ቀይ መስመር (redline) …! ? በተምሳሌታዊ መሰመርነት፣ ጥቅም ላይ መዋል የጀመረው፤ እኤአ ከ1952 ጀምሮ መሆኑን አንዳንድ የታሪክ ድርሳናት ያትታሉ። ቀይ መስመር ለሚመከሩ (recommend) ለሚደረጉ የስኬት፣ የጥንቃቄ፤ ገደቦች፣ ወሰኖችና ጣራዎች እንዳይጣሱ አበክሮ ማስጠንቀቅን፣ ማሳሰብን ያመለክታል።
የመጀመሪያው ፍጥነት፣ እርቀት፣ ከፍታ፣ ጥራት ወዘተ. ላይ የሚመክርን፣ የሚጠበቅን፣ የሚጣልን፤ ገደብ፣ ጣራ፣ ወሰን ይወክላል። ይሄኛው ቀይ መስመር ክቡር ጠ/ሚ ዐቢይ አሕመድ የመጀመሪያ ካቢኒያቸውን ለሕዝቡ ይፋ ባደረጉበት ወቅት ሐምሌ መግቢያ አካባቢ 2010 ዓ.ም በፓርላማው ፊት ያሰመሩት አይነት መሆኑ ነው። ክቡር ጠ/ሚ ከአራት ዓመት በፊት ለአዳዲሶቹም ሆነ ለነባሮች የካቢኔ አባላት የአገልግሎት አሰጣጥንና ሙስናን በቀይ መስመር አስምረው ነበር። መንግስታቸው በአገልግሎት አሰጣጥ ላይ የሚስተዋሉ ብልሹ አሰራሮችንም ሆነ ሙስናን እንደማይታገሱ ያስጠነቀቁበት አጋጣሚ ነበር።
ከአራት ዓመታት በኋላ በአገልግሎት አሰጣጡ የነበሩ ችግሮችም ሆኑ ሙስናው ተባብሶ ቀጥሏል። ቀዩ መስመር መሬት ላይ የሌለ የሀሳብ መስመር ስለነበር ወይም አሸዋ ላይ የተሰመረውን ቀይ መስመር፤ ሙሰኞች ንፋስ ሆነው ጠርገው አጥፍተው ቀይ ምንጣፍ አድርገውታል። እዚህ ላይ ልብ መባል ያለበት ጉዳይ እዚህ ደረጃ ላይ የደረስነው በአንድ ጀምበር አይደለም። ቢያንስ ላለፉት 50 ዓመታት የመጣንበት ፖለቲካዊ፣ ኢኮኖሚያዊና ማህበራዊ ቀውስ ከፍተኛ ድርሻ አለው። ለዚህ ቀውስ ደግሞ እንደ ዜጋ፣ መንግስት፣ የሀይማኖት፣ የትምህርት፣ ወዘተረፈ ተቋማት በየድርሻችን ተጠያቂነት አለብን። ማናችንም ለዚህ ቀውስ ተጠያቂ ነው ብለን በማንም ላይ ጣት የመቀሰር የቅስም ልዕልና የለንም። የሁላችንም ድርሻ ስላለበት። ከዚህ ቀውስ መውጣት የምንችለው እንደ ዜጋ ኃላፊነታችንን በአግባቡ ስንወጣ ብቻ ነው። ወደ ነገረ “ቀይ መስመር” ስመለስ፤
ሁለተኛውና እኤአ ከ1968 ወዲህ ጥቅም ላይ እየዋለ ያለው ቀይ መስመር ደግሞ የዜጎችን የኢኮኖሚ አቅም ላይ ተመስርቶ የኢንሹራስና የሪል እስቴት ኩባንያዎች የሚፈፅሙትን አድልዎና ማግለል የሚያሳይ ነው። እዚህ ላይ አፍሪካን አሜሪካንን ያስታውሷል። ወደ አገራችን ስንመጣ ደግሞ ጎሳንና ሀይማኖትን መሠረት አድርገው የሚስተዋሉ የአገልግሎት አሰጣጥ አድሉዎችን ማንሳት ይቻላል። ይሁንና ዲፕሎማሲያዊው፣ ፖለቲካዊው ቀይ መስመር ደመቅ ብሎ መሰመር የጀመረው እንደተባበሩት መንግስታት አይነት ተቋማት ብቅ በቅ ማለት ከጀመሩ ወዲህ ነው። በተለይ ካለፋት 11 ዓመታት ወዲህ የሶሪያን የእርስበርስ ዕልቂት ተከትሎ ቀይ መስመሩ አቧራው ተራግፎ ከመደርደሪያው ወረደ ።
