«በብርሃን ለመመላለስ ሥራችንን ከጊዜያችን ጋር እናጣጥም›› ሲስተር ዘውዴ አበራ

ግቢው ጠበብ ያለ ነው። ሆኖም የተለያዩ ሥራዎች እንዲከናወኑበት በሚያመች መልኩ ተከፋፍሏል። ባህላዊ የንብ ቀፎዎች በየግድግዳውና ጣሪያው እንዲሁም አጥርና ቆጥ ላይ ተንጠልጥሎ ይታያል። መግቢያው አካባቢም እንዲሁ የተለየ ሥራ አለ። የእንስሳቱ ተዋጽኦ ምርቶች፣ ሻይና ቡና ለገበያ የሚቀርብበት ቦታ መሆኑን ከፊት ለፊቱ ያለው ማስታወቂያ ያሳብቃል። ምግብም በየአይነቱ መኖሩን ያመለክታል። ይህንን ስመለከት ስለሲስተር ዘውዴ አበራ ከሰማሁትም በላይ አስደናቂ ሆነብኝ። አንድ በሥራ ላይ ያለች የጤና ባለሙያ እንዴት ከሥራዋ በተጨማሪ ይህንን ሁሉ ሥራ ልታከናውን ትችላለች? የሚል ጥያቄ በውስጤም ተፈጠረ። ግን ማየት ማመን ነውና በአድናቆት ተቀበልኩት።

ሲስተር ዘውዴን ሳገኛት ተክለ ሰውነቷ ፣ ገጽታዋ ያላት አጠቃላይ ሁኔታ በተደላደለ ኑሮ ያለፈች ያስመስላታል ። ታሪኳ ግን ከዚህ እሳቤዬ የተለየ ነው ። በርካታ የሕይወት ውጣውረዶችን አሳልፋለች።

ተግባቢነትና ጨዋታ አዋቂነቷን ደግሞ ያለ መድሀኒት ህሙማንን ፈዋሽ ነርስ ብቻ ሳይሆን ጥሩ ነጋዴ የመሆን እድልንም አጎናጽፏታል። ያለሥራ የሚባክን ጊዜ የሌላት ታታሪ ናት። የሥራ አማራጮችን በፍጥነት መመልከቷ፤ ሁሌም ኑሮዋን ለማሸነፍ የምትተጋ ባተሌ አድርጓታል።

በአንድ ሥራ ላይ ብቻ የሙጥኝ ከማለት በትርፍ ሰዓትና ጊዜ ተጨማሪ ገቢ ማስገኛ ላይ መሰማራቷ ውጤታማ እንድትሆን አድርጓታል።ይህች ለብዙዎች አርአያ መሆን የምትችል ሴት በመሆኗ በጥንካሬዋ፣በስራፈጣሪነቷ… ሰዎች ይማሩበት ዘንድ የዛሬው ‹‹የሕይወት ገጽታ›› አምዳችን እንግዳ አድርገናታል።

የሁለት ቤት ልጅነት በወሎና ጎንደር መሐል ባለች ዳውንት በተሰኘች ስፍራ ተወልዳ አድጋለች። ቤተሰቦቿ አርሶአደሮች ናቸው። በግብርና ሥራ የተሻለ ገቢ ለማግኘት የሚታትሩና ልጆቻቸውን ለማሳደግ የሚጥሩ። በዚህ ውስጥ ደግሞ የዘውዴ ተሳትፎ እጅጉን የበረታ ነበር። ምክንያቱም ሴትነት በገጠሩ ማህበረሰብ ዘንድ ትልቅ የቤት ውስጥ ሥራ ኃላፊነትን መሸከም የሚጠይቅ ነው። እናም ዘውዴም በአልጠነከረ ጉልበቷ ከርቀት ውሃ መቅዳት እንጨት መልቀም…ሠርታለች። ቤት ውስጥም ቢሆን ከእናቷና እህቶቿ ባሻገር ምግብ ማብሰል የእርሷም ኃላፊነት ነው፡፡

አካባቢው ሞቃታማ ስፍራ በመሆኑ ደግሞ የተለመደው ሥራ ከግብርናው ባሻገር ከብት ማርባት በመሆኑ ከብቶችን የመጠበቅም ድርሻ ከተሰጣቸው መካከል ትገኝበታለች። በአጠቃላይ በሚሠራው ሥራ ሁሉ እርሷ ቅመም ናት። ይህ ግን በውዴታ እንጂ በግዴታ የምታደርገው አልነበረም፡፡መቀመጥ ስለማትወድ ተደራራቢ ኃላፊነቶችን በመውሰድ ትሠራለች እንጂ ይህንን ለምን አላደረግሽም የሚላት አልነበረም፡፡

