አዲስ አበባ፦ ሙስና የሀገሪቱ ኢኮኖሚ እንዲዛባ፣ ፍትሐዊ የሀብት ክፍፍል እንዳይኖር፣ የሥራ አጥ ቁጥጥርና ድህነት እንዲጨምር የሚያደርግ በመሆኑ አምርረን መታገል አለብን ሲሉ የኢፌዴሪ መከላከያ ሚኒስቴር ጽሕፈት ቤት ኃላፊ ገለጹ።
የኢፌዴሪ መከላከያ ሠራዊት አመራርና አባላት በሀገር አቀፍ ደረጃ ለ18ኛ ጊዜ የሚከበረውን የፀረ-ሙስና ቀን “ሙስናን መታገል በተግባር ነው!” በሚል መሪ ቃል አክብረዋል።
የመከላከያ ሚኒስቴር ጽሕፈት ቤት ኃላፊ ብርጋዴር ጄኔራል ይልማ መኳንንቴ የፀረ-ሙስና ቀን በማጠቃለያ መድረኩ ላይ እንደተናገሩት፤ ሙስና የሀገሪቱ ኢኮኖሚ እንዲዛባ፣ ፍትሐዊ የሀብት ክፍፍል እንዳይኖር፣ የሥራ አጥ ቁጥርና ድህነት እንዲጨምር ያደርጋል። እንዲሁም የጤናና የትምህርት ተቋማት እንዲዳከሙ፤ የዲሞክራሲ መርሆች እንዲጣሱ እና ግልጽና አሳታፊ የመንግሥት አሠራር እንዳይኖር የሚያደርግ ነው። ሙስና የአገር እድገት ፀር በመሆኑ አምርረን መታገል አለብን ብለዋል።
ሙስናን ለመከላከልም እንደተቋም አደረጃጀትና አሠራር ማጠናከር፤ የሥነ ምግባርና የሞራል እሴቶች ግንባታ፤ የሙስና መከላከል ጥናትና ክትትል ማጠናከር አስፈላጊና ወሳኝ ነው ያሉት ብርጋዴር ጄኔራል ይልማ፤ ሙስና በአገራችን እያደረሰ ያለው ሁሉ አቀፍ ጉዳትና የስነ-ምግባር ብልሹነት ትውልዱ ላይ የሚያስከትለው የሞራል ውድቀት ለሀገር እድገት ፀር መሆኑን ገልጸዋል።
እንደ ተቋም ዓለም አቀፍ የጸረ ሙስና ቀንን ባለፉት ዓመታት በተለያዩ ሁነቶች ሲከበር መቆየቱን አውስተው፤ አምና በ2014 ዓ.ም ከነበረው የሕግ ማስከበር ዘመቻ ጎን ለጎን በመምሪያዎችና በክፍሎች እለቱ መከበሩን አስታውሰዋል። በበጀት ዓመቱ በስነ ምግባርና ጽንሰ ሃሳብ ዙሪያ በርካታ የግንዛቤ ማስጨበጫ ስልጠናዎች መሰጠታቸውንም ተናግረዋል።
ሙስናና ብልሹ አሠራርን ትርጉም ባለው ሁኔታ ለመከላከል ዜጎች በፀረ-ሙስና ትግሉ ሊሳተፉ እንደሚገባ የገለጹት የመከላከያ ስነ ምግባር መከታተያ ዳይሬክቶሬት ዳይሬክተር ኮሎኔል አስፋ ደበሌ ፤ የትውልድ የስነ-ምግባር ግንባታ በጠንካራ ስነ ምግባር በመምራት ሌብነትንና ብልሹ አሠራርን በመታገል የሀገር እድገትን እናፋጥናለን ሲሉ ገልጸዋል።
እንደ ኮሎኔል አስፋ ገለፃ፤ ሙስናና ብልሹ አሠራር ጥቂቶችን በጊዜያዊነት በመጥቀም ብዙኃኑን ለድህነት የሚዳርግ ነው። የኅብረተሰቡን ፍትሐዊ ተጠቃሚነት በማደናቀፍ አድሎና ብልሹ አሠራርን በማስፋፋት በሐዝብ መካከል አለመተማመንን ይፈጥራል።
የሙስና ቀንን ስናከብር ሙስናና ብልሹ አሠራርን በመታገል ከብልሹና ሌብነት የፀዳ በሕግ የተመራ አሠራር መከተል እንደሚገባና ባለሙያዎችም ያለ ምንም እጅ መንሻ አገልግሎት እየሰጡ መሆናቸው መፈተሽ እንደሚያስፈልግ ተናግረዋል።
በሥነ ሥርዓቱ ላይ የሠራዊቱ አመራሮች፣ አባላት እና ሌሎች ባለድርሻ አካላት የተገኙ ሲሆን ለውይይት መነሻ የሚሆኑ ጽሑፎችም በውይይቱ ቀርቧል።
ሳሙኤል ወንደሰን
አዲስ ዘመን ኅዳር 28/ 2015 ዓ.ም