ዛሬ ዘውዴ መታፈሪያ እንደልማዱ ብስጭትጭት እያለ ወደ ማምሻ አካባቢ መሸታ ቤት ሲገባ ገብረየስ ገብረማርያምን ሲቆዝም አገኘው።ዘውዴ በረዥሙ ተነፈሰና ከገብረየስ አጠገብ ባለው ወንበር ላይ ሲቀመጥ ተሰማ መንግስቴ እንዳልመጣ ገብቶት ብስጭቱን ዋጥ አደረገ።ዘውዴ፣ ገብረየስን ቆዝሞ ስላየው ከሱ በላይ አዝኖ ይሆናል ብሎ በመገመት ብስጭቱን ገታ አድርጎ ያላበው ቢራ ሲል አዘዘ።ብዙም ሳይዘገይ ተሰማ መንግስቴ በፈገግታ ታጅቦ የዘውዴን እግር ተከትሎ ተቀላቀላቸው።እርሱም የሚጠጣውን አዝዞ ተመሳሰለ።
ተሰማ ሁለቱን የመጠጥ ቤት ጓደኞቹን እያየ ‹‹ እህስ እንዴት ናችሁ? ›› ሲል በመጣበት መንፈስ ፈገግታውን ለማጋራት እየሞከረ ጨዋታውን ጀመረ።ዘውዴ ግን በተቃራኒው ግንባሩን ቋጥሮ ‹‹ ይኸው እንዳለን አለ።በአጥንታችን ብንቀርም ቆመን እየሔድን ነው።›› ብሎ የውስጥ ብስጭቱን በሚያስተነፍስ መልኩ በረዥሙ እ…እፎይ አለ።ገብረየስ ዘውዴን አየት አድርጎት፤ ‹‹ ደግሞ ዛሬ ምን ሆንክ? መቼም ሁሉም ነገር አንተ ላይ ብቻ የሚከሰት ማስመሰል ሥራህ ሆኗል፤ በተማረርክ ቁጥር በየዕለቱ ተጨማሪ የሚያማርር ነገር እያጋጠመህ የህይወት ዘመንህ ሁሉ መራራ እየሆነብህ ነው።›› አለው።
ዘውዴ፣ በገብረየስ ንግግር እየተበሳጨ፤ ‹‹ ከኢትዮጵያ ምድር እንሰው ጤፉ ካልጠፉ እንዴት ማማረሬን አቆማለሁ? ሰውን በሰውነቱ ከማየት ይልቅ መናቅ ወይም ማንጓጠጥ እንደትክክለኛ ሥራቸው ቆጥረውት የስነምግባር ጉድለታቸውን በአደባባይ የሚያሳዩ ባለጌዎች በሞሉባት ዓለም ውስጥ እየኖርኩ እንዴት አልማረርም? ›› ሲል ያማረረውን ጉዳይ ደፋፍኖ ምሬቱን ዓለም አቀፋዊ አደርጎ በደንብ አግዝፎ አቀረበላቸው።
ተሰማ ከት ከት ብሎ ሳቀ።‹‹ የዛሬው ጉዳይህ አገራዊ ብቻ ሳይሆን ዓለም አቀፋዊ ሆኗል ማለት ነው።ስታጋንን ነው ወይስ የገጠመህ ጉዳይ ዓለምን በሙሉ የሚመለከት ሆኖ ነው? ዓለም አንተ ላይ ካደመ በጣም ያዝናናል። አንተ ስትማረር እኛን እንድንስቅ ይጋብዘናል።›› ብሎ ፊቱን አዞረና እያጨበጨበ አስተናጋጁን ጠርቶ በዛው በጋለ ፈገግታ በታጀበው ፊቱ የሚጠጣውን በድጋሚ አዘዘ።
ገብረየስ፣ በተሰማ ንግግር እና በዘውዴ ምሬት ትንሽ ፈገግ ብሎ፤ ‹‹ሰው በሰው ቅቤ በጨው እንደሚባለው መረዳዳት ፍሬያማ ውጤት ያስገኛልና ያማረረህን ግልፅ አድርገህ ብትነግረን መላ ይፈለግልሃል።በተናጥል ራስን ገንጥሎ መማረር ራስን ከመጉዳት ውጪ ምንም ትርፍ የለውም።ለዛውም ቤተሰብን እና አንድ ተቋምን አልፎ አልፎ አገርን ከማማረር በተጨማሪ ዓለምን ማማረር ላይ መድረስ ከባድ ነው።ስለዚህ ከምትማረር ይልቅ ያበሳጨህን አውቀን፤ ብናግዝህ ይሻላል።›› አለው።ገብረየስ ይሔን ያለው ተሰማ የዘውዴን ምሬት እንደተራ ነገር ማየቱ ግጭት እንዳይፈጥር እና የዘውዴ ጉዳይን ችላ ማለትም ሁሉንም ዋጋ ያስከፍላል ብሎ በመስጋቱ ነበር።
