
ሰሚራ ሃይረዲንና ሦስቱ ጓደኞቿ የአዲስ አበባ ከተማ ነዋሪ ናቸው:: ባለትዳርና የቤት እመቤቶች ሲሆኑ ሴቶች በብዛት በማይታዩበት የማኑፋክቸሪንግ ዘርፍ ተሰማርተዋል:: በተለይ ብዙ ሴቶች ደፍረው በማይገቡበት አምራች ዘርፍ ተደራጅተው ለመሥራት አስበው ነው ሥራ የጀመሩት።
አራቱ ጓደኛሞች ሥራውን ለመጀመር ፍላጎትና ተነሳሽነቱ ስለነበራቸውና በሀሳቡ ስለተስማሙ ብቻ ሰተት ብለው ወደ ሥራው አልገቡም:: ሀሳባቸው በጥልቀት በማሰላሰል በታቀዱ ሥራ ዙሪያ መረጃዎችን በማሰባሰብ የዳሰሳ ጥናት እንዲያደርጉ የግድ ብሏቸዋል::
የጀመሩት ከግብ ለማድረስ ወደፊት መጓዝን እንጂ ወደ ኋላ ማፈግፈግ የማይሹት ጓደኛሞቹ ባደረጉት ጥናት መሠረት ስለሚሰሩት ሥራ በደንብ እውቀቱ እንዲኖራቸው በመፈለግ ከሥራቸው ጋር አብሮ የሚሄድ ሙያ ለመቅሰም የሚያስችላቸውን ዲዛይነርነት ትምህርት ተምረው ዲዛይነር መሆን ቻሉ::
ዲዛይነሮቹ ጓደኛሞች ወደ አምራችነቱ ዘርፍ ለመቀላቀል ከንፋስ ስልክ ላፍቶ ክፍለ ከተማ የመሥሪያ ቦታ ሼድና መነሻ ብድር ስላገኙ ሥራቸውን ‹‹አሃዱ›› ብለው ጀመሩ:: ማምረቻ ቦታቸውን ሀና ማርያም አካባቢ አደረጉ:: በ2015 ዓ.ም ሰሚራና ፋጡማ ጨርቃጨርቅና ሕብረት ሽርክና ማኅበር የተሰኘ ድርጅት መሠረቱ:: ባደረጉት የገበያ ጥናት መሰረት የወንዶች ሕጻናት ልብሶች በጥራት ማምረት ጀመሩ:: ጥራት ላይ ትኩረት መስጠታቸው ምርቶቻቸው በፍጥነት በገበያ ተቀባይነት እንዲያገኙ ምክንያት ሆናቸው::
ሥራውን ከጀመሩ ሁለት ዓመት ከስድስት ወራት ገደማ ሆኗቸዋል:: በአጭር ጊዜ በገበያ ተቀባይነት ከማግኘት ባሻገር ከፍተኛ ለውጥ አሳይተው ውጤት ማስመዝገብ ችለዋል:: ይህ ሥራቸውም በተለይ ለሴቶች አርአያ ተደርጎ የሚጠቀስ ነው::
ልብስ የማምረት ሥራውን በ100 ሺ ብር ካፒታል የጀመሩ ሲሆን፤ በአሁኑ ወቅት ከሦስት ሚሊዮን ብር በላይ ካፒታል ማስመዘገብ ችለዋል:: ከጥቃቅን ወደ አነስተኛ አምራችነት ተሸጋግረዋል:: አራት ሆነው ቢደራጁም ለተጨማሪ ስድስት ሰዎች የሥራ እድል በመፍጠር አስር ሆነው ጀምረው፤ ዛሬ ከ90 በላይ ለሚሆኑ ሰዎች ቋሚ የሥራ እድል መፍጠር ችለዋል::
እነ ሰሚራ ወደ ቢዝነሱ ሲገቡ ሥራውን ከመጀመራችን በፊት ስለቢዝነሱ በደንብ ለማወቅ የሌሎች ሰዎች ልምድና ተሞክሮ ለመቅሰም ጥረት አድርገዋል:: በዚያም የቀሰሙት ልምድና ተሞክሮ ስለሚያመርቱት ምርት ብዙ እንዲያወቁና ድርጅታቸው በአግባብ እንዲመሩ እንደረዳቸውም ሰሚራ ትናገራለች::
