ባለፈው ሳምንት የስነ ጽሑፍ ባለሙያዎችን አስተያየትና ማብራሪያዎች መሠረት አድርገን ስለ ምሳሌያዊ አነጋገሮች አውርተናል። ስለ ፈሊጣዊ አነጋገሮች እንመለስበታለን ባልነው መሠረት እነሆ ዛሬ ስለ ፈሊጣዊ አነጋገሮች ምንነት እናወራለን።
ለእንግሊዝኛ ቋንቋ የምንሰጠውን ትኩረት ያህል ለአገር ውስጥ ቋንቋዎች አንሰጥም። በዚህም ምክንያት ቋንቋዊ የሆኑ ነገሮች ልብ አይባሉም፤ የአገር ውስጥ ቋንቋ አለማወቅ እንደ አለማወቅ አይቆጠርም። እንደ አለማወቅ የሚቆጠረው እንግሊዝኛ አለማወቅ ነው። የእንግሊዝኛ አጻጻፍ የተሳሳተ ሰው ብዙ ይሳቅበታል፤ በአገር ውስጥ ቋንቋ መሳሳት ግን እንደምንም አይቆጠርም።
እርግጥ ነው ቋንቋ በራሱ እውቀት አይደለም፤ ዳሩ ግን የውጭ ቋንቋዎች በየዘርፉ የተብራራና የተደራጀ ማብራሪያ ሲኖራቸው የአገር ውስጥ ቋንቋዎቻችንም ሊኖራቸው ይገባል።
ፈሊጣዊ አነጋገር ብዙ ሰው ልብ የሚለው አይደለም። ፈሊጣዊ ንግግሮቹን በልማድ እንጠቀማቸዋለን፤ ፈሊጣዊ ንግግር ምንድነው? ቢባል ግን ለማብራራት እንቸገራለን።
ፈሊጣዊ ንግግር በእንግሊዝኛው ‹‹Idiom›› የሚባለው ነው። Idiomatic Speech/ Expression ይሉታል። በእነዚህ ቃላት ላይ እጅግ ብዙ ማብራሪያዎችን እናገኛለን፤ በአማርኛው ሲሆን ግን አናገኝም።
በ1983 ዓ.ም በደራሲ ዳኛቸው ወርቁ እና አምሳሉ አክሊሉ የተጻፈ እና በኩራዝ አሳታሚ ድርጅት የታተመ ‹‹የአማርኛ ፈሊጦች›› የሚል መጽሐፍ አለ። መጽሐፉ ከመግቢያው እንደሚነግረን በእንግሊዝኛ ቋንቋ ላይ እንጂ በአማርኛ ቋንቋ ፈሊጣዊ ንግግሮች ላይ የተጻፉ መጻሕፍትና ማብራሪያዎች የሉም። መጽሐፉን ለመጻፍ ያነሳሳቸውም ይህን ችግር ተረድተው ነው። ከዚህ መጽሐፍ እና ሌሎች የእንግሊዝኛ ማብራሪያዎች ባገኘነው መረጃ ፈሊጣዊ ንግግር ምንድነው? የሚለውን እንመልከት።
ፈሊጣዊ ሐረጋት ወይም ዓረፍተ ነገሮች የሚፈጠሩት ከሁለት ቃላት ጥምረት ነው። የፈሊጣዊ ንግግር ትርጉም በቃላቱ መሠረታዊ ትርጉም አይደለም። የቃላቱ መሠረታዊ ትርጉም ማለት እነዚያ ቃላት የቆሙለት የተለመደው (እማሬያዊ) ትርጉማቸው ማለት ነው። ፈሊጣዊ አነጋገር የሚፈጠረው ከእነዚህ ቃላት መሠረታዊ ትርጉም ባህሪ በመነሳት ሌላ ተደራቢ ትርጉም ለመስጠት ነው። ግልጽ ለማድረግ በምሳሌ ይሁን።
‹‹የግንባር ሥጋ›› የሚባል ፈሊጣዊ ንግግር አለ። ይህ ሐረግ የተፈጠረው ግንባር እና ሥጋ ከሚሉ ቃላት ነው። ሁለቱም ቃላት መሠረታዊ (የተለመደው እማሬያዊ ትርጉም ማለት ነው) አላቸው። ግንባር የጭንቅላታችን የፊት ክፍል ሲሆን ሥጋ ደግሞ የእንስሳትም ሆነ የሰው አጥንትን የሚሸፍነው ክፍል ማለት ነው።
