ዘውዱ በብዙዎች እንደ አንድ ነፍስ አዳኝ ፍጡር ይታወቃል። ኤችአይቪ/ኤድስን በመጋፈጥና መከላከል ተግባር ፊት መሪነትም እንደዚያው። ሕልፈቱን ተከትሎ ቀርቦ ወደ ነበረው የሕይወት ታሪኩ እንሂድ።
ዘውዱ ጌታቸው ኤች.አይ.ቪ/ኤድስን በሚመለከት ፀጥታና ዝምታ በሰፈነበት ወቅት ራሱ ከቫይረሱ ጋር እንደሚኖር ይፋ በማውጣት «ትውልድ ይዳን በእኛ ይብቃ!!» ብሎ ኤድስን ለመዋጋት የተነሳ ኢትዮጵያዊ ጀግና ነበር። ዘውዱ ጌታቸው የአንደኛ ደረጃ ትምህርቱን በመስፍን ሀረር ትምህርት ቤት፤ የሁለተኛ ደረጃ ትምህርቱን ደግሞ በተፈሪ መኰንን ትምህርት ቤት ተምሮ ካጠናቀቀ በኋላ በአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ ቴክኖሎጂ ፋክልቲ በመግባት የከፍተኛ ደረጃ ትምህርቱንም አጠናቋል። በአሰላ አጠቃላይ ሁለተኛ ደረጃ ትምህርት ቤት በመምህርነት እንዲሁም በዚላ፣ በበርታ፣ በሱርና፣ በሶጀት ኮንስትራክሽን ድርጅቶች በመካኒክነት ሠርቷል።
«እኔ ከቫይረሱ ጋር የምኖር ነኝ።» በማለት የኢትዮጵያ ሕዝብን በአደባባይ ለማስተማር መውጣት እጅግ በጣም ጥቂት ቆራጦች ብቻ የሚደፍሩት ተግባር በነበረበት በዚያን ክፉ ቀን ብቅ ብሎ ለአገር የሚጠቅም ታላቅ ተግባር ሲያከናውን የቆየ ሰው ነበረ። ዘውዱ በኢትዮጵያ የመጀመሪያ የሆነውን ከቫይረሱ ጋር የሚኖሩ ሰዎች ማህበር «ተስፋ ጎህ ኢትዮጵያ»ን በ1990 ዓ.ም. ከአሥር ጓደኞቹ ጋር በመመስረት ከቫይረሱ ጋር የሚኖሩ ወገኖች መብታቸውን ለማስከበር እንዲታገሉ ከማሰባሰቡም በላይ ኤች.አይ.ቪ/ኤድስን ለመከላከልና ለመቆጣጠር በሚደረገው ትግል ውስጥ ጉልህ አስተዋፅኦ አድርጓል። ራሱ ከቫይረሱ ጋር እንደሚኖር ይፋ አውጥቶ በማሳወቁ ምክንያት ይደርስበት የነበረውን አድልኦና መገለል በቆራጥነት በመፋለም ዛሬ ኤች.አይ.ቪ/ኤድስን በሚመለከት ኢትዮጵያ ውስጥ ለተገኙ አዎንታዊ ለውጦች ከፍ ያለ ድርሻ አበርክቷል።
ዘውዱ ጌታቸው በአገርና በዓለም አቀፍ ደረጃ ተስፋ ጎህን በመወከል የኤች.አይ.ቪ/ኤድስ ችግር በአገራችን እያደረሰ ያለውን እውነታ በመናገርና ለበሽታው መንግሥት ትኩረት እንዲሰጥ ጥሯል። በተጨማሪም «ተስፋ ብርሃን» በኤድስ ምክንያት ወላጆቻቸውን ላጡ ሕፃናትና ወጣቶች ማህበርንም በመመስረት ኤች.አይ.ቪ/ኤድስን የሚያስከትለውን ሰብዓዊና ማህበራዊ ቀውስ በመታገል አያሌ ታዳጊዎችን ከመበተን አድኗል።
