ሃውለት ሁሴን በአጣዬ ከተማ ሰላማዊ በተሰኘች ሰፈር ትኖራለች። ለዓመታት ሁለትና ሶስት ሰዓታትን በእግሯ ተጉዛ የመጠጥ ውሃ ስትቀዳ ቆይታለች። ውሃውን በጀሪካን ቀድታ በጀርባዋ አዝላ አንዴ ዳገቱን አንዴ ቁልቁለቱን ስትል ደክሟት ከቤት ትደርሳለች።
አንዳንዴ በለስ ቀንቷት ውሃውን በአህያ ጭና ብታመላልስም ያን ያህል ጉልበቷንም ጊዜዋንም አታድንም። ውሃውንም በፈለገችው ሰዓት ለመጠጥም ሆነ ምግብ ማብሰያነት አታገኘውም። ምክንያቱም ቦታው በመራቁ የተነሳ ብዙ ጊዜ ማትረፍ አትችልምና። ከዚያም የሚብሰው ደግሞ እንዲህ ለፍታ የወሰደችው ውሃ እምብዛም ጥራት ያለው ባለመሆኑ የተነሳ ለመጠጥነትና ለምግብ ማብሰያነት መጠቀም አለመቻሏ ነው።
ዛሬ ግን እዛው በምትኖርበት አካባቢ ፕላን ኢንተርናሽናል ኢትዮጵያ የተሰኘው ግብረሰናይ ድርጅት ከዩኒሴፍ ጋር በመተባበር የንፁህ መጠጥ ውሃ በመገንባቱ እፎይ ብላለች። ውሃው በደጇ በመሆኑም ብዙ ጉልበት ሳታወጣ ቀድታ ለመጠጥ፣ ለፅዳትና ምግብ ማብሰያነት ትጠቀማለች። በውሃው ውስጥ የማከሚያ ኬሚካል በመግባቱ የጤና መታወክ ይደርስብኛል ከሚል ስጋትም ተላቃለች።
ከዚህ አልፎ ዛሬ ላይ ውሃው የሚገኘው ከበሯ ላይ በመሆኑ የውሃው አስቀጂ ለመሆንም በቅታለች። የንፁሕ መጠጥ ውሃው በአቅራቢያ በመሠራቱ እርሷ ብቻ ሳትሆን የአካባቢው ጎረቤቶቿም ከልፋትና ከንፁሕ መጠጥ ውሃ እጦት ተገላግለዋል።
ይህ ሆኖ ሳለ ታዲያ ለአካባቢው ማኅበረሰብ የተገነባው የንፁህ መጠጥ ውሃ ከነዋሪው ቁጥር ጋር የማይመጣጠንና አሁንም ወረፋ የሚታይበት በመሆኑ ተጨማሪ ግንባታ እንደሚያስፈልግ ሃውለት ትናገራለች። ቦታው ዳገታማ በመሆኑ ደግሞ አልፎ አልፎ የኃይል መቆራረጥ ያጋጥማልና ይህም ቢታሰብበት መልካም ነው ትላለች።
መስኪያ መሐመድም በዛው የአጣዬ ከተማ ሰላማዊ ሰፈር ነዋሪ ናት። ልክ እንደ ሃውለት ንፁህ የመጠጥ ውሃ ለመቅዳት ሁለትና ሦስት ሰዓታትን በእግሯ ትጓዝ ነበር። አውሬሳ ከተባለው ስፍራ ውሃ ቀድታ ተሸክማ ስትጓዝ መሽቶባት ያውቃል። ውሃውን በፈለገችው ሰዓት ባለማግኘቷ ቤተሰቦቿ ተጠምተዋል፤ተርበዋልም።
እርሷም ቢሆን ውሃ ቀድቶ ለቤተሰብ ለማምጣት በሚፈጅባት ጊዜ ምክንያት ከትምህርቷ ተስተጓጉላለች። ከዚህ በፊት የንፁሕ መጠጥ ውሃ በቅርበት ማግኘት የማይታሰብ በመሆኑ ዛሬ ውሃው በሰፈሯ ሲገባ ለእርሷ ትንግርት ሆኖባታል። ፕላን ኢንተርናሽናል ኢትዮጵያ በሰፈሯ የገነባው የንፁሕ መጠጥ ውሃ ፕሮጀክት የዓመታት ድካሟን አስቀርቶላታል። በዚህም ደስታዋ ወደር የለውም። አሁን ላይ የጀሪካን ውሃ በጀርባ አዝሎ ረጅም ርቀት መጓዝ ለእርሷ ታሪክ ሆኗል።
