የነገዋ የሴቶች ንጋት

ሴቶች በሕይወታቸው ልዩ ልዩ ችግሮች ይገጥማቸዋል:: ችግሮቹ ደግሞ ማኅበራዊ አልያም ኢኮኖሚያዊ ሊሆኑ ይችላሉ:: በዚህም ኑሯቸውን ለማሸነፍ ሲሉ ወደተለያዩ ዓረብ ሀገራት ይሰደዳሉ፤ ስንት ደክመው የሠሩበት ሳይከፈላቸው ባዶ እጃቸውን የሚመለሱ ጥቂት ሴቶች አይደሉም:: በቤተሰብና በተለያዩ ኢኮኖሚያዊ ችግሮች ምክንያት ሳይፈልጉ ኑሯቸውን በሴተኛ አዳሪነት የሚገፉ፤ እጅ አጥሯቸው በየጎዳናው ወድቀው ምፅዋት የሚጠይቁ ቀላል ቁጥር የላቸውም።

በዚህ ሕይወት ውስጥ ያሉ ሴቶችን ደግሞ የማንቃትና የማብቃት ኃላፊነት የሁሉም ሰው ድርሻ በመሆኑ «የነገዋ ተሃድሶ የሴቶች ክህሎት ማበልጸገያ ማዕከል» ከተቋቋመ በኋላ ብዙዎች እፎይታን ያገኙ ይመስላል። ከእነዚህ ሴቶች መካከል ደግሞ ፌቨን ታደሰ አንዷ ሆና ተገኝታለች።

ፌቨን የአዳማ ከተማ ልጅ ናት። ቤተሰቦቿ በዝቅተኛ ገቢ የሚተዳደሩ በመሆናቸው እንደልቧ ልጅነቷን መኖር አልቻለችም ነበር። ሀገር አቋርጣ እስከ መሰደድ የሚደርስ ችግር አጋጥሟታል። ቤሩት እንድትሄድ የገፋፋቻት የአክስቷ ልጅ ስትሆን ለስምንት ዓመታት በውጭው ሀገር ተንገላታለች። አስባው የማታውቃቸውን ሥራዎችም እስከ መሠራት ደርሳለች።

ዓረብ ሀገር ጭምቷንና ለቤተሰቧ ሟች የሆነችውን ፌቨንን ሱሰኛ ያደረገና ሰርታ ገንዘብ የማይበረክትላት እንዲሁም ምንም ጥሪት ሳይኖራት ወደ ሀገሯ እንድትመለስ ያደረጋት ሀገር መሆኑን ትናገራለች። አጫሽና ቃሚነቷ ደግሞ ለቲቪ በሽታ ዳርጓታል። ከቤተሰቡ ጭምር እንድትገለልና ጎዳና ሕይወቴ እንድትል ያስገደዳትም ነበር።

ፌቨን በጎዳና ኑሮ ከማለፏ በፊት በርካታ ውጣ ውረዶችን ተሻግራለች:: እናቷን በሞት ያጣችው ገና የ10 ዓመት ልጅ ሳለች ነበርና ቀጣይ ሕይወቷን ለመምራት አዲስ አበባ በአክስቷ ቤት ለመማር ሞክራለች:: ከቤሩት መልስም ራሷን ለመቻል ያልሞከረችው ነገር አልነበረም:: ነገር ግን ምንም ዓይነት ገንዘብ አልነበራትምና ማንም ሊቀበላት አልወደደም። ህመሟ ደግሞ ከብዙ ነገር ያራቃት ነበር።

አንዱ አለችኝ፤ ትደግፈኛለች ያለቻትን አክስቷን ያሳጣት ምክንያትም ህመሟ የሳንባ በሽታ በመሆኑ ከፍተኛ ጥንቃቄ ካልተደረገበት በስተቀር ወደ ቤተሰቡ ይተላለፋል በሚል ነበር። ስለዚህም ፌቨንን ማስወጣት ሌሎቹን መታደግ ነው ብላ ስላሰበች የተወሰነ ጊዜ ከተንከባከበቻት በኋላ ከቤት እንድትወጣ አድርጋታለች። ይህ ደግሞ ፌቨንን የት ልግባ ያሰኛት መጥፎ አጋጣሚ ነበር።

