በኮሪያ ህገመንግስት እ.እ.አ ከ1953 ጀምሮ የጸደቀው የውርጃ ህግ የሴቶችን ጤና አደጋ ላይ የሚጥልና መብታቸውን የማያከብር ነው በሚል የሰባዊ መብት ተሟጋቾችና የተለያዩ ኮርያውያን ቅሬታቸውን ለማሰማት አደባባይ ወጡ።
የቢቢሲ ሪፖርተር ላውራ ብቸከር በአገሪቱ በፍርድ ቤት አካባቢ የነበረውን ተቃውሞ እንደገለጹት፤ በመቶዎች የሚቆጠሩ ሰልፈኞች በፍርድ ቤት ቅጥር ግቢ ውስጥ ተገኝተው አንዳንዶቹ የውርጃ እገዳ ህጉ መነሳት እንዳለበት
ተቃውሟቸውን ሲያሰሙ በአንጻሩ ሌሎች ደግሞ የውርጃ ህጉ ባለበት እንዲቀጥል ለፍርድ ቤቱ ጥሪያቸውን አቅርበዋል።
እ.እ.አ የ1953 የሀገሪቱ ጽንስ ማቋረጥን የሚያግደው ህግ ሴቶች አስገድዶ መደፈር ካልገጠማቸውና ጽንሱ ለጤናቸው አስጊ ካልሆነ በስተቀር የሚያስወርዱ ሴቶች ህግ ፊት ቀርበው ቅጣት እንዲጣልባቸው ያስገድዳል። የአገሪቱን የውርጃ ህግ ለመቃወም አደባባይ የወጡ የአገሪቱ ዜጎች እንደተናገሩት፤ የውርጃ ህጉ አድሏዊ መሆኑን እና ሴቶች በራሳቸው አካል ላይ እራሳቸው መወሰን እንዳይችሉ የሚያግድ ነው።
ይሁን እንጂ በተቃራኒው በርካታ ቁጥር ያላቸው ደቡብ ኮሪያዊያን ክርስቲያኖች በአንጻሩ እንደተናገሩት፤ ፅንስ ማቋረጥ ወንጀልና ሀጢያት ነው። ስለዚህ ጽንስ ለማቋረጥ የሚከለክለው የአገሪቱ ህግ ሊቀየር አይገባም። ምክንያቱም ሴቶች ጽንስ ከማቋረጣቸው በፊት ውሳኔያቸውን በጥልቀት እንዲያጤኑ ያስገድዳቸዋል።
በተጨማሪ ራሳቸውን ላልተፈለገ እርግዝና እንዳይጋለጡ ጥንቃቄ እንዲያደርጉ ይረዳቸዋል ሲሉ ተደምጠዋል። ነገር ግን በአገሪቱ የውርጃ ህጉ ይነሳ የሚል ተቃውሞ እየበረታ በመምጣቱ የአገሪቱ ፍርድ ቤት የውርጃ ህግ እ.እ.አ በ2020 መጨረሻ ላይ መሻሻል እንዳለበት ትዛዝ አስተላልፏል።
ደቡብ ኮሪያ ፅንስ ማቋረጥን ከሚከለክሉ ጥቂት አገሮች መካከል አንዷ መሆኖ ይታወቃል።
አዲስ ዘመን ሚያዝያ 4/2011
በ ሶሎሞን በየነ