የምኞት ግሮሰሪ እንደተለመደው ዛሬም ፀሐይ ለመጥለቅ ስታዘቀዝቅ እርሷ በበኩሏ ደመቅመቅ ማለት ጀማምራለች።እየጨለመ ሲመጣ ቀያዮቹ መብራቶች መድመቅ ጀመሩ፤ የጠጪው ቁጥር ደግሞ እየተበራከተ ነው።ጫጫታው ደመቅ ብሏል፤ ግሮሰሪዋ በከፍተኛ ድምፅ ተጨናንቃለች።ተሰማ መንግስቴ፣ ዘውዴ መታፈሪያ እና ገብረየስ ገብረማሪያም የሚጠጡትን አዝዘው እየተዝናኑ፣ እየተሳሳቁ፣ ድምፃቸውን ከፍ አድርገው በሆነ ባልሆነው እየተከራከሩ ይጯጯኋሉ።
ዘውዴ፣ ‹‹ለወትሮ አገሬው ቸር ነበር።ቸርነቱ ከትውልድ ወደ ትውልድ ሳይሸጋገር በነበር ቀረ እንጂ።ትውልዱ ስስቱ ወደር አጣ።ለፍቶ ከማግኘት ይልቅ ሳይሰራ በአቋራጭ መበልፀግን እንደትክክለኛ መንገድ ወሰደው።ያልለፋበትን ተገቢ ያልሆነ ሃብትና ንብረት ማፍራት ጀግንነት ሆነ።በአደራ የተሰጠ ስልጣንን ለራስ ጥቅም ማዋል፣ አደራን አለመጠበቅ፣ እምነት ማጉደል፣ አለመታመን፣ በጉቦና በምልጃ፣ በአድልዎ ውሳኔን ወይም ፍትህን ማዛባት በአገር ውስጥ ይህ ሁሉ ነገር ተንሰራፍቶ ከማየት መሞት ይሻላል።›› አለ መረር ብሎ።
ተሰማ በበኩሉ፤ ‹‹ኢትዮጵያ ወንጀለኞችን አሳልፎ መስጠት የሚደነግግ የተባበሩት መንግስታት የፀረ ሙስና ኮንቬንሽንን በታህሳስ 2003 ዓ.ም ፈርማለች።ግን ለራስ ወይም ለቡድን ጥቅም ሲባል ስርዓቶችን፣ ህጎችን፣ ደንቦችንና አሰራሮችን የመጣስ ተግባር በአደባባይ ሲፈፀም ነበር።የፖለቲካ መሪዎች ስልጣንን መከታ በማድረግ የህዝብን ጥቅምና ፍላጎት ችላ በማለት የራስን እና የቡድንን ጥቅም ለማስጠበቅ ሲሉ፤ የመንግስት እና የሕዝብ ሃብትና ንብረት ላይ ስርቆት፣ ዝርፊያና ማጭበርበር ይፈጽማሉ።ህግና ስርዓትን በመጣስም በዝምድና እና በትውውቅ፣ በፖለቲካ ወገንተኝነት፣ በጎሰኝነት፣ በሃይማኖት ትስስር ተመርኩዞ አድልዎ መፈፀም ከተራው የተለያዩ ዕቃዎችን ያለቀረጥ እያስገቡ ነጋዴን ከማክሰር እና አንዱን ወገን ከመጥቀም ጀምሮ ለዘመናት የተሰራበት የባለስልጣናት መንገድን ማወቅ እውነት ነው በእርግጥም ያሳምማል።›› ብሎ መጠጡን ተጎነጨ።
ገብረየስ በበኩሉ፤ ‹‹ፍትህን ማጉደል፣ ስልጣንንና ሃላፊነትን አለአግባብ በመጠቀም ሕገወጥ ጥቅም ማግኘት ትልቅ ጥፋት ነው።መጥፊያው መልሚያው የሚመስለው ሰው ደግሞ ጥቂት አይደለም።አንዳንድ ጊዜ ሰዎች ችግር የሚያስከትልባቸው ነገር የሚጠቅማቸው ይመስላቸዋል።ብዙ ጓደኞቼ ሳይዘሩ ማጨድ፤ ሳይራመዱ መሔድ የሚጠቅም መስሏቸው መርፌ ውጠው ማረሻ ለመትፋት ተገድደዋል።ትንሽም ቢሆን እያወቁ ስህተት መፈፀማቸው ከፍተኛ መዘዝ አስከትሎባቸው እንደኔ በነፃነት መኖር አዳግቷቸዋል።›› አለ።
