እርሷ ራሷ ልዩ ቅኝት ናት፤ ያልተደመጠች፣ ያልተፈጠረች፣ ያልተጠናች የምታጓጓ ኢትዮጵያዊት ቅኝት ።እርሷ ቅኝቶችን ታሳምራለች እንጂ ቅኝት እርሷን አያሳምራትም፤ እርሷ ራሷ ባህል አሳማሪ እንጂ ባህል አያሳምራትም፤ እርሷ የባህል አልባሳትን ታስውባቸዋለች እንጂ የባህል አልባሳት እርሷን አያስውባትም ።እርሷ ኢትዮጵያን አክብራ፣ አስዋባ፣ አድምቃታለች እንጂ፤ ኢትዮጵያ እርሷን አላከበረቻትም፣ አላደመቀቻትም ።እርሷ ፈጣሪዋ በሰጣት እስትንፋስ የአምባሰል ቅኝትን አስተዋውቃለች እንጂ አምባሳል ቅኝቱ እርሷን አላስተዋወቃትም ።ብዙ የተዜመላቸው ሰንሰለታሞቹ የአምባሰል ተራሮችን እንኳ እርሷ አግዝፋቸዋለች እንጂ ተራሮቹ እርሷን አላገዘፏትም፡፡
ለዚህም ነው በተለይ የአምባሰልን የዜማ ቅኝት ሲነሳ ሁሌም ከትውስታችን ቀድማ በሚስረቀረቀው ድምጿ ከነደርባባ ፊቷ ድቅን የምትለው ።ለዚህም ነው የኢትዮጵያን መሳጭ ቅኝቶች ሲነሱ ሁሉንም ቅኝቶች አግዝፋ የገዘፈች ናት የምትባለው ።እርሷ የባህል አምባሰደርና የቅኝቶች ንግስት ከመሆን አልፋ ማርና አምባሰልን ያዋሀደች እርሷ ማሬዋ ነች፡፡
“የአምባሰል ማር ቆራጭ ይወጣል በገመድ፣
አደራ ቢሰጡት ይበላል ወይ ዘመድ፡፡
የአምባሰል ገደሉን ምን ያሽሟጥጡታል፣
ፈረስ ባያስጋልብ ማር ይቆርጡበታል፡፡”
ለዚህም ይመስላል ብዙዎች “የአምባሰሏ ንግስት” የሚሏት ።እርሷ ግን ከአምባሰል ቅኝት አልፋ በአራቱም የሙዚቃ ቅኝቶች ነፍስ ዘርታ እንደምታቀነቅን የሚያውቁት ግን “የቅኝቶች ንግስት” እንደሆነች መስክረውላታል ።የዛሬዋ የዝነኞች ገጽ አምዳችን ትኩረት የክብር ዶክተር ድምፃዊት ማሪቱ ለገሰ(ማሬዋ)።
ማንም በሙሉ ስሟ የሚጠራት የለም ። ብዙዎች “ማሬዋ” ሲሏት፤ ብዙዎች ደግሞ “ማርዬ” በማለት ያቆላምጧታል ።ብዙዎች ደግሞ “የአምባሰሏ ንግስት” እያሉ በብዛት ከምትታወቅበት የአምባሰል ቅኝት ጋር ያወዳጇታል ።ማሬዋ ግን ሁሉንም ኢትዮጵያዊ ቅኝቶች በአንድ መድረክ ላይ አሳምራ በማቀንቀን በተግባር ያስመሰከረች ናት ።ለመድረክ የተፈጠረች በመሆኗ ያለምንም የሙዚቃ መሳሪያ አዳራሹን በድምጿ ብቻ ታናጋዋለች፡፡የአድማጮቿን ጆሮ ለመሳብም ማይክ መጨበጥ ብቻ በቂዋ ነው፡፡
(አንችሆየ)
“አንች ሆዬ ምነው የሚሏት ዘፈን
አምና ብር በላች ዘንድሮም ወይፈን
ኧረ ደሴ ደሴ ገራዶ ገራዶ ገራዶ
