ጥንዶቹ የመልካም ትዳር ተምሳሌት ናቸው። በመዋደድ፤ በመተሳሰብ፣ ያድራሉ። ቤት ይዘው ጎጆን ማሰብ ከጀመሩ ወዲህ የሁለቱም ባሕርይ በአንድ ሲጓዝ ኖሯል። ‹‹አንተ ትብስ ፣ አንቺ ›› ይሉት እውነት ገብቷቸዋል። አንዳቸው ለሌላቸው ጥላ ከለላ፣ አጋር መከታ መሆናቸውን ያያቸው ሁሉ ይመሰክራል።
ጥሩ ማዕድ አስፋው ትዳሯን ታከብራለች፣ ባሏን ትወዳለች። እሱ ስራ ውሎ እስኪገባ ዓይኗን አታምነውም። ደጅ ደጁን እያየች፣ መምጫውን ትናፍቃለች። ቤት ሲደርስ ከድካሙ እንዲያርፍ፣ የቀን ውሎውን እንዲረሳ ከቡናው፣ ከእራቱ እያለች ጎኑ ታመሻለች። የባሏ ስራ ጉልበት ፈታኝ አድካሚ ነው። ያጋጠመውን ትጠይቃለች፣ የዋለበትን ያወጋታል። ቤቱ በሳቅ ሁካታ ደምቆ ያመሻል።
ጥሩ ማዕድ ስለባለቤቷ በጎነት መስካሪ ነች። መልካምነቱን ስትገልጽም ቃላቶች ያጥሯታል። ሁሌም ከአድናቆት ጋር ምስጋናን መሸለም ልምዷ ነው። የባጃጅ ሹፌሩ አባወራ ስለሚስቱ ክብር አለው። ከልቡ ይወዳታል። ከመውደድ ባለፈ ደግሞ አጋርነቷን ያምናል። ጥሩ ማዕድ ሚስቱ ብቻ አይደለችም። የችግሩ መፍትሄና መላ ነች። የሕይወቱ ቅመም ጭምር።
ባልና ሚስቱ ትዳር ይዘው ጎጆ ማቅናት ከጀመሩ ዓመታት ተቆጥረዋል። በእነዚህ ጊዜያት ክፉ ደጉ የጋራቸው ሆኖ አልፏል። ኑሮ ቢከብዳቸውም ለራሳቸው አያንሱም። የመጀመሪያ ልጃቸውን በስስት እያዩ በፍቅር ያሳድጓታል። ሁሌም ስለእሷ ነገና ስለእነሱ የወደፊት ሕይወት ያስባሉ። መተሳሰባቸው ሕይወት፣ ኑሯቸውን አቅንቷል። ሰላማቸውን ጠብቋል።
አዲስ እንግዳ
አሁን ጥሩ ማዕድ ሁለተኛ ልጇን ነፍሰጡር ናት። ድንገት ባወቀችው እርግዝና አልተከፋችም። የራሴ ትለው መኖሪያ ቤት ባይኖራትም የተሰጣትን ልትቀበል ተዘጋጅታለች። ባተሌው ባሏ የቤተሰቡ ኑሮ ያሳስበዋል። ተቀጥሮ በሚሰራበት ውሎ ያገኘውን ይዞ ቤቱን ይሞላል። አሁን የልጅ ቁጥር በአንድ ሊጨምር ነው። ይህን ሲያስብ ስለ ሕይወት ይጨነቃል ፣ ባለቤቱንና ራሱን እየደመረ ስለነገው ያቅዳል። ዘወትር እረፍት የለሽ ነው። ማልዶ ይሮጣል፣ መሽቶ ይገባል። ጠዋት ወጥቶ ማታ ሲመለስ ድካም ልፋቱን በሚስቱ፣ በልጁ ፈገግታ ይረሳል።