‹‹ሰው በሰው የተጠጋ ሰው ወጋ እንደሚባለው ነው።›› ብሎ ዘውዴ ከት ብሎ ሳቀ።‹‹አንድ ሰው ሌላውን ለማጥቃት የሚደፍረው ሰው ሲኖረው ነው።በሥራው በዕውቀቱ እና በብቃቱ ሳይሆን በሰው ስልጣን ያገኘ ሰው ሌላውን ሰው መዝኖ አቅሙ ከእርሱ በታች ወይም አጋር የሌለው መሆኑን አረጋገጦ ከመጉዳት ወደኋላ አይልም።አቅም ወይም አጋር የሌለው ሰው ለተንኮለኞች የተጋለጠ ነው።እኔ ሰው ስላልነበረኝ፣ ወገን ስላልነበረኝ ብዙ ግፍን ተቀብያለሁ።አንተ ቢያንስ ሙስና አልቀበልም ወይም በአቋራጭ ሃብት አላግበሰብስም ብለህ ስስትን በመጠየፍህ ሃብታም ባትሆንም ብዙ አልተጎዳህም።
ሙሰኞች ግን ‹መኖሪያዋን ትታ መዞሪያዋን› እንደሚባለው የበለጠ ጠቃሚ የሆነውን ጉዳይ በጥንቃቄ ይዘው በመጠቀም፤ አገርን ማሳደግ የህዝቡን ሕይወት መለወጥን ትተው የስግብግብነታቸው ብዛት ከአገር አልፎ ወደ ሌሎች አገራት እስከማሻገር የደረሰ ሙስና ውስጥ መግባታቸውን ሳስብ በእውነት ኢትዮጵያዊ በመሆኔ እሸማቀቃለሁ፤ አፍራለሁም።ይህ ሃቅ መካድ የለበትም።በኢትዮጵያዊነታችን ብዙ ሊያስኮሩን የሚችሉ ሃብቶችም ሆነ ታሪኮች ቢኖሩንም እንደዚህ የሚያሳፍር ዓይን ያወጣ እና የሚያሸማቅቅ ምድሪቱ እንዴት እንዲህ ዓይነት ሰው አበቀለች? ብሎ ለመጠየቅ የሚያስገድድ፤ ከዚህ ሕዝብ መፈጠርን የሚያስጠላ የሰዎችን ስህተት ሳይ እገረማለሁ።መገረም ብቻ አይደለም እበሳጫለሁ።
የኢትዮጵያ ህዝብ የባለስልጣን ጉዳይ ሁልጊዜም ጎረምሳ፣ ‹ለፍቅር ብቀርባት ለጠብ አረገዘች› እንደሚለው ለመልካም ነገር ቢሾምም ተንኮል አውጠንጥነው ለጥሩ ነገር ታስበው የነበሩ ባለስልጣናት ሊያግዝ የሚችልን ቅን አስተሳሰብ አጣምሞ በማሰብ፤ የህዝብን አደራ እና እምነት በማንኳሰስ የራሳቸውን ክብር በማግዘፍ ሰዎችን ያስነባሉ፤ ግፍ ይሰራሉ፤ አልፈው ተርፈው ተጨባጭነት የሌለው ነገር በማውራት እነርሱ መታሰር እያለባቸው ሃቀኞችን አስረው ያሳስራሉ።በመጨረሻም ‹ለእግሩ የተጠየፈ ለራሱ አተረፈ› እንደሚባለው ቀላሉን በመካከለኛ ደረጃ የመኖር ዕድልን ዘግተው፤ ህዝብን እና አገርን የመጥቀም በርን ከርችመው በስስታቸው፤ በሌብነታቸው ለእስር ወይም ለስደት በመዳረግ ቤተሰባቸውን እና ራሳቸውን ለባሰ አደጋ ያጋልጣሉ።› በማለት ዘውዴም በበኩሉ የሚጠጣውን ብድግ አድርጎ ጨለጠ።