ከ1996 ዓ.ም ጀምሮ በኤች.አይ.ቪ/ኤድስ ምክንያት በሥራ ቦታ የሚደርሰውን አድልኦና ማግለል ይበልጥ ለመታገል ወደ ማህበሩ ለመምጣት ያልደፈሩትን ወገኖች በስልክና በሌሎች የመገናኛ አውታሮች በመጠቀም የምክር አገልግሎት ለመስጠትና ከኤች.አይ.ቪ/ኤድስ ጋር የሚኖሩ ወገኖች ሰብአዊ መብት እንዲከበር ይበልጥ ለመታገል «አዲስ ምዕራፍ» የተባለ ድርጅት አቋቁሟል። እስከ ሕልፈተ ሕይወቱ ድረስም ሠርቷል። ዘውዱ ጌታቸው ባደረበት ሕመም ምክንያት በተለያዩ ሆስፒታሎች በሕክምና ሲረዳ ቆይቶ በተወለደ በ45 ዓመቱ ታኅሣሥ 18 ቀን 1997 ዓ.ም. ከዚህ ዓለም በሞት ተለይቷል።
ይህ ነበር አጠር ባለ መልኩ ለንባብ በቅቶ የነበረው የዘውዱ ጌታቸው የሕይወት ታሪክ።
የኤች.አይ.ቪ በሽታን ለመከላከል እና ባለበት ደረጃ ለመግታት «ትውልድ ይዳን በእኛ ይብቃ» በሚል ክቡር ሰብአዊ አላማ ተነሳስተው ከኤችአይቪ ቫይረስ ጋር የሚኖሩ ወገኖችን ለመታደግ የመሠረቱትን «ተስፋ ጎህ ኢትዮጵያ»ን ያስታወሰ ወዲያውኑ በአእምሮው የሚመጣለት ተስተዋሽ ቢኖር በቀዳሚነት ዘውዱ ጌታቸው እና ባልደረቦቹ ናቸው።
ከኤች.አይ.ቪ ቫይረስ ነፃ የሆነ ትውልድ ማየትን ራእዩ ያደረገው ተስፋ ጎህ ኢትዮጵያ ከ10 ሺህ በላይ ከኤች.አይ.ቪ ቫይረስ ጋር የሚኖሩ አባላትን ማሰባሰብ የቻለ፤ በመላው አገሪቱም 12 ቅርንጫፎች ያሉት፤ ለትርፍ ያልቆመ፣ ከማንኛውም የፖለቲካና የኃይማኖት ወገንተኝነት ነፃ የሆነ ማህበር ነው። የዚህ ሁሉ ስኬት ባለቤት ደግሞ የዛሬው ተስተዋሽ ባለውለታ ዘውዱ ጌታቸውና አጋሮቹ ናቸው።
የማህበሩ አላማ ከኤች.አይ.ቪ ቫይረስ ጋር የሚኖሩ ወገኖችና ወላጅ አልባ ሕፃናት እንክብካቤ እንዲያገኙ መርዳት፣ ከኤች.አይ.ቪ ቫይረስ ጋር የሚኖሩ ወገኖችና ወላጅ አልባ ሕፃናት መብት እንዲከበር መታገል፣ ኤች.አይ.ቪ/ኤድስን ለመከላከልና ለመቆጣጠር በሚደረ ገው ትግል በግንባር ቀደምትነት መሰለፍ፤ እንዲሁም፣ በትምህርት፣ በድጋፍና ክብካቤ ፕሮግራሞች አማካኝነት የአባላቱ ጥያቄዎች የሚሟሉበትን መንገድ ማፈላለግና የአባላቱን መብት ማስጠበቅ ሲሆኑ፤ ከዚህ ሁሉ ጀርባ ዛሬ እያስታወስነው ያለው ባለውለታ ዘውዱ ጌታቸው አለ።
ዘውዱ ከራሱም አልፎ ከቫይረሱ (የሰውነትን የበሽታ መከላከያ በተለይ የነጭ ደም ሴሎችን (ህዋሳትን) በማጥቃት በቀላሉ ሰውነት ለበሽታ እንዲጋለጥ የሚያደርግ ቫይረስ) ጋር የሚኖሩ ወገኖቻችን ላይ በማንኛውም መልክ የሚከሰተውን መድሎና መገለልን ሲታገል፣ ከቫይረሱ ጋር የሚኖሩ ወገኖቻችን የኤች.አይ.ቪ/ኤድስን በተመለከተ በሚቋቋሙ ምክር ቤቶችና መድረኮች ሁሉ በውሳኔ ሰጪነት ደረጃ ተሳትፎና ውክልና እንዲኖራቸው ለማድረግ ሲታገል፣ የአባላትን አቅም በመገንባት በማህበሩ እንቅስቃሴዎች ሁሉ እንዲሳተፍ ሲያድደርግ፣ መገናኛ ብዙኃንን በመጠቀም ኤች.