በገጠሩ ማህበረሰብ ዘንድ ሴት ልጅ ሙያ ከሌላት ለጋብቻ የሚፈልጋት አይኖርም ተብሎ ስለሚታመን የቤት ውስጥ ሥራ መሥራት ሥራዋ ነው። ያም ቢሆን ግን በፍቅር እንጂ በግዴታ እንድታደርገው ማንም አይጫናትም። ስለዚህም ከቤተሰቦቿ ጋር ያሳለፈችውን የልጅነት ጊዜዋን ስታስብ በእጅጉ የተደሰተችበት ስለመሆኑ ታነሳለች።

ዘውዴ በባህሪዋ አልችልምን አታውቅም። «አትችይውም» የሚላትንም ሰው አትቀበልም። እንዲህ የሚላት ሰው ከገጠማት የማትችለው እንኳን ቢኖር ሞክራ ለማሸነፍ የምትጣጣር ናት፤በእችላለሁ መንፈስ ተገንብታለች።

ጠንካራና ብዙ ሥራዎችን ማከናወን መቻሏ እንዲሁም ታታሪ መሆኗ ዘውዴን ከአክስቷ ዓይን ውስጥ እንድትገባ አድርጓታል። ከልጆቿ እኩል እያሳደገቻት ልታስተምራት ቃል ገብታም 10 ዓመቷ ላይ አዲስ አበባ አመጣቻት ።

አክስቷ ጋር ከመጣች በኋላ ግን ያሰበችው ነገር አልሆነም። መሥራት ብትወድም ከአቅሟ በላይ የሚሆኑ ጫናዎች ተፈጥረዋል። እንክብካቤውም እንደ ልጅ ሳይሆን እንደ ሰራተኛ ሆኖባታል። እማራለሁ ብላ ብትመጣም የማጥኛ ጊዜ እንኳን አልነበራትም። ለዚህ ጫና መፈጠር ምክንያቱ ደግሞ የቤቱ ውስጥ ታናሽ መሆኗና የሁሉንም ፍላጎት ለማሟላት በከፍተኛ ሁኔታ ደፋ ቀና ማለቷ ነው፡፡

ቤት ውስጥ ስድስት ልጆች አሉ። እርሷና አክስቷ ሲደመሩ ስምንት ይሆናሉ። ለሁሉም የሚሆን ምግብ የምታዘጋጀው እርሷ ነች። ቤት የምታጸዳውና እቃና ልብስ የምታጥበውም በዚያች ባልጠነከሩ እጆቿ ነው። የከተማ ልጅ ናቸውና ሥራ አይችሉም የሚል እሳቤ ስላለ አብዛኞቹ በሥራ አያግዟትም። ረድተዋታል ከተባለ የምትፈልገውን የትምህርት ቁሳቁስ በመግዛትና ጠንካራ እንደሆነች በመንገር ብቻ ነው። በተለይ መምህር የነበረችው የአክስቷ ልጅ የእርሷን የትምህርት ፍላጎትና ለመለወጥ ያላትን ጉጉት በሚገባ ታውቀዋለችና ነገ የተሻለ እንደሚሆንላት ትነግራታለች። በዚህና ነገዋን ለማሳመር ዛሬ ላይ ጎንበስ ብላ መከራዎቿን ማሳለፍ እንዳለባት በማመን የዓመታት የሥራ ጫናዎች ታግሳ ኖራለች፡፡

ዋጋ የተከፈለበት ትምህርት

ዘውዴ ትምህርትን አሀዱ ያለችው አዲስ አበባ አክስቷ ቤት ከገባች በኋላ ነው። ነገር ግን እንደማንኛውም ልጅ የምታጠናበት ጊዜ ፤ የቤት ሥራዋን የምታከናውንበት ሰዓት ኖሯት የተከታተለችው አልነበረም፡፡ይሁን እንጂ የደረጃ ተማሪነቷን ማንም አልቀማትም ። ምክንያቱም እርሷ ከትምህርት ቤት አንድም ቀን ቀርታ አታውቅም። ማርፈድና ከክፍል ውጪ መሆንንም አትመርጥም። በዚህ ደግሞ መምህሮቿ የሚሰጧትን ትምህርት በሚገባ ትከታትላለች። ያልገባትን ጠይቃ ትረዳለች። የእረፍት ሰዓቷን ደግሞ የቤት ሥራ መስሪያና የተማረችውን ማጥኛ በማድረግ የትምህርት ቤት ቆይታዋን በአግባቡ ትጠቀምባታለች። ይህ ደግሞ በየጊዜው ተሸላሚ እንድትሆን አስችሏታል።

‹‹ትምህርትን በሚገባ ለመረዳት አላማ ያለው ሰው መሆን ያስፈልጋል። በአለው አጋጣሚ የሚሰጠውን የቤት ሥራ መሥራትና ማጥናትም የግድ ይላል፡፡›› የምትለው ዘውዴ እስከ ስምንተኛ ክፍል በአላት የአክስቷ ቤት ቆይታ ቢሆን ኖሮ አይደለም ጎበዝ ሰነፍ ሆናም በትምህርት ቤቱ መቆየት አትችልም ነበር። ከትምህርት ቤት እስከመባረር የሚያደርሳት ችግር ይገጥማታል። ሆኖም በራሷ ጥረት ይህንን ፈትታዋለች።

