የሠራሽ ምሕረት ከተወለደች ጀምሮ ዓይነሥውርና መስማት የተሳናት ናት፡፡ የሰራሽ አሁን የ15 ዓመት ታዳጊ ብትሆንም የኑሮ አለመመቸት ብሎም የሚረዳት ማጣት እስከ ቅርብ ጊዜ ድረስ ባለችበት ቁጭ ብላ እንድትውል አድርጓታል፡፡ ይህ ሁኔታ ደግሞ እግሮቿ እንደልባቸው እንዳይንቀሳቀሱ እንዲሁም የህይወት ክህሎት የሚባሉትን ራስን ችሎ መመገብ፣ መልበስ፣ መጸዳዳትና ሌሎችንም እንዳታውቅ አድርጓት ቆይቷል፡፡ ይህ ሁኔታ ደግሞ ማንኛውንም የምታከናውናቸውን ነገሮች በሰዎች እርዳታ እንዲሆን አስገድዷል፡፡
የሠራሽን የሚፈታተናት የቤተሰቦቿ አቅመ ደካማነት ብቻ ሳይሆን ዓይነ ሥውርና መስማት የተሳናቸው (ተደራራቢ የአካል ጉዳት ያለባቸው) ምን ዓይነት ድጋፍ እንደሚሹ አለማወቃቸውም ጭምር ነው፡፡ ምግብና መጠጥ ስትፈልግ፣ መፀዳዳት ሲኖርባት ወይም ስትታመም የምትገልጽበትን መንገድ አይረዱላትም፡፡ ከቤተሰቦቿ ከእናቷና ታላቅ እህቷ ጋር ትግባባለች፡፡ነገር ግን ሰው ስላለመደች ሌሎች ሰዎች ሲቀርቧት ትፈራለች፡፡ ፍላጎቷን የሚገነዘብላት ስታጣ ራሷን ትነክሳለች፣ ዕቃም ትሰብራለች።
እናቷም ሆኑ ሌሎች ቤተሰቦቿ የሰራሽ ልጃቸውን የመሰሉ ተደራራቢ የአካል ጉዳት ያለባቸው እንዳሉ ባለማወቃቸው ምክንያት ፈጣሪያቸውን ያማርሩም ነበር፡፡ ችግሯን ተረድተው መርዳት መቸገራቸው ደግሞ ይበልጡኑ ያስከፋቸዋል ፡፡ ከዓይነሥውራን ወይም መስማት ከተሳናቸው አብዛኞቹ መማር ቢችሉም ተደራራቢ የአካል ጉዳት ያለባቸው በመሆኑ ዕድሉን አያገኙም፡፡ የሠራሽ ከልጅነቷ አንስቶ ብትደገፍ እንደሌሎች ልጆቻቸው ትሆን እንደነበር እናቷ ቢያምኑም በማንና እንዴት ልትደገፍ እንደምትችል ደግሞ እርግጠኛም ሳይሆኑ ኖረዋል ፡፡
ቢዘገየም የሰራሽ አሁን ላይ ዓይነሥውራንና መስማት የተሳናቸው ማኅበርን በመቀላቀሏ ብዙ ለውጦችን አምጥታለች፡፡ በበትር እየታገዘች መንቀሳቀስ፣ በራሷ መመገብና የምትፈልገውን መግለጽ የምትችልባቸው መንገዶች በሥልጠና በማግኘቷም የተወሰነ ለውጥ እየታየባት ነው ፡፡ነገር ግን የሰራሽ የምታገኛቸውን ስልጠናዎች ከማዕከሉ ወጥታ ቤት በምትሄድበት ጊዜ ለመተግበር ትቸገራለች፤ ምክንያቱ ደግሞ የመርጃ መሳሪያዎቹን በቅርብ ማግኘት ስለማትችል ነው፡፡ ይህም ቢሆን ግን አሁን ላይ ከቀድሞ ሁኔታዋ የተለየ ሆናለች ፡፡
ዓይነሥውር ናትና የመስማት እክል ከውልደት አንስቶ ወይም ከጊዜ በኋላ ሊገጥም ይችላል፡፡ ጉዳቱ ሙሉ በሙሉ መስማትና መናገር የማይችሉ፣ ነገር ግን በከፊል የሚያዩ፣ በከፊል የሚሰሙና ሙሉ በሙሉ ማየት የማይችሉና በከፊል የሚያዩና በከፊል የሚሰሙትን ያካትታል፡፡ የተለያየ አካል ጉዳት ያለባቸውን ሰዎች የሚያሰባስቡ ማኅበራት ከተቋቋሙ አስርተ ዓመታትን ቢያስቆጥሩም ተደራራቢ የአካል ጉዳት ያለባቸው ማኅበር የተመሠረተው ግን በ1996 ዓ.ም ነው፡፡
