የፊፋው ፕሬዚዳንት ጂያኒ ኢንፋንቲኒሆ የኳታሩ 2022 የአለም ዋንጫ ከዚህ በፊት ከተካሄዱት ሁሉ የአለም ዋንጫ ውድድሮች ምርጡ መሆኑን ሰሞኑን ተናግረዋል። ‹‹ሁሉንም የዓለም ዋንጫ ጨዋታዎች ተመልክቻለሁ እናም በግልፅ ይህ በዓለም ዋንጫ ታሪክ የምንግዜውም ምርጥ የምድብ ጨዋታዎች የታየበት መድረክ ነው። በዚህም መሰረት የዓለም ዋንጫው ቀሪ ጨዋታዎች እጅግ በጣም ተስፋ ሰጪ እና አጓጊ እንዲሆኑ ያደርገዋል፣በእውነቱ እስካሁን የተመለከትነው የኳታሩ ዓለም ዋንጫ ብዙ አስደናቂና ሊታመኑ የማይችሉ ትዝታን የሚፈጥሩ ጨዋታዎችን አስመልክቶናል›› ሲሉ ፕሬዘዳንቱ ለካታር አድናቆታቸውን ገልፀዋል፡፡
ባለፉት ሶስት ሳምንታት ገደማ ስኬታማ የአለም ዋንጫ ጨዋታዎችን አስተናግዳ ከዛሬ ጀምሮ የሩብ ፍጻሜ ፍልሚያዎችን የምታካሂደው ኳታር ከተጠበቀው በላይ ስኬታማ ውድድር ማሰናዳቷን በርካቶች ምስክርነታቸውን ሰጥተዋል። የአለም ዋንጫው ስኬታማ መስተንግዶ የፈጠረባት ትልቅ ተነሳሽነትም የአለማችንን ታላቅ የስፖርት መድረክ ኦሊምፒክ ለመጀመሪያ ጊዜ በመካከለኛው ምስራቅ ለማሰናዳት ፍላጎት አሳድሮባታል። በዚህም እኤአ የ2036 ኦሊምፒክን በመዲናዋ ዶሃ ለማዘጋጀት የሚያስችላትን ጨረታ ለማቅረብ ጉዳዩን በትኩረት እንደያዘችው ዘገባዎች አመልክተዋል።
ኳታር የአለም ዋንጫውን ለማዘጋጀት ከፊፋ ይሁንታ ስታገኝ ውድድሩ ወትሮ የሚካሄድበት የሰኔ ወር መጨረሻ በአገሪቱ ከፍተኛ ሙቀት ያለበት ከመሆኑ ጋር ተያይዞ ትልቅ ስጋት አድሮ ነበር። ይሁን እንጂ ይህን ስጋት ለመቅረፍ ትንሿ ከበርቴ አገር ኳታር ስቴድየሞቿ በዘመናዊ አየር ማቀዝቀዣዎች እንዲታገዙ ከማድረግ ባሻገር የአለም ዋንጫው ከሰኔ ይልቅ ህዳር ወር ላይ እንዲካሄድ ማድረግ ችላለች። በዚህም ስኬታማ ሆና ከሙቀት ጋር በተያያዘ ያለውን ትችትና ስጋት ማስቀረት ችላለች። አሁንም የ2036 ኦሊምፒክን ለማዘጋጀት ስታስብ ታላቁ የስፖርት መድረክ ከሚካሄድበት ሐምሌና ነሐሴ ወር ወደ ህዳር እንዲመጣ በማሰብ መሆኑን ሚረር ትናንት ያወጣው ዘገባ ጠቁሟል።