በአክስቷ ቤት ውስጥ የሚደርስባት የሥራ ጫና ትምህርቷ ላይ ጥላ እንዳያጠላበት ስጋት የገባት ባለታሪካችን፤ በዚህ አይነት ሁኔታ በዚያ መቆየት እንደሌለባት ለራሷ ነገረች። ፈተናው ሲበረታባት ውጤቷ እንደፈለገችው ላይሆን እንደሚችል በመገመትም ማቄን ጨርቄን ሳትል ዋና አላማዋ ተምሮ መለወጥ ነውና ጫናዋን ለመቀነስና በሚገባ ትምህርቷን ለመከታተል ስትል አዲስ አበባን ትታ ወደ ትውልድ ቀየዋ ተመለሰች። በዚያም ለትምህርት ይቀርበኛል በምትለው ስፍራ ቤት ተከራይታ ትምህርቷን ቀጠለች። 9ነኛና 10ኛ ክፍልን በዚያው ተማረች።

11ኛ እና 12ኛ ክፍልን ግን በዚያ መማርን አልፈለገችም። ምክንያቱም በቀጥታ ኮሌጅ ገብታ ሥራ በመያዝ ቤተሰቧን ማስደሰት ትሻለች። በተለይም አባቷን ደስተኛ ማድረግና የሚፈልገውን ትምህርት መማር ለእርሷ የውጤቷ መጀመሪያ እንደሚሆን ታምናለች። እናም ምንም እንኳን ውጤቷ ፕሪፓራቶሪ የሚያስገባት ቢሆንም አማራጯን እርሱን አላደረገችም። ኮሌጅ ገብታ ለመማርም የግድ አክስቷ ጋር መመለስ እንዳለባት ወስና ዳግመኛ ወደ አዲስ አበባ መጣች። በአዲስ አበባ ቅድስት ልደታ ጤና ሳይንስ ኮሌጅ በክፍያ ለመማርም ተመዘገበች።

የመጀመሪያው የአክስቷ ቤት ፈተና አሁንም አለቀቃትም። የነርስነት ሙያ ትምህርት ደግሞ እንደ ትናንቱ በትንሹ ክፍል ውስጥ አጥንቶ የሚበቃ አይደለም። ብዙ ማጥናትን፤ የተግባር ልምምድንና ጊዜን ይፈልጋል። ያንን ለማድረግ ደግሞ የአክስቷ ቤት አላስቻላትም። ስለዚህም ወደ አዲስ አበባ የመጣችበት አላማ በትምህርት ራሷን ለውጣ ቤተሰቦቿን ለማገዝ ነውና ቤቱን ትታ መውጣት ግዴታዋ ሆነ። የምታውቀው ሰው ስለሌለም በብዙ ተፈተነች። ያለምግብ ለአራት ቀን ያህል አደረች። መጠለያ አጥታም የቤተክርስቲያን ደጃፍን የሙጥኝ አለች፡፡ችግረኛ ተማሪዎችን እየከፈሉ የሚያስተምሩት ልጅም እስከመሆን ደርሳለች፡፡

የማታውቃቸውን ሥራዎች በመጀመርና የገቢ ምንጯን በማስፋት ግን ሌላ የትምህርት እድል ጭምር እንድታገኝ የሆነች ጠንካራ ሴት ነች። ንግድ ባንክ ውስጥ በጽዳት ሰራተኝነት ስትገባ ሁኔታውን ስትረዳው በዚህ ብቀርስ በሚል ከነርስነት ትምህርቷ ባሻገር የፋይናሽያል አካውንቲግ ትምህርትን በድግሪ መማር ችላለች። ይህና መሰል ጥረቷ ደግሞ ጥሎ አልጣላትም። ገና ሳትመረቅ ሲኦሲ ፈተናዋን አልፋ በቀጥታ ወደ ሥራ እንድትገባ የሆነችበትን እድል ሰጥቷታል።

በሰዎች ደስታ ለመደሰት

ሲስተር ዘውዴ የጤና ሙያን ስትመርጥ በሁለት ዋና ዋና ጉዳዮች ምክንያት ነው። የመጀመሪያው ሰዎችን ለመርዳት መፈለጓ ሲሆን፤ ለዚህም የጎረቤታቸው ባህላዊ ሀኪም ሥራዎች ገፋፍቷታል። እርሱ አልተማረም ግን በርካቶችን በልምዱ ፈውሷል። ስለዚህም እርሷም የእርሱ ልምድ ይህንን ያህል ሰው ማገዝ ከቻለ በዘመናዊ መልኩና በትምህርት ቢታገዝ ምን ያህሎቹን ዜጎች ከበሽታቸው መታደግ እንደሚችሉ ዘወትር ታስበው ነበር። ስለዚህም የበለጠ ሰዎችን ለማዳን ስትል ትምህርቱን ተማረች፡፡

