የማዕድን ሚኒስቴር “ዓለም አቀፍ የማዕድን ኤክስፖ” ከሰሞኑ እንዳዘጋጀ ይታወቃል። በኤክስፖውም የማዕድን ኩባንያዎች፣ የጌጣጌጥ አምራቾችና ላኪዎች፣ የማዕድን ቴክኖሎጂ አምራቾችና አስመጪዎች እንዲሁም የፋይናንስ ተቋማት ተሳትፈውበታል። አምራቾችን ከሀገር ውስጥ እና ከውጭ ገዢዎች ጋር በቀጥታ ያገናኛል በሚል የተዘጋጀው ይህ ኤክስፖ በኢትዮጵያ ለመጀመሪያ ጊዜ መዘጋጀቱ ተመላክቷል።
ለመጀመሪያ ጊዜ በተዘጋጀው የማዕድን ኤክስፖ ከውጪ የሚመጡ የማዕድን ኩባንያዎች መሳተፋቸው በኢትዮጵያ ያለውን የማዕድን ኢንቨስትመንት አማራጭ እንዲመለከቱና የማዕድን ኢንቨስትመንት ላይ እንዲሳተፉ እድል የሚፈጥር ነው። ከዚህ በተጨማሪም የማዕድን ቴክኖሎጂ አምራቾች በኤክስፖው መሳተፋቸው ለኢትዮጵያ የማዕድን ዘርፍ አዳዲስ የቴክኖሎጂ አማራጮችን የማስተዋወቅ እድል የሚፈጥር እንደሆነ ከማዕድን ሚኒስቴር የተገኘው መረጃ ያመላክታል፡፡
አምራቾችን ከሀገር ውስጥ እና ከውጭ ገዢዎች ጋር በቀጥታ በማገናኘት የገበያ ትስስር መፍጠር ያስችላል በተባለው ዓለም አቀፍ የማዕድን ኤክስፖ በርካታ አምራቾች፣ ላኪዎችና የተለያዩ ኩባንያዎች ተገኝተዋል። ከእነዚህም መካከል በኤግዚቢሽኑ የኦፓል ምርት ይዘው የቀረቡት በርካቶች ነበሩ። በዘርፉ የተሰማሩ ባለሙያዎች ኤግዚቢሽኑ በመዘጋጀቱ ምርቶቻቸውን ይዘው ለመውጣትና ለማስተዋወቅ ሰፊ ዕድል የፈጠረላቸው መሆኑን በማንሳት በሀገሪቷ ያለውን የማዕድን ሃብት አይነትና መጠን ማኅበረሰቡ መረዳት እንዲችል ያደረገ ኤክስፖ መሆኑንም ሲገልጹ ተደምጠዋል።
ከተለያዩ የሀገሪቷ አካባቢዎች የከበሩ ማዕድናትን ይዘው በኤግዚቢሽኑ ከቀረቡት አምራቾች መካከል ከወሎ ደላንታ የተለያዩ የኦፓል አይነቶችን ይዘው የቀረቡት የጀምስቶን የማዕድን አቅራቢ ኃላፊነቱ የተወሰነ የግል ማህበር የማዕድን ልማት ባለሙያ አቶ ዑመር ሽፈሬ አንዱ ናቸው። አቶ ዑመር፤ የተለያየ መጠንና ይዘት ያላቸውን ኦፓሎች በኤግዚቢሽኑ ይዘው ቀርበዋል።
‹‹ጀምስቶን የማዕድን አቅራቢ ኃላፊነቱ የተወሰነ የግል ማኅበር የደላንታ የኦፓል ምርቱን በኤግዚቢሽኑ ማቅረቡ ሰፊ የገበያ ዕድል የሚፈጥረለት መሆኑን የጠቀሱት አቶ ዑመር፤ በሀገሪቱ ያለው የማዕድን ሃብት እጅግ በርካታ እንደመሆኑ ብዙ ሊሠራበት የሚገባው ዘርፍ ነው። ዘርፉን ለማሳደግና ተጠቃሚ መሆን እንዲቻል የገበያ ትስስር መፍጠር ቀዳሚው ጉዳይ ነው በማለት እስካሁን ባለው ሂደትም በአካባቢው በቂ የሆነ የገበያ ትስስር አለመኖሩ ገልጸዋል።
