ኢትዮጵያ የብሔር፣ ብሔረሰቦችና ሃይማኖቶች ተቻችሎ በሠላም አብሮ የመኖር ምሳሌነቷን ያሳየች፣ በብዝሃነት አጊጣ የተፈጠረች ውብ አገር ብትሆንም፤ ይሄን ውበቷን የሚያጠለሹ በርካታ ክስተቶች መስተዋል ከጀመሩ ውለው አድረዋል፡፡
የእኩይ ዓላማ ባለቤቶች ፀረ ሰላም እንቅስቃሴ ሳቢያ በህዝቦች መካከል መተሳሰብ ሳይሆን መከፋፋል፤ መደጋገፍን ሳይሆን መገፋፋት፤ መመሰጋገን ሳይሆን መወቃቀስ፤ አንዱ የአንዱ አለኝታነቱ ሳይሆን ባላንጣነቱ፤ ወዘተ. እየጎላ በመምጣቱ ህዝቦች አንድ ላይ እያሉ ተራርቀዋል፡፡ በአንድ ላይ የሚኖሩባትን የጋራ ቤት ከመገንባት ይልቅ የባጧን ሰንበሌጥ እየመዘዙ የግል ቤታቸውን ለመገንባት አቆብቁበዋል፡፡ ይህ ደግሞ ወጥቶ መግባት፣ ዘርቶ መቃም፣ ወልዶ መሳም፣ አጊጦ መታየት፣ ወዘተ ተፈጥሯዊ ዑደታቸውን ጠብቀው እንዳይጓዙ፤ ሰዎችም ከሰዎች ጋር ያላቸውን ማህበራዊ፣ ኢኮኖሚያዊና ፖለቲካዊ መስተጋብሮች ለማካሄድ እንዲሳናቸው እያደረገ ይገኛል፡፡
በሚሊዮኖች የሚቆጠሩ ዜጎችን ያፈናቀለው የሶማሌና የኦሮሚያ ክልል፣ በጌዲዮና ጉጂ ዞኖች አዋሳኝ እንዲሁም በተለያዩ ሀገሪቱ አካባቢዎች ተፈጥረው በነበሩ ግጭቶች የተፈጠረው ጠባሳ ፈውስ ሳያገኝ፣ በሶማሌ ክልል ጅግጅጋ ከተማ ላይ የተፈጠረው አሳዛኝ ድርጊት መደገሙ ለሰላም የተሰጠው ዋጋ ዝቅ ማለቱን ያመላከተ ነበር፡፡ እነዚህ በሌሎች አካባቢዎች ያጋጠሙ ክስተቶችም በሰው ህይወት፣ አካልና ንብረት ላይ የከፋ ጉዳት አድርሰዋል፤ ማህበራዊና ኢኮኖሚያዊ መስተጋብርንም አቃውሰዋል፡፡
ይህ ሁሉ ሆኖ ግን ስለ ሰላም ከምላስ ያለፈ ተግባር ሳይታይ በደቡብ፣ በኦሮሚያ፣ በቤኒሻንጉል ጉሙዝ፣ በአማራ ብሎም በትግራይ ክልሎች አዋሳኝ አካባቢዎች ይሄው መተነኳኮስ ቀጥሎ የበርካታ ዜጎችን ህይወት እየነጠቀ፤ አካል እያጎደለ፣ ንብረት እያወደመና ማህበራዊ ህይወትንም እያናጋ ይገኛል፡፡ ይህ ደግሞ የሰላም ዋጋዋ የመዘንጋቱ ውጤት ነው፡፡
ታዲያ «ጅብ ከሄደ ውሻ ጮኸ» እንዲሉ፤ ሰላም ዋጋዋ ተዘንግቶ ግጭት ከተከሰተና የሰው ህይወት ካጠፋ፣ አካል ካጎደለ፣ ንብረት ካወደመና ማህበራዊ እሴትን ካናጋ በኋላ ቢያዝኑ፣ ቢጸጸቱ፣ ቢያነቡና ቢቆጩ ምን ሊረባ? በራስ አቅም፣ በማህበራዊ እሴት ችግሮችን በምክንያት አስልቶ ማስቀረት ሲቻል፤ በጸጸት፣ በእንባና ቁጭት ለማይመለሰው ኪሳራ መንግሥት ላይ ጣት ቢጠቁሙ፤ አፋጣኝ መፍትሄና ድጋፍ ይስጥ ቢሉስ የእለት ሕይወትን ለማትረፍ ካልሆነ በቀር ምን ሊፈይድ? ችግሩ ከተከሰተ በኋላስ የተጣላሁት ከወንድሜ፣ ከአብሮ አደጌ፣ ከአምቻና ጋብቻዬ፣ ወዘተ. ቢሉት ሰላም ዋጋዋን ካጣች በኋላ ምን ትርፍ ይኖረው ይሆን?
