የአካል ጉዳት ካሳ ጠያቂው ፍትህ ተነፈገኝ እና የድርጅቱ ምላሽ

እንደ መንደርደሪያ፤

ዓለም አቀፉ የሰራተኞች ድርጅት አባል አገሮች የአገራቸውን ተጨባጭ ሁኔታ መሰረት በማድረግ የሥራ ላይ ደህንነትና ጤንነት ሕጎችን እንዲያወጡ እና የወጡ ሕጎችንም ወደ ተግባር እንዲለወጡ የማድረግ ኃላፊነት የአስፈጻሚው አካል ነው። ኢትዮጵያም የድርጅቱ አባል እንደመሆኗ የሥራ ላይ ደህነነትና ጤንነትን የማረጋገጥ ኃላፊነት አለባት። ይህንንም በሕገ መንግስቷ ላይ በግልጽ አስቀምጣለች። በሕገ መንግስቱ ላይ በተለይ አንቀጽ 42 ንዑስ ቁጥር 2 ላይ በዋናነት ሰራተኛው ጤናማና ከአደጋ ነጻ የሆነ የሥራ አካባቢ የማግኘት መብት ያለው ስለመሆኑ ተደንግጎ ይገኛል።

በኢትዮጵያ የሥራ ላይ ደህንነትና ጤንነትን ማረጋገጥ የሚያስችሉ የአሰሪና ሰራተኛ ሕጎችና አዋጆች ወጥተዋል። ሕጎቹ ይውጡ እንጂ ሙሉ ለሙሉ በሁሉም አካላት ተግባር ላይ መዋላቸው ግን ጥያቄ ውስጥ ይገባል። በኢትዮጵያ ባለው ነባራዊ ሁኔታ ድርጅቶች የሥራ ላይ ደህንነት መስፈርትን አሟልተው ከማሰራት እንዲሁም በሥራ ላይ ደህንት ስለሚደርስ የጉዳት ካሳ ክፍያ የሚታይባቸው ሰፊ የአፈጻጸም ክፍተቶችም ይህን ያመለክታሉ።

የዛሬው የፍረዱኝ ዓምዳችን በሥራ ላይ ከሚደርስ የጉዳት ካሳ ጋር የተያዘ ሲሆን የካሳ አከፋፈል ምን ይመስላል፤ የሕክምና ማስረጃ የምስክር ወረቀት እንዴት ይሰጣል ፣ የአሰሪና ሰራተኛ ጉዳይ አዋጁስ በጉዳዩ ላይ ምን ይላል የሚለውን የሚዳስስ ነው ።

የአሰሪና ሰራተኛ ጉዳይ አዋጁ ስለሰራተኛው መብትና የጉዳት ላይ ካሳ ምን ይላል?

በአሰሪና ሰራተኛ ጉዳይ አዋጅ 1156/2011 በአንቀጽ 92 ንዑስ አንቀጽ አንድ ስር የተደነገገው የአሰሪውንና የሰራተኛውን ግዴታዎች ያስቀምጣል። አሰሪው በዋናነት ስለሙያ ደህንነትና ጤናማነት የተደነገጉ ሁኔታዎችን የማክበር ኃላፊነት አለበት። ይሄንን ወደ ተግባር ለመቀየር ደግሞ መሟላት ያለባቸውን ነገሮች የማሟላት ኃላፊነት ያለበት ስለመሆኑ በአዋጁ ዘርፍ ሁለት አንቀጽ 99 ንዑስ አንቀጽ አንድ እና ሁለት እንዲሁም አንቀጽ 100 ፤ 101 እና 102 ንኡስ አንቀጽ አንድ እስከ ሶስት በግልጽ ተቀምጧል።

ለተጎጂዎች ሕክምና የመስጠት፤ ለደረሰው ጉዳት ደግሞ አግባብነት ያለው ካሳ መከፈሉን ማረጋገጥ አስፈላጊ መሆኑንም አዋጁ ይደነግጋል። ከደረሰው ጉዳት ጋር ተመጣጣኝ የሆነ ካሳ መከፈል ያለበት ስለመሆኑ ከአሰሪና ሰራተኛ ጉዳይ አዋጁ በተጨማሪ የፍትሃብሔር ሕጉ የሚያስቀምጠው ጉዳይ ነው።

በአዋጁ በግልጽ እንደተመላከተው ማንኛውም ሰራተኛ የሚሰራበትን ተቋም ንብረት በአግባቡ መጠበቅና መያዝ እና መጠቀም እንዳለበት፤ እንዲሁም ቀጥሮ የሚያሰራ ድርጅት የሰራተኞችን ሰብአዊ መብት ማክበር እንደሚጠበቅበት ይደነግጋል። ባለው ተጨባጭ ሁኔታ ግን ሕጉን በውል ተገንዝቦ የሚሰራ ሰራተኛም ሆነ ሆነ የሚያሰራ ድርጅት እምብዛም አይስተዋልም። ሰራተኛው ሕጉን የመገንዘብ አቅም ባልዳበረባቸው ሀገራት ሰራተኞች መብታቸው ማስከበር ሲሳናቸው ይስተዋላል።

