የኳታሩ የአለም ዋንጫ ከተጀመረ እነሆ ሳምንት አለፈው:: እንደተለመደው አይኖች ሁሉ ወደ መካከለኛዋ ምስራቅ ሀገር ዞረው ሁሉም ሰው ሙሉ ትኩረቱን እዚያው ላይ አድርጓል:: ኳሱም እንደተጠበቀው ዘና የሚያደርግ እየሆነ ነው:: የሳውዲን እና የአርጀንቲናን ጨዋታ ያየ ሰው ለዚህ ምስክር መሆን ይችላል:: ጨዋታው አዝናኝ እና አስደሳች ከመሆኑም በላይ እግር ኳስ ለምን ተወዳጅ ስፖርት እንደሆነም አመላካች ነው:: በኳስ የማትታወቀው ሳኡዲ አረቢያ ለዋንጫ የታጨችውን አርጀንቲናን የረታችበት መንገድም አሰደናቂ ነው::
በእግር ኳስ የተነሳ የሚናደዱ እና የሚሰዳደቡ ሰዎች መብዛት ያስገርማል:: በጣም አስገራሚ እኮ ነው፤ ዛሬም በዚህ ዘመን ቡድኔን ተናገራችሁብኝ ብለው የሚዘላለፉ ሰዎች አሉ:: እኔ ራሴ በአንድ የሆነ አገር ደጋፊ ነኝ በሚል ሰው በግል የማህበራዊ ድረገጽ እንዳልሸጥ እንዳልለወጥ ተደርጌ ተሰድቤያለሁ:: ይሁን ግድየለም ሀገር ወደ ሰላም በምትሄድበት በዚህ ወቅት ጦርነት አልከፍትም ብዬ አሰናበትኩት እንጂ ነገሩስ ራሱን የቻለ ጦርነት ቀስቃሽ ነገር ነበር:: እውነቱን እንነጋገር ከተባለ ኳስ ስሜታዊ ያደርጋል፤ የሚወዱት ቡድን ሲያሸንፍ የሚፈጥረው ደስታ ከፍተኛ ነው:: ሲሸነፍም ንዴቱ እንደዚያው ነው:: ብሽሽቅም የኳስ ባህል ነው፤ ነገር ግን መስመር አልፎ መሰዳደብ እና መዛዛት አላስፈላጊ ነገር ነው:: አሁን አንድ ኢትዮጵያዊ በሆነ አገር ሽንፈት ተናድዶ ሌላ ኢትዮጵያዊን መታ ቢባል ነውር አይሆንም፣ እነሱስ ይሄን ቢሰሙ አይሰቁብንም፣ በእውነቱ የኛ ነገር እኮ ቅቤ አንጣሪዋ እያለች ጎመን ቀንጣሽዋን ምች መታት እንደማለት ነው::
ሌላኛው ትዝብቴ ደግሞ ምን መሰላችሁ፤ ምእራባውያኑ በኳታር ላይ እያደረጉ ያሉት ጫና እና እኛ የተረዳንበት መንገድ አስገርሞኛል:: ሁላችንም እንደምናየው ምእራባውያኑ የኳታርን የአለም ዋንጫ ለማጠልሸት የተቻላቸውን ሁሉ እያደረጉ ነው:: ነገሩ በእርግጥ አስገራሚ አይደለም:: የትኛውም ነገር እነሱ በሚፈልጉት መልኩ የራሳቸውን እሴቶች ለማንጸባረቅ ካልተጠቀሙበት ነገሩን እንደማይጠቅም አድርገው ማጣጣል የተለመደ አካሄዳቸው ነው::
