‹‹ወረዳ 14 ቦታው ባዶ ቦታ እንጂ ግሪን ኤሪያ አለመሆኑን ገልጾልኛል ››የቦሌ ክፍለ ከተማ የመሬት ዝግጅት እና ማስተላለፍ ዘርፍ ኃላፊ
ከ15 ቀናት በፊት በቦሌ ክፍለ ከተማ ወረዳ 14 የተፈጠረን ውዝግብ መሰረት በማድረግ በኢትዮጵያ ፕሬስ ድርጅት የአዲስ ዘመን ጋዜጣ ዝግጅት ክፍል አንድ የምርመራ ዘገባ መስራታችን ይታወሳል ።
የዚህ የምርመራ ዘገባ መነሻም «የቦሌ ክፍለ ከተማ እና የወረዳ 14 የመሬት ልማትና አስተዳደር ጽህፈት ቤት ከህገወጦች ጋር በመተባበር ከ30 ዓመታት በላይ ያለማነውና ስንጠቀምበት የኖርነውን የአረንጓዴ ስፍራ ወይም ግሪን ኤሪያ ሊነጥቁን » ሲሉ የቦሌ ክፍለ ከተማ ወረዳ 14 ማዕድን እና ኢነርጂ ቁጥር አራት ነዋሪዎች ለዝግጅት ክፍላችን አቤት ማለታቸው ነበር ።
በመጀመሪያው የምርመራ ዘገባ እንደተገለጸው ውዝግብ ከተፈጠረበት ጉዳይ ጋር ተያይዞ ቀጣይ ክፍል የምርመራ ዘገባ እንደሚኖር እና በክፍል ሁለትም ጉዳዩ የሚመለከታቸውን አካላትን ምን አሉ የሚለውን ይዘን እንደምንመጣ ቃል ገብተን ነበር። በገባነው ቃል መሰረትም ጉዳዩ ይመለከታቸዋል ያልናቸውን አካላት አነጋግረን ቀጣዩን ክፍል ዘገባ ይዘንላችሁ ቀርበናል ።
ለመነሻ ከባለፈው ዝግጅት
የክፍል አንድን የምርመራ ዘገባ ያነበቡ እና የዛሬውን የምርመራ ዘገባ ለማንበብ ለሚጠባበቁ እንዲሁም የዛሬውን የምርመራ ዘገባ እንደ አዲስ ለሚያነቡ አንባቢያን ደግሞ እንደመነሻ እንዲጠቀሙት ለማድረግ በክፍል ሁለት ወደተዘጋጀው የምርመራ ዘገባ በቀጥታ ከመግባታችን በፊት ከአስራምስት ቀናት በፊት የሰራነው የምርመራ ዘገባ ምን ይመስል እንደነበር በወፍ በረር ልናስቃኛችሁ ወደድን።
በቦሌ ክፍለ ከተማ ወረዳ 14 ልዩ ስሙ ገርጂ እየተባለ በሚጠራው አካባቢ በማህበር ለተደራጁ የከተማዋ ነዋሪዎች ቤት ሰርተው እንዲኖሩ ለማድረግ መንግስት በ1983 ዓ.ም በርካታ ባዶ ቦታዎችን ለነዋሪዎች አስተላለፈ።
ተደራጅተው የመኖሪያ ቤት መስሪያ ቦታ ከመንግስት ከተሰጣቸው ማህበራት መከካልም ዛሬ ላይ ውዝግብ በተነሳበት ቦታ የሚገኙት የማዕድን እና ኢነርጂ ቁጥር አራት ማህበር አንዱ ነበር ። ቦታው እስካሁንም ድረስ የማዕድን እና ኢነርጂ ቁጥር አራት ማህበር እየተባለ ይጠራል።
የማዕድን እና ኢነርጂ ቁጥር አራት ማህበር ነዋሪዎች ቦታውን ሲረከቡት እንደዛሬው የለማ እና የሁሉንም አይን የሚስብ ሳይሆን በቅጡ እንኳን መውጫ መግቢያ የሌለው እና ያለማ ነበር ። ቦታው ያለማ ስለነበር የአካባቢው ነዋሪዎች ለበርካታ ጊዜያት በተደጋጋሚ በሌቦች ከፍተኛ ዝርፊያ ሲፈጸምባቸው ነበር። የአካል ጉዳት የደረሰባቸውም ቁጥራቸው ቀላል እንዳልነበር የማህበሩ ነዋሪዎች በክፍል አንድ ገልጸውልናል።