ምክንያቱም የሰላም ዋጋዋ በመዘንጋቱ ሰዎች ሠርተው ከሚበሉበት አውድ ተሰድደዋል፤ ዘርተው ከሚቅሙበት መሬት ተፈናቅለዋል፤ ወልደው ለመሳም አጋራቸውን አጥተዋል፤ የወለዱትን ለማሳደግ እጅ አጥሯቸዋል፤ ልጆችም ያላሳዳጊ ቀርተዋል፤ ሠርተው የሚበሉ እጆች ለልመና ተዘርግተዋል፤ ነገን በተስፋ የሚናፍቁ ሕፃናት ከትምህርት ገበታቸው ተለይተው በስደተኞች ካምፕ ታጉረዋል፤ ሀብትና ንብረታቸው የወደመባቸው፣ ቤተሰብ ከጎናቸው በሞት የተለያቸው ወገኖችም ቅስማቸው ተሰብሯል፡፡
ታዲያ ይህ ሁሉ ስለ ሰላም ዋጋ በአግባቡ ያውቃል የሚባለው ህዝብ ከራሱ አልፎ ለሌሎች ማስረዳት ሲችል ለራሱ ማወቅ ተስኖት ሰላሙን በራሱ ጊዜ አሳልፎ በመስጠት ለጥላቻና ግጭት በመዳረጉ በራሱ ላይ የጋበዘው ነው፡፡ እናም የሰላም ዋጋዋ በሰብዓዊ ልማት፣ በኢኮኖሚ እድገት፣ በፖለቲካ ተጽዕኖ፣ በዴሞክራሲ ስር መስደድ፣ በጥብቅ ማህበራዊ ቁርኝት፣ ወዘተ. እየተባለ ተዘርዝሮ የሚገለጽ ብቻ አይሆንም፡፡ የሰላም ዋጋዋ ለሰው ልጆች ብቻ ሳይሆን ለየትኛውም ፍጡር በቃላት ተገልጾ ይሄን ያህል ነው የሚባል አይደለም፡፡
ኢትዮጵያችንም ሰላም ስትሆን ለዓለም አብነት የሚሆን ተግባርን አከናውናለች፡፡ በሥልጣኔም ማማ ተቀምጣለች፤ የማይፋቅ የደመቀ ታሪክም በየዘመናቱ አጽፋለች፡፡ በአንጻሩ ሰላሟ ሲደፈርስ ህዝቦቿን ለግጭት ዳርጋ የህይወትና የአካል ጉዳትን አስተናግዳለች፤ ሰርቶ ለመብላት የማይቻልበት የግጭት አውድ በመሆንም በሚሊዮኖች የሚቆጠሩ ዜጎቿን በረሃብ አለንጋ አስገርፋለች፡፡ በእነዚህ ሁነቶቿም በዓለም የረሃብና የጦርነት ተምሳሌት እስከመሆን ደርሳለች፡፡
ታዲያ አሁንም እየሆነ ያለው ከእነዚህ ሁለቱ አማራጮች አንዱን መያዝ ግድ ወደሚልበት ውሳኔ መድረስን የሚጠይቅ ነው፡፡ ምክንያቱም ወይ ለሰላም ዘብ ቆሞ ሰላምን በማስፈን ኢትዮጵያ ለዜጎቿ ምቹ እንድትሆን ማስቻል፤ ካልሆነም በተጀመረው መልኩ የግጭትና የመበላላት አውድማ አድርጎ አሳልፎ ለበላተኛ መስጠት ነው፡፡
ይሁን እንጂ ኢትዮጵያውያን ካላቸው ባህልና ልምድ፣ ታሪክም ጭምር አገርን ለህዝቦቿ የምትመችና በአንድም አብረው የሚኖሩባት የማድረግ እንጂ አሳልፎ ለጠላት መስጠትን አያስቡትም፡፡ ዛሬ ላይ የሚታዩ ግጭቶችና ይሄን ተከትሎ የሚታዩ ማህበራዊና ኢኮኖሚያዊ ቀውሶችም ለጊዜው የህዝቦች መስሜት መነዳት የፈጠረው የሰላምን ዋጋ የመዘንጋት እንጂ የማህበራዊ እሴት መሸርሸር ላለመሆኑ እሙን ነው፡፡
እናም ይህ የሰላም ዋጋዋ የተዘነጋበት ሁነት በጊዜ ሊታረም፤ ህዝቦች የአብሮነት እሴታቸውን መልሰው ለሰላማቸው አብረው ሊሰለፉና የደረሰውን ማህበራዊና ኢኮኖሚያዊ ክስረት የሚክስ ተግባር ሊከናወን ይገባዋል፡፡ ለዚህ ደግሞ ሁሉም በአንድ ሆኖ ስለ ሰላም ሊሰራ፣ ዋጋዋንም የከበረ መሆኑን ሊያውቅ የግድ ነው፡፡ ለዚህ የእኩይ ዓላማ ባለቤቶች የሆኑ ፀረ ሰላም ኃይሎችንም አደብ ማስገዛት አስፈላጊ ነው፡፡