ኳታር የአለም ዋንጫውን ባማረና በደመቀ ሁኔታ እያስተናገደች በማገባደድ ላይ ብትገኝም ከጅምሩ አንስቶ በተለይም በምእራባውያን መገናኛ ብዙሃኖች ከሰብአዊ መብት አያያዝ፣ከሴቶችና ስደተኞች መብት እንዲሁም ለአለም ዋንጫው ስቴድየሞች ግንባታ ከሌላ አገራት በሄዱ ሰራተኞች ሞት ጋር በተያያዘ እየተብጠለጠለች ነው። ይህ ጉዳይ አሁንም ኳታር ኦሊምፒክን የሚያክል ግዙፍ ውድድር ለማዘጋጀት በምትሄደው ርቀት እንቅፋት ሊሆንባት እንደሚችል ዘገባው ጠቁሟል። የአለም ዋንጫው ስኬታማ መስተንግዶና የገነባችው መሰረተ ልማት ግን ኳታር ኦሊምፒክን ለማዘጋጀት ላላት ፍላጎት አንድ ትልቅ ነጥብ እንደሚያስቆጥርላት ይጠበቃል።
ዘሰን ያወጣው መረጃ እንደሚያመለክተውም ዶሃ በአለም ዋንጫው ምክኒያት በተጋነነ ወጪ የዘረጋቻቸው መሰረተ ልማቶች ወደፊት ኦሊምፒክን በመጠነኛ ወጪ ለማስተናገድ እንደሚያስችላትና ለዚህም አቅምና ብቃቱ እንዳላት ይህ የአለም ዋንጫ ማሳያ መሆን ችሏል።
ዶሃ የበጋ ኦሊምፒክን በብቸኝነት ለማዘጋጀት ፍላጎት ያላት ቢሆንም ከሳውዲ አረቢያ ጋር በጥምረት እንድታዘጋጅ የአለም አቀፉ ኦሊምፒክ ኮሚቴ ግፊት ሊያደርግባት እንደሚችል ተጠቁሟል። ይህ ደግሞ ዶሃና ሪያድ በፖለቲካ አይንና ናጫ ከመሆናቸው ጋር ተያይዞ ላይሳካ የሚችልበት እድል ጠባብ አይደለም። የ2036 ኦሊምፒክን ለማዘጋጀት የሕንዷ ሙምባይ፣የኢንዶኔዢያዋ ጃካርታና የቱርኳ ኢስታንቡል ፍላጎት እንዳላቸው መረጃዎች የሚጠቁሙ ሲሆን ዶሃ ይህን ወርቃማ እድል ለማግኘት ትልቅ ፈተና ማለፍ ይጠበቅባታል።
ይሁን እንጂ ዶሃ ከተፎካካሪዎቿ ከተሞች አኳያ ለዘንድሮው አለም ዋንጫ የዘረጋችው መሰረተ ልማትና አስደናቂ ስቴድየሞቿ አሁንም ኦሊምፒክን ለማዘጋጀት ሚዛን የሚደፋ የበላይነትን እንድትይዝ ሊያደርጋት ይችላል። ኳታር የተሳካ የአለም ዋንጫ ማዘጋጀቷ ከእግር ኳስ የዘለለ ጉዳይ እንደማይሆንና ሌሎች የሚነሱባትን ጥያቄዎች መመለስ እንደማይችል የሚሞግቱም ቁጥራቸው ትንሽ አይደለም።
የ2036 ኦሊምፒክ አዘጋጅ አገርን የአለም አቀፉ ኦሊምፒክ ኮሚቴ መርጦ ይፋ ከማድረጉ በፊት ዶሃ የውድድሩን ስርጭት የሚያስተላልፉ የቴሌቪዥን ጣቢያዎችን እንዲሁም ስፖንሰሮችን ከወዲሁ ማሳመን እንደሚጠበቅባት የሚረር ዘገባ ጠቁሟል።
ቀጣዮቹ ሁለት የበጋ ኦሊምፒክ ውድድሮች በፈረንሳይ ፓሪስ እንዲሁም በአሜሪካ ሎሳንጀለስ እንደሚካሄዱ የሚታወቅ ሲሆን የ2032 ኦሊምፒክንም የአውስትራሊያዋ ብሪስቤን እንድታሰናዳ የአለም አቀፉ ኦሊምፒክ ኮሚቴ ይሁንታ ሰጥቷታል።
ቦጋለ አበበ
አዲስ ዘመን ዓርብ ኅዳር 30 ቀን 2015 ዓ.ም