ከዳር ሆኖ ከአንደኛው ጥግ ሌላኛው ጥግ ማየት አይቻልም፡፡ ከዳር ሆኖ ለሚመለከት ሰው፣ መሬት ከሰማይ የተጋጠመ ይመስላል፡፡ ከአንዱ ጫፍ ሌላኛው ጫፍ ለመድረስ ቢያንስ በተሽከርካሪ የአራት ሰዓት ጉዞ ማድረግ ግድ ይላል፡፡
ከደቡባዊ የባሌ ሮቤ ከተማ መውጫ ጀምሮ ሲናና እና አጎራባች ወረዳዎችን ጨምሮ በስንዴ አዝመራ ተሸፍኗል፡፡ ከህዳር 22 እስከ 23 ቀን 2011 ዓ.ም በኦሮሚያ ክልል የሚከበረውን የአርሶ አደሮች የመስክ ቀን አስመልክቶ ይህን አካባቢ ለማየት ከፌዴራልና ከኦሮሚያ ክልል በተለያዩ የሥራ ኃላፊነት ላይ ያሉ አመራሮች፣ ባለሙያዎች፣ ተመራማሪዎች፣ አርሶ አደሮችና መገናኛ ብዙሃን ተገኝተዋል፡፡
በመስክ ምልከታው ላይ ከነበሩት አርሶ አደር ብርሃኑ ጣሶ እንደሚሉት፤ ምርታማነት እንዲጨምር መንግሥት ለዓመታት ከፍተኛ ጥረት ሲያደርግ ቆይቷል፡፡ አዳዲስ ቴክኖሎጂዎችን፣ አሰራሮችንና ስልቶችን በማምጣትም በትንሽ መሬት ላይ ጥራት ያለው ምርት ማምረት እየተቻለ ነው፡፡ የመንግሥትም ልፋት ፍሬ አፍርቷል፤ እነርሱም ቢሆኑ የምርታማነት ስኬትን ተጎናፅፈዋል፡፡ በዚህም ቀደም ሲል በሄክታር 35 ኩንታል ምርት የሚያገኙ ቢሆንም፤ በዘመናዊ አሠራርና ግብዓት በመታገዝ በሄክታር እስከ 45 ኩንታል ስንዴ እያመረቱ ነው፡፡ ይህ ጥረትና ውጤት እንደተጠበቀ ሆኖ አርሶ አደሩ አሁንም የተለያዩ ችግሮች አሉበት፡፡
አርሶ አደሩ እንደሚሉት፤ ጥራት ያለው ትርፍ ምርት ቢመረትም በአግባቡ የሚረከቡ ማህበራት ወይንም ዩኒየኖች ባለመጠናከራቸው አርሶ አደሮች ከማምረት ባለፈ በልፋታቸው ልክ በጥሩ ዋጋ አይሸጡም፡፡ በምርት ወቅት አንድ ኩንታል ስንዴ እስከ 900 ብር ሲሆን፤ በወራት ልዩነት ደግሞ እስከ 1ሺ400 ብር መድረሱ ከፍተኛ የዋጋ መዋዠቅ አለ፡፡ ይህ ደግሞ አርሶ አደሩ ምርቱን ሲቸግረው ከመሸጥ ውጭ ሁሉንም ተጠቃሚ የሚያደርግ የገበያ ሥርዓት ያለመዘርጋቱ ውጤት ሲሆን፤ ከሚመለከታቸው አካላት ጋርም በአግባቡ አልተሰናሰለም፡፡ ከዚህ ባለፈም ምርታቸውን ወደ ገበያ በወቅቱ ለመውሰድ የመንገድና ትራንስፖርት ችግር አለ፡፡
በተመሳሳይ፣ በአካባቢው ፀረ አረም መድሃኒትን በአውሮፕላን መረጨት ቢጀመርም፤ ሰብልን በስፋት የሚያጠቃ በሽታ ሲከሰትም መድሃኒት ርጭቱ በሰው ጉልበት በመሆኑ በሽታውን ቶሎ መግታት ስለማይቻል፤ በሌላው ዓለም ለዚሁ ሥራ የሚውል መድኃኒት የሚረጭ አውሮፕላን በሰፊው ሥራ ላይ እንዲውል ፍላጎት አላቸው፡፡
‹‹ሲናና ወረዳ ጠንካራ አርሶአደሮች ያሉበት፣ በስንዴ ምርቱም ከፍተኛ የሆነ ነው፡፡ አለፍ ሲል ደግሞ በባሌ ሮቤ አካባቢ ያለን አርሶ አደሮች ራሳችንን መመገብ ብቻ ሳይሆን ለኢትዮጵያም የሚተርፍ ምርት የማምረት ውጥን አለን›› የሚሉት ደግሞ አርሶ አደር ጋሻው ሸረፋ ናቸው፡፡ አቶ ጋሻው እንደሚሉት፤ በአካባቢው ተፎካካሪ የሆኑ አርሶ አደሮች ተፈጥረው በየዓመቱ ምርታማነት ላይ ጭማሪ እያሳየ ቢሆንም፤ ተፎካካሪ ነጋዴዎች ባለመበራከታቸው የገበያው ዋጋ በገዥና ሻጭ ፍላጎት የተመሰረተ ሳይሆን በደላላ የሚተመን ነው፡፡ ገበያውም በአርሶ አደሮች መካከል የተፈጠረውን ፉክክር በሚያስተናግድ መልኩ እንዳልተቀረፀ ያስገነዝባሉ፡፡