የአቤቱታ አቅራቢው ሮሮ

መናገሻ የሚገኘው ሀሚድ ከድር እና ወንድሞቹ ጠቅላላ ብረታብረትና ሚዛን ማምረቻ ድርጅት ተቀጥሮ ለሶስት ዓመት ከስምንት ወር ያህል የሰራው አቶ ድሪባ አበበ የማሽን ላይ ሥራ እያከናወነ ባለበት ወቅት እጁ ላይ ጉዳት አጋጠመው። የማሳከም ግዴታ የድርጅቱ በመሆኑ ታክሞ ቢሻለውም ማሽን ላይ መስራት ባለመቻሉ ከድርጅቱ መሰናበቱን ገልጿል።

አቶ ድሪባ የሰራተኞች ማህበር አባል በመሆንም የድርጅቱ ሰራተኛ መብት እንዲከበር የበኩሉን አስተዋጽኦ አድርጓል። እሱ እንዳለው፤ በተወሰነ መንገድ የደህንነት መጠበቂያ ጫማ፤ ለበያጆች ደግሞ መነፅር ያቀርባል። ማሽን ላይ እየሰራ ያለ ግን ሌላ የደህንነት መጠበቂያ የለውም። እሱም በድርጅቱ ማሽን ላይ ሥራ እያከናወነ ባለበት ወቅት እጁ ላይ ጉዳት እንዳጋጠመው ይናገራል።

በድርጅቱ የማትጊያ በሚል ከደመወዝ በተጨማሪ በሚሰሩት የሚዛን ክፍሎች ቁጥር ማለት በ‹‹ፒስ›› በመሆኑ ሰራተኛው ከፍ ያለ የደመወዝ ክፍያ ለማግኘት ደህንነት መጠበቂያ ቢሟላም ባይሟላም ሥራ መስራት አያቆምም ። በሚሰሩት የ‹‹ፒስ›› ሥራ በቀነሰ ቁጥር የወር ደመወዙ የሚቀንስ በመሆኑም ብዙ ጌዜ ለደህንነት መርህዎች የተገዛ አይደለም። በዚህ ሳቢያም በተቋሙ የማሽን ሥራ ላይ እንዳለ በእጁ ላይ አደጋ ደርሶበታል።

ድርጅቱ የማሳከም ግዴታ ስላለበት አሳክሞት ከሕመሙ አገገመ። እንዲያም ሆኖ ግን እጁ ማሽኑን ማንቀሳቀስ ስለማይችል በተገቢው መንገድ እስከሚሻለው ድረስ ሕክምና የወሰደበት ተቋም ለስድስት ወር ያህል ቀላል ሥራ እንዲያሰሩት፣ ከዚያ በኋላ እዩት የሚል የሕክምና ማስረጃ ወደ ድርጅቱ ጽፎለት ቢያቀርብም ቀላል የሚባል ሥራ ስለሌለ ማሽን ላይ ሥራ ተባለ። የሚሰራበትን ‹‹የቶርኖ›› ማሽን ለማንቀሳቀስ የእጁ ጣቶች በደንብ ስለማይሰሩ መስራት አልቻለም።

የሚያደርገው ጠፋውና መስራት እንደማይችል ለድርጅቱ አሳወቀ። ድርጅቱም መስራት ካልቻልክ በራስህ ፍላጎት መልቀቂያ አስገባና ውጣ የሚል ምላሽ ሰጠው። በተሰጠው ምላሽ መሰረትም ሳይወድ በግድ የመልቀቂያ ደብዳቤ አስገብቶ የአገልግሎት በሚል 10 ሺ ብር ተቀብሎ ከድርጅቱ እንደተሰናበተ ይናገራል።

የታከመበት የሕክምና ተቋም የሰጠውን የሕክምና ማስረጃው ለምኒሊክ ኮምፕሪሄንሲቭ ስፔሻላይዝድ ሆስፒታል የሕክምና ማስረጃውን ላከ። ከድርጅቱ ከተሰናበተ በኋላ የደረሰብኝ የአካል ጉዳት ነው፤ ከሥራም ስለተሰናበተ የጉዳት ካሳ እንዲከፈለው የሚያስችል የሕክምና ምስክር ወረቀት ለማግኘት ወደ ሆስፒታሉ በመሄድ ካሳ ለመጠየቅ የሚያስችለው የምስክር ወረቀት እንዲሰጠው ጠየቀ።