አለቀልህ ልቤ ተንዶ ተንዶ” በማለት ርግት ባለ ቅላጼ የአንችሆዬ ቅኝትን ስታቀነቅን በተመሰጦ ጆሮውን የሚነፍጋት ከቶውንም አይኖርም።እንደሚታወቀው “የአንች ሆዬ” ቅኝት ፍቅር የያዘው ሰው የፍቅሩን መጠንና የፍቅረኛውን ውበት ለመግለጽ እየተቀባበለ የሚያንጎራጉረው ቅኝት ነው ።ማርዬም ፍቅር አሲያዥ ዜማዋን ስታንቆረቁር በፍቅር ዓለም በሚያከንፍ ምህታት የምታዜም ትመስላለች ።አፍታም ሳትቆይ ቅኝቷን ትቀይርና ወደ ባቲ ትወስደናለች።የባቲ ቅኝት ደግሞ ሁለት አይነት የዜማ ስልት ያሉት በመሆኑ ብዙ ጊዜ በባቲና በአካባቢው ያለውን ውበት በማውሳት የሚዜም ስልት ነው ።እንኳን ለሚያውቀው ይቅርና አካባቢውና የማያውቀው ሁሉ የአካባቢው መልከአምድራዊ አቀማመጥ በህሊናው እንዲገዝፍበት ታደርገዋለች ።“የባቲ ቅኝት” ፍቅርና ጥላቻን፤ እንዲሁም ደስታና ሀዘን የሚገልጥበት ቅኝት እንደሆነ ባለሙያዎች ይናገሩታል ።
(ባቲ)
“ኧረ ባቲ ባቲ.. ባቲ ገንደላዩ፣
ሃድራው የሚሞቀው ደራርበው ሲተኙ፡፡
እንደምነው ባቲ ቀርሳ ወንዛ ወንዙ፣
አርቲና አሽኩቲው ቀጠናዩ ብዙ፡፡
የሰው ሁሉ ህመም ራስ ወገቡን ነው፣
የኔስ በሽታዬ ባቴን ነው ባቴን ነው፡፡” በማለት አዚማ ሳንጠግባት ወደ ትዝታ ቅኝት ስትሸጋገር ከመሰንቆው ቅኝት ቀድማ ነው፡፡
የትዝታ ቅኝት በአምስት ድምጻች የሚዋቀር ዜማ በመሆኑ ብዙ ጊዜ ለስለስ ያሉ ዜማዎችን ለማዜም የሚጠቀሙበት የሚያረጋጋ ቅኝት ነው ።ማህበረሰቡ ለሀዘን፣ ለትካዜና ለብሶት መሰል የሕይወት ገጠመኞች ለመግለጽ የሚጠቀሙበት እንደሆነም ይነገርለታል፡፡
(ትዝታ)
“ትዝታሽን ውሰጅ ብለህ የላክብኝ ፣
በል እዛው ይቀመጥ እኔም ያንተ አለብኝ፡፡
በትዝታ ባህር ከወዲህ ሰጥሜ፣
ስጋዬን ጨርሼ ቀርቻለሁ በአጽሜ፡፡” በማለት በትዝታ ባህር ስታንሳፍፈን ትቆይና አፍታም ሳትቆይ በብዙ ወደምትታወቅበት አምባሰል ስትወስደን ከቅኝቷ ዝንፍ አትልም፡፡
(አምባሰል)
“አመለኛው እግሬ መጓዝ የለመደ፣
ሀይቅን ሲዞር ውሎ ውጫሌ ወረደ፡፡
እንዴት ነሽ ውጫሌ እንደምነሽ ጭሳ፣
የተቋደስንብሽ ፍቅርን እራት ምሳ፡፡
እኚህ አምባሰሎች አበላል ያውቃሉ፣
ከገብስ እንጀራ ላይ ሳም አርጉ ይላሉ፡፡”
ስኬት- በጥበብ ቤት
ደርባባዋ ማሬዋ ለሙዚቃ ባላት የገዘፈ ፍቅር የተነሳ የገጠር ኑሮዋን ርግፍ አድርጋ ትታ ከተወለደችበት የደሴ ዙሪያ ከድጆ ገጠር ደሴ ከተማን መስፈንጠሪያዋ ነበር ያደረገቻት አድርጋለች ።የልጅነት ባሏን ተከትላ ወረሂመኖ የሄደችው ቆንጆዋ ማሬዋ የገጠር ኑሮን እንዳልወደደች ታስታውሳለች ።እናም ባሏን የነፍሷ ጥሪ ወዳለበት ደሴ ከተማ እንዲወስዳት አደረገችው። ደሴ ከተማ ላይ ለባሏ የሚሆን ሙያ ባይኖርም ለእርሷ የነፍስ ጥሪ አጋዥ የሆነውን መሰንቆ በመግዛት እንዲለማመድ አድርጋዋለች ።መሰንቆ አለማምዳም በየመጠጥ ቤቱ እየተዘዋወሩ ሲዘፍኑ ነፍሳቸውን አስደስተው የእለት ገቢያቸውን እንዲቋጥሩ የደሴ ከተማ አላሳፈረቻቸውም ።የደሴ ከተማም ማርዬ የነፍሷን ጥሪ ታሳርፍ ዘንድ የፍቅር ሙሃባን የምታጎናጽፈው አርሂቡ ብላ ተቀብላ ወደ ወሎ ላሊበላ የኪነት ቡድን በብቃት አቀላቅላታለች፡፡
