ጠቅላይ ሚኒስትር ዶክተር ዐቢይ አሕመድ፣ ከኢኮኖሚ ጉዳይ ጋር ተያይዞ ከህዝብ እንደራሴዎች ለተነሱ ጥያቄዎች ምላሽ ሰጥተዋል። በተለይም የማክሮ ኢኮኖሚ ሁኔታችን ምን ይመስላል? ዕድገታችን በንግግሩ አልተመላከተም፤ የዘንድሮ ዓመት የዕድገት ዕቅዳችን ፤ የባለፈው ዕድገታችንስ ምን ያህል ነው? የሚል እና መሰል ጥያቄዎች ተነስተውላቸው ማብራሪያ ሰጥተዋል።
የኢትዮጵያም ኢኮኖሚ በቀላሉ የማይሰበር (ረዚሊያንት) መሆኑን የተናገሩት ጠቅላይ ሚኒስትሩ፤ የተጀመረው ዕድገት መቀጠል የሚችል መሆኑን ለኢትዮጵያ ኢኮኖሚስቶች ብቻ ሳይሆን በዓለም አቀፍ ደረጃ ያሉ ይህንን ጉዳይ የሚገመግሙ ሰዎችን ግራ እስኪያጋባቸው ድረስ ኢኮኖሚው ያጋጠመውን ፈተና ተቋቁሞ መሻገር ችሏል። ጫና ተቋቁሞ መሻገር ችሏል ሲባል የኢትዮጵያ ኢኮኖሚ በ2014 የበጀት ዓመት መጨረሻ ላይ 6 ነጥብ 16 ትሪሊዮን ደርሷል። ይህም ማለት በዶላር ሲሰላ 126 ነጥብ 7 ቢሊየን ዶላር ማለት ነው ሲሉ አብራርተዋል። የነፍስ ወከፍ ገቢ ኢትዮጵያ ውስጥ አንድ ሺህ 212 ዶላር ደርሷል። ይህ ብቻ ሳይሆን ከምስራቅ አፍሪካ አንደኛው ግዙፉ ኢኮኖሚ የኢትዮጵያ ኢኮኖሚ ሆኗል ብለዋል።
ከሰሃራ በታች ካሉ የአፍሪካ አገራት ሶስተኛው ግዙፍ ኢኮኖሚ የኢትዮጵያ ሆኗል። ይህ ዳታ የመንግስታችን ዳታ አይደለም። የዓለም ባንክ ዳታ ነው። የዓለም ባንክ ዘንድሮ ባደረገው ግምገማ ከምስራቅ አፍሪካ አንደኛው ኢኮኖሚ ተበልጦ የነበረውን አስተካክሎ፤ ከሰሃራ በታች ሶስተኛው ግዙፉ ኢኮኖሚ መሆን ችሏል ሲሉ ነበር ያብራሩት።
ኢንዱስትሪም ዘንድሮ አራት ነጥብ ዘጠኝ በመቶ ዕድገት አስመዝግቧል ሲሉ የተናገሩት ጠቅላይ ሚኒስትሩ፤ ኢንዱስትሪ ከአምናው በተወሰነ ደረጃ ቅናሽ አሳይቷል ብለዋል። ቅናሽ ያሳየበት ምክንያት በኮንስትራክሽን ዘርፍ ከሲሚንቶ ጋር ተያይዞ ያለው ዕድገት ያዝ የተደረገ እንደሆነ ጠቅሰው፤ እንደአምናው ስላልሆነ አጠቃላይ በኢንዱስትሪው ላይ ያሳደረው ጫና ቢኖርም በማኑፋክቸሪንግ ግን ጥሩ ውጤት ተገኝቷል ማለታቸው ይታወሳል።
ጠቅላይ ሚኒስትሩ በሰጡት ማብራሪያ፤ የኢትዮጵያ ኢኮኖሚ ላለፉት ዓመታት በተለይም ባለፈው ዓመት በርከት ያሉ ሰው ሰራሽ ፈተናዎች እና አደጋዎች ገጥመውት ነበር። ከፍተኛ ፈተና ከነበሩት ውስጥም ጦርነት በአገር ውስጥም በውጪም መሆኑ ነው፤ የዩክሬን እና የራሺያ ጦርነት በዓለም ደረጃ የፈጠረው ጫና እንዲሁም ድርቅ ኮረናን ጨምሮ በኢኮኖሚው ላይ በስፋት ዱቀሳ ያሳረፉበት ዓመት ነበር ማለት ይቻላል።