ዘውዴ፣ ከገብረየስ ንግግር ከተል አድርጎ ‹‹ ሁሉም ሲሠራ እውነተኛ እና ትክክለኛ ህግን ተከትሎ ሃላፊነትን ከመወጣት ይልቅ በትዕቢት ተወጥሮ ህግ ጥሶ እጅ መንሻን እንደግዴታ እና እንደመብት ማየቱ ያስገርማል።እጅ መንሻ ያልሰጠ አገልግሎት አታገኝም መባሉ ህግ አክባሪን እንዴት እንደሚያበሳጭ አይገባችሁም።ይህ ችግር በኢትዮጵያ ብቻ ሳይሆን በዓለም ላይ መኖሩ ያስገርማል።በጣም የሚያስደንቀው ደግሞ ትናንት ተገልጋይ ሆኖ ሲሰቃይ የነበረው ሰው ‹ተድረው ቢመለሱ የውሃ መንገድ ረሱ› እንደሚባለው ዞሮ ራሱም እጅ መንሻ ጠያቂ መሆኑ በጣም ያስገርማል።›› አለና ንግግሩን በጥያቄ ቀጠለ።
‹‹ የሚሠራ ሥራ ሁሉ እንደታሰበው አጥጋቢ የማይሆነው ለምን ይመስላችኋል? ›› ሲል ለሁለቱም ጥያቄ አቀረበ።ተሰማ ምላሽ ለመስጠት አቆበቆበ፤ ዘውዴም አልጨከነበትም እንዳሾፈበት ቢያውቅም ‹‹ እስኪ ከቻልከው መልሰው።›› ሲል ዕድሉን ለተሰማ ሰጠው።ተሰማ በበኩሉ የዛሬው የዘውዴ ኩራት እና ንግግሩ ፈገግ እያሰኘው፤ ‹‹ በመረዳዳትና በመተባበር ላይ አተኩረን በጋራ ስለማንሰራ ተግባራችን ሁሉ የግል ሩጫ ላይ ስላዘነበለ፤ ህግን ተከትለን ስለማንራመድ ነው።›› ሲል ምላሽ ሰጠ።
‹‹መልሱን ትንሽ ደራርበህ ጭብጡን መላ ቅጥ አሳጣኸው፤ ምላሹ ግን ጥሩ ነው።አንተ ካነሳኸው የኅብረት ሐሳብ ሌላም ሌሎች ችግሮች አሉ።እስኪ ገብረየስም ሞክር ።›› ሲል ዘውዴ፣ ገብረየስ ሃሳብ እንዲሰጥ ጋበዘው።ገብረየስ የተሰጠውን ዕድል ተጠቅሞ የሚገምተውን ‹‹ ማንኛውም ሰው አላፊ ስለሆነ የማይሞት ሥራ መሥራትን እንደገና እንደመወለድ ቆጥሮት የተቻለውን ሁሉ ከመስራት ይልቅ በአፉ ‹ሰውና እንጨት ተሰባሪ ነው› እያለ በተግባር ግን ሞትን በመርሳቱ ስኬታማ መሆን አልቻልንም።›› ሲል ተናገረ።
ዘውዴ ፈገግ አለ።በፈገግታ ውስጥ ቆይቶ መልሶ ‹‹ የሰዎች ምልከታ ያስገርማል።›› ካለ በኋላ፤ እርሱ ሊናገር የፈለገውን በቀጥታ አለመናገራቸው እያስገረመው የሁለቱም የመሸታ ቤት ጓደኞቹ ሃሳብ ከእርሱ ምን ያህል የራቀ እንደሆነ ተረዳ።እርሱም በበኩሉ ሃሳቡን አወሳስቦ መግለፅ ጀመረ።‹‹ ዋናው ጉዳይ ምን መሰላችሁ፤ ትዕቢት ነው።ሁሉም ካለው ዓቅም በላይ ትዕቢተኛ መሆኑ ነው።ትዕቢት ባይኖር እኔ ዛሬ ላይ ያለኝ ሃብት ፣ የዕውቀት አቅምም ሆነ ጤናዬ ከዚህ በላይ የተሻለ ይሆን ነበር።ለሁላችንም ተመሳሳይ ነው።ወደ አገር ሲመጣም ኢትዮጵያ በትዕቢቷ የዓለም ጭራ ሆናለች።ያሏትን ትልልቅ ነገሮች አጥታለች።ይኸው አሜሪካን ሳይቀር በትዕቢቷ ዓለምን ካልተቆጣጠርኩ በማለቷ ብዙ ዋጋ እየከፈለች ነው።›› አለ።