ማሬዋ በወሎ ላሊበላ ኪነት ውስጥ እያለች ነው ዝናዋ መናኘት የጀመረው ።በ1975 ዓ.ም በሙዚቃ አፍቃሪያን ዘንድ ከፍተኛ ተቀባይነት ያገኘው ‹‹አምባሰል›› የተሰኘ ሙሉ ካሴት ምስክሯ ነው። በመጀመሪያው የካሴት ስራዋ 12 ዘፈኖች የያዘ ሲሆን ትዝታ፣ ባቲና የአንቺ ሆዬ ቅኝቶችን ያካተተ ተወዳጅ አልበም በመሆኑ፤ በመላው ኢትዮጵያ ማሪቱ ለገሰ የተሰኘች ድንቅ ድምጻዊት ወሎ ላይ እንደተፈጠረች ያስተዋወቀ ነበር።
ማርዬ ለወሎ ላሊበላ የሙዚቃ ቡድን እንደፈርጥ የምትታይ፤ ደምቃ የምታደምቃቸው በመሆኗ የቡድኑ አባላት በስስት ነበር የሚንከባከቧት ።እርሷን በማየትም እነ ዚነት ሙሀባ፣ ጸሀይ ካሳና ጸሀይ አማረን የመሰሉ እንስት ድምጻውያን እንዲፈጠሩ ምክንያትም ሆናለች። በወሎ ባህል አምባ የኪነት ቡድን ቆይታዋም “እንደው ዘራፌዋ” የተሰኘው ወኔ ቀስቃሽ ሙዚቃዋ የዘመኑ ባለውለታ እንደነበር ይነገርለታል፡፡
በኢትዮጵያ የኪነጥበብ ታሪክ ውስጥ “ሊደገም የማይችል ድንቅ ስራ” የተባለለት የህዝብ ለህዝብ ዘመቻ ነው፡፡በመላው ዓለም በመዘዋወር ባቀረቡት የጥበብ ስራ የኢትዮጵያን መገለጫ የነበረውን የርሀብ ገጽታ ቀይረውበታል ።የኢትዮጵያን መሳጭ ባህል ለዓለም አስተዋውቀውበታል ።በዚህ የምርቶች ምርጥ የህዝብ ለሕዝብ ቡድን ውስጥ ለመካተትም ያበቃት በአንድ ድምጽ የሚመሰከርለት ብቃቷ እንደነበር አይካድም፡፡
ማርዬ በሕዝብ ለሕዝብ የባህል ቡድን ጋር አብራ ተጉዛ መላውን ዓለም አይታለች ።በቡድኑ ውስጥ ቆይታዋ ብዙ ገጠመኞችና ልምዶችን አትርፋለች። በወቅቱ ከነበረው መንግስትም ከፍተኛ አድናቆትና ሽልማትን ተቀብላለች ።
የባህል ልብስ ውጭ ሌላ ልብስ ባለመልበስ የምትታወቀው ማሬዋ የባህል ልብሶቻችን በመላው ዓለም በማስተዋወቅም የባህል አምባሳደርነት ሚናዋን በሚገባ ተወጥታለች። ማሬዋ “የፈረንጅ ቀሚስ የሞት መድሃኒት ነው ቢባል በቤቴ የለም” በማለት ነው ለባህሏ ያላትን ፍቅር ከነፍሷ እንደምታስበልጥ የምትናገረው ።ከ600 በላይ የባህል አልባሳት እንዳላትም በኩራት ጠቁማናለች፡፡
ማርዬና እርጅና ሳይገናኙ የተላለፉ ይመስላሉ።በዙሪያዋ አድናቂዎቿና ወዳጆቿ እስካሉ ደረስ ስለምንም ነገር አለመጨነቋን በምክንያትነት ትገልጻለች ።ለዚህም ነው ያለማርጀቷ ምስጢር ለብዙዎች መነጋገሪያ የሆነው ።ማሬዋ በሁሉም ኢትዮጵያዊ ዘንድ ተወዳጅ በመሆኗ “እንደተወደደች የኖረች፣ በኖረችም ቁጥር እንደ ንጹህ ማር ጣዕሟ ያልተቀየረ የባህል ሙዚቃ መድኃኒት ናት” ተሰኝታለች፡፡