በተለይ ደግሞ ረብጣ ውጭ ምንዛሪ ወጥቶበት ከውጭ የሚገባውና በጥራት ከፍተኛ ደረጃ ያለው የማካሮኒ እና ፓስታ ስንዴ የሚያመርቱ አርሶ አደሮች ቢበራከቱም፤ ለመደበኛ ጥቅም ከሚውለው ስንዴ የተለየ ዋጋ ባለመኖሩ የአርሶ አደሩን የተፎካካሪነት መንፈስ እየጎዳው ነው፡፡
አቶ አማረ ቢፍቱ፣ በሲናና ግብርና ምርምር ማዕከል የምርምር ስርፀት የሥራ ሂደት ሲሆኑ፤ የአርሶ አደሮቹ ችግር ከነባራዊ ሁኔታ ጋር የተጣጣመና እውነት እንደሆነ ይመሰክራሉ፡፡ አርሶ አደሩ በቴክኖሎጂ በመታገዝ፣ ምርጥ ዘር በመጠቀምና በወቅቱ የአረምና ዋግ መድኃኒት በሰብሎች ላይ እንዲረጭ ለዓመታት ግፊት ሲደረግ መቆየቱን ያስታውሳሉ፡፡ ቀድሞ በግፊት እንዲሠራ ይደረግ የነበረው አሁን አርሶ አደር ጠያቂ ሆኗል፡፡ ይሁንና አርሶ አደሩ አሁን ከደረሰበት ንቃተ ህሊና እና ቴክኖሎጂን የመጠቀም ፍላጎት ጋር የሚጣጣም አሠራር አልተዘረጋም፡፡
በተለይ የማዳበሪያ አቅርቦት መዘግየት፣ የምርጥ ዘር፣ የአረም እና ዋግ መድኃኒቶች ከፍተኛ እጥረት መከሰት የቀድሞውን ልፋት መና እያስቀረው ነው፡፡
አርሶ አደሮች ጤናማ የገበያ ሥርዓት ባለመዘርጋቱ ተጎድተናል የሚለው እውነት እንደሆነ አቶ አማረ ያብራራሉ፡፡ እርሳቸው እንደሚሉት፤ ሳይንስ እንደሚመክረው ለፓስታና ማካሮኒ የሚሆን ስንዴ ፕሮቲን ይዘቱ ከ10 እስከ 12 በመቶ ነው፡፡
በባሌ ሮቤ ዙሪያ ያሉ በርካታ ወረዳዎች ግን 15 ከመቶ የፕሮቲን ይዘት ያለው ስንዴ እያመረቱ ቢሆንም፤ በዋጋ ደረጃ ግን አንዳች ተጠቃሚ አልሆኑም፡፡ ይልቁንም ተጠቃሚ የሆኑት ዝቅተኛ የፕሮቲን ይዘት ያለው ስንዴን 15 ከመቶ ፕሮቲን ካለው ጋር በመቀላቀል የሚያስፈጩ ነጋዴዎች ናቸው፡፡
በተመሳሳይ ምርት በሚሰበሰብበት ወቅትም ከፍተኛ ቁጥር ያለው ደላላ በእርሻው ቦታ የሚርመሰመስ ሲሆን፤ ገበያው የሚወሰነው በአርሶ አደሩ እና ነጋዴው ባለመሆኑ መንግሥት ሊያስብበት ይገባል፡፡ በመድኃኒት ረገድም ከፍተኛ እጥረት በመኖሩ፣ የአርሶ አደሩ ቡቃያ በዋግ በሽታ እየተጠቃ ነው፡፡ በተለይ ደግሞ አንዳንድ ነጋዴዎች ከፍተኛ መጠን ያለው መድኃኒት በማከማቸት በሽታው ሲከሰት ከመደበኛ ዋጋው በብዙ እጥፍ በመሸጥ አርሶ አደሩ እየመዘበሩት ነው፡፡ ይህን ችግር ያቃልላሉ ተብለው የተቋቋሙ ዩኒየኖችና ፌዴሬሽኖችም ኃላፊነታቸውን በአግባቡ አልተወጡም የሚል እምነት አላቸው፡፡
በኦሮሚያ ክልል እርሻና ተፈጥሮ ሃብት ቢሮ ኃላፊ አቶ ዳባ ደበሌ በበኩላቸው፤ አርሶ አደሮች የሚያነሷቸውን ችግሮች አግባብነት እንዳላቸው ተገንዝበናል ይላሉ፡፡ እርሳቸው እንደሚሉት፤ በማዳበሪያ አቅርቦት ረገድ እንደ አገር ችግር የለም፤ በ2010 በጀት ዓመትም ክልሉ በጠየቀው መሠረት መቶ በመቶ ተገዝቷል፡፡
ይሁንና በወቅቱ ለአርሶ አደሩ በማድረስና ፍላጎቱን በመመለስ ረገድ ክፍተት ሊኖር ይችላል፡፡ በመንገድ በኩልም ከፌዴራል መንግሥት ጀምሮ በቅንጅት የሚሠራ ነው፡፡ የመድኃኒት እጥረቱ ግን እንደ አገር ካጋጠመው የውጭ ምንዛሪ እጥረት ጋር በተያያዘ የተከሰተ ሲሆን፤ መድኃኒቱን በተቻለ መጠን በአውሮፕላን ለማስገባት ጥረት ተደርጓል፡፡ ይሁንና በአርሶ አደሩ መካከል ጤናማ ፉክክር እንዲኖር የገበያ ሥርዓቱን ማዘመን ይገባል፡፡
አዲስ ዘመን ህዳር 24/2011
በክፍለዮሐንስ አንበርብር