በወሎ ደላንታ አካባቢ የተሻለ የኦፓል ምርት ስለመኖሩ የጠቀሱት አቶ ዑመር፤ በኤግዚቢሽኑ ለዕይታ ካቀረቧቸው የኦፓል አይነቶች መካከልም ክርስታል፣ ፖሊሽ ኦፓልና እርጥብ ገና ያልደረቀ ኦፓል የሚገኝበት መሆኑን አስረድተዋል። ምርቶቹ ለገበያ ለማቅረብ ከፍተኛ የሆነ የገበያ ችግር በመኖሩ መሰል ኤግዚቢሽኖችን ማዘጋጀት ለዘርፉ ዕድገት ጠቃሚ ነው። በተለይም የገበያ ትስስር ለመፍጠርና ገበያ ለማፈላለግ ሰፊ ዕድል የሚፈጥር እንደሆነ በማመን ምርቶቻቸውን ይዘው እንደመጡ ተናግረዋል።
ከዚህ ቀደም በነበራቸው ልምድ በአካባቢው የሚገኘውን የማዕድን ሃብት በተለይም ኦፓሎችን ለላኪዎች ይሸጡ እንደነበር ያስታወሱት አቶ ኡመር፤ ኦፓሎቹ ወደ ውጭ ገበያ የሚላኩት በላኪዎቹ አማካኝነት ነበር። ነገር ግን በአሁን ወቅት ድርጅቱ የማዕድን ሃብቱን በራስ አቅም ወደ ውጭ ገበያ ለመላክ ፈቃድ በማውጣት በዝግጅት ላይ ሲሆን ዓለም አቀፍ የማዕድን ኤግዚቢሽን መከፈቱ ጥሩ አጋጣሚ በመሆኑ የገበያ ትስስር የሚፈጥርና በማዕድን ዘርፉ አዳዲስ የቴክኖሎጂ አማራጮችን የማስተዋወቅ እድል ያሰፋል ብለዋል፡፡
መንግሥት ለዘርፉ በሰጠው ልዩ ትኩረት የማዕድን ሃብቱ አሁን ላይ የተሻለ እንቅስቃሴ እየታየበት እንደሆነ በማንሳት በተለይም ኤግዚቢሽኑ የሚፈጥረው ሰፊ የገበያ ዕድል ስለመኖሩ ነው ያስረዱት። በዕለቱም ለዕይታ ያቀረቡት ኦፓል እሴት የተጨመረባቸው ሲሆኑ ለገበያ የሚቀርቡትም በግራም እንደሆነ ነው ያስረዱት። ከፍተኛ መጠን ያላቸውና ለኢንዱስትሪ ግብዓት መሆን የሚችሉት ደግሞ በቶን የሚሸጡ እንደሆነ መረዳት ተችሏል፡፡
የማዕድን ሃብቱ ከመሬት ውስጥ ተቆፍሮ የሚወጣና በሂደት ጸድቶና ደርቆ ለገበያ ይቀርባል። በአገሪቱ ደላንታ አካባቢ የሚገኘው ኦፓል አንደኛ ሲሆን በዓለም አቀፍ ደረጃም ተመራጭ እንደሆነ ነው የተጠቀሰው። በቀጣይ መንግሥት የገበያ ትስስሩን በማጠናከር ከተለያዩ ካምፓኒዎች ጋር መገናኘት የሚያስችሉ መሰል ኤግዚቢሽኖች ቢዘጋጁ ሰፋፊ የገበያ ዕድሎችን መፍጠር ይቻላል። የገበያ አማራጩም ከማዕድን ዘርፉ የሚገኘውን ኢኮኖሚያዊ ጠቀሜታ ከፍ ያደርገዋል ብለዋል።
የማዕድን ሃብቱ ከአምጪዎቹ በተከታታይ መቅረብ አለበት መቆራረጥ የለበትም የሚሉት አቶ ጌታቸው ታደሰ የጀምስቶን ማዕድን አቅራቢ ማናጀር በበኩላቸው የከበሩ ማዕድናት በሀገሪቱ የተለያዩ አካባቢዎች በስፋት ይገኛሉ። እነዚህን ማዕድናት በማልማትና እሴት በመጨመር ለውጭ ገበያ በማቅረብ ሀገሪቷ ከዘርፉ ኢኮኖሚያዊ ጠቀሜታ ማግኘት አለባት ይላሉ። የገበያ ትስስር መፍጠር ያስችላል በተባለው ኤግዚቢሽንም በወሎ አካባቢና ከሰሜን ሸዋ አካባቢ ያሰባሰቧቸውን የከበሩ የማዕድን አይነቶች ይዘው ቀርበዋል፡፡
እንደ አቶ ጌታቸው ገለጻ ኦፓሎቹ የሚገኙት በዋናነት ከወሎ ደላንታ ሲሆን ከሰሜን ሸዋ የሚገኘው የማዕድን ዓይነት ገበያ ውስጥ በስፋት አለመግባቱ ነው። ለዚህም ምክንያት ሲቆረጥ በቀላሉ የሚቆረጥና ጥንካሬው እምብዛም መሆኑ ነው። በመሆኑም በዋናነትና በስፋት ለገበያ እየቀረበ ያለው የወሎ ደላንታ ኦፓል ነው። ድርጅቱም ኦፓሉን እሴት በመጨመር አለስልሶ ለተለያዩ ጌጣጌጦች ጥቅም ላይ መዋል እንዲችሉ በማድረግ ለውጭ ገበያ እያቀረበ ይገኛል፡፡