ተሰማ እና ገብረየስ ግራ ተጋቡ።ገብረየስ ‹‹ እኔ በትዕቢቴ ያጣሁትን አላውቅም።ትዕቢተኛ ሆኜ አላውቅም።›› ሲል ተሰማም ‹‹ እኔም ትዕቢተኛ ሆኜ በትዕቢቴ ተጎድቼ አላውቅም።የእኛ ይቅር ኢትዮጵያ በምን አቅሟ በትዕቢቷ ምን አጣች? እገሌስ እገሊትስ ምን በማጣት ላይ ነች? ይህችን ገለጥለጥ ብታደርግልኝ ደስ ይለኛል›› አለ።
ዘውዴ ምላሽ መስጠት ጀመረ።‹‹የኢትዮጵያን ታሪክ በደንብ ካጠናችሁ ጅቡቲም ግዛቷ ነበረች ።በታሪክ አጋጣሚ ጅቡቲን በማጣቷ ምክንያት አሁን ላይ በየዓመቱ አምስት ቢሊየን ዶላር ትከፍላለች።ከጅቡቲም በኋላ ብዙ ነገር አጥታለች።ከዚህ በኋላ ያጣቻቸውን ትልልቅ ነገሮች ከገለፅኩ ገብረየስ ይከፋል።ታላላቅ የሚባሉት ሀገራትም በገዛ ትዕቢታቸው በየአገሩ ጉዳይ ጣልቃ እየገቡ የዜጎቻቸውን ህይወት አደጋ ላይ እየጣሉ ነው።
ይህ አገር ላይ ይባል እንጂ እያንዳንዳችን ላይ የሚታይ ነገር ነው።ሁላችንንም ወደ ኋላ እየጎተተን ይገኛል።በተለይ የእኛ የኢትዮጵያውያን ትዕቢት እየደነደነ በስለት እንደማይበሳ ቆዳ እየጠነከረ ነው።‹ቀጥኜ ቢያዩኝ ጅማት ለመኑኝ› እንደሚባለው ሰውን ቀጥኖ እና አጥሮ ወይም ያደፈ ልብስ ለብሶ ሲያዩ እየናቁ ተገቢውን አገልግሎት የማይሰጡ ስንት ሰራተኞች እንዳሉ ቤት ይቁጠራቸው።ከዚህ ሁሉ ግን ተገልጋይ ተለማማጭ እና እጅ መንሻ ሰጪ መሆን አለበት ብለው ህዝብን ንቀው በህዝብ ላይ የሚጫወቱ ትዕቢተኞችን ማየት እንዴት እንደሚያበግን ልገልፅላችሁ አልችልም።›› አለ።
ገብረየስ ‹‹ ዘውዴ ዛሬ ሰኔና ሰኞ ሳይሆንብህ አልቀረም።መጥፎ አጋጣሚ ደግሞ በማንም ላይ የተለመደ ነው።ብዙ መማረር አያስፈልግም።›› ሲል፤ ዘውዴ ብልጭ አለበት።ቀጠለና ‹‹ ትዕቢት እና ሰው መናቅ በምንም መልኩ የሚያዋጣ አይደለም።ፍየል እንደአቅሟ ታግታለች፤ የትኛውም ሰው እንደአቅሙ በውስጡ ጠቃሚና ለአለም የሚያበረክተው የማይናቅ ትልቅ ሚና አለው።ማንም የማንንም ሚና መወጣት አይችልም።ሁሉም የየራሱ የተፈጠረበት ሚና አለው።ነገር ግን ብዙዎች ይህን አይገነዘቡም። ይህ ካለማወቅ የሚመጣ በሽታ ስለሆነ መታረም አለበት፤ ተፈላጊው ትሁት መሆን ነው። ትህትና ዓለምን ያተርፋል።በሰማይም ያፀድቃል።›› ሲል ፤ ገብረየስ በበኩሉ፤ ‹‹ አሁን ወደ ስብከት መጣህ፤ ይህ ምርጥ ነው።›› በማለት ዘውዴ በሰጠው ሃሳብ ፈገግ እያለ ጨመረና ‹‹ ታዲያ ትህትና ከማን እና ከየት ይጀመር?›› የሚል ጥያቄ አቀረበ።
