ሐዋሳ:- ባለፉት አምስት ዓመታት ብቻ በሁሉም የኢትዮጵያ መግቢያ በሮች 3ነጥብ 737 ቢሊዮን ብር የሚያወጡ እቃዎች በኮንትሮባንድ መንገድ ሊገቡና ሊወጡ ሲሉ መያዛቸውን የገቢዎች ሚኒስቴር አስታወቀ፡፡ ሕገወጥ የጦር መሳሪያዎችን በስፋት እየገቡ መሆኑንም ጠቅሷል፡፡
የገቢዎች ሚኒስቴር በኮንትሮባንድ ንግድ ዙሪያ ትናንት በሐዋሳ ከተማ ከባለድርሻ አካላት ጋር ተወያይቷል፡፡ በወቅቱ የውይይት መነሻ ጽሁፍ ያቀረቡት የገቢዎች ሚኒስትር ዴኤታ አቶ ዘመዴ ተፈራ እንደተናገሩት፤ ከ2006 ዓ.ም እስከ 2010 ዓ.ም ድረስ ብቻ 3ነጥብ2 ቢሊዮን ብር የሚያወጡ እቃዎች ሊገቡ ሲሉ፤ በተመሳሳይ 537 ሚሊዮን ብር የሚያወጣ ዕቃ ከአገር ሊወጣ ሲል በድምሩ 3ነጥብ 737 ቢሊዮን ብር የሚያወጡ የኮትሮባንድ እቃዎች ተይዘዋል፡፡
«በአገራችን ኮንትሮ ባንድ እና ህገወጥ ንግድ ከጊዜ ወደጊዜ እየተባባሰ መጥቶ ልንወጣው ከማንችለው ጫፍ ደርሰናል» ያሉት ሚኒስትር ዴኤታው፤ ይህም በአገሪቱ ኢኮኖሚያዊ እንቅስቃሴ ላይ እያሳደረ ካለው አሉታዊ ተፅዕኖ ባሻገር ለማህበራዊና ፖለቲካዊ ችግሮች ምንጭ እየሆነ መምጣቱን አስረድተዋል፡፡
በተጨማሪም የታክስ አስተዳደር ሥርዓቱን እየተፈታተነ የሀገር ውስጥ ገበያና ኢንቨስትመንት እንዲዳከም በማድረግ ህጋዊ ነጋዴውን ከገበያ ውጭ በማድረግ አሳሳቢ ደረጃ መድረሱን ተናግረዋል፡፡በህገወጥ መንገድ እየገቡ ካሉ እቃዎች ውስጥ በዋናነት ጊዜ ያለፈባቸውና ደረጃቸውን ያልጠበቁ መድኃኒቶችና ምግብ ነክ ሸቀጦች፤ እንዲሁም አደንዛዥ እፆች በህብረተሰቡ ጤና ላይ ከፍተኛ ተፅዕኖ እየፈጠሩ መሆኑን ጠቁመዋል፡፡
በሌላ በኩልም ፀረ ሰላም ኃይሎች በአገሪቱ የመጣውን ፖለቲካዊ ለውጥ ለመቀልበስ በተለያዩ የረቀቁ ዘዴዎች ተጠቅመው ሕገወጥ የጦር መሳሪያዎችን በስፋት እያስገቡ መሆናቸውን ሚኒስትር ዴኤታው አስታውሰዋል፡፡ ይህም አሸባሪነትን ፋይናንስ በማድረግ አካባቢን፣ አገርንና አህጉርን የማተራመስ ሚና እየተጫወተ እንደሚገኝ ጠቁመዋል፡፡ በተለይም በሀገሪቱ አንዳንድ ክልሎች ለእርስ በርስ ግጭት ምክንያት እየሆነ ከመምጣቱ ባሻገር አለመረጋጋትን በመፍጠር ለዜጎች ደህንነት ስጋት መሆኑንም ገልጸዋል፡፡
