ክፍል አንድ
የአሁኑ የኢትዮጵያ ብሔራዊ ቴአትር የቀድሞው ቀዳማዊ ኃይለ ሥላሴ ቴአትር ቤት በ1948 ዓ.ም ሕዳር 3 ቀን በቀዳማዊ ኃይለሥላሴ ተመርቆ ሥራውን የጀመረ አንጋፋ ቴአትር ቤት ነው። ከተመሰረተበት ጊዜ አንስቶ የኢትዮጵያ ሕዝብ ወግ እና ባሕል፤ የአኗኗር፤ የዕለት ተዕለት ክንውን፣ የማኅበረሰቡን ሐዘን፤ ማግኘትና ማጣት፣ ጭቆና እና ነፃነትን፤ ትውፊት እና አኗኗርን በጥበባዊ መንገድ ከሽኖና አዋዝቶ ከሕዝቡ ለሕዝቡ መልሶ ሲያደርስ የቆየ የጥበብ ቤት ነው።
ተቋሙ በርካታ የጥበብ ሰዎችን ማፍራት የቻለ ዛሬም አዳዲስ የቴአትር ትምህርትን የሚማሩ ሕጻናት እና ወጣቶች ብሔራዊ ቴአትር መግባትና መሥራት ሕልማቸው ነው። ይህ ሰባት አሥርት ዓመታትን ሊደፍን አንድ ዓመት ብቻ የቀረው ቴአትር ቤት ቀዳማዊ ኃይለሥላሴ ከነቤተሰቦቻቸው ቴአትር ይመለከቱበት እንደነበር የታሪክ ድርሳናት ያስረዳሉ።
የዛሬው የፍረዱኝ ዓምድ ዝግጅታችን ትኩረቱን ያደረገው በዚሁ ባለግርማ ሞገሱ የኢትዮጵያ ብሔራዊ ቴአትር ቤት ዋና ዳይሬክተር እና በሰራተኞች መካከል የተፈጠረን ውዝግብ ነው። ሰራተኞች ስንል ሁሉም ሰራተኞች እንዳልሆኑ ልብ ሊባል ይገባል። ስለሆነም ለሰራተኞች ደህንነት ሲባል ‹‹ቅሬታ አቅራቢዎች›› በሚል ይቀርባል።
በቴአትር ቤቱ ለረጅም ጊዜ የሰሩ፤ እየሰሩ ያሉ ሰራተኞችና አመራሮች ‹‹በዋና ዳይሬክተሩ የተበላሸ እና ከሕግ ያፈነገጠ አሰራር ባለግርማ ሞገሱ የኢትዮጵያ ብሔራዊ ቴአትር ቤት የተቋቋመለትን ዓላማ ስቷል፤ ረስቷልም። የቁልቁለት ጉዞውንም ከጀመረ ዓመታት ተቆጥረዋል። በቴአትር ቤቱ የተፈጠረውን እና እየተፈጠረ ያለውን ችግር ተመልክቶ የኢትዮጵያ ሕዝብ ይፍረደን›› ሲሉ ለኢትዮጵያ ፕሬስ ድርጅት አዲስ ዘመን ጋዜጣ የመልካም አስተዳደር እና ምርመራ ቡድን አቤት ብለዋል። ጋዜጣችንም የኢትዮጵያ ሕዝብ ግራ ቀኙን አይቶ መፍረድ ይችል ዘንድ ከሰዎች እና ከሰነዶች የተገኙ ማስረጃዎችን አደራጅቶ አቅርቧል።
የመልካም አስተዳደር እና ምርመራ ቡድኑም ከጉዳዩ ጋር በተገናኘ በርካታ የምርመራ ግኝቶችን ማግኘት ችሏል። ከጉዳዩ ጋር በተያያዙ የደረስንባቸውን የምርመራ ግኝቶችንም በተለያዩ ክፍሎች በጽሁፍ ለሕዝብ የምናቀርብ ይሆናል። በዛሬው እትም ላይ የምናስነብባችሁ ከቅሬታ አቅራቢዎች እና ከሰነዶች የተገኙ በድርጅቱ ውስጥ የታዩ የፋይናንስ ኦዲት ግኝቶችን እንዲሁም የግዥ መመሪያን ሳይከተሉ የተፈጸሙ ክፍያዎችን ነው።
ከተቋሙ የተገኙ የሰነድ እና የሰው ማስረጃዎች
አብዛኛዎቹ አቤቱታ አቅራቢዎች በሰነድ አስደግፈው ያቀረቧቸው ናቸው። የምርመራ ቡድኑ ከአቤቱታ አቅራቢዎች እና በምርመራ ካገኛቸው የሰነድ ማስረጃዎች ላይ ምንም ሳይጨምር እና ሳይቀነስ ማስረጃዎችን እንደወረደ ወደ ጽሁፍ ቀይሯቸዋል። ለአንባቢያን ግልጽ ይሆን ዘንድ የተገኙ ማስረጃዎችን በቁጥር ቅደም ተከተል ከተራ ቁጥር አንድ እስከ 27 ተቀም ጠዋል።