ፌቨን የዚህን ጊዜ አንድ ውሳኔ ላይ ደረሰች። ማንም በቀላሉ ወደማያገኛት ቦታ መጓዝን መረጠች። ተስፋዋን ለማለምለምም የሕክምና ክትትሏ ሳይቋረጥ የምትኖርበትን ቦታ አሰበች። ፍላጎቷን እውን የምታደርግበት ቦታ ድሬዳዋ እንደሆነ በማመንም ማቄን ጨርቄን ሳትል ሪፈር አጽፋ ወደ ድሬዳዋ ሆስፒታል አቀናች። የሳንባ ህመምተኞች ልዩ እንክብካቤና ጥበቃ ይደረግላቸው ነበርና ችግሯን ሁሉ ረሳች። ከስድስት ወር ሕክምና በኋላም ወደ ጤናዋ ተመለሰች።

የሳንባ ሕክምና በቀላሉ ዳግም ለመቀስቀስ ሰፊ እድል አለው። ስለዚህም ቀጣይነት ያለው ክትትልና ጤናማ ምግቦችን መመገብን ይጠይቃል። በዚያ ላይ እንደ ፌቨን ያሉ ሱሰኞችም ከዚህ ልምዳቸው መውጣት ግድ ይላቸዋል። ይሁንና ፌቨን ግን ይህንን ማድረግ የሚያስችላት አቅም ላይ አይደለችም። የሲጋራ ሱሷ ከሁሉም ሰው ያርቃታል። በዚያ ላይ የተመጣጠነ ምግብ ላግኝ ብትል በምን ገንዘብ ልታደርገው ትችላለች። ስለዚህም በሕይወቷ ፈርዳ ቤሩት ሀገር ትሰራ የነበረውን የሀሺሽ ቤት ሥራ ቀጠለች።

ሀሺሽ ቤት መሥራት ጠቀም ያለ ገንዘበ ቢያመጣም የጤናዋ ጉዳይ ግን ‹‹አፈንጅልኝ›› በሚሉት ተጠቃሚዎች አማካኝነት ጤናዋ ተቃወሰ። ሰውነቷም ከሳ እነሱም ሊያሰሯት አልፈቀዱም። በዚህም አዳማንም ሆነ ድሬዳዋን ጎዳና ላይ ልትኖርባቸው እንደማትችል ተሰማትና ከዓመት ስድስት ወር ቆይታ በኋላ በአዲስ አበባ ከተማ ከተመች።

ፌቨን ጎዳና ሕይወቷ እንዲሆን በፍጹም መፍቀድ አልፈለገችም ነበር። በዚህም ሥራ ለማግኘት ለፍታለች፤ እቃ አጣቢ አድርገዋት የተወሰነ ገንዘብ እንዲሰጧት እንኳን ለምናለች። ግን ማንም ፈቃዱን ሊሰጣት አልወደደም። ይልቁንም ሁኔታዋን እያዩ የሚያባርሯት ጥቂቶች አልነበሩም። ስለዚህም ከቤተሰብ ቤተሰብ የላት፤ ለሥራም ቢሆን የሚመርጣት ስላልነበረ ሁሉም ነገር ፊቱን ሲያዞርባት ምርጫዋ ጎዳና አደረገች።

ጎዳና ነው ቤቴ

ሕልሟን መኖር ያልቻለችው ፌቨን ጎዳና ላይ የወጣችበት አካባቢ አደይ አበባ ነው። በዚህ ስፍራ እንደ እርሷ ነገሮች የጨለሙባቸው ብዙ ናቸው። ስለዚህ ለእንግዳነቷ ፊት አልነሷትም:: ካላቸው አካፍለው ከለበሱት ገፈው በሰላም እንድታርፍ ያደርጓታል:: እርሷም ብትሆን ከሱሰኞቹ ጋር ሱሷን አብራ እየተጋራች፤ የልባቸውን ከሚያጫውቷት ጋርም እንዲሁ ችግሯን እየተነፈሰች መጥፎዎቹን ነገሮች ረስታቸዋለች።

