ከዓመታት በፊት- ልጅነት
ከስራ መልስ በእጇ ያለውን ገንዘብ ደጋግማ ትቆጥራለች ። ለዛሬ ውሎዋ በቂ ነው ። ከእሷ ይህን ያህል ካለ ሌሎች ባልንጀሮቿን አትረሳም። የያዘችውን ይዛ ከያሉበት ትፈልጋቸዋለች ። ሲገናኙ እንደ አቅሟ ትጋብዛቸዋለች። እነሱም ቢሆኑ እንደ እሷ ናቸው። ያላቸውን ይዘው፣ ያገኙትን ቋጥረው ይፈልጓታል። እንዳሻቸው ተገባብዘው የልባቸውን ሞልተው ይሸኛኛሉ ።
ጓደኛሞቹ አይለያዩም። መፈላለጋቸው ሁሌም ለአንድ ዓላማ ነው። በቀጠሮ ተገናኝተው ዋንጫቸውን ያነሳሉ። በርከት ሲሉ ግብዣው ይደራል፣ መጠጡ ይደረደራል። ጅማሬቸው ፈዘዝ፣ ቀዝቀዝ፣ እንዳለ ጥቂት ይዘልቃል ። ቆይቶ ጨዋታ ሳቁ ፣ ሞቅታው ስካሩ ይከተላል። ልክ እንደ ትናንቱ፣ እንደአምና ካቻምናው ።
ደግሞ በሌላ ቀን ሌላ ቀጠሮ ይያዛል ። ለቁምነገር አይደለም ። ለመጠጥ፣ ለጨዋታው ቀን ቀጠሮ ይቆረጣል። ሁሉም ለልምዱ ያለውን ይዞ፣ ያገኘውን ቋጥሮ ከመሸታው ይገኛል ። ድራፍት፣ ቢራው ይቀዳል፣ ሙዚቃ ዳንሱ ይደራል ። ሳቅ ጨዋታው ይደምቃል። የዛኔ ወጣትነት ትርጉሙ ፣ ልጅነት ለዛው ይታያል።
በዚህ ሰዓት ማንም ምንም አይመስለውም። የእጁ እስኪያልቅ፣ የኪሱ እኪሲደርቅ በዛሬ አናት ቆሞ ነገውን ያስባል። የነገው ንጋት ከትናንቱ አይለይም። ለሁሉም ብርጭቆ ውስጥ ተደብቆ፣ ራስን የመርሳት ቀጠሮ ነው ። ቀኑ ከመጠጥ ፣ ከጭፈራው ተዋዶ፣ መልሶ ከእነሱ ሊዛመድ ጊዜውን ሳይስት ይደርሳል ። ሁሉም ‹‹በአስረሸ ምቺው››፣ በመዝናናት ሰበብ ዕድሜ ጊዜውን ይፈጃል።
ከዓመታት በኋላ
ሲቲና ሀሰን ዛሬ ላይ ሆና የልጅነት ጊዜዋን ስታስብ ውስጧ በዥንጉርጉር ስሜት ይመላል ። የአፍላነት ዕድሜዋ ለእሷ መልከ ብዙ ሆኖ አልፏል ። የዛኔ ከትምህርት ይልቅ ማንነቷ የተሰጠው ለጉልበት ስራ ነበር። እሷን መሰል ከሆኑት ጋር በቡና ለቀማ ስራ ገንዘብ ታገኛለች ። ከምታገኘው ገንዘብ ጥቂቱን ብቻ ለእናቷ እየሰጠች በርከት ያለውን ብር በእሷ አገላለጽ ‹‹ትጨስበታለች፣ ትጨብስበታለች››
እናት ልጆቻቸውን የሚያሳድጉት ያለአባት ነው። አባወራው ከሞቱ በኋላ በቤታቸው ድህነት ሰፍኗል ። ቀድሞ የነበረው አቅም ማጣት ብሶ ቤተሰቡ ቢቸገር ወይዘሮዎ ልጆቻቸውን ለማሳደግ ጉልበታቸውን ከፈሉ። እንዲያም ሆኖ ለእሳቸው የሚያስብ አልተገኘም። ሁሉም በአፍላነት ዕድሜ ተፈተነ፣ እናትን የሚረዳ በወጉ የሚያግዝ ልጅ ጠፋ ።
