የዓለም ሊቀ ሊቃውንት፣ የኪነ ጥበብ ምሑር፣ እጅግ የተከበሩ የዓለም ሎሬት ሰዓሊ አፈወርቅ ተክሌ ያረፉት ከዛሬ ሰባት ዓመታት በፊት፣ በዚህ ሳምንት (ሚያዝያ 2 ቀን 2004 ዓ.ም) ነበር።
እጅግ የተከበሩ የዓለም ሎሬት ሜትር አርቲስት አፈወርቅ ተክሌ ከአባታቸው አቶ ተክሌ ማሞ እና ከእናታቸው ከወይዘሮ ፈለቀች የማታወርቅ ጥቅምት 13/1925 ዓ.ም በቀድሞው ሸዋ ጠቅላይ ግዛት፣ አንኮበር ከተማ ተወለዱ።
ገና በጨቅላ ዕድሜያቸው ፋሺስት ኢጣልያ ኢትዮጵያን በግፍ ስለወረረች፣ የልጅነት ትዝታቸውም ይሄው የግፍ ወረራ እና ጦርነት ያስከተለው የሰው፣ የንብረት እና የባህል ጥፋት ነበር።
ከነፃነት በኋላም ዐቢይ ሥራቸው በወረራ የተበላሸችውን ሀገራቸውን እንደገና መገንባት ነበር። ለዚህም የሀገር ግንባታ አስፈላጊውን እውቀት መሸመት የፈለጉት በማዕድን ምሕንድስና ዘርፍ ነበር። ወላጆቻቸውና ዘመዶቻቸው ግን የኪነ-ጥበብ ስጦታቸውን በቤታቸውና በከተማው ዙሪያ በሚስሏቸው ስዕሎች ተገንዝበውት ነበር።
ገና በአሥራ አምስት ዓመታቸው በ1940 ዓ.ም ለከፍተኛ ትምህርት ተመርጠው የምሕንድስና ትምህርታቸውን ለመከታተል ወደ እንግሊዝ አገር ተላኩ። በትምህርት ቤት ቆይታቸውም፣ የባዕድ ባህላት፣ የአየር ለውጥ እና የተለመደው የተማሪ ቤት ዝንጠላ ቢያስቸግራቸውም ትምህርታቸውን በትጋት ሲከታተሉ ቆይተው በተለይም በሒሣብ፣ በኬሚስትሪ እና በታሪክ ትምህርቶች ጥሩ ውጤት በማምጣት ሰለጠኑ።
ነገር ግን አስተማሪዎቻቸው የተፈጥሮ ስጦ ታቸው ኪነ-ጥበብ እንደሆነ ለመገንዘብ ብዙም ጊዜ አልወሰደባቸውም። በእነርሱ አበረታችነትም በዚህ ስጦታቸው ላይ የበለጠ ለማተኮር ወስነው በለንደን (Central School of Arts & Crafts) ተመዝግበው መማር ጀመሩ። ከዚህ ትምህርት ቤት ትምህርታቸውን ሲያጠናቅቁም፣ ለከፍተኛ ጥናት ወደ ስመ ጥሩው የለንደን ዩኒቨርሲቲ የስሌድ ኪነ ጥበብ ትምህርት ቤት (Faculty of Fine Arts at Slade) የመጀመሪያው አፍሪቃዊ ተማሪ በመሆን ገቡ።
በዚህ ትምህርት ቤት ውስጥም በስዕል፣ ቅርጽ እና በአርክቴክቸር ጥናቶች ላይ አተኩረው ተመረቁ። ትምህርታቸውን አጠናቀው ወደ ኢትዮጵያ ሲመለሱ፣ በየጠቅላይ ግዛቶቹ እየተዘዋወሩ (በየቦታው እስከ ሦስት ወራት በመቀመጥ) የኢትዮጵያን ታሪክና የብሔረሰቦቿን ባህልና ወግ ሲያጠኑ ቆዩ።
