‹‹ሌብነት በጣም አታካች ነገር ሆኗል። በተለይ የገጠመንን አገራዊ ፈተና እና ችግር እንደ ዕድል የወሰዱ ሰዎች ቀይ መስመር ያልነውን ሌብነት ቀይ ምንጣፍ አድርገውታል። ቀይ ምንጣፍ አድርገው በነፃነት የሚንሸራሸሩበት ሰዎች እየተፈጠሩ ሄደዋል›› ሲሉ ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አህመድ ሰሞኑን ለህዝብ እንደራሴዎች በሰጡት ማብራሪያ ላይ ተናግረዋል።
‹‹አዲስ አበባ ውስጥ ኢትዮጵያ ውስጥ ፋይል በእግሩ አይሄድም የሚለው ቋንቋ የተለመደ ቋንቋ ነው። ፋይል በእጅ ብቻ ነው የሚሄደው በእግሩ አይሄድም። ሌብነት ልምምዱ ብቻ ሳይሆን እንደ መብት መወሰዱ አደገኛ ነገር ነው። ሌብነት የኢኮኖሚ ነቀዝ ነው፣ የዕድገት ነቀርሳ ነው። ሌብነት ባለበት ማደግም መኖርም አስቸጋሪ ነው። ምክንያቱም ሌቦች መስረቃቸው ብቻ አይደለም፤ ከሰረቁ በኋላ ገንዘቡ ባንክ አይሄድም። ባንክ ከሄዱ መስረቃቸው ይታወቃል።
ከሰረቁ በኋላ በትክክለኛው ሆቴል ሄደው በትክክለኛው ዋጋ በትክክለኛ ክፍያ መብላት መጠጣት መልበስ ይቸገራሉ፤ ሁሉ ነገር ድብብቆሽ ስለሆነ። ድብብቆሽ ደግሞ ወደ ህገወጥ ቢዝነስ ስለሚወስደው አንዴ የተሰረቀ ገንዘብ ወደህጋዊ ለመምጣት ይቸገራሉ›› ሲሉ ነበር የሙስናውን የክፋት ደረጃ ያብራሩት።
በተጨማሪም አገራዊ ኮሚቴ አቋቁመን ጥናት እያጠናን እንገኛለን። የተከበረው ምክር ቤት፣ መላው የኢትዮጵያ ህዝብ ለዚህ ዓላማ ብቻ የተዘጋጁ ስልኮች አሉ፤ ቢሮዎች አሉ፤ መረጃ ሰነድ በማቀበል ቢያንስ ባናጠፋ እንኳን ሌብነትን አንገት እንድናስደፋ በጋራ እንስራ። መጠየቅ ብቻ ሳይሆን በጋራ ቆመን ተረባርበን ትንሽ አንገት ለማስደፋት ጥረት እናድርግ ሲሉም ጥሪ ማቅረባቸው ይታወሳል። ይህን የጠቅላይ ሚኒስትሩን ሐሳብ በተመለከተ የህግ ባለሙያዎች ሙያዊ ትንታኔ ይሰጣሉ።
የህግ ባለሙያው አቶ በፍርዴ ጥላሁን እንደሚያብራሩት፤ በአሁኑ ወቅት በአገራችን ሥር የሰደደ ችግር በመኖሩ ምንም ዓይነት አገልግሎት ያለ እጅ መንሻ አይከናወንም። በአገልግሎት ደረጃ ህዝባዊ አገልግሎት የሚባሉትም ከቀበሌ እስከ ሚኒስቴር ድረስ አብዛኛው ያለ ሙስና መገልገል ከባድ ሆኗል። ከሁሉም የከፋው ደግሞ የመሬት ጉዳይ ሲሆን፤ ማዘጋጃ ቤቶች አካባቢ አንድ ሰው ኢትዮጵያዊ ሆኖ በዜግነቱ እንደ መብት ብቻ በማሰብ መገልገል አይችልም። በብዛት አገልግሎት በገንዘብ እየተሸጠ ነው። ይህም ህገ ወጦች በህግ ሽፋን ህጋዊ እስከ መሆን ድረስ መዝለቃቸውን ያስገነዝባል። ይህም የተስፋፋው መሰል ግለሰቦችና ቡድኖች በህግ ቁጥጥር ስር ውለው የህግ የበላይነት በእነርሱ ላይ ባለመተግበሩ የተነሳ ነው ይላሉ።
