ከ2010 ዓ.ም በፊት በነበሩት ዓመታት የህዳር ወር ሙሉውን የብሄር ብሄረሰቦች ወር ነበር ማለት ይቻል።ህዳር 29 ቀኑ በሚከበርበት ክልል ስቴዲየም ውስጥ የመንግስት ባለሥልጣናት ይገኛሉ።ከህዳር 29 በፊት ባሉት ሳምንታት ሁሉ የሚወራው ስለህዳር 29 ነው።የመንግስት መገናኛ ብዙኃን ሰፊ ሽፋን ይሰጡት ነበር።የግል መገናኛ ብዙኃን እና የመንግስት ተቃዋሚዎች ደግሞ ‹‹ለፖለቲካ ፍጆታ ነው›› እያሉ ይቃወሙት ነበር።
ባለፉት አራት ዓመታት ደግሞ ብዙ ነገሮች እንደገና እየተስተካከሉ ስለነበር በፊት በነበረው ልክ ሰፊ ሽፋን ሲሰጠው አልነበረም።ከባለፉት ሦስት ዓመታት አንፃር የዘንድሮው የተሻለ ትኩረት የተሰጠው ይመስላል።ከቀኑ ቀደም ብሎ ባሉ ሳምንታት የብሄር ብሄረሰቦች ቱባ ባህሎችና አከባበሩ ሽፋን ሲያገኙ አስተውለናል።
ለመሆኑ ግን ከዚህ በፊት በነበሩት ዓመታት የብሄር ብሄረሰቦች ቀን የብሄር ብሄረሰቦችን ባህልና ጥበብን የሚያሳይ ነበር?
ኢትዮጵያ የበርካታ ብሄር ብሄረሰቦች ባህልና ጥበብ ስሪት ናት።ዲያቆን ዳንኤል ክብረት በብሄራዊ ቴአትር በተደረገ አንድ መድረክ ላይ የተናገረውን እዚህ ላይ ልጥቀስ።ኢትዮጵያ የብሄር ብሄረሰቦች ስሪት መሆኗን በሰውነታችን ቅርጽና አቅጣጫ አመሳስሎ ነበር የገለጸው።ጭንቅላታችን በሰሜን ይገለጻል።የሰሜን ኢትዮጵያ አናት የሆነው የትግራይ ክልል አካባቢዎች ጭፈራ የአንገትና የጭንቅላት እንቅስቃሴ ነው።የታችኛው ሰሜን የሆነው የአማራ ክልል አካባቢዎች ጭፈራ ደግሞ በትክሻ እንቅስቃሴ የሚታወቅ ነው።የመሐል ኢትዮጵያ አካባቢዎችን የሚይዘው የኦሮሞ ጭፈራ ደግሞ በወገብ እንቅስቃሴ የሚታወቅ ነው።የአገራችን የደቡብ ክፍል የሆኑት የደቡብ ብሄር ብሄረሰቦች ደግሞ በዳሌ እና በእግር እንቅስቃሴዎች የሚታወቁ ናቸው።ኢትዮጵያ የእነዚህ ስሪት ናት፡፡
የኢትዮጵያ መለያዎች የሚባሉት የብሄር ብሄረሰቦችን መለያዎች፣ የዕደ ጥበብ ውጤቶች፣ የሽምግልና እና የስነ ቃል ጥበቦች የያዙ ናቸው። የአፋር ዳጉ ባህላዊ የመረጃ ሥርዓት፣ የኦሮሞ ባህላዊ የገዳ ሥርዓት፣ የራያ የ‹‹ዘወልድ›› ሥርዓት እና የመሳሰሉት ውጤቶች ናት ኢትዮጵያ።
እንግዲህ የሚያሳዝነው ነገር ‹‹ለብሄር ብሄረሰቦች ማንነት ቆሜያለሁ›› ሲል የነበረው ኢህአዴግ እነዚህን ነገሮች አለማስተዋወቁ ነው። ብልጽና አስተዋውቋል ወይ የሚለውን የዘንድሮውን ጨምሮ ወደፊት የምንታዘበው ይሆናል።