ሲቲና ዛሬም ድረሰ የሚቆጫት የእናቷ ህይወት ነው፡፤እሳቸው ለልጆቻቸው መኖር ማንነታቸውን ሰጥተዋል ።ቤተሰቡ እንዳይቸገር፣እንዳይራብ ያልሆኑት የለም። እሷ ወጣትቷን ለውለታቸው አልከፈለችም። በየቀኑ መጠጣት፣ ማጨስና መቃም ልምዷ ነበር።
ዛሬ ያለፈውን ታሪክ መለስ ስትልበት ስለእናቷ አብዝቶ ይቆጫታል።በአንድ ወቅት ለደረሰባቸው የመኪና አደጋ ራሷን ተጠያቂ ታደርጋለች።በወቅቱ ህይወታቸው ቢተርፍም አንድ እግራቸውን አጥተው ነበር፡፤ከጉዳታቸው በኋላም እግራቸው አርተፊሻል ሆኖ ዓመታትን ለልጆቻቸው ዋጋ ከፍለዋል።
በወቅቱ የቤቱ ትልቅ ልጅ የቤተሰቡን ሀላፊነት ተረክቦ የሙት አባቱን ድርሻ ተወጥቷል። ታናናሾቹን እንደ ልጆቹ እያየ ፣ ወጣትነቱን፣ አፍላነቱን ቆጥቦ የቤቱ ሻማ ሆኗል። ሲቲና ግን ይህ ሁሉ አይገባትም። የእሱን ልፋት ድካም ከምንም አትቆጥርም።
ሌላው ወንድሟ እንደእሷው በሱስ የተጠመደ ወጣት ነበር ። እናት ከክፉ ባህሪይው ሊመልሱ ብዙ ታግለዋል።ከሌሎች እንዳይጋጭ፣ ሰላማዊ እንዲሆን ያልሞከሩት የለም።
ከዓመታት በኋላ ሲቲና በዕድሜ በሰለች። ይህ ጊዜ ከፍቅር ጓደኛ አጣምሮ ከትዳር፣ ቁምነገር አደረሳት። እናት አሁንም ‹‹ደክሞኛል›› አላሉም፣ፈጽሞ አልራቋትም። ከጎኗ ሆነው ፍቅራቸውን ለገሷት።የትዳሯ ቀኝ እጅ ሆነው ‹‹አለሁሽ ››አሏት።
የሲቲና የትዳር ህይወት ከአውቶቡስ ተራ ይጀምራል። ባለቤቷ የስራ ሰው ነው። ድለላ እንጀራው ከሆነ ቆይቷል። እሷን ጨምሮ አንድ ልጃቸውን በወጉ ለማሳደር ሮጦ ያድራል። ስለኑሮ አስባ አታውቅም። እናቷም ከጎኗ አልራቁም። በቸገራት እየጠየቁ፣ በጎደለው እየሞሉ፣ አብረዋት ዘለቁ ። ለሲቲና የእሳቸው መኖር ችግር ያቀላል። ከሰው ያውላል። እሷ እንዳሻት ሆና ለመግባት እናት የልብ አድርሰዋል።
ሲቲና አሁን ሁለተኛውን ልጅ አርግዛለች ። ከጎኗ ባልና እናቷ አልራቁም ፡ ያሻትን እየሞሉ፣ የጠየቀችውን ያቀርባሉ። ባተሌው ባለቤቷ ሌት ተቀን ይለፋል። ቤተሰቦቹ ያላቸው የሞላቸው ቢሆኑም ከእነሱ አይፈልግም። ለአንድ ልጁና ወደፊት ለሚወለደው ህጻን አርቆ ያስባል። የእሱ መስራት ለራሱ ቤተሰብ መድህን ነው። የእሱ መድከም ለወደፊት ህይወቱ ህይወት ነው።
ሲቲና ያለፈችበትን አትረሳም። ድህነት ለእሷ ብርቅ አይደለም። ማጣት ይሉትን አሳምራ ታውቀዋለች። እሷና ወንድሞቿ ከአጉል ባህሪያቸው ጋር ችግር ሲፈትናቸው ኖሯል። ዛሬ ላይ ሲቲ ትዳር ይዛለች። ስለቤተሰቧ እያሰበች ፣ እሷም ለጎጇዋ ታቅዳለች። ለትንሹ ልጅዋና ፣ላልተወለደው ህጻን ትጨነቃለች።