ጥሩ ማዕድ ጊዜዋን ለልጇና ለባሏ ታውላለች። በአባወራዋ ትከሻ የሚያድረው ቤት ብዙ ያሻዋል። እሷ ጎዶሎን ለመሙላት የአንድ ሰው እጅ ብቻ እንደማይበቃ ታውቃለች። የባጃጅ ስራ ተባረው፣ ተናጥቀው የሚያድሩበት ነው። ለአሰሪው በእለት የሚጠበቀውን ማስገባት ግድ ይላል። እንዲህ ሲሆን እንደሱ ተቀጥሮ ለሚሰራ ይከብዳል። ያም ሆኖ በእነሱ ቤት ችግር አልገባም። ያላቸውን እያብቃቁ ፣ የእጃቸውን አመስግነው ያድራሉ።
ጥሩ ማዕድ እርግዝናዋ እየገፋ ነው። እንደቀድሞው ተሯሩጣ ባታድርም ለቤት ጎጆዋ አላነሰችም። አባወራዋን ለስራ ሸኝታ የሚጠብቃትን ትከውናለች። ልጇም ብትሆን በእሷው ሀላፊነት ትውላለች። የሚያሻትን፣ እየሞላች፣ የጠየቀችውን እየሰጠች የልቧን ትሞላለች። ወይዘሮዋ በየወሩ የእርግዝና ክትትል አላት። ከጤና ባለሙያዎች ምክር እየወሰደች፣ የተባለችውን ትሰማለች። ባለሙያዎቹ ዘወትር ማለዳ ብዙሃንን ከማስተማር አይቦዝኑም።
ነፍሰጡር ሴት በእርግዝና ጊዜዋ ማድረግ ስላለባት ጥንቃቄ፣ ስለአመጋገብ ፣ ጤንነቷ፣ ስለአኗኗሯ ደኅንነቷ ቁምነገር ያስጨብጣሉ፣ ያስተምራሉ። ጥያቄ እየጠየቁ ምላሽ ይሰጣሉ። ምላሽ እየሰጡ፣ በምሳሌ ያስረዳሉ። ጥሩ ማዕድ ከሌሎች ጎን ሆና ሁሉን ትሰማለች። ቤት ስትደርስ የሰማችው ይረሳታል፣ ስለምግቧ አስባ፣ ተጨንቃ አታውቅም። ቤት ካፈራው ያማራትን ትጋራለች።
ዘጠነኛው ወር
ወይዘሮዋ መክረሚያዋን ጉድ ጉድ እያለች ነው። የመውለጃ ወሯ ገብቷል። ለአራስ ቤቷ የሚበጃትን እያሟላች ፣ ቤቷን ታሳምራለች፣ ጓዳዋን ታዘጋጃለች። ለ‹‹እንኳን ማርያም ማረችሽ ጥየቃ ለሚመጡ እንግዶቿ የአቅሟን ማድረግ አለባት፤ ካላት ቆጥባ ያስቀመጠችውን ለመስተንግዶው ታውላለች። ወልዳ ስትገባ ጠያቂ ወዳጅ ዘመድ አይጠፋም። ይህን እያሰበች በሀሳብ ትርቃለች። ከራቀችበት ስትመለስ የጎደለውን ትሞላለች፣ ያሰበችውን ታደርጋለች።
አንድ ማለዳ ጥሩ ማዕድ የተለየ ህመም ተሰማት። ያዝ ለቀቅ የሚያደርጋት ስሜት ምጥ መሆኑ አልጠፋትም። ሰሞኑን ከሀኪም ቤት ስትመላለስ በቅርብ እንደምትወልድ ተነግሯታል። በሚሆነው አልደነገጠችም። ይህን እውነት በመጀመሪያ ልጇ ታውቀዋለች። ጥርሷን ነክሳ ለሚሆነው ሁሉ ተዘጋጀች።
