ከቅርብ ግዜያት ወዲህ በኢትዮጵያ ፈጣን ለውጥ እያስመዘገቡ ካሉ ዘርፎች መካከል የሳይንስና ቴክኖሎጂ አንዱ እየሆነ ነው። መንግሥት ልዩ ትኩረት በመስጠት እየሠራቸው ያሉ ተግባራት ይህንኑ የሚያመላክቱ ናቸው። እንደ ምሳሌነት ብናነሳ ታዳጊዎች፣ ወጣቶችና በዘርፉ ላይ የሚሠሩ ምሑራንና ተመራማሪዎችን የሚያግዙ ተቋማትንና መሠረተ ልማቶችን መገንባቱ መጥቀስ እንችላለን። በተለይ ታዳጊዎች በፈጠራና ምርምር የቴክኖሎጂና ሳይንስ ግኝቶች ላይ ያላቸው ተሳትፎ እንዲያድግ ልዩ ልዩ ማዕከላት እየተገነቡ ነው። ከእነዚህ ውስጥ ወጣቶችንና ታዳጊዎችን የሚያበረታታው ሳይንስ ሙዚየም ተጠቃሽ ነው።
ከላይ ካነሳናቸው የመንግሥትና የዘርፉ ባለሙያዎች ጥረት ባሻገር ኢትዮጵያ ዓለም አቀፍ ግንኙነቶችን እና የልምድ ልውውጦችን በማድረግ እረገድ ስኬት እያስመዘገበች ትገኛለች። ለዚህ ማሳያ የሚሆኑ በርካታ የትብብር ማዕቀፎችን ከልዩ ልዩ አገራት ጋር ከመፈራረም ባሻገር ዓለም አቀፍ መድረኮችና የኢኖቬሽን፣ ሳይንስና ቴክኖሎጂ ግንኙነቶችን ላይ እየተሳተፈች ነው። በዚህ ምክንያት ዘርፉን የሚያነቃቁ በሮች እየተከፈቱ ይገኛሉ። ከተሳትፎ ባሻገር ደግሞ በያዝነው ወር አንድ ታላቅ ጉባኤ ለማድረግ ዝግጅት አጠናቅቃለች። ይህ መድረክ “ዓለም አቀፉ የበይነ መረብ አስተዳደር ጉባኤን” ሲሆን ለኢትዮጵያ ዘርፉን ከማሳደግ አንፃር በር ከፋች እንደሆነ እየተነገረለት ነው። የፊታችን ኅዳር 19 ተጀምሮ ለሦስት ተከታታይ ቀናት የሚቆየው መድረኩ በርካታ ሁነቶች ያካተተ ነው።
እንደሚታወቀው ኢትዮጵያ የዲጂታል ኢትዮጵያ 2025 ስትራቴጂን ቀርፃና አፅድቃ ወደ ሥራ ገብታለች። ከዚህ የስትራቴጂ ሰነድ እንደምንረዳው የዲጂታል ዕድሎችን በመጠቀም ፈጠራ የታከለበትና በእውቀት ላይ የተመሠረተ ኢኮኖሚ ለመገንባት የመንግሥት ተነሳሽነት መኖሩን ነው፡፡ ከአገር በቀል የኢኮኖሚ ማሻሻያ አጀንዳ እና የአስር ዓመት የልማት ዕቅድን ከመሳሰሉ ቁልፍ ሀገራዊ ስትራቴጂዎች ጋር እንዲሁም እንደ አፍሪካ ኅብረት አህጉራዊ ዲጂታል ትራንስፎርሜሽን ስትራቴጂ ካሉ ዓለም አቀፍ ስትራቴጂዎች ጋር የተሳሰረ መሆኑንም ያስረዳናል፡፡
ይህን ስትራቴጂ ለማሳካት ደግሞ በመጪው ኅዳር ወር የሚካሄደው “ዓለም አቀፍ የበይነ መረብ አስተዳደር ጉባኤ” አይነት መድረኮች ጠቀሜታቸው የጎላ ነው። በተለይ የበይነ መረብ አጠቃቀም ፍትሐዊነት፣ እድገትና አስተዳደርን በተመለከተ ኢትዮጵያ ከአደጉ አገራት ልምድ ለመለዋወጥ እድሉን በስፋት የምታገኝበት ይሆናል። ከዚያም ባለፈ የአገር ገፅታን ለመገንባት፣ ወጣቶች በዲጂታል ቴክኖሎጂና መሰል ዘርፎች ላይ በቀጥታ ተሳታፊ እንዲሆኑና ትስስር እንዲፈጥሩ አጋጣሚውን የሚከፍት ዝግጅት እንደሚሆን ይጠበቃል።
