እንደምን አላችሁልኝ ውድ የአዲስ ዘመን ጋዜጣ ወዳጆቼ፤ ለዛሬው ጽሑፌ መንደርደሪያ ይሆነኝ ዘንድ ከመጽሐፍ ቅዱስ አንድ የታሪክ ሃሳብ ልዋስ ወደድኩ። ታሪኩ እንዲህ ነው፤ አንድ ሰው ጌታ እየሱስ ክርስቶስን በመንገድ ሲመጣ አየውና ወደ እርሱ ሮጦ በመንበርከክ ቸሩ መምህር ሆይ የዘላለም ሕይወት እወርስ ዘንድ ምን ላድርግ ብሎ ጠየቀው። እርሱም እንዲህ አለው፤ ትዕዛዛትን ፈጽም። እነሱም አታመንዝር.፣ አትግደል አትስረቅ፣ በሐሰት አትመስክር፣ አታታል እናትና አባትህን አክብር፣… የሚሉት ናቸው አለው።
እኔም ለዚህ ጽሑፌ ማጠንጠኛ የሚሆነኝ ሃሳብ ከእነዚህ ህያው ትዕዛዛት ውስጥ የምናገኘውን አንድ እውነት “አትስረቅ” በሚለው ቃል የተጠቃለለው ነው። “ሌብነት” በፈጣሪ አታድርጉ ተብሎ ከተደነገጉ ከአስርቱ ትዕዛዛት አንዱ በመሆኑ፤ መስረቅ በአደባባይ አዋርዶ በሕግ ከማስጠየቅም በላይ እስከ ሞት ድረስ ተከትሎ ገሀነም እሳት ውስጥ የሚያስወረውር ሐጢያት ነው::
ሌብነት በምድር ጥዩፍ፣ በሰማይም ሐጢያት ከመሆኑም በላይ፤ በህዝቦች ላይ የሚፈጥረው ጉዳት ከፍ ያለ ነው። ይሄን የተገነዘቡት ጠቅላይ ሚኒስትር ዶክተር ዐቢይ አሕመድም፣ ከሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት አባላት ለተነሱላቸው ጥያቄዎች ምላሽ እና ማብራሪያ ሲሰጡ ሙስናን በተመለከተ አንስተው ባስረዱበት ወቅት፤ ሙሰኞች “ፋይል በእጅ ካልሆነ በእግር አይሔድም” እያሉ ሕዝቤን አስቸግረውብኛልና እባካችሁ አግዙኝ ሲሉ ድፍን ኢትዮጵያ እየሰማቸው በሕዝብ ተወካዮች ፊት ተማፅነዋል።
“ሙስና” በሚል የዳቦ ስም የሚቆለጳጰሰው ሌብነት ከሀገሪቱ የፀጥታ ችግር እኩል ስጋት ሆኖ በአገልግሎት አሰጣጥ ላይ ከፍ ያለ አደጋን ደቅኗል። በተለይ ከመሬት ጋር በተያያዙ አሰራሮች፣ በፋይናንስ ዘርፍ፣ በሽያጭና በግዥ ሒደቶች፣ በፍትህ አደባባዮች፣ በተለያየ የመንግስት ተቋማት፣ በልማት ድርጅቶችና፣ የህዝብ ተቋሟት በሚያጋጥመው ሙስና ሕዝቡ እየተማረረ ስለመሆኑም ነው አጽንዖት ሰጥተው ያስረዱት። ስለሆነም ተባብረን ይህንን ነቀርሳ ከስሩ ነቅለን እንኳን መጣል ባንችል አንገቱን እናስደፋ ሲሉም ጥሪ አቅርበዋል።
አብዛኛው የኢትዮጵያ ሕዝብ መንግስት ቁርጠኛ ከሆነ ጥሪውን ተቀብሎ ለማገዝ ዝግጁ መሆኑን በሶሻል ሚዲያው ላይ የተንሸራሸሩትን አስተያየቶች ለመዳሰስ ሞክሬያለሁ። ይሄ ችግሩን ለመፍታት የመንግስት ቁርጠኝነቱ ካለ ሕዝቡ ከችግሩ ለመገላገል ካለው መሻት የተነሳ ተባባሪ ለመሆን ያለውን ፈቃደኝነት ያየሁበት ነው። በሌላ በኩል ደግሞ አንዳንድ ተችዎች ጠቅላይ ሚኒስትሩ ይሄን የሚሉት ሌባ ባለስልጣኖቻቸው ጠፍተዋቸው ሳይሆን የሕዝቡን ልብ ለመያዝ ነው ሲሉ ትዝብታቸውን በአስተያየት መስጫው ላይ አስቀምጠው አንብቤያለሁ። ሌሎች ደግሞ በጣም ዘግይተዋል፤ ሌብነት መብት ሆኖ አዲስ አበባ ላይ በአዋጅ ሊወጣ ትንሽ ሲቀረው ነው መንግስት የባነነው በማለት ተስፋ በቆረጠ አስተያየት ሀሳባቸው መግለጻቸውን ተመልክቻለሁ። እኔም እነዚህን ሀሳቦች መነሻ በማድረግ የራሴን ጥያቄዎች እያነሳሁ የመሰለኝን ምልከታና መፍትሄ ያልኩትን ለማጋራት ወደድሁ።
ለመሆኑ ሌብነት ምንድነው?