የሕክምና ምስክር ወረቀት የሚሰጠውን የምኒሊክ የሕክምና ቦርድ ሲጠይቅም ቦርዱ ስትሰራበት የነበረው ድርጅት የአካል ጉዳት መጠንን የሚገልጽ ደብዳቤ ይጻፍልህ የሚል ምላሽ ሰጠው። በነገሩት መሰረት ለድርጅቱ ማመልከቻ ጽፎ ቢያስገባም ድርጅቱ የጉዳት ካሳ መክፈል ስለማይፈልግ ሊሰጠው ፈቃደኛ ሳይሆን ቀረ።

ሲሰራበት የነበረው ድርጅትም ጡረታ ከፋይ ስለሆነ መስጠት አንችልም የሚል ምላሽ ሰጠው። ‹‹የትም ሄጄ መብቴን የማስከብርበት አቅም ስለሌለኝ እንዲሁ ያለ ጉዳት ካሳ ቀረሁ። ምንም ሥራ ሳላገኝ ስድስት ወር ሙሉ ተቀመጥኩ። ዛሬ የጥበቃ ሥራ እየሰራሁ ቤተሰብ እየመራሁ ነው። ሰራተኛ ማኅበር በተሰበሰበበት በሥራ ላይ ያሉትም ቢሆኑ ከፈለጋችሁ የትም መሄድ ትችላላችሁ፤ ምንም አታመጡም በሚል ሰራተኛውን ያስፈራራሉ። ይህ በእሱ ብቻ ሳይሆን በሌሎች ሰራተኞች ላይ እየደረሰ ያለ ግፍ ነው ሲል አቶ ድሪባ ያብራራል።

በሥራ ላይ ያሉ የድርጅቱ ሰራተኞችስ ምን አሉ?

ስማቸው እንዳይጠቀስ የፈለጉ በድርጅቱ ሥራ ላይ ያሉ ሰራተኞች ድርጅቱ በሰራተኞች ላይ የሚያደርሰው ጫና የሚፈጸመው በተጠና እና በተደራጀ መንገድ ነው። በአቶ ድሪባ ላይ የደረሰው ጉዳት በእኛ ላይ ላለመድረሱ ምንም ዋስትና የለንም። በድርጅቱ ከተቀጠርን ከአምስት ዓመትና ከዚያም በላይ ቢሆነንም የሥራ ዕድገት ስንጠይቅ ከፈለጋችሁ መልቀቅ ትችላላችሁ የሚል የማን አለብኝነት ምላሽ ይሰጣቸዋል።

ደመወዛችን የሚከፈለው በ‹‹ፒስ›› ስለሆነ ወጥነት የለውም። ፒስ ማለት በተሰራው ሥራ ልክ ማለት ነው። ቋሚ ሰራተኛ ተብለን ተቀጥረን ለምሳሌ 4ሺ513 ብር ደመወዝ በቅጥር ውሉ ላይ ያለ ደመወዝ ቢሆንም፣ በፒስ ሰርተን የምናገኘው ብር ከደመወዙ በላይ ነው።

ፒስ የሚባው የሚዛን እቃዎቹ መቶ ፍሬዎች ቢሆኑ ፍሬዎቹ የሚሰሉበት ሳንቲም ስላለ ተባዝቶ በወር መጨረሻ ከደመወዝ ጋር ተድምሮ የሚከፈል ነው። አንድ ሰው አምስት ሺ ብር ቢሰራ በወር ውስጥ ከስድስት ሺ ብር ላይ ደመወዝ ከሚባለው አራት ሺ 513 ተቀንሶ ተቀናሹ ላይ ግብር ደመወዙ ላይ ደግሞ ጡረታ እና ግብር ይከፈልበታል። የሰራተኛ ማህበር ለድርጅቱና ጉዳዩ ለሚመለከታቸው ሌሎች ተቋማት አቤቱታ ቢያቀርብም መፍትሔ አላገኘም።

ሰራተኛው እየተማረረ እንዲለቅ ማድረግ የድርጅቱ ተግባር ነው። ‹‹የመብት ጥያቄ ስንጠይቅ ከተመቸህ ሥራ፤ ካልተመቸህ ትተህ ሂድ የሚል ምላሽ ይሰጠናል። ለእናንተ በሚከፈለው ደመወዝ ሁለት ሶስት ሰራተኛ ቀጥረን ማሰራት እንችላለን የሚል ምላሽ ይጠብቀናል። መብላት ስላለብን ይህን ሁሉ እየቻልን መብታችን ተረግጦ እንኖራን›› ሲሉ ያስረዳሉ።

የዳግማዊ ሚኒሊክ ኮምፕሬሄንሲቭ ስፔሻላይዝድ ሆስፒታል ስለሕክምና ምስክር ወረቀቱ ምን አለ?