በ1983 ዓ.ም መንግስት ለማዕድን እና ኢነርጂ ቁጥር አራት ማህበር የመኖሪያ ቤት ሲሰጥ ከመኖሪያ ቤቱ በተጨማሪ የአካባቢው ማህበረሰብ የሚገለገልበት የአረንጓዴ ስፍራን (ግሪን ኤርያ) ጨምሮ ነበር። ይህንን የአረንጓዴ ስፍራ የማህበሩ አባላት እስከዛሬ ድረስ እያለሙ እየተጠቀሙበት ይገኛል ።
ይሁን እንጂ ምክንያቱ በውል በማይታወቅ አግባብ በመስከረም ወር 2015 ዓ.ም ማንነታቸውን የማያውቋቸው የተለያዩ ሰዎች ወደ አረንጓዴ ስፍራው (ግሪን ኤርያው) አብዝተው ይመላለሳሉ። በዚህም ግራ የተጋቡት ማዕድን እና ኢነርጂ ቁጥር አራት ነዋሪዎች ለቦታው ፀጉረ ልውጥ የሆኑትን ሰዎች ለምን ወደ ቦታው እንደሚመላለሱ ይጠይቋቸዋል። ሰዎችም ቦታውን ሊገዙ መምጣታቸውን ይነግሯቸዋል።
ይህን ተከትሎ የማዕድን እና ኢነርጂ ቁጥር አራት ማህበር ነዋሪዎች «ሻጩ ማን ይባላል ? »በማለት ቦታውን ለመግዛት የመጡ ሰዎችን ይጠይቃሉ። ገዥዎችም‹‹ አቶ ብርሃኑ መኮነን ደገፋ›› የሚባሉ ሰው መሆናቸውን ተናግረው በቦታው ላይ የተሰራውን ካርታ ያሳያሉ።
ያልጠበቁት ነገር የገጠማቸው የማዕድን እና ኢነርጂ ቁጥር አራት ማህበር ነዋሪዎች ጉዳዩን ለማሳወቅ ወረዳ 14 ይሄዳሉ። ነገር ግን ስለጉዳዩ የሚያውቅ የወረዳ አመራር ሳያገኙ ይቀራሉ። ይህ በእንዲህ እንዳለ አረንጓዴ ስፋራው ላይ ስለተፈጠረው ችግር ለማስረዳት ወደ ክፍለ ከተማ መሬት ልማት እና አስተዳደር ጽህፈት ቤት ያመራሉ። የክፍለ ከተማው መሬት ልማት እና አስተዳደር ጽህፈት ቤትም ጉዳዩ ይመለከተዋል ስላለው የመሬት ማስተላለፍ ዘርፍ ለተባለው ክፍል ይመራቸዋል። ጉዳዩ የተመራለት የመሬት ማስተላለፍ ዘርፍ የተባለው ክፍልም ግሪን ኤርያው የእናንተ ስለመሆኑ ያላችሁን ማስረጃ ሁሉ ይዛችሁ ኑ ብሎ ያዝዟቸዋል።
የማዕድን እና ኢነርጂ ቁጥር አራት ማህበር ነዋሪዎችም በታዘዙት መሰረት ግሪን ኤርያው የእነሱ ስለመሆኑ ያስረዳልናል ያሉትን ሰነድ ሁሉ በመያዝ ወደ የመሬት ማስተላለፍ ዘርፍ ክፍል ቀረቡ ።
ሰነዱን ይዘው በመቅረብ ጉዳዩን ለመሬት ማስተላለፍ ዘርፍ ለተባለው ክፍል እያሳዩ ባለበት ወቅት ስለጉዳዩ ምን አይነት እውቅና እንዳልነበረው ሲነግራቸው የነበረው በቦሌ ክፍለ ከተማ የወረዳ 14 የመሬት ልማትና አስተዳደር ጽህፈት ቤት መሬቱን አቶ ብርሃኑ መኮነን ደገፉ ለተባሉ ሰው ወኪል ሊያስተላልፍ ሲሞክር ተገኘ። በዚህም የአካባቢው ነዋሪዎች እና በቦሌ ክፍለ ከተማ የወረዳ 14 የመሬት ልማትና አስተዳደር ጽህፈት ቤት መካከል አለመግባባት ተፈጠረ።
ይህን ተከትሎ ነዋሪዎቹ ጉዳዩን ለአዲስ ዘመን ጋዜጣ ዝግጅት ክፍል በመያዝ «የቦሌ ክፍለ ከተማ እና የወረዳ 14 መሬት ልማትና አስተዳደር ጽህፈት ቤት የተሰራብንን በደል የኢትዮጵያ ህዝብና መንግስት ተመልክቶ ፍርድ ይስጠን » ሲሉ ጥቆማ አደረሱን። ዝግጅት ክፍሉም ከጉዳዩ ጋር ተያይዞ በርካታ ምርመራዎችን አደረገ።
