በመንግስትና በሕወሓት መካከል በደቡብ አፍሪካ ፕሪቶሪያ የተደረሰበት የሰላም ስምምነት ዜና ከተሰማ ማግስት ጀምሮ አገርና ህዝብ በአዲስ ተስፋና የታሪክ መንገድ ላይ ናቸው። ስምምነቱም የፈጠረው ደስታ በቀላሉ የሚታይ አይደለም ። ጥቅማችንን ያሳጣናል ብለው ከሚያስቡ ጥቂቶች በስተቀር ሁሉንም ኢትዮጵያዊ የገዛ ነው።
እሰየው! አሁን ላይ ያለፉትን ሁለት ዓመታት ችግሮቻችንን መቀልበስ በሚያስችል መግባባት ላይ ደርሰናል። ይሕ በአንድ አገርና በአንድ መንግስት ሥር ለሚተዳደሩ ወንድማማች ሕዝቦች እጅግ አስፈላጊ ነው። ለቀጣይ እጣ ፈንታቸውም ወሳኝ አቅም ነው ።
የችግሩ ግንባር ቀደም ገፈት ቀማሽ ከመሆን ባለፈ የከፈለውም አላስፈላጊ ዋጋ ለግምት የሚከብድ በመሆኑ፤ የሰላም ስምምነቱ ብዙ ቱሩፋቶች ይዞ ስለመምጣቱ ለህዝባችን ማብሰር የሚያስፈልገው አይደለም ።
ዛሬ ላይ ኑሮውን በማያባራ ግጭትና ሁከት ውስጥ አድርጎ በጭንቀት ይመራ የነበረው የትግራይ ሕዝብ ሰላም በመውረዱ ከጭንቀት ወጥቷል። ተረጋግቶ ወደ መኖርም እያመራ ነው። ስምምነቱን ተከትሎም መንግሥት ወደ ትግራይ ክልል ሰብዓዊና ቁሳዊ ድጋፍን በስፋት ተደራሽ ሲያደርግ እያስተዋልንም እንገኛለን።
ተደራሽ እያደረጋቸው የሚገኙ የምግብና የጤና ቁሳቁሶች እለት እለት እየጨመሩ ነው። ይህ ደግሞ የእለት ምግብ አቅርቦት ችግር ውስጥ ለነበረው ለትግራይ ወንድሞቻችን ምን ማለት እንደሆነ መናገር የሚችሉት እነሱ ናቸው።
ከዚህም ባለፈ በጦርነቱ ተቋርጠው የነበሩ እገልግሎቶችን ማስጀመር፤ ፈራርሰውና ከጥቅም ውጪ ሆነው የነበሩ የአገልግሎት ተቋማትን መገንባትና መጠገን ቀጥሏል። ሩቅ ሳንሄድ የጦር አውድ በነበረችው አላማጣ ከተማ ያለውን ብናይ በጦርነት ውስጥ ማስቀጠል ያልተቻሉ አገልግሎት የሰላም ስምምነቱን ተከትሎ ማስቀጠል እየተቻለ ነው።
በከተማዋ ተዘግተው የነበሩ የንግድ ተቋማት ተከፍተዋል ለሕብረተሰቡ አገልግሎት እየሰጡ ነው። ሌሎች በርካታ ማህበራዊ አገልግሎቶችም ወደ ሥራ እየገቡ ነው። የጤናና የትራንስፖርት አገልግሎቶች ሕብረተሰቡን ወደ ማገልገሉ ተመልሰዋል።
የከተማዋ ነዋሪዎች በሚያስተማምን ሁኔታ የንፁሕ መጠጥ ውሃ አገልግሎት እያገኙ ነው። እንደውም የሁለት ጂ እና የሶስት ጂ የኢንተርኔት አገልግሎትም ተጀምሯል። የኢንተርኔት አገልግሎቱን ፈጣን ለማድረግ በጦርነት የተበጣጠሱ ፋይበሮችን የመጠገኑ ሂደት እየተፋጠነ ነው።
የሰላም ስምምነቱን ተከትሎ የኢትዮጵያ አየር መንገድም ወደ ትግራይ ክልል አቋርጦት የነበረውን በረራ ዳግም ለመጀመር ሰፊ ዝግጅት እያደረገ መሆኑም እየተሰማ ነው። በዚህም ለህዝቡ የሰብዓዊ አቅርቦት ድጋፎችን በስፋት ለማድረስ ታስቦ እየተሰራ ነው።
የአየር መንገዱ የስራ ኃላፊ ሰሞኑን ሲናገሩ እንደተደመጠው፤ በክልሉ ከሚገኙ ኤርፖርቶች መካከል የመቀሌ እና የሽሬ አየር ማረፊያ ተቋርጦ የነበረውን በረራ ዳግም ለማስቀጠል ምቹ በሆኑበት ደረጃ ላይ ይገኛሉ። በአንፃሩ የአክሱም አየር ማረፊያ በግጭቱ የደረሰበት ጉዳት መጠነ ሰፊ በመሆኑ ለበረራ በሚመች መልኩ የማስተካከሉን ሥራም የመሥራቱ ጉዳይ ታሳቢ መሆኑን ጠቁመዋል።