የፕሬዚዳንት ባሻር አላሳድ አገዛዝ አሸባሪዎች በሚላቸው ተፋላሚዎቹና ንፁሀን ላይ የኬሚካል ጦር መሳሪያ በመጠቀም መጠርጠሩን ተከትሎ አለማቀፉ ማህበረሰብ፤ ምዕራባውያንና ዩናይትድ ስቴትስ ቀይ መስመር ይጣስና (የኬሚካል ጦር መሳሪያ ትጠቀምና …! “) ፤ ወዮ ልህ …! እያሉ አላሳድን በየፊናቸው ማንገራገር ያዙ፤ በተለይ የያኔው የአሜሪካ ፕሬዚዳንት ኦባማ ቀይ መስመሩ ከተጣሰ ዋ… ! ? እያሉ ያዙኝ ልቀቁኝ ሲሉ ቢባጁም አላሳድ በንፁሀን ላይ የኬሚካል ጦር መሳሪያ መጠቀሙ፤ ቀዩን መስመር መጣሱ ቢረጋገጥም ሴኔቱ እርምጃ እንዲወስድ የሚያስችለኝን ድጋፍ ስለነፈገኝ ምንም ማድረግ አልቻልኩም ብለው አረፉት ።
ይሁንና ፕሬዚዳንታዊ ስልጣናቸውን ተጠቅመው በአላሳድ ላይ እርምጃ ባለመውሰዳቸው ዛሬ ድረስ በሪፐብሊካኖችና በሰባዊ መብት ተሟጋቾች ይብጠለጠላሉ። ትራምፕም የሶሪያ ነገር በተወሳ ቁጥር ኦባማ በጊዜው ባሰመረው ቀይ መስመር መሰረት እርምጃ ባለመውሰዱ ነው ለዚህ ቀውስ የተዳረግነው እያሉ በየመድረኩ ይወርፉታል። አሜሪካ፣ የአውሮፓ ሕብረትና ኔቶ ደግሞ ራሽያ የዩክሬንን መውረር ተከትለው አጎራባች ከሆኑ የኔቶ አባል አገራት በአንዱ ላይ ራሽያ ጥቃት ብትፈጽም፤ በመላው ኔቶ አገራት ላይ እንደተፈጸመ ይቆጠራል የሚልና ራሽያ የኒውክሌር የጦር መሳሪያ ብትጠቀም የከፋ የአጸፋ ምላሽ ይጠብቃታል የሚሉ ቀያይ መስመሮች ተሰምረዋል። ወደ ተነሳሁበት ነጥብ ስመለስ፤ የክቡር ጠ/ሚኒስትሩ ቀይ መስመርም በበርካታ ውስጣዊና ውጫዊ ምክንያቶች የተነሳ እንደ ፕሬዚዳንት ኦባማ የሀሳብ መስመር ብቻ ሆኖ በመቅረቱ ወደ ቀይ ምንጣፍነት ሊያድግ ችሏል።
ሌብነትም ሆነ ሙስና በእነዚህ አራት ዓመታት የተፈጠረ ሳይሆን ለቀደሙት 27 ዓመታት ተቋማዊና መዋቅራዊ ሆኖ ሲሰራበት የኖረ ነው። ሙስና ገንግኗል። በቀላሉ የሚያስወግዱት ችግር ከመሆን ተሻግሯል። እንደ ክፉ ደዌ ያልተጋባበት ዘርፍ የለም። በከተማ መሬት፣ በግንባታው ዘርፍ፣ በግዥ ስርዓቱ፣ በጉምሩክ፣ በዳኝነት ስርዓቱ፣ በፍትሕ ስርዓቱ፣ በአገልግሎት አሰጣጥ፣ በሀይማኖት ተቋማት፣ በትምህርቱ፣ በጤናው፣ ወዘተረፈ የተንሰራፋው ሙስና ተቋማዊና መዋቅራዊ ሆኖ ማቆጥቆጥ የጀመረው ከ1983 ዓ.ም አንስቶ ነው።