የቀድሞው በቦሌ ክፍለ ከተማ የወረዳ 14 የከተማ ውበት እና አረንጓዴ ልማት ጽህፈት ቤት ምላሽ
የቀድሞው የቦሌ ክፍለ ከተማ ወረዳ 14 የከተማ ውበት እና አረንጓዴ ልማት ጽህፈት ቤት ኃላፊ የነበሩት አቶ አለማየሁ ፋፉ ይባላሉ። አቶ አለማየሁ ፋፉን ያነጋገርንበት ዋና አላማ ውዝግብ የተነሳበትን ቦታ በአረንጓዴ ስፍራነት ለማልማት በነበረው እንቅስቃሴ ከማዕድን እና ኢነርጂ ቁጥር አራት ማህበር ነዋሪዎች ጋር አካባቢውን ለማልማት በርካታ ደብዳቤዎችን ይጻጻፉ ስለነበር ነው ። አቶ አለማየሁ ስለጉዳዩ የሚከተለውን ብለውናል ።
አቶ አለማየሁ እንዳሉት፤ የከተማ ውበትና አረንጓዴ ልማት ጽህፈት ቤት በማዕድን እና ኢነርጂ ቁጥር አራት በአረንጓዴ ስፍራነት ይለማ የነበረው ቦታ በአረንጓዴ ስፍራነት የተከለለ አልነበረም። ክፍት ቦታ ስለነበር ለከተማ ውበት እና ጽዳት ሲባል የቦሌ ክፍለ ከተማ ወረዳ 14 የከተማ ውበት እና አረንጓዴ ልማት ጽህፈት ቤት በጊዜአዊነት እንዲለማ የተደረገ ነው ።
ውበት እና ጽዳት ክፍት ቦታዎችን እንዲያለማ ኃላፊነት ለከተማ ውብትና አረንጓዴ ልማት ጽህፈት ቤት በመመሪያ የተደገፈ መብት ተሰጥቶታል የሚሉት አቶ አለማየሁ ፤ በዚህም ባዶ ቦታዎችን በማህበርም ሆነ ለባለሃብት በመስጠት በግዜአዊነት ማልማት እና ማስለማት እንደሚቻል ያስረዳሉ።
ይህን ተከትሎ የአዲስ ዘመን ጋዜጣ ዝግጅት ክፍል በከተማ ውስጥ በየትኛውም አካባቢ የሚገኝን ክፍት ቦታ የከተማ ውብትና አረንጓዴ ልማት ጽህፈት ቤት እንዲለማ ማድረግ ይችላል ? መመሪያስ አለ ? ስንል ጠየቅናቸው። አቶ አለማየሁም ‹‹አዎ !› የሚል ምላሽ ከሰጡ በኋላ ስለመመሪያው እንዲህ ሲሉ አብራሩ፤ ‹‹ በከተማችን ውስጥ ባዶ ቦታዎች ሲኖሩ የከተማ ውብትና አረንጓዴ ልማት ጽህፈት ቤት እንዲያለማቸው የሚፈቅድ አዋጅ አለ። ማንኛውም ክፍት ቦታ የከተማን ውበት ለማስጠበቅ ሲባል በጊዜአዊነት እንዲለማ ይደረጋል። ይሄን አሰራር የሚፈቅደው አዋጅም አዋጅ 365/2011 እንደሚባል እና በዚህ አዋጅ ስር አንቀጽ 14 ላይም ስለባዶ ቦታዎች እጣ ፋንታ በግልጽ መቀመጡን ይናገራሉ።
በማዕድን እና ኢነርጅ ቁጥር አራት ስር የሚገኘውን የግሪን ኤርያ አይነት መሬት ላይ ካለው ነባራዊ ሁኔታ አንጻር ለልማት ተነሺዎች መስጠት ይቻላል ? ተብለው የተጠየቁት አቶ አለማየሁ ‹‹አዎ›› የሚል ምላሽ ሰጥተዋል። አቶ አለማየሁ አክለውም አይደለም የግሪን ኤርያን ይቅርና ነዋሪዎችም ተነስተው ቦታው ለልማት ሊውል እንደሚችል ነው የገለጹልን ።