አሁን መስኪያ ወዲያው ንፁሕ ውሃ ቀድታ መጠጣት፣ ምግብ ማብሰልና ልብስ ማጠብ ችላለች። የምትወደው ትምህርቷንም ሳታቋርጥ እየተማረች ነው። የእርሷ ደስታ ወደቤተሰቦቿም ተጋብቷል።
የሃውለትና መስኪያ ታሪክ በንፁሕ ውሃ መጠጥ እጦት የሚሰቃዩ የበርካታ በገጠሪቷ ኢትዮጵያ የሚኖሩ ሴቶች ታሪክ ነው። አዎ! አሁንም በተለያዩ የሀገሪቱ ክፍሎች የሚገኙ በርካታ የኢትዮጵያ ሴቶች ንፁሕ መጠጥ ውሃ ፍለጋ በእግራቸው ሁለትና ሦስት ሰዓታትን ከፍ ሲልም እስከ አራት ሰዓት ይጓዛሉ። ሌላው ቀርቶ የአፍሪካ መዲና በምትባለው አዲስ አበባ እንኳን ጥቂት የማይባሉ ሴቶች የንፁሕ መጠጥ ውሃ ፍለጋ ጀሪካ ይዘው ከአንዱ ቤት አንዱ ቤት ሲዘዋወሩ ማየት ብርቅ አይደለም። ውሃ ማግኘትም ብርቅ የሆነባቸው ቦታዎችም አይጠፉም።
በኢትዮጵያ አሁንም የመጠጥ ውሃና የንፅሕና መጠበቂያ አገልግሎቶችን ማግኘትና በሚፈለገው ልክ ተደራሽ ማድረግ እጅግ ፈታኝ እንደሆነ መረጃዎች ያመላክታሉ። በተለይ የንፁሕ የመጠጥ ውሃን በሁሉም አካባቢ ተደራሽ ለማድረግ እቅድ ተይዞ ሥራዎች እየተሠሩ ነው ቢባልም አሁንም ብዙ ሥራዎች ይቀራሉ ።
እነዚህን ችግሮችን ለመፍታት ከሚንቀሳቀሱ ተቋማት መካከል ፕላን ኢንተርናሽናል ኢትዮጵያ አንዱ ሲሆን፤ የንፁሕ መጠጥ ውሃና የንፅሕና ተቋማት ግንባታ ፕሮጀክቶች የዚህ መርሐ ግብር አንዱ አካል አድርጎ በመሥራት የመጠጥ ውሃ ተደራሽነት አነስተኛ በሆነባቸው አካባቢዎች እየተተገበረ የሚገኘው ‹‹ብሔራዊ ዋን ዋሽ›› መርሐ ግብርን እውን ያደርጋል።
አቶ አሳልፍ ደርቤ የአጣዬ ከተማ ከንቲባ ናቸው። እርሳቸው እንደሚሉት፤ ከተማዋ ላለፉት አራት ዓመታት ተደጋጋሚ ችግሮች ሲያጋጥሟት ቆይቷል። ከሀገራዊ ለውጡ ማግስት በከተማዋ ሰባት ጊዜ ጦርነት ተካሂዷል። ከዚሁ ጦርነት ጋር በተያያዘም በከተማዋ የ225 ሰዎች ሕይወት ጠፍቷል። 423 መኖሪያ ቤቶች ተቃጥለዋል። 50 የሚጠጉ ሆቴሎችም ወድመዋል። በተጨማሪም ከጦርነቱ ጋር ተያይዞ በዋናነት የውሃ አገልግሎቱ ቆሟል። በዚህም ፕላን ኢንተርናሽናል ኢትዮጵያ በከተማዋ በመምጣት ዘርፈ ብዙ የውሃ አገልግሎቶችን ገንብቷል።
የመጀመሪያው በ3 ነጥብ 7 ሚሊዮን ብር ወጪ በሦስት ቀበሌዎች ላይ 12 ኪሎ ሜትር የውሃ መስመር ዝርጋታ ሲሆን፤ የውሃ ቦኖዎችም ከዚሁ ጋር ተያይዞ ተገንብተዋል። ሮቶዎችም ተቀምጠዋል።