እንግዲህ በወቅቱ ኢህአዴግን ይወቅሱት የነበሩ አካላት ትክክል ነበሩ ማለት ነው።የተጠቀመው ለፖለቲካ ፍጆታ ብቻ ነበር።ለዚህ ደግሞ ግልጽ ማሳያዎች አሉ።ከቀበሌ ጀምሮ እስከ ፌዴራል ድረስ ይደረግ የነበረው ፖለቲካዊ ስብከት እንጂ የብሄር ብሄረሰቦችን ባህልና ጥበብ ማስተዋወቅ አልነበረም።የአሁኑ መንግሥት ከዚያ ስህተት መማር አለበት።
በዕለቱ ህዳር 29 ቀን የሚከበረውን ዋናውን ዝግጅት እንኳን ማስታወስ በቂ ማሳያ ነው።በመላው አገሪቱና በመላው ዓለም በቀጥታ ሥርጭት የሚተላለፈው የብሄር ብሄረሰቦችን ጥበብና ባህል የሚያሳይ ጥናት ወይም ውይይት ሳይሆን የፖለቲከኞች የፖለቲካ ስብከት ነበር።ለዚያውም አንዱን አጥቂ አንዱን ተጠቂ በማድረግ አሁን ድረስ ማባሪያ የሌለው ግጭት ውስጥ እንዲገቡ የሚያደርጉ ንግግሮች ነበሩ የሚደረጉ።የሚደሰኩረው ግን በተቃራኒው ነበር።ከሦስት ሺህ ዘመናት በላይ የኖሩ ብሄር ብሄረሰቦችን ‹‹እኔ ነኝ የፈጠርኳቸው›› ማለት ነበር የቀረው።በብሄር ብሄረሰቦች ቀን በሚደረገው የኢህአዴግ ስብከት መሰረት፤ ቋንቋዎች ሁሉ የተፈጠሩት ከ1983 ወዲህ ነው፣ ሃይማኖት ሁሉ የተፈጠረው ከ1983 ወዲህ ነው፣ የብሄር ብሄረሰቦች አልባሳት ሁሉ የተፈጠሩት ከ1983 ወዲህ ነው፤ በአጠቃላይ የብሄር ብሄረሰቦች ፈጣሪ እኔ ነኝ እያለ በተቃራኒው ግን ሲጨፈልቅ ነበር።ቀላል ምሳሌ እናንሳ፡፡
በዕለቱ ህዳር 29 ቀን እንኳን ትርዒቱ በትክክል አይቀርብም።እዚህ ላይ ሁለት ስህተት ነበር ያለው።አንደኛው፤ በቂ ጊዜ ተሰጥቶት የብሄር ብሄረሰቦች ባህልና ጥበብ በትክክል አይታይም ነበር።ሁለተኛ፤ አቅራቢዎች ትክክለኛ የባህሉ ከዋኞች ሳይሆኑ በአበል የሚመጡ ካድሬዎች ናቸው።በየዓመቱ ዝግጅቱ ላይ የሚታደሙት ተመሳሳይ ሰዎች ናቸው።የሌላ ብሄር ተወላጅ ሆነው የአንዱን ብሄር ልብስ ለብሰው አስመስለው ያቀርባሉ።ያ ደግሞ ትወና እንጂ ትክክለኛውን የብሄሩን ወካይ ማሳየት አይደለም።ስለዚህ ልቦልድ አሳዩን እንጂ ባህል አላሳዩንም።
የአንዲት አገር ምንነት የሚታወቀው አገሪቱ ውስጥ ባሉ መገለጫዎች ነው።የህንድ ባህል፣ የናይጀሪያ፣ የሶማሊያ… እያልን የምንገልጸው በመገለጫዎቻቸው ነው። አንድ ምልክት ታይቶ ‹‹ይሄ የእገሌ አገር ነው›› ይባላል።የኢህአዴግ ህዳር 29 ግን እነዚህን ነገሮች ሲጨፈላልቅና ሲያድበሰብስ እንጂ ለዓለም አቀፉ ማህበረሰብ ሲያስተዋውቅ አልነበረም። ያስተዋወቀው ብሄር ብሄረሰቦችን በጥርጣሬና በጥላቻ እንዲተያዩ የሚያደርግ ዲስኩር ነው።