ሰባ ደረጃ አካባቢ የሚገኘው የኢትዮጵያ ማየትና መስማት የተሳናቸው ብሔራዊ ማኅበር የሠራሽን ለመሰሉ ሥልጠና ይሰጣል፡፡ ታዳጊዎች ራሳቸውን እንዲችሉ የሚረዳ የክህሎት ሥልጠናና አዋቂዎች የሙያ ሥልጠና እንዲያገኙ ይደረጋል ፡፡ ሹራብና ብሩሽን የመሰሉ መገልገያዎች መሥራት ይማራሉ፡፡ ተደራራቢ የአካል ጉዳት ያለባቸው መሥራት አይችሉም የሚለውን የተሳሳተ አመለካከት ለመቅረፍ የሚያስችልም ስለመሆኑ በራሳቸው አንደበት ይናገራሉ፡፡
ወይዘሪት ሮማን መስፍን የማኅበሩ መሥራችና ዳይሬክተር ናቸው፡፡ ሮማን በቀኝ ጆሮአቸው በቅርበት ሲያነጋግሯቸው ይሰማሉ ፡፡ የአራት ዓመት ሕፃን እያሉ በመውደቅ ምክንያት ዓይናቸው ጠፍቶ ሰበታ የዓይነ ሥውራን ትምህርት ቤት እያሉ ደግሞ የጆሯቸው የመስማት ብቃት መቀነሱንም ይናገራሉ፡፡
ዓይነሥውራንና መስማት የተሳናቸው የሚገጥማቸው ውጣ ውረድ ለመቀነስ ማኅበሩን ከሌሎች ዓይነሥውራንና መስማት የተሳናቸው እንዲሁም ያልተጎዱ አጋዥ ግለሰቦች ጋር አቋቁመዋል፡፡ ከዓይነሥውራንና መስማት የተሳናቸው ልጆቻቸው ጋር መግባቢያ መንገዶችን የማያውቁ ቤተሰቦች በርካታ መሆናቸውና ዘመን አመጣሽ መሣሪያዎች በቀላሉ አለመገኘታቸው ተጎጂዎች በየቤታቸው እንዲቀሩ አድርጓቸዋል ይላሉ ፡፡
ተደራራቢ የአካል ጉዳት ያለባቸው ከሌሎች ከሚግባቡበት መንገድ አንዱ ታግ ታይል (በእጅ መዳሰስ) ነው፡፡ በተጨማሪ የብሬል ታግታይል (በእጅ ብሬል እየዳሰሱ) መግባባት ይቻላል፡፡ በከፊል ማየት የሚችሉ የምልክት ቋንቋ ይጠቀማሉ፡፡ ከአጋዥ መሣሪያዎች መካከል ፐርኪንስን ታይፕ (በአስተርጓሚ ታግዞ የሚነበብበትና ምላሽ የሚሰጥበት) አንዱ ነው፡፡
ሙሉ በሙሉ ዓይነሥውር የሆኑና መስማት የተሳናቸው ለመንቀሳቀስ የሚረዳቸው ሚኒ ጋይድ የሚባል መሣሪያ አለ፡፡ በአንድ እጃቸው በትር ይዘው ሲጓዙ አቅጣጫቸውን እንዲያስተካክሉ ሚኒ ጋይዱ ቫይብሬት እያደረገ ይመራቸዋል። ሮማን እንደሚሉት ፣ ከነጭ በትር፣ ብሬልና መስማት የሚያግዝ (ሒሪንግ ኤይድ) ውጪ ሌሎች መሣሪያዎች በቀላሉ አይገኙም፡፡
በቅርብ ወደ ኢትዮጵያ የመጣችው ኢትዮጵያዊት አሜሪካዊት ሀበን ግርማ የምትጠቀምበት ብሬል ዲስፕሌይ የተባለ መሣሪያ ነው፡፡ ሀበን ከሐርቫርድ ዩኒቨርሲቲ በሕግ የተመረቀች ዓይነሥውርና መስማት የተሳናት የአካል ጉዳተኞች መብት ተሟጋች ናት፡፡ ከሐርቫርድ ምርጥ 20 ሕግ ተማሪዎች አንዷም ናት፡፡ ሮማን እንደሚሉት ፣ እንደ ሀበን ዕድሉን ያገኙ በጣት የሚቆጠሩ ሲሆኑ፣ አጋዥ መሣሪያ ማግኘት አንዱ የለውጥ መጀመሪያ ነው ይላሉ፡፡ ማኅበሩ መሣሪያ በዕርዳታ ሲያገኝ በየክልሉ ቢያካፍልም የመሣሪያው ውድነት እንደሚፈለጉት እንዳይዳረስ ያግዳቸዋል፡፡
