እ.ኤ.አ ከ 1914 እስከ 1918 ዓ.ም ድረስ የዘለቀውና የ15 ሚሊዮን ሰዎችን ሕይወት የቀጠፈው ጦርነት በታሪክ የመጀመሪያው የዓለም ጦርነት ተብሎ ይታወቃል። የጦርነቱ ማብቃት ሊታወጅ ጥቂት ሲቀረውና ዕልቂቱ ቆመ ሲባል ግን የዓለም ሕዝብ ሌላ ፍዳ ማስተናገድ ግድ ሆነበት። በጦርነት ተወጥሮ የቆየው ዓለም አሁን ደግሞ በእንፍሉዌንዛ በሽታ ከዳር እስከ ዳር ተጠቃ። በተለምዶ የእስፓኒሽ ፍሉ ተብሎ የሚታወቀው ይህ ወረርሽኝ መነሻው ከወደ አሜሪካ እንደሆነ ይታመናል። ይህም እ.ኤ.አ በጥር ወር 1918 ዓ.ም በአንደኛው የዓለም ጦርነት ማብቂያ ዋዜማ የተከሰተው ወረርሽኝ በመሆንም ለበርካቶች ሞት ምክንያት ሆኗል።
የታሪክ ድርሳናት ስለዚህ ወረርሽኝ ሲገልጹ በካንሳስ በሚገኘው ፉንስተን የወታደራዊ ማሰልጠኛ ማዕከል የተቀሰቀሰው ወረርሽኙ በሦስት ቀናት ብቻ 45 ሺህ የሚሆኑ ወታደሮችን ጨርሷል፤ የተረፉትም አትላንቲክን አቋርጠው አውሮፓን እንደረገጡ በሸታውም አውሮፓ ስለመድረሱ ይነገራል። የእንፍሉዌንዛ በሸታው ለመጀመሪያ ጊዜ የታየው በፈረንሳይ አገር ቢሆንም ወቅቱ የጦርነት ነበርና ለሌሎች የፕሮፓጋንዳ መጠቀሚያ ይሆናል በሚል ለሕዝብ ሳይገለጽ ተደብቆ ቆይቷል። በሽታው ይፋ የሆነው እ.ኤ.አ በኅዳር ወር 1918 ዓ.ም በስፔን አገር ነበር።
ስፔን በጦርነቱ ተካፋይ አልነበረችምና የተከሰተባትን ችግር በቶሎ ይፋ አደረገችው። በቶሎ ይፋ ማድረጓ ደግሞ በሽታው «ስፓኒሽ ፍሉ» የሚል ስያሜንም እንዲይዝ አድርጎታል፤ አሁን ዓለም ከጦርነት ወደ በሽታ ፊቱን አዞረ፤ መገናኛ ብዙኃኑ ሁሉ ስለተከሰተው በሽታ በስፋት ዘገቡ፤ አወሩ። ምን ይደረግ የሚለው ነገርም በእጅጉ አሳሳቢ ነበር። ወረርሺኙም ዓለም ላይ ለመዛመት ብዙም ጊዜ አልፈጀበትም። በኢትዮጵያም በሽታው መታየት ጀመረ። የመጀመሪያው የበሽታው ምልክት በዓለም ላይ ከታየ ከአስር ወር በኋላ ኢትዮጵያ ደረሰ። ኢትዮጵያም ችግሩ እንዳጋጠማት በኅዳር ወር 1911 ዓ.ም ይፋ አደረገች።
በዚህም ከኅዳር 7 እስከ ኅዳር 20 ቀን 1911 ዓ.ም ለአስራ አራት ቀናት ገደማ የቆየው በሽታው ብዙዎችን ፈጀ። ወረርሽኙ እስከ አርባ ሺህ ኢትዮጵያውንን ለሞት መዳረጉ ይነገርለታል፤ በአዲስ አበባ ከተማ ብቻ ዘጠኝ ሺህ ዜጎች በበሽታው መሞታቸውንም ነው መረጃዎች የሚያመለክቱት። በተለይም ኅዳር 12 ቀን 1911 ዓ.ም በርካታ ኢትዮጵያውያን የሞቱበት ስለመሆኑም ታሪክ ያወራል። ታዲያ ኢትዮጵያውያን በየወቅቱ ለሚገጥሟቸው ቸግሮች ሁሉ መፍትሔ አያጡምና ይህንን በሽታ እንዴት እንለፈው? ሲሉ መከሩ፤ በምክክራቸውም ብቸኛው ያገኙት መላ ደግሞ ሁሉም ከየቤቱና ከአካባቢው ቆሻሻን በመሰብሰብ እንዲያቃጥል፤ በጠቅላላው ቤቱንና አካባቢውን ጽዱ እንዲያደርግ የሚል ነበር።
በዚህም ኅዳር 12 ቀን በጽዳት ዘመቻ እንዲያልፍ በአዋጅ ተነገረ፣ ኅዳር በታጠነ ማግስትም በሽታው ጋብ አለ። በሂደትም ወደ መጥፋቱ ሄደ። ከዚያ በኋላ ባሉት ዓመታት ይህ ነገር እንደባህል ተወስዶ በየዓመቱ ኅዳር 12 ቀን የጽዳት ዘመቻ እየተደረገ ሁሉም በየአካባቢው ቆሻሻን ሰብስቦ እያቃጠለ ችግሩንም፣ በሽታውንም፤ በጠቅላላው መጥፎ ነገሮችን ሁሉ ከጭሱ ጋር ብን ብለው እንዲጠፉ እየተመኘ ዛሬ ላይ ደርሰናል።