ባላፉት ስድስት የበጀት ዓመታቶች በቴአትር ቤቱ በተደራጀ የጥቅም ትስስር ከዚህ በታች ከተራ ቁጥር አንድ እስከ ስድስት በተቀመጡት ነጥቦች በድምሩ ብር 32,180,016.66 ከሕግ አግባብ ውጪ የሕዝብ እና መንግሥት ሀብት ስለመመዝበሩ፤ ከተራ ቁጥር ሰባት እስከ መጨረሻው ያሉት ነጥቦች ደግሞ በተቋሙ ያለውን አጠቃላይ የብልሹ አሰራር ሂደት የሚያሳዩ ናቸው።
- ከ2012 እስከ 2015 በጀት ዓመት በአዲስ አበባ ከተማ ለተከናወኑ ስልጠናዎች፣ ስብሰባዎች፣ ለዕቅድ አፈጻጸም ውይይቶች፣ ችግኝ ተከላዎች፣ በቢሮ ውስጥ ለተከናወኑ ሥራዎች በአዳማ ከተማ እንደተካሄደ በማስመሰል በአዳማ ከተማ በሚገኙ ሆቴሎች ስም የቁርስ፣ የምሳ፣ የእራት እና የአልጋ ክፍያዎች ከመመሪያ ውጪ 12,000,000.00 ተከፍሏል።
- ከቴአትር ቤቱ ወደ መስክ የሚያስወጣ ምንም ሥራ በሌለበት በ2016 ዓ.ም የበጀት ዓመት ብቻ ለቴአትር ቤቱ ከተፈቀደለት ውሎ አበል በጀት ጣሪያ በላይ ብር 4,854,098.00 ከሠራተኞች ከእውቅናቸው ውጪ ተከፍሎ ተገኝቷል። (በውስጥ የበጀት ዝውውሮች ድግግሞሽ የተሟላ)
የመስክ ሥራ ሳይኖር መስክ መወጣቱ ሳያንስ ለአንድ ቀን ጉዞ የአምስት ቀን፤ ለሁለት ቀን 10 ቀን የውሎ አበል ተከፍሏል። በተመሳሳይ ጊዜ በአዳማ ከተማ ለሚገኙ ሆቴሎች ‹‹በሪፍሬሽመንት›› ሽፋን ሰራተኞች ባልቆዩባቸው ቀናት ብዛት እንዲከፈል ተደርጓል።
- ከ2012 ዓ.ም እስከ 2016 ዓ.ም የበጀት ዓመት ለትውፊታዊ ትውን ጥበባት ጥናትና ስልጠና ክፍል የተመደበን የመንግሥትን እና የሕዝብ ሀብት ብር 11,147,770.00 ከተበጀተለት ዓላማ ውጪ ተጠቅሞ ያልተሰሩ ሥራዎችን እንደተሰሩ ተደርገው ለመንግስት ሪፖርት ቀርቧል።
- በ2015 እና በ2016 የበጀት ዓመታት ብቻ ‹‹ከትሬዠሪ›› እና ከውስጥ ገቢ የተገኘን በጀት ብር 3,322,104.63 በሙዚቃ ትርኢት ለተሳተፉ ባለሙያዎች በቃለ ጉባኤዎች በሚወሰኑ የክፍያ ጣሪያ መተመኛ ደብዳቤዎች ከሕግ አግባብ ውጪ ለግለሰቦች ክፍያ ተፈጽሟል።
በ2016 ዓ.ም በጀት ዓመት የተገኘው የውስጥ ገቢ እና ጥቅም ላይ የዋለው ብር 1,578,946.65 ሲሆን፣ የተፈቀደው የሙዚቃ ክፍል የውስጥ ገቢ ጣሪያ ብር 800,000.00 መሆኑ እየታወቀ በልዩነት የሚታየው ብር 778,946.65 ወደ መንግሥት ግምጃ ቤት ፈሰስ አለመደረጉ፣ በገቢ ሂሳብ ‹‹ሌጀር›› እንዳይመዘገብ ተደርጎ እና በአደራ የባንክ ሂሳብ ቁጥር ተቀምጦ ወጪ ተደርጓል።
ከግዥ ክፍል እውቅና ውጪ፣ የግዥ መመሪያ ተጥሶ፤ በማይመለከታቸው ሠራተኞች የግዥ ውል ተፈርሞ በብር 862,038.73 በየወጪ አይነቱ ከአንድ አቅራቢ የሙዚቃ ግጥም፤ ዜማ፣ ማቀናበር፣ ሚክሲንግ፣ ማስተሪንግ፤ የድምጽ መሳሪያዎች ኪራይ እና የሙዚቃ መሳሪያዎች ጥገና ክፍያ ተፈጽሟል።