በዋናነት ለጌጣጌጥ አገልግሎት የሚውሉት እነዚህ የከበሩ ማዕድናት በስፋት የሚፈለጉት፣በአውሮፓ፣ በጀርመን፣ በአሜሪካና በተለይም በሕንድ እንደሆነ አቶ ጌታቸው አስረድተው ድርጅታቸውም በአሁን ወቅት ማዕድናቱን በቀጥታ እየላከ መሆኑን ነው ያነሱት። ከዚህ ቀደም የከበሩ ማዕድናት ለላኪዎች ያስረክቡ እንደነበር በማስታወስ አሁን ላይ ሥራው እየተለመደ በመምጣቱ በርካታ ባለሙያዎችን በማሳተፍ እሴት ጨምረው በቀጥታ መላክ መጀመራቸውን ነው ያስረዱት፡፡
በተፈጥሮ ከከርሰ ምድር የሚገኙ የከበሩ ማዕድናት በብዛት በአገሪቱ ጥቅም ላይ ሲውሉ አይስተዋልም ለዚህም የማኅበረሰቡ የግንዛቤ እጥረት ነው የሚሉት አቶ ጌታቸው፤ በዋናነት ማዕድናቱ በሀገሪቱ ስለመኖራቸው ለኅብረተሰቡ ማሳወቅና ከሃብቱ ተጠቃሚ መሆን እንዲችሉ ማድረግ አስፈላጊ ነው። ከዚሀ በተጨማሪም በዘርፉ በመሰማራት ከውጭ ባለሃብቶች ጋር የገበያ ትስስር በመፍጠር ከራስ አልፎ ሀገሪቷ ከዘርፉ ተጠቃሚ እንድትሆን ማድረግ ያስችላል። ለዚህም በዘርፉ አስፈላጊና ተከታታይ የሆነ ስልጠና በመስጠት ባለሙያ በማፍራት ተገቢ እንደሆነ አስገንዝበዋል።
በኤግዚቢሽኑ መክፈቻ እንደተገለጸው ኢትዮጵያ ለተለያዩ ኢንዱስትሪዎች ግብዓትነት የሚውሉ የከበሩ ማዕድናት ያላት ሀገር ናት። ይህንን ሃብትም ለሕዝብ ለማስተዋወቅና ጥቅም ላይ ለማዋል የሚረዳ በመሆኑ የተለያዩ ኤግዚቢሽኖችን ማዘጋጀት ተገቢ እንደሆነ ነው የተጠቀሰው። በዕለቱም የኢፌዴሪ ፕሬዚዳንት ሳሕለወርቅ ዘውዴ በተፈጥሮ ሃብቷ በተለይም ከመሬት ውስጥ ተቆፍሮ በሚወጣው የከበሩ ማዕድናቶቿ እጅግ ሃብታም ሀገር እንደሆነች ነው የተናገሩት፡፡
የእነዚህ የከበሩ ማዕድናት ሃብት ባለቤት የሆነው የኢትዮጵያ ሕዝብ እንደመሆኑ ሃብቱን በግላጭ መመልከት እንዲችል ኤክስፖው መዘጋጀቱን አድንቀው፤ ማኅበረሰቡ ማዕድናቱን እንዲያውቅ፣ ጠቀሜታቸውን እንዲረዳና አልምቶ መጠቀም እንዲችልም ዕድል የሚፈጥር በመሆኑ ሊበረታታ ይገባል በማለት ምስጋናቸውን አቅርበዋል። ሀገሪቷ ያላትን ሃብት ከማስተዋወቅ ባሻገር ኤግዚቢሽኑ ሰፊ የገበያ ትስስር መፍጠርና የልማት ቴክኖሎጂ ልውውጥ ማድረግ የሚስችል በመሆኑ ሊበረታታ ይገባልም ብለዋል፡፡