“ሌብነት”ን የወንጀለኛ መቅጫ ሕግ እንደሚተረጉመው፤ ህገ-ወጥ በሆነ መንገድ የሌላ ሰውን ንብረት ያለ ባለቤቱ ፍቃድ መውሰድ ነው። በተለምዶ ግን ሌብነትን ከማምታታት፣ ከማጭበርበር እና ሌሎች ድርጊቶች ጋር ያመሳስሉታል። በዚህ ተግባር ላይ የተሰማሩ ሰዎች ሌቦች እየተባሉ ይጠራሉ። ሌባን ደግሞ ማንም አይወደውም:: በዚህ ምክንያት ኃላፊነት በጎደላቸው ባለስልጣኖቿ የምትመዘበረውን ድሃ ሀገራችን ኢትዮጵያ፤ ፀረ ሙስና ኮሚሽን አቋቁማ ሌብነትን አርቆ ለመቅበር ስትሰራ ቆይታለች፤ አሁን ደግሞ ይሄን ለማድረግ ጥርሷን ነክሳ ተነስታለች። ለዛሬው መጣጥፌ ብዕሬን ተደግፌ እንድቆዝም ያደረገኝ ምክንያትም ይኸው ነው።
በቅድሚያ “በእርግጥ ሌብነትን በአዋጅና በዘመቻ ማስቆም ይቻላል?” በማለት እራሴን እንደ ዜጋ እጠይቃለሁ:: መልሴም አዎን! ይቻላል! የሚል ነው!። ይህ የሚቻለው ግን መንግስት ብቻ በሚሰራው ስራ ሳይሆን ሁላችንም የየድርሻችንን ስንወጣ እንደሆን አምናለሁ። ምክንያቱም እንደምናውቀው ሌብነት ሀገርን የሚያጠፋ ወረርሽኝ ነው። የመንግስት ባለሥልጣኖችን የሚያነቅዝ ነቀርሳ ነው:: ሌብነት በፍቅረ ነዋይ የታወሩ ደላሎችና ባለሃብቶች፣ ከፍተኛ የመንግስት ባለስልጣኖችን ጨምሮ አንድ ላይ የሚሞሸሩበት ክለብ ነው::
ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ በሕዝብ ተወካዮች ፊት በቀጥታ በሚተላለፈው የቴሌቪዥን መስኮት ውስጥ እየታዩ “ሌባ ቤት እንጂ አገር የለውም። አገር አልባው ሌባ የሰረቀውን ገንዘብ በአግባቡ እንኳን መጠቀም አይችልም” በማለት በምሳሌ ተናግረዋል። ባለቤት አልባ ሕንፃዎች እስከ አሁን ድረስ የኔ ነው ባይ አጥተው በየከተማው ውስጥ ተገትረው እንደቀሩ ለምክር ቤቱ በዝርዝር ማስረዳታቸውም የዚሁ ማሳያ ነው።
ጠቅላይ ሚኒስትሩ በዚያን ወቅት ንግግራቸው ወቅት፤ ሌቦች ቤቱን ይሰሩታል እንጂ አይኖሩበትም:: ገንዘቡን ይሰርቁታል እንጂ ደህና ሆቴል ገብተው በአግባቡ ሊጠቀሙበት እንኳን አይችሉም ሲሉ የሆዳቸውን በሆዳቸው አርገው የደህንነት ስጋት የሆነባቸውን ሙስና ለመፋለም ቁርጠኝነታቸውን አሳይተዋል። ለሌቦቹም ምህረት እንደሌላቸው በምሬት አስጠንቅቀዋል:: ሳይውሉ ሳያድሩም የፀረ ሙስና ብሔራዊ ኮሚቴ ማቋቋማቸውን ገልጸው፤ የሾሟቸውን ባለስልጣኖች ስም ዝርዝራቸውን ይፋ አድርገዋል።