አንድቀን ግን ህልሟን የሚያጨልም፣ ውጥን ዕቅዷን የሚሰብር ክፉ አጋጣሚ አገኛት። ‹‹የቤቴ ራስ፣ ትዳሬ›› ያለችው አጋሯን ድንገቴ ሞት ነጠቃት። ቅስሟ ተሰበረ፣ ቀኗ ጨለመ። የተረገዘ ልጁን ሳየይ ሞት ስለወሰደው ባለቤቷ አምርራ አለቀሰች፣ክፉኛ አዘነች።ሲቲና ገና የስድስት ወር ነፍስጡር ናት። ድንገቴው ሀዘን ግራ አጋብቷታል። ትይዘው ትጨብጠው አጥታለች።
አሁን ለሲቲና ህይወት ቀላል አይደለም፤ ራሷንና ቤተሰቦቿን ለማኖር ልፋት ድካም ይጠብቃታል። ከዚህ በኋላ በባሏ ትከሻና ሀሳብ ማደር አይኖርም። መለስ ብላ የእናቷን ልፋት፣ ድካም አሳታወሰች። እሷና ወንድሞቿ አባታቸውን በልጅነት ዕድሜያቸው አጥተዋል፤ እናት እነሱን ለማሳደግ ብዙ ዋጋ ከፍለዋል። ጎንበስ ቀና ብለው ጎዶሎ ሞልተዋል።አሁን ደግሞ ይህ ዕጣ በእሷ ላይ ደርሷል። እናት ዛሬም ቢሆን ከጎኗ ናቸው ። ሀዘኗን ተጋርተው ‹‹አለሁሽ›› ብለዋታል። ያም ሆኖ ተዝናንታ አልተቀመጠችም። ጎዶሎውን ሞልታ የባሏን ድርሻ ለመሸፈን ፣ በጉልበት ስራ ዋለች።
ለመኖር
ሲቲና ባለቤቷ እንደሞተ ውላ አላደረችም ። በየቤቱ ልብስ ማጠብ ጀመረች፡ ይህን ለማድረግ ውሀ የሞላ ጀሪካን መሸከም፣ በምልልስ ጉልበት መክፈል ግድ ይላታል። ይህ አጋጣሚ ግን ሌላ ችግር አስከተለ፣ ነፍሰጡሯ ያለዕረፍት መድከሟ ለእሷና ለጽንሱ ጤና እክል ፈጠረ።
እርግዝናዋ ስምንት ወር እንደያዘ ሲቲና ክፉኛ ታመመች። ጠዋት ማታ ጎኗን እየሸነቆረ ምቾት ለነሳት ህመም ፈጥና ሆስፒታል ደረሰች። ሀኪም ዘንድ በቀረበች ጊዜ ህጻኑ በአቀማመጡ ቦታውን እንደለቀቀ ተነገራት። ደነገጠች ፣ አተርፍ ባይ አጉዳይነቷ ዋጋ አሰከፈላት። ወደ ጤናዋ ለመመለስ ቀናትን በቆጠረ ህክምና በስቃይ ከረመች።
ሲቲና ዘጠኝ ወር ስኪሞላት ከስራ አልራቀችም። በተገኘው ሁሉ እየገባች ጉልበቷን ትከፍላለች፤ ገንዘብ ይዛ ለመመለስ ከታዘዘችው ትውላለች።ይህ ሁሉ ሲሆን እንደ ነፍሰጡር በወጉ ‹‹ልብላ ልጠጣ›› አትልም።አንዳንዴ ርሀብ ሲጸናባት ጽንሱ አይንቀሳቀስም። እንዲህ ባጋጠማት ጊዜ ትደነግጣለች፡፤ ተመልሳ እንደማትሰራም ለራሷ ትወስናለች። ግን አትችልም።ህይወት ዳግም ያሮጣታል። አንዳንድ ልበ ቅኖች ችግሯን አውቀው ያጎርሷታል፡ ይህኔ ዛሬን ትረሳለች፤ መልሳ የነገ ውሎዋን ታስባለች፡፤