የወሎ ዩኒቨርሲቲ ሰኔት ሰኔ 8 ቀን 2008 ዓ.ም ባደረገው ስብሰባ በሕይወት ዘመኗ ላበረከተችው የላቀ አስተዋጽኦ የክብር ዶክትሬት በሌለችበት አበርክቶላታል። የመመረጧ ምክንያት ደግሞ ከኢትዮጵያ ሙዚቃ እድገት፣ በተለይም ከአራቱ የሙዚቃ ቅኝቶች መካከል አምባሰል የሙዚቃ ቅኝት ለእሷ ብቻ የተፈቀደላት እስኪመስል ድረስ በማዜም ለወሎ የሙዚቃና ኪነ ጥበብ እድገት የአበረከተችው አስተዋጽኦን ከግምት በማስገባት እንደነበር በወቅቱ ተገልጦ እንደነበር ይታወሳል። ከእውቅናው በተጨማሪም ዩኒቨርሲቲው በውስጡ ያቀፈውን የወሎ ላሊበላ የባህልና ኪነ ጥበብ ማእከል የበላይ ጠባቂ እንድትሆንና ያላትን ልምድ ለዩኒቨርሲቲው የሙዚቃ ትምህርት ክፍል የምታካፍልበት እድል ሰጥቷት እንደነበር ይታወሳል።
ያልታሰበው ስደት
የደርግ መንግስት ወድቆ ኢህአዴግ አገሪቱን የተቆጣጠረበት ነበር የማርዬ የሕይወት መስመር የተቀየረው ።ለውጡን ተከትሎ የወሎ ላሊበላ ኪነት ቡድን ሲበታተን የማርዬም እጣ ፋንታ ከምትወደው የሙዚቃ ቡድን መለየት ነበር ።ቡድኑ ተበታትኖ ከጥበብ ስራ ቢርቅም እርሷ ግን ከቡድን በላይ የሆነው የፈጣሪ ስጦታ በእጇ ላይ ስላለ ብዙም አልተቸገረችም ነበር፡፡
ያላት ሀብት ድምጿና አድናቂዎቿ ነበሩና ወደ አዲስ አበባ በመምጣት ካሳንችስ አካባቢ የምሽት ቤት ከፈተች ።እርሷ ብቻዋን ምቾትን አልተመኘችምና የፈረሰው የወሎ ላሊበላ ኪነት ቡድን ሙያተኞችን ከተበተኑበት አሰባስባ ማሰራት ጀመረች ።እውቅናዋ እየናኘ በመጣበት በዚህ ወቅት ነበር ወደ አሜሪካ ያልታሰበ የስራ ጥሪ የቀረበላት፡፡የቀረበላት ማማለያ አሸነፋትና የማታውቃትን አሜሪካ ተመኘቻት፡፡
ከፍተኛ ዝናን እያገኘ የመጣውን የምሽት ቤቷን ዘግታ ከተወሰኑ ሙያ ባልደረቦቿ ጋር ወደ አሜሪካ አቀናች ።የሄዱበት ስራ እንደታሰበው የተሳካ ባለመሆኑ “ከዛሬ ነገ ትንሽ ገንዘብ ሰርተን እንመለሳለን” ሲሉም ጊዜው ነጎደ ።የካዛንችሱ ምሽት ቤቷም ከነንብረቱ በሃራጅ ተሸጠ ።በሁኔታው ተስፋ የቆረጠችው ማሬዋ ቀልቧን አገሯ ላይ አድርጋ በስጋዋ ስደትን ተቀብላ 23ቱን አመታት ተጋፈጠቻቸው ።በነዚህ አመታት ሁሉ ወደአገራ ለመመለስ ብታስብም ህጋዊ የመኖሪያ ፈቃድ አላገኘችምና ሊሳካላት እንዳልቻለች በቁጭት ትናገራለች ።በስደት መኖሩ የውዴታ ግዴታ ሆኖባት የአገር ናፍቆትን ተላምዳው መኖርን ምርጫዋ አደረገች፡፡
ወደ አገር ቤት
ማርዬ በእድሜዋ በርካታ ሀዘንና ደስታን አስተናግዳለች ።ከአብራኳ ካፈራቻቸው 12 ልጆች መካከል በሕይወት ያለው አንዱ ብቻ ነው፡፡በተለያዩ ጊዚያት ልጆቿን ሞት ቢነጥቃትም በስደት ላይ እያለች ያጣቻቸው የሶስቱ ልጆቿን ሀዘን ግን ብዙ በብዙ ፈትኗት እንደ ነበር ትናገራለች ።በሰው አገር ሃዘኗን ዋጥ አድርጋ በሕይወት ባለው አንድ ልጇ እና በልጅ ልጆቿ እየተጽናናች ወደአገሯ የመምጫዋን እለት በመጠባበቅ 23 ዓመታትን ከናፍቆት ጋር እየታገለች አሳልፋለች፡፡
