ወቅቱን በትክክል መግለጽ ቢያዳግትም ከሁለተኛው የዓለም ጦርነት በኋላ ፋሽን ትኩረት እንዳገኘ ታሪክ ያወሳል።በ1960ዎቹ ደግሞ ቀለም ፋሽን ሆኖ ሰዎች ስለ አልባሳታቸው፣ ቤታቸው እና መኪኖቻቸው ቀለም ማተኮተር ጀምረዋል።ይኸው የቀለማትና የፋሽን ስብጥርም ተጠናክሮ እስካሁን ዘልቋል።
የሰዎች ማንነት በተለያየ መንገድ ሲገለጽ፤ ዘወትር የምንታይባቸው አልባሳት ከመገለጫዎቻችን መካከል ይጠቀሳል።በእርግጥ ከሰዎች አለባበስ አስቀድሞ ከዓይናችን የሚገባው የልብሳቸው ቀለም ነው።የሁለቱ ውህደት ደግሞ አንድን ሰው አሊያም ስዕብናውን በተወሰነ መልኩ ሊገልጽልን ይችላል።ይህም ብቻ አይደለም የምንመለከታቸው ቀለማት በስሜታችን ላይም ለውጥ የማምጣት አቅማቸው ከፍተኛ ነው።ደማቅና ለዓይን ማራኪ የሆኑ የቀለም ዓይነቶች በሰዎች ስሜት ውስጥ ደስታን የመጫር አቅማቸው ከፍተኛ ሲሆን፤ በአንጻሩ ጠቆር ያሉና ደብዛዛ ቀለሞች የደስታ ስሜትን ወደማጥፋቱ ያመዝናሉ።
ይህንንም ከልምድ በመነሳት መረዳት ይቻላል፤ ለአብነት ያህል በኢትዮጵያ ባህል ነጭ መልበስ የደስታ እንዲሁም የበዓል መገለጫ ነው።ጥቁር ልብስ የሚለበሰው በሃዘን ጊዜ ሲሆን፤ ነጭ ሸማ በሚለበስበት ጥንታዊው ዘመን እንኳን በተለያየ መንገድ ነጠላንና ሌሎች ልብሶችን ማጥቆር የተለመደ ነው።በጸደይ ወቅት፣ በክረምት እና በበጋም ቢሆን የሚለበሱ ልብሶች የራሳቸው ቀለማት አላቸው።አለባበስ በጾታ፣ በእድሜ፣ በሃይማኖት፣ በአኗኗር ሁኔታ፣ አቅም፣… እንደሚለያይ ሁሉ ቀለማትም እነዚህን ሁኔታዎች ሊያሳዩ ይችላሉ።
ቀለም ከሰው ልጅ ሥነልቦና ጋር ቀጥታ ተዛምዶ ያለው እንደመሆኑ ፋሽን እና ቀለምም ሊነጣጠሉ የማይችሉ የአንድ ሳንቲም ሁለት ገጽታዎች መሆናቸውን የዘርፉ ባለሙያዎች ይጠቁማሉ።አንድ ዲዛይነር ወደ ስራ ሲገባ ለሚነድፈውና በአእምሮው ከሚያወጣው ቅርጽ በእኩል በምን ዓይነት ቀለም ልብሱን እንደሚያዘጋጅ ያስባል።በሌላ በኩል ደግሞ ቀለምን ተንተርሰው የልብስ ዲዛይኖች ይዘጋጃሉ።ይህ ሊሆን የቻለበት ምክንያት ደግሞ ቀለሞች የየራሳቸው የሆነ ትርጓሜ ያላቸው እና ከሰዎች ስሜት ጋር የተገናኙ በመሆናቸው ነው።
ለዛም ነው ሰዎች ልብስ ለመግዛት ወደ ገበያ ሲያቀኑ ከዲዛይኑ እና ከተሰራበት ጥሬ እቃ እኩል የቀለም አማራጮችን የሚፈልጉት።ቴክስታይል ቱደይ የተባለው ድረገጽ በጥናት ላይ ተመስርቶ እንዳስነበበው ከሆነ ገዢዎች የወደዱትን አልባሳት ለመግዛት ቀለሙ 86 ከመቶ ድርሻ አለው።አንድ ሸማች ሊገዛ በወደደው የልብስ ቀለም ለመሳብም 92 ሰከንዶች ብቻ ይፈጅበታል።