በነገራችን ላይ ከለውጡ ወዲህ በተከበሩ የብሄር ብሄረሰቦች ቀን ላይ የቁንጅና ውድድር መካሄዱን አስታውሳለሁ።በቁንጅና ውድድሩ አሸናፊ የሚሆኑት ቆነጃጅት የሰላም አምባሳደር ይሆናሉ።የሰላም አምባሳደር ሆነውም በየክልላቸው ከወጣቶች ጋር ስለሰላም ይወያያሉ። እንዲህ ሲሆን ጉዳዩ ለወጣቶች ቅርበት ይኖረዋል፤ ምክንያቱም ወጣቶች ለኪነ ጥበባዊ ጉዳዮች ቅርብ ናቸው።በጥበባዊ ሥራዎች ቀልባቸው ይሳባል።
ከዚህ በፊት ይከበር የነበረው የብሄር ብሄረሰቦች ቀን ምንም ፋይዳ አልነበረውም ማለት ግን አይቻልም።ምንም እንኳን ጭፈራ እና የፖለቲካ ዲስኩር ቢሆንም እግረ መንገዱን ግን ብዙ ነገሮችን አስተምሯል።በከፊልም ቢሆን ብሄር ብሄረሰቦችን አስተዋውቋል።
የአንደኛ ደረጃ እና የሁለተኛ ደረጃ ትምህርት ቤት ተማሪ እያለሁ የብሄር ብሄረሰቦች ቀን ሲከበር ትኩረት ሰጥቼ ነበር የምከታተለው።በፊት በሬዲዮ የምሰማቸው የምን ብሄር እንደሆነ የማላውቃቸው ደስ የሚሉኝ ሙዚቃዎች ነበሩ።በእንዲህ አይነቱ አጋጣሚ ግን ጋዜጠኛው ስለዚያ ዘፋኝ ታሪክና የማንን ብሄር እንደተጫወተ ሲናገር ‹‹ኧኻ ለካ ይሄ ዘፈን የእንትን ብሄር ነው›› እያልኩ ማወቅ እጀምራለሁ።
ሌላው ደግሞ ስለኢትዮጵያ ማሳወቁም ጥሩ አጋጣሚ ነበር።ትምህርት ቤት ውስጥ የእገሌ ዋና ከተማ ማነው? እገሌ ተራራ የት ይገኛል? እግሌ ዋሻ የት ነው? የሚሉ ጥያቄዎችን እንጠያየቅ ነበር፤ ፈተናም ይመጡ ነበር።ታዲያ እነዚህን የምናውቃቸው በእንዲህ አይነት አጋጣሚ ሲነገሩ ነበር። የአገርን ታሪክ ማወቅ ማለትም ይሄ ነው።
በተለይም የሁለተኛ ደረጃ እና መሰናዶ ትምህርት ቤት እያለን ደግሞ ከዚህም አለፍ ያሉ ነገሮችን መረዳት እንጀምራለን።ለምሳሌ የሚቀርቡ ጥናቶችን፣ የሚደረጉ ውይይቶችን፣ ስለ ህገ መንግስት ማወቅ መከታተል ጀምረናል። ችግሩ ግን ነገሩ ለፖለቲካ ፍጆታ መሆኑን እየተረዳን ስመጣ የበፊቱን ያህል በተመስጦ የምንከታተለው አልሆነም።‹‹አሁን እንዲህ ባይባል ምን ችግር አለው?›› ማለት ጀመርን። ኢህአዴግ በልጆች አዕምሮ ውስጥ የራሱን ዓላማ እያሰረጸ ነበር ማለት ነው፡፡