ጨለማ የዋጠው ደስታ
ክፉዎቹ የችግር ቀናት እንዳለፉ የሲቲና ሁለተኛ ልጅ በሰላም ተወለደ። ለእሷ ይህ ጊዜ ድብልቅልቅ ስሜት ነበረው። አዲሱን ልጅ ስትቀበል ከደስታዋ ሀዘኗ አመዘነ፤ ፈገግታዋን ዕንባዋ ዋጠው ፣ ሳቋን ለቅሶዋ ነጠቀው። ልጇን ታቅፋ ባሏን አስታወሰች ፣ዛሬን ከጎኗ ቢኖር የሚሆነውን እያሰበች አነባች ። ክፉኛ ሆድ ባሳት።
የባሏ ቤተሰቦች ያላቸው ፣የሞላቸው መሆኑን ታውቃለች፡፤በቅርቧ ቢገኙም ችግሯን ይዛ ፊታቸው መቆም አልፈለገችም። ጓደኞቹ ያዋጡላትን ጥቂት ገንዘብ ይዛ መሮጥ ያዘች ። በአራስ ጎኗ ልብስ ማጠብ፣አሻሮ መቁላት ጀመረች። በደረቷ ጀብሎ ይዛ ማስቲካ ከረሜላ ሸጠች።
እናቷ ልጆቿን ይይዛሉ፣ እሷ ከሌላ ስራ የተረፋትን ጉልበት በድንጋይ ሸከማ ታውለዋለች። ሰርታ ስትገባ እጇ ባዶ አይሆንም። ለቤቷና ለልጆቹ የጎደሎውን ትሞላለች፣ ሲነጋ በትናንቱ ድካም ለመመለስ ጸንታ ትቆማለች። ጥቂት ጊዜያትን እንዲህ በድካም አለፈች። እናቷ ሁሉን ትተው ከእሷ ናቸው። እሷም ለሁለቱ ህጻናት ብቸኛ ተስፋቸው ናት።
አሁን ልጇቿ ትምህርት ቤት መዋል ጀምረዋል። የእሷ መጥቆር መክሳት ለእነሱ ነውና ድካሟ ልፋ አይሰማትም።ጥቅት ቆይቶ ትንሹ ልጅ ታመመ። እናት በየቀኑ ግንባሩን እየዳሰሰች ‹‹አይዞህ›› ትለዋለች። እያደር ግን የልጁ ጉዳይ አሳሳቢ ሆነ። ህመሙ ሰላም ነሳው፤ ይዛው ሀኪም ፊት ቀረበች ። የህክምናው ውጤት በጭንቅላቱ ውስጥ የነርቭ ችግር መኖሩን አመለከተ ። ልጁ ሲጫወት የወደቀ ቢሆንም ይህን ደብቆ አልተናገረም። እንዲህ መሆኑ ለሲቲና ስጋት ሆነ ልጇን እንዳታጣው ፈራች ።የጭንቅ ዓመታት አለፉ።
ዛሬን
አሁን የሲቲና ሁለት ልጆች ወጣቶች ሆነዋል። የመጀመሪያው ሀያአንድ፣ ሁለተኛው ደግሞ አስራስምንተኛ ዓመቱን ይዟል። ሁለቱም ለስራ ደርሰዋል። እናታቸውን ለማገዝ፣ ከድካም ለማሳረፍ የሚያንሱ አይደሉም። ዛሬም ግን ሁለቱም ለእናታቸው ልጆች እንደሆኑ ነው ።
አሁንም ልጆቿን እናት ሲቲና ከትከሻዋ አላወረደቻቸውም። ዛሬም የእሷን እጅ ያያሉ። አሁንም ከእሷ ይጠብቃሉ። ሁለቱም ስለነገ ያስቡ አይመስልም። ከራሳቸው ይልቅ የእናታቸውን ትኩስ እንጀራ ይናፍቃሉ። በዕድሜቸው ከመስራት ይልቅ የእናታቸውን ጉልበት ይጠብቃሉ።