ከመንግስት ካዝና ደመወዙን ብቻ ተቀብሎ የሚያገለግል ባለሙያ እና አመራር እየጠፋ ነው። በስርቆት ሃብት ያካበቱት ደግሞ ሌሎችን እየጠመዘዙ ወደጥፋት መስመራቸው እያስገቡና እንደአገር ወደ ነቀዘ አሰራር እየነጎዱ ነው ሲሉ የህግ ባለሙያው ያብራራሉ።
በሌላ በኩል ደግሞ አገሪቱ ያላትን ሃብት በአግባቡና በሚዛኑ እንዳንጠቀም ሙስና ከፍተኛ ችግር መፍጠሩን የሚናገሩት አቶ በፍርዴ፤ ሃብት በጥቂት ግለሰቦች እና ባለሃብቶች እጅ ገብቷል። ይህም የሚፈልጉትን ቡድንና ሰንሠለት መስርተው ከባለሙያ፣ ባለስልጣን፣ ደላሎች፣ ባለሃብቶች ብሎም በየደረጃው ያሉ ተባባሪ አመራሮች ጋር በጋራ የሚዘውሩት አደገኛ አካሄድ እንዲፈጠር ዕድል እየሰጠ ነው።
በአሁኑ ወቅት በአገሪቱ የሚስተዋለው በሁለት የተከፈለ ቡድን ነው የሚሉት የሕግ ባለሙያው፤ በራሱ ቡድን ተደራጅቶና አደራጅቶ በሙስና መረብ መንግስት ለመሆን የሚውተረተር አካል መኖሩንና በሌላ በኩል ደግሞ የመንግስትነትን ህልውና ለማስቀጠል ከፍተኛ ጥረት እያደረገ ያለ አካል ነው ይላሉ።
ከእነዚህ ሐሳቦች በመነሳትም መደምደም የሚቻለው ጠቅላይ ሚኒስትሩ በህዝብ እንደራሴዎች የመሰብሰቢያ አዳራሽ ተገኝተው የሰጡት ማብራሪያ፤ ከእውነታው ቢያንስ እንጂ እንደማይበዛ ይጠቁማሉ። ከዚህም በተጨማሪ ሙስናን ለመዋጋት የተዋቀሩት የጸረሙስና ብሄራዊ ኮሚቴዎችም አስፈላጊነትን ያብራራሉ።
እንደ ባለሙያው ማብራሪያ፤ ሙስና እየፈጠረ ያለውን አገራዊ ቀውስ ለመመከት በጠቅላይ ሚኒስትሩ የተዋቀረው ቡድን በጣም የሚደነቅ ሲሆን ውጤታማ የሚሆንባቸው በርካታ ዕድሎችም መኖራቸውን ያብራራሉ። ሆኖም የእነዚህ ኮሚቴዎች ጥረት ገቢራዊ እንዲሆን ህዝባዊ ተሳትፎ መኖር አለበት ባይ ናቸው። ይህ ጥረት ከታከለበት ሙስና ሙሉ ለሙሉ ባይጠፋም እንኳን መቀነስ ይቻላል።
በአሁኑ ወቅት ሙስና ብሄራዊ አደጋ አድርጎ መውሰድ ካልተቻለ እና በተወሰኑ ኮሜቴዎች ላይ ብቻ ከተጣለ ሁነኛ መፍትሄ አይገኝም፤ ሙስና ኢትዮጵያን ክፉኛ የሚፈትን ጉዳይ ይሆናል። በአሁኑ ወቅት ህዝቡ በትልቅ ምሬት ውስጥ ያለ መሆኑን ግምት ውስጥ ማስገባትና ይህንንም ለመመከት የሚቻለው በነቃ ህዝባዊ ተሳትፎ መሆኑንም ማረጋገጥ ይገባል። በሌላ ገጽ መንግስት ካልተጠናከረ የህዝብ ጥረት ብቻውን ዋጋ የለውም።
የዚህ ኮሚቴ መቋቋምም ፖለቲካዊ ትርጉም ያለው ሲሆን፤ ህዝብ በሙስና በእጅጉ የተማረረ ስለመሆኑ ያሳያል። መንግስት ይህንን ሙስና አሰራር ካልቀነሰ በህዝብ ዘንድም አመኔታ የሚያጣ ይሆናል። ስለሆነም ይህን ማድረግ ደግሞ የማንኛውም ህጋዊ መንግስት ግዴታ ሲሆን፤ ህዝብም ከመንግስት ማስተማማኛ ይፈልጋል ብለዋል።