ብቻዋን አይደለችም። ከጎኗ ባለቤቷና የቅርብ ሰዎች አሉ። ከሀኪም ቤት ስትደርስ ወደ አንድ ክፍል ገብታ ምርመራ ተደረገላት። ሀኪሙ በእጁ ያለውን የህክምና ካርድ ደጋግሞ ያነባል። አንዳንድ ጉዳዮችን እየጠየቃት ነው። ስሜቱ ምጥ መሆኑ እንዳረጋገጠ ወደ ማዋለጃ ክፍል እንድትሄድ አዘጋጃት።
በማዋለጃው ክፍል
አሁን ጥሩ ማዕድ የሆስፒታሉ ልብስ ተሰጥቷት ወደ ማዋለጃው እያለፈች ነው። የጀመራት ህመም በርትቷል። ስሜቱን ልትቋቋም ጥርሷን ትነክሳለች። ለአፍታ አስጨንቆ ለቀቅ ሲደርጋት ‹‹እፎይ›› ትላለች። ይህ እረፍት እንደማይቀጥል ታውቀዋለች። ቀጣዩ ጭንቀት ፈታኝ እንደሚሆን እያሰበች ራሷን ታበረታለች።
ጥሩ ማዕድ ከማወለጃው ገብታ እንደቆየች ጥቂት ሀኪሞች ወደእሷ ቀርበው ከበቧት። በፊታቸው የሚነበበው ጭንቀት ሌላውን ያስጨንቃል፤ በክፍሉ የገባችውን ወላድ ለማነጋገር ቸኩለዋል። ጥሩ ማዕድ የእነሱን ገጽታ ያስተዋለች አይመስልም። ገፍቶ የመጣውን ምጥ ለማሸነፍ ከራሷ ትግል ገጥማለች።
ሀኪሞቹ ከአጠገቧ ደርሰው አንድ ጉዳይ አነሱባት። ጉዳዩ ለጥሩ ማዕድ አዲስ ባይሆንም ክፉኛ ደነገጠች፣ ልቧ ያለማቋረጥ ደጋግሞ ሲመታ ተሰማት። ይህ ለእሷ የሞትና ሕይወት ትግል ነው። ዕንባዋ በጉንጮቿ እየፈሰሰ በዓይኖቿ ተማጸነች። እየተሰማት ያለው ህመም ከምጡ አይሎባታል። መተንፈስ እየተሳናት ነው። ሁኔታዋን ያዩት ሀኪሞች ፈጥነው ከእጇ መለኪያ አደረጉ። ደሟ ቀድሞ ከነበረው በእጥፍ ጨምሯል። ዓይኖቿን ጨፈነች፣ ገለጠች። ከቀናት በፊት ስለሰማችው እውነት ደጋግማ አብሰለሰለች። ጥልቅ ሀሳቧ ወደኋላ አጠንጥኖ መለሳት።
ከቀናት በፊት
ጥሩ ማዕድ ዘጠነኛ ወሯ እንደገባ የመጨረሻውን አልትራሳውንድ ተነሳች ። በወቅቱ ውጤቱ ከእጃቸው የደረሰ ሀኪሞች ወይዘሮዋን ሊያነጋግሯት እንደሚሹ አሳወቋት። እንደተባለችው ከሀኪም ፊት ቀርባ የምትባለውን ጠበቀች። ሀኪሙ በእርጋታ፣ በጥንቃቄ እያስረዳ የሆነውንና ማድረግ የሚገባትን አሳወቃት። የምርመራው ውጤት በተረገዘው ልጅ ወገብና ጭንቅላት ላይ ውሃ ስለመኖሩ ያመለክታል።