አይ.ቪ/ኤድስን ለመከላከሉ ዘመቻ ኅብረተሰቡን ስለበሽታው በስፋት ሲያስተምር፣ በተለይም 4ቱን «መ»ዎች (መታቀብ፣ መወሰን፣ መጠቀም እና መመርመር) ተግባራዊ እንዲያደርግ ሲመክር፣ ቫይረሱን ለመከላከል መወሰድ ስላለባቸው እርምጃዎች ሲዘክር …፣ ከኤች.አይ.ቪ ቫይረስ ጋር ተስማምቶ ለመኖር መከተል ስላለባቸው መመሪያዎች ግንዛቤ ሲያስጨብጥ፤ ማህበሩ ለወደፊቱ በራሱ ገቢ የሚተዳደርበትን ሁኔታ ማመቻቸትና አባላቱም አምራች ዜጋ የሚሆኑባቸውን ስልቶች መቀየስን፤ አባላቱ በማናቸውም ብሔራዊና ዓለም አቀፋዊ እንቅስቃሴዎች ውስጥ የጎላ ተሳትፎ እንዲኖራቸው ማድረግን … በተመለከተ ሲታትር የነበረ ሰው እንደ ነበር ነው ስለ እሱ የተፃፉት እንደሚያስረዱን።
ኅብረተሰቡ ስለ ኤች.አይ.ቪ/ኤድስ ያለውን ግንዛቤ አሳድጎ ራሱን እንዲጠብቅና በዚህም የወረርሽኙን ተዛማጅነት ለመቀነስ በአባላት አማካኝነት በተለያዩ መድረኮች ትምህርት ሲሰጥ የነበረው ዘውዱ፣ ምን ይሉኛልን ሰብሮ በመውጣት ለብዙዎች ተስፋ ሆኖ የኖረ ሰው ነበር።
ዘውዱ በኤድስ (የኤች.አይ.ቪ የመጨረሻ ደረጃ) ሳቢያ ወላጆቻቸውን ላጡ ሕፃናት የሚገባውን ድጋፍ መስጠት፣ በኤድስ ሳቢያ ታመው አልጋ ላይ ለዋሉ አባላት ሁለገብ ድጋፍ ማድረግ ወዘተርፈ ተገቢ መሆኑን አምኖና አሳምኖ ተግባራዊ ሲያደርግ የነበረ ሲሆን፤ ከኤች.አይ.ቪ/ኤድስ ጋር የሚኖሩ ወገኖች መገለልና መድልዎ እንዳይደርስባቸው መከላከል፤ በዚህ ረገድ የሚከሰቱ አጋጣሚዎችን ለሕግ አካላት በማቅረብ የመብት ማስከበር ሥራዎችን ሁሉ ሲሠራ እንደነበር መረጃዎች ያመለክታሉ።
«የኢትዮጵያውያንን ሕይወትንም፣ አብሮነትንም ከአሰቃቂው እልቂት የታደገ የክፍለ ዘመኑ ጀግና!!» በሚል ርእስ በአሌክስ አብርሃም (ድሬትዩብ) የቀረበው ጽሑፍ እንደሚያስረዳው ያንን ወቅት፣ ያንን ዘውዱ ብቅ ብሎ ስለ በሽታው፣ ዝምታው፣ መገለሉ፣ አድልኦና መገፋቱ … በግልፅ መናገር የጀመረበትን ወቅት … «ያ መራር ወቅት ልጆችን ከወላጅ ለየ …. ሚሊዮኖች ያለወላጅ ቀሩ …. ደማቅ ትዳሮች በአስደንጋጭ ሁኔታ ፅልመት ዋጣቸው … ሰዎች ተፈራሩ! ማንም ሰው ድንገት ካሳለው፣ ሰውነቱ ከቀነሰ …የቅርብ የሚላቸው ሁሉ ይርቁት ጀመር … እንኳን ምልክቱ ታይቶ እከሊት እኮ ብዙ ወንዶች ጋር ትሄዳለች ከተባለ ወይም እከሌ’ኮ ሴቶች ያበዛል የሚል ሃሜት ከተነዛ አክ እንትፍ ብሎ የሚተፋው ሕዝብ አያሌ ነበር …. በሽታው ምንድን ነው? …ማን ስለበሽታው ትክክለኛውን ይናገር … የሃይማኖት አባቶች ሳይቀሩ ’በስምንተኛው ሺህ አመንምን የሚባል በሽታ ይመጣል፤ መርገምት ነው’ ብለው በግልፅ እስከመስበክ ደርሰው የነበረበት ጊዜ ነው። መርገምቱ ግን ቤተክርስቲያን ወላ መስጊድ አልማረም።» ሲል ይገልፀዋል።