እዚህ ጋ አንድ ነገር ለማንሳት ወደድኩ፤ እሱም፣ “ለመሆኑ ሌቦቹ የሚኖሩት የት ነው?” የሚል ይዘት ያለው ነው። ይሄን ሳነሳም የፀረ ሙስና ብሔራዊ ኮሚቴው ተደራሽነት የት ድረስ እንደሆነ ለመረዳት ከመሻት የመነጨ ነው። ምክንያቱም የፀረ ሙስና ብሔራዊ ኮሚቴው አዲስ አበባን ብቻ ሳይሆን ምናልባት ሌሎችንም ክልሎች አብሮ ይፈትሹት ይሆን? የሚለው ጥያቄ ሁሉም ጋ መነሳቱ ስለማይቀር ነው። ሆኖም መልሱን ለመስማትም ሆነ ውጤቱን ለማወቅ ጊዜን መጠበቅ ግድ ነው።
ሙስና (ሌብነት) የተሰኘው ህብረተሰባዊ ጠንቅ በአንድ ሀገር ወይንም በአንድ ክልል ብቻ የተወሰነ ሳይሆን የክልሎች አስተዳደር የማይገድበው አገራዊ ችግር በመሆኑ፤ ሁሉም ክልሎች የፈጠረባቸውን ጫናና ያመጣባቸው ጣጣ አሳስቧቸው ፀረ ሙስና ኮሚሽን ቀደም ብለው አቋቁመዋል። ሆኖም አገራችን ሌብነትን በዘመቻ ለማጥፋት እስከ አሁን ድረስ አልችል ብላ፣ አዲስ የፀረ ሙስና ብሔራዊ ኮሚቴ ማቋቋሟን ይፋ አድርጋለች::
ቀደም ባሉት ጥቂት አመታት ኢትዮጵያ ውስጥ ኪሳቸው የሞላውን ሚሊዬነሮች በባዶ ኪስ ሙሰኞች ከመተካትና ለጥቂት ጊዜ ለማስደንገጥ ከመሞከር ባለፈ ፀረ ሙስና ዘመቻው ተሳክቶለት ሌብነትን ከክልሉ አስወግጃለሁ ያለና አፉን ሞልቶ በድፍረት የተናገረ የክልል መንግስትም ሆነ የከተማ አስተዳደር እስከ አሁን ድረስ ሲናገር አልሰማንም:: ምክንያቱም ላለፉት 27 ዓመታት በሙስና ወንጀሎች የሚፈፀሙት ሌብነቶች በሚስጥርና በጥንቃቄ በመሆኑ ወንጀሉን የሚያሳይ ምንም አይነት ምልክት እንዳይኖር በወኪሎቻቸው አማካኝነት የመረጃ ሰነዶቹን ሁሉ ለማጥፋት ከፍተኛ ዘመቻ ይደረግ እንደነበረ መረጃና ደህንነቱ በሚገባ ጠንቅቆ ያውቃል::
የዛሬን አያድርገውና ስም አይጠሬ ባለስልጣኖች በቴሌቪዥን መስኮት እየወጡ በሚዲያ ላይ አይኔን ግንባር ያደርገው ብለው ሲምሉ መንግስት ተጨባጭ ማስረጃ እያለው ከመሞገትና ለፍርድ መቀጣጫ ከማድረግ ይልቅ ለሰላም ቅድሚያ በመስጠት ዝምታን ሲመርጥ፤ ሕዝቡም የውሾን ነገር ያነሳ ውሾ ይሁን በማለት ሆድ ይፍጀውን እያንጎራጎረ ፀጥ አለ:: ዛሬ ደግሞ ሌብነት እንደመብት በአዋጅ ሊወጣ ትንሽ ሲቀረው በሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት ጠቅላይ ሚኒስትሩ አግዙኝ በማለት ጥሪ ሲያቀርቡ፤ አንጀቱ ሲቃጠል የኖረው ሕዝብ “እረ ጎበዝ ..!” ማለቱ ብዙም አያስገርምም።
