤት!” እያልን የምንማጸነው።
ዝምታን መርጠን በጉምጉምታ ስሜታችንን በየጓዳችን ለመግለጽ መሞከራችን ባይቀርም በኅሊናችን፣ በብዕራችን፣ በትውልድና በፈጣሪም ዘንድ ጭምር እንደሚያስወቅስ ስለምናምን “ሳይቃጠል በቅጠል” እንዲሉ፤ የግፍ ድርጊቱ ፈጥኖ እንዲቆም መጠየቁ አግባብም የዜግነትና የሙያ ግዴታም ጭምር መሆኑ እንዲታወቅልን እንፈልጋለን።
ይህ ከማቆጥቆጥም አልፎ በየአካባቢው ሥር እየሰደደ በመሄድ ላይ ያለው የአሸባሪ አጋቾች ድርጊት በእንጭጩ ካልተቀጨና የፍትሑ በትር ጠንከር ካላለ በስተቀር መዘዙ ውሎ ሲያድር ተመዞ ላያልቅ እንደሚችል በመሰል ችግር የተጠቁ የብዙ ሀገራት ታሪክ ትምህርት ሊሆነን ይገባል።
የአጋች ታጋች ድራማው “የተዘወተረ ክስተት” በሆነባቸው በርካታ ሀገራት የዜጎች ሕይወት እንደምን ወደ ምድራዊ ገሃነምነት እንደተለወጠ እየሰማንም እያየንም ስለሆነ በዝርዝር መተንተኑ እጅግም አስፈላጊ ላይሆን ይችላል። ሥጋታችንን የምንገልጠው ዛሬ ዳዴ እያለ በእንፉቅቅ የሚሄደው የአፈናና የእገታ ተግባር ነግ ተነግወዲያ የሀገሪቱ ዋና መከራ ሆኖ አሳራችንን እንዳያበዛ በመፍራትም ጭምር መሆኑ ይታወቅልን።
“እስረኞቹ አጋቾች”፤
አንድ ሰው በአስተሳሰቡና በአመለካከቱ የራሱ እስረኛ መሆን ሲጀመር ሌሎችን በግፍና በእብሪት ድርጊቶች ለማሸማቀቅና በደመነፍስ እየተመራ የወንጀል ድርጊቶችን ለመፈጸም አቅም እንደሚያገኝ የሥነ አእምሮ ጠበብቱ በሚገባ ትንታኔ ሰጥተውበታል። አስተሳሰብ በክፉ ድርጊቶች ሲበከልና ሲበረዝ የውስጥ ዕይታ አድማስ ይጠባል። የዕይታ አድማስ መጥበብ ከጀመረ ደግሞ አሻግሮ ሩቅ ለማየትና አሰላስሎ ለመወሰን አቅም ስለማይኖር የግልፍተኝነት ጭካኔ የእልህ መወጣጫና መገለጫ መሣሪያ ይሆናል።
ንጹሐን ዜጎችን ለማገት በድፍረት የሚንቀሳቀሱት ጨካኝ ዜጎች መገለጫቸው አንድም ተስፋ መቁረጥ ነው። አንድም የሱስ ባሪያ መሆናቸው ነው። አንድም ራስ ተኮር ትርክትን እየፈጠሩና ማንነታቸውን አሳንሰው ስለሚመለከቱ ለበቀልና ለግፍ ፈጣኖች ስለሆኑ ነው። አንድም ከኋላ ለሚገፋቸው “ዱር አደር” ኃይል ተንበርካኪ በመሆን ወኔያቸው ስለሚሰለብ ነው። በአንድምታው ብዙ ጉዳዮችን መዳሰስ ቢቻልም ጠለቅ ብሎ ሁሉንም ምከንያቶች መዘርዘሩ ስለማይሞከር ለማሳያነት ይበቃሉ የተባሉት ምሳሌዎች ብዙ አቅጣጫዎችን ለማሳያት ፍንጭ እንደሚሰጡ ተስፋ እናደርጋለን።
ከቅርብ ጊዜያት ወዲህ በዘረፋና በእገታ ተግባር ላይ የተሰማሩት ዓላማ ቢስ ግለሰቦች ንጹሐን ዜጎችን በማገት “ይህን ያህል የማስለቀቂያ ገንዘብ (ቤዛ) ካልከፈላችሁ ታጋቾቹን እንገድላቸዋለን” የሚለው መደራደሪያቸው የድኩም አስተሳሰባቸው እስረኛ መሆናቸው ብቻም ሳይሆን የኅሊና ቀውስ ተጠቂዎች እንደሆኑም ጭምር ለመገመት አይከብድም።