«… የሰብዓዊነት ጋሻውን ይዞ ፊት ለፊት በመውጣት ለመጀመሪያ ጊዜ የተፋለመው ጀግና ዘውዱ …. ይባል ነበር።» በማለትም ስለ ዘውዱ ሊነግረን ይንደረደራል – የአሌክስ ጽሑፍ።
በሽታውንና ተጠቂዎችን፣ የማኅበረሰቡንና የሚዲ ያውን ሁኔታም «እነዛ ህመምተኞችን የሚታደጉ የወደቁትን በደዌ የተጠቁትም የሚያነሱ ደግ ምእመናን ይህን ነገር ፈሩት …. ህመሙ አውሬ ተደርጎ ተሳለ … በወቅቱ ለማስተማሪያነት ተብለው የሚቀርቡ ምስሎች ሁሉ የባሰ አሰቃቂና አስፈሪ ሆነው የቫይረሱን ተጠቂዎች ሕዝቡ እንዲያገላቸው አደረጉ። መንገድ ላይ ሰውነታቸው ቆሳስሎ የወደቁ የቫይረሱ ተጠቂ ናቸው በሚል አስተሳሰብ ከሩቅ ሳንቲም ከመወርወር ውጪ ማን ደፍሮ ምግብ ያቀብላቸው … የሰው ልጅ በየመንገዱ በእንደዛ ዓይነት አሰቃቂ ሁኔታ ሲሞት ማየት በራሱ አሰቃቂ ነገር ነበር። … ከአንድ ቤት ሚስትም፣ ሠራተኛ፣ አባወራም… በዚሁ ምክንያት ያለቁበት አጋጣሚ ብዙ ነበር። … እናትና አባት አልቀው አያቶች በደካማ አቅማቸው የልጅ ልጆቻቸውን ያሳደጉበት … ከዚህም በላይ አፈር አይንካችሁ ተብለው በቅንጦት ያደጉ ልጆች በረንዳ የፈሰሱበት አሰቃቂ ትእይንት ነበር … ይሄ ተረት አይደለም። በእኛው ዕድሜ የታየ መራር ሃቅ ነው።» በማለት ያስታውሰናል። ጽሑፉ ዘውዱ ጌታቸው ይህንን ሁሉ ጥሶ የወጣ መሆኑን እስክንረዳ ድረስ ያስረዳናል።
(በነገራችን ላይ፣ ኤድስ አሁንም ስጋት እንጂ የተወገደ ነገር አይደለም። ባለፈው አመት የዓለም ኤች.አይ.ቪ/ኤድስ ቀን መከበርን አስመልክቶ የወጣው መረጃ እንደሚያሳየው «በመላው ዓለም የበርካቶችን ሕይወት ሲቀጥፍ 40 ዓመታት ተቆጥረዋል። ካለፉት ሁለት ዓመታት ወዲህ የብዙዎች ትኩረት የኮሮና ቫይረስ ላይ ቢሆን ዛሬም የብዙዎች ስጋት ነው ኤች.አይ.ቪ/ኤይድስ። በተለይ አፍሪካ ውስጥ ከ25 ሚሊዮን ሕዝብ በላይ የዚህ በሽታ ተጠቂ ነው።)
በወቅቱ፣ «የምክር አገልግሎት ስላልነበረ ብዙዎች ቫይረሱ በደማቸው ውስጥ መኖሩን ሲያውቁ ራሳቸውን ያጠፉ ነበር …» ይህ ማለት በወቅቱ የዘውዱ ጌታቸው ዓይነት ሰዎች (የሚያስተምር፣ የሚያረጋጋ፣ አድልኦና መገለልን የሚያወግዝ፣ እራሱን በአርአያነት (የቫይረሱ ተጠቂነት) የሚያቀርብ ወዘተ) ምን ያህል አስፈላጊ እንደነበሩ የሚያመለክት ሲሆን፤ ዘውዱ ወደ ፊት ይመጣ ዘንድም ምክንያት እንደነበረው ያሳየናል።