ተሰማም፣ ‹‹ በስልጣን መባለግም ሆነ ስልጣንን ተገን አድርጎ መዝረፍ፣ ጉቦ መቀበል እና ሙስና መፈፀም በየትኛውም አገር እና በየትኛውም ጊዜ ያለ ነው።ዋናው ጉዳይ ችግሩን በምን መንገድ እንከላከለው ወይም እንቀንሰው የሚለው ነው፤ ራሺያዎች ‹የሁሉም የሆነ የማንም አይሆንም።› እንደሚሉት ወንጀሉ ሲፈፀም ቀጥታ ተጠቂ ስለማይኖር የኔ ጉዳይ ነው ብሎ አስፈላጊውን መረጃ አሟልቶ በማቅረብ የሙስና ድርጊቱ እንዲመረመርና አጥፊዎች እንዲቀጡ የሚያደርግ ሰው ላይገኝ ይችላል።ምክንያቱም እንደሌሎቹ ወንጀሎች ቀጥተኛ ተጠቂ የለም።በሌላ በኩል እንደነውር የማይቆጠርበት ሁኔታ መኖሩ በራሱ ችግር ነው።ለማጋለጥ የሚሞክር እንደምቀኛ መታየቱ እና ንፁሃንን መኮነን እየበረታ መሄዱ ሙስናን እንደሚያስፋፋው አያጠያይቅም።
ሙስና ከስርቆት፣ ከድብደባም ሆነ ከአስገድዶ መድፈር በተለየ መልኩ በድብቅ የሚፈፀም ወንጀል ነው።በምስጢርና በጥንቃቄ የሚፈፀም ከመሆኑም ባሻገር አጥፊው ለምርመራ መነሻ የሚሆን አሻራን የማጥፋት አቅም አለው።በሁለት ሰው እና ከዛ በላይ በሆኑ ሰዎች ትስስር በውሳኔ ሰጪና ውሳኔ ተቀባይ የሚፈፀም ነው።ምስጢሩን የሚያውቁ ብቸኛዎቹ ሰዎች እነርሱ ናቸው።እነርሱ ደግሞ ለጥቅማቸው ሲሉ ማስረጃ ሊሰጡ አይችሉም።ሁለቱም በህግ አይን ወንጀለኞች በመሆናቸው ምስጢሩን ይገፉበታል።እነዚህ ሁሉ ጉዳዮች ሲታዩ መመርመር፣ ማጋለጥ፣ መክሰስና አጥፊን መቅጣት ቢገባም እንደሚታሰበው ቀላል አይደለም።›› አለ።
ገብረየስ በበኩሉ፤ ‹‹የኢትዮጵያ ነገር ሁልጊዜም ያስገርመኛል።ህዝቡ በራሱ ጥቅም ላይ መለገም ያለበት አይመስለኝም።የፀረ ሙስና ኮሚሽንም ሆነ የፍትህ አካላት ሙሰኞችን ለመቅጣት ፍቃደኛ ከሆኑ የሚያግዝ እና የሚረዳ ሲገኝ ተረጂው አደናቃፊ መሆን ‹መነኩሴ ቤቷ ሲሰራ ሐረግ ትሸሸጋለች› እንደሚባለው ነው።እርግጥ ነው፤ ህዝቡ ለማይጠቅም ነገር ጊዜን፣ ጉልበትንና ገንዘብን ማጥፋት የለበትም።ነገር ግን ደግሞ ሙሰኛ እና አድልዎ ፈፃሚን ዝም ብሎ በማለፍ የገዛ አገርን መጉዳት መቆም አለበት ብሎ አምኖ ሌባ እና ሙሰኛ ምንጊዜም ሌባ ነው።ሰርቶ አገር እና ህዝብን ለማይጠቅም መናኛ ባለስልጣን ማዘን አያስፈልግም ብሎ ደፍሮ ለሚመለከተው አካል ያቀረበ ሲኖር ማበረታታት እና ከጎኑ መሆን ያስፈልጋል።