የብሄር ብሄረሰቦች ቀን ሲከበር ዘንድሮ 17ኛ ዓመቱ ነው።ከግማሽ በላይ የሚሆኑትን በቀጥታ ሥርጭት ተከታትያለሁ።አንደኛውን ደግሞ በአካል የሚከበርበት ስቴዲየም ውስጥ ሆኜ ተከታትያለሁ።ከዕለተ ቀኑ በተጨማሪም በዓሉ ሰሞን የሚዘገቡ ዘገባዎችንና የሚሰሩ ፕሮግራሞችን ተከታትያለሁ። በእነዚህ ሁሉ ውስጥ ጥሩ ነገሮች ቢኖሩም ብዙ የታዘብኳቸው ነገሮችም አሉ።
እስኪ ከስሙ እንነሳ፤ ‹‹የብሄር ብሄረሰቦን ቀን›› ማለት ምን ማለት ነው? ጠለቅ ያለ ሳይንሳዊ ትንታኔ የሚጠይቅ አይመስለኝም።የብሄር ብሄረሰቦች ቀን ማለት በቃ ብሄር ብሄረሰቦች ባህላቸውን የሚያሳዩበት ማለት ነው።እርግጥ ነው በውስጡ ብዙ ነገሮች ይኖራሉ።ግን በዚህ ዕለት እውን የብሄር ብሄረሰቦች ቀን ይታያል? ነገሩን ግልጽ እናድርገው።
በብሄር ብሄረሰቦች ቀን የሚታየው ትርዒት ትክክለኛ እዚያ አካባቢ ያሉ ማህበረሰቦች የሚያሳዩት ሳይሆን በአማተርም ይሁን በትልልቅ አርቲስቶች ትወና ነው።ይሄ ደግሞ ቴአትር ወይም ፊልም እንጂ ትክክለኛው ባህል አይሆንም።እርግጥ ነው አቅራቢዎቹ እዚያው አካባቢ ተወልደው ያደጉ ሊሆኑ ይችላሉ፤ ዳሩ ግን በየባህል ማዕከሉ የሚሰሩ የኪነት ቡድን አባላት ናቸው።ከኪነት ቡድን አባላቱ በላይ የአካባቢውን ባህል የሚገልጹት ነዋሪዎች ናቸው።
ይሄም ይሁን ግደለም፤ ትርዒቱን የሚያሳዩት በየዓመቱ ተመሳሳይ ሰዎች ናቸው።የመጀመሪያው ዓመት አዲስ አበባ የሄደው በዓመቱ ሐዋሳ፣ ቀጥሎ ድሬደዋ፣ ቀጥሎ መቀሌ…. እያለ በሁሉም ቀኖች ላይ የሚገኝ አይጠፋም።ይሄ ሁሉ ሲሆን እንግዲህ ሌሎች አልተሳተፉም ማለት እኮ ነው።ይሄ እኮ ቱባ(Typical) የሚባለው ባህል ነው፤ ስለዚህ ለምን በከያኒያን ይቀርባል? በከያኒያን (ታዋቂ አርቲስቶች) የሚቀርብበት ምክንያት መንግስት በሚፈልገው ልክ ለማቅረብ እንዲያመቸቸው ነው።በየመሃሉ ፖለቲካዊ መልዕክቶች እንዲተላለፉ ነው።በራሳቸው በባህሉ ባለቤቶች ቢቀርብ ግን ቱባውን ባህል ማየት ይቻል ነበር።
እሺ ይሄም ይሁን ብለን እንለፈው።በከያኒያኑ የተሰራው ራሱ በአግባቡ ይታያል? ለዚያ ዝግጅት ከስድስት ወር ያላነሰ ጊዜ ይባክንበታል።ለዝግጅቱ ጊዜና ገንዘብ ባክኗል።ዝግጅቱን ለማሳየት እስከ 1 ሺህ ኪሎ ሜትር ርቀት የሚጓዙም አሉ።ይሄ ሁሉ ድካም ተደክሞበት ግን ዝግጅቱ አይታይም።እርግጥ ነው ማታ በዋዜማ የሚደረግ ዝግጅትም አለ፤ ያ የዋዜማው ዝግጅት ግን የታዋቂ የኪነ ጥበብ ሰዎች ሥራ የሚቀርብበት ነው።በሌላ በኩል ደግሞ በዋዜማው ዝግጅት ላይ ባለሥልጣናትና የተለዩ ሰዎች ብቻ የሚገኙበት ነው።
