ታሪክ ፍጹም ህያው ይሆን ዘንድ በመዘክር ሲታወስ፣ በማሳያ ሲገለጥ እሰየው ነው ። ‹‹በቃል ያለ ይረሳል ፤ በፅሁፍ ያለ ይወረሳል ›› እንዲሉ በየዘመናቱ የተከወኑ ሁነቶች በድርሳነ – ታሪክ ሲከተቡ ለትውልድ ያልፋሉ ፣ ደማቅ አሻራን ያትማሉ። ይህ ብቻ አይደለም፣ አይረሴ ታሪኮች ትኩረት ተችሯቸው በታሰቡ ጊዜ እውነታቸው ሳይዛባ፣ ሀቃቸው ሳይዛነፍ በአስረጂነት ለመዝለቅ ታላቅ ጉልበት ይኖራቸዋል።
እንዲህ መሰል ታሪኮች ለሀገርና ሕዝብ ልዩ መገለጫዎች ናቸው። እውነታውን የሚያሳይ ታሪክን፣ የሚመሰክር ማስታወሻ በተቀመጠላቸው ጊዜም ስማቸው ሳይጠፋ ፣ ቀለማቸው ሳይደበዝዝ ዘላለማዊ ድምቀትን ይላበሳሉ። እውነታው እንዲህ ሲሆን ታሪክ በአፈ- ታሪክነት አያልፍም ። በይስሙላና በ ‹‹ነበር›› ብቻ አይዘከርም።
ሀገራችን ኢትዮጵያ በየዘመናቱ በርካታ የሚባሉ አስከፊ ታሪኮችን አልፋለች ። ድንቁ ተፈጥሮዋ ማርኳቸው ሊማርኳት ፣ ሊያንበረክኳት ከሻቱት ድንበር ዘለል ጠላቶቿ ጀምሮ በየምክንያቱ በእሳት በወላፈኑ ተፈትናለች። ሁሌም ቢሆን አይበገሬ ጀግኖቿ ‹‹እምቢኝ ፣ ለሀገሬ፣ ለዳር ድንበሬ›› ሲሉ ሕይወታቸውን ሰውተዋል፣ አካላቸውን አጉድለው ቤት ንብረታቸውን በትነዋል። እንዲህ አይነቶቹን የሀገር ባለውለታዎች ታሪክ ሲያወሳቸው ፣ ትውልድ ሲዘክራቸው ይኖራል።
ከጥንት ጀምሮ ጦርነት አስከፊው የሀገራችን መገለጫ እንደሆነ ዘመናት ተቆጥረዋል። በዚህ እውነታ መሀልም ዜጎች በበርካታ ፈታኝና እሾሀማ መንገዶች አልፈዋል። ሞት ርሀብና ፣ መፈናቅልን ጨምሮ ኢትዮጵያ በመልከ ብዙ ገጽታዎቿ ስሟ ሲነሳ፣ ማንነቷ ሲብጠለጠል ኖሯል። ክብር ይግባቸውና በርካታ ጸሀፊያን እነዚህን ታሪኮች በድንቅ ብዕራቸው ከትበው ፣ ለታሪክ አቆይተውታል።
ይህን መሰሉን እውነታ የያዙ መጽሀፍት ፣ ሀውልቶች፣ መታሰቢያዎች፣ አደባባዮች፣ ሙዚየሞችና መሰል የታሪክ መዘክሮች በወጉ ተይዘው ለትውልድ ያልፉ ዘንድ ለክብራቸው ማሰብና መጨነቅ የግድ ይላል። በነዚህ ታሪካዊ አሻራዎች ላይ የሚያርፉ የታሪክ ንቅሳቶችም በዋዛ ሊጠፉና ሊደበዝዙ አይገባም።
የቀደመውን ሃሳቤን አልዘነጋሁም። ስለታሪክና ቋሚ መዘክር ያነሳሁትን ርዕሰ ጉዳይ። አዎ ! ይህን ለማለት መነሳቴ በበቂ ምክንያት ነው። ስለምን ለሚሉኝም አንድ እውነታን በማሳያነት ልጠቁም እወዳለሁ። ርዕሱን እግረ መንገዴን ላንሳው እንጂ ዋንኛ ጉዳዬ ታሪክንና የመዘክርነቱን ጠቀሜታ ለማውሳት አይደለም።