ቅሬታ የተነሳበት ቦታ እርስዎ የወረዳ 14 ከተማ ውብትና አረንጓዴ ልማት ጽህፈት ቤት ኃላፊ በነበሩበት ወቅት ከእርስዎ መስሪያ ቤት ጋር በመተባበር በአረንጓዴ ቦታነት እየለማ ነበር ። ስለዚህ ምን ይላሉ ተብለው የተጠየቁት አቶ አለማየሁ ‹‹ቦታው አረንጓዴ ስፍራ አልነበረም›› ሲሉ መልሰዋል። የአዲስ ዘመን ጋዜጣ ዝግጅት ክፍልም የእናንተ መስሪያ ቤትም ከአረንጓዴ ስፍራው ጋር ተያይዞ ቅሬታ ካነሱት የአካበቢው ነዋሪዎች ጋር የተላላካችኋቸው ደብዳቤዎች የሚያሳዩት ግን ቦታ በአረንጓዴ ቦታነት ሲለማ መቆየቱን ነው ። ስለዚህ ምን ይላሉ? ተብለው ለቀረበላቸው ጥያቄ። አቶ አለማየሁ ሲመልሱ ፤ የእነሱ መስሪቤት የጻፍነው ደብዳቤ ክፍት አረንጓዴ ቦታ የሚል እንጅ አረንጓዴ ቦታ የሚል አለመሆኑን ገልጸው፤ ይህ ቦታ በጊዜአዊነት እንዲለማ እንጂ ካርታ ስላልነበረው በጊዜአዊነት ሲለማ መቆየቱን ገልጸዋል።
የእናንተ መስሪያቤት ቦታውን ባዶውን እንዳገኘው ነው እየነገሩኝ ያለው። ቦታውን ባዶውን ነው ያገኛችሁት? ተብለው የተጠየቁት አቶ አለማየሁ ‹‹አዎ ! ቦታውን ባዶውን ነው ያገኘነው›› የሚል ምላሽ ሰጥተዋል። ይህን ተከትሎ የአዲስ ዘመን ጋዜጣ ዝግጅት ክፍልም ነዋሪዎቹ ግን ከ1983 ዓ.ም ጀምሮ እንደአለሙት ይናገራሉ። ስለዚህ ምን ይላሉ? ሲል ጠየቀ ። አቶ አለማየሁም ‹‹ስለዚህ ጉዳይ የማውቀው ነገር የለም በማለት ምላሽ ሰተዋል ››።
የማዕድን እና ኢነርጂ ቁጥር አራት ነዋሪዎች ለግሪን ኤርያው መብራት እና ውሃም እስከማስገባት የደረሰ ልማት ነው ያከናወኑት። ይሄን እንዴት ይመለከቱታል ? ተብለው የተጠየቁት አቶ አለማየሁ ፤ ‹‹ከመንግስት አካል መብራት እና ውሃ እንዲያስገቡ የፈቀደ አካል የለም›› ሲሉ ይመልሰዋል። ይህ ተከትሎ መብራት እና ውሃ እንዲያስገቡ የተፈቀደበትን ከመብራት ሃይል እና ከውሃ ልማት መስሪያቤቶች ህጋዊ ደብዳቤ የተጻፈ ደብዳቤ አለ ብለን አሳየናቸው ። ስለዚህ ምን ይላሉ? ስንልም የጠየቅናቸው አቶ አለማየሁ « ስለዚህ ጉዳይ የማውቀው ነገር የለም» ሲሉ መለሱ።
የቦሌ ክፍለ ከተማ የመሬት ዝግጅት እና ማስተላለፍ ዘርፍ ሃላፊ ምላሽ
የቦሌ ክፍለ ከተማ የመሬት ዝግጅት እና ማስተላለፍ ዘርፍ ሃላፊ አቶ ጌታሁን ነጋሳ ይባላሉ ። የአዲስ ዘመን ጋዜጣ ዝግጅት ክፍልም በቦሌ ክፍለ ከተማ ወረዳ 14 ስለሚገኘው የማዕድን እና ኢነርጂ ቁጥር አራት ግሪን ኤሪያ ምን ያውቃሉ? ሲል ለተጠየቁት ጥያቄ በሰጡት ምላሽ እንደገለጹት፤ ቅሬታ የተነሳበትን ቦታ የማዕድን እና ኢነርጂ ቁጥር አራት ነዋሪዎች በግሪን ኤሪያ ሲጠቀሙበት መቆየታቸውን የሰሙት የማዕድን እና ኢነርጂ ቁጥር አራት ነዋሪዎች ለክፍለ ከተማ ቅሬታ ካቀረቡ በኋላ መሆኑን ይናገራሉ ።
ከነዋሪዎቹ ቅሬታ ጋር ተያይዞ ጉዳዩን ለማጣራት ከወረዳ 14 ጋር መነጋገራቸውን የገለጹት አቶ ጌታሁን ፤ ወረዳው ቦታው ባዶ ቦታ እንጂ ግሪን ኤሪያ አለመሆኑን ገልጾልኛል።