ከውጭ ሲመለሱ የተመደበላቸውን ሚኒስቴራዊ ሥራ ትተው የኪነ-ጥበብ ሥራቸው ላይ በማተኮር ስዕሎቻቸውን በአገር ውስጥና በውጭ እያሳዩ ለማገልገል ቆረጡ። በሃያ ሁለት ዓመታቸውም በ1946 ዓ.ም ሥራቸውን የሚያሳይ የመጀመሪያውን የኪነ-ጥበብ ትርዒት በአዲስ አበባ ማዘጋጃ ቤት አቀረቡ።
ወዲያውም ከዚህ ትርዒት ባገኙት ገቢ ተመልሰው ወደ አውሮፓ በመሄድ ለሁለት ዓመታት በኢጣልያ፣ በፈረንሳይ፣ በስፔን፣ በፖርቹጋል፣ በብሪታንያና በግሪክ የጠለቀ የኪነ- ጥበብ ጥናት አከናወኑ። በተለይም በነዚህ አገሮች ውስጥ በስደት የሚገኙትን የኢትዮጵያ ጥንታዊ ሃይማኖታዊ የብራና መጻሕፍት በጥልቅ አጠኑ። በተጨማሪም፣ የመስታወት ስዕል (Stained Glass Art) እና የሞዛይክ አሠራርን ጥበብ ተምረው ወደአገራቸው ተመለሱ።
ከዚያም ንጉሠ ነገሥቱ የመናገሻ ቅዱስ ጊዮርጊስ ቤተ-ክርስቲያንን በሃይማኖታዊ የግድግዳና የጣሪያ ስዕሎች፣ የሞዛይክ ሥራዎች፣ መስኮቶቹንም በመስታወት ስዕሎች እንዲያሳምሩት ነግረዋቸው አሁን የምናያቸውን እንደ “የዳግማዊ ምጽአት ፍርድ”፣ የእመቤታችንን ንግሰት የሚያሳየው “ኪዳነ ምሕረት”፣ እና የቀዳማዊ ኃይለ ሥላሴን የዘውድ ሥርዓት የሚያሳዩ ሥራዎቻቸው ይገኙበታል።
አከታትለውም አሁን በሐረር ከተማ የሚገኘውን የልዑል ራስ መኮንንን ሐውልት ሠሩ። የስዕል እና ሌሎች የኪነ ጥበብ ሥራዎቻቸውም በቴምብሮች፣ በሀገር ውስጥም ሆነ በውጭ ሀገር የኪነ ጥበባት ትርዒቶች ላይ እጅግ በጣም እየታወቁና እየገነኑ መጡ።
እጅግ የተከበሩ የዓለም ሎሬት ሜትር አርቲስት አፈወርቅ ተክሌ በውጭ አገር የተማሩ ቢሆኑም፣ እሳቸው ‹‹ዋጋ ቢስ›› የሚሉትን፣ እንደሌሎች (ምዕራባውያንም ሆኑ ሌሎች) የሚጠቀሙበትን ‹‹ኩረጃ›› ላለመከተል በትጋት ጥረዋል።
ከአያሌ ድንቅ ሥራዎቻቸው መካከል አዲስ አበባ፣ በአፍሪቃ አዳራሽ መግቢያ የሚታየው በመቶ ሃምሳ ካሬ ሜትር ላይ የተሳለው ትልቅ የመስታወት ስዕል፣ በአዲስ አበባ በመናገሻ ቅዱስ ጊዮርጊስ ቤተ ክርስቲያን የሚገኙ ስዕሎች፣ በአዲስ አበባ በቅዱስ ጳውሎስ ሆስፒታል የሚገኘው የመጀመሪያው የ‹‹ዳግመኛ ምጽዓት ፍርድ›› ስዕል፣ በሐረር የልዑል ራስ መኮንን ሐውልት፣ ‹‹እናት ኢትዮጵያ››፣ በለንደን ‹‹ታወር ኦፍ ለንደን›› የቅዱስ ጊዮርጊስ ጸሎት ቤት ከብርና ከእንጨት የተሠራ የመንበር መስቀል እንዲሁም በሩሲያ፣ በአሜሪካ እና በሴኔጋል ትርዒቶች የታየው ‹‹የመስቀል አበባ›› ተጠቃሽ ናቸው።