ይሁን እንጂ ከዚሁ ጉዳይ የማይርቀውንና በዋዛ የማይታለፈውን አንድ ትዝብት ሳላነሳው ማለፍ የሚቻለኝ አልሆነም። ከታሪክ መዘክርነት ጋር የሚወሳው ይህ ጉዳይ ምን ይሆን ? የምትሉኝ ብትኖሩ ደግሞ እውነታውን እንድታውቁት ከእኔ ጋር ትጓዙ ዘንድ ጋበዝኳችሁ። ተከተሉኝ።
ከየትኛውም የከተማችን አቅጣጫ ወደ ዋናው የቦሌ ጎዳና ለሚመጣ መንገደኛ ስፍራው ዋንኛ መጋቢ መንገድ ነው። እግር ጥሎት ወደዚህ አቅጣጫ የሚያቀና ቢኖር ቦታውን አስተውሎ ለማየት የሚቸግር አይሆንም ። ይህ ስፍራ ትውልድ በዋዛ የማይዘነጋው ፣ ሀገር በቀላሉ የማትረሳው አስከፊ ታሪክ ያረፈበት ህያው መዘክር ነው።
በዚህ ስፍራ ዛሬን ሙታን የሆኑ ፣ የትናንት ባለታሪክ ትውልዶች በርካታ አጽም በክብር አርፏል። በዚህ ስፍራ በዝምታ የተዋጠ ፣ ተናጋሪ ታሪክ ይጮሃል። ኢትዮጵያ በስመ- አብዮት ውድ ልጆቿን የገበረችበት ፣ የአይተኬ ትውልድ እውነታም ይታያል፣ ይነበባል ። አዎ! ይህ ስፍራ የግፍና በደል፣ የሀገርና ትውልድ ሞትን ማሳያ መስታወት ነው። የወንድማማቾች ፣ የፖለቲካ ልዩነት ያስከተለው እልቂትና መዘዝ ምስክርነት ነው።
ይህ መዘክር ሞቶ በማይሞት ሕያውነት ፣ በደም ታሪክ ተጽፎ፣ ሟችና ገዳይን በአንድ የሚያስታውስ አይረሴ እውነታ ተገልጦበታል። በዚህ ቦታ የሚታየው አልፎ ያላለፈ ታሪክ ኢትዮጵያ በዘመኗ ዋጋ ካስከፈሏት አስከፊ እውነታዎች ዋንኛው ማሳያ ነው። የቀይ ሽብር ሰማዕታት ሙዚየም።
አንዳንዴ አንዳንድ ታሪኮች በጥቂት ሰዎች አንደበት ብቻ ኖረው ፣ተወስነው ያልፋሉ፣ በወጉ ሳይጻፉና ፣ ሚስጥራቸው ሳይነገርም እንደዋዛ ይረሳሉ። አንዳንዴ ደግሞ እውነታው ከአንዱ ወደ አንዱ ሲቀባበል ተሸራርፎ ይቀራል። የኋላ ኋላ ይህም ወግ ቀርቶበት በ ‹‹ነበር ብቻ ነበርነቱ ይወሳል። በሰማዕታቱ ሙዚየም ግን ያለፈው ታሪክ በነበር ብቻ አልቀረም። የሆነው ሁሉ በእማኝነት ፣ ተረጋግጦ ታሪክ ራሱን እንዲናገር ፣ ያለፈውን እንዲመሰክር ህያው ሆኖ ተዘክሯል።
እነሆ! ይህ የታሪክ መዘክር በባለ ታሪኮቹና በተከታዩ ትውልድ መሀል ክፉውንና አስተማሪውን የታሪክ እውነታ ቁልጭ አድርጎ ያሳያል። የዛኔ በዘመነ ደርግ የአፍላነት ሥልጣን በኢሀአፓ ሜኤሶንና ሌሎች አንጃዎች የፖለቲካ ምህዋር የእልፍ ወጣቶች ደም በከንቱ ፈሷል። በማርክዚዝም ሌኒኒዝም ርዕዮት በርካቶች ባልተመለሰው ባቡር ተሳፍረው እንደወጡ ቀርተዋል።
ለዕድገት ሥልጣኔው በዳዴ የነበረች አገራችን በቀይ ሽብር ፣ ነጭ ሽብር ጦስ ልጆቿን የአብዮቱ ወላፈን በልቶባታል፣ ሰልቅጦባታል። እናት በግፍ ለተገደለ ልጇ የጥይቱን ዋጋ እንድትከፍል መቀነቷን ትፈታ ዘንድ ተገዳለች። ሀገር በቀላሉ የማትተካቸው ምሁራን አስከሬን ከመንገድ ውሎ በአውሬ እንዲበላ፣ በውርደት እንዲንገላታ ሆኗል።