ከሰሞኑ የኢኖቬሽን ቴክኖሎጂ ሚኒስትር ኅዳር 19 የሚካሄደውን ዓለም አቀፍ የበይነ መረብ አስተዳደር ጉባኤ አስመልክቶ ጋዜጠኞች እና የመንግሥት ተቋማት የሕዝብ ግንኙነት ባለሙያዎች መድረኩን በማስተዋወቅ ረገድ የበኩላቸውን እንዲወጡ ጠይቆ ነበር። በድረ ገፅና እና በቀጥታ መድረክ በተላለፈው በዚህ መግለጫ ላይ ስለጉባኤው ምንነትና ጠቀሜታዎች ሰፋ ያለ ማብራሪያም ተሰጥቶበት ነበር።
የኢኖቬሽንና ቴክኖሎጂ ሚኒስትር ዴኤታ ሁሪያ አሊ “በአዲስ አበባ የሚካሄደው የበይነ መረብ አስተዳደር ጉባኤ የአፍሪካን የዲጂታል ጉዞ ቅርፅ ለማስያዝ የሚያስችሉ ጉዳዮች ይነሱበታል” ይላሉ። የኢኖቬሽንና ቴክኖሎጂ ሚኒስቴር፣ የአፍሪካ ኢኮኖሚክ ኮሚሽን እና የተባበሩት መንግሥታት የኢኮኖሚና ማኅበራዊ ጉዳዮች ልማት በጉባኤው ዙሪያ በአካል እና በኦንላይን ለተሳተፉ ጋዜጠኞች ጋዜጣዊ መግለጫ በሰጡበት ወቅት ሀሳባቸውን የሰጡት ሚኒስትር ዴኤታዋ ኢትዮጵያ ይህንን ጉባኤ በስኬት አስተናግዳ ለማጠናቀቅ ብሔራዊ ኮሚቴ በማቋቋም እየሠራች መሆኑን ያነሳሉ። በተለየ መልኩ ጉባኤው የተሳካ እንዲሆን አስፈላጊው ዝግጅት በመጠናቀቅ ላይ መሆኑን የሚናገሩት ወይዘሮ ሁሪያ በተለያዩ የተመረጡ የኢንተርኔት አስተዳደር ጉዳዮች ዙሪያ ይመክራል በማለት የበይነመረብ አስተዳደር ጉዳይ የመሪዎች ቅድሚያ አጀንዳ እንዲሆን እንደሚሠራ ነው የሚገልፁት።
ዣን ዡ በተባበሩት መንግሥታት ድርጅት የሕዝባዊ ተቋማት እና ዲጂታል መንግሥት ዲቪዥን ዳይሬክተር ናቸው። ከኢኖቬሽን ቴክኖሎጂ ሚኒስትር ጋር መድረኩ በስኬት ስለሚጠናቀቅበት መንገድ በተለያዩ ግዜያት ምክክር ያደርጋሉ። እንደ እርሳቸው እይታ “ጉባኤው የአፍሪካን የዲጂታል ጉዞ ቅርፅ ለማስያዝ የሚያስችሉ ጉዳዮች ይነሱበታል” የእርሳቸው አስተዳደርም ይህ ዓላማ ግቡን እንዲመታ የድርሻቸውን ይወጣሉ።
ኢትዮጵያ በመጪው ኅዳር 19 ቀን በምታስተናግደው ዓለም አቀፉ የበይነ መረብ አስተዳደር ጉባኤ ላይ ከ2ሺ እስከ 2ሺ 500 የሚደርሱ ተሳታፊዎች እንደሚታደሙበት የኢኖቬሽን ቴክኖሎጂ ሚኒስትር ይፋ አድርጓል። የዝግጅት ክፍላችንም ይህንን ጉባኤ በተመለከተ የሚኒስትር መሥሪያ ቤቱ ሚኒስቴር ዴኤታ የሰጡትን ማብራሪያ ተከታትሎ“ የተወሰኑ ነጥቦች ሰለ በይነ መረብ አስተዳደር ጉባኤ ምንነት፣ ጉባኤው ስለሚያነሳቸው ጉዳዮች እና ለኢትዮጵያ ስላለው ጠቀሜታ ከዚህ እንደሚከተለው አቅርቦላችኋል።
የበይነ-መረብ አስተዳደር ጉባኤ ምንድነው?