የተለያዩ ምሁራን በኢኮኖሚ እድገቱ ዕድሎች እና ፈተናዎች ዙሪያ ያላቸው አተያይ ምን ይሆን ስንል አነጋግረናቸዋል። ዶክተር ዓደም ፈቶ በኢትዮጵያ ኢኮኖሚክስ አሶሴሽን ተመራማሪ ናቸው። የጠቅላይ ሚኒስትሩ ንግግር በግርድፉ ብቻ ወስዶ እድገት አለ ወይንም የለም የሚል መከራከሪያ ከማቅረብ ማሳያዎችን መጥቀስ አግባብ ስለመሆኑ ይናገራሉ።
‹‹የኢትዮጵያ ኢኮኖሚ ላለፉት ዓመታት በተለይም ባለፈው ዓመት በርከት ያሉ ሰው ሰራሽ ፈተናዎች እና አደጋዎች ገጥመውት ነበር። ከፍተኛ ፈተና ስለነበረ፤ ጦርነት በአገር ውስጥም በውጪም የዩክሬን እና የራሺያ ጦርነት በዓለም ደረጃ የፈጠረው ጫና እንዲሁም ድርቅና ኮረና ያመጡት ጫናዎች መኖራቸውና ይህም በስፋት በኢኮኖሚው ላይ ጫና ያሳረፈበት ዓመት ነበር መባሉን ይስማሙበታል።
እንደ ዶክተር ዓደም ገለፃ ፤ ታዲያ ይህን ሁሉ ጫና ተቋቁሞ የቀጠለ ኢኮኖሚ አድጓል ለማለት ማሳያ አለ ባይ ናቸው። ነገር ግን ዕድገቱ የተመሰረተበትን መንገድ አይቀበሉትም። በአሁኑ ወቅት 80 ከመቶ የሰው ሃይል የተሰማራው በግብርና ነው። ወደ ውጭ የሚላከው ምርትም ዋነኛ ምንጩ ግብርና ነው። ይህም ኢኮኖሚውን ጠንካራ አድርጎታል። ይህ ባይሆን ኖሮ ኢኮኖሚው መውደቁ አይቀሬ ነው። ኢትዮጵያ በተፈጥሮም ሆነ በሰው ሃይል ብዙ አቅም አሏት። ይህም ቢሆን ግን የሚያኩራራ አይደለም። ብዙ የመልማት ፀጋዎች ያሏት ሀገር ናት፤ ይህ ጸጋ ለወደፊትም የሚጠቅም ነው ይላሉ።
‹‹የባለፈው ዓመት የጂዲፒ እድገት ስድስት ነጥብ አራት በመቶ ነው የሚሉት ጠቅላይ ሚኒስትሩ፤ በዚህ ዓመት ያለን ዕቅድ ቢያነስ ሰባት ነጥብ አምስት ነው። በተለይ አሁን የተፈጠረው የሰላም ሁኔታ ማስጠበቅ ከቻልን ቢያንስ ሰባት ነጥብ አምስት በመቶ እናድጋለን ብለን እናስባለን። የባለፈው ዓመት ስድስት ነጥብ አራት ዕድገት የተረጋገጠው ቀደም ሲል እንዳነሳችሁት ብዝሃ ዘርፍ፣ ብዝሃ ተዋናኝ መሆን አለበት። ኢኮኖሚያችን፤ ግብርና መር፣ ኢንዱስትሪ መር እያልን በተወሰነ ሴክተር መታቀብ የለብንም፤ ሰፋ ያሉ የልማት ዘርፎችን እንደዋና መንቀሳቀሻ አድርገን ብንሰራባቸው አቅሞች ስላሉ ሊወጡ ይችላሉ›› ሲሉም ጠቅላይ ሚኒስትሩ ግብርና መዘመን እንዳለበት መጠቆማቸውም ይታወሳል፤ የኢኮኖሚ ምሁሩም በዚሁ ሃሳብ ይስማማሉ።