ዋናው ዝግጅትና ብዛት ያለው ታዳሚ ሚገኘው በዕለቱ ነው።በዚያን ቀን ግን ያ ሁሉ የተደከመበት ሥራ አይታይም።የብሄር ብሄረሰቦችን የአለባበስ፣ የአጨፋፈርም ሆነ ሌላ ትዕይንት ለማየት የሚገባ ሰው ማየት አይችልም።ይህ ሁሉ የሚሆነው የሚያሳዩበት መድረክ ስለሌለ ነው።ይሄ ማለት ሙሉ በሙሉ አያቀርቡም ማለቴ አይደለም።
መድረክ መሪው ‹‹አሁን የእገሌ ብሔር ባህላዊ ትርዕቱን እያሳየ ያልፋል›› ይላል።መጀመሪያ ላይ የተጠራው ምናልባት ትንሽ የመታየት ዕድል ያገኝ ይሆናል።ከዚያ ቀጥሎ ግን እያከታተለ ‹‹ቀጥሎ የእገሌ ብሄር …›› እያለ ሁሉንም ይጠራል።አንዱ በአንዱ ላይ እየተደራረበ የሚያልፈው ብሄር የማን እንደሆነ አይታወቅም።እንዲያውም መድረክ መሪው የሚሰጠው ማብራሪያና በክቡር ትሪቡኑ ሥር የሚያልፈው ብሔር ሌላና ሌላ ሊሆን ይችላል።ለምሳሌ እሱ በፍጥነት የትግራይን ጠርቶ ቀጥሎ የአማራን ቀጥሎ የኦሮሚያን ሊጠራ ይችላል።ስለ ሶማሌ ብሄር እያወራ የሚያልፈው ግን ገና የኦሮሚያ ወይም የአማራ ሊሆን ይችላል።ታዲያ በዚህ ሁኔታ ቀኑ የብሄር ብሄረሰቦች ባህል ታየበት ነው የሚባል?
ቢያንስ ቢያንስ አንድ ክልል ውስጥ ያሉ ብሔሮች ብቻ እንኳን በአንድ ጊዜ ቢያልፉ። እነርሱም ገለጻ እየተደረገ ተራ በተራ ቢሆን።አንዱን ክልል ጨርሶ ቦታ ከያዘ በኋላ ሌላውን ክልል ደግሞ ማሳለፍ። ይህ የማይመች ከሆነ መተው እንጂ እያደበላለቁ ማሳለፍ ምንም የሚገልጸው ነገር የለውም፤ ምናልባትም የሚያውቁት የዚያው አካባቢ ሰዎች ናቸው። ለእነርሱ ከሆነ ደግሞ ያን ያህን ጊዜና ገንዘብ ማባከን ለምን አስፈለገ? በዚህ ሁሉ ውስጥ የምንረዳው ነገሩ የፖለቲካ ፍጆታ እንደነበር ነው።
ከዚህ በፊት የነበረውን የብሄር ብሄረሰቦች ቀን አከባበር ማስታወስ ያስፈለገበት ምክንያት፤ አቀራረቡ መቀየር እንዳለበት ለማሳየት ነው።የብሄር ብሄረሰቦችን ባህልና ጥበባት በተመረጡ አምባሳደሮች አማካኝነት ዓመቱን ሙሉ ማስተዋወቅ የአገሪቱ ብሄር ብሄረሰቦች እንዲተዋወቁ ያደርጋል።ይሄም ሕብረ ብሔራዊ አንድነትን ይፈጥራል። ስለዚህ የብሄር ብሄረሰቦች ቀን የብሄር ብሄረሰቦች ባህልና ጥበባት የሚታዩበት ይሁን። አከባበሩም ከፖለቲካዊ ዲስኩር ይልቅ ቱባ ባህሉን በማሳየት ቢሆን የተሻለ ይሆናል።አገርን ማወቅ ማለት በአገራችን ውስጥ ያሉ ሕዝቦችን ማወቅ ነውና ለማወቅ አብረን እናክብር!
ዋለልኝ አየለ
አዲስ ዘመን ህዳር 29 ቀን 2015 ዓ.ም