ይህ ችግር በእርግዝና ወቅት በነርቭ ዘንግ ላይ የሚያጋጥም ክፍተት ነው። የህክምና አጠራሩም ‹‹ ስፓይና ቢፊዳ ኤንድ ሀይድሮ ሴፋለስ ›› ይባላል። የህብለ ሰርሰር በአግባቡ ያለማደግና በጭንቅላት ውስጥ ከመጠን ያለፈ ፈሳሽ መኖር በቅድመ ወሊድ ጊዜ ሊያጋጥም የሚችል የጤና ችግር ነው። የነርቭ ዘንግ ክፍተት ከመጀመሪያዎች የእርግዝና ሳምንታት አንስቶ የሚከሰት ቢሆንም ችግሩ የሚታወቀው ግን በመጨረሻዎቹ የመውለጃ ሳምንታት ላይ ነው። የዚህ ችግር መነሻ በእርግዝና ወቅት የፎሊክ አሲድን በአግባቡ አለመጠቀም መሆኑ ይታወቃል።
ወይዘሮዋ እንደ እናት ልጇን ወልዳ መሳምን ናፍቃለች። ሀኪሞቹ ግን ይህ ከመሆኑ በፊት በልጇ መኖር አለመኖር ላይ ፈጥና እንድትወስን እየጠበቋት ነው። እያለቀሰች ምክንያቱን ጠየቀች። ሀኪሞቹ በአግባቡ ሊያስረዷት ጊዜ ወሰዱ። ልጁ ከነችግሩ ከተወለደ የመኖር ህልውናው ያሰጋል ተባለች።
እንዲህ አይነት ልጆች፣ በየጊዜው ጭንቅላታቸው ያድጋል፣ ለመንቀሳቀስ፣ ራሳቸውን አውቀው ለመጸዳዳትና በወጉ ለመኖር ይሳናቸዋል። የወገብ ላይ ክፍተቱም ፓራላይዝድ የመሆን ዕድላቸውን የሚያሰፋ ነው። በዓይን በአዕምሮና በጤናቸው ላይ የሚኖረው ጉዳት የከፋ መሆን ያለ ሌሎች እገዛ ሕይወታቸውን እንዳይቀጥሉ ያስገድዳል። ይህ አይነቱ ችግር ከወሊድ በፊት በታወቀ ጊዜ በህክምና ጽንሱ እንዲወገድ ይወሰናል።
ውሳኔ
አሁን ጥሩ ማዕድ እውነታውን አውቃለች። ዘጠኝ ወር ሙሉ ያረገዘችው ልጅ ጤናው የተጓደለ፣ የመኖር ህልውናው በእጅጉ የሚያሰጋ ሆኗል። ከእንግዲህ ከነችግሩ ልጇን መቀበልና ሀኪሞች እንዳሏት ፅንሱን ማስወገድ የግል ውሳኔዋ ይሆናል። ወይዘሮዋ ከራሷ ተጨቃጨቀች፣ በሀሳብ ሽቅብ ቁልቁል ወረደች፣ በጭንቀት ተወጥራ ክፉ ከደግ አሰበች።
እሷ ልጇን ፈጽሞ ማጣት፣ አትሻም። እንደተባለችው ብትፈጽም ሀጢያት መሆኑ አሳሰባት። ‹‹እሺ፣ እምቢ›› ሳትል ከራሷ ሞገተች፣ እነሱ እንደሚሏት ማድረግ፣ መፈጸም አልሆነላትም። የተረገዘችው ሴት መሆኗን አውቃለች። ልጇ ምንም ብትሆን የፈጣሪዋ ስጦታ ናት። ደግማ ደጋግማ አሰበች። በቃ! ልጇን ከነህመም፣ ከነችግሯ ትቀበላታለች። ወሰነች። ለሀኪሞቹ ‹‹ልጄን ተውልኝ ትፈጠር›› ስትል አሳወቀች። ቃሏን ተቀበሉ፣ ውሳኔዋን አከበሩ።
ስጦታ