ለሌላው ወደ ሙያው የሳባት የአባቷ ባህላዊ መድሀኒት ቀማሚነት ነበር ። በመማር ዜጎችን የበለጠ መታደግ ይቻላል የሚል አቋም ነበራትና ብዙዎችን በጤናው ዘርፍ ለመታደግ ትምህርቱን መርጣ ገባች። በዚህ ደግሞ ዛሬ ድረስ ለብዙዎች ተስፋ ሆናለች። ለአብነት እንኳን ብናነሳ ከሥራ ባልደረቦቿ ጋር በመሆን ከጤና ጣቢያ አልፋ ቤት ለቤት በመሄድ የጤና አገልግሎት እየሰጠች ከችግራቸው የሚላቀቁበትን እድል ፈጥራለች። በሳምንት ሁለት ቀን ወደ 38 የሚደርሱ ሕጻናት ከዋና ሥራቸው በተጨማሪነት ያለምንም ክፍያ በምትሠራበት ጤና ጣቢያቸው በተሰጣቸው አንድ ክፍል ውስጥ የፊዚዮቴራፒ አገልግሎት ትሰጣለች።

አብዛኞቹ ሕጻናት ደግሞ የአዕምሮ እድገት ውስንነት ያለባቸውና አካል ጉዳት ያጋጠማቸው ናቸው። የአልጋ ቁራኛ የሆኑም አሉ። ይህ ደግሞ የመማር እድላቸውን በብዙ መልኩ ገድቦታል። እናም ዘውዴ በምትሰጣቸው ምክረሀሳቦችና የፊዚዮቴራፐ ሕክምና ብዙ ነገሮች እንዲቀየሩ ሆኗል። በተለይ ደግሞ ሥራዋን ከቤተሰቦቻቸው መጀመሯ ነገሮች ቀላል እንዲሆኑ አግዘዋል። ወላጆቻቸው ዝቅተኛ ገቢ ያላቸው በመሆናቸው ለልጆቻቸው የሚያደርጉት ነገር ግራ ስለሚገባቸው ተስፋ በመቁረጥ ውስጥ ነበሩ። ይህ ደግሞ በቀላሉ የሚታከም አይደለም። ብዙ መመላለስንና ልፋትን ይጠይቃል። የእርሷ ውጣውረድ ብዙዎችን ከአጎነበሱበት ቀና የሚያደርግ ነውና እርሷ ያለፈችበትን ስትነግራቸውና በስነልቦና ስታግዛቸው ለነገም ለካ ነገ አለው እንዲሉ አስችሏቸዋል። ተስፋቸው እንዲለመልም ሆኗል።

በዚህም ትምህርት ቤት ያልገቡ ልጆች የትምህርት ቤት ደጃፍን ረግጠዋል። የአልጋ ቁራኛ የነበሩም መንቀሳቀስ ጀምረዋል። ከሁሉም በላይ ደግሞ መደሃኒት ያልጀመሩና ተስፋ የቆረጡ የኤች አይቪ ኤድስ ህሙማንን መደገፍ በመቻላቸው መድሃኒት እና ህክምናቸውን ፤ እንዲጀምሩ አድርገዋል።

አብዛኛውን ጊዜ ይህን አገልግሎት የምትሰጠው ኮየ ፈጬ አካባቢ በአስር ዘጠና የጋራ መኖሪያ ቤት (ኮንዶሚንየም) ለሚኖሩ ሰዎች ሲሆን፤ እነዚህ ሰዎች አብዛኛዎቹ ገቢያቸው አነስተኛና አቅመ ደካሞች ስለሆኑ ሁሌም ከጎናቸው መሆኗ የአኗኗር ዘይቤያቸውን ጭምር እንዲቀይሩ መደላደልን ፈጥራላቸዋለች።

ሲስተር ዘውዴ ለእነዚህ ሰዎች ከምትሰጠው የሕክምና አገልግሎት በተጨማሪም አቅሟ በፈቀደ ሁሉ ካላት ላይ ትረዳቸዋለች፤ የልጅነቷን የማጣት ዘመን ለእነርሱ በማድረግ ለራሷ ደስታን ትፈጥራለች። ይህ ተግባሯ ዛሬ ላይ ብቻ የሚሆን ሳይሆን ቀጣይነት ያለው እንደሚሆንም አጫውታናለች፡፡