የሙስናው ባለቤቶች ወንጀሉን የሚፈፅሙት በሚስጥርና በጥንቃቄ ስለሆነ በአዋጅና በዘመቻ ብቻ ሌባን ለመያዝ ትንሽ ሊያስቸግር ይችል ይሆናል:: ሌባውን በቅድሚያ ለመመርመር መነሻ ሊሆን የሚችል አሻራ እንዳይኖረው የሚዘርፉበት ስልት ቤተሰባዊ ሌብነት በመሆኑ ከደረቅ ወንጀሎች ጋር ሲነፃፀር ሚስጥሩ ከወጣ ሁሉም ተያይዘው እንደሚጠፉ ስለሚያውቁት የሌብነቱን ወንጀል ትንሽ ውስብስብና እረቂቅ ያደርጉታል።
የለውጡም መንግስት ቢሆን ለናሙና ጥቂት ሰዎችን ብቻ አስሮ ህግ ፊት ቢያቀርብም ሕዝቡ ግን በፍትሕ ስርአቱ ላይ ያለው ጥርጣሬ የሆድ ቁርጥት ሆኖበት እየተማረረ ከመጮህ ያለፈ ፍትህ አላገኘም። ሙስናም ዘውዱን ደፍቶ ከሚኒስቴር መስሪያ ቤት እስከ ቀበሌ ድረስ ሕዝቡን አራቁቱን እስኪቀር ድረስ አሟጦ ገፎታል:: እኛም እውነቱን ለመፃፍ ስንነሳ ሁሉም ነገር ትርጉም እየተሰጠው ፅሁፎቻችን ስለሚቆራረጡ ብዕረ ሰባራ እንሆናለን በሚል ስጋት እያየን እንዳላየን እናልፈዋለን:: ዛሬ ግን የቁርጥ ቀን መጥቷልና ጨከን ብለን እውነቱን እንነጋገራለን::
በኔ ግምት የሌብነት ዋናው የችግሩ ምንጭ የመንግስት የራሱ አሰራርና አወቃቀሩ ነው። የለውጡ መንግስት በእንደመር እሳቤ ሌቦቹን እያወቀ በሪፎርም ሊለውጥ ሞከረ እንጂ ሙሉ በመሉ ጠራርጎ አላስወጣቸውም:: ሪፎርሙ ደግሞ ዘገምተኛ በመሆኑ ሙስናን ማጅራቱን ይዞ ለፍትህ አካል ለማቅረብ ዝቋላ ተራራን የመውጣት ያክል ከብዶት እስከ አሁን ድረስ ክብረ ወሰኑን ይዞ ቆይቷል።
“ሙስና” ገንዘብ መስረቅ ወይንም ማባከን ወይንም በስልጣን ያለ አግባብ መጠቀም ብቻ ሳይሆን፤ ስራን በተገቢ ሁኔታ ባለመስራት ህዝብን በማጉላላት ከለውጡ ጋር ባለመደመር በኃላፊኑት ላይ ተቀምጦ ለውጥ በማደናቀፍ ሌት ከቀን ከአሸባሪዎች ጋር በመተባበር የሚሰሩ ሌቦች ከቀበሌ እስከ ላይኛው ቢሮ ድረስ አሁንም እየተሹለከለኩ አሉ።
የዝውውር ምደባም ሲወጣ የመንግስት ገንዘብ ለመዝረፍ በሚያመች ቦታ በዘመድ አዝማድ በእጅ መንሻ አለቆቻቸውን እያባበሉ ከከፍተኛ መምሪያ ኃላፊነት እስከ አምባሳደርነት በጉቦ ብቻ እድገት የተሰጣቸው ከፍተኛ ባለስልጣኖችን እንደነበሩ ሕዝቡ ጠንቅቆ ያውቃል። ምደባ በችሎታ ሳይሆን በማሽቃበጥ በትውልድ አካባቢና በሀሰት የትምህርት ማስረጃ በጉቦና በጓደኝነት እስከ አሁን ድረስ የሀገሪቱ ዋና ችግር ሆኖ በይደር ተከድኖ ተቀምጧል:: ሌላው ቢቀር ባለስልጣኖቻችን አጃቢዎቻቸውና የቤት አገልጋዮቻቸው ሳይቀሩ የነሱን ቋንቋ ካልተናገሩ አንቀበልም እያሉ የደህንነት መስሪያ ቤቱን የሚያስቸግሩ እንዳሉ መንግስትም ሕዝቡም ያውቃል::