ሙስናን ለመከላከል ሰከን ብሎ ምንጩንና የደረሰበትን ደረጃ መመርመር ይጠይቃል። ያልበከለው ያላዳረሰው ዘርፍ የለምና። ዋና ዋናዎችን ተጠያቂ ከማድረግ ባሻገር አሰራርንና አደረጃጀትን መፈተሽ፤ ክፍተቶችን/loopholes/ ማስተካከል፤ የጸረ ሙስና ትግልን እያንዳንዱ ተቋም የመደበኛ ስራው አካል Mainstream ማድረግም ይጠይቃል። በሀይማኖት ተቋማት ማሻሻያ በማድረግ ተከታዮቻቸውን በምሳሌ መምራት እንዲችሉ ማብቃት፤ ስርዓተ ትምህርቱ ሙስናን የሚጸየፍ ትውልድ ከመቅረጽ አንጻር መቃኘት አለበት።
አገራዊ ንቅናቄ ማቀጣጠል፤ ለዜጋው አርዓያ የሚሆኑ ከሙስናና ከብልሹ አሰራር የጸዱ መሪዎችን ወደፊት ማምጣት፤ ብዙኃን መገናኛዎችን ማብቃት፤ የጸረ ሙስና ኮሚሽንን ተግባርና ስልጣን በማሻሻል ኃላፊነቱን እንዲወጣ ማስቻል፤ መንግስትም ሆነ ገዢው ፓርቲ ከባለሀብቱ ጋር ያለውን ያልተገባ ግንኙነት ማረም፤ የመንግስት ሰራተኛውን ደመወዝና ጥቅማጥቅም ማሻሻል ግድ ይላል። የሚራብና የሚታረዝ ሲቪል ሰርቫንት ይዞ ሙስናንና ብልሹ አሰራር መከላከል አይቻልምና። በሲሚንቶም ሆነ በነዳጅ ግብይቱ የሚስተዋለው አይን ያወጣ ሌብነት መንግስትን እስከመገዳደር ደርሷል።
በሌሎች ዘርፎችም ሌቦችና ሙሰኞች መንግስትን በንቀት ቁልቁል ማየት የጀመሩት ለዚህ ነው። እንደ ዜጋ ሁላችንም በአንድም በሌላ መልኩ ሌባ ነን። ብናጣ ብናጣ የስራ ሰዓት እንሰርቃለን። ሌቦች ሲሰርቁ ባላየ ባልሰማ እናልፋለን። ሲሾም ያልበላ፣ ሲሻር ይቆጨዋል፤ እያልን እዚህ አድርሰነዋል። በአገራችን ከዋነኛዎቹ የሙስና እና የብልሹ አሰራር ምንጮች አንዱ በአሰራሮችና በሕጎች የሚስተዋሉ ክፍተቶችን ተጠቅሞ መክበር ነው። ዛሬ በአገራችን ካሉ ባለሀብቶች ቁጥራቸው ቀላል ያልሆኑት ቢሊየነር የሆኑት በባንክ ኢንዱስትሪው ያለውን ክፍተት ከውስጥ አዋቂዎች ጋር በመጠቀም ነው።
ከ20 ዓመት በፊት የላዳ ሹፌርና ቅቤ ነጋዴ ወይም ልብስ ሰፊ ዛሬ ቢጠሩት የማይሰማ የናጠጠ ሀብታም የሆነው በየዘርፉ ያለን ክፍተት በመጠቀም ነው። በረንዳ ላይ የጀበና ቡና የምትሸጥ የእኔ ቢጤን አፍንጫዋን ይዞ ግብር የሚያስከፍል መንግስት፤ ክፍተቱን ተጠቅመው ለሚቦጠቡጡት ግን እሩህሩህ አንጀታም ነው። ሰሞነኛውን የአሰራር ክፍተትን በመጠቀም የተከፈተውን አዲስ የሙስና ዘርፍ ላስተዋውቃችሁ ።