በ2016 ዓ.ም በጀት ዓመት ብቻ ከፌዴራል መንግሥት ሠራተኞች አዋጅ፣ ከሲቪል ሰርቪስ ኮሚሽን እና ከሰው ሀብት ልማት አስተዳደር እውቅና ውጪ በተቀጠረ ቋሚ ሠራተኛ መደብ ላይ እና ጡረታ የወጡ ሠራተኞችን በኮንትራት ውል ቅጥር ፈጽሞ ብር 135,918.76 ለግለሰቦች ተከፍሏል።
- በ2015 ዓ.ም እና በ2016 ዓ.ም የበጀት ዓመታት ብቻ ቴአትር ቤቱ ልክ እንደ ግንባታ ተቋም ከተፈቀደለት የበጀት ጣሪያ በላይ ብር 250,840.00 ለጉልበት ሥራ ከፍሎ ተገኝቷል።
- በ2015 ዓ.ም እና በ2016 ዓ.ም የበጀት ዓመታት ብቻ በተቋሙ ለመስተንግዶ ከተፈቀደ የበጀት ጣሪያ መመሪያ በላይ በግለሰብ ተከራይቶ ለሚሠራው የፏዬ የሠራተኞች ክበብ ከፋይናንስ ውጪ ብር 605,806.03 ተከፍሏል።
- ያልተሰሩ የቴአትር፤ የሙዚቃ፤ የብሔር ብሔረሰቦች እና ሕዝቦች የትውፊት ጥናቶች የፈጠራ እና የመድረክ ሥራዎች እንደተሰሩ ተደርጎ የሃሰት ሪፖርት ለመንግሥት ቀርቧል።
- ዋና ዳይሬክተሩ ለመንግሥት ኃላፊነታቸው መስጠት የሚገባቸውን ጊዜ ሰጥተው በዕቅድ፣ በስትራቴጂ እና በጠንካራ ክትትል ከመንግሥት የተጣሉባቸውን ኃላፊነቶች እየተወጡ አይደለም።
- በቴአትር ቤቱ ሹመት ካገኙበት ዕለት አንስቶ ‹‹አልቃሽና ዘፋኝ›› የሚባለውን በየሳምንቱ እሁድ እሁድ የሚታይ እና በርካታ ተመልካች የነበረውን ቴአትር ጨምሮ ሌሎችንም በተመልካች እጥረት በሚል ሰበብ በደብዳቤ አንስተው እሮብ ምሽት ይታይ የነበረን ተመልካች አልባ የሆነ ‹‹እምዬ ብረቷ›› የሚባለውን የውርስ ትርጉም ቴአትራቸውን ለእሁድ አዛውረው ላለፉት 5 ዓመታት ተመልካች ሳይኖረው በመድረክ እንዲቆይ እና ከመንግስት በጀት የደራሲና የአዘጋጅ እንዲከፈሏቸው አድርገዋል።
- ያለበቂ ጥናት አራት የመንግሥት ተሽከርካሪዎችን እንዲወገዱ ሲወሰን ለውስጥ ኦዲት ጥቆማ በመቅረቡ ቻንሲና የሞተር ቁጥር በባለሙያ እንዲታይ ሲጠየቅ በቸልታ ታልፏል።
- አቶ ፋንታሁን ኬሬቦ ላለፉት 5 ዓመታት በአዲሱ መዋቅር የታጠፈው የትውፊታዊ ትውን ጥበባት ጥናትና ስልጠና ክፍልን የመሩ በዚህም ምክንያት ተገምግመው የሥራ ዲሲፕሊን እርምጃ ሊወሰድባቸው ሲገባ ከዋና ዳይሬክተሩ ጋር ባላቸው የጥቅም ትስስር የድልደላ ኮሚቴ ሰብሳቢ ተደርገው ከፍተኛ ገቢ ሰብሳቢ በሆነ ክፍል ውስጥ በዕድገት ተመድበዋል።
- በ2015 ዓ.ም እና በ2016 ዓ.ም በጀት ዓመታት ብቻ የሙዚቃ ዳይሬክተር ተወካይ ወይዘሪት ግራሴላ ሊዊጂ ከዋና ዳይሬክተሩ ጋር ባላቸው የጥቅም ትስስር የመንግሥት ገቢ ከመመሪያ ውጪ በአደራ ሂሳብ ተቀምጦ እንዲከፈል ማድረጋቸው፤ በአንጋፋ ባለሙያዎች እና በበርካታ ሠራተኞች ከፍተኛ ክስ እየቀረበባቸው በውክልና ክፍሉን ለሁለት ዓመታት እንዲመሩ መደረጉ እና በአዲሱ መዋቅር በዕድገት ተመድበዋል።
