ቴክኖሎጂ እያንዳንዱን የዓለምን እንቅስቃሴ በተቆጣጠረበት በአሁኑ ወቅት፣ ምቹና ቀልጣፋ ኑሮንም ሆነ ዘላቂ የምጣኔ ሀብት እድገትን ከቴክኖሎጂው ዘርፍ እድገት ውጭ ማሰብ የሚቻል አይሆንም። ዛሬ በምጣኔ ሀብታቸው የዓለማችን ቁንጮ የሆኑት ልዕለ ኃያላን አገራት የቴክኖሎጂ ዘርፋቸው እጅግ የዳበረ ነው። የእነዚህ አገራት ዜጎች ዕለታዊ እንቅስቃሴ በቴክኖሎጂ ውጤቶች የታገዘ በመሆኑ ኑሯቸው ምቹና ቀላል ነው።
ኢትዮጵያም የዚህ ቴክኖሎጂ ተቋዳሽ ለመሆን በትኩረት መስራት ውስጥ ገብታለች። ከአስር ዓመቱ የኢትዮጵያ አገራዊ የልማት እቅድ ስትራቴጂካዊ ምሰሶዎች (Strategic Pillars) መካከል አንዱ የኢንፎርሜሽን ቴክኖሎጂ ተደርጎ ተይዟል። ይህን ለማሳካት ደግሞ የኢኖቬሽንና ቴክኖሎጂ ዘርፉን ውጤታማነት ማሳደግ ወሳኝ ግብዓት እንደሆነ ይታወቃል። ግብይትን የሚያቀላጥፉ የቴክኖሎጂ ውጤቶች መስፋፋትና ማደግ በዚህ ሂደት የሚኖራቸው ሚና ከፍተኛ ነው።
የግሉ ዘርፍ በአገራዊ ኢኮኖሚው ላይ ከሚኖረው ወሳኝ ሚና አንፃር በግሉ ዘርፍ የሚከናወኑ መሰል የቴክኖሎጂ አሰራሮችን መደገፍ ምጣኔ ሀብታዊ እድገቱን ዘላቂ ለማድረግ ጉልህ አስተዋፅኦ ይኖረዋል። ከቅርብ ጊዜያት ወዲህ ምርትና አገልግሎትን በዘመናዊ አሰራር የሚያቀርቡ ቴክኖሎጂዎች በብዛት ወደ ስራ እየገቡ ይገኛሉ። አገልግሎት ፈላጊዎችንና ባለሙያዎችን በቀላሉ የሚያገናኘውና ኑሮን ምቹና ቀላል፣ አካባቢን ውብ በማድረግ ተግባር ላይ የራሱን አስተዋፅኦ እያበረከተ የሚገኘው ‹‹ጉዳይኦን (GoodayOn)›› ቴክኖሎጂ የዚህ ማሳያ ነው።
በ‹‹ጉዳይ›› (Gooday) ኃላፊነቱ የተወሰነ የግል ማኅበር ተሰርቶ ለአገልግሎት የበቃው ይህ ቴክኖሎጂ፣ ተለምዷዊውን የሥራና አገልግሎት ፍለጋ ዘዴን ለማዘመንና የዲጂታል ግብይት አሰራርን እውን ለማድረግ እየሰራ ይገኛል። የድርጅቱ ተባባሪ መስራችና ዋና ስራ አስኪያጅ ወይዘሮ ትዕግሥት አፈወርቅ ስለቴክኖሎጂው ምንነትና ፋይዳ የሰጡንን ማብራሪያ ይዘን ቀርበናል።
‹‹ጉዳይኦን›› (GoodayOn)፣ አገልግሎት አሰጣጡና ፋይዳዎቹ
‹‹ጉዳይኦን (GoodayOn)›› አገልግሎት ፈላጊዎችን እና ባለሙያዎችን (ስራንና ሰራተኛን) የሚያገናኝ የዲጂታል ግብይት ቴክኖሎጂ መተግበሪያ (Mobile Application) ነው። ይህ መተግበሪያ ዘርፈ ብዙ ጥቅሞች ያሉት ሲሆን፤ ዋናው ፋይዳው የተለያዩ አገልግሎት ፈላጊዎችን (ስራ) እና ባለሙያዎችን/ሰራተኞችን በማገናኘት የስራ እድል መፍጠርና የአገልግሎት ሂደትን ማቀላጠፍ ነው። ቴክኖሎጂው ለሰራተኞች የዲጂታል ተደራሽነት እድል (Digital Presence) መስጠት እንጂ ኤጀንሲ ሆኖ የሚያገለግል አይደለም። ይህ ለሰራተኞች የዲጂታል ተደራሽነት እድል (Digital Presence) የመስጠት ባህርይው ‹‹ጉዳይኦን›› (GoodayOn) መሰል አገልግሎት ከሚሰጡ የቴክኖሎጂ ተቋማት የተሻለና የተለየ እንዲሆን ያደርገዋል።