አሁን እያረጉት ያሉትም ነገር ይሄንኑ ነው:: ከአሁን በኋላ የአለም ዋንጫም ሆነ ሌላ ትልቅ ውድድር ማዘጋጀት ከምእራባውያኑ ጋር በእሴት ወደማይቀራረቡት አፍሪካ፣ መካከለኛው ምስራቅ እና አንዳንድ የእስያ ሀገራት እንዳይሄድ ለማሳመን ነው የማጣጣል ዘመቻው አላማ:: ብዙ የኛ ሀገር ሰውም ይሄን ተረድቶታል:: ታዲያ ይህ የምእራባውያን አካሄድ እንዲህ ከገባን ይህን መሰል ነገር በገዛ ሀገራችን ላይ ሲያካሂዱ ለምንድን ነው የማይገባን፤ በአንድነት ለምን አንቆምም:: እነሱ የማያዙት መንግስት እና እነሱ የሚፈልጉት ነገር የማይፈጸምባት ሀገር ኢ ዴሞክራሲያዊ ፤ ኋላቀር ፤ ሰላም አልባ እንደሆነች አድርገው ሲስሉ እያየን አይደል::
ስለዚህ በኳታር ላይ ለሚያደርጉት ነገር ያሳየነውን ሀዘኔታ ለገዛ ሀገራችንም ማድረግ አለብን:: እንዲያውም ልናውቀው የሚገባው ዋነኛ ጉዳይ ኳታር የፈለገ ጫና ቢደረግባት መቋቋም የምትችል ሀገር ናት:: የነዳጅ ሀብቷ የፈጠረላት የኢኮኖሚ ጉልበት አለ:: አልጀዚራን የሚያህል ግዙፍ የፕሮፓጋንዳ መሳሪያም የግሏ ነው:: ብዙ ውስጣዊ ትርምስም የለባትም:: ለዚያም ነው ባህር ተሻግራ አፍሪካ ቀንድ ድረስ የሚደርስ ፖለቲካዊ ክንድ መዘርጋት የቻለችው:: ከዚህ አንጻር ከታየ ኢትዮጵያ ኳታርን የምትበልጠው በህዝብ ብዛት ብቻ ነው:: ኢትዮጵያ በተጽእኖ ውስጥ ለመውደቅ ቅርብ ናት:: ታዲያ እኛ ግን ለተጽእኖ ቅርብ ከሆነችው ከገዛ ሀገራችን ይልቅ ተጽእኖ ተቋቁማ የአለም ዋንጫን ለማዘጋጀት ለቻለችው ኳታር አዝነናል:: ይህ አግባብ አይደለም:: እንዲያውም ለዚህ የሚስማማው አባባል አሽቃባጭ ዝናብ ወንዝ ዳር ያካፋል የሚለው ነው::
አንድ ትዝብት ልጨምር፤ የአለም ዋንጫውን የሚያስተላልፉ መገናኛ ብዙሀን ውስጥ ባሉ ጋዜጠኞች ዘንድ ያለው የእውቅት ክፍተት:: በጋዜጠኝነት ስራ አቅራቢው እና ተደራሲው በእውቀት በጣም የተቀራረቡበት ዘርፍ የስፖርት ጋዜጠኝነት ዘርፍ ነው:: ጋዜጠኛው ያለውን መረጃ ያህል አድማጩም በስልኩ ይዞ ነው የሚዞረው:: ስለዚህም ጋዜጠኛው ሰሚው የማያውቀውን ነገር ፈልጎ ማምጣት አለበት:: ነገሩ ግን እንደዛ አይደለም፤ ብዙውን ጊዜ እንዲያውም ሰሚው ከተናጋሪው ቀድሞ መረጃ ይደርሰዋል:: ይህ አሳፋሪ ነገር ይሆናል::
ስለዚህም ይህን የአለም ዋንጫ የሚያስተላልፉ ጣቢያዎች እና የስፖርት ጋዜጠኞች የአለም ዋንጫውን በርከት ላለ ጊዜ የተከታተሉ ሰዎችን ቢጋብዙ መልካም ይሆናል:: ለምሳሌ ያህል ከ1994ቱ የአለም ዋንጫ አንስቶ እስካሁን ያሉትን 7 የአለም ዋንጫዎች የተመለከቱ እና እያንዳንዱን ጨዋታ የሚያስታውሱ ሰዎች አሉ:: ጋዜጠኛ ባይሆኑም ስቱዲዮ ተገኝተው ያን ትውስታቸውን እያስታወሱ አሁን ያለውን ጨዋታ ቢያዋዙ ለተመልካቹ አዝናኝም ጠቃሚም ይሆናሉ:: ይህንን ነገር እስኪ ሚዲያዎችም አስቡበት::
አቤል ገብረኪዳን
አዲስ ዘመን ህዳር 19/2015