ወይም የአውሮፓ ሀገራት ውስጥ የመኖር ዕድል ቢሰጠኝ መኖር የምፈልግበት ምክንያት አንድ ብቻ ነው። የረቀቀ ቴክኖሎጂ፣ ፈጣንና ምቹ መሠረተ ልማት ወይም ሌላ የሥልጣኔ መለያ የሆኑ ነገሮች ከሀገሬ ውጭ ለመኖር አጓጉተውኝ አያውቁም። የሰለጠኑ በሚባሉ ሀገራት የምቀናው በጤና የመኖር መብታቸውን ብቻ ነው።
ከአውሮፓ ሀገራትም ሆነ አሜሪካ የመጡ ሰዎች ካገኘሁ የምጠይቀው የመሠረተ ልማት ደረጃቸውን አይደለም፤ በጤና የመኖር መብት ላይ ያለውን ጥበቃና ጥንቃቄ ነው። የሚነግሩኝ ነገር ሁሉ ያስቀናኛል።
ዛሬ ላወራ የፈለኩት ስለ ድምጽ ብክለት ነው። በሰለጠኑት ሀገራት የድምጽ ብክለት እጅግ ትልቅ ጉዳይ ነው፤ በእኛ ሀገር ግን የቅንጦት ነው። ምናልባትም ‹‹ምን ያህል ሥራ ፈት ቢሆን ነው!›› ያሰኝ ይሆናል። የድምጽ እና የአየር ብክለት ግን እንደ ቀላል የሚታዩ አይደሉም። የአየር ብክለት ባናሳካውም ቢያንስ አጀንዳ ስለሆነ እና በተደጋጋሚ ስለሚወራበት ማንም ያውቀዋል። እጅግ ልብ ያልተባለውና የጆሮ ጠላት የሆነው የድምጽ ብክለት ግን በአገራችን አደገኛ ችግር እያመጣ ነው።
የድምጽ ብክለት በሰለጠኑት ሀገራት ከፍተኛ ጥበቃ የሚደረግበት ነው። እያንዳንዷ የምትወጣ ድምጽ መለኪያ አላት፤ ከዚያች ካለፈ ለቃቂው አካል ይጠየቃል። እንኳን ሌላ የተሽከርካሪ ክላክስ መጠን አለው። ከዚያ ካለፈ ይቀጣል፤ መጠን ብቻ አይደለም፤ ክላክስ የሚያደርግባቸው ምክንያቶች ውስን እና የታወቁ ብቻ ናቸው።
በኢትዮጵያ ግን ልብ በሉ! ከፊቱ ያለው ተሽከርካሪ መብራት ይዞት እያየ ከኋላ የመጣው ያለምንም ማቋረጥ ለረጅም ደቂቃ ያንባርቃል። መብራት ይዞት እያየ እንዴት ይሄዳል ብሎ ይሆን? ከፊቱ ያሉ ተሽከርካሪዎች የቆሙበትን ምክንያት እያወቀ አካባቢውን የሚያናውጥ ክላክስ ያስጮሃል።
የሕግ ባለሙያው አብዱ ዓሊጂራ ከጋዜጠኛ መዓዛ ብሩ ጋር በሸገር ኤፍ ኤም 102.1 ‹‹ሸገር ካፌ›› ፕሮግራም በአንድ ወቅት በዚሁ ጉዳይ ላይ ሲያወሩ ሰምቼ ነበር። አብዱ ሕጎቹን ሲናገር ከወንጀል ሕግ ያልተናነሱ ናቸው። የሚገርመው ግን ከራሳቸው ከአሽከርካሪዎች ጀምሮ እነዚያን ሕጎች አብዛኛው ሕዝብ አያውቅም፤ አብዱ ራሱ ይህን ሲናገር ነበር። ክላክስ የሚደረግበት ምክንያት ተወስኖ የተቀመጠ ነው፤ ከዚያ ውጭ ያደረገ ይቀጣል።