የማዕድን እና ኢነርጂ ቁጥር አራት ነዋሪዎች ቦታውን ከ1983 ዓ.ም ጀምሮ በግሪን ኤሪያነት ሲጠቀሙት እንደቆዩ ይናገራሉ። ከዚህ ባለፈ በቦታው ላይ ውሃና መብራትም አስገብተውበታል። በአንጻሩ የእናንተ መስሪቤት ደግሞ ቅሬታ የተነሳበትን ቦታ በ2011 ዓ.ም ወደ መሬት ባንክ አስገብቶታል ። ይህ ሁለት ጉዳይ የሚቃረን ነገር ነው። እዚህ ላይ የእርስዎ አስተያየት ምንድን ነው? ሲል የአዲስ ዘመን ጋዜጣ ዝግጅት ክፍል የጠየቃቸው አቶ ጌታሁን ፤ የእርሳቸው መስሪያቤት ቦታውን ግሪን ኤርያ ብሎ የሚይዘው ቦታው ከፕላኑ አንጻር ግሪን ከሆነ እና የፕላን ጥበቃ ካለው ብቻ መሆኑን ይገልጻሉ።
ከዚህ ውጭ ግን ክፍት የሆኑ ቦታዎች በመረጃዎች መሰረት ይሰበሰቡና ወደ መሬት ባንክ ይገባሉ። ወደ ባንክ የገቡ ቦታዎችም ፕላኑ ከሚፈቅደው እና ከሚያዘው አንጻር ታይታ ለሚፈለገው የልማት ስራዎች እንዲውሉ ይደረጋል። የማዕድን እና ኢነርጂ ቦታውን በግሪን ኤርያነት ሲጠቀሙበት እንደቆዩ እና የማዕድን እና ኢነርጂ ቁጥር አራት ነዋሪዎች ቦታውን በአረንጓዴነት እያለሙ ስለመሆናቸውና በቦታው ላይ በጋራ ለመስራት የሚያስችሉ ደብዳቤዎችን ከቦሌ ክፍለ ከተማ የከተማ ውበት እና አረንጓዴ ልማት ቢሮ ጋር ለበርካታ ጊዜ መጻጻፋቸውን ሰነዶች ያሳያሉ። ስለዚህ ምን ይላሉ ? ተብለው የተጠየቁት አቶ ጌታሁን፤ ስለቦታው ከወረዳ 14 ለበርካታ ጊዜያት መጻጻፈቸውን ጠቁመው፤ ቅሬታ ያነሱት ሰዎች ቦታውም ለግሪን ኤርያ ሳይሆን ለመኪና ማቆሚያነት ይጠቀሙበት እንደነበርና ይህን ተከትሎ ቦታው ክፍት ቦታ ስለሆነ ወደ መሬት ባንክ ሊገባ መቻሉን ገልጸዋል።
የልማት ተነሽ የሆኑት አቶ ብርሃኑ የልማት ተነሺ ስለመሆናቸው በተለያዩ ደብዳቤዎች ተገልጿል። ከዚህ ጋር ተያይዞ በቦሌ ክፍለ ከተማ ወረዳ 11 ቁጥር ቦ/ክ/ከ/ወ.11/4067/2013 በቀን 10/09/2013 ዓ.ም አርሶ አደሩ ለልማት ተነሽ መሆናቸው ለክፍለ ከተማው ጽፏል። በአንጻሩ ክፍለ ከተማው ደግሞ በቁጥር ቦ/ክ/ከ/የ/ይ/አስ/ጽ/ቤት 184996/2012 በቀን 1716/2012 ዓ.ም አርሶ አደሩ የልማት ተነሺ ስለመሆናቸው ከወረዳው ቀድሞ ጽፏል። መረጃ ከወረዳው ሳያገኝ ክፍለ ከተማው ከምን ተነስቶ ነው አርሶ አደሩ የልማት ተነሺ መሆናቸውን የጻፈው ? ሲል የአዲስ ዘመን ጋዜጣ አቶ ጌታሁንን ጠይቆ ነበር ።
ለተጠየቁት ጥያቄ ምላሽ የሰጡት አቶ አቶ ጌታሁን እንደተናገሩት፤ የአይሲቲ ፓርክ ተነሺዎች የተነሱት ለፕሮጀክት ስራ ነው ። ፕሮጀክት ሲሰራ ደግሞ የራሱ የሆነ አሰራር አለው ። በዚያ አሰራር መሰረትም ክፍለ ከተማው ደብዳቤ ከመጻፉ በፊት በወረዳ ደረጃ የልማት ተነሺ ስለመሆናቸው በቃለ ጉባኤ የተያዘ ሰነድ ነበር። ያ ሰነድ ከወረዳ ለክፍለ ከተማ ደርሶታል። ክፍለ ከተማም ያንን ሰነድ መሰረት አድርጎ መብት ለመፍጠር ደብዳቤ መጻፉን አመላክተዋል። የፕሮጀክት አሰራር ምን እንደሚመሰል በግልጽና በዝርዝር አስረድተዋል። ዝግጅት ክፍሉም ከሚኖረው ሰዓት አንጻር ዝርዝር ጉዳዩን ትቶታል ።