- ወ/ሮ ሙሉእመቤት ሀብታሙ በግዥና የፋይናንስ ዳይሬክቶሬት ሆነው ቢመደቡም በጥቅም ትስስር የተሰጣቸውን ኃላፊነት ገሸሽ በማድረግ ሀብት ምዝበራዎች ሲያሳልጡ የቆዩ በአዲሱ መዋቅር ሚስጥሮችን ለማፈን እና ለማዳፈን የውስጥ ኦዲት ሥራ አስፈጻሚ ሆነው በዕድገት እንዲመደቡ ተደርጓል።
- የሂሳብ ባለሙያዎቹ ወ/ሮ ታሪኳ ምትኩ እና ወይዘሪት ሕይወት በቀለ በክፍያዎች ውስጥ ሁሉ ስማቸው የማይጠፋ፤ ማጭበርበሮችን ሁሉ በመስማማት ሲያሳልጡ የቆዩ እና በአዲሱ መዋቅር በሂሳብ ባለሙያነት በዕድገት በነበሩበት ክፍል የተመደቡ ናቸው።
- የበጀት፣ ዕቅድ፣ የግዥ እና ፋይናንስ ኃላፊዎች የሚከፈሉ ያልተገቡ ክፍያዎችን ሲቃወሙ በመቆየታቸው ምክንያት ፈራሚዎች ብቻ ተደርገው ቆይተዋል።
- የአትዮጵያ ብሔራዊ ቴአትር የሠራተኞች መረዳጃ እድር መሪዎች በወጣው ደንብ መሰረት ለዋና ዳይሬክተሩ ተጠሪ ቢሆኑም በምርጫ በየሁለት ዓመቱ የማይተኩ፤ ከፏዬ የሠራተኞች ክበብ አዳራሽ እና ከግራሩ ቅጥር ጊቢ የሚያገኟቸውን ከብር 200,000.00 በላይ የቤት ኪራዮች በተመለከተ ሪፖርት የማያቀርቡ፣ የመንግስት ቤት ተከራይቶ ለምዝበራ የተመቻቸላቸው፤ በዋና ዳይሬክተሩ ክትትል የማይደረግባቸው እና በውስጥ ኦዲት እንዲታዩ ፈቃደኛ አይደሉም።
- የአዲሱ መዋቅር ትግበራ በ2014 በጀት ዓመት የተጀመረ ቢሆንም ከ2 ዓመታት በላይ በዋና ዳይሬክተሩ ትኩረት ማጣት፤ ለጥቅም ትስስር ኔትወርክ መጠናከር መንገድ ሲፈለግ ሆነ ተብሎ ዘግይቷል።
- በአዲሱ መዋቅር ድልደላ ለማሕደር ጥራት፣ ለትምህርት ዝግጅት እና ለመሳሰሉት 50%፤ ለብቃት ማረጋገጫ ፈተና 15% እና በመንግስት 7 መለኪያዎች ተቀምጠውላቸው 35% በዋና ዳይሬክተሩ የሚሞሉ ሲሆን አብረዋቸው የሕዝብ ሀብት ለመዘበሩ ከ31 እስከ 34 ነጥብ በመስጠት ለቀጣይ ምዝበራ ተቋሙን አደላድለዋል።
- ዋና ዳይሬክተሩ ስልጣናቸውን ተጠቅመው፤ የዩኒቨርሲቲውን ፈተና ውጤት ጠብቀው፣ በድልደላ ኮሚቴ የተሞላውን ውጤት ተቀብለው፣ ከሕግ አግባብ ውጪ በማስተያየት ይታገሏቸው ለነበሩ መካከለኛ ሥራ አመራሮች ሆን ብለው ከ35% ከ9 እስከ 17 የማይገባ ነጥብ በመስጠት ከማለፊያ ውጤት በታች እንዲያገኙ አድርገዋል። በዚህም ዳይሬክተርና ቡድን መሪ ሆነው ለረዥም ዓመታት መንግሥትን ያገለገሉ በርካታ አንጋፋ ባለሙያዎች ከደረጃቸው ዝቅ ብለው በባለሙያ መደብ እንዲመደቡ ተደርጓል።
- ተጠሪ በሆንበት ሚኒስቴር መስሪያ ቤት በኩል ወደ ቻይና ለሥራ የተጓዙ 1 ሰራተኛ ከሁለት ቀን በኋላ እንደሚመለሱ እየታወቀ የአዲሱ መዋቅር የብቃት ማረጋገጫ ፈተና እንዲያልፋቸው ተደርጓል።
