የሕይወት ፈተና በእጅጉ ከጎዳቸው ሴቶች መካከል አንዷ ነች፡፡ አንዱን ልሙላ ስትል ሌላው ይጎልባታል፡፡ ከዚህም አልፎ የማትወጣው ማቅ ውስጥ አስገብቷታል፡፡ ለዚህም የራሷን ዕድልና ባለቤቷን ተጠያቂ ታደርጋለች፡፡ ባለቤቷ ዋና ትኩረቱ መጠጥ ላይ ብቻ በመሆኑ እንኳን ልጆቹን ራሱንም መቆጣጠር አይችልም፡፡ ቀኑን በሸክም ሲለፋበት የዋለውን ገንዘብ ያለስስት ይጠጣበታል፡፡ ከዚያም ብሶ ቤቱ ለምን ጎደለ እያለ ዘወትር ጭቅጭቅ ይፈጥራል፡፡
ልጆቹ የአባታቸውን ባህሪ አይተው እንዳይጠሉት ብዙ ችግሮችን ተጋፍጣ ታሳልፋለች። የቤቱ አባ ወራ ባለቤቷ ሳይሆን እሷ በመሆኗ ለባለቤቷም ለልጆቿም የሚሆን ገንዘብ ፍለጋ ሌት ከቀን ትባዝናለች። የሁለት ልጆች እናት መሆን ከባድ እንደሆነ በነበረባት ጫና የተነሳ ያየችው ለምለም ትምህርታቸው እንዳይስተጓጎል ሥራ ሳትመርጥ ደፋ ቀና ትላለች። ልጆቼን ብላ ለኤች አይቪ ኤድስ ቫይረስ የተጋለጠችውም በዚህ አጋጣሚ ነበር።
ትናንትም ዛሬም እነርሱን ለማሳደግ አባትም እናትም ሆናለች፡፡ ዛሬ ባለቤቷ በሕይወት ባለመኖሩ የተነሳ ሙሉ አባወራነቱን ተረክባለች፤ እማወራውም እርሷ ነች። ስለዚህም ቤቱን ሙሉ ለማድረግ ማልዳ ወጥታ ምሽት ላይ ትመለሳለች። በአንድ ሥራ የቤቷን ቀዳዳ መድፈን ስለማትችልም የተለያዩ መኖርያ ቤቶች ውስጥ በተመላላሽ ሰራተኛነት ለመሥራት ትዋትታለች።
ከምትሰራባቸው ቤቶች መካከል አንዳንዶቹ ለፆታዊ ትንኮሳ ይጋብዟታል። በተለይ አንዱ ግለሰብ ውበቷ አማላይ በመሆኑ የእሱ እንድትሆን ይፈልጋልና እንደልቧ የሚያሰራትም አልነበረም። ግን እርሷ ቤተሰቤ የምትለው አላትና ሀሳቡን በየጊዜው ትቃወማዋለች። ጫናው ሥራዋን የማታ ማታ ለማቋረጥ እስክትወስን ድረስ ታግሏታል። ሆኖም የቀን ጎዶሎ ገጠማትና ሥራውን ማቋረጥ አቃታት፡፡ ባለቤቷ በድንገት መንገድ ላይ ሞቶ በመገኘቱ አስከሬኑ መጣለት። አሁን ቆራጥ ውሳኔ ካልወሰነች በስተቀር የፈለገቺውን ያህል መራመድ አትችልም፡፡ ስለዚህም ልታቆመው ያሰበችውን ሥራ ቀጠለች። የአሰሪዋንም ፍላጎት ፈጸመች፡፡ ውሳኔዋ ትክክል እንዳልነበረ የተረዳችው ግን ለኤች አይቪ ከተጋለጠችና ከረፈደ በኋላ ነበር።
ለምለም ለበሽታው ከተጋለጠች በኋላ የምታደርገው ጠፍቷት ብዙ ጊዜያትን አሳልፋለች። ሁኔታውን እንባ እየተናነቃት‹‹ባለቤቴ ከሞተ ከወራት በኋላ ወደ አሰርዬ ቤት ሄድሁ። በሀሳቡ እንደተስማማሁም ገለጽኩለት። ደስተኛ ሆኖም አብሬው እንድተኛ አደረገኝ። ግን አንድም ቀን ለቫይረሱ ተጋላጭ መሆኑን ገምቼ አላውቅም። ምክንያቱም ራሱን ይጠብቃል። ሽቅርቅር ነው፡፡ እናም መተኛቴ ምንም አልመሰለኝም ነበር። እንደውም ሌሎች ጋር መስራቴን አቁሜ እርሱ በሚሰጠኝ ብቻ ልጆቼን ማስተዳደር ጀመርኩ።
አንድ ቀን ግን ክፉኛ ታመምኩ። ለህክምናም ወደ ጤና ጣቢያ ሄድኩ። የሰማሁትን ግን ማመን ከበደኝ። ቫይረሱ በደምሽ አለ ተባልኩኝ። አምኜው ልብሱን የማጥብለት፣ ምግብ የማዘጋጅለትና የደስታ ምንጩ የሆንኩለት ሰው በሽተኛ አደረገኝ›› ስትል ሁኔታውን ታስረዳለች፡፡