የአዲስ ዘመን ጋዜጣ ዝግጅት ክፍልም የአይሲቲ ተነሺ የሆኑ ሰዎችን ወረዳ 11 ድረስ በመሄድ ለማናገር ሞክሯል። እነኝህን ሰዎች አቶ ብርሃኑ መኮንን የተባሉት ግለሰብ የአይሲቲ ፕሮጀክት ተነሺ መሆናቸውን ታውቃላችሁ ? ሲል ነበር ጥያቄውን የጀመረው። ነዋሪዎችም አቶ ብርሃኑ መኮንን የተባሉትን ግለሰብ እንደማያውቋቸው ይናገራሉ። ስለዚህ ምን ይላሉ ስንል አቶ ጌታሁንን ጠይቀናቸው ነበር። ሰዎችን ሁሉንም አንድ ባንድ እከሌ እከሌ ተነሺ ነው ማለት እንደማይችሉ ገልጸው፤ ይህንን ጉዳይ በዝርዝር የሚያውቀው የወረዳ አስተዳደሩ መሆኑን ጠቁመዋል።
የአዲስ ዘመን ጋዜጣ ዝግጅት ክፍል ወረዳ 11 ድረስ በአካል በመሄድ ለማጣራት እንደሞከረው ለአይሲቲ ተነሺዎች በ2014 ዓ.ም ካርታ የተሰራለት ሰው አለመኖሩን ስማቸው እንዳይጠቀስ የፈለጉ አካላት ይገልጻሉ። ስለዚህ እርስዎ ምን ይላሉ? ስንል ጠይቀናቸው ነበር ። አቶ ጌታሁንም መረጃው ውሸት እንደሆነና ከአይሲቲ ፕሮጀክት የተነሱ ሰዎች እስከዛሬዋ ቀን ድረስ መብት እየተፈጠረላቸው እንደሚገኙ ተናግረዋል።
አቶ ብርሃኑ መኮንን የተባሉት ግለሰብ አርሶ አደር ናቸው። በልማት የተወሰደባቸው መሬት ያለማ እና የእርሻ ስራ ይከወነበት የነበረ ነው። ምትክ የተሰጣቸው ቦታ ግን ገርጂ እየተባለ ከሚጠራው የከተማዋ ውድ ቦታ ላይ ነው። ስለዚህ ምን ይላሉ? ተብለው የተጠየቁት አቶ ጌታሁን እንደተናገሩት፤ ምትክ የሚሰጡት በመመሪያው መሰረት በቦሌ ክፍለ ከተማ ከሚገኝ ቦታ ነው። ይህን ተከትሎ የአዲስ ዘመን ዝግጅት ክፍል መመሪያው በምትክነት የሚሰጠው ቦታ ተመጣጣኝ መሆን እንዳለበት ይጠቁማል። ስለዚህ ከአይሲቲ ፓርክ አንስቶ ገርጂ ላይ መስጠት ተመጣጣኝ ነው ብለው ያስባሉ? ተብለው የተጠየቁት አቶ ጌታሁን ‹‹አዎ! ተመጣጣኝ ነው›› የሚል ምላሽ ሰጥተዋል ።
የልማት ተነሺው 500 ካሬ ሜትር እንዲሰጠው ተወስኖለት ነበር እናንተ 400 ካሬ ሜትር ሰጣችሁ ? ሲል የአዲስ ዘመን ጋዜጣ ዝግጅት ክፍል አቶ ጌታሁንን ጠይቆ ነበር። አቶ ጌታሁንም ካለን የመሬት እጥረት አንጻር ታይቶ አንድ የልማት ተነሺ ፈቃደኛ እስከሆነ ድረስ 20 በመቶ ድረስ ተቀንሶ ሊሰጥ እንደሚችል በመመሪያ መቀመጡን ገልጸው ፤ አቶ ብርሃኑም በዚያ አግባብ መስተናገዳቸውን ይናገራሉ።
በርካታ የማዕድን እና ኢነርጂ ቁጥር አራት ነዋሪዎች ለተለያዩ ተግባራት የሚጠቀሙበትን የነበረን ቦታ በልማት ተነሺ ስም ለአንድ ሰው መሰጠቱ ተገቢ ነው ብላችሁ ታምናላችሁ ? ተብሎ ለቀረበላቸው ጥያቄ አቶ ጌታሁን ጥያቄው እንደማይመለከታቸው እና ጥያቄው የመልካም አስተዳደር ጉዳይ መሆኑን ጠቁመዋል።