ንብ አናቢዋ ሲስተር

ሲስተር ዘውዴ ራሷን በራሷ የማስተማር ግዴታ ሲመጣባት ነበር ተጨማሪ ገቢ ማስገኛ ሥራ መሥራት እንዳለባት የወሰነችው። ይህ ደግሞ የመጀመሪያ ሥራዋን አመላክቷታል፡፡በአቅራቢያዋ ማድረግ የምትችለው ተግባር ነው። መኖሪያዋን ያደረገችው በልደታ ቤተክርስቲያን ውስጥ ስለነበር ለትምህርት ቦታዋ እንዳይርቃት በማሰብ ከቤተክርስቲያኑ ደጃፍ ላይ ጧፍና እጣን እንዲሁም ሻማ መሸጥ ጀመረች። ይህ ሥራ ብዙ ጊዜ በበዓላት ወቅት ብቻ የሚከናወን በመሆኑም ሌላ ተጨማሪ ሥራ መሥራት እንዳለባት አሰበች። ይህንን ሥራ ሳታቋርጥም አትክልትና ፍራፍሬዎችን ከአትክልት ተራ በማምጣት በጉሊት መልክ መድባ መሸጡን ተያያዘችው። አሁን ትንሽም ቢሆን ገንዘብ የሚያስገኝላት ቢሆንም ከትምህርቷ ጋር እየተጋጨ ስላቃታት ብዙ ሊያዘልቃት አልቻለም።

ትንሽ ቤት ኪራይ የምትከፍልበት ገንዘብ ስታገኝ እርሱን ከፍላ ሌላ የሥራ አማራጭ መፈለግ ጀመረች። እድል ቀናትና በዚያው በሜክሲኮ አካባቢ ባንክ ቤት በጽዳት ሰራተኛነት ለመቀጠር በቃች። ይህ ሥራዋ ተመርቃ በጤናው ዘርፍ እስክትቀጠር ድረስ በብዙ መንገድ ያገዛት እንደነበር ትናገራለች ። አንዱ ትምህርቷን ያለምንም መጨናነቅ እንድትከታተል ማገዙ ነው። ሌላው ደግሞ ተጨማሪ ትምህርት እንድትማርና ሲኦሲዋን ከምረቃ በፊት በአግባቡ እንድታጠናቅቅ የረዳት ነው፡፡

ባለታሪካችን የተለያዩ ሥራዎችን ብታከናውንም እንደ ጤና ሥራው ልቧን እርፍ የሚያደርገው የለም። መንፈሷ የሚታደሰው ችግረኞችን ተረድታ ህመምተኞችን አክማ ስትወጣ ነው። በተለይም ሰዎችን ከውስጣዊ ሕመማቸው እንዲታከሙ ስታደርግ ራሷን ያጽናናች ያህል ይሰማታል። በዚህም ከምረቃ በኋላ ሌሎች የሥራ አማራጮች ቢኖሯትም ሌላ ሥራ ለምኔ አለችና በግል ሆስፒታል ውስጥ ተቀጥራ ሥራዋን ጀመረች።

ነርስ ብትሆንም እንደ ጠቅላላ ሀኪም በጎደለው ሁሉ እየገባች ሰዎችን ማገዟን ቀጠለች። ይህ ደግሞ የተሻለ ልምድ ባለቤት አርጓታል። በጥርስ ሕክምና ባትማርም ለማከም የሚያስፈልጉ ነገሮችን ጠንቅቃ እንድታውቅ አግዟታል። ምልክቶቹን ሰምታም አፋጣኝ መፍትሄ ሲያስፈልግ ለሰዎች መድህን መሆን ችላለች።

እንግዳችን ረዘም ላለ ጊዜ በሆስፒታሉ ከሠራች በኋላ የባለቤቷ ሀሳብ አሸነፋትና እንደ እርሱ ጫት ንግድ ውስጥ ገባች። የንግድ ሥራው በእጅጉ ትርፋማና ብዙ ገቢ የሚያስገኝላቸው ነበርና ለዓመት ያህል ዘለቀችበት። ሆኖም ቃል የገባችውና እየሠራች ያለችው ሥራ ተቃራኒ በመሆናቸው የአዕምሮ ወቀሳውን ልትቋቋመው አልቻለችም። ሰዎችን በአዳነችበት እጇ ጫት እየቀነጠበች ሰዎችን እንዲሞቱ መጋበዟን አዕምሯዋ ሊቀበለው አልቻለም። ስለዚህም ከዚህ ሥራ ለመውጣት ወሰነች።

በቀጥታም ወደ ጤናው ሥራ ለመግባት በአቃቂ ክፍለ ከተማ ውስጥ በሚገኘው ቀሊንጦ ጤና ጣቢያ አመለከተች። ውጤቷ ጥሩ ነበርና ያለማቅማማት ተቀበሏት። አሁን ድረስም ቦታ ብትቀይርም የጤና ሥራዋን ሳታቋርጥ ብዙዎችን እያገዘች ትገኛለች።