በጠራራ ፀሐይ ግለሰቦችንና ቡድኖችን እያፈኑ መውሰዳቸው ብቻም ሳይሆን ስለ እኩይ ድርጊታቸው በሕጋዊ አካል በኩል ታድነው እርምጃ እንደሚወሰድባቸው መዘንጋታቸው የድኩምነታቸው አንዱ መገለጫ ተደርጎ ሊወሰድ ይችላል። በዚህ ፈጣን የቴክኖሎጂ ዘመን እንቅስቃሴያቸውን በቀላሉ መቆጣጠር እንደሚቻልና ግንኙነታቸውንና የቤዛው ገንዘብ የሚገባበትን የባንክ ሂሳብ ቁጥር በግላጭ ሲሰጡ በቀላሉ ሊደረስባቸው እንደሚችል ያለመረዳታቸው በራሱ የአስተሳሰብ እስረኞቹ አመለካከት ምን ያህል እንደጠበበና የኮሰመነ እንደሆነ ማረጋገጫ ሊሆን ይችላል።
ይህን መሰሉ የእርምጃ አወሳሰድ በግልጽ እየታወቀ እስከ ዛሬ አጋቾቹ እንዳሻቸው ሲፈነጩ ለምን ዝም ተባሉ? ለሚለው ጥያቄ መልሳችን “ሚስትህ ወለደች?” ተብሎ የተጠየቀው አባወራ “ማንን ወንድ ብላ!” በማለት የመለሰው መልስ “ከልብ ካለቀሱ እምባ አይገድም” ከሚለው ቢሂል ጋር ተጣምሮ ቢታወስ ያግባባን ይመስለናል።
ማንኛውም ድርጊት ይዘገይ ካልሆነ በስተቀር ተሰውሮ ሊቀር አይችልም። ይህ እውነታ ያልገባቸው ወይንም ገብቷቸውም የልብ ልብ የተሰማቸው አንዳንድ የመንግሥት ሹመኞችና በዙሪያቸው የተኮለኮሉት ደላሎችና አቀባባዮች በአስተሳሰባቸው እስረኛ ሆነው በሕዝብ ላይ ግፍ ለመፈጸም የሚጨክኑት “ሆዳቸው አምላካቸው፤ ነውራቸው ክብራቸው” ስለሆነ ነው። ነገሮችን አዙሮ ለማየትና ቆም ብሎ ኅሊናቸውን ለማድመጥና ሰክኖ ለማሰላሰል የተሳናቸውም የወረደው ሰብዕናቸው ስለማይፈቅድላቸው እንጂ እውነቱ ጠፍቷቸው አይደለም።
በተውገረገረ የቅዠት አስተሳሰባቸው ራሳቸውን በራሳቸው አጥረውና ጠፍረው የሚኖሩ እንደነዚህ ዓይነት የጥፋት መልዕክተኞች ሌላው ሰው ለእነርሱ ሰብዓዊ ፍጡር እንዳልሆነ እስከ ማሰብ ድረስ የሚደርሱ ከንቱዎች ናቸው። ሕግም ከእነርሱ ጉልበት በታች እንደሆነ ስለሚያምኑ ቀኑ ቀን ወልዶ ፍትሕ በአራት ዓይናማ አትኩሮቱ ወደ ብርሃን አውጥቶ በአደባባይ እንደሚገልጣቸው ለማመን ልባቸውን ሞራ ስለደፈነው እውነት እንደሚያሸንፍ ለማመን ዝግጁ አይደሉም።
እውነትና ንጋት እያደር እየጠራ ሄዶ ፍርዳቸውን በሚቀበሉበት ዕለት የውርደታቸውን ዋንጫ እያንገሸገሻቸውም ቢሆን እንደሚጎነጩ ለማስተዋል የዘቀጠው አስተሳሰባቸው የኅሊናቸውን ብርሃን ስላሰወር እንደ ሰው ለማሰብ የሰውነት ብቃት የላቸውም። ማጠንጠኛችን፡- “ፍትሕ ወይ ወዴት አለህ!” የሚለው ብርቱ ጩኸት ፈጥኖ ምላሽ እንዲያገኝ የሚመለከታቸው ሁሉ ጨክኖው የታዳጊነት ኃላፊነታቸውን እንዲወጡ እነሆ አቤቱታችንን ይድረስ የምንለው የነገው ቀናችን ስለሚያስፈራን ነው።