ከእነዚህ ቃላት የተፈጠረው ‹‹የግንባር ሥጋ›› የሚለው ፈሊጣዊ ንግግር ‹‹ደፋር፣ ጀግና፣ ግልጽ›› የሚል መልዕክት የሚያስተላልፍ ነው። ይህ ትርጉም የተሰጠው ደግሞ ሐረጉን ከፈጠሩት ቃላት ባህሪ በመነሳት ነው። ግንባር ፊት ለፊት የሚገኝና ማንም በቀላሉ የሚያየው የሰውነት ክፍል ነው፤ የሚደበቅ አይደለም። ግንባር ላይ ያለ ሥጋ ጠንካራ ነው። ስለዚህ አንድ ግልጽ እና ደፋር የሆነ ሰው ‹‹የግንባር ሥጋ›› ይባላል። ይሄ ማለት ግንባር ላይ ያለውን ሥጋችንን እየገለጽን ሳይሆን የሰውየውን ግልጽ ተናጋሪነትና ድፍረት እየገለጽን ነው ማለት ነው።
ፈሊጣዊ ንግግር ቃላት መጀመሪያ ከቆሙለት እሳቤ በመነሳት ተመሳሳይ ለሆኑ ሌሎች እሳቤዎች ይውላል ማለት ነው።
እዚህ ላይ ልብ ማለት ያለብን አንድ ነገር አለ። የምሳሌያዊ ንግግሮች እና ፈሊጣዊ ንግግሮች ባለቤት የጥንቱ ማህበረሰብ ነው። በዚህ ማህበረሰብ ውስጥ የሚታሰቡ እሳቤዎች አንዳንዶቹ ልማዳዊ ናቸው፤ በሳይንስ ካሰብነው ላይመጣጠን ይችላል። ለምሳሌ ሆድ እና ልብ የማሰቢያ ክፍል ተደርገው ነው የሚታሰቡት። ‹‹ነገር በሆዱ ይዞ›› ይላሉ። ሀሳብ የሚያብሰለስለው ሆዱ ውስጥ ነው ተብሎ ስለሚታሰብ ነው።
በዚህ መሠረት ‹‹ሆደ ሰፊ›› የሚለውን ፈሊጣዊ ንግግር እንውሰድ። ሆደ ሰፊ የተባለበት ምክንያት ሰው የሚያስበው በሆዱ ነው ተብሎ ይታሰብ ስለነበር አስተሳሰቡ ሰፊ የሆነ፣ ቻይ፣ ታገሽ ለማለት ነው። በጥሬው እንተርጉመው ከተባለ ደግሞ ‹‹ሆደ ሰፊ›› ሲባል ምናልባትም ሆዳም (ብዙ የሚመገብ) ለማለት ሊመስል ይችላል። በፈሊጣዊ ንግግር ግን ሆደ ሰፊ ማለት ቻይ ወይም ታጋሽ ማለት ነው።
በዚሁ እግረ መንገድ ስለ እማሬያዊና ፍካሬያዊ ፍቺ(ትርጉም) እናውራ። እማሬያዊ ትርጉም ማለት የአንድ ቋንቋ ቃል መጀመሪያ የታሰበለትና በመደበኛነት የሚያገለግልበት ትርጉም ማለት ነው። ፍካሬያዊ ፍቺ ማለት ደግሞ ከዋናው ቃል በመነሳት ሌላ ተደራቢ ትርጉም ሲሰጠው ማለት ነው። ለምሳሌ፤ እሳት የሚለው ቃል የሚገልጸው ለማብሰያነት፣ ለማቀጣጠል፣ ብርድን ለማስለቀቅ የምንሞቀው በአጠቃላይ የሚነደውን እሳት ይገልጻል። ከእሳት ባህሪ በመነሳት ግን እሳት የሚለው ቃል ሌላ ተደራቢ ትርጉም ይሰጠዋል። ይሄውም ኃይለኛ፣ አስፈሪ፣ የማይነካ ማለት ነው። ገበያ እንኳን ሲወደድ ‹‹እሳት ሆነ›› ይባላል፤ የማይነካ ማለት ነው።
ከዚህ በመነሳት ፈሊጣዊ ንግግሮች ይፈጠራሉ። ለምሳሌ፤ ዓይን ያው ዓይን ነው፤ ለማየት የምንጠቀምበት የሰውነት ክፍል ማለት ነው። ከዚህ በመነሳት ግን የመርፌ ዓይን፣ የእንጀራ ዓይን የሚሉ ፈሊጣዊ ንግግሮች ይፈጠራሉ። መርፌም ሆነ እንጀራ ግዑዝ አካል ናቸው፤ አያዩበትም።