‹‹ማዕድን በባህሪው አላቂ ሃብት እንደመሆኑ ያለንን ውስንና አላቂ ሃብት በአግባቡ መጠቀም ተገቢ እንደሆነና ዘርፉን ከሕገወጥ መንገድ መከላከል አስፈላጊ ነው›› ያሉት ፕሬዚዳንቷ፤ የማዕድን ዘርፉ በብዛት ለሕገወጥ ተግባር የተጋለጠ መሆኑን ገልጸዋል። በተለይም የማዕድን ሃብቱን በተለያየ መጠን ማልማት የሚቻል በመሆኑ በቀላሉ በሕገወጥ መንገድ ሃብቱን መጠቀም ያስችላል። ለዚህም ሕጋዊና ፍትሐዊ በሆነ መንገድ የአካባቢ ጥበቃን ማስጠበቅ በሚያስችል መንገድ መሥራት ከተቻለ በድህነት ውስጥ ያለውን ሕዝብ ከድህነት ማውጣት የሚስችል ዘርፍ እንደሆነ ነው ያስረዱት።
የማዕድን ሚኒስቴሩ ኢንጅነር ታከለ ኡማ በበኩላቸው፤ ኢትዮጵያ ያላትን የማዕድን ሃብት ለበርካታ ዓመታት ሳትጠቀምበት መቆየቷን አንስተው በአሁን ወቅት ዘርፉ ላይ ያሉ ችግሮችን በመቅረፍ የሀገሪቱ ክፍለ ኢኮኖሚ የማድረግና ተጠቃሚነቷን ለማረጋገጥ ትኩረት ተሰጥቶት እየተሠራ እንደሆነ ገልጸዋል። እንደሳቸው ገለጻ፤ ማዕድን የሀገሪቱ ክፍለ ኢኮኖሚ ግንባታ እንደመሆኑ ካለፉት ሁለትና ሦስት ዓመታት ወዲህ በኮንስትራክሽን፣ በኢንዱስትሪና በሌሎች ዘርፎች ላይ የመጣው ለውጥ በማዕድንም እየመጣ መሆኑን አብራርተዋል። በሚቀጥሉት አስር ዓመታትም የማዕድን ክፍለ ኢኮኖሚ አሁን ለኢኮኖሚው እያዋጣ ካለው አንድ በመቶ ያልበለጠ ጂዲፒ ለሚቀጥሉት አስራ አራትና አስራ አምስት ዓመታት ከ17 በመቶ በላይ ሊያዋጣ የሚችል እንደሆነና ተስፋ የተጣለበት እንደሆነም ተናግረዋል።
ዘርፉን ለማሳደግ የሚረዱ አዋጆችና ፖሊሲዎች ተቀርጸው ተግባራዊ መደረጋቸውን የገለጹት ሚኒስቴሩ፤ በተለይም ከተለያዩ የውጭ አገራት የሚገቡ ውድና የከበሩ ማዕድናትን በሀገር ውስጥ ለመተካት እየተሠራ ነው ብለዋል። ለዚህም ግልጽ፣ ሊያሠራና ተግባራዊ ማድረግ የሚያስችል የማዕድንና የፔትሮሊየም ፖሊሲ ተቀርጾ ሥራ መጀመር ተችሏል። ዘርፉን የሚመራው የማዕድን ሚኒስቴርም አስፈላጊ የሆኑ አዋጆችና መመሪያዎችን አደራጅቶ ከፌዴራል እስከ ክልል ማውረድ መቻሉን ገልጸዋል፡፡
ኤክስፖው መዘጋጀቱ የተለያየ የገበያ ትስስሮችን በስፋት ለመፍጠርና ምርቶቻቸውን ለማስተዋወቅ ሊያግዛቸው የሚያስችል ትልቅ ዕድል እንደሆነ የገለጹት የኤክስፖው ተሳታፊዎች እንዲህ አይነት ኤክስፖ በተለያየ ጊዜ ቢዘጋጅ መልካም እንደሆነ ጠቁመዋል። በዘርፉ የተሠማሩና ማዕድን አግኝተው የት መሄድ እንዳለባቸው የማያውቁ በርካታ ሰዎች ስለመኖራቸው በማንሳትም እንዲህ ያሉ መድረኮች ዘርፉን ይበልጥ ሊያስተዋውቁ ይችላሉ፡፡
እንዲህ አይነት አጋጣሚዎች በተለይም የገበያ ትስስርን በመፍጠር ረገድ አበርክቷቸው ጉልህ መሆኑን በመግለጽም ገበያውና ምርቱም በቀጥታ የተገናኘበት እንደሆነ አንስተዋል። ኤክስፖው ማዕድናቱን ለማኅበረሰቡ ከማስተዋወቅ ባለፈ በአፍሪካ ደረጃ መዘጋጀቱ ሰፊ የገበያ ትስስር መፍጠር አስችሏል። በተጨማሪም ሲፈላለጉ የነበሩ የተለያዩ አካላትን በማገናኘት ጉልህ ሚና ያለው መሆኑንም አስረድተዋል።
ፍሬሕይወት አወቀ
አዲስ ዘመን ህዳር 14/2015