እንደ ዳይሬክተሯ ገለጻ፣ ማኅበሩ ሥራ ሲጀምር በየክልሉ ጉዳተኞችን ያሰባስቡ ነበር፡፡ ስለ ጉዳቱ የጠለቀ ዕውቀት ባለመኖሩ አንዳንዶች ቤት ውስጥ ታስረው ተቀምጠው ነበረ፡፡ ከእንቅስቃሴ ታግደው የነበሩ ልጆችን መሠረታዊ ክህሎት ለማስተማር ጊዜ ወስዷል፡፡ አሁንም ከየቤቱ የተደበቁ አካል ጉዳተኞች ዕርዳታ እንዳላገኙ ያስረዳሉ ፡፡ ዓይነ ሥውራንና መስማት የተሳናቸው ፍላጎቶቻቸውን ማሟላት እንዲሁም መደበኛ ትምህርትና ሥራ የሚያገኙበትን መንገድ ማመቻቸት የመንግሥትም ግዴታ ነው ይላሉ ፡፡
‹‹እንደማንኛውም ሰው የሚያስፈልጋቸው ተሟልተ ውላቸው በነፃነት የመኖር መብታቸው መጠበቅ አለበት፡፡ ከውልደትም ይሁን ከጊዜ በኋላ አደጋው ሲከሰት ማግለል ሳይሆን እንደማንኛውም ሰው ማኅበራዊ ሕይወታቸው በተመቻቸ መንገድ መምራት አለባቸው፤›› ባይ ናቸው፡፡
ተደራራቢ የአካል ጉዳት ያለባቸው ግለሰቦች ቤተሰቦች ከፍተኛ ኃላፊነት እንዳለባቸው አያይዘው የሚገልጹት ዳይሬክተሯ፤ ሁሉም የድርሻውን ከተወጣ ማህበሩም ያለበት የበጀት እጥረት ይፈታል የበጀት እጥረቱ ተወገደ ማለት ደግሞ በየክልሉ ቅርንጫፍ ከፍቶ ዕርዳታ መስጠት ይችላል በማለት ሁኔታውን ያብራራሉ፡፡
ተደራራቢ የአካል ጉዳት ያለባቸውን የሚወክልና ድምፃቸውን የሚሰማ የለም፤ማኅበሩን የሚደግፉ ተቋሞች ቢበራከቱ ቢያንስ መሠረታዊ የክህሎት ሥልጠና ለሕፃናት መስጠት ይቻላል ፡፡ አሁን የሚሰጠው አገልግሎት በአገሪቱ ካሉት ጉዳተኞች ቁጥር አንፃር አናሳ ነው፡፡
ዓይነሥውርና መስማት የተሳናቸው ልጆች ያሏቸው ቤተሰቦች ባለማወቅ ልጆቻቸውን መሠረታዊ የአኗኗር ክህሎት ሳያስተምሩ ይዘገያሉ፡፡ ይህ ሊቀረፍ የሚችለው በአፋጣኝ ወደ ባለሙያ በመሄድ ክህሎቱን እንዲማሩ በማድረግ ሲሆን ተደራራቢ የአካል ጉዳት የሚገባውን ያህል ሰፊ ትኩረት እንዳላገኘ በመግለጽ ስለ ሌሎች የአካል ጉዳቶች ያለው ግንዛቤ አነስተኛ ሆኖ ሳለ ብዙም ያልታወቀውን ተደራራቢ ጉዳት ለመቀበል ለኅብረተሰቡ ያዳግታል ይላሉ፡፡
የቀለም ትምህርት ለማግኘት በከፊል መስማት ወይም በከፈል ማየት የሚችሉ የተሻለ ዕድል አላቸው ፡፡ ተደራራቢ አካል ጉዳት ያለባቸው ሰዎች ግን እንደማንኛውም ሰው መኖር እንዲችሉ የማኅበረሰቡ ቀና አመለካከት የግድ መታከል አለበት ፡፡
‹‹ዓይነ ሥውራንና መስማት የተሳናቸው ተደራራቢ ጉዳታቸው ሕይወታቸውን ፈታኝ ያደርገዋል፡፡ በዳሰሳ ወይም በሌላ መንገድ የመግባባት ልምዱ ስለሌለ አንዳንዴ መፈጠራቸውን እስኪጠሉ ይማረራሉ፤ በአደባባይ ወጥተው ከሚታዩ ተደራራቢ የአካል ጉዳት ሰለባዎች ቁጥር ቤተሰቦቻቸው በየጓዳው የደበቋቸው ይበልጣሉ፡፡ ችግሩን የመቅረፍ ኃላፊነት የእያንዳንዱ ግለሰብ ነው፡፡ አካል ጉዳት አማክሮ አይመጣም በማንም ላይ ሊደርስ ይችላል፤›› በማለት ነግ በኔ ብሎ ማሰብ ተገቢ እንደሆነ ያሳስባሉ፡፡
እፀገነት አክሊሉ
አዲስ ዘመን ሐሙስ ኅዳር 15 ቀን 2015 ዓ.ም