የበይነመረብ አስተዳደር ጉባኤ ከበይነመረብ ጋር ተያይዞ ያሉ ዕድሎችን እንዲሁም ፈተናዎችን በተመለከተ የሚነሱ ሀሳቦች የሚንሸራሸሩበትና የጋራ ግንዛቤ የሚፈጠርበት፣ ለፖሊሲ አውጪዎች የመነሻ ሃሳብ የሚገኝበት የውይይት መድረክ ነው፡፡
በይነ-መረብ ጥቅሞች እንዳሉት ሁሉ የተለያዩ ጉዳቶችም አሉት፡፡ ይህም ከመረጃ መረብ ወንጀሎች፣ ከጥላቻ ንግግሮች፣ የሐሰትና የተዛቡ ዜናዎች ስርጭት አኳያ የተለያዩ ማኅበራዊ፣ ፖለቲካዊና ኢኮኖሚያዊ አሉታዊ ጎኖች አሉት። የበይነመረብ አስተዳደር ፎረምም እነዚህን ጉዳዮች በሕግና በሌሎች ማዕቀፎች የሚፈቱበት አግባብ የሚመላከትበት ጉባኤ ነው፡፡ ጉባኤው አስገዳጅ የሆኑ ውሳኔዎች የሚወሰኑበት ሳይሆን ውሳኔ አመንጪና ሰጪ የሆኑት የግሉን ዘርፍና መንግሥትን በጉዳዮቹ ላይ የመረጃና የፖሊሲ ሀሳብ መነሻ ሆኖ የሚያገለግል ነው፡፡
የበይነ መረብ (ኢንተርኔት አስተዳደር ፎረም) “IGF” ከኢንተርኔት አስተዳደር ቁልፍ አካላት ጋር በተያያዙ የሕዝብ ፖሊሲ ጉዳዮች ላይ የብዙ ባለድርሻ አካላት ውይይት ይደረጋል። እንደ አውሮፓውያኑ አቆጣጠር በ2006 ከተካሄደው ከመጀመሪያው ስብሰባ ጀምሮ (አይ ጂ ኤፍ) በተባበሩት መንግሥታት ድርጅት ዋና ጸሐፊ “በቱኒስ አጀንዳ ለኢንፎርሜሽን ሶሳይቲ” በተቀመጠው ትእዛዝ መሠረት በየዓመቱ ይጠራል። ፎረሙ የውይይት መድረክ እንደመሆኑ መጠን የተለያዩ ባለድርሻ አካላትን በእኩል መጠን መረጃ ለመለዋወጥ እና መልካም ተሞክሮዎችን ለመለዋወጥ ወደ ጠረጴዛው ያቀርባል። አይ ጂ ኤፍ የበይነ መረብ እድሎችን እንዴት ከፍ ማድረግ እና አደጋዎችን እና ተግዳሮቶችን እንዴት እንደሚፈታ የጋራ ግንዛቤን ያመቻቻል።
ምንም እንኳን የቱኒዝ አጀንዳ በሕጋዊ መንገድ አስገዳጅ ባይሆንም የዓለም አቀፍ ጉባዔ ስለ መረጃ ማኅበር ዓላማዎችን እና የድርጊት መስመሮችን በሀገር አቀፍ፣ በክልላዊ እና በዓለም አቀፍ ደረጃ ትግበራን በተመለከተ ተከታታይ ምክሮችን ይዘረዝራል። ከእነዚህም መካከል ብሔራዊ ኢ-ስትራቴጂዎችን እንደ ሰፊው አገራዊ የልማት ዕቅዶች መገንባት፣ የሁለትዮሽ እና የባለብዙ ወገን የቴክኒክ ድጋፍ ፕሮግራሞችን በመጠቀም፣ የተባበሩት መንግሥታት የክልል ኮሚሽኖችን እና የተባበሩት