ቀደም ሲል እንዳልነው የፈሊጣዊ ንግግሮች ፈጣሪዎች የጥንቱ ማህበረሰብ ነው። ስለዚህ ቃላቱም የቆዩ እና ምናልባትም አሁን አገልግሎት ላይ የሌሉ ሊሆኑ ይችላሉ። ለምሳሌ ‹‹ቆሌ›› የሚለው ቃል ያገለግል የነበረው የጣዖት አምልኮ (ውቃቢ) በነበረበት ጊዜ ነው። አሁንም ድረስ ግን ‹‹ቆሌዬን ገፈፈው!›› የሚባል ፈሊጣዊ አነጋገር አለ። አስደነገጠኝ፣ ክብሬን አሳጣኝ፣ አቀለለኝ እንደማለት ነው። ቆሌ ቢስ ማለት ደግሞ ያልተረጋጋ፣ ችኩል፣ ቀላል ማለት ነው።
የፈሊጣዊ ንግግሮች አስፈላጊነትና ጥቅም ሀሳብን በተዝናና መንገድ ጥልቅ መልዕክት ማስተላለፍ ነው። ሰዎች በባህሪያችን በጣም ግልጽ ከሆነ ነገር ይልቅ ትንሽ ሸፈን ያለ ነገር መተርጎም እንወዳለን። ከስብሰባዎች እና ከመድረክ መልዕክቶች ይልቅ በኪነ ጥበብ መልክ የሚሠሩ መልዕክቶች አይረሴ የሚሆኑት ለዚህ ነው። ውስጠ ወይራ የሆኑ ነገሮች ወደ ሰዎች አዕምሮ ውስጥ ሰርስሮ የመግባት ኃይል አላቸው።
የቋንቋና ሥነ ጽሑፍ ባለሙያዎች እንደሚሉት፤ ፈሊጣዊ ንግግሮችን በቀላሉ የሚረዷቸው ቋንቋውን የተላመዱ ሰዎች ናቸው። አለበለዚያ በጥሬው (Literally) ሊተረጉሙት ይችላሉ። ለዚህም ነው አንድ በሌላ ቋንቋ አፉን የፈታ ሰው የአማርኛ ፈሊጣዊ ወይም የምሳሌያዊ ንግግር ቃላት ሲናገር ‹‹ቅኔ እየፈለጠ ነው›› የሚባል። ከመደበኛዎቹ ቃላት አልፎ ፈሊጣዊ ቃላትን ከተናገረ ያ ሰው ቋንቋውን ተላምዶታል ማለት ነው። ያ ባይሆን ኖሮ ‹‹ሆደ ሰፊ›› ሲባል ሆዱ ትልቅ የሆነ ወፍራም ሰው ይመስለው ነበር።
ፈሊጣዊ ንግግሮችን የሥነ ጽሑፍና የጥበብ ሰዎች ብቻ ሳይሆን ፖለቲከኞችም በየመድረኩና በየመገናኛ ብዙኃኑ ይጠቀሟቸዋል። ንግግራቸውን ለዛ ስለሚያላብሰው እና መልዕክቱን በጥልቀት ስለሚያስተላልፍላቸው ነው። እገሌ ንግግር አይችልም ወይም ሲናገር ይዘባርቃል ከማለት ይልቅ ‹‹የምላስ ወለምታ›› በሚል ሊገለጽ ይችላል። ሌባ ላለማለት የእጅ አመል ሊባል ይችላል።
የፈሊጣዊ ንግግሮች ቃላት በግልጽ እንደሚታየው የውስጥም ሆነ የውጭ የሰውነት ክፍሎቻችን ላይ የሚያተኩሩ ናቸው። ይህ ነገር በአማርኛ ቋንቋ ብቻ ነው ወይስ በሌሎች ቋንቋዎችም ያለ ነው? የሚለውን ደራሲ ዳኛቸው ወርቁ እና አምሳሉ አክሊሉ በወቅቱ ዳሰሳ አድርገዋል። ልክ እንደ አማርኛው ሁሉ በኦሮምኛም ያገኙት ተመሳሳይ ነገር ነው። በሌሎች የውጭ አገራት ቋንቋዎች ላይ ተመሳሳይ ነገር ይኖር ይሆን? የሚለውን ለሌሎች አጥኚዎች ጥቆማ ሰጥተዋል።