በሰላም ስምምነቱ ትግበራ አኳያ በመንግሥት በኩል በየትኞቹም መገናኛ ብዙሃን ግጭት ቀስቃሽ መልዕክቶች እንዳይተላለፉ ከማድረግ ጀምሮ እንዲህ የሚያበረታቱ የትግበራ ጥረቶች የመኖራቸውን ያህል በሕወሓት በኩል ያለውም እጅግ የሚደነቅና የሚበረታታ እንደሆነ ማየት የሚያስችሉ ብዙ አመርቂ እንቅስቃሴዎች ይታያሉ። በሕወሓትም በኩል የሚታየው አበረታች ነው።
ይህም ሆኖ ግን አንዳንድ ወገኖች ምን አልባትም ከውጭም/ከአገር ውስጥም ያሉ ግለሰቦች ይሄ የሁለቱ ወገኖች ስምምነት የወለደው የሰላም ቱሩፋት የተዋጠላቸው አይመስሉም። እነዚህ ጥቂት ወገኖች ወይም ግለሰቦች ከግጭት አንዳች የሚያተርፉት ነገር ያላቸው ሊሆኑ እንደሚችሉ አያጠራጥርም/የግጭት ነጋዴዎች /።
”አውቆ የተኛ ቢቀሰቅሱት አይሰማም ”እንዲሉ ለነዚህ ክፍሎች ስለ ሰላም ፋይዳ እየነገሩ ግንዛቤ ማስጨበጡ ድንጋይ ላይ ውሃ የማፍሰስ ያህል ከንቱ ነው። ዕውቁ ኒውሮሳይንቲስት፣ ሳይኮሎጂስትና ሳይኪያትሪስት የአንጎል ሳይንቲስት ፕሮፌሰር ድሪው ዌስተን እንደሚለው፤ እንዲህ ዓይነት ግለሰቦች ወይም ክፍሎች አእምሯቸው የስምምነትና የሰላም ሀሳቡን እንዳይቀበል አደንዝዘውታል።
የሚታያቸው ግጭቱ፤ ተከትሎት የሚከሰተው ብጥብጥና ሁከት እነሱ ከዚህ ሊያተርፉ የሚችሉት ጥቅም ብቻ ነው። ‹‹You can’t teach an old dog a new trick›› ወይም በአማርኛው ሲተረጎም ”ያረጀን ውሻ አዲስ ሙድ” አታስተምረውም እንዲሉት ዓይነቱ የቆየ አባባል ካረጁ ካፈጁ ወዲህ ጭንቅላታቸው አዲስ ዓይነት ልምምድን በፍፁም በጄ ብሎ አይቀበልም።
በዓመታት ተመሣሣይ የአስተሳሰብ መንገድና ያንን መንገድ መቀየር እንደሌለበት በተግባር ተሞክሮ እንደተረዳ የሚያምንን እንደ ጉቶ የደነደነን የጎልማሳ ወይ የአዛውንት ሰው አዕምሮ፣ ከሚያውቀው የተቃረነ ወይም አዲስ ነገርን ላስተምርህ ብንለው ቢፈልግም ጭንቅላቱ በጄ አይለውምና መከራው ብዙ ነው።
ውሻውን በቡችልነቱ አግኝተን የፊት እግሩን አንስቶ እጃችንን እንዲጨብጥ፤ በኳስ እንዲጫወት፤ ሽኮኮ እያደነ እንዲደሰት፤ የሰርከስ ትርዒት አክሮባቲስት እንዲሆን፣ ወይ ቀላል የመደመርና የመቀነስ ስሌቶችን እንዲሰራልን፤ አልያም የተቀበረ ፈንጅ እንዲያነፈንፍ አስተምረነው ቢሆን ኖሮ ለመቀበል የሚያዳግተው እንደማይኖር ሁሉ የነዚህ የሰላም ስምምነቱ ያልተዋጠላቸው ሰዎች ነገርም እንዲሁ እንደ ቡችላው መሆን ነበረበትና አይገርምም።
ፕሮፌሰር ድሪው ዌስተን፤ እኛ ሰዎች ፖለቲካ- ነክ መረጃዎችን እና የህግ-ነክ መረጃዎችን እንዲሁም ከቆየ አስተሳሰባችን ወጣ ያሉ አዲስ አስተሳሰቦችን የምንቀበልበትንና ‹‹ፕሮሰስ›› የምናደርግበትን (የምናሰላስልበትን ወይም የምናብላላበትን) መንገድ ያጠናበትን መጥቀስ አስፈላጊ ይመስለኛል።
ፕሮፌሰሩ ከ20 ዓመት በላይ በተለያዩ ሰዎች አንጎል ላይ ተመራምሮ እንዳገኘው ግኝት የፈለገውን ያህል ፊደል የቆጠሩ የፖለቲካ ደጋፊዎች – የሚደግፉትን የፖለቲካ ፓርቲ – ወይም የሚከተሉትን ፖለቲከኛ ግድፈቶች – ወይም ግልጽ ያሉ የተቃረኑ አቋሞች – የሚያየውን የአንጎላቸውን ክፍል አደንዝዘውታል። ምንም እንከኖችን እንዳያይ፣ እንዳይሰማ፣ አዳፍነውታል።
በዚህ ምክንያት የሰላም ስምምነቱ ሀሳብ ሳይዋጥላቸው ቢቀር አይጭነቀን። ሆኖም አንጎላቸውን የመለወጥ ጥረታችንን ሳናቋርጥ ስምምነቱን አእምሯችን የተቀበለልን ሁሉ ለሰላም ለስምምነቱ ትግበራ በየፊናችን እንትጋ!።
ሰላማዊት ውቤ
አዲስ ዘመን ኅዳር 24/ 2015 ዓ.ም