‹‹መቀመጥ መቆመጥ ነው›› ብላ የምታስበዋ እንግዳችን ባገኘቻቸው አጋጣሚዎች ሁሉ ተጠቅማ ራሷን የሚለውጡ ተግባራትን ታከናውናለች። ተጨማሪ ሥራዋን የምትሠራው በሥራ ምክንያት ባወቀችው ኮዬ ፈጨ መንደር ውስጥ ነው። በቦታው ቤት ሠርታ ትኖራለችና ተጨማሪ የሥራ ዕድል ለራሷ በመፍጠር ከጤና ባለሙያነት ሥራዋ በተጓዳኝ የተለያዩ ሥራዎችን ታከናውናለች። ዋና የገቢ ምንጯ ከአደረገቻቸው መካከል ደግሞ ንብ የማነቡ ሥራ አንዱ ነው። ንብ ማነብ የሙሉ ቀን ጊዜ እና ክትትል ስለማይፈልግ መደበኛ የሥራ ጊዜዋን ሳትጋፋ የምትፈጽመው ነው። በዚህም በንብ ማነብ ሥራዋ በትንሽ ወጪ ጥሩ ገቢ ታገኛለች።

ዘውዴ ትንናት ላይ ከ40 የማያንስ ባህላዊ ንብ ቀፎች በግቢዋ ውስጥ ነበራት። ዛሬ ግን ወደ 28 ዝቅ ብሏል። ምክንቱም ዘመናዊ ቀፎ ስለሌላት ንቦቹ ተናዳፊ በመሆናቸው ከጎረቤት አጣሏት፤ ሰው ገለው ከምታሰር በሚልም በዝቅተኛ ዋጋ ቁጡ ናቸው የምትላቸውን መርጣ ሸጠቻቸው። በዚህም ሁሌም ትቆጫለች። አሁንም ቢሆን ዘመናዊው የንብ ቀፎ ካልመጣላት በብዙ መልኩ እንደምትቸገር ታነሳለች። እናም በዚህ አጋጣሚ የሸገር ከተማ አስተዳደር ቢያየኝ ስትል ትማጸናለች።

እርሷ ጥያቄዎችን ስታቀርብ በምክንያት ነው። ያላትን ሀብትና አቅም አሟጣ በመጠቀምም ነው። ከዚህ አንጻርም የሸገር ከተማ አስተዳደር መፍትሄ እንደሚሰጣት ታምናለች። እስከአሁንም በብዙ ነገር እንዳገዛት ትናገራለች። 500 ዓሳዎችን አግኝታ እንድትሠራ ያደረጓትም እነርሱ መሆናቸውን አልሸሸገችም። ሆኖም የበለጠ ለመሥራት ቦታና ዘመናዊ የንብ ቀፎ የምታገኝበት እድል ቢመቻችላት ደስተኛ እንደምትሆን ታነሳለች። ሥራው በእርሷ እና ባለቤቷ ብቻ የሚንቀሳቀስ ባለመሆኑ ለብዙ ዜጎችም የሥራ እድል እንደምትፈጥር ታምናለች። ስለሆነም በዚህ አጋጣሚ አግዙኝ ስትል መልዕክቷን ታስተላልፋለች።

ሲስተር ዘውዴ ከአላት 28 የንብ ቀፎ በዓመት ሦስት ጊዜ ታመርታለች። በአንድ ጊዜ ከ150 እስከ 200 ኪሎ ማር እንደምታገኝ ትናገራለች። ለዚህ ምርታማነት ያገዛት ከንቦች ጋር ያላት ትውውቅ የቅርብ ጊዜ ከልጅነቷ ጀምሮ የነበረ በመሆኑ ነው። በዕድሜ ትንሽም ብትሆንም ከቤተሰቦቿ በቻለችው መጠን ሥራውን ለምደዋለች። በዚህም በመኖሪያ ስፍራዋ ለዚህ ሥራ የሚሆን ምቹ ሁኔታን ፈጥራለች።

‹‹ሕይወት ዳገትና ቁልቁለት አለው›› የምትለው ሲስተር ዘውዴ፤ የተደላደለ መንገድ ላይ መድረስ የሚቻለው ሥራን ሳይንቁና ሳይመርጡ ማከናወን ሲቻል ብቻ እንደሆነ ታምናለች። በዚህም የሰዎችን ጤና ለመጠበቅ ተፈጥሯዊ የሆኑ ምርቶች ላይ ትኩረቷን አድርጋ ትሠራለች። ለዚህም ምስክር የሚሆነው ራሷ ከምታመርተው ማርና ዓሳ በተጨማሪ ሌሎች ልዩ ልዩ ምርቶችን አምራች ከሚባሉ ቦታዎች እያመጣች ከቢሮዋ አጠገብ በከፈተቻት አነስተኛ ሱቅ ውስጥ ማቅረቧ ነው። ለምሳሌ ቅቤና አይብ ከአሰላ፤ ቡናን ደግሞ ከጅማ እያስመጣች ቤት ለቤት ጭምር ታቀርባለች፡፡