እንደ ከንቲባው ገለፃ፤ በማኅበረሰቡ ውስጥ ሰፊ የውሃ ችግር የነበረ በመሆኑ ይህን የውሃ ችግር ፕላን ኢንተርናሽናል ኢትዮጵያ በብዙ መልኩ ፈትቶታል። አሁንም ቢሆን በከተማዋ የውሃ፣ የጤናና የትምህርት የመሠረተ ልማት ችግሮች በመኖራቸው እነዚህን የማስጀመር ሥራዎች እየተከናወኑ ይገኛሉ። ነገር ግን እነዚህ የመሠረተ ልማት ሥራዎች ሙሉ በሙሉ ባለመጀመራቸው በቀጣይ ፕላን ኢንተርናሽናልን ከመሰሉ መንግሥታዊ ያልሆኑ ድርጅቶች ጋር በመተባበር ለመሥራት ጥረት ይደረጋል።
በፊት ከነበረው ሁኔታ አንፃር ማኅበረሰቡ በተሻለ ሁኔታ የውሃ አገልግሎቶችን ጨምሮ ሌሎች የመሠረተ ልማት ተጠቃሚነትን እያገኘ እንደሆነ የሚያነሱት ከንቲባው፤ በፕላን ኢንተርናሽናል ኢትዮጵያ አማካኝነት የተገነቡ የንፁሕ መጠጥ ውሃ ፕሮጀክቶች በቂ ባለመሆናቸው ተጨማሪ የመጠጥ ውሃ ጉድጓድ ቁፋሮ ማካሄድ እንደሚጠይቅ ይናገራሉ። መጠባበቂያ ንፁህ መጠጥ ውሃና የመስመር ዝርጋታም እንደሚያስፈልግ ያስረዳሉ። ይህን ማድረግ ካልተቻለ ቀደም ሲል በግጭቱ ምክንያት ከተማዋን ለቆ የወጣው ማኅበረሰብ ሲመለስ ከፍተኛ የውሃ እጥረት ሊያጋጥም ይችላል። በመሆኑም የንፁሕ መጠጥ ውሃውን ይበልጥ ለማስፋት በመንግሥትና መንግሥታዊ ባልሆኑ ድርጅቶች መካከል በትብብር መሥራት እንደሚጠበቅም አስገንዝበዋል።
በሌሎች የመሠረተ ልማት ግንባታዎች ላይም ርብርብ ማድረግ እንደሚያስፈልግ የሚገልጹት አቶ አሳልፍ፤ ለዚህም ፕላን ኢንተርናሽናል ኢትዮጵያ ብቻ ሳይሆን ሌሎችም መንግሥታዊ ያልሆኑ ልማታዊ ድርጅቶች ድጋፋቸውን ማሳየት ይኖርባቸዋል ይላሉ።
በፕላን ኢንተርናሽናል ኢትዮጵያ የዋሽ ፕሮጀክት ማናጀር አቶ ወንደሰን አድማሱ እንደሚናገሩት፤ ድርጅቱ በአማራ ክልል የተለያዩ ዞኖችና ወረዳዎች በተለያዩ ፕሮግራሞች ማለትም በንፁሕ መጠጥና ንፅሕና፣ ትምህርትና ጤና ላይ መዋዕለ ንዋዩን በማፍሰስ ማኅበረሰቡን እያገለገለ ይገኛል። ከእነዚህ ተግባራት ውስጥ አንዱ የንፁሕ መጠጥ ውሃ አቅርቦት ሲሆን፤ ይህም በሰሜን ሸዋ ዞንና በኦሮሞ ብሔረሰብ አስተዳደር ተግባራዊ የሆነ ነው። ለዚህም ፕሮጀክት ወደ 70 ሚሊዮን ብር ተመድቦ በስምንት ወረዳዎች የተለያዩ ሥራዎችን ለማከናወን ተሞክሯል።
ከተከናወኑት ዋና ዋና ተግባራት ውስጥ 16ቱ የተለያዩ የውሃ ተቋማትን የማስፋፋት ሥራዎች ይገኙበታል። በግጭቱ ምክንያት በደብረብርሃን ከተማ ተፈናቅለው በተፈናቃይ መጠለያ ጣቢያዎች ውስጥ ለሚገኙ ወገኖች የመፀዳጃ ቤት ግንባታዎችም ተከናውነዋል።10 የሚሆኑ ሻወር ቤቶችም በእነዚሁ ተፈናቃይ መጠለያ ጣቢያዎች ውስጥ መገንባታቸውንም ያነሳሉ።