ብዕረ መንገዳችንን ሌላም ተቀጥላ ሃሳብ ጠቀስ አድርገን እንለፍ። በኢትዮጵያ ምድር እየታገቱ ያሉትና ቤዛ የሚጠየቅባቸው ግለሰቦች ብቻም አይደሉም። ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር) “የሕዝብም የመንግሥትም” ያለመሆኑን የገለጹት ውሱን የሀገሪቱ የመሬት ሀብትም በእብሪተኛና በሕሊና ቢስ የመንግሥት ሹመኞችና በአቀባባይ ደላሎች አማካይነት በጠራራ ፀሐይ ታግቶ አጥር እየታጠረ ሲከለልና ሲቸበቸብ በእህህታ እየተብሰለሰለን “የፍትሕ ያለህ!” እያልን ስንጮኽ መክረማችን የሚዘነጋ አይደለም። ይህን መሰሉ ችግር ሊቀረፍ ነው መባልን እንደሰማን የተሳልነውን ስዕለት እንደየእምነታችን ለፈጣሪ ለማድረስ አልዘገየንም።
ይህ ጸሐፊ በሚኖርበት ክፍለ ከተማ ውስጥ በአስተሳሰባቸው የታሰሩ፣ በሕሊናቸው የታወሩ ደላሎችና ሹመኞች የሚፈጹሙትን የመሬት ወረራ እገታ ግፍ ሲያስተውል የኖረው እንባ በተቀላቀለበት ትዝብት ጭምር ነው። ማስረጃ አቅርብ ከተባለ መኖሪያ ቤቱን ተጎራብቶ በተወረረው መሬት ላይ የተገነቡትን በመቶዎች የሚቆጠሩ ቤቶችን በማስረጃነት ማቅረብ ይችላል። በአጽማቸው ቆመው የቀሩትና በታጋች አጋች ሤራ በተጠላለፉ የሌብነት ድራማዎች መሠረታቸውና ኮለናቸው ተገትሮ የቀረው ጅምር ቤቶች “ድምጽ አውጥተው ስለሚጮኹ” ራሳቸው ለራሳቸው ተጨባጭ ምስክሮች ናቸው።
ሌላውና በእገታ ቱሻ ተተብትቦ የኖረው የአብዛኞቹ የኢትዮጵያ ምሑራን እውቀትና ጥበብ ነው። ያለ መታደል ሆኖ ሀገራዊ ሃይማኖቶቻችንና የፖለቲካው ሥርወ መሠረቶች ለዘመናት ታጥረው የኖሩት በግለኝነትና በድብቅ ፍላጎቶች ማህደር ውስጥ ታሽገው መሆናቸው የትዝብታችንም የታሪካችንም አካል ናቸው። እኒህን መሰል የሀገራችን አንጡራ የጥበብና የዕውቀት ሀብቶች ዛሬም ድረስ በእገታ ተጠርዘውና ለመቃብር ዝግጁ ተደርገው የመኖራቸው ምሥጢር ፍቺ ሊገኝላቸው አልቻለም።
ይህን መሰሉ ዕንቆቅልሻችን “ምን ዕንቁላል ድፍን፣ ያያችሁ እንደሆነ ዐይናችሁ ድፍን” እንዲል የልጅነታችን ጨዋታ፤ ከብርሃን ተሸሽገውና ታግተው ያሉ እውቀቶችና ጥበቦች በቅብብሎሽ ለትውልድ ቢተላለፉ፣ ተላልፈውም ሥራ ላይ ቢውሉ ኖሮ የዛሬው ድህነታችንና ኋላ ቀርነታችን ብሔራዊ መታወቂያችን ባልሆነ ነበር።
የቀረው የዓለም ማኅበረሰብ እውቀቱንና እምቅ የአዕምሮ ሀብቱን ለማጋራት በሚቻኮልበት በዚህ የፈጣን ቴክኖሎጂ ዘመን እዚሁ እኛ ሰፈር ያለንን መልካምነት በስስትና በንፉግነት ሸሽገን አፈር ለማልበስ የመቃብር ጉድጓድ ስንምስ ውለን ማደራችን እንደ ባህል ወስደን በማጽደቅ ስለተጎናጸፍነው ይሞቀን ካልሆነ በስተቀር አይቀዘቅዘንም።
ካሁን ቀደም በዚሁ ዐምድ ሥር በዓለማችን ላይ ከፍተኛ ተነባቢነት ያተረፈውን የእንግሊዛዊ ጸሐፊ የቶድ ሄኒሪን አንድ መጽሐፍ ጠቀስ ያደረግሁበትን አጋጣሚ አስታውሳለሁ። የመጸሐፉ ርዕስ “DIE EMPTY” የሚል ሲሆን ተቀራራቢና የተፍታታው ትርጉሙ “መክሊትህን ለበጎነት አንጠፍጥፈህ እለፍ” የሚል ሃሳብ ያዘለ ነው።