ለአገር ስንት ነገር ያበረክታሉ የተባሉ ምሁራን፣ ታላቅ ብለን ቡራኪያቸውን የተቀበልን የሃይማኖት አባቶች (ከሁሉም ሃይማኖቶች) የቀለም ዘር የዘሩብን አስተማሪዎቻችን …. በቫይረሱ አለቁ። አንዳንድ ቢሮዎችማ ባዶ እስከሚሆኑ ሠራተኞቻቸውን የተነጠቁበት ወቅትም ነበር … ኢትዮጵያ በታሪኳ ኤች.አይ.ቪ/ኤድስ የነጠቃትን ያህል ዜጋ የቀማት ጦርነትም አጋጣሚም መሪም አልነበረም። ዋናው ችግር ለቫይረሱም ሆነ ለቫይረሱ ተጠቂዎች የነበረው የተሳሳተ ግንዛቤ ነበር …. በወቅቱ ደፍሮ ስለኮንዶም የሚተነፍስ ዜጋ ነበር ማለት አይቻልም …. ቫይረሱ በምን ይተላለፍ በምን አይተላለፍ በግልፅ ግንዛቤ አልተፈጠረም። የሚለው የጸሐፊው አስተያየትም የዘውዱን ውለታም በሚገባ ያስታወሰ (ከ’ነፀፀቱ) ነበር።
አሌክስ አብርሃም ስለ ዘውዱ
[…] በዚህ ሁሉም በተፈራራበት ሺዎች ቤታቸውን በላያቸው ላይ ቆልፈው በድብቅ በሚያልቁበት ጊዜ ኢትዮጵያን እርዳታም፣ ማስፈራሪያም፣ ማግለልም ሊታደጋት ባልቻለበት ወቅት … ለመጀመሪያ ጊዜ አንድ ሰው ድንገት አደባባያችን ላይ ተከሰተ። ይህ ሰው አቋሙን በመመልከት፤ አነጋገሩንና ፈገግታውን በማየት ማንም ቀጥሎ የሚናገረውን ነገር ይናገራል ብሎ አልጠበቀም ነበር … ግን ተናገረው።
‹‹እኔ ከኤች.አይ.ቪ ቫይረስ ጋር አብሬ ነው የምኖረው … ኤች.አይ.ቪ/ኤድስ ቫይረስ በደማችን ውስጥ ቢገኝ እንኳን ህክምና ከተከታተሉ እንደማንኛውም ሰው መኖር፣ መሥራት … ይቻላል›› አለ። አጭር ግን ሚሊዮኖች መናገር አቅቷቸው ትውልድ የገበሩበት ንግግር።
ወጣቱ የአገራችንን የእልቂት ታሪክ ሙሉ ለሙሉ በሚባል ሁኔታ ገለበጠው። አገር ምድሩን በድፍረቱና በሰብዓዊነቱ አጥለቀለቀው … በቫይረሱ የተያዘን ሰው በግላጭ አይቶ የማያውቀው ሕዝብ …. የከሳውን ሁሉ የሚጠረጥረው ሕዝብ … ቫይረሱ የነበረባቸውን ወገኖቹን በማግለል ሲበድላቸው፣ ባለማወቅ ሲጨርሳቸው የነበረው ሕዝብ … በዚህ ወጣት ቃል … ወደ ቀልቡ ተመለሰ።
ሕዝቡ ቁጭ ብሎ ‹‹ምን እናድርግ›› አለ። ተመካከረ …. እናም በተበታተነ ሁኔታ ይደረግ የነበረውን ዘመቻ፤ በሹክሹክታና በፍርሃት በየጓዳው የተደበቀውን እልቂት፤ በተባበረና በተቀናጀ ሁኔታ «ሀ» ብሎ ጀመረው ….. የዚህን ወጣት የአገር ባለውለታ አርዓያ የተከተሉ፣ በመቶዎች የሚቆጠሩ ከቫይረሱ ጋር የሚኖሩ ዜጎች አደባባይ ወጡ፤ ‹‹በእኛ ይብቃ ትውልድ ይዳን››ም አሉ።
ትውልድን ከእልቂት አገርንም ከትውልድ መካንነት ያተረፈ ትንታግ …