‹‹ ሁሉም ነገር እየተስተካከለ እና መሰረት እየያዘ የሚመጣው ከቤት ጀምሮ ነው።የእብድ ቀን አይመሽም እንደሚባለው እንዲሁ ማበድ ከቀጠለ መፍትሔ የለም።እኔ እና አንተ ሚስቶቻችን ላይ እና ልጆቻችን ላይ የምናሳየውን ትዕቢት ከቀነስን ልጆቻችንን በትህትና መንገድ ካሳደግን ከዛ ይጀምራል።እየቀጠለ ሲመጣ አገር፤ እየተስፋፋ ሲሔድ አለም ላይ ለውጥ ይመጣል።›› ሲል ዘውዴ ለቀረበለት ጥያቄ ምላሽ ሰጠ።ተሰማ ግን የዘውዴ ሃሳብ አልተዋጠለትም።
‹‹ ትክክል ነው።ህፃናት በትኩስ መንፈስ ነገሮችን ፈጥኖ የማወቅና የመሥራት ፍላጎታቸው ከፍተኛ ቢሆንም የወላጆችንና የታላላቆችን ምክር ይሻሉ።መምከርህ በትህትና እንዲያድጉ መሥራትህ መልካም ነው።ነገር ግን አንደኛ መነሻህን እና ያጋጠመህን አልገለፅክልንም።ሁለተኛ ነገሩን ሁሉ ከትዕቢት ጋር አጣብቀኸው አማራጭ ሃሳብ ማሳጣትህ ትክክል አይደለም።›› ሲል ተሰማ ዘውዴን መሞገት ጀመረ።
ዘውዴ በበኩሉ፤ ‹‹እሺ አስቀድሜ ያጋጠመኝን ልግለፅ፤ ትናንት እኔ እና አምስት ጎረቤቶቼ ቤት የመብራት ሃይል ከተቋረጠ አምስት ቀን እንዳለፈ ነግሪያችሁ ነበር።እንዲሠራልን ብናመለክትም ምላሽ አላገኘንም።አንድ ጎረቤቴ በጨለማ መክረም እንደደከመው፤ ለልጆቹ ምግብ የሚየበስለው፣ ልብስ የሚያጥበው፣ ልጆቹ የሚያጠኑት በኤሌክትሪክ ሃይል መሆኑን አስታውሶ፤ ቶሎ እንዲሠራ ብር አዋጥተን እንድንሰጥ ጠየቀኝ።ነገር ግን ለምን የአገልግሎት ክፍያ እየከፈልን ተጨማሪ ክፍያ እንከፍላለን በትክክል ቅሬታ አቅርበን አንስተናገድም? ስለው ቅር ተሰኘ።‹አንተ ትራሱን ዘቅዝቆ እንደሚተኛ እንግዳ አስቸጋሪ ሰው ነህ።› አለኝ።
ከህግ ውጪ በሽርክና በምልጃ መሥራትም ሆነ ማሠራት አልወድም።ስለው ‹የቤት አመል ከገበያ ያወጣል እንደሚባለው ነው።ችግሩ ደግሞ የአንተ መጎዳት ብቻ ሳይሆን በአንተ ትዕቢት ቤተሰብህን አልፈህ ተርፈህ ጎረቤቶችህን መጉዳትህ ነው።› ሲል ሞገተኝ።ለሙስና የሚሆን ምንም ገንዘብ እንደማላወጣ ነገር ግን ቤተሰቤም ሆነ ጎረቤቶቼ እንዳይጎዱ ከሥራ ቀርቼም ቢሆን ኤሌክትሪኩን እንደማሠራ ተናገርኩኝ።ይሁን እንጂ ከሥራ ቀርቼ ኤሌክትሪኩን ላሠራ ብልም ማሠራት አልቻልኩም።ምክንያቱም ከእኔ በላይ ትዕቢተኛ አጋጠመኝ።‹ብልሽቱን ለማስወገድ እና የአካባቢው ሰው አገልግሎቱን እንዲያገኝ ለማስቻል የሚያስፈልግ ዕቃ አለ።ያ ዕቃ ባለመኖሩ ብልሽቱን ለማስተካከል ጊዜ ይጠይቃል፤ በዛ ላይ ቀድመው ያመለከቱ ሰዎች በመኖራቸው የሚሠራውም በተራ በመሆኑ ወዲያው ሊሰራላችሁ አይችልም› የሚል ምላሽ ተሰጠኝ።