- በትምህርት ማስረጃ ማጣራት ወቅት እርግጠኛ ግድፈት ያልተገኘባቸው 12 ሰራተኞችን ሆን ብሎ በግለሰቦች አስተያየት ከውድድር ውጪ ተደርገዋል።
- በአዲሱ መዋቅር የተፈፀመው ድልደላ በሲቪል ሰርቪስ ኮሚሽን እና በዋና መ/ቤታችን ሚኒስትሮች በወቅቱ እንዲታይ እና እንዲፀድቅ አልተላከም።
23 ለአዲሱ መዋቅር የበጀት ጭማሪ ገንዘብ ሚኒስቴር ቀደም ብሎ ተጠይቆ እንዲላክ ሳይደረግ፤ የሠሩትን ሥህተት ለመሸፈን ለሠራተኞች ደሞዝ እንዲተከል ደብዳቤ ለሰው ሁበት፣ ለፋይናንስ እና በጀት ክፍሎች መጻፉ እና ያልተገባ ግፊት ተደርጓል።
- ዋና ዳይሬክተሩ ከማኔጅመንት ቡድናቸው ጋር ተገቢ የውይይት መድረክ ባለፉት 6 ዓመታት ያልነበራቸው መሆኑ እና ስብሰባ ካደረጉም አሉባልታ ሰብስበው ለዛቻና ለማስፈራራት መድረኩን የሚጠቀሙበት ሆኗል።
- ባልተገቡ የዲሲፒሊን ክሶች የሴራ መረብ ዘርግቶ ጠያቂ ሠራተኞችን በክሶች አስመርረዋል።
- ዋና ዳይሬክተሩ በሥራ ቦታቸው የማይገኙ፣ በሹፌራቸው በኩል የሂሳብ ሰነዶች ጭምር ቤታቸው እየተላከላቸው የሚፈርሙ፣ በተለያዩ አደገኛ ሱሶች የተጠመዱ፣ ቂመኛ፣ በሥራ ቦታቸው ባልተገኙባቸው ጊዜያት ሁሉ ለፀሐፊያቸው ተጠሪ ወደ ሆኑበት ተቋም ሚኒስትሮች እና ወደ ሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት ለስብሰባዎች እንደሄዱ፣ አንዳንዴም ቀረጻ እና የመንግሥት አስቸኳይ ትዕዛዝ ከቢሮ እንዳጠፋቸው በመናገር በሥራ ቦታቸው የማይገኙ መሆናቸው።
- በ2016 በጀት ዓመት ብቻ ዋና ዳይሬክተሩ አቶ ማንያዘዋል እንደሻው የ181 ቀናት፤ አቶ ፋንታሁን ኬሬቦ የ185 ቀናት፤ ወ/ት ግራሴላ ሊዊጂ 167 ቀናት፣ አቶ ሙሉቀን ጌታቸው 174 ቀናት፣ ወ/ት ስንዱ በቀለ የ144 ቀናት፣ ወ/ሮ ሙሉእመቤት ሀብታሙ 123 ቀናት፤ ወ/ት ኩሪ አየለ 135 ቀናት፣ ወ/ሮ ታሪኳ ምትኩ 118 ቀናት፣ ወ/ት ሕይወት በቀለ 123 ቀናት፣ አቶ ባደግ አሰፋ 150 ቀናት የቀን ውሎ አበል በአዳማ ከተማ የሥራ ጉዳይ በሌለበት ገንዘብ አለአግባብ ወጪ ተደርጎ መከፈሉ የመንግሥትን ሀብት ያባከነ ነው።
ከ2012 ዓ.ም እስከ 2015 በጀት ዓመት ያለመመሪያ የተፈፀሙ በተቋሙ ሂሳብ ሰነዶች ውስጥ ቁልጭ ብለው የሚገኙ የአዳማ ከተማ የቀን ውሎ አበሎች፣ የሪፍሬሽመንት፣ የሆቴል፣ እና የትውፊታዊ ትውን ጥናቶች የወጪ ክፍያዎች በኦዲት ምርመራ ሊረጋገጡ የሚችሉ መሆናቸውን ገልጸው፤ በተመረጡ ሰነዶች ምርመራ በ2014 እና በ2015 በጀት ዓመቶች በዋና ኦዲተር እና በውስጥ ኦዲት ሪፖርቶች የቀረቡ ግኝቶችን መመልከት እንደሚቻል ያስረዳሉ።