ኅብረተሰቡ የውሃ ተቋማት በዘላቂነት አገልግሎት መስጠት እንዲችሉ ከኅብረተሰቡ ለወጡ ተወካዮች የአቅም ግንባታ ስልጠናዎች ተሰጥተዋል። ከዚህ በተጨማሪም ፕሮጀክቱ ተግባራዊ በሚሆንባቸው ስምንት ወረዳዎች ውስጥ ባሉ የውሃ ተቋማት ውስጥ ላሉ ባለሙያዎች የውሃውን ጥራት ከማረጋገጥ አንፃር ከክልሉ ውሃ ቢሮ ጋር በመቀናጀት ስልጠና እንዲያገኙ እንደተደረገም ያስረዳሉ።
ከጤና ጋር በተያያዘ ማኅበረሰቡ ራሱን እንዴት መጠበቅ እንዳለበት የአስተሳሰብ ግንዛቤ ለውጥ እንዲያመጣ የሃይጂን ሳኒቴሽን ማስተዋወቅ ሥራዎች መከናወናቸውን የሚያነሱት አቶ ወንደሰን፤ ይህ በመደረጉ በኅብረተሰቡ ላይ ከመጠጥና ንፅሕና ጉድለት ጋር በተያያዘ ሊከሰቱ የሚችሉ ተላላፊ በሽታዎችን ለመከላከል ተችሏል። በዋናነት በደብረብርሃን ከተማ የተፈናቃይ መጠለያ ጣቢያ ውስጥ ለሚገኙ ተፈናቃዮች የንፅሕና መስጫ ተቋማትን በመገንባት ተላላፊ ያልሆኑ በሽታዎችን ለመከላከል እንዳስቻለም ይናገራሉ።
እንደ ማናጀሩ ማብራሪያ፤ፕላን ኢንተርናሽናል ኢትዮጵያ በአጣዬ ከተማ 12 ኪሎ ሜትር የውሃ መስመር ዝርጋታ አካሂዷል። ይህም ሦስት ቀበሌዎችን የሚሸፍን ሲሆን፤ በዚሁ አገልግሎት 55 ሺህ የሚሆኑ ሰዎች ተጠቃሚ ይሆናሉ። በተጨማሪም 25 ሜትር ኪዩብ ሪዘርቩዬርና አንድ ወተር ፖይንትም ተሠርቷል። በሌሎች አካባቢዎች ላይም በተመሳሳይ ዋተር ፖይንቶች ተሠርተዋል። ይህ ደግሞ ኅብረተሰቡ ከገባበት ከፍተኛ የውሃ እጦትና ከዚሁ ጋር ተያይዞ ሊከሰት የሚችለውን ችግር ለመቅረፍ ተችሏል።
መንግሥት በውሃ አገልግሎት ከሚሠራቸው ሥራዎች ጎን ለጎን ሊኖር የሚችለውን ክፍተት ከመሙላት አኳያም ፕላን ኢንተርናሽናል ኢትዮጵያ የራሱን አስተዋፅኦ እንዳበረከተ የሚናገሩት አቶ ወንደሰን፤ በሚቀጥሉት ጊዜያት ፕላን ኢንተርናሽናል ኢትዮጵያ 35 ሚሊዮን ብር በመመደብ በስምንት ወረዳዎች ከንፁሕ ውሃ መጠጥና ከንፅሕና ጋር በተያያዙ ሥራዎችን ለመሥራት እየተንቀሳቀሰ መሆኑን ይገልጻሉ። ይህንኑ ፕሮጀክት በእነዚህ ወረዳዎች ላይ ተግባራዊ በማድረጉም 170 ሺህ የኅብረተሰብ ክፍሎች ተጠቃሚ እንዲሆኑ አስችሏል።
ይህ ደግሞ ሴቶችን ርቆ ከመሄድና ከጉልበት ብዝበዛ እንዲሁም ሰዓታቸውን ከመቆጠብ አኳያ የማይተካ ሚና እንደሚኖረው ሁሉም ይረዳዋል። ስለሆነም መንግሥታዊም ሆነ መንግሥታዊ ያልሆኑ ተቋማት የውሃ ችግርን ለመፍታት የተቻላቸውን ሁሉ ቢያደርጉ መልካም እንደሆነ በመጠቆም ሀሳባችንን እንቋጭ። ሰላም!!
አስናቀ ፀጋዬ
አዲስ ዘመን ኅዳር 13/ 2015 ዓ.ም