ትናንት ብር እናዋጣ ላለው ሰውዬ ሔጄ ስነግረው ‹ቀድሞም ነግሬህ ነበር። አንተ በምትለው መንገድ ምንም ነገር አይሆንም።አንተ እንቢ ስትለን እኛ አንተን ትተን አራታችን አዋጥተን ነገ ጠዋት ይቀጠልላችኋል ተብለናል።› አለኝ።በጣም ያስገረመኝ ሁላችንም በትዕቢት መወጠራችን ነው።እኔም አላዋጣም አልኩኝ፤ በህጋዊ መንገድ እንሂድ ብዬ ተከራከርኩኝ። እነርሱም የእኔን ሃሳብ ችላ ብለው በህጋዊ መንገድ መሄድ እንደማያዋጣቸው አስበው የመረጡትን መንገድ ሄዱበት። ያለእጅ መንሻ አናገለግልም ላሉት የመንግስት ሰራተኞች ያልተገባ እንቢተኛነታቸውን እንዲያበረቱ አገዟቸው። ስለዚህ ይኸው ያልተገባ እንቢተኝነታቸው ይቀጥላል። ህግ ያከበረ ይቃጠላል፡፡
ድሮ ድሮ ሰው ለወደደው ያለውን ድንግጥ ብሎ ያቀርባል ይባል ነበር። ዘንድሮ ግን ሰው ያለውን ሁሉ የሚያቀርበው ላቀበለው ነው። ላቀበለው ያቀብላል።ይህ ደግሞ እጅግ ያሳዝናል። ማንኛውም ሰው በዓለም ሲፈጠር ይህች ዓለም የተሰጠችው የአቅሙን እንዲጠቀምባት እንጂ አንዳንዶች እንደሚያደርጉት ጨልጦ ቀድቶ እያንጠፈጠፈ ባዶ እንዲያደርጋት አይደለም።
ከዓለም የሚወስዱትን መመጠን አስፈላጊ ነው።ሰው ባይል ፈጣሪ ማን አዘዘህ? ማለቱ አይቀርም።ቅዳ እንጂ መች ጨልጥ ተባልክ? እንደሚባለው ሁሉ አሜሪካንም ሆነች ሌሎች አገሮች በኢትዮጵያም ሆነ በሌላ አገር ያሉ ዘራፊ ባለስልጣናት መጠየቃቸው አይቀርም።በዓለም ሲፈጠሩ የተፈጠሩበት ምክንያት አላቸው።
የተላከ ወንድ በነገሮች ውስጥ ውስጡን ባያምንበትም ላኪዋ የልቧ እንዲደርስ ለማድረግ ወይም ያሰበችው እንዲፈፀምላት ሲል ብቻ አንዳንድ ጊዜ የማይችለውን ጉዳይ ጭምር ከመፈፀም እንደማይመለሰው ሁሉ፤ ሁሉም ገንዘብን በማምለክ በገንዘብ ታብዮ በትዕቢት ተወጥሮ ምን የላከው ምን አይፈራም እንደሚባለው ሆኗል።ይህ ዓለምን እንዳያጠፋ እሰጋለሁ።ስለዚህ በዋናነት መማረሬን ትቼ መፍትሔው ሙስናን ለመታገል መንግስት የሚወስደው እርምጃ አስተማሪ እና ፈጣን መሆን አለበት።በተጓዳኝ ሌብነትን የሚጸየፍ ትውልድ ለመገንባት ደግሞ ወላጆች እና ትምህርት ቤቶች አተኩረው መስራት አለባቸው።ያለበለዛ ጉዳቱ የከፋ ነው።›› ብሎ ያጋጠመውን ከራሱ ፍልስፍና ጋር አጣምሮ በመግለፅ ረዥሙን ዲስኩሩን አጠናቀቀ።
ምሕረት ሞገስ
አዲስ ዘመን ህዳር 29 ቀን 2015 ዓ.ም