በሥራ ላይ ለሚደርስ የሕክምና ጉዳት የሕክምና የምስክር ወረቀት በምን መልኩ እንደሚሰጥ፤ በምን አይነት የአሰራር ማእቀፍ እንደሚከናወን የዳግማዊ ምኒሊክ ኮምፕሬሄንሲቭ ስፔሻላይዝድ ሆስፒታል ዋና ሥራ አስኪያጅ ዶክተር ተከተል ጥላሁን ሲያብራሩ ፤ ከቦርድ የሕክምና መረጃ አሰጣጥ ጋር ተያይዞ ያለው አሰራር ማንኛውም ሰው የሕክምና ማስረጃ የማግኘት መብት አለው።

እዚህ ላይ ግን የቦርድ ሰርተፊኬትና የሕክምና ማስረጃ ይለያያል። የሕክምና ማስረጃ ማንኛውም ሰው ታክሞ ስለበሽታዬ ማስረጃ ይሰጠኝ ብሎ ጥያቄ ካቀረበ በጽሁፍ ወይም ደግሞ በማብራሪያ መልኩ የጉዳት መጠኑን ጨምሮ የሕክምና ማስረጃ የሚሰጥበት አሰራር ነው። ይህ በመደበኛ መልኩ ለታካሚ ሊሰጥ የሚችል ነው።

የቦርድ የሕክምና ማስረጃ ከተጠየቀ ግን በቦርዱ ውሳኔ የሚሰጥ ስለሆነ የታካሚው ማስረጃን ለመስጠት በፍርድ ቤት ታዞ የደረሰበት የጉዳት አይነት ዘላቂ ይሁን ጊዚያዊ ተለይቶ፣ ባለው የጉዳት መጠን በመቶኛ ተገልጾ የሚሰጥ ነው። በዕለት ተዕለት እንቅስቃሴ ላይ ጭምር መሰል ጫና እንደሚያደርስ ተገልጾ የሚጻፍባቸው ጊዚያትም ይኖራሉ። ይህ ግን በፍርድ ቤት ወይም በኢንሹራንስ የተጎዳው አካል ጥቅም ሊያገኝበት ወይም ጉዳቱን ሊያካክስለት የሚችለው መስሪያ ቤት ሲጠይቅ የሚሰጥ ማስረጃ ነው ይላሉ።

ማስረጃው ሲሰጥም ሶስት ሀኪሞች ቁጭ ብለው የእያንዳንዷን ጉዳት አይነትና መጠን መርምረው መቶኛ አውጥተው በሆስፒታሉ የበላይ ኃላፊ ተረጋግጦ ለጠየቀው አካል መረጃው እንደሚሰጥ ያብራራሉ።

ከፍርድ ቤት ባሻገር በአንድ ድርጅት ሥራ ላይ እያለ ጉዳት የደረሰበት ሰው ታክሞ ካገገመ በኋላ ጉዳቱ ጊዚያዊም ይሁን ሌላ የሚሰራበት ድርጅት የጉዳት ካሳ እንዲከፍል ቦርዱ የሕክምና ምስክር ወረቀት ማስረጃ ይጸፍልኝ ብሎ ሲጠየቅ ድርጅቱ ይጻፍልህ ብሎ ምላሽ መስጠቱ በሕግና በአሰራር የተደገፈ አሰራር ነው ወይ? ተብሎ ለተነሳላቸው ጥያቄ ዶክተር ተከተል ሲመልሱ ፤ ታካሚው የጉዳት መጠኔን ይዤ ልክሰስ ካለ ለራሱ የሚሰጥ ሰርተፊኬት አለ። በዚህም የተመረመረበትንና ሕክምናውን ያጠናቀቀበትን ሁኔታ የሚገልጽ ማስረጃ ተጽፎ ይሰጠዋል።

ለክስ እጠቀማለሁ ብሎ ወደ ፍርድ ቤት ከሄደ ደግሞ ፍርድ ቤት የቦርዱን የሕክምና ማስረጃ ይፈልጋል። ሕክምና የሰጠው ባለሙያ ሳይሆን የቦርድ ሰርቲፊኬት ወሳኝ ነው። የቦርድ ተቋማት የራሳቸው አሰራርና ደንብ ስላላቸው ቦርዱ ለግለሰቡ ማስረጃ አይሰጥም። ድርጅቶች የራሳቸውን ጥቅም የሚጎዳ ከሆነ መረጃ ስጡት ብለው ላይጠይቁ ይችላሉ።

ድርጅቱን የመክሰስ መብት የተጎጂው አካል በመሆኑ በክስ ወቅት በፍርድ ቤት ማስረጃ እንዲሰጥ ከሳሽ ክስ አቅርቧል። ባቀረበው ክስ መሰረት ማስረጃው ተጣርቶ ይምጣ ተብሎ ፍርድ ቤት  በደብዳቤ ሲጠየቅ የሕክምና ቦርዱ ጽፎ ይሰጣል።

የግል ሰርተፊኬት ግን በአመልካቹ ጥያቄ መሰረት ማስረጃ ይሰጣል። አልሰጥም የሚል አካል ካለ ቢሯችን ከፍት ስለሆነ መጥተው መጠየቅ ይችላሉ። የታከሙበት አካባቢ ሥራ ክፍሎችን ማስረጃ በመያዝ መጠየቅና በየደረጃው መጠየቅ ተገቢ ነው ሲሉ አስታውቀዋል።