‹ሲያይ የሞተን ሲሰማ ቅበረው› እንደሚባለው እያወቀ ችግር ውስጥ የሚወድቅ ሙሰኛ ለማዳን መቸገር አያስፈልግም።እያወቀም ቢሆን መቅጣት የግድ ነው።የስነምግባርና የፀረሙስና ኮሚሽንም ሆነ ጠቅላይ አቃቤ ህግ ብቻ በየደረጃው ያለ የሙስና ወንጀልን ለመከላከል ሃላፊነት የተሰጠው አካልም ሌባ ተይዞ ዱላ እንደማይጠየቀው ሁሉ አጥፊ ሲገኝ ተይዞ ቅጣት እንዳይቀር መስራት አለባቸው።ህዝብም ሃላፊነቱን መወጣት እና መጠቆም አለበት።›› አለ።
ተሰማ በበኩሉ፤ ‹‹እርግጥ ባለስልጣናትም አንዳንድ ጊዜ ‹ለድካም የጣፈው ቢነግድ አይተርፈው› እንደሚባለው አንዳንድ ሰው ባለስልጣን ሆኖ ሃቅ ላይ ተመስርቶ ምንም ጥረት ቢያደርግ ያሰበውን ያህል አይሳካለት ይሆናል።ነገር ግን ይህ የደከሙትን ያህል አለማግኘት፤ ወይም ስኬታማ አለመሆን ተስፋ ሊያስቆርጠው አይገባም።ለውሻ ሞት ፊት አይነጩለትም፤ ገና ለገና እንደሆነ ባለስልጣን ትልቅ ህንፃ ወይም ቤት መገንባት ስላልቻሉ ማዘን አይገባም። ቀላል ለሆነ ነገር ብዙ ማዘን ተገቢ አይደለም።በማዘን ወደ ዝርፊያ መግባት አያስፈልግም።
ከመዝረፍ እና ሙስና ውስጥ ከመዘፈቅ ይልቅ ተግባርን በትጋት ማከናወን ወሳኝ መሆኑን በትክክል መገንዘብ ተገቢ ነው።ያለበለዚያ ሰው ዘረፈ ብሎ መዝረፍ ‹መውጫህን ሳታይ አትግባ› እንደሚባለው መውጫ ማሳጣቱ እና ግራ ማጋባቱ አይቀርም።ምን ጊዜም ቢሆን በተለይ በውሳኔ ሰጪነት መደብ ላይ ያሉ ግለሰቦች ጥንቃቄ ማድረጋቸው አስፈላጊ ነው።ለሚፈፅሟቸው ድርጊቶች ሁሉ ስህተት እንዳይፈፀም በቅድሚያ ሁኔታዎችን ማገናዘብና ማየት አለባቸው።በተለይ በገንዘብ ወይም በሌላ ትስስር ተታልሎ ሚዛን መሳት ከመጣ ከባድ ነው።
ያለበለዚያ ‹መርፌ ሰርቆ ማረሻ ቢተኩ ልብ አይሆን፤› እንደሚባለው ይሆናል።ስም እምነት በማጉደል አንድ ጊዜ ከተሰበረ በኋላ ለማደስ ያስቸግራልና ቀድሞ ማሰብ ያስፈልጋል።ሰው የፈለገውን ያህል ቢዘርፍ የፈለገውን ያህል ቢንገበገብ በዕለት ከአንድ እንጀራ የተረፈ ምግብ እንደማይበላ እሙን ነው።ሰው የፈለገውን ያህል ቢዘርፍ አብሮት የሚቀበር እና እስከወዲያኛው ዓለም አብሮት የሚኖር ነገር የለም።ስምን ሰብሮ ከመሞት ስምን በመልካም ተክሎ ማለፍ ይሻላል።›› ሲል ሁሉም መስማማታቸውን ገልጸው መሰላቸታቸውን በመጠቆም ወሬውን ወደ ሰሞንኛው የዓለም የእግር ኳስ ዋንጫ ቀየሩ።
ምሕረት ሞገስ
አዲስ ዘመን ህዳር 22/2014