ሰሚራ እንደምትለው « ሥራውን ከመጀመራችን በፊት የምንሠራው ሥራ በእውቀት ለመሥራት እንድንችል አራታችንም የዲዛይኒንግ ትምህርቱን ተምረናል:: ቀጥሎ የሥራ ክፍፍል አድርገን ሁለቱ የገበያ ትስስሩን በበላይነት ሲሠሩ ሁለታችን ደግሞ ምርቶቹን ማስመረት ላይ ትኩረት አድርገን እየሠራን ነበር:: መጀመሪያ ላይ የማኔጀመንቱንም ሆነ ሱፐርቫይዘርነቱን ሥራ ራሳችን ነበር የምንሠራው:: አቅማችን ከፍ እያለ ሲመጣ የማናጀሮችን እና ሱፐርቫይዘሮችን ለመቅጠር በቃን» ትላለች::
‹‹ሥራው ስንጀምሩ ሴቶች እንደመሆናቸው መጀመሪያ ላይ የጀመርነውን ሥራ ከግብ አድርሰን ሠርተን መወጣት እንችል ይሆን ወይም ሳንችል ቀርተን ወደኋላ እንመለስ ይሆን ብለን መስጋታችን አልቀረም›› የምትለው ሰሚራ፤ በተለይ ከመንግሥት የመሥሪያ ቦታ ስንቀበል ተጨማሪ ኃላፊነት ወሰድን፤ እኛም አድገን ለሥራ አጥ ዜጎች የሥራ እድል ምንፈጥርበት በመሆኑ ተጨማሪ ኃላፊነት እንድንወስድ አድርጎን ስለነበር የነበረብን ኃላፊነት ድርብ እንደነበር ይሰማናል ነበር ያለችው::
‹‹ብዙ ሰዎች አትችሉትም፤ ጀምራችሁ ከምታቋርጡ ቢያንስ በትንሹ ጀምራችሁ ሞክሩ ሲሉን ነበር›› የምትለው ሰሚራ፤ ምንም እንኳን ሰዎች ቢያስፈራሩንም እኛ ግን እርስ በርሳችን እየተበረታታንና እየተደጋገፍን ሥራውን በሰፊው ለመጀመር በማሰብ በቁርጠኝነት በመሥራታችን ዛሬ ለደረስንበት ደረጃ ደርሰናል ትላለች::
ከመነሻው የወንዶች ሕጻናት ልብስ ለመሥራት የመረጡበት ምክንያት አንድ ነገር ላይ ትኩረት አድርጎ ጥራት ያለው ሥራ በመሥራት የበለጠ ውጤታማ ለመሆን በማሰብ መሆኑን ትናገራለች::
በአሁኑ ወቅት ድርጅቱ የወንዶች ሕጻናት ልብስ በማምረት ምርቶች ለሀገር ውስጥ ገበያ በስፋት እያቀረበ መሆኑን ትገልጻለች:: ጥራት ላይ ትኩረት አድርገው በመሥራታቸው ምርቶቻቸው የገበያ ተቀባይነት ማግኘቱን ገልጻ፤ ተደራሽነት በማስፋት ከአዲስ አበባ ከተማ ውጪ ባሉ በተለያዩ ክልል ከተሞች የገበያ ትስስር በመፍጠር እያስረከቡ መሆኑን በኩራት ትናገራለች::
« የምናመርታቸውን ምርቶች የሚረከቡን ደንበኞች ምርቶቹ የተሻለ ጥራት ስላላቸው በብዛት እንድናመርት ይጠይቁናል፤ እኛም ስንጀምር ጀምሮ ጥራት ላይ የበለጠ ትኩረት ሰጥተን እየሠራን ነው:: በተለይ የኢትዮጵያን ምርቶች ጥራት ደረጃ በማሻሻል የተሻለ ማምረት እንደምንችል በምርቶቻችን እያስመሰከር ነው›› ብላለች::