እነሆ ትንሽዬዋ ህጻን ከእናቷ አቅፍ ገብታለች። ጥሩ ማዕድ ያመነችበትን፣ ውስጧ የነገራትን ማድረጓ አላስቆጫትም ። የተሰጣትን ልትቀበል ፈቅዳለችና ለሚሆነው ሁሉ ራሷን አዘጋጀች። ልጇን መባ/ስጦታ /ብላ ስትሰይማት በምክንያት ነው። ስጦታዋን አልጣለቻትም ፈጽሞ አላፈረችባትም። ሕይወት ዘርታ እስትንፋሷን ከሰጠቻት ቀን ጀምሮ ፈተናዋ ፈተና ሊሆን ከጎኗ ሆናለች።
በመጀመሪያዎቹ ቀናት እናት ልጇን ታቅፋ ወደ ዘውዲቱ ሆስፒታል አቀናች። ለሰባት ወራትም አልጋ ይዛ በህክምናው ቆየች። የህጻን መባ ጸጋዬ ጤንነት አስቀድሞ እንደተባለው ሆነ። አዲሷ ጨቅላ ቀዶ ህክምና ተደረገላት። ጥቂት ቆይቶ ግን አካሏ ኢንፌክሽን ፈጠረ። የህጻኗ ለስላሳና ስስ ሰውነት በቁስል ስቃይ ተፈተነ።
ህክምናው በተጀመረ አራት ወራት ውስጥ የጭንቅላቷ ውሃ መጨመሩ ተነገራት። ጭንቅላቷ ለሁለት ጊዚያት ቀዶ ህክምና ተደርጎለት ‹‹ሻንት›› የተባለ መሳሪያ እንዲገባላት ሆነ። እናት ከሆስፒታል ሳትለይ ስለልጇ ሕይወት ታገለች። አንዳንዴ የወገብ ላይ ቁስሏ አንስታ ለማቀፍ ያስቸገራታል፣ እንዳሻት ለማጥባትና እንደልጅ ለማገላበጥ ህመሙ ፈታኝ ነበር። ይህ ባጋጠማት ቁጥር ጥሩ ማዕድ በትካዜ ትቆዝማለች፣ የልጇ ህመምና ስቃይ ውስጧ ዘልቆ ይሰማታል።
በጎ ምክር
አንድ ቀን ወይዘሮዋ የአንዲት ልበ ደግን ነርስ ምክር ከልቧ አዳመጠች። ቃሏ ለማንነቷ ትርጉም ሰጠው። ነርሷ ጠንካራና ጎበዝ እናት ከሆነች የልጇን ጤና መጠበቅ እንደሚቻላት ነገረቻት። ምክሯ ውስጧን አረሰረሰው። ያለቻትን ልትሆን፣ በጽናት ልትቆም ራሷን አሳመነች፣
ህጻን መባ አሁን አንድ ዓመት ከአምስት ወር ሆኗታል። የጭንቅላቷ ዕድገት ባለበት ቢገታም ከወገቧ በታች አትንቀሳቀስም። እንደ ዕድሜ እኩዮቿ መዳህ፣ መንፏቀቅ አትችልም፣ ዕቃ ይዛ ልትቆም አትሞክርም። በየጊዜው የህክምና ክትትል አይለያትም።
እናት ጥሩ ማዕድ ሙሉ ጊዜዋን ለልጇ ሰጥታለች። ስራ በመስራት ባሏን ለማገዝ፣ ጓዳዋን ለመሙላት አልተቻላትም። ልዩ ትኩረት የምትሻው መባ ከትከሻዋ ሳትወርድ ትውላለች። ድንገቴ ጉዳይ ቢገጥማት፣ ለጎረቤት፣ ወዳጅ ዘመድ ‹‹አደራ›› ብላት አትወጣም። የእሷ ሕይወት ‹‹እሷና እሷ›› ብቻ ነች።