እጅግ የተከበሩ የዓለም ሎሬት ሜትር አርቲስት አፈወርቅ ተክሌ ዓለም አቀፍ ዝናን ባስገኙላቸው ሥራዎቻቸው ምክንያት በርካታ ሽልማቶችን ያገኙ ሲሆን ለአብነት ያህል በ1958 ዓ.ም የቀዳማዊ ኃይለሥላሴ የሽልማት ድርጅት ተሸላሚም ናቸው።
በ1958 ዓ.ም በሩስያ ሞስኮ ታላቅ የስዕል ኤግዚቢሽን አሳዩ፤ በተለያዩ ዩኒቨርሲቲዎች በመገኘት አስደናቂ ንግግሮችን አደረጉ። በ1959 ዓ.ም በአሜሪካ መንግሥት ግብዣ በዋሽንግተን እና ኒው ዮርክ ከተሞች የአንድ ሰው የስዕል አውደ ርዕይ ለሕዝብ አቀረቡ። በታወቁና ከ22 በላይ በሆኑ ዩኒቨርሲቲዎችና ተቋማት በመገኘት ንግግር አደረጉ፤
በ1964 ዓ.ም የሰው ልጆችን ወንድማማችነትና የሰላም ልዕልናን የሚመሰክረውን ሥራቸውን በተለያዩ አገሮች አቀረቡ። በዚህ ሥራቸው በ1971 ዓ.ም በአልጀርስ የጥበብ ፌስቲቫል የወርቅ ሽልማት ክብርን አገኙ።
በፈረንሳይ አገር ባቀረቡት የሥዕል ሥራ የጃፓን፣ የፈረንሳይና የሜክሲኮ ተወዳዳሪዎችን በልጠው አንደኛ ወጥተው ከመሸለማቸውም በላይ፣ የቤናል የሎሬት ማዕረግን ክብር አገኙ።
እ.ኤ.አ በ2000 ዓ.ም በዋሽንግተን ዲሲ በተጠራው 27ኛው የአሜሪካ ባዮግራፊካል ኢንስቲትዩት ዓለም አቀፍ ጉባዔ ላይ የዓለም ሎሬትነት ክብርን ተቀዳጁ።
እ.ኤ.አ በ2004 በአየርላንድ ደብሊን ላይ በተጠራው የሳይንስ፣ ባህልና ጥበብ ጉባኤ ለሰው ልጆች ትምህርትና ለጥበብ ዕድገት ለዓለም ባበረከቱት መልካም ተግባር ‹‹የዳቪንቺ አልማዝ ሽልማት››ን ሲቀበሉ፣ በዚሁ ጉባኤ በአሜሪካ ዩናይትድ ካልቸራል ኮንቬንሽን (United Cultural Convention) የተባለው ተቋም ለዓለም ጥበብ ዕድገት ላበረከቱት መልካም ሥራ የጀግና ክብር ኒሻን ሸልሟቸዋል።
እጅግ የተከበሩ የዓለም ሎሬት ሜትር አርቲስት አፈወርቅ ተክሌ ባደረባቸው ጽኑ ሕመም በሕክምና እየተረዱ ሳለ፣ ማክሰኞ፣ ሚያዝያ 2 ቀን 2004 ዓ.ም በተወለዱ በ79 ዓመታቸው በአዲስ አበባ ካዲስኮ ሆስፒታል አርፈዋል። የቀብር ሥርዓታቸውም በመንበረ ጸባኦት ቅድስት ሥላሴ ካቴድራል ተፈጽሟል፡፡
አዲስ ዘመን ሚያዝያ 4/2011
በአንተነህ ቸሬ