ባለሙያዎችን የሚፈልጉ አገልግሎት ፈላጊዎች መተግበሪያውን ከፕሌይስቶር (Play Store) ወይም ከአፕስቶር (App Store) ላይ በማውረድ (ዳውንሎድ በማድረግ) ማስታወቂያቸውን በቀላሉ ወደ ‹‹ጉዳይኦን›› (GoodayOn) ማስተላለፍና በዚህ ቴክኖሎጂ በኩል ማሰራጨት ይችላሉ። ማስታወቂያዎቹ ወደ መተግበሪያው የመረጃ ቋት (Database) ውስጥ እንዲገቡ ይደረጋል። በዚህ ሂደት ቴክኖሎጂውን ለመጠቀም የተመዘገቡ (መተግበሪያውን ያወረዱ) ስራ ፈላጊዎችም የስራ እድሎችን መመልከት ይችላሉ። የ‹‹ጉዳይኦን›› (GoodayOn) ባለሙያዎች ደግሞ ማስታወቂያዎች ተስተካክለው እንዲወጡ የማገዝ፣ ምክር የመስጠትና ክትትል የማድረግ ተግባራትን ያከናውናሉ።
ቴክኖሎጂው በተለያዩ ምክንያቶች መተግበሪያውን መጠቀም ለማይችሉ ሰዎች ደግሞ በ9675 የጥሪ ማዕከል (Call Center) አማካኝነት አገልግሎት የሚያገኙበት አማራጭም አለው። በጥሪ ማዕከሉ በኩል አገልግሎቱን ማግኘት የሚፈልጉ ሰዎች ዝርዝር መረጃዎችንና ፍላጎቶቻቸውን በማስመዝገብ የአገልግሎት ጥያቄያቸውንና የስራ ፍላጎታቸውን ማሳካት ይችላሉ። አገልግሎት ፈላጊው ወደ 9675 ሲደውል የት አካባቢ እንደሚገኝ ይጠየቃል፤ አድራሻው ከተለየ በኋላ አገልግሎት ፈላጊው ካለበት ቦታ በቅርበት ላይ የሚገኙ ባለሙያዎች አድራሻ ተሰጥቶት አገልግሎት ፈላጊውና ባለሙያው እንዲገናኙ ይደረጋል።
አዲስ አበባን ጨምሮ በበርካታ ከተሞች የሚገኙ ስፍራዎች ስራ ፍለጋ በሚወጡ ሰዎች ምክንያት ሲጨናነቁ ይስተዋላል። የስራና ሌሎች ማስታወቂያዎችም በየመንገዶች ላይ በሚገኙ የኤሌክትሪክ ምሰሶዎች፣ አጥሮችና ግድግዳዎች ላይ ተለጥፈው መመልከትም የተለመደ ነው። ‹‹ጉዳይኦን›› (GoodayOn) ዲጂታል መተግበሪያ ሰዎች ለስራ ፍለጋ ከቤታቸው ወጥተው እንዳይንገላቱ ያስችላቸዋል፤ ይህም ስራ ፈላጊዎቹ ለትራንስፖርት የሚያወጡትን ወጪ እንዲያስቀርላቸው ከማድረጉ ባሻገር በህዝብ ትራንስፖርት አገልግሎት ላይ መጨናነቅና እንግልት እንዳይኖር ያግዛል፤ አላስፈላጊ ለሆነ የደላላ ክፍያ እንዳይጋለጡም ያደርጋቸዋል። ከዚህ በተጨማሪም ማስታወቂያዎች በየመንገዱ ላይ እንዳይለጠፉ በማድረግ ለከተማ ጽዳትና ዘመናዊነት የራሱን አስተዋፅኦ ያበረክታል።
ከቴክኖሎጂው ተጠቃሚዎች ፍላጎት መገንዘብ እንደተቻለው በገበያው ላይ ከፍተኛ የሆነ የምግብ ዝግጅት፤ የቧንቧ፣ የኤሌክትሮኒክስ እቃዎች (ቲቪ፣ ፍሪጅ፣ ምድጃ …) ጥገናና የጽዳት ባለሙያዎች፣ አስጠኚዎች፣ ተመላላሽ ነርሶች፣ ሞግዚቶች፣ የፊኒሺንግ ሰራተኞች የሌሎች ባለሙያዎች ፍላጎት አለ። ቴክኖሎጂው እነዚህ ባለሙያዎች በተለምዶ ደላሎች ከሚጠይቁት ክፍያ ነፃ ሆነው ከአገልግሎት (ባለሙያ) ፈላጊዎች ጋር እንዲገናኙ ያስችላቸዋል።