ደራሲው የሚሞግተው እያንዳንዱ ሰው ከታጠረበት እኔ ብቻ አስተሳሰብ ተላቆ ለሌሎች ጥቅም አስቦ ያለውን ሁሉ አሟጦ በማካፈል እንዲያልፍ ነው። “በአስተሳሰባችን በረት” ውስጥ አግተን ያከማቸናቸውና ያጎርናቸው መክሊቶቻችን (ሀብታችን፣ እውቀታችን፣ መልካም ምክሮቻችንና አስተሳሰባችን ወዘተ.) የዕድሜ ድካም ሳይጫጫነን በፊት በጉብዝናችን ወራት ነፃ ወጥተው ለሰው ልጆች ሁሉ በምልዓት ጥቅም እስካልሰጡ ድረስ ከንቱ የከንቱ ከንቱ ነው” የሚል ነው። ዛሬ ጠፍረን ያሰርናቸው በጎ ስጦታዎቻችን በጊዜው አገልግሎት ላይ እስካልዋሉ ድረስ “ቀናችን ሲቆረጥ” ሞት በሚሉት አይምሬውና ጨካኙ ጀግና ተማርከን ያከማቸነው ሁሉ “ለብልና ለምስጥ ሲሳይ” መሆናቸው እንደማይቀር ደራሲው አስረግጦ አስምሮበታል።
በዚህ ዐምደኛ ግምታዊ ስሌት መሠረት የሀገራችን ተጨባጭ ሁኔታ ቢፈተሽ በሕጋዊ ከለላ ጥላ ሥር ተጠብቀው እየታረሙ ካሉት እስረኞች ይልቅ በአስተሳሰባቸው ታስረው የተተበተቡት የራስ በራስ እስረኞች ቁጥር ሳይበልጥ የሚቀር አይመስለንም። ስንቱን አግተንና በስንቱ ኃይል ታግተን ኑሯችን ኑሮ ሳይመስል እስከ መቼ እየቆዘምንና እያነባን እንኖራለን? አንዳች ሀገራዊ ተስፋ ብልጭ ብሎ በተወለደ ማግሥት ተከትሎ የሚመጣው “የእንግዴ ልጅ” አበዛዙ ምን ይሉት አዚም እንደሆነ አልገባንም፣ ሊገባንም አልቻለም፣ ወደፊትም ይገባን እንደሆን እርግጠኛ ለመሆን አዳግቶናል።
ኢትዮጵያ ሆይ! አዲሱ የእገታና የታጋቾች ድራማ መጋረጃ የሚዘጋው መቼና እንዴት ነው? ያልገባንን መጠየቅ፤ አንቺም እንዲገባን መመለስ “በሕገ መንግሥትሽ ወርቃማ የዲሞክራሲ ቅብ መጽሐፍ” ውስጥ በዝርዝር የቀረበልን “ሜኑ” ስለሆነ “በሕግሽ አምላክ!” ብለን የምንጮኸው መፍትሔ እንድትሰጭን ነው። ዘንግተሸው ከሆነም ስምሽ የተጠቀሰበትን የዋስትና አንቀጽ ከራስሽ ሕገ መንግሥት እንደሚከተለው እናስታውስሻለን።
“ኢትዮጵያ ባጸደቀቻቸው ዓለም አቀፍ ስምምነቶች እና በሌሎች የኢትዮጵያ ሕጎች በሰው ላይ የተፈጸሙ ወንጀሎች ተብለው የተወሰኑትን ወንጀሎች፣ የሰው ዘር የማጥፋት፣ ያለ ፍርድ የሞት ቅጣት እርምጃ የመውሰድ፣ በአስገዳጅ ሰውን የመሰወር፣ ወይንም ኢ-ሰብዓዊ የድብደባ ድርጊቶችን በፈጸሙ ሰዎች ላይ ክስ ማቅረብ በይርጋ አይታገድም። በሕግ አውጭው ክፍልም ሆነ በማንኛውም የመንግሥት አካል ውሳኔዎች በምሕረት ወይንም በይቅርታ አይታለፉም።” (አንቀጽ 28፡1) እኛ ልጆችስ ብሶታችንን ሳንገደብ ዘርዝረን አራግፈንብሻል፤ አንቺስ ምን መልስ ትሰጭናለሽ? በትዕግሥት እንጠብቃለን። ሰላም ይሁን።
(በጌታቸው በለጠ /ዳግላስ ጴጥሮስ)
gechoseni@gmail.com
አዲስ ዘመን ታኅሣሥ 1 /2015