የማዕድን እና ኢነርጂ ቁጥር አራት ነዋሪዎች አንድ መውጫ እና መግቢያ ብቻ ነው ያላቸው ። በደስታ እና በሃዘን የሚጠቀሙት ይሄንኑ ቦታ ብቻ ነው ። ይህ መሆኑን ማንም ሰው ከሰፈሩ ፕላን አይቶ የሚገነዘበው ነው። ከዚህ አንጻር የእናንተ መስሪያቤት ይህን ቦታ ለልማት ተነሺ መስጠቱ ተገቢ ነው ብለው ያምናሉ? ሲል ለተነሳው ጥያቄም ጉዳዩ የከተማ ፕላን ጽህፈት ቤት እንጂ እርሳቸውን እንደማይመለከት ተናግረዋል።
ከቦሌ ክፍለ ከተማ መሬት ልማት እና አስተዳደር ጽህፈት ቤት የተገኙ የሰነድ ማስረጃዎች
ሰነድ አንድ
በቀን 17/6/2012 ዓ.ም በቁጥር ቦ/ክ/ከ/የ/ይ/አስ/ጽ/ቤት 184996/2012 የቦሌ ከፍለ ከተማ የመሬት ይዞታ አስተዳደር ጽህፈት ቤት የመደበኛ ይዞታዎች ካርታ ዝግጅት የስራ ሂደት ለመሬት ልማትና ከተማ ማደስ ጽህፈት ቤት የሚከተለውን ደብዳቤ ጽፎ ነበር ።
በአይሲቲ ፕሮጀክት ተነሺ የሆኑ ባለይዞታዎችን በተመለከተ በዴስኩ በኩል የተሰጠ ውሳኔ ሃሳብን ስለማሳወቅ መሆኑ በጉዳዩ ተመላክቷል።
የቦሌ ክፍለ ከተማ የመደበኛ ይዞታዎች ካርታ የስራ ሂደት አግባብ ያለው አካል ሳይፈቅድ የተያዙ ቦታዎችን ለማስተካከል እና ለመከላከል ባወጣው የመመሪያ ቁጥር 18/2006 መሰረት በልማት ተነሺ የሆኑ ባለይዞታዎችን መስተንግዶ እንድንሰጥ በቁጥር አአ/መልማቢ/01/1710 በቀን 10/10/06 እና ይአስ /848/07 በቀን 27/01/2007 ዓ.ም ተገልጻል። ከዚህ ባሻገር የመሬት ልማት እና ማኔጅመንት ቢሮ ስለ አርሶ አደር እና የአርሶ አደር ልጆችን መስተንግዶ አሰጣጥ በቀን 15/6/08 በቁጥር አአ/መልማቢ/ 01/2245/08 እና በቀን 11/8/10 በቁጥር ይአስ/2235/10 የካቢኔ የውሳኔ አቅጣጫ ተቀምጧል።
በመሆኑም በመመሪያው በአንቀጽ 6 በንዑስ አንቀጽ 6 ነጥብ 4 ከሚያዚያ 1997 ዓ.ም የተያዙ ስለመሆናቸው ቢረጋገጥም የከተማ ፕላን እና አካባቢ ሽንሻኖ የማይቀበላቸው ህጋዊ ባልሆነ መንገድ የተያዙ ይዞታዎች ተጣርቶ በሚቀርበው መረጃ መሰረት የግለሰቦችን ስም በማደራጀት በደንቡ ላይ በተደነገገው መሰረት ምትክ ቦታ እንዲያገኙ ለመሬት ልማት እና ከተማ ማደስ ጽህፈት ቤት እንዲተላለፍ በሚል ተገልጿል።
ይህን መነሻ በማድረግ በአይሲቲ ፓርክ ልማት ተነሺ ሆነው ከመሬት ልማትና ከተማ ማደስ ጽህፈት ቤት መረጃቸው ተደራጅቶ ዝርዝራቸው ከተላኩት የልማት ተነሺዎች መካከል በቦሌ ክፍለ ከተማ ወረዳ 14 የማዕድን እና ኢነርጂ ቁጥር አራት የአረንጓዴ ስፍራ ወይም ግሪን ኤርያን በልማት ተነሽነት ስም የተሰጡት አቶ ብርሃኑ መኮነን አንዱ መሆናቸው ተመላክቷል። በዚህ መሰረትም አቶ ብርሃኑ መኮነን እና ቤተሰባቸው ለእያንዳንዳቸው 500 ካሬ ሜትር መሰጠት እንዳለባቸው ተገልጿል።