አንዳንዴ በተስፋ መቁረጥ ውስጧ ይፈተናል፣ ይከፋታል፣ ታለቅሳለች። ይህኔ ልበ በጎው ባለቤቷ ከጎኗ ሆኖ ‹‹አይዞሽ፣ አለሁሽ ›› ይላታል። የህጻኗ መልካም ባህርይ ደግሞ ሁሉን ያስረሳታል። አንዳንዴ የቤቷን ስራ ለመከወን መባን ከትከሻዋ አውርዳ ታስተኛታለች። ጉዳይዋ በበዛ ጊዜም ከአልጋ ማስተኛቱ ይደጋገማል። እንዲህ ሲሆን የህጻኗ ጀርባ ይላጣል፣ ቁስል ያላጣው አካሏ ሰበብ ፈልጎ ይቆጣል።
እናት ጥሩ በእርግዝናዋ ጊዜ ከሀኪም የተሰጣትን ምክር አትረሳም። የፎሊክ አሲድን የምግብ ይዘት በአግባቡ እንድትጠቅም ተነግሯት ነበር። በወቅቱ ይህን አለማድረጓ ለችግር እንደዳረጋት ታምናለች። ያም ሆኖ ልጇ እንድትወለድ በመፈቅዷ አትቆጭም።
ስለነገዋ መባ ታላቅ ተስፋን ባትሰንቅም የተቻላትን ለማድረግ አትቦዝንም፡፤ ልጇ ለእሷ ሕይወቷ ነች። ወደዚህች ምድር እንድትመጣ፣ እንድትኖር እስትንፋስ ሆናለች። ቀኝ እጅ የሆናት ባለቤቷ ቤት ጓዳቸውን ለመሙላት ከቀድሞው በባሰ ይሮጣል፣ ይተጋል።
በቤት ኪራይ ኑሮን መግፋት፣ ሕይወትን መምራት ፈታኝ ነው። አንዳንዴም የአንዳንድ ሰዎች በጎነት የጎደለው እይታ ችግሩን ከተሸከመው በላይ ጫና የሚፈጥር ይሆናል። ወይዘሮዋ በአንድ ወቅት የቤት አከራይዋ የልጇን ህመም በማሳበብ ክፉ ብላታለች። ከቤት አስወጥታለች። በርካቶች እንደሷ ባለመሆናቸው ግን ቅስሟ አልተሰበረም። ሁሉን ለፈጣሪዋ ትታ በብርታቷ ቀጥላለች።
አሁን የምትኖርበት ቤት ክፍያው ቢበዛም ሰዎቹ መልካም ናቸው። ችግሯን ይረዳሉ። እናት ጥሩ ቁጭ ማለቱን አትወድም። የሚያግዝ፣ የሚደግፋት ቢኖር ለልጆቿ ሰርታ መግባትን ትሻለች። ባለችበት አካባቢ በሴፍቴኔት ተጠቃሚ ለመሆን ያደረገችው ጥረት አልተሳካም። ዛሬም የቤተሰቡ ብቸኛ አማራጭ የአባወራው ትከሻ ነው። ነገ ህጻን መባ ከዛሬ የተሻለ ያስፈልጋታል። በአንድ ሰው አቅም ብቻ የቆመው ቤተሰብ በቤት ኪራይና በኑሮ ውድነት እየተፈተነ ነው።
ምክር
ወይዘሮዋ የሀኪሞች ምክር የገባት ቆይቶ ነው። በእርግዝናዋ ጊዜ ትኩረት ያልሰጠችው ጉዳይ ዋጋ አስከፍሏታል። ዛሬ ወዳና ፈቅዳ ወደዚህች ምድር ላመጣች ልጅ ታላቅ ሀላፊነት ተሸክማለች። ሌሎች እናቶች ግን በእሷ መንገድ አልፈው፣ ተመሳሳይ ዋጋ እንዳይከፍሉ አበክራ ትመክራለች። ‹‹ለእርግዝናችሁ ትኩረት ስጡ፣ የምትባሉትን ፈጽሙ›› ስትል።
መልካምሥራ አፈወርቅ
አዲስ ዘመን ኅዳር 24/ 2015 ዓ.ም