እንደ ህግ ባለሙያው ከሆነ፤ መንግስት ሙስናን ለመዋጋት የጀመረውን ጥረት ቢደነቅም በተወሰኑ ጉዳዮች ላይ ግን ጥንቃቄ ማድረግ ይገባል። የተቋቋመው ኮሚቴ አባላት የመንግስት የሥራ ኃላፊዎች ላይ ያተኮረ ነው። በክልል ደረጃም ይህ የሚቀጥል ይሆናል። ምንም እንኳን እነዚህን ሰዎች ሙሉ በሙሉ ሥራውን ብቻቸውን ያከናውናሉ ባይባልም ሁኔታዎች ጥያቄ ውስጥ የሚገቡበት ዕድል እንዳይኖርም ጥንቃቄ ማድረግ ይገባል የሚል እምነት አላቸው። በሌላ ጎኑ ደግሞ በተለይም ከፍተኛ ሃብት ያካባቱ ግለሰቦችና አካላት በገንዘብ ኃይል የእነዚህን ኮሚቴዎች ሥራ የሚያሰናክሉበትና እክል መፍጠር የሚችሉበት ዕድል ቢፈጠርስ ብሎ ማሰብ ተገቢ ነው።
ሌላው አስተያያታቸውን የሰጡን በዋቻሞ ዩኒቨርሲቲ የህግ መምህር እና ጠበቃ አቶ ፀጋዬ ደመቀ ናቸው። እርሳቸው እንዳሉት፤ ጠቅላይ ሚኒስትሩ በህዝብ እንደራሴዎች ፊት ቀርበው ሙስና በአገሪቱ የደረሰበትን ደረጃ የገለፁበት መንገድ ጉዳዩ አሳሳቢ ስለመሆኑ በግልፅ ያመላከተ ነው።
ሙስና በመናገር አይሆንም፤ በዚህም አይጠፋም። ችግሩን ለማቃለል የመንግስት አወቃቀር በደንብና በህግ የተደራጀ መሆን አለበት። ባደጉት አገራት ለሁሉም ነገር ሥርዓት የተዘረጋ ነው። ደካማ መሪዎች ወደ መሪነት ቢመጡ እንኳን ስርዓት ስለተዘረጋ መምራት አይከብዳቸውም። እኛ አገር ደግሞ ሁኔታዎች የተመሰረቱት በህግና ደንብ ከመሆን ይልቅ በግለሰቦች ላይ የተንጠለጠሉ ናቸው።
በአሁኑ ወቅት በመሬት፣ ትራንስፖርት እና መሰል አገልግሎቶች አካባቢ ዜጎች የሚፈልጉትን አገልግሎት ለማግኘት ያለሙስና ማሰብ ይከብዳል ሲሉ የአቶ በፍርዴን ሃሳብ ይጋራሉ። ጠቅላይ ሚኒስትሩም የተናገሩት ከቀይ መስመር አልፎ ወደ ቀይ ምንጣፍ መቀየሩ እርግጥ ነው። ይህ የሆነው ግን ለሙሰኞች ጥሩ መደላድል በመኖሩ ነው ባይ ናቸው። ጥፋተኛ ተብለው የተለዩት ላይ የሚተላለፈው ብያኔ ቀላልና ብዙም አስተማሪ ባለመሆኑ ሌሎችን ከጥፋት መታደግ አልቻለም። በተጨማሪም ፖሊስ፣ አቃብያነ ህግ፣ ፍርድ ቤቶች አሰራሮችም በውሉ የተናበበ ስለመሆናቸው ያጠራጥራል።
እነዚህ አካላትም ጠበቅ ያለ መረጃና ማስረጃዎች በማቅረብ ጥፋተኞች ላይ አስተማሪ እርምጃዎች ባለመውሰዳቸው አደገኛ ሁኔታ እየተከሰተ ነው። በዚህ አገር ያለው የሙስና አካሄድ ጠቅላይ ሚኒስትሩ ከተናገሩት በላይ እጅግ የገዘፈ ነው። የመንግስት ሹመኞች ወደ ስልጣን የሚመጡበት መንገድም ሌላኛው ሙስና በመሆኑ ጠቅላይ ሚኒስትሩ የገለጹት እንደተጠበቀ ሆኖ ይህንን መሰል ጉዳዮችን መፈተሽ ተገቢ ነው።
ጠቅላይ ሚኒስትሩ በማብራሪያቸው እንደገለፁት፤ ሙስናን ለመዋጋት ሲባል የተቋቋመው ኮሚቴ ክፋት ባይኖረውም ሙስና የአገር ጸር በመሆኑ የግማሽ እና የክፍለ ዘመን እሳቤ ያነገበ ተቋም እንጂ በተወሰኑ ግለሰቦች ጥረት እና ትጋት ላይ የተመሠረተ መሆን የለበትም። ይልቁንም ይህንን ችግር ለማስቀረት ሲባል የተቋቋሙ መሥሪያቤቶችን መፈተሽና ማጠናከር ይገባል።