ማርዬ ዛሬ ነጻነቷን አውጃለች ።ብዙ ያደከማት የመኖሪያ ፈቃዷን አግኝታለች ።ከ23 የናፍቆት ዓመታት በኋላ ወደ አገሯ የምትመጣበትን ቀን ቆርታለች ።ወደአገሯ ስትመለስ እጅሽ ከምን ለሚሏት አድናቂዎቿም ምላሽ የሚሆን አንድ አልበም ሰርታለች።በ ቅርቡም ወደአገሯ ስትመለስ የናፈቃትና በጉጉት የጠበቃትን ህዝብ በሙዚቃዋ ልታስደስተው ገናን ደሴ ላይ፤ ጥምቀትን ጎንደር ላይ እንዲሁም አዲስ አበባን ጨምሮ በተመረጡ ከተሞች የሙዚቃ ኮንሰርቶች ለመስራት እቅድ ይዛለች፡፡
በተለይም በተለያዩ ምክንያቶች የተጎዱ ወገኖቿን ለመደገፍ የሚያስችል የገቢ ማሰባሰቢያ ስራዎችን ለመስራት አቅዳለች ።በአዲሱ አልበሟም በሁሉም ቅኝቶች የተቀነቀኑ ተወዳጅ ሙዚቃዎችን እንዳካተተች ተናግራለች ።የአገርና የወዳጅ ዘመድ ናፍቆት ያንገላታት ማሬዋ ኢትዮጵያ ውስጥ ያልናፈቃት ነገር የለም። በተለይም ቡናው፣ ቄጤማው፣ ቀንጦው የወሎ ጢስ በአይኗ ላይ እየዞረባት እንደሆነ ተናግራለች፡፡
ስጋዋን በስደት፤ ነፍሷን አገራ ላይ ያደረገችው ማርዬ “በኢትዮጵያ ጉዳይ አትምጡብኝ” በማለት ትታወቃለች ።ለድጋፍ ማሰባሰቢያ ሰልፍ ከተጠራ ባንዲራዋን ይዛ በባህል አልባሳቷ ደምቃ ለመውጣት የሚቀድማት የለም ።እነሆ ዛሬ የስደት ኑሮዋን ልትቋጭ ጓዟን ሸክፋለች ።እናም አድናቂዎቿና ወዳጆቿ ለክብሯና ለአበርክቶዋ የሚመጥን የደመቀ አቀባበል ሊደረግላት “ማሪዋን ያላችሁ…” ተብሎ የመምጫዋ ቀን አድናቂዎቿ በመጠባበቅ ላይ ናቸው፡፡
የሙያ አጋሮቿ እነ ድምጻዊት ጸሀይ ካሳ የአሜሪካን አገር አላማጆቻ ናቸው ።በደስታዋም ሆነ በሀዘኗ ከጎኗ ሳይለዩ አብረዋት አዝነዋል፤ አብረዋት ተደስተዋል።በህመሟ ጊዜም አብረዋት ታመዋል።አሁንም በአሜሪካ ዋሽንግተንና አካባቢው ለሚገኙ አድናቂዎቿ የሽኝት መርሃ ግብር ሲያዘጋጁ የቀደማቸው የለም ።ወደ ኢትዮጵያ ስትመጣም በአዲስ አበባና ለተለያዩ ከተሞች የደመቀ አቀባበል ለማድረግ ከተለያዩ አካላት ጋር በመተባበር ሁኔታዎችን በማመቻቸት ላይ መሆናቸውን ተናግረዋል። ከአድናቂዎቿ ጋር የምትገናኝበትንም መድረኮች በማመቻቸት ላይ ናቸው ።“ማርዬ የተወለደችበት አካባቢ ሀብት ሳትሆን የመላው ኢትዮጵያውያን ሀብት ናት” የምትለው ድምጻዊት ጸሀይ ካሳ አሸኛኘቷም ሆነ አቀባበሏ ለአገሯ ላበረከተችው አስተዋጽኦ በሚመጥን መልኩ እንዲሆን አደናቂዎቿም ሆኑ መላው ኢትዮጵያውያን ድጋፍ እንዳይለያቸው ጥሪዋን አስተላልፋለች፡፡
ድምፃዊት ማሪቱ ለገሰ
አዲስ ዘመን ኅዳር 25/ 2015 ዓ.ም