… ዘውዱ ሚሊዮኖችን ከአስከፊው ጠላት መንጋጋ ያስጣለ የኢትዮጵያ ሕዝብ የምን ጊዜም ጀግና ነው። ዘውዱ ለየትኛውም ዘር፣ ለየትኛውም ሃይማኖት፣ ለየትኛው የኅብረተሰብ ክፍል … ሳይሆን ለመላው ኢትዮጵያዊ፣ ለመላው በምድሪቱ ላይ ላለ እና ለሚኖር የሰው ልጅ ሁሉ የሚሊዮኖች ዓይን እየገረፈው፤ የሚሊዮኖች ምላስ እየዘለፈው፤ በማይረሳ ጀግንነቱ ፍርሃትን ድል የነሳ … ሌሎችም ተስፋ መቁረጥና ፍርሃትን ድል እንዲነሱ ፈር የቀደደ …. የእውነት ጀግናችን ነው። የማይከፈል ውለታው አለብን።
እንዳለመታደል ሆኖ እኛ ኢትዮጵያውያን የማስታወስ ችሎታችንን እያጣን ነው … ክፉኛ እያጣን ነው … ለምሳሌ የዘውዱን ሥራ ይቅርና የአባቱን ስም እንኳን ለማግኘት የሞከርኩት ሙከራ አልተሳካም። 952 ስለኤችአይቪ መረጃ የሚሰጥ ነፃ የስልክ መስመር ነው። ብታምኑም ባታምኑ ስለዘውዱ ስጠይቅ ልጅቱ ልታውቀው አልቻለችም …
አንድ ሦስት ቦታ የነፃ ምርመራና ምክር አገልግሎት የሚሰጥባቸውም ቦታዎች ጠየኩ፤ አንዱ እዚህ፣ የድል አደባባይ የሚባለው ጋ ነው … ዘውዱን አያውቁትም። ስለዘውዱ ኢንተርኔት ላይ ጎግል አድርጋችሁ አንዲት ነገር ማግኘት ከቻላችሁ ሞክሩ፤ እኔ አላገኘሁም። እንዲህ ነን እንግዲህ እኛ። እስቲ ምን ትላላችሁ የተጮኸበት ጩኸን ከጩኸታችን ጋር የምንከስም የዜና እና የወረት ትውልዶች ሆነናል! ጀግኖቻችንን … የተፈጠሩ ሁኔታዎችን ላይ ሁሉ እንጮሃለን …. ወዲያው እንረሳለን … ያዝ፣ ለቀቅ ብቻ … ጩኸት ብቻ ነው።
[የዘውዱን ወደ አደባባይ መምጣት ተከትሎ] ቫይረሱ በደሙ ውስጥ የሚገኝ ሰው እንደማንኛውም ሰው መሥራት፣ መማር፣ ህክምናውን እየተከታተለ በሚገባ መኖር እንደሚችል ሕዝቡ አመነ። ያገለላቸውን ወገኖቹን በይቅርታ ልብ ዳግም ቀረባቸው። ሆስፒታሎች የተለያዩ አሠራሮችን ዘረጉ … ሚሊዮኖች ለምርመራ የታጠፈ ክንዳቸውን ዘረጉ … እጅግ በጣም ብዙ የፀረ-ኤድስ ክበባት በየትምህርት ቤቶች ተቋቋሙ … በሕይወት ተስፋ የቆረጡ፣ ቫይረሱ በደማቸው ውስጥ የተገኘ ግለሰቦች ህክምናቸውን በአግባቡ በመከታተል፣ የወጣትነት ተስፋቸውን ያጨለ መውን የግንዛቤ ማጣት ገ’ፈው ከመሰሎቻቸው ጋር ትዳር በመመስረት ወልደው ለመሳም በቁ።
ይህ የሚነግረን የዘውዱ ጌታቸውን ያልተተካ ሚና ብቻ ሳይሆን የዘውዱንና ባልደረቦቹን (መምሕር መስፍን ሽፈራውን ጨምሮ) ባለ ውለታነትና ያልተከፈለ እዳ መኖሩን ነውና ይህ ወደ ፊት ይለወጣል የሚል ተስፋን በመሰነቅ የዛሬውን፤ ዘውዱ ጌታቸውን የሚያስታውስ ጽሑፋችንን እናጠናቅቃለን።
ስም ከመቃብር በላይ ነው!!!
አዲስ ዘመን ህዳር 14/2015