መንግስት ዓለም አቀፉን የነዳጅ ዋጋ ጭማሬን ለማስተካከል ለህዝብ አገልግሎት የሚሰጡ ተሽከርካሪዎችን ድጎማ እንደሚያደርግ ይታወቃል። በዚህ ሂደት መንግስት ለነዚህ የህዝብ አገልግሎት ሰጭ (ታክሲ፣ ሚኒባስ እና አገር አቋራጭ) የትራንስፖርት አይነቶች እንደሚጠቀሙት የነዳጅ ፍጆታ መጠን ድጎማ የሚደረግላቸው ሲሆን ለሚኒባስ እና ለታክሲ በትንሹ በቀን 1200 ብር ይደጎማሉ፤ ይህም አላማው ለህብረተሰቡ የትራንስፖርት ዋጋ እንዳይጨምር፣ ባለንብረቶችም እንዳይጎዱ ያለመ ነው። ነገር ግን በዚህ የድጎማ ስርዓት እነዚህ የሚኒባስ እና የታክሲ ባለንብረቶች (ሾፌሮች) ከሚታሰብላቸው የቀን 1200 ብር ውስጥ ለነዳጅ ቀጂው 200 ብር በማሰብ ነዳጁን ሳይቀዱ እነርሱም ምንም ሳይሰሩ መኪናቸውን ቤታቸው ውስጥ በማቆም ያለምንም ወጭ በቀን 1000 ብር በወር 30000 ብር እየዘረፉ ይገኛሉ።
በዚህ ሂደት ፦
1- መንግስት በሚያደርገው የቁጥጥር እና የክትትል ክፍተት ሌቦች እንዲበለፅጉበት ትልቅ የፋይናንስ ምንጭ ሆኗል።
2- ባለንብረቶች ያለምንም ድካም እና ወጭ በቀን 1000 ብር በማግኘታቸው ንብረቶቻቸውን ቤታቸው በማዋላቸው ህብረተሰቡ በትራንስፖርት እጥረት መቸገር ጀምሯል።
3- የአገር እና የህዝብ ንብረት ግቡን ላልመታው ዓላማ እየተመዘበረ ይገኛል።
4- የትራንስፖርት መኪኖች በየቤቱ መቆም በመጀመራቸው እጥረት እያጋጠመ በመምጣቱ ህዝቡ ላይ ከታሪፍ በላይ በመክፈል ለተጨማሪ ችግር ተዳርጓል። ስለሆነም የትራንስፖርት ሚኒስቴር እና በየከተማው የሚገኙ የትራንስፖርት ቢሮዎች ጥብቅ ቁጥጥር በማድረግ የህዝብ እንግልት እንዲቀነስ፣ ያለ አግባብ እየተመዘበረ ያለው የህዝብ እና የአገር ሀብት ለታለመለት አላማ እንዲውል ያላሰለሰ ክትትል እና ቁጥጥር ይደረግ። ይህ መረጃ ሁሉንም ባለንብረት እና ሾፌሮች ጨፍልቆ በአንድ ቅርጫት የሚያስገባ ሳይሆን መንግስት የሰጠውን ድጎማ በአግባቡ በመጠቀም አገር እና ህዝብን እያገለገሉ ያሉ ጠንካራ ሾፌሮችም ሞልተዋል።
ይህ ዘ-ሐበሻ ላይ የተመለከትኩት ዘገባ ሙስናም ሆነ ብልሹ አሰራር በመንግስት ተቋማት ብቻ ሳይሆን በማህበረሰቡ ዘንድም እየተንሰራፋ መሆኑን ያመለክታል። ሙስና እንደ ተስቦ ያልተጋባበት የህይወት ቅንጣት የለም። ስለሆነም ለመከላከል የሚደረገው ጥረት መላ ሕዝቡን ባነቃነቀ አግባብ ሊሆን ይገባል። መንግስት መዋቅሩንና ተቋሙን ከመፈተሽ ጎን ለጎን ተግባራዊ ዕንቅስቃሴ ጀመሯል። እንደ ዜጋ ደግሞ ኃላፊነታችንን መወጣት ይጠበቅብናል። በጠቅላይ ሚኒስትሩ የፓርላማ ማብራሪያ ማግስት የጸረ ሙስና ኮሚቴ መቋቋሙን በሚያበስረው መግለጫ ሙስና በጊዜ ካልተገታ ለአገር ህልውናና ደህንነት አደገኛ መሆኑ ተብራርቷል። በፍትሕ ሥርዓቱ ውስጥ ስላላው ብልሹ አሠራር ፓርላማው ጠንከር ያለ ክትትል ማድረግ እንደሚገባው ጠቁመዋል።