በተጨማሪም አቤቱታ አቅራቢዎቹ፤ ‹‹በሂሳብ የወጪ ሰነዶች ቁጥር የወጪ ምክንያታቸውን እና የወጣውን ገንዘብ መጠን ጠቅሰው ባዘጋጇቸው የሂሳብ ሰነድ ቁጥሮች፤ ለማሳያነት የተካተቱ የሂሳብ ወጪ ሰነዶች ኮፒ፣ የበጀት ዘገባ ምዝገባዎች እና አንዳንድ የሂሳብ ወጪ ሰነዶችን አያይዘን ጥቆማችንን ለኢትዮጵያ ፕሬስ ድርጅት በዝርዝር አቅርበናል። በቡድን ተደራጅተው ከሕግ አግባብ ውጪ የመንግሥትን በጀት ላልተፈቀዱ ዓላማዎች በማዋል ምዝበራ የፈጸሙ እና የአሠራር ችግሮችን የፈጠሩ የሥራ ኃላፊዎችን እና ሠራተኞችን ዝርዝር ጭምር ያቀረብን ስለሆነ አስቸኳይ ማጣራት ተደርጎ ተቋሙን ከውድቀት እንድትታደጉት በአክብሮት እንጠይቃለን›› ሲሉ ቅሬታ አቅራቢዎች ለምርመራ ቡድኑ በጽሁፍ ጥቆማቸውን ሰጥተዋል።
በዚሁ መሰረት እንደ አቤቱታ አቅራቢዎቹ ገለጻ፤ ተቋሙ የውስጥ ገቢን መጠቀም የሚያስችል የጸደቀ መመሪያ ወይም ሰርኩላር በሌለበት በርካታ ክፍያዎች ተፈጽመዋል። ቴአትር ቤቱ ከተለያዩ ተቋማት ጋር ውል ፈጽሞ ገቢ ሲያገኝ ከሕግና ከመመሪያ ውጭ ክፍያዎች እንዲፈጸሙ ይደረጋሉ የሚሉት ጥቆማ ሰጭያችን፤ ከተገኘው ገቢ ውስጥ አብዛኛው ተመልሶ ወጭ እንዲደረግ እና ለመንግስት የሚቀር ገቢ እንዳይኖር እንደሚደረግ በማስረጃ በማስደገፍ ይናገራሉ።
ከውስጥ ምንጮች ባገኘነው የሰውና የሰነድ ማስረጃ፤ አቶ አገረሰላም ሻፊ የተባሉ ሰራተኛ በተቋሙ ውስጥ ሲቀጠሩ የሰው ሃብት አስተዳደር ማስታወቂያ አውጥቶ አልቀጠራቸውም። የተቀጠሩበት የሥራ መደብም የከበሮ ተጫዋች ነው። ነገር ግን ተቋሙ በቋሚነት የተቀጠረው የከበሮ ተጫዋች አለው። የሰው ሃብት ሳያውቃቸው መቀጠራቸው አግባብነት የሌለው ጉዳይ ሆኖ ሳለ በልምምድ ጊዜ የተፈጥሮም ሆነ የሰው ሰራሽ አደጋ ቢደርስ እኝህን ሰው መጠየቅም ሆነ የጉዳት ካሳ መክፈል እንደማይቻል ምንጫችን ያስረዳሉ።
እኝህ ሰው በምን አግባብ እንደተቀጠሩ እንደማያውቁ የሚናገሩት የመረጃ ምንጫችን አቶ አገረሰላም፤ በድርጅቱ ወጭ የፓስፖርት እድሳት ተደርጎላቸው ሕንድ ሀገር ድረስ በመሄድ የ17ቀን የውሎ አበል እና የክብር መጠበቂያ ክፍያ በዶላር እንደተከፈላቸው ሰነዶችን ዋቢ በማድረግ ለምርመራ ቡድኑ ገልጸዋል። በተለያዩ የመድረክ ክፍያዎችም እንዲሁ ክፍያ እንደተፈጸመላቸው ተመላክቷል።
ሰባ ዓመታትን ሊደፍን በጣት የሚቆጠር ቀናት የቀሩት የኢትዮጵያ ቤሔራዊ ቴአትር ቤት የራሱ የሆነ ሳውንድ ሲስተም የለውም የሚሉት ምንጫችን፤ ይህ ሳውንድ ሲስተም ተቋሙ መንግሥታዊ በመሆኑ እና ለድርጅቱ አስፈላጊ የሚባል በመሆኑ በቀላሉ ግዥ መፈጸም ሲችል አላግባብ የሳውንድ ሲስተም ክራይ በመፈጸም ተቋሙ ለከፍተኛ ወጭ እንደተዳረገም ይናገራሉ። ይህ ግዥ አለመፈጸሙ በድርጅቱ ውስጥ የጥቅም ትስስር እንዲፈጠር እና የሳውንድ ሲስተም አከራዮች ከመመሪያ ውጭ እንዲፈጸሙ ምክንያት ሆኗል ይላሉ።