ቴክኖሎጂው ያስገኛቸው ውጤቶች
ቴክኖሎጂው ስራ ከጀመረ ሁለት ዓመታት ቢሆነውም በሚገባ ተጠናክሮ መንቀሳቀስ የቻለው ግን ባለፈው አንድ ዓመት ነው። እንቅስቃሴው የሚያሳየውም ብዙ የስራ እድሎችና ባለሙያዎች እንዳሉ ነው። በሁለት ዓመታት ውስጥ ከ80ሺ በላይ ሰዎች የተመዘገቡና መተግበሪያውን ያወረዱ (ዳውንሎድ ያደረጉ) ሲሆን፣ ከዚህ ውስጥ 35ሺ የሚሆኑት ሰዎች ባለሙያዎች ናቸው። እስካሁን ድረስ ከመተግበሪያው ላይ ከ250ሺ በላይ ፍለጋዎች ተከናውነዋል፤ ይህም መተግበሪያውን የሚጠቀሙ ሰዎች ከ250ሺ ጊዜያት በላይ ሰራተኞችን መፈለጋቸውን የሚጠቁም ነው። ከዚህ ውስጥ ከ70ሺ በላይ ሰራተኞች ስራ ሰርተው ገንዘብ አግኝተዋል።
የጥሪ ማዕከሉ ደግሞ በአንድ ወር ከአንድ ሺ በላይ የሰራተኞች ጥያቄዎችን ያስተናግዳል። ባለፈው አንድ ዓመት በተለያዩ ቦታዎች ማስታወቂያ ከለጠፉ ባለማስታወቂያዎች ጋር በመነጋገር ከአምስት ሺ በላይ ማስታወቂዎችን ወደ መተግበሪያው እንዲገቡና ባለቤቶቹም እንዲመዘገቡ አድርጓል። እስካሁን ድረስ አገልግሎቱን በተደጋጋሚና በንቃት እየተጠቀሙ ያሉ በርካታ ተጠቃሚዎች አሉ። በአጭር ጊዜ ውስጥ ከ80ሺ በላይ ምዝገባዎች መከናወናቸው ‹‹ጉዳይኦን›› (GoodayOn) ተፈላጊነቱ እየጨመረ እንደመጣ ማሳያ ተደርጎ ይወሰዳል።
‹‹ጉዳይኦን›› (GoodayOn) ባለሙያዎችንና አገልግሎት ፈላጊዎችን በማገናኘት ከፈጠረው የስራ እድልና የአገልግሎት መሳለጥ በተጨማሪ፣ አገልግሎቱን ለሚያመቻቹና የምክርና ድጋፍ አገልግሎት ለሚሰጡ 11 ሰዎች ቋሚ የስራ እድል ፈጥሯል። ከዚህ በተጨማሪም ተለማማጅ ሰራተኞችን (Interns) ተቀብሎ አቅማቸው እንዲጎለብት አድርጓል፤ ከተለማማጆቹ መካከልም የተወሰኑትን በቋሚነት በመቅጠርም የስራ እድል ፈጥሮላቸዋል፤ በአሁኑ ወቅትም ስምንት ተለማማጅ ሰራተኞችን ተቀብሎ አቅማቸው እንዲጎለብትና በንድፈ ሃሳብ ያገኙት እውቀት በተግባር እንዲዳብር እያደረገ ይገኛል። ድርጅቱ አገልግሎት ለሚሰጡ ባለሙያዎችም ምክር ይሰጣል። ባለሙያዎች ከአገልግሎት ፈላጊዎች ጥሩ ያልሆነ አስተያየት ቢሰጥባቸው ባለሙያዎቹ ተጨማሪ ስልጠናና የአቅም ማጎልበቻ እንዲያገኙ ያደርጋል።
‹‹ጉዳይኦን›› (GoodayOn)›› ስራ ፈላጊዎች ብቻም ሳይሆኑ ተጨማሪ ገቢ ማግኘት የሚፈልጉ ሰዎችም ስራዎችን እንዲሰሩ እድል ይፈጥራል። ብዙ ሰዎች ሁለትና ከዚያ በላይ ስራዎችን እየሰሩ ገንዘብ እያገኙ ነው። ‹‹ስራ ሰርተን ገንዘብ እናገኛለን›› ብለው አስበው የማያውቁ ሰዎች በዚህ ቴክኖሎጂ አማካኝነት እየሰሩ ገንዘብ እያገኙ ነው። በየዓመቱ በርካታ ተማሪዎች ከከፍተኛ ትምህርት ተቋማት ስለሚመረቁ አጫጭር ስልጠናዎችን እየወሰዱ ተጨማሪ ስራዎችን እንዲሰሩ እድል ፈጥሮላቸዋል።