በፍትሕ ሥርዓት ውስጥ ዳኛ፣ ዓቃቤ ሕግና ፖሊስ ቃለ መሃላ ፈጽሜያለሁ ቃሌን ጠብቄያለሁ እምነት አለኝ የሚሉ ቢኖሩም፣ እነዚህ ሰዎች ግን በተቋሞቻቸውና በቤተሰቦቻቸው እንደ ሞኝ እንደሚቆጠሩና በእውነት ላይ ተመርኩዞ የሚሠራ አካል ሞኝ፣ ያልገባውና ያልሠለጠነ ተደርጎ በጓደኛው እንደሚሰደብ አስረድተዋል። በ2014 ዓ.ም. በፓርላማው ቀርበው ስለዳኞች ብልሹ አሠራር ያደረጉት ንግግር አንዳንዶችን እንዳላመማቸው የገለጹት ጠቅላይ ሚኒስትሩ፣ “ሌብነት አለ ሲባል ዝም ብሎ ሳይሆን በቴሌግራም ግሩፕ ከፍተው ጉቦ የሚቀባበሉ ዳኞች” በመኖራቸው መሆኑን አስረድተዋል።
ከዚህ በፊት ባልተለመደ ሁኔታ የፍትሕ ሥርዓቱ በጀት ከአስፈጻሚው ወጥቶ ለፓርላማ የገባው አሁን መሆኑን በመግለጽ፣ ተቋማቱ በብዙ ተደግፈዋል መሻሻል ካለባቸው አሁን ነው ብለዋል። ነገር ግን አሁን ነገሩ ከተናጋ መቼም የማይቃና በመሆኑ እውነተኛ የሆኑ አገርን የሚወዱና ቃላቸውን የሚያከብሩ ሰዎች ተባባሪ ሆነው ጠንካራ ሪፎርም መሥራት እንደሚያስፈልግ ተናግረዋል።
ሌብነት በጣም አታካች ጉዳይ መሆኑን የጠቀሱት ጠቅላይ ሚኒስትሩ፣ “የገጠመንን አገራዊ ፈተናና ችግር እንደ ዕድል የወሰዱ ሰዎች ቀይ መስመር ያልነውን ሌብነት ቀይ ምንጣፍ አድርገውት በነፃነት የሚንሸራሸሩበት ሰዎች በዝተዋል፤” ብለዋል። በአዲስ አበባም ሆን በአጠቃላይ ኢትዮጵያ ውስጥ ፋይል በእግሩ አይሄድም የሚባል ንግግር እየተለመደ የመጣ ስለመሆኑ በመግለጽ፤ ሌብነት ልምምዱ ብቻ ሳይሆን እንደ መብት መወሰዱ አደገኛ እንደሆነ አብራርተዋል።
“ሌብነት የኢኮኖሚ ነቀዝና የዕድገት ነቀርሳ ነው፤” ያሉት ጠቅላይ ሚኒስትሩ፣ ሌብነት ባለበት ማደግም መኖርም አስቸጋሪ ነው። ምክንያቱም ሌቦች መስረቃቸው ብቻ ሳይሆን፣ ከሰረቁ በኋላ ገንዘቡ ባንክ ስለማይሄድ ከሰረቁ በኋላ ወደ ሕገወጥ የንግድ ሥርዓት ውስጥ እንደሚገቡ አስረድተዋል። ለዚህም ማሳያው በአዲስ አበባ በርካታ ሕንፃዎች ባለቤት አልባ ሆነው መገኘታቸውን በመጠቆም፣ “ሌብነትን እንደ ብልፅግና ሳይሆን እንደ ማኅበረሰብ እየተለማመድነው በመሆኑ በየሁሉም ተቋማት ውስጥ መፍትሔ ካልተበጀ ጉዳቱ ያመዝናል፤” ብለዋል።”ድሮ ሳይሠሩ የሚበሉ ይባል ነበር፣ አሁን የመጡት ደግሞ የሚሠራውን መርጠው የሚበሉ ወይም እየሠራ የሚንቀሳቀስን ሠራተኛና ሥራውን የሚበሉ ናቸው፤”ብለዋል።
በቁምላቸው አበበ ይማም (ሞሼ ዳያን)
fenote1971@gmail.com
አዲስ ዘመን ኅዳር 20/ 2015 ዓ.ም