ይህ ሌት ተቀን መሪር ኀዘንና ጩኸት፣ የማያንሰው ታሪክ በዘመኑ ጠብታ ዕንባን ተነፍጎ ኀዘን እሪታን ተነጥቆ፣ በዝምታ እንዲሸበብ ግዴታ ተጥሎበት አልፏል። ይህ አይረሴ ታሪክ ኢትዮጵያ መቼም የማትረሳው ፣ አይሽሬ ጠባሳዋ ነው። እንዲህ አይነቱን ታሪክና ትውልድ የማይዘነጋው፣ እውነታ ደግሞ ዛሬ በዚሁ የቀይሽብር ሰማዕታት ሙዚየም ህያው ሆኖ ተዘክሯል።
ወደ ትዝብቴ ከማቅናቴ በፊት ሀሳቤን በርካቶች አንደሚጋሩት አምናለሁ ። ምናልባትም በዚህ ታሪካዊ አካባቢ የሚያልፉ መንገደኞች ከእኔ በፊት እውነታውን በዝምታ አስትለውትም ይሆናል። እኔ ግን ዝም አልልም ፤ አዎ ! ‹‹ዝምታ ወርቅ ነው፣ ድንቅ ነው›› ፣ ቢባልም ለአሁኑ ወርቅነቱም ድንቅነቱም ይቅርብኝ ።
ከጥቂት ጊዜያት በፊት በከተማችን ጥቂቶች ባስነሱት ነውጥ በርካታ ንብረቶች መውደማቸው አይዘነጋም። ህንፃዎች፣ ተሽከርካሪዎች፣ የመንገድ መብራቶችና ሌሎችም ። በወቅቱ ለዚሁ ችግር ሰለባ ከሆኑት መካከልም የቀይ ሽብር ሰማዕታት ህንጻ አንዱ ሆኖ ይጠቀሳል።
ድርጊቱን ፈጻሚዎቹ በህንፃው ላይ ይህን የማድረጋቸው ምክንያቱ ባይታወቅም ይህ ታላቅ የታሪከ መዘክር ግን ጉዳቱን የማስተናገድ ክፉ አጋጣሚ ደርሶታል። እነሆ! ይህ ክስተት ካለፈ ጥቂት የማይባሉ ጊዜያት ተቆጥረዋል። አብዛኞቹ የጉዳቱ ተቀባዮችም ሰባራቸውን ለውጠው ስንጥቃቸውን ጠግነው ወደነበሩበት ገጽታ ከተመለሱ ቆይቷል።
ታላቁ የቀይሽብር ሰማዕታት ሙዚየም ግን ዛሬም ድረስ ከጉዳቱ አላገገመም። ከነቁስሉ፣ ከነስብራቱ እንደታመመ አላፊ አግዳሚው ያስተውለዋል። ይህ ሙዚየም ውስጡ ብቻ ሳይሆን ውጫዊ ገጽታው ጭምር ለእይታ አስኪስብ ከትዝብት ወድቋል።
ሙዚየሙ የአንድ ትውልድን እልቂትና አስከፊ ገጽታ የያዘ መዘክር ነው። በዚህ ስፍራ በየዕለቱ በርካታ እግሮች ይመላለሳሉ፣ በርካታ ዓይኖችም በአስተውሎት ያተኩራሉ ። ትኩረቱ ግን የውስጡን እንጂ የውጭ ገጽታውን ያየው፣የቃኘው አይመስልም።
የሙዚየሙ ውጫዊ አካል ትናንት በሆነበት ክፉ አጋጣሚ ራሱን ሳያድንና ሳያክም ከነስብራቱ ፣ ከነክፉ አሻራና ህመሙ መታየትን መርጧል። ይህ ለምን ሆነ? ብዘዎቻችን የምንጋራው ጥያቄ ይመስለኛል። ለጥገና የሚሆን አቅም ጠፍቶ ? ወይስ በተለመደው ግዴለሽነት ተዘናግቶ። እኔ በትዝብት ዓይኖቼ ይህን ብያለሁ። መልሱን ለሚመለከታቸው በመተው ።
መልካምሥራ አፈወርቅ
አዲስ ዘመን ህዳር 26/2015