ድርጅቱ ልብሶቹን ለማምረት በግብዓትነት የሚውሉ ማቴሪያሎችን ከአስመጪዎች በመግዛት ይሰራል:: በተጨማሪም በሀገር ውስጥ ባሉ ግብዓቶችም በመጠቀም የሚሠሩ ጅንስና የመሳሳሉ ጥራት ያላቸው ልብሶች ያመርታል:: በአሁኑ ወቅት በወር ከ15ሺ ፍሬ በላይ ልብሶችን ያመርታል::
ልብሶቹ እንደ ጅንስ፣ ፈር፣ የተለያዩ የልጆች ልብሶች የሚያጋጊጡ ላይቶች እና የተለያዩ ግብዓቶች በመጠቀም ይሰራሉ:: አንዳንድ ጊዜ የምርቶች ግብዓት እጥረት እንደሚያጋጥም ሰሚራ ጠቅሳ፤ ግብዓቶቹን እንደልብ በሚገኙበት ወቅት ገዝቶ ለማስቀመጥ ካላቸው አቅም አንጻር ያላቸው ገንዘብን እዚያ ላይ አውሎ ማስቀመጥ አስቸጋሪ እንደሆነባቸው ትናገራለች:: ስለዚህም የገበያው ዋጋ በየጊዜው በሚቀያየረው ቢሆንም ባለው ዋጋ እየገዙ እንደሚሠሩ ታመላክታለች::
የግብዓት እጥረት ለመፍታት አቅማቸው በፈቀደ መሠረት ክፍተቶችን እየሟሉ በመሥራት ላይ መሆናቸውን ትናገራለች። ሥራዎቻቸው ክፍተት እንዳይኖር አድርገው በመሥራታቸው ብዙ ዜጎች የሥራ እድል ለመፍጠር መቻላቸውን ትጠቁማለች::
ድርጅቱ የተለያዩ ምርቶችን በማምረት ከውጭ በከፍተኛ ዶላር የሚገባ ምርት በሀገር ውስጥ እየተካ ይገኛል:: ጥራት ያለው የተሻለ ምርት እያመረተ በመሆኑ ጉዳዩ ከሚመለከታቸው ከተለያዩ ተቋማት የምስክር ወረቀት ተሰጥቷቸዋል::
ሰሚራ እንዳብራራችው፤ የልብሶቹ ዋጋም የሕብረተሰቡን የመግዛት አቅም ያማከለ ነው:: በዋጋ ከውጭ ከሚመጣው አንጻር ሲታይ በግማሽ የሚቀንስና በጥራት ደግሞ የተሻለ ነው:: ከውጭ የሚመጡት ልብሶች ገበያ ላይ ከሦስት ሺ ብር በላይ ይሸጣሉ:: ነገር ግን በሀገር ውስጥ የሚመረቱት ልብሶች ዋጋቸው ግን እንደየልብስ አይነት የሚለያዩ ቢሆንም ሙሉ ልብሶች ከስምንት መቶ ብር እስከ ሁለት ሺህ ብር ዋጋ ወጥቶላቸዋል:: ቲሸርት ብቻውን ከሆነ ግን ከሦስት መቶ እስከ አራት መቶ ብር ለገበያ ይቀርባል::
ልብሶቹ ሕብረተሰቡ በብዛት የሚፈልጋቸው ልጆቻቸው ደግሞ የሚወዷቸው እንዲሆኑ ተደርገው በመሥራታቸው ብዙ ወላጆች ለልጆቻቸው ገዝተው ያለብሳሉ:: ከዚያም ባሻገር ጥራቱን የጠበቀ ልብስ በአቅማቸው ገዝተው ልጆቻቸውን ማልበስ በመቻላቸው ብዙዎች ያመሰግኑናል:: ልብሶቻችን በጥራት የተሠሩ በመሆናቸው ብዙዎች የሚመሰክሩት ነው፤ ይሄ የምናገኘው ግብረ መልስ የበለጠ እንድንሠራና እንድንጠነክር እያደረገ ነው:: ምርቶቹ በገበያ ላይ ያላቸው ተፈላጊነት እንዲጨምርና በብዛት እንድናመርትም አድርጎናል ትላለች::