ስራ ሰርተው የማያውቁ ሰዎች እንዲሁም ተመርቀው ስለስራ ብዙም ልምድ የሌላቸው ወጣቶች ‹‹ለካ ይህም ተሰርቶ ገንዘብ ይገኛል›› ብለው ደፍረው ስራ መስራታቸውና ገንዘብ ማግኘታቸው እንዲሁም ቴክኖሎጂው ትልቅና አወንታዊ የሆነ ማኅበራዊ ተፅዕኖ (Social Impact) መፍጠሩ ትልቅ ትርፍና ስኬት እንደሆነ ወይዘሮ ትዕግስት ይናገራሉ።
የቴክኖሎጂው የአገልግሎት ደህንነት ዋስትና
የዘመኑ የቴክኖሎጂ ውጤቶች እጅግ የረቀቁና ውስብስብ መሆናቸው፣ የተጠቃሚዎች ሁለገብ የመረጃ አገልግሎት ደህንነት ጉዳይ ትኩረት እንዲያገኝ ምክንያት ሆኗል። ‹‹ጉዳይኦን›› (GoodayOn) መተግበሪያ፣ ለአገልግሎት ደህንነት ዋስትና የሚሰጡ አሰራሮችን ተግባራዊ ያደረገ ቴክኖሎጂ ነው። አገልግሎት ፈላጊው መታወቂያ ሳይኖረውና መታወቂያው ወደ መተግበሪያው ስርዓት ሳይገባ አይመዘገብም። መተግበሪያው ማረጋጋጫ (Verification) ካልሰጠው ማስታወቂያውንም ሆነ ፍላጎቱን ሰው ሊመለከተው አይችልም። ቴክኖሎጂው የማረጋገጫ ኮድ (Verification Code) ስላለው በራሱ በግለሰቡ ስልክ ካልሆነ መመዝገብ አይችልም። መተግበሪያው በውስጡ ስልክ ቁጥር፣ መታወቂያና ፎቶ የሚቀመጡበት ስርዓት አለው። ይህም ደህንነቱ የተጠበቀ አገልግሎት ለማቅረብ ጥሩ ዋስትና ተደርጎ ሊወሰድ ይችላል።
የ‹‹ጉዳይኦን›› (GoodayOn) የደንበኞች ግንኙነት አመራር ዘዴ (Customers’ Relations Management Tool) የአገልግሎት ፈላጊዎችን ጥያቄ በግልፅ የሚያሳውቅ በመሆኑ በቴክኖሎጂ ድርጅቱና በአገልግሎት ፈላጊዎቹ መካከል ያለውን ግንኙነት ቀላል የሚያደርግ ነው። መተግበሪያው አገልግሎት ፈላጊዎች ስላገኟቸው አገልግሎቶች ያላቸውን አስተያየትና ግብረ መልስ (Feedback) መዝግቦ የሚይዝበት የአሰራር ስርዓት አለው። ይህም ግብረ መልስ የመስጠት እና ተጨማሪ መረጃዎችንና ጥያቄዎችን የመለዋወጥ ሂደቱን ፈጣንና ቀጣይ ያደርገዋል። ቴክኖሎጂው እያንዳንዱን የመልዕክት ልውውጥ በግልፅ ስለሚያሳይ የአገልግሎቱ ደህንነት የተጠበቀ እንዲሆን ያግዛል። በአጠቃላይ የ‹‹ጉዳይኦን›› (GoodayOn) የደንበኞች ግንኙነት አመራር ዘዴው ለአገልግሎት ደህንነት ዋስትና ተደርጎ ሊጠቀስ የሚችል የአሰራር ስርዓት ነው።
ያጋጠሙ ፈተናዎች