እንደ ሚኒስትር ዴኤታው ገለጻ፤ ትላልቅ ኮንትሮባንዶች ላይ ትኩረት ያለማድረግ ችግሩን ከመሰረቱ ለመፍታት የአስፈፃሚ ተቋማት ቁርጠኝነት ማነስ፤ እና በቅንጅት የመስራት ችግር ለህገ ወጥ ንግዱና ኮንትሮባንድ መስፋፋት አብይ ምክንያቶች ናቸው፡፡ በተጨማሪም በባለሙያዎች እና በፍትህ አካላት የሥነምግባር ግድፈቶች፣ የአቅምና ሎጅስቲክ እጥረት ችግሩን አባብሰውታል፡፡
የገቢዎች ሚኒስትር ወይዘሮ አዳነች አቤቤ በበኩላቸው እንደተናገሩት፤ መድረኩ፣ ባለድርሻ አካላት የሀገሪቱ ኢኮኖሚ የጀርባ አጥንት የሆነው የገቢ አሰባሰቡ ሥርዓት በኮንትሮባንድ ንግድ እየተዳከመ መሆኑን ተገንዝበው የበኩላቸውን ሚና እንዲወጡ ለማድረግ ያለመ ነው፡፡ በመሆኑም ሁሉም አገር ወዳድ ህዝብ ኮንትሮባንድ እና ህገ ወጥ ንግድ በራስ ላይ የተቃጣ ኢኮኖሚያዊ ውንብድና መሆኑን ሊገነዘብ ይገባል፡፡ ከመንግሥት ጋር በመሆንም ህገ ወጦችን በቁርጠኝነት መከላከልና በህግ ተጠያቂ ማድረግ ከህብረተሰቡ የሚጠበቅ ተግባር ነው፡፡
በመድረኩ የተሳተፉ ባለድርሻአካላት በበኩላቸው ህገወጥ ንግድ እና ኮንትሮባንድ መባባስ በዋነኝነት የከፍተኛ አመራሩ ቁርጠኝነት ማነስ መሆኑን ተናግረዋል፡፡ በተጨማሪም ከቅርብ ጊዜያት ወዲህ ጉምሩክ ላይ ለሚሰሩ የፖሊስ አባላት የሚሰጠው ማበረታቻ በመቅረቱ አባላቱ ህገ ወጥ መሳሪያ ሲገባ ጭምር ቸል የማለት ዝንባሌ እንደሚታይባቸው ጠቁመዋል፡፡
ወይዘሮ አዳነች በኩላቸው፤ በተሳታፊዎች የተነሱት ቅሬታዎች ተጨባጭነት ያላቸው መሆኑን ተናግረዋል፡፡ በተለይም የከፍተኛ አመራሩ ቁርጠኝነት ችግር መኖሩን አምነው ይህንን ለመፍታትም ተቋሙን በሚኒስትር እና በኮሚሽን ደረጃ እንዲዋቀር በማድረግ ስር ነቀል ሪፎርም በማካሄድ በአመለካከት ላይ ያለውን ሰፊ ክፍተት ለመሙላት እየተሰራ እንደሆነ ጠቁመዋል፡፡ በተመሳሳይም በአስፈፃሚው አካል ላይ ያለውን የአቅም ችግር ለመፍታት አሰራሩን በቴክኖሎጂ የማዘመን ሥራ እየሰራ መሆኑን ገልጸዋል፡፡
የጉምሩክ ኮሚሽን ምክትል ኮሚሽነር አቶ መላኩ ፋንታ በበኩላቸው፤ ከዚህ ቀደም ለፖሊስ አባላት ይሰጥ የነበረው ማበረታቻ እንዲቆም የተደረገው ህገወጥ ተግባራትን የመከላከል ኃላፊነት ያለባቸው በመሆኑ ማበረታቻው እንደማያስፈልግ በመታመኑ መሆኑን ተናግረዋል፡፡ ከዚያ ባለፈ ግን በኮንትሮባንድ የሚገኘውን ገቢ ተቋሙን ለማጠናከር እንዲውል መወሰኑን አስገንዝበዋል፡፡
አዲስ ዘመን ህዳር 24/2011
በማህሌት አብዱል