ቦርዱ የሕክምና ማስረጃ የሚጽፍበት አግባብ በሕግና በአሰራር የተደገፈ ነው? በሚል ለቀረበላቸው ጥያቄም፤ ከሀገር ውስጥም ሆነ ከሀገር ውጭ ለሆነ ሕክምና የሚሰጠው የሕክምና ማስረጃ የሚሰራበት አሰራር አለው። በጉዳት መጠን ላይም የትኛውም የአካል ክፍል ሲጎዳ ስንት ፐርሰንት ይጻፋል የሚለው እያንዳንዱ አካል ክፍል ላይ በሚደርስ ጉዳት የሚጻፍ ማስረጃ ዓለም አቀፍ የሕክምና ሕግን የተከተለ አሰራር አለ። የሆስፒታሉ ብሎም የጤና ዘርፉ አሰራር አለው። ስለዚህ አዋጅ የለውም፤ ወጥ ሆነ መመሪያ የለውም።

ወጥ የሆነ መመሪያ ከሌለው፣ አሰራሩ ከሕግና ደንብ የማይቀዳ ከሆነ ስለምንስ ተጎጂዎች ካሳ እንዲያገኙ ከድርጅቱ ይሁንታ ደብዳቤ እንዲጻፍ ተደረገ? ጉዳዩ ተጎጂዎችን ሳይሆን ድርጅቶችን እንደ መደገፍ አይቆጠርም? ተብሎ ለተነሳላቸው ጥያቄ ሲመልሱ ‹‹ሁሉ ነገር መመሪያ የለውም። መመሪያ የሌላቸው ተቋማት የራሳቸው መተዳደሪያ ደንብ ይኖራቸዋል፤ ምክንያቱም ተቋሙ ከሚገጥመው ከዕለት ተዕለት የራሱ የአሰራር ስርዓቶች የራሱ የሆነ የአሰራር መመሪያዎች ይኖሩታል። የቦርድ አሰራርም ከነዚህ መሰል የተቋሙ መመሪያና አሰራሮች አንዱ ነው። ተቋሙ በራሱ ይህ የእኔ አሰራር ነው ብሎ የሚያወጣቸው የ‹‹ኦፕሬሽናል›› ስታንዳርድ ውስጥ የቦርድ አሰራር አንዱ ነው ብለዋል።

የቦርድ አሰራር በሕክምና ስርዓቱ አላግባብ ጥቅም ላይ ከሚውልበት ስርዓት አንዱ ቦርድ ነው። ከሚገጥመን ፈተና አንዱ ሀገር ውስጥ መታከም የሚችሉትን ዶላር ለማግኘት ሲባል ወደ ውጭ ሀገር ሂዶ ለመታከም ማስረጃ ይሰጠኝ በማለት ያልተገባ ሥራ የሚሰራበት ነው። ስለዚህ በየሆስፒታሉ የሚሰራውን ሥራ በአንድ አንድ ማዕከል ሜዲካል ቦርድ ተቋቁሞ ሊሰራበት ይገባል። ይህ ሲሆን እንግልትን ይቀንሳል፤ የአሰራር ወጥነት ለማምጣት፤ የሀገርን ጥቅም ለማስከበር፤ ሲባል ወጥ የሆነ በማዕከል የሚመራ አሰራር ሊኖር ይገባል።

የቦርድ የሕክምና የምስክር ወረቀት ለውሳኔ ሰጭ ተቋማት የሚያገለግል ነው፤ የተለዩ መንግሥታዊና የግል ድርጅቶች የሚጠቀሙበት አቅም ያለው ማስረጃ ነው። እናም ወደ አንድ መስመር የሚመጣበትና ወጥ የሆነ ደብዳቤ የሚወጣበት አሰራር ላይ ለመድረስ እንደ ጤና ዘርፍ መሰራት አለበት ይላሉ።

የሀሚድ ከድርና እና ወንድሞቹ ጠቅላላ ብረታብረትና ሚዛን ማምረቻ ድርጅት ምን ምላሽ ሰጠ?