ከዚህ ጋር በተያያዘም በሰው እና በሰነድ ባረጋገጥነው መረጃ መሰረት ቴአትር ቤቱ ለሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት መስከረም 30/2015 ዓ.ም ለተካሄደው የ6ተኛ የምክር ቤቱ ሁለተኛ ዓመት የሥራ ዘመን መክፈቻ ጉባኤ ለማቅረብ ዞዊ ባንድ እና ኢንተርቴመንት ለተሰኘ ተቋም ለሙዚቀኛ እና ለሳውንድ ሲስተም ኪራይ 70ሺ ብር ክፍያ በቀን 15/07/2015 ፈጽሞ እያለ በተመሳሳይ ለዚሁ ቀን በቃለጉባኤ ለሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት መስከረም 30/2015 ዓ.ም ለተካሄደው የ6ተኛ የምክር ቤት ሁለተኛ ዓመት የሥራ ዘመን መክፈቻ ፕሮግራም ላይ የሙዚቃ ባንድ አቅርቧል በሚል ለኢስት አፍሪካ ባንድ በድጋሚ 29/02/2016 የ90ሺ ብር ክፍያ እንዲከፈለው ተደርጓል።
ተቋሙ ከዞዊ ባንድ እና ኢንተርቴመንት ጋር ውል ከመፈጸሙ በፊት ምንም አይነት የጨረታም ሆነ የፕሮፎርማ ማሰባሰብ ሳይደረግ በቃለጉባኤ ብቻ እንዲመረጥ በማድረግ ክፍያ ተፈጽሞለታል። በተጨማሪም በአንድ መድረክ ተሳትፎ በተለያየ ጊዜ እና የገንዘብ መጠን ሁለት ጊዜ ክፍያ እንደተከፈለው እና ብሔራዊ ቴአትር ግን የራሱ አራት ሙሉ ባንድ እንዳለው ይናገራሉ።
በቃለጉባኤው ላይ የድምጽ ባለሙያውን አወዳድሮ ለመቅጠር የነበሩት ቀናቶች አጭር መሆናቸው ቢገለጽም፤ ይህ አይነቱ አካሄድ ለሙስና እና የመንግሥትን ገንዘብ ከመመሪያ ውጭ እንዲከፈል በማድረግ የመልካም አስተዳደር ጥያቄን እንደሚያስነሳ ምንጫችን ይናገራሉ።
በተመሳሳይ በዓለም ሥራ ድርጅት አስተባባሪነት በተዘጋጀው የ100ኛ ዓመት የአሰሪና ሰራተኛ ጉዳይ ኮንፍረንስ የመክፈቻ ፕሮግራም ላይ ለቀረበው የባሕል ሙዚቃ የሙዚቃ ባለሙያ አወዳድሮ ለማሰራት አጭር ቀናት ብቻ ስለነበሩት በሚል በኮሚቴ ተወስኖ ገቢ ከተደረገው 191ሺ 630 ብር ላይ 85ሺ ብር ለኢስት አፍሪካ ባንድ ክፍያ እንዲፈጸም ተደርጓል። በኮሚቴ እየተወሰነ ከጨረታ ውጭ የሚፈጸሙ ግዥዎች ለሙስና ክፍት መሆናቸውንም ባለሙያው ተናግረዋል።
በ2014 ዓ.ም የባሕልና ስፖርት ሚኒስቴር በምስራቅ አፍሪካ የባሕልና ጥበባት ፌስቲቫል ላይ ለቀረበው የሙዚቃ ትርኢት 200ሺ ብር ለቴአትር ቤቱ ሲከፈለው 141ሺ 906 ብር በተለያየ የብር መጠን ለ46 የድርጅቱ ሰራተኞች ገቢ ተደርጓል።
ጶጉሜ 15/2015 በተከበረው ኢትዮጵያ ከሸማችነት ወደ አምራችነት በሚል ጽንሰ ሃሳብ በለገጣፎ በተከበረው በዓል ላይ ለተሳተፉ ባለሙያዎች ክፍያ በቃለጉባኤ ተወስኖ እንዲከፈላቸው ተደርጓል። ቃለጉባኤው የሞያ የሥራ ድርሻ የገንዘብ ክፍያ መጠን በተለያየ ግዜ በውስጥ የክፍያ መመሪያ ደንብ እንደሚከፈል የሚታወቅ መሆኑን ጠቅሶ፤ የሀገሪቱን ተጨባጭ ሁኔታንና የኢኮኖሚ የመግዛት አቅም ያልተመጣጠነ በመሆኑ አዲስ የውስጥ የክፍያ መመሪያ እስከሚወሰን