አሁን ፌቨን ሃሳቧን በትንሹም ቢሆን አቅልላለች። የሚረዷት፤ ቤተሰቤ ነሽ የሚሏት ጓደኞችን አግኝታለች። ሥራና ዓላማ ይሉት ግቧን እርግፍ አድርጋ ትተዋለች:: ምክንያቱም ዛሬም ስላልተሻላት ማንም አይፈልጋትም። በርግጥ አንፈልግሽም መባሏ እንጂ መሥራትና መለወጥን ዘወትር ትሻለች፤ እንደዚያም ሆና እንኳን ለመሥራት የማትሞክረው ነገር አልነበረም። ግን ሰዎች ሁሌም ያገሏታል፤ ያሸማቅቋታል። በዚህም ምርጫዋ ልመናና ሱሷን ማስቀጠል አድርጋ ዓመታትን አሳለፈች::

ጎዳና ላይ ሕይወት በእጅጉ መራር ነው:: በልቶ ማደር፣ ለብሶ ማማር ብርቅ ነው:: የእናት ቤት እንጀራ፣ የጎረቤትና የወዳጅ ዘመድ ፍቅር ሩቅ ነው:: ፌቨን እና ጓደኞቿም በዚህ እውነታ ውስጥ እያሳለፉ ነው ዓመታትን የገፉት:: በተለይ የገላ ውሃ ለማግኘት ያለው ፍልሚያ በምንም መልኩ የሚገለጽ አልነበረም:: በትንሹ ቢነሳ ሁለት ወር ክረምት ምንም ዓይነት ውሃ ገላዋን ሳይነካው ያሳለፈችበትን ጊዜ አትረሳውም። ለገላዋ ውሃ ያገኘችው አዲስ ዓመት ሲመጣ ነው። ከዚያ በኋላ ደግሞ የነገዋ ስትገባ ነው ውሃ እንደ ልብ አግኝታ መታጠብ የጀመረችው። ይህ ደግሞ ለሴት ልጅ ምን ያህል ፈታኝ እንደሚሆን መናገር ለቀባሪው አረዱት ይሆናል።

ነገዋ የነገዎቹ ብርሃን

ፌቨን ወደ የነገዋ ስትገባ የነገ ተስፋዋን በምንም መልኩ አስባበት አይደለም። ዛሬዋን ስለአነጉላት በማመስገን እንጂ። ለእርሷ ነገ ምንም ሊሆን ይችላል። ዛሬ ግን ረጅም ጊዜ የናፈቀችውን ንጹህ አልጋ፤ ንጹህ ምግብና ንጹህ ውሃ አግኝታለች። በዚህም እንደልቧ መታጠብ፤ ሳትሳቀቅ በቂ እንቅልፍ ማግኘትና በሽታዋን እስከ መጨረሻው በተመጣጠነው ምግብ ማስወገድ ችላለች። ከዚያም ባሻገር ስለነገዋ እንድታስብ ሆናለች። ሱሰኝነቷን ትታ የነገዋ ጥሩ ዲዛይነር ለመሆንም እንድትተጋ እድል አግኝታለች። በዚህ ደግሞ ‹‹ዛሬ ብሞት እንኳን አይከፋኝም›› ትላለች።

የነገዋን ተሃድሶ ክህሎት ማበልፀጊያ ማዕከል ግን ለእነ ፌቨን ከዚህ ያለፈ ልዩ ስጦታዎችን ያበረከተ ነው:: ህልማቸውን እውን እንዲያደርጉ ታቅዶበት የተሠራ ነው። ከጎዳና ሕይወት አርቆ የነገ ሕልማቸውን እንዲኖሩት የማድረግን እቅድ ያነገበም ነው። እነርሱ የትናንቱ አስከፊ ኑሮ ‹‹ነበር›› እንዲሉት ይፈልጋል፤ ለዚያም ይተጋል:: ነገ ከማዕከሉ ወጥተው አዲስ ሕይወት አዲስ ሥራ እንደሚጀምሩም ይሻልም። ከዚያም አልፎ ተለውጠው ከቤተሰባቸው ጋር ከልጆቻቸው ጋር እንዲገናኙ እድል ይፈጥሮላቸዋል። ቤተሰብ ለሌላቸውም ቤተሰባዊ ሕይወታቸውን ያጠናክርላቸዋል።