የፈሊጣዊ ንግግሮች አካል ክፍል ላይ ማተኮር በውጭ አገራት ቋንቋዎችስ ምን ያህል ይታወቅ ይሆን ብዬ ሳስስ ‹‹Idiomatic expressions with body parts in English and French›› በሚል ርዕስ በአውሮፓውያኑ 2020 የተሠራ ጥናት አገኘሁ።
በጥናት ትንታኔው ውስጥ፤ እግር፣ ክንድ፣ አንጎል፣ ጆሮ፣ ዓይን፣ ፊት፣ ጣት፣ ጫማ እግር(Foot)፣ ፀጉር፣ እጅ፣ ጭንቅላት(ራስ)፣ ልብ፣ ተረከዝ(Heel)፣ አንገት፣ አፍንጫ፣ ቆዳ፣ ጥርስ፣ ምላስ… የሚባሉት የሰውነት ክፍሎች ተጠቅሰዋል። እያንዳንዳቸው የተጠቀሱት ራሳቸውን ችለው ርዕስ ሆነው ነው። በአንዱ የሰውነት ክፍል ብቻ በእንግሊዝኛም በፈረንሳይኛም ብዙ ፈሊጣዊ ንግግሮች አሉ። ስለዚህ በውጭ ቋንቋዎችም ፈሊጣዊ ንግግሮች የሰውነት ክፍል ላይ ያተኩራሉ ማለት ነው።
በነገራችን ላይ የእነ ዳኛቸው ወርቁ መጽሐፍ የተጻፈው በ1979 ዓ.ም (የመጀመሪያው ዕትም) ነው። በዚህ ወቅት ደግሞ የበይነ መረቡ ዓለም አልነበረም።
ወደ አማርኛ ፈሊጣዊ ንግግሮች ስንመጣ ከላይ በእንግሊዝኛና ፈረንሳይኛ በተዘረዘሩት የሰውነት ክፍሎች ሁሉ ፈሊጣዊ ንግግር አለ። ለምሳሌ፤ እጄ ሰባራ (ሙያ የሌለው)፣ ፀጉረ ልውጥ (የአካባቢው ሰው ያልሆነ)፣ ልበ ደንዳና (ግደለሽ)፣ እግረ እርጥብ (ዕድለኛ)፣… እያልን ብንቀጥል በአንዱ የሰውነት ክፍል ብቻ ብዙ ፈሊጣዊ ንግግሮች አሉ።
ወደ ውስጥ የሰውነት ክፍል እንኳን ብንገባ፤ ሀሞታም(ጎበዝ)፣ ሀሞተ ቢስ(ፈሪ)፣ ሀሞቱ የፈሰሰ(ሰነፍ) የሚሉትን እናገኛለን።
ለምን የሰውነት ክፍሎቻችን ላይ አተኮሩ? ለሚለው ለጊዜው በጥናት የተደገፈ መረጃ አላገኘሁም። እስከዚያ ግን መገመት እንችላለን። የሰውነት ክፍሎቻችን ተግባራቸውን በቅርበት የምናውቃቸውና በየድርጊቱ የምናያቸው ናቸው። ስለዚህ ክስተቶችን ሁሉ በእነርሱ ለመመሰል ቀላል ነው። ቀደም ባለው ዘመን እንዲህ እንደ አሁኑ የረቀቀ ቴክኖሎጂ አልነበረም። ስለዚህ ነገሮችን የምናነፃፅረው አጠገባችን ባሉት እንስሳት እና ከራሳችን የሰውነት ክፍሎች ድርጊት ጋር በማመሳሰልና በማነፃፀር ነው።
ለእንግሊዝኛ ቋንቋ የምንሰጠውን ትኩረት ያህል ለአገራችን ቋንቋዎችም እንስጥ! የራሳችንን ቋንቋ ማወቅ እንግሊዝኛ እንዳናውቅ አይከለክልም፤ እንዲያውም የበለጠ ያቀርባል። ‹‹የቋንቋ ትምህርት ክፍል፣ የቋንቋ ተማሪ›› ሲባል የግድ የአንድ ቋንቋ ማለት አይደለም። እንግሊዝኛ ቋንቋ ላይ መራቀቅ አማርኛን በቀላሉ እንድንረዳ ያደርጋል እንጂ እንዲከብደን አያደርግም። ምክንያቱም የቋንቋው ባህሪያት ተመሳሳይነት ይበዛቸዋል። ስለዚህ ለአገራችን ቋንቋዎችም ትኩረት እንስጥ!
ዋለልኝ አየለ
አዲስ ዘመን ሐሙስ ኅዳር 15 ቀን 2015 ዓ.ም