መንግሥታት ኤጀንሲዎችን በአፈፃፀም ሂደት ውስጥ ማሳተፍ እና የሁሉም ባለድርሻ አካላት በአፈፃፀም እንቅስቃሴዎች ውስጥ ተሳትፎን ያካትታሉ። ለምሳሌ በ2015 የዓለም አቀፍ ጉባዔ ስለ መረጃ ማኅበር ውጤቶች አፈፃፀም አጠቃላይ ግምገማም ተጠርቶ ነበር። አጀንዳው በተባበሩት መንግሥታት ጠቅላላ ጉባኤ ከሚያዝያ 2006 ባወጣው ውሳኔ 60/252 ጸድቋል።
ከ2022 መድረክ ምን እንጠብቅ
እንደሚታወቀው በይነ-መረብ ጥቅሞች እንዳሉት ሁሉ የተለያዩ ጉዳቶችም አሉት፡፡ ይህም ከመረጃ መረብ ወንጀሎች፣ ከጥላቻ ንግግሮች፣ የሐሰትና የተዛቡ ዜናዎች ስርጭት አኳያ የተለያዩ ማኅበራዊ፣ ፖለቲካዊና ኢኮኖሚያዊ አሉታዊ ጎኖች አሉት፡፡ የበይነ-መረብ አስተዳደር ፎረምም እነዚህን ጉዳዮች በሕግና በሌሎች ማዕቀፎች የሚፈቱበት አግባብ የሚመላከትበት ፎረም ነው፡፡
ይህ ፎረም ለመጀመሪያ ጊዜ እኤአ በ2006 በአቴንስ፣ ግሪክ ከተደረገ በኋላ እስካሁን ድረስ 16 ግዜ በተለያዩ ሀገራት ተካሂዷል። 17ኛው ፎረም ደግሞ ኅዳር 2015 በኢትዮጵያ ይካሄዳል፡፡ በኅዳር 19 ቀን ኢትዮጵያ በምታካሂደው ጉባኤ አምስት አበይት ጭብጦች ላይ ይመክራል ተብሎ ይጠበቃል።
የመጀመሪያው አጀንዳ “ከበይነ መረብ ግንኙነት ውጪ የሆኑ ሕዝቦችን ማገናኘትና ሰብዓዊ መብትን መጠበቅና ሰዎችን ከጥቃት መከላከል” የሚል ሲሆን በሁለተኛነት ደግሞ “ዳታን በአግባቡ ማስተዳደርና የግል ዳታ ጥበቃ” የተመለከቱ ሃሳቦች ይነሳሉ። ሦስተኛው የጉባኤው አጀንዳ “የተቆራረጠ የኢንተርኔት አገልግሎትን መቅረፍ” የሚል ሲሆን በዚህ ዙሪያም ሰፊ ምክክሮች እንደሚደረግ ይጠበቃል። የበይነ መረብ አስተዳደር ሲነሳ ሌላኛው ቁልፍ ጉዳይ “ደህንነትን ማረጋገጥ፣ ጥበቃ ማድረግና ተጠያቂነትን ማስፈን” የሚለው ነጥብ ሲሆን ይህም በአራተኛ ደረጃ በጉባኤው በአጀንዳነት ተነስቶ ምክክር ይደረግበታል።
የመጨረሻውና አምስተኛው የመድረኩ ቁልፍ አጀንዳ “የመጪ ግዜ ቴክኖሎጂዎች የሆኑትንና እንደ ሰው ሰራሽ አስተውሎት (Artificial Intelligence)” ላይ የሚያተኩር ሲሆን በዚህ ዙሪያም ሰፋ ያለ ምክክር፣ የሃሳብ ልውውጥ እንዲሁም ጥናታዊ ጽሑፎች እንደሚቀርቡ ይጠበቃል።
ኢትዮጵያ ለምን ተመረጠች?