በተጨማሪም በቀን 200 እንጀራ ከማቅረብ አልፋ በሌሊት በመነሳት ስድስት አይነት ወጥ ሰርታ ለባለቤቷ በማስረከብ ገቢዋን ከፍ እያደረገች ዜጎች ጤናማ ምግብ እንዲያገኙ ታደርግም ነበር። ለሲስተር ዘውዴ ምሽቱም ቀን ነው። በሥራ የሚራመድ ሰዓት። ግን ሠርታ እንዳልጠገበች ታስባለች። ብዙ መሮጥ እንዳለባት ታምናለች። በዚህም ቀጣይ ላይ ልትሠራቸው ያሰበቻቸው በርካታ ተግባራት አሏት።

ለእርሷ የመንግሥትም ሆነ የንግድ ሥራ ትጋትንና ደከመኝ ሳይሉ መሥራትን የሚጠይቅ ነው። በዚህም በሁለቱም ሥራዎቿ ቀልጣፋና ከግብ ማድረስ የምትፈልጋቸውን መጨረሻ የምታይ ነች። ለአብነት በንግዷ ዙሪያ ስትሠራ አንደበቷ ማስታወቂያዋ ነው። ለመቶ ሰው ሥራዬን ባስተዋውቅ ከዚያ ውስጥ 10ሩ ይገዛኛል የሚል እምነት አላት። ይህም ውጤታማ የሆነችበት ተግባር እንደሆነ ታስረዳለች። ሥራዋ ምርጥና ታማኝነት የታከለበት በመሆኑ ደግሞ የማይፈልጋት የለም።

ታዋቂና በብዙ ሰዎች ዘንድ ተወዳጅ የማርና የእንስሳት ተዋዕጾዎችን አቅራቢዋ ሲስተር ዘውዴ፤ ‹‹ሰው ጤነኛ ከሆነና ዓላማ ካለው ሠርቶ መለወጥ አያቅተውም የሚል አቋም አላት። ነገሮችን በየአቅጣጫው የማየት ልዩ ችሎታ ከአለውና አልችልም ብሎ ራሱን ካላሰነፈ በስተቀር ቢወድቅም ይነሳል ብላ ታምናለችም። በዚህ ደግሞ ገበያ እንዴት እንደሚመራ አውቃበታለች። ሴት መሆኗ ደግሞ በብልሃት ነገሮችን እንድታከናውን እድል ሰጥቷታል። ዛሬም ቢሆን ከባለቤቷ የምትጠይቀው አንዳች ነገር የለም። እርሱም ከእርሷ ባልተናነሰ መልኩ የሚሠራ ቢሆንም የእርሷን ያህል ግን ፈጣን አይደለም። ብዙ ገቢ የሚገኝበትን አማራጭ የምታመላክተው እርሷ ነች። ሰዎችን በማግባባት ንግዷን የምታጧጧፈውም በእርሷ አማካኝነት ነው፡፡

በምንም ያልተበገረው ማንነት

የሰው ልጅ ‹‹አንድም ከፊደል ሀ ብሎ ሁለትም ከመከራ ዋ ብሎ›› ይማራል እንደሚባለው ሁሉ ሲስተር ዘውዴም ከትምህርትና ከመከራዎቿ ያገኘቻቸውን ልምዶች ወደ ጥሩ መስመር አስገብተዋታል። ኑሮዋን በተሻለ አቅም እንድትመራም አስችሏታል። የጥንካሬዎቿ ምንጭም ሆነውላታል። እነዚያን ማረፊያ አጥታ የተንገላታችባቸው፤ ርቧት መከራ ያየችባቸው መጥፎ ገጠመኞቿ በዛሬው ሕይወቷ ውስጥ የሚተረጎሙትም የብርታትና የጥንካሬን ተምሳሌት ተደርገው ነው። ምክንያቱም ጊዜዎቹን ስታስባቸው በመልካም ጎዳና እንድትጓዝ አቅጣጫን አመላክተዋታል። ራበኝ፤ ጠማኝ ማለቷም ለሌሎች መድረስን አስተምረዋታል።

ዛሬን አሻግራ እንድታይ እድል ከፍቶላታል። ሌሎችን እንድታስብና ከማዕዷ ቆርሳ እንድታካፍልም አድርገዋታል። በእነርሱ ውስጥ ማለፏ የማይታየውን ብቻ ሳይሆን የሚታየውንም የደጅ በረከት እንድታፍስም አግዟታል። ከምንም በላይ የፈገግታዋ ምንጭ ሆነውላታል። በመከራዋ ትስቃለች እንጂ አንድ ዘለላ እንባ አታፈስም።ይሄ ጥንካራዋ ዛሬ ላይ ማየት ያለባትን ሁሉ እንድታይ አስችሏታል።