አዎ ዛሬ ላይ ቆሜ እኔም ለአገሬ የምመኝላት ከኅዳሩ ጭስ ጋር ችግሮቿ ብን ብለው እንዲጠፉ፤ የእሷን መጥፋት የሕዝቦቿን መበተን የሚመኙ ሁሉ ከጭሱ በኋላ ሀሳባቸው ብን እንዲል ነው። ወትሮም ቢሆን ለችግሮቻችን ራሳችን መፍትሔ ማስቀመጥ የማይሳነን እኛ ዛሬም ለተፈጠረብን ወደፊትም ሊፈጠርብን ለሚችለው ችግር ሁሉ ከዛሬ 104 ዓመት በፊት የወሰድነውን ዓይነት መፍትሔ መውሰድ ይገባናል።
በእርግጥ ችግራችንን በራሳችን አቅም ለመፍታት የምንችል ሕዝቦች መሆናችንን ባለፉት ሁለት አመታት በተፈጠረብን ችግር አሳይተናል። አሁን ላይ ያለንን አቅም የዓለም ኃያላን ነን ባዮችም የተገነዘቡት ይመስለኛል። የሰላም አማራጭን ከመረጥን በኋላም ቢሆን እኛ ካልገባንበት እናንተ ለራሳችሁ ሰላም ማምጣት አትችሉም በማለት ያሾፉብንንም ጥቂት አፍሪካውያን ወዳጆቻችንን ይዘን በድል አጠናቀነዋል፤ ምክንያቱም ሲወርድ ሲዋረድ አብሮን የቆየ ችግር መፍቻ ብልሃት ስላለን ነው። አሁንም ይህ አቅማችን በደንብ ዳብሮ የሄድንበት ርቀትም መስመር ይዞ ይቅርታና ሰላማችን ከልባችን ሆኖ ስለልጆቻችን ብለን መጪውን ጊዜያችንን ብሩህ ማድረግ ይገባናል።
ከዛሬ 104 ዓመት በፊት አቅም ያላቸውን የዓለም አገራትን እንኳን ፈትኖ ያልቻሉት በሽታ አገራችንም ገብቶ ሕዝብን ሊፈጅ አገርን ባዶ ሊያስቀር ቆርጦ ሲነሳ ብልሆቹ የእኛዎቹ ኢትዮጵያውያን እናትና አባቶቻችን በብልሃት ችግሩን እኛው በእኛው ብለው በወሰኑት መሠረት ኅዳርን አጥነው በጭስ አስፈሪውን ደዌ አባረውታል፤ መጥፎውን ጊዜም በድል ተወጥተውታል። ይህ አኩሪ ነገር እነሆ በታሪክ ተመዝግቦ ይገኛል።
ኅዳር ሲታጠን…
የኢትዮጵያ ሰማይ በበረከት ይታወድ…
በምድሯም ሁሉ የምር የሆነ እርቅ ይውረድ…!
አሜን…! አሜን..! ይሁን…!
እያልን የምር የሆነውን እርቃችንን ከልባችን አውርደን አገራችንን ወደፊት የምትሄድበትን መንገድ ማመቻቸቱ ደግሞ ከእኛ ከዛሬዎቹ ተማርን ተመራመርን አወቅን መጠቅን ከምንለው ልጆቿ የሚጠበቅ ነገር ነው።
ኅዳር ወር ሲታጠን ችግር መከራው ይሄዳል፤ ይህንንም ታሪክ አስተምሮናል። ከኅዳር ቀጥሎ የሚመጡት ወራቶች ደግሞ የሚያጓጉ ምድር በረከቷን አብዝታ የምትሰጥበት በጠቅላላው ጥጋብ በምድር ለይ የሚሰፍንበት ስለመሆኑ ደግሞ ኢትዮጵያዊ የሆነ ሁሉ የሚያውቀው ሃቅ ነው። ታዲያ ኅዳርን አጥነን ችግራችንን አባረን የዘራነውን አጭደን ከምረን ወቅተንና ጎተራ ከተን ሰርግ ደግሰን ዘመድ አዝማድ ጠርተን ብሉልኝ ጠጡለኝ የምንባባልበት ሁኔታ ይፈጠር ዘንድ እርቃችንን የምር እናድርገው።
ዛሬ አገር የደከመች፣ እኛም የተጣላን መስሏቸው በእሳት ላይ ቤንዚን ለማርከፍከፍ ደፋ ቀና የሚሉቱ ምን ብናደርግ ይታመሳሉ ብለው እንቅልፍ የሚያጡት ባሳየናቸው አንድነትና ሰላም ወዳድነት አንገታቸውን ደፍተዋል። ነገር ግን እነዚህ ኃያላን ሽንፈታቸውን አምነው የሚቀመጡም አይደሉምና አሁንም ነቅተን እርቃችንን ከልባችን አድርገን ማሳየት ይገባናል። ያን ጊዜ እንደልባችን መንጻት ሆኖ የኅዳር ጭስ ችግራችንን ይዞ ብን ይላል። አበቃሁ፤
ሰላም!
በእምነት
አዲስ ዘመን ኅዳር 16/ 2015 ዓ.ም