ሲቲና ግን ይህ ሁሉ ምንም መስሏት አያውቅም። ዛሬም ስለ ልጆቿ ልፋቷ ቀጥሏል። እሷም እንደ እናቷ ታትራ፣ ለፍታ በላቧ ወዝ ታሳድራቸዋለች። በጉልበቷ ድካም ታኖራቸዋለች ። ሁሌም ስለነገ ስታስብ ከልጆቿ አጣምራ ነው። እነሱን ለማስተማር ፣ ከቁምነገር ለማድረስ ሰልችቷት አያውቅም ።
አሁን ትናንት ብዙ የሆኑላት ደግ እናቷ ከጎኗ የሉም ። ስለእሳቸው ብዙ ቢቆጫትም ከመልካምነታቸው ተምራለች፤ ስለእሷ የከፈሉትን ዋጋ በልጆቿ ልትደግም፣ በራሷ ህይወት ልታሳይ ዛሬን እንደነቃች ነው ።‹‹ለላም ቀንዷ አይከብዳት›› ሆኖ ‹‹ልጆቼ ደርሰዋል፣ ይበቃኛል›› ብላ አልተወቻቸውም። ዛሬም ለእሷ ልጆች ናቸው። አሁንም ከእጇ አልወጡም፤ ከዓይኗ አልራቁም።
ሁለተኛው ልጇ በልጅነቱ የደረሰበት ጉዳት ዛሬ ድረስ ተከትሎታል።ይህ ችግር እናት ሲቲናን ሲያሳስባት ኖሯል። በቅርብ ጊዜ ያገኘው ህክምና ግን ተስፋ ሰጪ ነው። እንዲህ መሆኑ ከማንም በላይ እናትን በተስፋ አኑሯል።
ወይዘሮ ሲቲና ቤት ዛሬም ችግር ነቅሎ አልወጣም። በወር ትንሽ ደሞዝ ከሚከፈላት ቦታ የጽዳት ስራ አላት። ገቢው ሶስት ነፍሶችን አጥግቦ አያሳ ድርም። ዛሬ ቢሞላ ነገ ጎዶሎው ይበዛል። አሁን ቢገኝ ኋላ የሚያሳስብ፣ የሚያስጨንቀው ይበዛል። ሲቲና ልክ እንደትናንቱ ሩጫዋን ይዛለች።
አሁንም አስኪደክማት ትሮጣለች፤ ለመኖር በአማራጮች ሁሉ ትገኛለች። እንዲሁ ሆኖ ኑሮን ለማሸነፍ ደክሟት አያውቅም። አንዳንዴ ደግሞ ከእጅ ይጠፋል፣ ከቤት ይጎድላል፤ ልምዱ ሲቀር ፣ የታሰበው ሲጠፋ ይከፋል፤ ያስተክዛል። አጋጣሚው ባስ ሲል አይኖች ይማትራሉ። እግሮች ከአንድ ሰፍራ ያዘወትራሉ። እንዲህ መሆኑ ለጎደለው ሆድ፤ ላጣው እጅ መፍትሄ ያመጣል።
በቅርቡ በልደታ ክፍለከተማ አካባቢ የተከፈተው የምገባ ማዕከል እናት ሲቲናን የመሰሉ ወገኖችን ያስታውሳል። በራባቸው ጊዜ ጎራ ብለው ይጎርሱበታል። ቢሻቸው የያዙትን ቋጥረው ሌሎች ያቃምሳሉ። ቢያንስም ይህ ቁራሽ ዛሬን ያሳድራቸዋል። ነገን ያሻግራቸዋል።
አንዳንዶች በቀን ለአንዴ ቀምሰው የማያድሩ ምሰኪኖች ናቸው። ሮጠው መስራት፣ ያልሆነላቸው በርካቶች ደግሞ በሚያገኙት በረከት ፈጣሪያቸውን ያመሰግናሉ፤ እንደ ሲቲና አይነቶቹም ምገባውን ይመርጡታል። በዕድሜ ባይደክሙም የዕለት እንጀራው ለእጃቸውን መንጣት፣ ለቤታቸው ማጣት መፍትሄ ሆኗል። ሰርተው፣ ሮጠው ቢያድሩም እንጀራው እንጀራቸው ነው። ቀን አልፎ ፣ ነገ አስኪነጋ ተስፋቸው ሆኗልና።
መልካምሥራ አፈወርቅ
አዲስ ዘመን ኅዳር 17/ 2015 ዓ.ም