ውድ የአዲስ ዘመን ጋዜጣ ወዳጆቼ፤ እነዚህን ሀሳቦች ሳነሳ ተስፋ ለማስቆረጥ ፈልጌ ሳይሆን ሌብነትን የሚያክል ዘንዶ አንገቱን አንቆ የዋጠውን ለማስተፋት ኮሚሽን ብቻ መቋቋሙ በቂ ነው ብዬ ስለማላምን ነው። በመሆኑም ስር የሰደደውንና የገዘፈውን ሙስና በሚፈለገው መልኩ ለማስወገድ ባይቻል እንኳን ለማዳከም እንዲቻል ከታሰበ ከብዙ በጥቂቱ የሚከተሉት ጉዳዮች ከግምት ሊገቡ ይገባል ብዬ አምናለሁ።
1ኛ. ሙስናን ለመዋጋት በአስቸኳይ እያጣራ ቅጣት የሚሰጥ ልዩ ፍርድ ቤት ማቋቋም ያስፈልጋል፤ ለዚህም ጠንካራና ቆራጥ ዳኞችን የዘመቻው አካል ማድረግም ምርጫ የሌለው ጉዳይ ነው::
2ኛ. ከዘርኝነትና ከጥቅመኝነት የፀዳ የፍትህ ስርአቱን በአግባቡ የሚተነትን ትንታግ ዐቃቢ ሕግ መርጦ መመደብ የግድና አስፈላጊ ነው።
3ኛ. ምርመራውን ያለምንም ተፅዕኖ በነፃነት የሚያከናውን በፀረ ሙስና የሰለጠነ የደህንነትና የፖሊስ ኃይል መመደብ ወሳኝ ጉዳይ ነው::
4ኛ. ከህዝብ የሚቀርቡለትን ጥቆማዎችና አቤቱታዎችን ጆሮ ሰጥቶ ሚስጥራቸውን ጠብቆ በታማኝነት ሌቦቹን የሚያጋልጥ ሆድ አደር ያልሆነ ጋዜጠኛ ያስፈልገናል።… ወዘተ…ወዘተ..! ያስፈልጋሉ።
በመሆኑም ዘመቻው በዚህ አይነት ጠንካራ ተቋም ተደግፎ ካልተመራ በዋስትናና በገንዘብ ቅጣት ብቻ የሚያበቃ የአንድ ሰሞን የሚዲያ ፍጆታ ሆኖ እንዳይቀር የመንግስት ቁርጠኝነት ወሳኝ ነው። ምክንያቱም ሌብነት እንደ ሸረሪት ድር ውሉ የማይታወቅ ስለሆነ በአንድ ሳምንት ዘመቻ የሚወገድ አይደለም። ሌብነት የክረምት ጎርፍ በመሆኑ ሁሉንም ጠራርጎ ስለሚወስድ ጥንቃቄና ብልሃት ይጠይቃል። በህብረተሰቡ ውስጥ ያለው አመለካከት ገና ባልተቀየረበት ሁኔታ ኮሚሽኑ ብቻ ሌብነትን ሙሉ ለሙሉ ይቀረፋል ብሎ መቀበልም አይችልም። በአንጻሩ የተመደቡት የኮሚሽኑ አባላት ካለባቸው ተደራራቢ የስራ ኃላፊነት አኳያ በትክክል ይህንን ተቋም ይመሩታል ወይ የሚል ስጋት በብዙዎቻችን አዕምሮ መመላለሱ አልቀረም። ሆኖም ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ፣ “ሙስናን ጨርሶ ባናጠፋውም አንገት እናስድፋለን” ባሉት መሰረት መሞከሩ አይከፋም።