የሀሚድ ከድርና እና ወንድሞቹ ጠቅላላ ብረታብረትና ሚዛን ማምረቻ ድርጅት የሰው ኃይል አስተዳደር ኃላፊ አቶ ደጀኔ ወልደሚካኤል የሰው ሀብት ዳይሬክተር የሰራተኞች ቅሬታን አስመልክቶ በሰጡት ምላሽ እንዳሉት፤ ድርጅቱ ብረትን ወደ ሚዛን የሚቀይር ፋብሪካ እንደመሆኑ መጠን በሰራተኞች ላይ አደጋ እንዳይደርስ መሟላት ያለበትን የደህነት መጠበቂያ እንደ ጫማና የአይን መነጽር ያሉትን አሟልቶ ያሰራል።

ሲቀጠሩም በአሰሪና ሰራተኛ አዋጁ መሰረት መብትና ግዴታቸውን እንዲያውቁ በማድረግ ነው። ወደ ሥራ እንዲገቡ የሚደረገውም በዚሁ ሁኔታ ነው። የሥራ ላይ ጉዳት ሲደርስ ወደ ሕከምና ለመውሰድ ዝግጁነት ባለው መልኩ የሚሰራበት ሁኔታ አለ። በድርጅቱ ወጥ የሆነ የሕብረት ስምምነት የለም። ስምምነት ማለት በእያንዳንዱ ጉዳይ የጋራ መግባባት ይዞ የጋራ አቋም እንዲኖር ማድረግ ነው። በድርጅቱ ካለው የሰራተኛ ማሕበር ጋር ስምምነት ላይ ለመድረስ አዳጋች ነገር የለም።

በድርጅቱ የሰራተኛ ማሕበር ለይስሙላ ቢኖርም መብት ለማስከበር ጥያቄ ካቀረበ ስልታዊ ጥቃት ይደርስብናል ሲሉ የተናገሩ ከሥራ የተሰናበቱና በሥራ ላይ ያሉ ሰራተኞች አሉ፤ ድርጅቱ መብታችን እየተጣሰብን ነው የሚል ቅሬታ እያቀረቡ ናቸው በሚል ላነሳንላቸው ጥያቄ፤ ‹‹ቅሬታው እውነትነት ያለው ነው ብዬ አልወስደውም›› ሲሉ ገልጸዋል።

እሳቸው እንዳሉት፤ የአሰሪና ሰራተኛ አዋጁ እንደሚለው አንድ ሰራተኛ በድርጅቱ በደል ቢደርስበት በሰራተኛ ማህበር፤ በወረዳ ሰራተኛና ማህበራዊ ጉዳይ እንዲሁም አለፍ ሲል በፌደራልም ሆነ በክልል ደረጃ የሚጠይቅበት መንገድ አለ። ስለሆነም እስካሁን ድረስ በዚህ መንገድ የጠየቀን አካል የለም።

የሰው ኃይል አስተዳደር በደል ቢፈጽም አስተዳደሩን መጠየቅ ይችላል። ከዚህ ውጭ ደግሞ ከሰራተኛ ማህበር እስከ ኮንፌዴሬሽን ድረስ ሂደው አቤቱታ ማቅረብ ይችላሉ። ከዚያ በሻገር ደግሞ በህጉ እንደተቀመጠው እስከ ሥራ ክርክር ችሎት ድረስ መሄድ ይቻላል። የትኛውም ሰራተኛ አሁን በሥራ ላይ ያለ ይሁን ከሥራ የተሰናበተ መብቱ ተከብሮለት ስርዓት ባላው ሁኔታ ድርጅቱ ያስተናግዳል።

በህጉ መሰረት ድርጅቱ የሚያስተናግድ ከሆነ አቶ ድሪባ ላይ የተፈጸመው ድርጊት ህጉን መጣስ አይሆንም ወይ? የሚል ጥያቄ አቀርብንላቸው። እሳቸው በሰጡት ምላሽ ‹‹እውነት ነው አቶ ድሪባ አበበ የድርጅቱ ሰራተኛ ነበር። ስለዚህ ከሥራ ሲሰናበት የአሰሪና ሰራተኛ አዋጁ በሚያዘው መሰረት ሁሉንም ጉዳይ ፈጽመን ሸኝተነዋል። ለዚህ ደግሞ ማስረጃ አለ። የህክምና ማስረጃው በእጃችን ላይ ይገኛል። ከዚህ ውጭ በሥራ ላይ ካሉትም ሰራተኞች ጋር በጥሩ ሁኔታ እየሰራን ነው›› ብለዋል።

አቶ ድሪባም ከስድስት ወር በፊት ደውሎ የሥራ ልምድ ጠይቆ ጽፈን ሰጥተነዋል። ጉዳት ደርሶበት የነበረው ከ2014 በፊት ነው። ስለዚህ ማንኛውም ሰራተኛ ጉዳት ሲደርስበት በህጉ መሰረት መጠየቅ መብቱ ነው። በማንኛውም ጫና ቢለይ እስከ 90 ቀናት ድረስ ወይም በሶስት ወር ጊዜ ውስጥ ለየትኛውም አካል አመልክቶ ካሳውን መቀበል ይችላል። አሁን ግን የመጠየቂያ ጊዜው አልፏል።