የኢኖቬሽን ቴክኖሎጂ ሚኒስትር መረጃ እንደሚጠቁመው ኢትዮጵያ 17ኛውን የበይነ መረብ አስተዳደር ጉባኤ እንድታዘጋጅ የተመረጠችበት ምክንያት በቴክኖሎጂ ዘርፍ የተለያዩ ለውጥና እድገቶች እያስመዘገበች መሆኗ፣ ለዚህም ማሳያ የሚሆነው ኢትዮጵያ የዲጂታል ኢትዮጵያ 2025 ስትራቴጂ ፀድቆ ወደ ሥራ መግባቱ፣ በቴሌኮም ዘርፍ የተለያዩ የማሻሻያዎች በማድረግ ዘርፉን ለዓለም አቀፍ ተወዳዳሪዎች ክፍት ማድረጓ እና የቴሌኮምና የበይነ መረብ ተደራሽነትን ለማሳደግ እያደረገች ባለው ጥረት ነው፡፡ ሌላኛው ምክንያት ኢትዮጵያ ወደ 56 ሚሊዮን ገደማ የሞባይል ተጠቃሚ መሆኗና ከ20 ሚሊዮን በላይ የበይነመረብ ተጠቃሚዎች መኖራቸው አዘጋጅ ሀገር ሆና እንድትመረጥ አስችሏታል።
ኢትዮጵያ ከዚህ ጉባኤ ምን ትጠቀማለች ?
የኢኖቬሽን ቴክኖሎጂ ሚኒስትር ያወጣው መረጃ እንደሚያመለክተው ኢትዮጵያ ዓለም አቀፉን የበይነ መረብ አስተዳደር ጉባኤ ስታስተናግድ የተለያዩ ጥቅሞችን ታገኛለች። ከእነዚህም ውስጥ፤ እንግዳ ተቀባይና የመቻቻል ተምሳሌት የሆነውን የኢትዮጵያ ሕዝብና የሰው ዘር መገኛ የሆነችውን ሀገር በዓለም አቀፍ ማኅበረሰብ ዘንድ ማጉላት እና ገጽታ ለመገንባት ፤ ኢትዮጵያ የጀመረችውን የቴሌኮም ሪፎርም እንዲሁም በዘርፉ ያሉ ውጤቶችን ለሌሎች ሀገራት ለማሳየት፤ የጉባኤው ተሳታፊዎች የሀገሪቱን እድገት እንዲገነዘቡ ለማስቻል፤ ከተለያዩ ሃገር አቀፍ እና ዓለም አቀፍ ባለድርሻ አካላት እና የልማት አጋሮች ጋር ትስስር ለመፍጠር፤እንዲሁም ከኮንፈረንስ ቱሪዝም ተጨማሪ የውጭ ምንዛሪ ለማግኘት ይጠቅማል።
ዳግም ከበደ
አዲስ ዘመን ኅዳር 13/ 2015 ዓ.ም