ሌብነት የለመደን እጅ በአንድ ሳምንት ውስጥ ለመሰብሰብ ቴሌቪዥን ላይ ወጥተን ስለተናገርን፣ ኮሚቴ ስላዋቀርን፣ ጋዜጣ ላይ ስለፃፍን ብቻ የምንፈልገው ግብ ላይ እንደርሳለን ብሎ ማሰብ ከባድ ሊሆን ስለሚችል በደንብ ልናስብበት ይገባል። በሌላ በኩል ደግሞ ይቻላል ብለን ደረታችንን ነፍተን ለመፋለም ዝግጁ እስከሆንን ድረስ፤ ሕዝቡም የሚዲያ ተቋማትም ሕግ አስከባሪዎችም የመፍትሔው አካል መሆን ይኖርባቸዋል። እንዲሆኑም ማስቻል ይጠበቃል።
እጃቸው በሙስና የቆሸሹ ሌቦች ዝም ብለው የሚቀመጡ ሳይሆን ጎርፉ እስከሚያልፍ እንደ ሰንበሌጧ አጎንብሰው ለማሳለፍ ፖስፖርታቸው አዘጋጅተው ቪዛቸውን አስመትተው የሚደበቁበት የአውሮፖና የአሜሪካን ዋሻ ሹልክ ለማለት እንደተዘጋጁ በእርግጠኝነት መናገር ይቻላል። ስለዚህ ለህሊናቸው ብቻ የሚሰሩ የመንግስት አመራሮችም ከህብረተሰቡ ጎን በመቆም ሌብነትን ተረት ለማድረግ የቢሮክራሲውን ሰረገላ ቁልፍ ለኮሚሽኑ መክፈት ግዴታ አለባቸው።
በአጠቃላይ ጣፈጠም መረረም ሌብነት የአገራችንና የጋራችን ችግር ሆኖ ከእንግዲህ በኋላ አይቀጥልም። ይህን ቁርጠኛ እርምጃ በጋራ የማንወስድ ካልሆነ ግን ችግሮቻችን ውስብስብ ሆነው ለሚቀጥለው ትውልድ የስራ ባህል ሳይሆን የሌብነት የቤት ስራ እንዳስተላልፍበት እሰጋለሁ። ይህ እንዳይሆን ደግሞ እንደ ዜጋ ለሁላችንም የተሰጠ ሀገራዊ ጥሪ በመሆኑ የቤት ስራችን አድርገን ልንወስደው ይገባል:: ምክንያቱም ስራው በስልጣን ላይ ላሉት ብቻ የሚተው ሳይሆን፤ ሌብነትን ተረት ለማድረግ የገባንበት ዘመቻ እውን ይሆን ዘንድ እያንዳንዳችን ምን ማድረግ እንችላለን ብለን ራሳችንን መጠየቅ፤ እርስ በእርሳችንም መመካከር ይጠበቅብናል።
ሙስናን ለማስቀረት የመጀመሪያው የመንግሥት ቁርጠኝነት መኖሩን በትክክል ካረጋገጥን፤ የፀረ-ሙስና ዘመቻ ስራ ተጀመረ ብለን እናረጋግጣለን። የኢትዮጵያ ሕዝብም ፍትህ አገኘ ብለን መናገር እንችላለን:: ይህ የሚሆነው እና ሙስናን ለመከላከል የሚቻለው ብዙዎቻችን በአካልና በቀለም ኢትዮጵያዊ ከመምሰል ባሻገር በነፍስና በድርጊት ኢትዮጵያዊ መሆናችንን ሙስናን ለመዋጋት በሚደረገው ዘመቻ ቁርጠኞች መሆናችንን ስናረጋግጥ ብቻ ነው:: ካለበለዚያ፣ ዛሬ ለሀገራችን ዋጋ ካልሰጠናት ነገ ሕይወት በተራዋ ዋጋ ታስከፍለናለች:: ለዛሬው በዚሁ አበቃሁ፤ በሌላ ጽሑፍ እስክንገናኝ ቸር ይግጠመን! ሰላም!
ከአለባቸው ደሳለኝ አበሻ (ለንደን)
አዲስ ዘመን ህዳር 12/2015