መሰል ችግሮችም አዋጆችን፣ መመሪያዎችና ደንቦችን በመፈተሽና አሰራርን በማጠናከር እንጂ በኮሚቴ ብቻ አይስተካከልም። ሙስና የሚፈጸመው በረቀቀ መንገድ በመሆኑ ተቋማትን በዚህ መንገድ መቅረጽና ማበረታታት ተገቢ ይሆናል። የዚህ ኮሚቴ መቋቋም የፌደራል የሥነ- ምግባር እና ፀረ-ሙስና ኮሚሽን ሥራ እና የአንዳንድ ተቋማትን ተልዕኮ የመጋፋት ዕድል ይኖረዋል ይላሉ። ይሁንና ግን በአንድም ይሁን በሌላ ሙሰኞችን ለመቅጣት የተሰነዱ ሰነዶችን በመፈተሽ መሻሻል ያለባቸውን በማሻሻል እና በሙስና ላይ የተጀመረውን ዘመቻ ማጠናከር ለነገ የማይባል ጉዳይ ነው የሚለው የአቶ ፀጋዬ አቋም ነው።
በተመሳሳይ አቶ በፍርዴም ሙስና የኢትዮጵያን ዕድገት በእጅጉ የሚያቀጭጭ መሆኑን በጽኑ ይስማማሉ። ይህም በመሆኑ አገሪቱ ቀደም ሲል የነበሩትንና በአሁኑ ወቅትም የምትጠቀማቸውን የፍትሃብሄር እና የወንጀል ህጎችን በመፈተሽ በሙስና ውስጥ የተዘፈቁ አካላት የሚቀጡበትን አርጬሜ ከለዘብተኝነት ወደ መረረ አቅጣጫ መቀየር አለበት ባይ ናቸው። ዳሩ ግን የኮሚቴው መቋቋም የፌደራል የሥነ-ምግባር እና ፀረ-ሙስና ኮሚሽን ሥራ ወይንም ተልዕኮ የመጋፋት ዕድል ይኖረዋል የሚለውን የአቶ ፀጋዬን ሐሳብ ግን አይቀበሉትም።
ይህ ኮሚቴ በዋናነት ጉዳዩን የሚመራ እንጂ በእያንዳንዱ ጉዳይ ጣልቃ አይገባም። ሆኖም ግን የሚመለከታቸውን አካላት በማስተሳሰርና በማስተባበር ወደ ተሻለ ደረጃ የሚወስድ ይሆናል። በአገሪቱ አሰራርና በተቋማት አደረጃጃት መሠረት የተቋቋመው የፌደራል የሥነ-ምግባር እና ፀረ-ሙስና ኮሚሽን አሰራርንም ህገ መንግስታዊና የራሱ ተልዕኮ ያለው በመሆኑ አንዱ ከአንዱ እንዳይጣረስ ማድረግ የሚቻልበት ዕድል መኖሩንም ያብራራሉ።
ኢትዮጵያ ብሔራዊ የፀረ ሙስና ኮሚቴ አባላትም ተልዕኮ አሁናዊ የአገሪቱን ችግር ከማቃለል አንፃር በማሰብ የተወሰደ አፋጣኝ ምላሽ እንጂ የተቋማትን ሁለንተናዊ መብት መጋፋት እንዳልሆነም ማሳወቅ ይገባል ባይ ናቸው። ጉዳዩ በሕዝብ እንደራሴዎች ዘንድ ይሁንታ የተደገፈ በመሆኑም ኮሚቴዎቹ በህጋዊ መንገድ ቅቡል ያደርጋቸዋል የሚል አመክንዮ አላቸው። ዳሩ ግን በአሰራር ላይ ክፍተቶች የሚከሰቱ ከሆነም የሚስተካከሉበት ዕድል ስለመኖሩም ያብራራሉ። ከምንም በላይ ግን እነዚህ አካላት ውጤታማ የሚሆኑበትን ዕድል ለመፍጠር ሁለንተናዊ ንቅናቄና የበርካታ ተቋማትን ርብርብ የሚፈልግ ስለመሆኑ ያስገነዝባሉ።
ሁለቱም ምሁራን እንደሚስማሙበትም ሙስና በአገሪቱ አስጊ ደረጃ ላይ ደርሷለ። ይሄንን ችግር ለመከላከልም ከተቋቋመው የብሄራዊ የጸረሙስና ኮሚቴ በተጨማሪ ቀደም ሲል ያሉ ተቋማትን መፈተሽ፣ ህግና መመሪያዎችን መከለስ እንዲሁም በአጥፊዎች ላይ አስተማሪ ቅጣት መበየን ወሳኝነት አለው የሚል ነው።
ክፍለዮሐንስ አንበርብር
አዲስ ዘመን ኅዳር 20/ 2015 ዓ.ም