ከሥራ ከወጣ ከሶስትና አራት ዓመታት በላይ ሆኖታል። ተጎጂው መብቱን ለማስከበር በሚያደርገው ጥረት ውስጥ የመጠየቂያ ጊዜው አልፏል መባሉ በተጠና መንገድ መብቱን መጋፋት፤ ህግን መሰረት አድርጎ ከተጠያቂነት ለመሸሽ የሚደረግ አሰራር አይሆንም ወይ? የሚል ጥያቄ ያቀርብንላቸው ኃላፊው፤ ‹‹በፍጹም ይህን አናስብም። ማንም ሰው የዘራውን ያጭዳል፤ እኔም ተቀጣሪ ሰራተኛ ነኝ፤ በእሱ ላይ የማደርሰው ነገር በእኔ እና በቤተሰቦቼ ላይ ሊደርስ ይችላል። ስለዚህ ህግ እስከፈቀደ ድረስ መብቱን እንዲያጣ አልፈቅድም›› ሲሉ ምላሻቸውን ሰጥተዋል።

እሳቸው እንዳብራሩት፤ ሰራተኛው ተገፍቶ እና ጥቅም እንዳያገኝ በመደለል የወጣበት ሁኔታ ቢኖርም ይህን ያህል ዓመት ለምን ቆየ የሚል ጥያቄ ያስነሳል። ከመክፈል ባለፈ እንደ ህሊናም የጎደለበት ነገር ካለ የምንወቀስበት ጉዳት ነው። ስለዚህ የቀረበው ክስ ስህተት ነው። በተገቢው መልኩ ህጉ በሚፈቅደው መልኩ ሰራተኛውን ሸኝተነዋል። ለዚህ የሰነድ ማስረጃዎች አሉ። ህጉ በሚፈቅደው መንገድ አንዳችም ነገር የጎደለበት የለም።

ህግ በሚፈቀድለት አግባብ ከተሸኘ አንዱ በአሰሪና ሰራተኛ ጉዳይ አዋጁ ላይ ካሳ ዘላቂም ይሁን ጊዚያዊ ጉዳት እንደየጉዳቱ መጠኑ በመቶኛ ተሰልቶ ይከፈለዋል ይላልና ይህ ባልተደረገበት ሁኔታ ህግ በሚፈቅድለት መጠን ተስተናግዷል ማለት ከአዋጁ ጋር አይጣረስም? በሚል ለቀረበው ጥያቄም በሰጡት ምላሽ፤ ‹‹መብቱ ሲነካ ቅሬታ ማቅረብ ብቻ የለበትም፤ በህግ መጠየቅም ይችላል። ምክንያቱም የሚያስከፍለው ከነወለዱና ከእነቅጣቱ ነው። የጉዳት ካሳ የሚያስከፍል ጉዳት አልደረሰበትም። ይህ ደግሞ በህክምና ማስረጃ ይረጋገጣል›› ብለዋል።

የጉዳት ካሳ ለመጠየቅ የህክምና ቦርድን ቢጠይቅ ቦርዱ ሊጽፍ የሚችለው ድርጅቱ ካሳ ለመክፈል ያመቸኝ ዘንድ የጉዳት መጠኑ ተጠቅሶ መረጃ ይላክልኝ ብሎ ለቦርዱ ሲያቀርብ ብቻ ነው። ስለዚህ የጉዳት መጠኑ ተጠቅሶ እንዲጻፍለት ድርጅቱ ለምን አላደረገም? የህክምና ማስረጃ እንዲጻፍልኝ ብሎ ማመልከቻ አላስገባም።

የህክምና ማስረጃ ለማን ነው እምንጽፈው፤ ቦርዱን ማስረጃ እንዲጽፍ የምንጠይቅበት አግባብ የለም። ምክንያቱም በአካል መጉደል የምስክር ወረቀት የተሰጠው ነገር የለም። ካሳ ለመክፈል የህክምና ቦርድ ማስረጃ እንዲሰጥ ብሎ ደብዳቤ እንደሚጻፍ እስካሁን አሰራር መኖሩንም አላውቅም። ስለዚህ ላለፉት ዓመታት የጉዳት ካሳ ይከፈለኝ ብሎ አልመጣም።

ከደረጃ እድገት ጋር በተያያዘ የተነሳው ቅሬታም የትኛውም ድርጅት አንድ አይነትና ወጥ የሆነ አሰራር የለውም። እንደ የድርጅቱ የሥራ ባህሪ፤ የሥራው ሁኔታ፤ እንደየሰራተኛው አቅም፤ የሥራ ቦታና ክፍል ይወሰናል። ለምሳሌ ብየዳ ዲፓርትመንት ውስጥ ያለ ሰራተኛ የማሽን ክፍል ላይ ክፍት ቦታ ቢኖር ወይም የሥራ ዕድገት ቢወጣ፣ አንድ ሰው ለቆ ቢወጣ፣ ከብየዳ ከፍል ሊገባ አይችልም። ለምን ሥራውን ሊሰራ አይችልም።