እንደ ዶክተሩ ማብራሪያ፤ ይህ አካሄድ መልካም ቢሆንም ማክሮ ኢኮኖሚው ብዙ ጉድለቶች አሉበት ባይ ናቸው። ከፍተኛ የዋጋ ንረት አለ። ምግብ ነክ ላይ 42 ከመቶ የሚደርስ ግሽበት አለ። ይህም ከዓለም አቀፍ መስፈርት ሁለት እጥፍ ነው። በገንዘብ የውጭ ብድር ጫናው በጣም ከፍ ያለ ነው፤ ይህም በእጅጉ ኢትዮጵያን ሊያሳስብ የሚገባ ነው። የመንግስት በጀት ጉድለት ያለበት ሲሆን ወጪና ገቢ የማይመጣጠን ነው። የወጪ እና ገቢ ንግድም ልዩነት ያለ ሲሆን፤ በአሃዝ 10 ቢሊዮን ዶላር ደርሷል። የውጭ ሀገር ገንዘብ ክምችትም ከአንድ ወር በታች የሆነ የገቢ ንግድ ለመሸፈን የሚውል በመሆኑ አደገኛ አካሄድ ላይ ነው።
ሥራ አጥነቱም 21 ከመቶ የደረሰ ሲሆን በትልቅ ከተሞቹ አሃዙ ወደ 30 በመቶ ደርሷል የሚሉት ዶክተር ዓደም፤ ከዚህም በተጨማሪ ኢትዮጵያ የኢኮኖሚ ትልቅ መዋቅራዊ ችግር ያለባት ሀገር ናት ብለዋል። እስካሁንም ከበሬ እርሻ ሳይዘል የተንጠለጠለውም በእርሻ እና አገልግሎት ላይ ብቻ ነው። ይህም ወደ ተሻለ መሸጋገርና ኢንዱስትሪውን ማዘመን እንደሚገባ ያመላክታል ሲሉ ያብራራሉ።
በ10 ዓመት ማክሮ ኢኮኖሚ እቅዱም በጣም የሚበረታታ ሃሳብ ቢሆንም፤ የሀገሪቱ ማክሮ ኢኮኖሚ ከፍተኛ የሆነ አለመመጣጠን ይታይበታል። መዋቅሩም ማነቆ ያለበት ነው። በአጠቃላይ የኢትዮጵያ ኢኮኖሚ ጠንካራ ቢሆንም፤ ብዙ ጉድለቶች አሉበት። ነገር ግን እነዚህን ማነቆዎች መፍታት ከተቻለ የኢትዮጵያ ኢኮኖሚ ትልቅ የማደግ ተስፋ አለው። በአሁኑ ወቅት የኢትዮጵያ ኢኮኖሚ ከግብርና ወደ አገልግሎት እየተሸጋገረ ስለሆነ ይህን በፍጥነት የማረምና ወደ ኢንዱስትሪውም የሚዞርበትን ምዕራፍ ማበጀት ይገባል። እነዚህና መሰል ችግሮች ከተስተካከሉ የሀገሪቱ ኢኮኖሚ ያድጋል። የህዝቡን የዲጅታል እውቀት ማጎልበትም ምጣኔ ሃብቱን ለማሳደግ የጎላ ሚና አለው ይላሉ።
በኢትዮጵያ ደን ልማት ከፍተኛ ተመራማሪ ዶክተር አደፍርስ ወርቁ በበኩላቸው፤ ባለፉት አራት ዓመታት በርካታ አረንጓዴ አሻራ ሌጋሲ የማስቀጠል ስራዎች መሰራታቸውን በኢትዮጵያ ኢኮኖሚ ላይ የሚኖረው አንድምታ በእጅጉ የላቀ መሆኑን ይናገራሉ። ችግኝ ከመትከል በላይ የተገኘው ውጤት በቁጥር ብቻ የማይገለፅ መሆኑን በመጥቀስም፤ የመሬት መጎሳቀልን በመጠበቅ ምርታማነት መጨመሩን ያብራራሉ። የአየር ንብረት መጋለጥን በመጠበቅ፤ የውሃ ሃብት መንከባከብና ሌሎች ፋይዳዎችን የሚሰጥ በመሆኑ የደን ኢንዱስትሪውን መልስ የሚሰጡ ሥራዎች ናቸው። ይህ ደግሞ ሀገሪቱ ከውጭ በሚሊዮኖች ዶላር የምታወጣውን ወጪ የቀነሰ ሲሆን፤ የሀገሪቱን ኢኮኖሚ በእጅጉ የሚያሳድግና፤ የአረንጓዴ ኢኮኖሚ ማደግን የሚያሳይ ነው። በአንድ ችግኝ ጣቢያ ለ10 ሰዎች የሥራ እድል የተፈጠረ ሲሆን በመላ ሀገሪቱ 121 ሺ የችግኝ ማፊያ ጣቢያዎች አሉ። በዚህም ተፈጠረው የሥራ ዕድል ወደ ሀገሪቱ ጠቅላላ ኢኮኖሚ ዕድገት ላይ የሚገባ እና በትልቁ በማክሮ ኢኮኖሚ የሚሰላ መሆኑን ያብራራሉ።