ትልቁ እና አደገኛው ክላክስ አደራረግ ደግሞ ከፊት ላለ እግረኛ የሚደረግ ክላክስ ነው። ክላክስ የሚደረገው ሰውየው ድምፁን ሰምቶ ገለል እንዲል እንጂ ተደነባብሮ እንዲወድቅ አይደለም። ሕጻናት ወይም ከገጠር የመጡ ሰዎች ተደነባብረው ወደ ተሽከርካሪው ራሱ ሊሄዱ ይችላሉ። ‹‹ጲጵ ጲጵ›› የሚል ድምፅ መስጠት ሲገባ፣ ገና ከሩቅ ላለ ሰው ያለምንም ማቋረጥ በረጅሙ አካባቢውን የሚያናውጥ ክላክስ ማድረግ መንገደኛው ተደነባብሮ ምናልባትም ከሌላ ተሽከርካሪ ጋር እንዲጋጭ ያደርጋል።
ሌላው አደገኛ የድምፅ ብክለት ደግሞ የሙዚቃ ነገር ነው። መቼም ስለሙዚቃ ጥቅምና አስፈላጊነት ለማንም ማስረዳት አያስፈልግም። ያም ሆኖ ግን የሰውን ጆሮ ጤና የሚያበላሽ አለቃቀቅ አንድ ሊባል ይገባል። ምግብ ቤቶች ገና በማለዳ በሞንታርቦ የጆሮ ታምቡር የሚበጥስ ሙዚቃ ይከፍታሉ። ደንበኛው የሙዚቃውን ለዛ ከማዳመጥ ይልቅ የውስጡን ጤና ነው የሚያዳምጥ። ከአስተናጋጅ ጋር የሚወራው በከፍተኛ ጩኸት ነው። አብሮን ካለ ጓደኛ ጋር ስናወራ ቆይተን ስንወጣ የጮህንበት ጉሮሯችን ሊዘጋ ሁሉ ይችላል። በማለዳ ምግብ ቤት ውስጥ ጆሮ የሚበጥስ ሙዚቃ መክፈት እስኪ ምንድነው አስፈላጊነቱ? የምር በዚያ ሙዚቃ የሚዝናና አለ? ቢኖር እንኳን ቢያንስ ለአብዛኛው ደህንነት ሲባል ገደብ ሊወጣ እና ቁጥጥር ሊደረግ ይገባል።
ሌላው የምታዘበው ደግሞ ተሽከርካሪዎች ውስጥ የሚከፈት ሬዲዮ ነው። አሁንም ስለሬዲዮ አስፈላጊነት ልናወራ አይገባም፤ ዳሩ ግን ጤናን የሚያውክ እና የሚወራውን መስማት እስከሚያስቸግር ድረስ የሚጮህ መሆን የለበትም።
እዚህ ላይ ያለኝን ትዝብት እጥፍ ድርብ የሚያደርገው ደግሞ የመንግሥት ሠራተኞች ማመላለሻ (ፐብሊክ ሰርቪስ) ውስጥ መሆኑ ነው። የመንግሥት ሠራተኛ ሁሉም ሊባል በሚችል መልኩ የተማረ ነው። ቢያንስ ዲፕሎማ እና የመጀመሪያ ዲግሪ ያለው ነው። ለአገር ዕድገትና ሥልጣኔ የሚሠራ ነው፤ ዳሩ ግን እንደዚያ ሲጮህ ምንም አይመስላቸውም።
በተለይ ደግሞ የተቀረጸ (ፕሮዳክሽን) ሥራዎች (ማስታወቂያዎች እና የተለያዩ መልዕክቶች ማለት ነው) ሲሆኑ በጣም ነው የሚጮሁት፤ የቀጥታ ሥርጭት ዜናዎችና ፕሮግራሞች ይሻላሉ። ሬዲዮ እንደዚያ እየጮኸ፣ ሰዎች ደግሞ ለመሰማማት ሲሉ በጣም እየጮሁ ያወራሉ። በዚህ ሁሉ ውስጥ ሰርቪሱ በድምጽ ይናወጣል። አንዳንድ ደፈር ያሉ ሰዎች ‹‹ኧረ ቀንሰው!›› ሲሉትም አይሰማም። ሁሉም ተስማምቶ ግን ‹‹እየተጎዳን ነው ይቀነስ›› ቢባል አሽከርካሪውም ተጠያቂ ይሆን ነበር።