«ሴት ልጅ ችግሯን አልቅሳ ትረሰዋለች» የሚባለው አባባል በእርሷ ዘንድ እንዳይሠራ የሆነውም ከዚህ የተነሳ ነው። የሚደርስባት ፈተና የበለጠ እንድትጠነክርና ምንም እንደማይፈጥርላት ተረድታ እንድትተጋ ያደረጋት ምንም ሳይሆን በሁለቱም በኩል የተሳለች ሰይፍ ስለሆነች ነው። ነጥራ የወጣች ወርቅ በመሆኗ ደግሞ ራሷን ከጎዳና ታድጋለች።

የምሽቱ ብርሃን

ያቺ አጋጣሚ እጅግ ልዩ ነበረች። ምሸት ብትሆንም በአሯሯጣት እብድ ምክንያት የነገ ውሃ አጣጯን አግኝታበታለች። ከሥራ ስትወጣ ምሽት ነበር። እየፈራችና እየቸረች ስትራመድም ድንገት አንድ እብድ ተከተላት። መተንፈስ እስኪያቅታትም አሯሯጣት። የዛሬው ባለቤቷም እንዳትጎዳ ብሎ ተከትሏቸው ሮጠ።

በወቅቱ እብዱ ቢቆምም ውሃ አጣጯ ግን ይከተላት ይዟል። የመጣው ይምጣ ብላ ስትቆም ነው ጤነኛ ሰው መሆኑን የተረዳችው። ያ ቅጽበት ደግሞ የነፍሴ ቤዛ፤ የምሽቱ ብርሃኔ እንድትለው አስቻላት። ስልክ ተለዋውጠው ነጋቸው ላይ አወሩ። በትዳርም ተሳሰሩ። በዚህም ዛሬ ላይ የሦስት ልጆች እናትና አባት ሆኑ።

መልዕክተ ዘውዴ

ሲስተር ዘውዴ ሰዎች አመኔታ እንዲያገኙ፤ በነብሳቸውም በረከትን እንዲያፍሱ ካሻቸው አንድ ነገርን አጥብቀው ሊወዱ እንደሚገባ ትመክራለች። ይህም ሰዎችን ሁሉ ምንም ሳያበላልጡ መውደድ ነው። በፍቅር ነገሮችን ማድረግ አሻናፊነትን በሁሉም መስክ መቀዳጀት ነው። ጥንካሬን ማግኘትና ነጋችንን ብሩህ ማድረግ ነው። ከሰዎች ጋር በሰላም መኖር ፤ የተሻለ አማራጮችን መመልከትም ነው ትላለች። በሌላ በኩል በእሽታ ውስጥ መልካም ነገሮችን መሰብሰብም እንደሚቻል ታምናለች። ሰዎች በተለይ ማድረግ የሚችሉትን ከማድረግ ወደ ኋላ ማለት እንደሌለባቸው ትመክራለች።

ለመንግሥት ሰራተኛ ጊዜ ማለት ስምንት ሰዓት የሚሠራበት ተብሎ ብቻ ይወሰዳል። እርሱም ቢሆን በአግባቡ ጥቅም ላይ ሲውል አይታይም። በዚህም ለውጣችን ከመስሪያ ቤት ጭምር እንዳይሻገር ሆኗል። ነገር ግን ሰዓት ገደብ ሳይኖረን ብንሠራ፤ ተቆጥሮ የተሰጠንን ብቻ ሳይሆን በጎደለው ሁሉ እየገባን ብንተጋና ብንሠራ ጊዜው ከሥራው ጋር ተዳምሮ የጨለመውን ሁሉ ያነጋልናል። እኛንና መስሪያ ቤታችንን ብቻ ሳይሆን ሀገራችን ሲለውጣት እናየዋለንም። ስለሆነም ጨለማችንን ለማንጋትና በብርሃን ለመመላለስ ካሰብን ሥራችንን ከጊዜያችን ጋር እናመጣጥነው፤ ሌሎችን ሳንጠብቅ የራሳችንን ድርሻም እንወጣ ስትልም ከተሞክሮዋ በመነሳት ትመክራለች።

በመጨረሻም ዛሬ ላይ የምንሠራው መጥፎም ሆነ ጥሩ ነገር ነገ ላይ ይከፍለናል ካለች በኋላ ሰዎች ለራሳቸውም ሆነ ለልጆቻቸው እንዲሁም ለሀገራቸው ሲሉ በጎ መሥራትን አዘውትረው ሊፈልጉት ይገባል። የሚከስቱት እውቀትም ሆነ ጉልበት መኖር የለበትም። ምክንያቱም ነገ ምን እንደሚፈጠር አይታወቅም። እናም ዛሬ ላይ ስማችንን ተክለን ለማለፍ ካሰብን ሌት ተቀን ለሀገራችን መልፋት አለብን በማለት መልዕክቷን ቋጭታለች።

ጽጌረዳ ጫንያለው

አዲስ ዘመን እሁድ ግንቦት 3 ቀን 2017 ዓ.ም

Recommended For You