ሰነድ ሁለት ፡-
በቦሌ ክፍለ ከተማ የወረዳ 11 ዋና ስራ አስፈጻሚ ለቦሌ ክፍለ ከተማ መሬት ልማትና ማኔጅመንት ከተማ ማደስ ጽህፈት ቤት በቁጥር ቦ/ክ/ከ/ወ/11/4067/2013 በቀን 10/09/2013 ዓ.ም የተጻፈ ደብዳቤ እንደሚጠቁመው የደብዳቤው ዓብይ ጉዳይ መረጃ መላክን የሚመለከት መሆኑን ገልጾ፤ በዚህም ደብዳቤ ወረዳው ከዚህ ቀደም በቁጥር ቦ/ክ/ከ/ወ.11/ጽ/ቤት 3924/2013 በቀን 01/07/2013 ዓ.ም በተጻፈ ደብዳቤ 165 አርሶደሮች እና አርሶ አደር ልጆች በአይሲቲ ፓርክ ልማት ተነሺ መሆናቸውን አጣርቶ መላኩን እና የቀሩትንም «የኤክስ ዋይ ኮርድኔት » አጣርቶ እስከሚልክ ድረስ የተላኩት የ165 አርሶ አደር ፋይሎች እንዲስተናገዱ እና አስፈላጊውን ትብብር እንዲደረግላቸው የሚገልጽ ሲሆን ከ165ቱ አርሶ አደሮች መካከልም አቶ ብርሃኑ መኮንን እና ቤተሰቦቻቸው እንደተካተቱ ተመላክቷል።
የጋዜጠኛው ትዝብት
ትዝብት አንድ፡- ውዝግብ የተነሳበትን ቦታ በአካል ተገኝቼ ተመልክቻለሁ። ግሪን ኤርያው ውስጥ ቆርቆሮ በቆርቆሮ የተሰሩ ውሃ እና መብራት የገባባቸው ቤቶች አሉ። የአካባቢው ማህበረሰብም ተቀያሪ መውጫ እና መግቢያ ስሌለለው ግሪን ኤርያውን ከግሪን ኤርያነት ባለፈ በደስታ እና በሃዘን ጊዜ ድንኳን በመትከል ጉዳያቸውን ሲከውኑ ተመልከቻለሁ። ይህ ቦታ ባይኖር ኖሮ አንድ መውጫ እና መግቢያ ያለው ይህ ማህበረሰብ በሃዘን እና በደስታ መውጫ እና መግቢያ ማግኘት እንደማይችልና ማናቸውም አይነት እንቅስቃሴ ለማድረግ እንደሚቸገር ለመታዘብ ችያለሁ።
ትዝብት ሁለት ፡- የልማት ተነሺ የተባሉትን ግለሰብ በአካል ማግኘት ስላልቻልን የልማት ተነሺ ናቸው የተባሉትን ግለሰብ ለማግኘት በቦሌ ክፍለ ከተማ ወረዳ 11 ድረስ በመገኘት የአይሲቲ የልማት ተነሺ የነበሩ ሁለት ስማቸው እንዳይጠቀስ የፈለጉ ሰዎች አቶ ብርሃኑ መኮነን ያውቁ እንደሆን ለመጠየቅ ሞክረን ነበር። ነገር ግን የተባሉትን ግለሰብ በአይሲቲ ፕሮጀክት መነሳታቸውን እንደማያውቁ እና ሰውየውንም ፈጽሞ እንደማያውቋቸው ነግረውናል።
ከአዘጋጁ፤ ተነሺ አርሶ አደር ናቸው የተባሉትን አቶ ብርሀኑ መኮነን ለማግኘት ጥረት አድርገናል። የልማት ተነሺ ናቸው የተባሉ ሰዎችንም አግኝተን ጭምር ለማነጋገር ሞክረናል፤ ሆኖም ግን እናውቃቸዋለን የሚል አካል ማግኘት አልቻልንም። እርሳቸውን በአካል ወይም ተንቀሳቃሽ ስልካቸውን ማግኘትም አዳጋች ሆኗል። እኚህ የልማት ተነሺ የተባሉትን ግለሰብ ካሉ ልናነጋግራቸው ሀሳባቸውንም ልናደምጥ ዝግጁ ነን። ሌሎች በዚህ ዙሪያ ሀሳብ፣ መረጃ፣ አስተያየት ለመስጠት ለሚፈልጉ ሁሉ ዝግጅት ክፍላችን የሚያስተናግድ መሆኑን ለመግለጽ እንወዳለን።
ሙሉቀን ታደገ
አዲስ ዘመን ኅዳር 21/ 2015 ዓ.ም