የነገዋ ሴቶች ተሃድሶና ክህሎት ማበልፀጊያ ማዕከል የጤናው ዘርፍ ምክትል ዳይሬከተር ልኬ ኃይለማርያም እንደሚናገሩት፣ ወደ ማዕከሉ የሚመጡ ሴቶች አራት መሠረታዊ ነገሮችን ያለፉ ናቸው:: የመጀመሪያዎቹ የጎዳና ላይ ሕይወት ይመሩ የነበሩ ሲሆኑ፤ ሁለተኛዎቹ በኢኮኖሚ ራሳቸውን ያልቻሉ ሴቶችና ወረዳው መታገዝ አለባቸው ብሎ የለያቸው ናቸው:: ሦስተኛዎቹ ሴተኛ አዳሪ የነበሩና በዚህ ሥራ ራሳቸውን ሲያስተዳድሩ የቆዩ ሲሆኑ፤ አራተኛዎቹ ደግሞ ውጭ ሀገር ሄደው ሳይሳካላቸው የተመለሱ ናቸው::

በማዕከሉ የሚገቡ ሴቶች ደግሞ እድሜያቸው ከ15 እስከ 40 ባለው የእድሜ ክልል ውስጥ የሚገኙ ሲሆኑ፤ ወደ ማዕከሉ ሲገቡ በቅድሚያ በማዕከሉ ለመቆየት ፍቃደኝነታቸው ይጠየቃል:: ፍቃደኝነታቸው ከተረጋገጠ በኋላ የጤና ምርመራ ይደረግላቸዋል:: ለዚህም በማዕከሉ ደረጃውን የጠበቀ ክሊኒክ ተዘጋጅቷል:: ፍቃደኝነታቸው ተረጋግጦ የሕክምና ምርመራ ካገኙ በኋላ ደግሞ ሴቶቹ በርካታ አገልግሎቶችን በማዕከሉ ያገኛሉ:: ከእነዚህ አገልግሎቶች ውስጥ አንደኛው ተጨማሪ የሕክምና አገልግሎት የሚያገኙበት ነው:: አገልግሎቱም የሚሰጠው ከጥሩነሽ ቤጂንግ ሆስፒታል ጋር በመተባበር ነው::

ሌላኛው ሴቶቹ በማዕከሉ የምግብ፤ የተሟላ የማደሪያ አገልግሎት እንዲያገኙ የሚደረግበት ነው:: እነዚህ መሠረታዊ ፍላጎቶች ከተሟሉላቸው በኋላም ወደ ሥልጠና ከመሄዳቸው በፊት ለሥልጠናው ራሳቸውን እንዲያዘጋጁና በፊት ከነበሩበት ሕይወት ወጥተው ወደ ራሳቸው ቀልብ እንዲመለሱ ተከታታይነት ያላቸው የሥነ ልቦና፣ ማይንድ ሴት፣ የሕይወት ክህሎት ሥልጠዎች ይሰጣቸዋል:: እነዚህን የተሃድሶ ሥልጠናዎች ካጠናቀቁ በኋላ ደግሞ ወደ ክህሎት ሥልጠና እንዲገቡ ይደረጋል::

በማዕከሉ 17 የተለዩ የክህሎት ሥልጠና ዓይነቶች ስላሉም ሴቶቹ ወደ እነዚህ የክህሎት ሥልጠናዎች የሚገቡበት ሁኔታ ይመቻቻል። ሙያ መርጠው ሥልጠናውን ከሦስት እስከ ስድስት ወር ባለው ጊዜ እንዲያጠናቅቁም ይደረጋል። ከዚያም ቅጥር የማፈላለጉ ሁኔታ አለያም በራሳቸው እንዲሠሩ የማድረግ እድል ይፈጠራል ብለዋል።