ችግሩ የአንድ አሽከርካሪ ወይም የአንድ ሬስቶራንት ብቻ አይደለም፤ እንደ አጠቃላይ ያለን ግንዛቤ ደካማ ስለሆነ ነው። የድምፅ ብክለትን እንደ ችግር ስለማናየው ነው። በየመንገዱ ዳር ያላስፈላጊ የሚለቀቁ ድምጾችን የሚቆጣጠር ስለሌለ ነው። ልብስ ቤቶች (ቡቲክ) ሁሉ ሳይቀር በሞንታርቦ ሙዚቃ ይለቀቃል። በተከታታይ ያሉ ቤቶች ሁሉም የየራሳቸውን ሙዚቃ ይለቃሉ፤ አላፊ አግዳሚው ግን የሚሰማው ጩኸቱን እንጂ አንዱንም ሙዚቃ የማጣጣም ዕድል አይኖረውም፤ ምክንያቱም አንዱ ሌላውን እየሸፈነ መረባበሽ ነው።
በነገራችን ላይ በድምፅ ብክለት ላይ የተሠሩ ጥናቶችና መጣጥፎች እንደሚያሳዩት ፈልገን የማንሰማው ድምፅ ሁሉ ‹‹ምቾት የሌለው›› ተብሎ ነው የሚገለጽ። በሌላ በኩል የድምጽ መጠኑም መለኪያ አለው። የድምጽ መለኪያ ዴሲቤል ይባላል፤ ከ60 ዴሲቤል በላይ የሆነ ድምጽ ሁሉ ጎጂ ነው። በዚህ መለኪያ አዲስ አበባ ውስጥ በየመንገዱ የምንሰማውን ድምጽ አስቡት።
ይህ ሁሉ ሲሆን ግን የድምጽ ብክለትን ማንም እንደ ችግርና እንደ ጎጂ አይቶት የሚያውቅ ያለ አይመስልም። ምንም እንኳን እንደ አጠቃላይ የጤና ደህንነት ላይ ያለን ግንዛቤ ደካማ ቢሆንም፣ ጆሯችንን ግን ትርፍ አካል ነው ያስመሰልነው። በነገራችን ላይ ጆሮ የድምፅ መቀበያ የሰውነት ክፍል ይሁን እንጂ ችግሩ ጆሮ ላይ ብቻ የሚቀር አይደለም። ከፍተኛ የሆነ የድምፅ ጫጫታና ጩኸት ሲበዛብን ራሳችንን(ጭንቅላት) የሚያመን ከጆሮ አልፎ ስለሚሄድ ነው። ስለዚህ የድምፅ ብክለት ከፍተኛ ችግር የሚያስከትል ነው።
ከተማ ነውና የድምጽ ጫጫታ አይኑር ማለት አይቻልም፤ ዳሩ ግን ነባራዊ ሁኔታው ከሚፈጥረው ውጭ ያሉትን እና ሆን ተብሎ ያለአዋቂነት የሚለቀቁ ድምጾችን መቆጣጠር ይቻላል። ገና በማለዳ ምግብ ቤት ውስጥ በሞንታርቦ አካባቢውን ማናወጥ አስገዳጅ አይደለም፣ የትራፊክ መብራት የያዘው ተሽከርካሪ ላይ ያላቋረጠ ክላክስ ማድረግ የሚያስቀጣ መሆን አለበት፣ ተሽከርካሪ ውስጥ ሬዲዮ እስከ ላንቃው መልቀቅ መከልከል አለበት፤ ድምጹ ቀነስ ቢል ምን ችግር አለው?
በአጠቃላይ ጆሮ ከአምስቱ የስሜት ሕዋሳት አንዱ እንጂ ትርፍ የሰውነት ክፍል አይደለምና የድምፅ ብክለት ትኩረት ይሰጠው!
ዋለልኝ አየለ
አዲስ ዘመን ህዳር 14/2015