በማኅበረሰቡ የዲጂታል ስርዓት ግንዛቤ ማነስ፣ ከተለመደው አሰራር በመላቀቅ ከአዳዲስ አሰራሮች ጋር በፍጥነት ለመላመድ በሚያጋጥሙ ልዩ ልዩ ችግሮች ምክንያት ‹‹ጉዳይኦን›› ቴክኖሎጂን ወደ ኅብረተሰቡ ለማስረፅ መንገዱ ቀላልና ምቹ አልነበረም። አብዛኛው ሰው ሊጠቀምበት የሚችል መተግበሪያ ከማበልጸግ ጀምሮ ለሴቶች ተደራሽ መሆን እና ፈቃድ ማግኘት የስራው ዋና ዋና ፈተናዎች ነበሩ። በበርካታ አገልግሎት ፈላጊዎች የሚፈለጉት ስራዎች ሴቶችን የሚመለከቱ ሆነው ሳለ ለሴቶች ተደራሽ መሆን ግን አስቸጋሪ ነበር። ወደ መኖሪያ ሰፈሮች በመንቀሳቀስ በተደረገው ጥረት ይህን ችግር በተወሰነ ደረጃ መቅረፍ ተችሏል። ወደ መኖሪያ ሰፈሮች ለመግባት የሚያስችል ፈቃድ ማግኘት ደግሞ በጣም ከባድና ፈታኝ ተግባር ነው።
እቅዶች
‹‹ጉዳይኦን›› (GoodayOn) መተግበሪያን የመጀመሪያ ስራው/አገልግሎቱ አድርጎ ያስጀመረው ድርጅቱ፣ ገበያን በዲጂታል አሰራር የማከናወን (Market Digitalization) እና ትልቅ የመረጃ ተቋም (Data Company) የመሆን ዋና ዋና እቅዶች አሉት። የ‹‹ጉዳይኦን›› (GoodayOn) መተግበሪያ ስለእያንዳንዱ አገልግሎት ፈላጊና ባለሙያ እንቅስቃሴ ሙሉና ዝርዝር መረጃ የያዘ የመረጃ ቋት ያለው መሆኑ፣ ድርጅቱ በቀጣይ ለያዘው ትልቅ የመረጃ ክምችት ተቋም የመሆን እቅዱ አዎንታዊ ግብዓት እንደሚሆነው ይጠበቃል። በተጨማሪም ለአገራዊ የመረጃ ክምችት የራሱ አበርክቶ ይኖረዋል።
እስካሁን ድረስ ሁሉንም አገልግሎቶች ያለምንም ክፍያ በነፃ እየሰጠ የሚገኘውና ከአዲስ አበባ በተጨማሪ በሌሎች አካባቢዎችም ለማስፋፋት አልሞ እየሰራ ያለው ‹‹ጉዳይኦን›› (GoodayOn)፣ ከጥቂት ወራት በኋላ እሴት ለተጨመረባቸው አገልግሎቶች (Value Added Services) መጠነኛ ክፍያዎችን ለማስከፈል አቅዷል። ስራው ሲጀመር ከነበረው ጊዜ ጋር ሲነፃፀር አሁን ትልቅ ለውጥና መሻሻል እንዳለ በግልፅ የሚታይ በመሆኑ፣ ድርጅቱ ስራውን አጠናክሮ በማስቀጠል ግብይትን በዲጂታል አሰራር የማከናወን እቅዱን ለማሳካት ይሰራል።
‹‹ጉዳይኦን›› (GoodayOn) ዜጎች የስራ እድል እንዲያገኙ እድል በመፍጠር እና የማስታወቂያ አሰራርን ዲጂታል በማድረግ የከተማ ንፅህናን በመጠበቅ የራሱን በጎ አስተዋፅዖ እያበረከተ በመሆኑ የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደርና ሌሎች ባለድርሻ አካላት ድጋፍ እንዲያደርጉ እና ለዘመኑ የሚመጥን አሰራር በመዘርጋት የዲጂታል ስርዓትን መተግበር እንደሚገባ ወይዘሮ ትዕግሥት ይናገራሉ። ‹‹ከአዲስ አበባ ከተማ ጋር በጋራ ብንሰራ በስፋት ወደ ኅብረተሰቡ ለመግባት ያስችለናል። ፈቃድ ለማግኘት ያለው ውጣ ውረድ እጅግ አስቸጋሪ ነው። እኛ የፋይናንስ ድጋፍ አንፈልግም። የምንፈልገው ገንዘብ፣ መሬት ወይም ቤት አይደለም። ፈቃድና ትብብር ነው የምንፈልገው›› በማለት በትብብር መስራት ወይዘሮ ትዕግሥት እንደሚስፈልግ አበክረው ያሳስባሉ።
አንተነህ ቸሬ
አዲስ ዘመን ኅዳር 20/ 2015 ዓ.ም