በዓመት 92 ሺ ሄክታር ደን ይመነጠር እንደነበር የገለጹት ዶክተሩ፣ ይህም በሀገሪቱ ኢኮኖሚ ላይ የሚፈጥረው ጫና በቀላሉ የሚገመት አይደለም። በአንድ ሀገር የማክሮም ሆነ የማይክሮ ኢኮኖሚ አካሄድና ዕድገት የሚመጋገብና የሚናበብ መሆን አለበት። የአረንጓዴ ልማት በማክሮ ኢኮኖሚ ላይ የሚጨምረው የራሱ የሆነ ትልቅ ትርጉም አለው ። በጠቅላላው ሲታይ የሀገሪቱ ኢኮኖሚ እድገትን ብቻ እያስመዘገበ ሳይሆን ዓለም እየተጨነቀችበት ያለውን የአየር ብክለትን በመከላከል ቀዳሚዋ ከመሆን በተጨማሪ አረንጓዴ ልማትና እድገትን ያረጋገጠ ነው ሲሉ ያስረዳሉ።
ኢትዮጵያም ከዓለም ከቀዳሚዎቹ 25 ትልቅ ብዝሃ ህይወት ካላቸው ሀገራት አንዷ ስትሆን፤ ከአፍሪካ ደግሞ ከቀዳሚዎቹ አምስት ተርታ ያሰልፋታል። ይህም በድምር ውጤት ሲታይ የሀገሪቱን ዕድገት በጽኑ የሚያረጋግጥ ነው ሲሉ ይጠቅሳሉ። ማክሮ ኢኮኖሚና የሀገር እድገት ከአረንጓዴ ልማት ጋር የማይነጣጠሉ ስለመሆናቸው ይጠቁማሉ። በዚህም የጠቅላይ ሚኒስትሩ ንግግር እነዚህን ታሳቢ ያደረገ ስለመሆኑም ያስረዳሉ።
ምሁራኑ እንደሚስማሙት፤ ኢትዮጵያ ያላትን የተፈጥሮ ሃብት ከተጠቀመች እና አረንጓዴ ኢኮኖሚን በመገንባት ረገድ የያዘቸውን ግብ ካጠናከረች እንዲሁም በዓለም አቀፍ መመዘኛ መሰረታዊ የሚባሉ ችግሮችን ካስተካከለች በቅርቡ ዕድገቷን ታረጋግጣለች የሚል እምነት አላቸው።
ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ በበኩላቸው፤ የብልፅግና ፍላጎት በአፍሪካ ገዘፍ ካሉ ኢኮኖሚዎች ውስጥ አንዱ ማድረግ አለብን ብለዋል። ፈተናዎችም ይበልጥ እንድንሰራ፤ እንዳንተኛ አግዞናል። የራሱ ስብራት ቢኖረውም፤ ተጠናክሮ ለመስራት ግን ዕድል ፈጥሯል የሚል የፀና እምነት አለኝ ሲሉ የምጣኔ ሃብት እድገት ላይ ያላቸውን ተስፋ ተናግረዋል።
ምሁራኑ የሚስማሙት ጠቅላይ ሚኒስትሩ በሰጡት ሀሳብ ዙሪያ ነው። በሀገራችን ኢኮኖሚውን ለማሳደግ የሚያስችል ሰፊ ዕድል አለ። ሆኖም እድገቱን የሚገዳደር ደግሞ ፈተና አለ ። የሚያጋጥሙ ሰው ሰራሽና ተፈጥሯዊ አደጋዎችን ተቋቁሞ ውጤታማ በሚያደርጉ ስራዎች ላይ ጉልበት ጨምሮ መስራት ከተቻለ ያልታዩ የልማት አማራጭ ዘርፎችን ማየትና ማስፋት ከተቻለ የሚታሰበው ዕድገትን ማረጋገጥ ይቻላል የሚል ትንበያ አላቸው።
ክፍለዮሐንስ አንበርብር
አዲስ ዘመን ኅዳር 27/ 2015 ዓ.ም