የፋሽንና የቀለም ዝምድና የዚህን ያህል ጥልቅ እንደመሆኑ ቀለም የወቅቱ ፋሽን ሲሆንም ይስተዋላል።ይህም ከተፈጥሮ ጋር ከመዋሃድ ባለፈ ፋሽንን መሰረት ያደረጉ የልብስ ቀለማት በተለይ ሊዘወተሩ በገበያ ላይም በስፋት ሊታዩ ይችላሉ።ለአብነት ያህል ባለንበት የፈረንጆቹ ዓመት 2022 ደማቅ ቀለማት ያላቸው አልባሳት፣ ጫማዎችንና ቦርሳዎችን በአልባሳት ሱቆችና ፋሽን ተከታዮች ዘንድ በስፋት ተመልክተናል።ይህ እንዴት ሊሆን ይችላል ለሚለው ጥያቄም ቴክስታይል ቱደይ የተባለው ድረገጽ ምላሹን ይሰጣል።ይኸውም ከፋሽን ዘርፍ የተውጣጡ ባለሙያዎች ኮሚቴ የገበያ ጥናት ላይ ተመስርተው የሚመርጡትን የቀለም ዓይነት በየዓመቱ ለሁለት ጊዜ በዚህ ዘርፍ ከተሰማሩ አካላት ጋር በመወያየት ከውሳኔ ላይ ይደርሳሉ።ይህም የሚሆነው ከሰው ልጆች ሥነልቦና ጋር ተያያዥነት ባለው መልኩ ሲሆን፤ ምርታቸውም በእነዚህ ቀለሞች ላይ ያተኮረ ይሆናል።
ከፋሽን ጋር ተያይዞ የሴትነት መገለጫ የሆነው ሮዝ ቀለም እንዲሁም ወንዶች የሚወከሉበት ሰማያዊ ቀለምም በዚሁ ኮሚቴ ስምምነት መሰረት የተፈጠረ እንጂ ከተፈጥሮ ጋር ምንም ግንኙነት የሌለው መሆኑን ልብ ይሏል። ለዓመቱ ፋሽን የሚሆነው ቀለም ከተመረጠ በኋላም የልብስ ዲዛይነሮች እና ማምረቻዎች ታዋቂ ግለሰቦችን፣ የኪነጥበብ ባለሙያዎችን፣ ፖለቲከኞችንና ተጽእኖ ፈጣሪ ግለሰቦችን በማስዋብ ወደተቀረው ሕዝብ እንዲጋባ ያደርጋሉ። ለአብነት ያህል እአአ በ2009 የወጣውና በርካቶች የተመለከቱት አቫተር የተባለውን ፊልም ማንሳት ይቻላል። በወቅቱ በፊልሙ ላይ ጎልቶ ይታይ የነበረው ቀለም በ2010 ጭምር የፋሽኑን ዓለም ተቆጣጥሮት ቆይቷል። የዚህ ዓመት የቀለም ፋሽንም ደማቅ ቀለሞች ስለመሆናቸው በገበያ ቦታዎች እንዲሁም በጎዳናዎች ላይ ከሚታዩት የሰዎች አልባሳት መረዳት ይቻላል።
እንደሚታወቀው በዓለም ላይ ከፍተኛ ጉዳትን ካሳረፈው የኮቪድ 19 ወረርሽኝና በእሱ ምክንያት ከተጣለው የእንቅስቃሴ ገደብ ዓለም የተላቀቀው በዚህ ዓመት ነው።በመሆኑም ደማቅ ቀለም ያላቸው አልባሳት በብዛት እንዲሁም በጥቂቱ ፈዘዝ ያሉ ቀለማት የዓመቱ መገለጫዎች ነበሩ። የዓመቱ ዋናው ፋሽን የሆነው ቀለም አረንጓዴ ሲሆን፤ በቀላሉ ሰውን ሊስብ የሚችልና የተመልካችንም ቀልብ መያዝ የሚችል ነው።ይህ ቀለም ተፈጥሮን የሚወክል እንደመሆኑ የሰዎችን ስሜት በማረጋጋት እንዲሁም ድብርትን ከመቀነስ አኳያ ተጠቃሽ ነው። ይህ ቀለም ወጥ ከሆኑ ልብሶች ባሻገር ከሌሎች ቀለማት ጋርም አቀላቅሎ በመልበስ ከወቅቱ ፋሽን ጋር መጓዝ ይቻላል።
በፋሽን ተከታዮች ዘንድ እምብዛም የማይደፈረው ደማቅ ብርትኳናማ ቀለምም ይህንን ዓመት ካደመቁ ፋሽኖች መካከል አንዱ ነበር።ሞቃት የሆነውና ተዝናኖትን የሚፈጥረው ይህ ቀለም ለበጋማ ወቅትና ለማታ ዝግጅቶች በተለይ ተመራጭ ነው።እንደ ነጭ ካሉ ቀለማት እንዲሁም ከወርቃማ ጌጣጌጥ ጋር ይበልጥ የሚስማማ እና የወቅቱን ፋሽን የሚገልጽ ቀለምም ነው።ስስነትን የሚያሳየውና የሴትነት መገለጫ የሆነው ደማቅ ሮዝ ቀለምም በዓመቱ በተለይ ከተዘወተሩ ቀለማት መካከል አንዱ ነው። በራስ መተማመን እና ብርታትን የሚወክለው ቀለሙ በአልባሳት፣ በመጫሚና በቦርሳ መልክ በስፋት ተመርቶ ገበያ ላይ ውሏል፡፡
ብርሃን ፈይሳ
አዲስ ዘመን ህዳር 26/2015