ሥራውን ስንጀምርም የኢትዮጵያ ምርቶች ጥራት የላቸውም እየተባለ ሲነገርና ምርቶቹን ሲያጣጣሉ እየሰማንና እያወቅን ነው የገባንበት የምትለው ሰሚራ፤ ይህንን አመለካከት በማስቀረት የምርት ጥራት ላይ ሠርተን ከሌሎች የሚበልጥና ተመራጭ የሆነ ልብስ በመሥራት ኢትዮጵያ የተሻለ ምርት እንድታመርት አድርገናል፤ ይህንንም በሥራችን ማስመስከር ችለናል:: የተሻለ ጥራት ያለው ልብስ እያመረትን የሕብረተሰቡን ፍላጎት እያሟላን ነው ስትል ታስረዳለች::
ወደ ሥራ ሲገባ ሁሉ ነገር አልጋ በአልጋ እንዳልነበርና ከመደራጀት አንስቶ የማምረቻ ቦታ እስከ ማግኘት የነበረው ሂደት ብዙ ተስፋ የሚያስቆርጡ ነገሮች አጋጥሟቸው እንደነበር ታነሳለች። ሆኖም ግን ሴቶች እንደሚችሉ ጠንክረው ሠርተው በአጭር ጊዜ ውጤት በማሳየታቸው ለብዙ ሴቶች አርአያ መሆን መቻል ብቻ ሳይሆን ብዙ ቦታዎች ላይ እየተጋበዙ ተሞክሯቸው እያካፈሉ መሆኑን የምትገልጸው በሙሉ ልብ ነው ::
‹‹ሴቶች ስለሆንን ሠርተን አሳይተን አሳምነናል:: በሁለት ዓመት ከስድስት ወር አጭር ጊዜ ቢሆንም እንደዚህ አይነት ለውጥ ያመጣሉ ተብሎ አልተጠበቀም:: እኛ ግን በሚደንቅ ሁኔታ ከሚጠበቀው በላይ ለውጥ አምጥተናል፤ ሴቶች መሥራት እንደምንችል አስመስክረናል፤ ሴቶችንም አስመስግነናል›› ብላለች::
ሴቶች ከወንዶች እኩል የሚያጋጥሟቸው ተግዳሮቶች በሙሉ በመወጣት የሚፈልጉበት ቦታ መድረስ እንደሚችሉ መጀመሪያ ራሳቸውን ሊያሳምኑ ይገባል የምትለው ሰሚራ፤ ሴቶች በተሰማሩበት የሥራ ዘርፍ ሁሉ ራሳቸውንም አሳምነው ሠርተው ማሳየት መቻል አለባቸው:: በማንኛውም ሥራ ዘርፎች ተግዳሮቶች ስለማይጠፉ እንዴት መወጣት እንዳለባቸው በማሰብ ሳይፈሩ በሚፈልጉት ሥራ ተሰማርተው አሸንፈው ለመውጣት ጥረት ሊያደርጉ ይገባል ባይ ናት::
በሥራ ውስጥም ብዙ ፈተናዎች እንደሚያጋጥሙ አውቀው በጥበብ ለማለፍ መዘጋጀትን ይጠይቃል:: ‹‹እኛ አሁን ላለንበት ደረጃ የደረስነው በብዙ ፈተናዎች ውስጥ አልፈን ነው:: በክረምት ወቅት ምርቶችን መሸጥ ሳንችል ገንዘባችን ሁሉ ማንቀሳቀስ ያልቻልንበት ጊዜ አጋጥሞን ነበር:: ይሁን እንጂ አንዳችን ሌላችንን እያበረታታን እያጠነከርን እርስ በርሳችን እየተደጋገፍን ወደፊታችንን እያየን ቀጥለናል:: በተጨማሪም ባለቤቶቻችንም የሚሰጡን ድጋፍ ብርታት ሆኖ ወደ ኋላ እንዳንመለስ ያሰብነው እንድናሳካ አስችሎናል›› በማለት ያሳለፉትን ፈተና እና ያጋጠማቸውን ተግዳሮት ያለፉበትን መንገድ በተመክሮ ትናገራለች።