በእለቱ የተሳተፉ ባለሙያዎች እንደየሥራ ድርሻቸውና ሞያ ተሳትፎአቸው ክፍያ እንዲፈጸም በቃለ ጉባኤ ተወስኗል። በዚህም ለ31 ባለሙያዎች 104ሺ 320 ብር ተከፍሏቸዋል። እዚህ ላይ የሚነሳው ጥያቄ የመንግሥት ተቋም ከመመሪያ ውጭ (በሚመለከተው አካል ሕጋዊ አግባብን ተከትሎ የጸደቀ መመሪያ አይደለም) በኮሚቴ የተፈለገውን ያህል ገንዘብ ለባለሙያዎች ይከፈል ተብሎ በቃለጉባኤ የሚወሰንበት አካሄድ ተገቢ አይደለም የሚል ነው።
ለአንድ መድረክ ስንት ብር መከፈል እንዳለበት የተወሰነ መመሪያ ሳይኖር አቶ ኩስያ ጦሎንጌ እና አቶ ስዩም ማሞ ለተባሉ የቀድሞ የድርጅቱ ሰራተኞች እና ጡረተኞች በወጭ ማስመስከሪያ ቁጥር 0005423 ጥቅምት 26/2016 ዓ.ም በድምሩ 6136 ብር እንዲከፈላቸው ተደርጓል።
በድርጅቱ የሰው ሃብት ልማት አስተዳደር ክፍል ውስጥ ሲሰሩ የነበሩ አንድ ግለሰብ ለቡድናችን እንደገለጹት፤ ሰዎች የጡረታ ጊዜያቸው እንዲራዘም የሚደረገው በዚያ ሙያ ላይ የሰው ኃይል ማግኘት የማይቻል መሆኑ ሲረጋገጥ ብቻ መሆኑን ይናገራሉ። ይህም ሲደረግ ከስድስት ወራት በፊት ለሲቪል ሰርቪስ በማሳወቅ ከአምስት ዓመት ላልበለጠ ጊዜ እንዲራዘም ማድረግ ይቻላል።
ብሔራዊ ቴአትር ግን የጡረታ ገንዘብ እየተከፈላቸው መደቡ ላይ ደግሞ እንዲሰሩ ተደርጓል። በኋላም በተደጋጋሚ በቀረቡ አቤቱታዎች በመድረክ ኮንትራት ውል ክፍያቸው እንዲቀጥል ተደርጓል። በተጨማሪም ለመድረክ ክፍያ የተወሰነ የክፍያ ጣሪያ ሳይኖር ክፍያዎች እየተፈጸሙላቸው ይገኛል።
የመረጃ ምንጮቻችን በሰነድ አስደግፈው እንደገለጹት፤ በተለያየ ጊዜ ዋና ዳይሬክተሩን ጨምሮ ሌሎች አመራሮች ለተወዛዋዥ እና ለሙዚቃ ባለሙያዎች የሚከፈል የላብ መተኪያ የጽዳትና የትራንስፖርት ክፍያ ላይ ስማቸው ተካቶ እንዲከፈላቸው ተደርጓል።
ከላይ ከተነሱት ጉዳዮች ጋር በተያያዘ የምርመራ ቡድኑ የሲቪል ሰርቪስ ኮሚሽን የኢንስፔክሽን መሪ ሥራ አስፈጻሚ የሆኑትን ዶ/ር ዋቅጋሪ ጃለታ እና ከዋና ኦዲተር መስሪያ ቤት ያገኘናቸውን የኦዲት ግኝቶች በቀጣይ ይዘንላችሁ የምንቀርብ ይሆናል።
ቡድኑ የቴአትር ሰራተኞች ካነሷቸው ችግሮች ጋር በተያያዘ የብሔራዊ ቴአትር ዋና ዳይሬክተር አቶ ማንያዘዋል እንደሻው ማብራሪያ እዲሰጡን በቀን 24/03/2017 በደብዳቤ ቁጥር TL1/2/4734 ብንጠይቀም ምላሽ ማግኘት አልቻልንም። ዳይሬክተሩን በእጅ ስልካቸው በተነሱት አቤቱታዎች ላይ ምላሽ እንዲሰጡን ብንጠይቅም ‹‹ግዜ የለኝም… ከፍርድ ቤት ውጭ ለባለጉዳይ ምላሽ አልሰጥም›› በማለታቸው የዳይሬክተሩን ምላሽ ማካተት አልተቻለም። ዳይሬክተሩ ፈቃደኛ ከሆኑ አስተያየታቸውን ይዘን የምንቀርብ ይሆናል።
መክሊት ወንድወሰን እና ሞገስ ተስፋ
አዲስ ዘመን ረቡዕ ታኅሣሥ 23 ቀን 2017 ዓ.ም