ስለዚህ የእኛ ድርጅት አሰራር በየዲፓርትመንቱ በአግባቡ የሥራ መደብ አለው። የሁሉም ዲፓርትመንት መደብ ይለያያል። አንድ ዲፓርትመት የሚሰራ ሰራተኛ በክፍል ሥራ መደብ ሲለቀቅ የነበረበትን ሥራ መደብ ለቆ ወደ ሌላው መደብ የመዛወር ፍላጎት አለ። ስለዚህ ያለመደብ በፍላጎት የሚሰራበት አሰራር የለም። ሥራውን ችሎ ወደ ሚፈልገው መደብ ለመሸጋገር የሥራ ሂደቱን ማረጋገጥ አለበት። ስለዚህ በሰራተኛ መካከል ልዩነት ተደርጎ የሚሰራ ሥራ አይደለም። ነገር ግን እንደ የሥራ ክፍሉ እና ችሎታ ዕድል ይሰጣል።

አሰራሩን በግልጽ ለሰራተኛው ከማስገንዘብ ይልቅ ሰራተኛ የይገባኛል ጥያቄ በጠየቀ ቁጥር ከፈለክ መልቀቅ ትችላለህ ብሎ ምላሽ የሚሰጥበት ሁኔታ እንዳለ ቅሬታ አቅራቢው ያነሳሉና በዚህስ ላይ ምን መልስ ይላሉ? በሚል ለቀረበላቸው ጥያቄም፡ ‹‹እንደዚህ አይነት ምላሽ የሚሰጥ ኃላፊ የለም። ይህን መሰል ምላሽ የሚሰጥ የቅርብ አለቃ ካለ ስህተት ነው›› ሲሉ መልሰዋል።

ሰራተኞቹ እንደሚሉት አንድ ሰራተኛ በስምንት ሰዓት ውስጥ የሚሰራው ሥራ ቋሚ ደመወዙ እንደሆነ የአሰሪና ሰራተኛ ጉዳይ አዋጁ ይደነግጋል። ነገር ግን በስምንት ሰዓት ውስጥ ሰርተን የምናገኘው ደመወዝ የፔሮልና የፒስ ተብሎ ይከፈለናል። ስምንት ሰዓት እየሰራን ማበረታቻ ተብሎ በፒስ በምንሰራው ሥራ በወር መጨረሻ ላይ የምናገኘው ደመወዝ ቋሚ ደመወዝ ይሁንልን ስንል ብንጠይቅም ተቀባይነት እያጣን ነው ይላሉ›› ቢዚህስ ላይ ምን ይላሉ ብለን ጠይቀናቸው። እሳቸውም ‹‹ይህ ከፋይናንስ ጋር የተያያዘ ቢሆንም ፔሮል ላይ ሌላ፣ እኛ የሚከፈለን ሌላ የሚለው ፍጹም ስህተት ነው። ሰራተኛው ከሚፈርምበት ፔሮል ውጭ ለሰራተኛ ክፍያ አይፈጸምም›› ሲሉ ይገልጻሉ።

ከሥራ ቅጥር ጋር በተያያዘም ደመወዙ እያንዳንዱ ሰራተኛ አምኖበት የሚገባበት ነው። ስለዚህ መሰረታዊ ክፍያ (basic salary) ብዙ ድርጅቶች ይጠቀሙበታል። የተሻለም አሰራር የሚባለው ይህ ነው። የዚህ መነሻው ማንኛውም ሰራተኛ ድርጅቱ ውስጥ ሲገባ ብቃት ቢኖረውም መሰረታዊ የደመወዝ ክፍያ አለው ማለት ነው።

ለምሳሌ አምስት ሺ ብር ቢቀጠር እና ሰራተኛው የተሻለ ብቃት እያዳበረ ከመጣ ድርጅቱ አምራች ስለሆነ ሰራተኛው እንዳይጎዳ ተጨማሪ በተነሳሽነት የተሻለ ምርት እንዲያመርት የማበረታቻ ወይም የማትጊያ ከፍያ በተጨማሪነት ይከፍላል። ሰራተኛው የማትጊያ ከፍያ ለማግኘት በተሰጠው የሥራ ሰዓት ውስጥ እኔ ተጨማሪ ሥራ ለምን አልሰራም ብሎ ቢሰራ የማበረታቻ ክፍያ ተጨምሮ ወር መጨረሻ ላይ ይከፈለዋል። ይህም ፔሮል ይገባል፤ ከዚህም ጡረታና የመንግስት ታክስ ተቆርጦ የተጣራ ገንዘቡ ይከፈለዋል።

ሀሚድ ከድር እና ወንድሞቹ ጠቅላላ ብረታብረትና ሚዛን ማምረቻ ድርጅት ሕጉ በሚፈቅደው መንገድ ሰራተኛውን ማስተናገዱን ቢገልጽም፣ ማስረጃውን እንዲያቀርብ ቢጠየቅም ማቅረብ ግን አልቻለም።

ሞገስ ተስፋ

ዘመን ረቡዕ ታኅሣሥ 9 ቀን 2017 ዓ.ም

Recommended For You