ዳይሬክተሯ እንደሚሉት፣ በማዕከሉ ውስጥ የገቡ ሴቶች የተለያየ ደረጃ ላይ የሚገኙ ናቸው። እስከ ዩኒቨርሲቲ ድረስ በትምህርቱ የዘለቁ እንዳሉ ሁሉ ምንም ያልተማሩም ይገኛሉ። ስለሆነም ሥልጠናው ሲሰጥ ይህንን ማዕከል ባደረገ መልኩ ነው። የጤና ሁኔታቸው፤ በቀላሉ ሥራ የማግኘት አማራጫቸውም ከግምት ውስጥ ይገባል። በዚህ ሁኔታም በመጀመሪያው ዙር 302 ሠልጣኞችን ማስመረቅ ተችሏል። ሲኦሲ ተፈትነውም 94 በመቶው ያለፉበትና ውጤታቸውም በጣም ከፍተኛ የሆነበት ሁኔታ ታይቷል።

ማዕከሉ እስከ 2 ሺህ የሚደርሱ ሠልጣኞችን ተቀብሎ የሚያስተናግድ ቢሆንም ወደ ማዕከሉ የሚገቡ ሴቶች ለመለወጥና የራሳቸው ጌታ ለማድረግ ብዙ መልፋትን የሚፈልጉ በመሆናቸው መቀበል እየተቻለ ያለው ከ500 አይበልጥም። አሁን እየሰለጠኑ ያሉትን እንኳን ብናነሳ 400 ናቸው። ስለዚህም በቀጣይ የማስፋትና ቀጣሪን የማብዛት እንዲሁም ማቋቋሚያ የሚያግዛቸውን ሰው የማግኘት እድሎች ከተመቻቹ ብዛቱን ከፍ የማድረግ እቅድ እንዳለም አጫውተውናል።

እስከ አሁን ባለው ሁኔታ ወደ ማዕከሉ የገቡ ሴቶች በብዙ ነገር መለወጣቸውን አይተናል። አንዱ የሰውነት ሁኔታቸው በእጅጉ መቀየሩ ነው:: ጤናማ መሆን ችለዋል። ከአመለካከት፣ ከአስተሳሰብና ማህበራዊ ግንኙነት አንጻርም ከፍተኛ ለውጥን አምጥተዋል። ሴቶች መሠረታዊ ነገሮች ከተሟሉላቸው፣ ማግኘት የሚገባቸውን ትምህርት ካገኙ የትኛውንም ዓይነት ሥራ የመሥራት አቅምና ብቃት እንዳላቸውም እያስመሰከሩ ይገኛሉ። ሆኖም ይህ ማዕከል ብቻ አጠቃላይ በሀገሪቱ ያሉትን ሴቶች ሕይወት ሊቀይር አይችልም። ስለዚህም ክልሎችም ባላቸው አቅም ልክ ሊያስቡበት ይገባል ባይም ናቸው።

እንደ አዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ማዕከሉ በተለያየ መልኩ እየተደገፈ ይገኛል። ተመራቂዎችን ከመቅጠር አልፎ ባለሀብቶችን በመጋበዝ የተቻላቸውን እንዲያደርጉ እየለፋ ነው። ሆኖም እንዲህ ዓይነት ማዕከል ገንብቶ ሴቶችን በተሃድሶና ክህሎት ማሠልጠንና ወደ ሥራ ማሰማራት በሀገር አቀፍ ደረጃ የመጀመሪያ ልምድ ነውና ክልሎችም መጥተው ልምድ እየወሰዱ ተሞክሮውን ማስፋት ይገባቸዋል::

ክልሎች ይህንን አደረጉ ማለት ደግሞ በአካባቢ ያቸው ጎዳና የወጡም ሆኑ በችግር ውስጥ ያሉ ዜጎችን ከአካባቢያቸው ሳይርቁ በአላቸው የተፈጥሮ ጸጋ ተጠቅመው እንዲለወጡ ማድረግ ይቻላል። የሥራ እድሉንም ቢሆን በቀላሉ ለመፍጠር አያዳግትም። እናም ለሴቶች ንጋት ከነገዋ ባሻገር ሌሎች የነገ ተስፋ ሰጪ ማዕከላትን ማቋቋም ያስፈልጋል ሲሉም ምክራቸውን ለግሰዋል።

ጽጌረዳ ጫንያለው

አዲስ ዘመን ማክሰኞ ሚያዝያ 28 ቀን 2017 ዓ.ም

Recommended For You