በተለይ ሴቶች ምንም አይነት ጥረት ሳያደርጉ እቤት ቁጭ ብለው ሥራ መፍጠርና መሥራት እንደማይችሉ አድርገው ማሰብ የለባቸውም፤ ከሌሎች ተመክሮ ወስደው ያሰቡት ሥራ ለመጀመር ጥረት ሊያደርጉ ይገባል:: ጥረት በማድረግ የቤቱን ሆነ የውጭ ሥራ ተወጥተውና ችለው ማሳየት ይችላሉ:: ይህ ደግሞ ለሴቶች ከላይ የተሰጠ ልዩ ስጦት ነውና ሳይፈሩ ችለው ሠርተው ካሳዩ ምንም አይነት የማይለወጡበት ምክንያት የለም ስትል ትመክራለች::
ሰሚራ በአሁኑ ወቅት እንደ ድርጅት በተጠየቅንበት ቦታ ሁሉ ፈቃደኛ በመሆኑ አቅም ለሌላቸው ደካሞችን የማዕድ ማጋራት፣ በመሳሳሉ ፕሮግራሞች አቅማቸው በፈቃደው ልክ በገንዘብና በቁሳቁስ ድጋፍ እያደረጉ መሆኑን ትናገራለች:: በቀጣይ የሚጠበቅባቸው ለማድረግ ዝግጁ መሆናቸውንም ትገልጻለች::
በቀጣይ ኢትዮጵያ ሰፊ በመሆኗ ብዙ በመሥራትና ጥራት ያላቸው ልብሶች በማምረት ሀገር ውስጥ ያለውን ፍላጎት ለማሟላት በደንብ በመሥራት ተደራሽነት ለማስፋት አቅደው እየሠሩ መሆኑን የምትገልጸው ሰሚራ፤ ለልብስ መሥሪያ ግብዓት የሚውሉ ጥሬ እቃዎች ከውጭ በማምጣት ሀገር ውስጥ ለማምረት በሂደት ላይ መሆናቸው ጭምር ትገልጻለች::
በተለይ ለሕጻናት ልብስ የሚሆኑ ማሳመሪያ ግብዓቶች በራስ አቅም በማምጣት ለግብዓት መግዣ የሚያወጡትን ወጪ መቀነስና ውጤታማ ሥራ የመሥራት ፍላጎት እንዳላቸው ትናገራለች:: ከዚህ ባሻገርም ምርቶች ወደ ውጭ ገበያ ለመላክ አቅደው እየተሠሩ መሆኑን ጠቁማለች::
በሚቀጥሉት ጊዜያት የማምረቻ ቦታ ማስፋፋያ ጥያቄ ለክፍለከተማው አቅርበው ምላሽ እየተጠባበቁ መሆኑን ገልጻ፤ በጎ ምላሽ የሚያገኝ ከሆኑ ሥራውን በፍጥነት በማስፋት ከ500 በላይ ለሚሆኑ ዜጎች የሥራ እድል በመፍጠር ትልቅ ድርጅት የመሆን ራዕይ መሰነቃቸው ትገልጻለች::
መንግሥትም ሆነ የሚመለከታቸው አካላት ድጋፍ ቢያደርጉላቸው ደግሞ ከዚህ የበለጠ ሥራ መሥራት እንደሚችሉ ታስረዳለች:: ከውጭ በግላቸው ለማስመጣት ያቀዱት ጥሬ ግብዓቶች ሲያስገቡ የተሻለ ትብብር እንዲደረግላቸው ትጠይቃለች:: የማስፋፊያ ቦታው ምላሽ በፍጥነት ቢሰጣቸው ለበርካታ ሥራ አጥ ዜጎች የሥራ እድል በመፍጠር ያለሙት በማሳከት ከዚህ በላይ እድገት በማስመዝገብ እንደሚሠሩ ተናግራለች::
እነ ሰሚራ ትልቅ ዓላማ አድርገው እየሠሩ ያለው ኢንዱስትሪ መንደር ለመግባት ነው:: ምርቶቻቸው የበለጠ ጥራት እንዲኖራቸው በመሥራት ጥራት ያላቸው ምርቶች በማምረት ኤክስፖርት ለማድረግ ይሠራሉ:: ይህም ሠርተው ራሳቸውንም ጠቅመው፤ ሀገራቸውም ለመጥቀም ያስቀመጡት ትልቁ ሕልማቸው ነው::
ወርቅነሽ ደምሰው
አዲስ ዘመን ማክሰኞ ግንቦት 5 ቀን 2017 ዓ.ም