በሽታው ጊዜ አይሰጥምና መድሃኒቱን መውሰድ እንዳለባት የወሰነችው ለምለም፤ ‹‹ልጆቼን ልምረጥ ህመሜን?›› ትላለች። ምክንያቱም ቫይረሱ በደሟ መኖሩን ለልጆቿ ብትነግራቸው ይጨነቁባታል፤ በዚያ ላይ መድሀኒቱ ያለምግብ መውሰድ አትችልምና እነርሱ ሳይበሉ ይህንን ለማድረግ ልቧ አይችልም። ስለዚህም ማንን መምረጥ እንዳለባት ግራ ገብቷት ዓመታትን አስቆጥራለች። ይህም ሆኖ መድሀኒቱን መውሰዷ ግን ብዙ ነገሯን ቀይሮላታል። ከበፊቱም በተሻለ ሁኔታ እንድትሰራ ጥንካሬን ሰጥቷታል።
አሁን ግን ከደረሰባት ችግር አንጻር እንደቀድሞው ወንደላጤ ቤት አትሰራም። ቤተሰብ ያላቸው ሰዎች ምርጫዎቿ ናቸው። ከዚያም ባሻገር ጠዋትና ማታ ላይ ሁለተኛው ሥራዋ አድርጋ ከደንብ አስከባሪዎች ጋር መሯሯጥ ቢኖረውም የመንገድ ላይ የልብስ ማዞር ሥራ ትሰራለች። በዓላት ባሉበት አካባቢዎች ላይ እየተዘዋወረችም ትሸጣለች። በዚያ ላይ ትልቁ ልጇ ተማሪ ቢሆንም በትርፍ ጊዜው ሊስትሮ እየሰራ ገንዘብ ይሰጣታል። በዚህም ቤቷ ሙሉ ባይሆንም ባላት ነገር ደስተኛ ነች።
ለምለም ቫይረሱ እንዳለባት ካወቀች በኋላ በብዙ መንገድ ህይወቷ ፈታኝ ሁኔታ ውስጥ ገብቷል። አንዱ በጤንነት ለማቆየትና ቫይረሱ በጤና ላይ ሊያስከትል የሚችለውን ጉዳት ለመቀነስ የተመጣጠነ ምግብ አስፈላጊ መሆኑ ነው። ለእርሷ ይህንን ማግኘቱ በፍጹም የማይታሰብ ነበር። ምክንያቱም ለእርሷ ቀርቶ ለልጆቿ የምታበላው አልነበራትም። እናም ለእኔ የሚለውን ትታ ለልጆቿ ትመግባለች። ይህ ደግሞ መድሀኒቱን በባዶ ሆዷ እየወሰደች እንድትቆይም አድርጓታል።
‹‹እኔ በሽታዬን ተቋቁሜ እነርሱን ላሳድግ›› በሚል መድሀኒቱን መውሰድ ብትጀምርም መድሀኒቱን ያለ ምግብ የምትወስድበት አጋጣሚ ብዙ ነበር፡፡ ምክንያቱም እናት መሆን ከባድ ነው። ታማሚ መሆንም ይብሳል። በእናትነት ወገን ሲታይ ከራስ በፊት ልጆች ይቀድማሉ። ከህመም አንጻር ምግብ ሳይበሉ መድሀኒት መዋጥም አይቻልም። እናም ልጆቼን ሳስቀድም ሕመሜን አልቻልኩትም ነበር። ለልጆቼ ወይስ ለራሴ የሚለው ግራ አጋብቶኝ ዓመታትን አሳልፌያለሁ። አሁን ይሄ ተለውጧል። ኑሮ ውድ ቢሆንምና የቤት ኪራይ ቢያጨናንቀንም ሁላችንም በልተን እናድራለን›› ትላለች።
‹‹ እስክሞት ድረስ ለልጆቼ ደስታ እሰራለሁ›› የምትለው ለምለም፤ በኤች አይቪ መያዝ ሰው እንደቀላል ማየት እንደሌለበት ትመክራለች። አሁን የተሻሉ ነገሮች ቢኖሩም የህይወት ፈተናው ግን አሁንም ከባድ መሆኑን ታስረዳለች፡፡ መገለልና መድሎ ማድረግ አሁንም አልቀረም፡፡ ከዚህ ቀደም የነበረው የግንዛቤ ማስጨበጥ ሥራ ጭምር የለም። እናም በሽታው ሕይወታችንን ሳያመሰቃቅለው እንንቃ መልዕክቷ ነው።
ባለፈው ዓመት የዓለም ኤች አይቪ ኤድስ ቀን በተከበረበት ወቅት የዓለም የጤና ድርጅት ባወጣው መረጃ እንዳመላከተውም፤ በኢትዮጵያ ውስጥም ፀረ ኤችአይቪ ህክምናው በመስፋፋቱ በተሐዋሲው የተያዙ ሰዎች ቁጥር ቢቀንስም በአሁኑ ሰዓት 622 ሺህ 326 ሰዎች ኤችአይ ቪ በደማቸው እንደሚገኝ መረጃዎች ያሳያሉ። ከእነዚህ ውስጥ 480ሺ827ቱ የፀረ-ኤችአይ ቪ መድሀኒት ይወስዳሉ። በዚህም የተጠቃሚው ሽፋን 77ነጥብ2 ከመቶ ደርሷል። ቀሪዎቹ ከቦታ ርቀት እስከ የአገልግሎት አቅርቦት ተደራሽነት ችግር ምክንያት የአገልግሎቱ ተጠቃሚ አልሆኑም። በመሆኑም ይህንን አስተሳሰብን በመቀየርና ተደራሽነትን በማስፋት ለውጥ ማምጣት ያስፈልጋል።
ጽጌረዳ ጫንያለው
አዲስ ዘመን ህዳር 22/2014